49 ዓመታት ወደኋላመምህርነት በዓይን የሚታይ ምስል ቢኖረውና በአንድ ጎበዝ ባለብሩሽ ሸራ ላይ ቢያርፍ፤ መልኩ መኮንን ሸገኔን በመሰለ። ሸገኔው የትምህርት ከራማ፣ የዕውቀት አድባር ለራሱ አስውቦ ያቆመው ታላቁ መምህር ነበር። “ማን ይናገር የነበረ” ከተባለ፤ ከማንም ቀድማ ትናገር! አዲስ አበባ፣ ይናገሩ! ጅማና ድሬዳዋ። በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት ምህዋር ውስጥ፤ ዕውቀትን እንደ ፀሐይ ጮራ እየፈነጠቀ፣ እንደ ኦርዮን ኮከብ እያብረቀረቀ፣ በአንድ ዘመን ትውልድ መካከል ተወንጭፎ ድንገት እልም! አለ። ገና በ42 ዓመቱ፣ ከዕለታት በአንዲት ጥቁር ቀን ከማይመልሰው የሞት ፈረስ ላይ ጭነው ነፍሱን ሰለቧት። በዚያው መራር የሞት ጽዋ በተጎነጨባት ዘመን ሀገሪቱን ይመሩ የነበሩት ኮሌኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም፤ ተማሪው ብቻ ሳይሆኑ አድናቂውም ጭምር ነበሩ። እንዲያውም በአንድ ወቅት ከአንድ ዕውቅ ደራሲና ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ “በጣም ብሩሕ ጭንቅላት ያለው ኃይለኛ፣ ደፋር ሰው ነው። ኢሕአፓን ‹ወይድ! ወሮበላ ኹላ!› የሚል ሰው ነበር፤ ገደሉት” አሉ ኮሎኔል መንግሥቱ። ሆኖም መኮንን ግን የእውነት እንጂ የኢሠፓ` ም ሆነ የማንም ደጋፊ አልነበረም። እርሱ ትምህርትን የሚሰብክና በዕውቀት የሚያጠምቅ የትውልዱ ሐዋሪያ ነበር። አፈር ሳይፈጭ ዳግም ሰውን የሚሠራ እንጂ ፖለቲካን የሚያቦካም አልነበረም።
ትውልድ
የሁሉም ነገር አሀዱ፣ የዚህ ታላቅ ሰው የሕይወት ቡራኬ የተሰጠበት ጊዜና ቦታ፤ 1927ዓ.ም ባሌ ጎባ ውስጥ ነበር። ከጥንዶቹ ከአቶ ሸገኔና ከወይዘሮ ዘነበች ጎጆ ታዛ ስር፣ በአንደኛው ቅዱስ ቀን ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ዱብ! አለ። በቀለም ቀንድ የሚዋጋ አርበኛ፣ መሃይምነትን የሚረመርም እልፍ ገዳይ ተወለደ። ስሙንም “መኮንን ሸገኔ” አሉት። በሳሩ ቅጠሉ እልልታ፣ በዛፎቹ ሽብሻቦ፣ እትብቱን በጎረሰችው የባሌ ጎባ ምድር ፈገግታ ውስጥ፤ የሁሉም ልቡስጥላ ሹክ የሚላቸው “ይህ ህጻን ለሀገሩ በርቶ፣ በሀገሩ አጽፎ፤ ስለሀገሩ የሚያልቅ የጠመኔ ሻማ ነው” የሚል ቃል ነበር። ሕይወት አንድ፣ ፈተናዋ ግን ብዙ ብዙ ነውና ገና በለጋው ዕድሜ የእናትና አባቱ የትዳር ክር ተበጥሶ፤ ኑሮን ከአባቱ ጋር ብቻ ለመግፋት ተገደደ።
እናት ፍለጋ
በ10 ዓመቱ፣ እናቱን ፍለጋ ከባሌ ጎባ ናዝሬት ኳትኖ አገኛት። ግን፣ ልቡ እዚህም ማረፊያ አጣ። አንድ ቀን ማለዳ ከእናቱ ቤት ወጥቶ ወደባቡር ጣቢያው አዘገመ። ሲደርስ ከወዲያ እየሰገረ የሚመጣውን ባቡር አላስተዋለም ነበር። ወደ ሐዲዱም ተጠጋ። ድንገት ግን አሳቻ ጊዜና ቦታ ላይ ፊት ለፊት ተፋጠጡ። የደመነፍሱን በርግጎ ከፍርጎው ሲቆምና ባቡሩ ቀጥ! ሲል አንድ ሆነ። ቅሉ፣ ባቡሩ የቆመው አንድ እጅና አንድ እግሩን ነክሶ ነበርና፣ ከዚያ በኋላ እግርና ክንፏን እንደተሰበረች ምስኪን ወፍ ሆነ። ሳይደግስ አይጣላምና በሌላ ጊዜ አንድ ደግ ቤተሰቡ ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ ይዞት በሄደ ጊዜ፤ የታላቁን መምህር መጀመሪያ የከሰተች ቀለም ብቅ አለች። ከዕለታት አንድ ቀን ጃንሆይ ለጉብኝት ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ጎራ ሲሉ፣ መኮንን በሆስፒታሉ አልጋ ላይ ተኝቷል። ጃንሆይን ተከትለው የመጡ አንድ በዕድሜ ጠና ያሉ አብሳሬ ዜና ሲመለከቱት አሳዘናቸው መሰል፣ ወደ መኮንን ጠጋ ብለው “አንተ ያለህ ተስፋ ትምህርት ብቻ ነው” ካሉት በኋላ፤ መማር እንደሚፈልግ ለንጉሡ እንዲጽፍና ደብዳቤውን በማዘጋጀት እንደሚያግዙትም ይነግሩታል። ነገሩ ቢሆንም ባይሆንም፣ “መኮንን ሸገኔ” የሚል ስሙን የያዘ ደብዳቤ ከንጉሥ ዙፋን ፊት መነበቡ ስሜት አለውና ደብዳቤው ተጻፈ። በንጉሥ ፊት ደብዳቤውም ሞገስን፣ መኮንንም ትምህርቱን አገኘ።
ትምህርትን ፍለጋ
በ1939ዓ.ም በአቡጊዳ የተጀመረው የትምህርትና የመኮንን ሸገኔ ግንኙነት፣ እጅና ጓንት ሆነ። በአንድ እጅ፣ በአንድ እግር ባለዘውዱን የቀለም ቀንድ ደፍቶ፣ በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት አቦሸማኔው ወደፊት ገሰገሰ። የ12 ዓመቱ ታዳጊ፣ በየትምህርት ዓይነቱ መቶን የግሉ አድርጎ አላስነካ አለ። በዚያ ላይ ስነ ልቦናው ከአለት የጠነከረ ነበር። በአካል ጉዳቱ እንኳንስ ሊሳቀቅ፤ በጓደኞቹ ተከቦ በራሱ እየቀለደ ያስቃቸዋል። አካላቱን በክራንች ምርኩዝ አስደግፎ፣ ጭንቅላቱ ግን ብዙዎችን ይደግፋል። የወጣቱ መኮንን ሸገኔ ቀጣይ መዳረሻ፣ ወደ መምህራን ማሠልጠኛ ነበር። ከማጠናቀቁ ቀደም ብሎም “ለንደን ማርቲኩሊሽን” የተሰኘውን ፈተና በጥሩ ውጤት አልፎ ዳግም ከጃንሆይ ጋር ተገናኘ። በአካሉ የደረሰውንም ጠየቁት። ከዚያማ እግሩ እንዲሠራለትና ትምህርቱንም በአሜሪካ እንዲከታተል ፈቀዱለት። ተምሮ ተመሰለ።
ወደ መምህርነት
1955ዓ.ም አስፋው ወሰን ትምህርት ቤት በመምህርነት ተመደበ። ከልጆቹን እናት ከወይዘሮ ሠናይት የወንድዐጥር ጋር የተገናኙትና የተዋወቁት፣ እዚህ የ7ኛ ክፍል መምህሯ ሳለ ነበር። ከተማሪዎቹ ፊት ቆሞ “እኔ ስሜ መኰንን ሸገኔ ይባላል። የሰነፍ ተማሪ ጠላት፣ የጎበዝ ተማሪ ወዳጅ ነኝ” የሚለው ንግግሩ ዛሬም ድረስ በወይዝሮዋ ዓይነህሊና እንደሚያቃጭል፣ በግለታሪክ መጽሐፉ ውስጥ ከትዝታዎቻቸው አንዱ ሆኖ ሰፍሯል። ሸገኔው ወደ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተዛውሮ እስከ ዩኒት ሊደርነት ሲያገለግል፣ የጎበዞች ወዳጅ ነውና ጎበዝ ጎበዙን ከአስፋው ወሰን ትምህርት ቤት ያስኮበልል እንደነበረም በታሪክ ማህደሩ ተከትቧል። ከተማሪዎቹም ጋር ሁሉ ከአስተማሪና ተማሪ ያለፈ አባታዊ ቁርኝት ነበረው። ኋላ እንደገና ወደ አሜሪካ በማቅናት በኢንዲያን ዩኒቨርሲቲ ማስተርሱን ተቀብሎ፣ 1961ዓ.ም ዳግም ወደሀገሩ ተመለሰ። ከአንዴም ሁለቴ የገነት በር የምትመስለንን አሜሪካን ረግጦ መመለሱ፣ ያውም ለአስተማሪነት፤ ለአብዛኛዎቻችን ቂልነትም ሊመስለን ይችላል። እርሱ ግን፤ ምን ችጋርና አሳር ቢገርፈው “ሀገርን መቀየር በትምህርት ነው” እያለ ነው ዝክንትሉን አንጠልጥሎ የሚመለሰው። ተመልሶም፣ የሚጨምር እንጂ የማይጎድለውን የዕውቀት ውቅያኖሱን በደብረ ብርሃን መምህራን ማሠልጠኛ አንጣለለው።መነሻው እንጂ መዳረሻው የማይታወቀው መኮንን፣ እንደገና በትምህርት ሚንስቴር ስር ወደ ተቋቋመው “ሸዋ ትምህርት ቤቶች” ተዛወረ። ያቺ ከ7ኛ ክፍል ተማሪው ጋር የተለኮሰችው የፍቅር እሳት፣ ዕለት ዕለት ስትንቦገቦግ ደርሳ ቀደም ሲል ብርሃኗ ወደትዳር ጎጆ መርታቸው ነበር። ጥንዶቹ ጋብቻቸውን የፈጸሙት አሜሪካ በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ነበር። ተመልሰው ሸዋ ት/ቤቶች ሳሉም፣ የበኩር ልጃቸውን ቀዳሚን ወልደው ለመሳም በቁ።
የመኮንን አሻራ
የታላቁ መምህር ወርቃማ አሻራ ካረፈባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል ሌላኛው ድሬዳዋ ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት ነው። ርዕሰ መምህር ሆኖ ሲሠራ፣ ከወትሮው በተለየ በርካታ ተማሪዎችን የማትሪክን ባህር እየከፈለ ከማሻገሩ፤ ትምህርት ቤቱ ከመላው ሐረርጌ ትምህርት ቤቶች በአንደኝነት እንዲሸለም አድርጓል። ደግሞ የደግነት ጥጉ፣ ከሩቅ መጥተው ለሚማሩት የቤት ኪራይ ሳይቀር ይደጉማቸዋል። ለተራበ ተማሪ እንስፍስፍ አባት ነው። ከሦስት ዓመታት ቆይታው በኋላ፣ በ1965ዓ.ም ከነቤተሰቡ ጠቅልሎ አዲስ አበባ ገባ። ስሙ ይጠራዋልና እዚህም ያመራው ወደ መርካቶ፣ ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት በርዕሰ መምህርነት ነበር። 1967ዓ.ም፣ የፖለቲካው ትኩሳት የኢትዮጵያን ሰማይና ምድር ያጋለበትና የመኮንን ሸገኔም የመጨረሻው መጀመሪያ የተመዘዘበት ነበር። በተለይ ከዚያ ወዲህ፣ ጊዜው የፖለቲካው እሳት በየትምህርት ቤቱ አጥር ላይ ሳይቀር የሚንቀለቀልበት ነበር። ሆኖም፣ መኮንን ግን እስትንፋሱ
እስትፋንሱ እስከተነጠቀችበት የመጨረሻ ደቂቃና ሴኮንድ ድረስ እጁን ለጠመኔ እንጂ ለፖለቲካው አልሰጠም። “ኋላ ደመከልብ እንዳትሆን!” ብለው ቢዝቱና ቢያዝቱበትም “ተማሩ ተማሩ” የሚል ግጥም ገጥሞ በብዕሩ ፎከረ። ጠመኔውና ጠመንጃቸውም ትግል ገጠሙ። ቢገባቸው ብሎ እንደገናም ሌላ ስንኝ አሰናኘ። “ምንም ብልኅ ቢሆን ያልተማረ ሰው የጐመን ዐጥር ነው ዶሮ ሚጥሰው” ብሎ።ለዚያም ነው በሄደበት ሁሉ የትምህርትን ውቃቤ የሚቀሰቅሰው። ትምህርት ቢዘጋ ባይዘጋ፣ 365 ቀናት ከተማሪዎቹ ጋር ነው። በክረምት “ሀገርህን እወቅ” የሚል ጉዞ አሰናድቶ በአራቱም አቅጣጫ ያስኮመኩማቸዋል። ለቀጣይ ዓመት እንዲዘጋጁ ቤተ መጻሕፍት በሳምንት ክፍት የሚሆኑበትን ቀናት ያመቻቻል። ሌላኛው የክረምት ገጸ በረከቱ፤ ሥራ መሥራት ለሚፈልጉ ተማሪዎቹ፣ በግልም ሆነ በመንግሥት ተቋማት አፈላልጎ ያስቀጥራቸዋል። ታዲያ እንዲህ ያለውን መምህር በታሪክ ከወዴት ያገኙታል?! ለተማሪዎቹ ዕውቀቱን ብቻ ሳይሆን ደሙንም መስጠቱ፣ በተማሪዎቹ እንጂ በአንዳንድ ባልደረቦቹና በበላይ አለቆቹ ግን አልተወደደለትም። እርሱ ግን ሕይወቱን ከሰጣቸው ተማሪዎቹ ወዲያ፣ ወደዱለትም ጠሉትም ጭንቁ አልነበረም። ግቡ ያልተማረ ብቻ ሳይሆን የተራበም እንዳይኖር ነው። “አገሪቷ ውስጥ ድኻ ሊኖር አይገባም” ይላል። በባዶ ሆድ ጭንቅላትን መሙላት ፈተና መሆኑን ያውቃልና። ለርሱ ዕውቀት ያለ ስነ ምግባር፣ እንጀራ ያለወጥ ማለት ነው። በየትኛውም ጊዜና ቦታ የዳኝነት ፍርዱ “ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያዊያን” የሚል ነው። “እኔ መኰንን ባለኹበት አስተዳደር ውስጥ ለቦታው በቂ ችሎታና ልምድ ያለው ኢትዮጵያዊ እያለ የውጭ አገር ዜጋ በምንም ዐይነት መሾም የለበትም” በማለት፣ ርዕሰ መምህር በነበረበት በአንደኛው ትምህርት ቤት ውስጥ በሀላፊነት መንበር ከተሰየመው ህንዳዊ እጅ ቁልፉን ተቀብሎ ለኢትዮጵያዊው መምህር ሰጥቶታል።ሸገኔው የሀገር ዋርካ፣ ሀገሩን ሲወድ ድንበር የለውም። ድሎት ከሞላበትና ጮማ ከሚቆረጥበት ገነት ይልቅ፣ የማህበረሰቡን አሳር የሚሸከምበትን ሲኦል ይመርጣል።
በልጆቹ የሚወደድ ምርጥ አባት
ሀገርን የመውደድ መጀመሪያ ከቤት ነውና እንኳንስ ለወለዳቸው፤ የሚያሳድጋቸውና የቤት አገልጋዮቹ ሳይበሉ ምግብ ወደ አፉ የማያስጠጋ የርህራሄና የደግነት አምሳል ነው። ምንም እንኳን ነፍስ በማያውቁበት ዕድሜ ቢለያቸውም፤ አንደኛ ልጁ ቀዳሚ መኮንን፣ ሁለተኛ ልጁ ካቢው መኮንን እና ሦስተኛ ልጁ መሸገች መኮንን፣ በመጽሐፉ ውስጥ ስለ አባታቸው የተናገሩት ሁሉ ልብ የሚነካና የሚያሞቅ ነው። ባለቤቱና ተማሪዎቹን ጨምሮ በርካቶች ስለመኮንን ያሰፈሯቸው ትዝታዎች ሁሉ እጅግ አስገራሚ ናቸው።
በመጨረሻ….
ዳሩአሳዛኙ መጨረሻ በአንዲት ቀን ጽለመት ለብሶና ጭጋግ ጎርሶ ካለበት ደረሰ። አንድ ዓመት ቀደም ብሎ፣ 1968ዓ.ም በቦሌ ሆምስ መንደር ለመጀመሪያ ጊዜ የራሱን ቤት ገዝቶ ነበር። “ቤት ለምቦሳ!” ተብሎና “ለምቦሳ ሰሩ!” ብሎ በቅጡ እንኳን ሳያርፍበት፤ በዓመቱ ሰኔ 15 ቀን 1969ዓ.ም የሞት ምጽአት አጓራ። በማለዳው “ሀገር ሰላም” ብሎ ከቤቱ የወጣው መኮንን፣ በጠዋቱ ምኒልክ ት/ቤት ውስጥ የዕለት ግብሩን የዕለት ግብሩን ሲያከናውን ቆየ። ሆኖም፣ በዚያን ሰሞን በአዲስ አበባ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሁሉ በኢህአፓ ቀጭን ትዕዛዝ ተዘግተው ነበር። የምኒልክ ት/ቤት ርዕሰ መምህር የነበረው መኮንን ግን “እየተማራችሁ ታገሉ፣ እየታገላችሁ ተማሩ” ብሎ፣ መዘጋቱን አሻፈረኝ! በማለት፣ እንደወትሮው ሁሉ ሥራውን ቀጥሏል።ወደምሳ ሰዓት ገደማ ባለቤቱ ሠናይት፤ ከምትሠራበት ትምህርት ሚንስቴር ወጥታ፣ በቀጥታ ወደ ምኒልክ ት/ቤት አመራች። የዚያን ዕለት ብቻ ሳይሆን፤ የምሳ ሰዓት ሲደርስ፣ የቋጠረችውን ስንቅ ይዛ ወደርሱ መሄድ የሁልጊዜም ተግባሯ ነው። ምክንያቱም ባለቤቱ መብላትን እስኪረሳ በሥራ ተጠምዶ ስለሚውል፣ እርሷ ስትመጣ ነው አብረው የሚበሉት። የዚያን ዕለት ግን ያለወትሮዋ ራሷን ያማትና ቅር ቅር ይላትም ነበር። ምሳቸውን ከበሉ በኋላ፣ ለህመሟ መድኃኒት አስገዝቶ በመኪና ወደ ቢሮዋ ሸኛት። “በረንዳው ላይ ኾኖ እያየኝ ሦስት ጊዜ ‹‹ቻው…ቻው…ቻው›› አለኝ” ስትል ያንን ቅጽበት ታስታውሰዋለች። ምናልባትም በሁለቱም ውስጥ አንዳች በውል ያልታወቃቸውና ያልተነጋገሩበት ስሜት ተፈጥሮ ነበር። መኮንን ወደ ቢሮው ተመልሶ፣ ከጠረጴዛው ላይ በታጨቁ ወረቀቶች አቀረቀረ። በዚያው ቅጽበት ከውጭ በሩ ላይ ቆሞ ወደ ውስጥ ያፈጠጠ አንድ ተማሪ መሳይ ወጣት ተመለከተ። ወደ ውስጥ እንዲገባ ወጣቱን ጋበዘው። ያ ወጣት ግን ጠመንጃ ያነገተ የሞት መልአክተኛ ነበር። ፊት ለፊቱ እንደቆመ፣ አንስቶ ግንባሩ ላይ አነጣጠረው። ፋታ እንኳን ሳይሰጠው ቃታውን ስቦ ያለርህራሄ ጥይቱን አርከፈከፈበት። የሚንጣጣ የጥይት እሩምታ የተማሪ ቤቱን ቅጥር አናወጠው። በቅጽበት ሁሉም ነገር እንዳልነበረ ሆነ። በቅጥሩ ዙሪያ በርቶ የነበረው የዕውቀት ፋኖስ እየተሰበረ፣ ጭል! ብሎ እየጠፋ በባሩድ ብልጭታና ሽታ ተተካ። ጠመንጃ ደግነው የገሀነም እሳት የሚለቁ የፖለቲካ ጀብደኞች ት/ቤቱን ወደ ሲኦልነት ቀየሩት። በግቢው የራማ ምድር ጩኸት በረከተ። ከአንደኛው ስፍራ ያንን ግዙፍ የትውልድ ዋርካ አገኙት። ቃታውን ስበው ዋርካውን ገነደሱት። ሸገኔን ገደሉት። በ42 ዓመቱ ቀጠፉት። ስንቱን የሚፈውስና ሀገሩ የምትድንበት ዕውቀቱ፣ ከደሙ ጋር ተቀላቅሎ ፈሰሰ። በዚህ መሃል፣ ወደ ሥራ ገበታዋ ተመልሳ የነበረችው ባለቤቱ ባላወቀችው ሁኔታ ልቧ እየረዳ፣ በጭንቀት ውስጧ ሰላም አጣ። ስልኩን አንስታ ወደ መኮንን ቢሮ ደወለች። “ሃሎ!” ያላት የምታወቀውና የምትናፍቀው የውድ ባለቤቷ ድምጽ ሳይሆን፣ የአንዲት ሴት ድምጽ ነበር። ስልኩን ያነሳችው ጸሐፊው ነበረች። የፍርሃቷ መጠን እያየለ፣ እንድታገናኛት ብትጠይቃት፤ አንድ በጥይት የተመታ ተማሪ ይዞ ወደሆስፒታል መሄዱን ነገረቻት። የሞተ ሰው እንዳለ የሰማችው ሠናይት፣ ወደ ትምህርት ቤቱ ገሰገሰች። በጣር ተሰቅዛ እንደምንም ከመድረሷ፣ ግቢው በሁካታና ዋይታ ተጥለቅልቋል። ቅድም ከአንዲት የምሳ አኮፋዳ ሲያጎርሳትና ስታጎርሰው የነበረው ውዱ ባለቤቷ፣ በደም የተለወሰ በድን ሆኖ አገኘችው። በሰኔ 22 ቀን 1969ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣም፤ በፊት ገጹ ይህን መርዶ አስነበበ። ከብዙዎች ጋር የሚወዳት ሀገሩም እንባዋን አፈሰሰች። ያ ጥቁር መጋረጃ፣ በሚያውቁትና በወዳጆቹ ልብ ውስጥ ሁሉ ለዘመናት ሲውለበለብ ቆይቷል። ኋላ ፕሬዝደንት የነበሩት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እና ራሱ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም፤ ሞቱ ከከነከናቸውና ካብከነከናቸውና በቅርብ ከሚያውቁት መካከል ነበሩ። ላያልፍለት ያ ሁሉ አለፈ። ግን ጀግና መኖር የሚጀምረው በሞቱ ነው። “ገደልነው!” ያሉ ዕለት፣ እርሱ ጥቂቶች ብቻ የሚያገኙትን ሌላ መኖር የጀመረበት ነበር። ዕድሜ ለተወዳጅ ሚዲያና ኮምኒኬሽን ይሁንና በትንሹ ይህ መጽሐፍ ብቻ ህያው መኮንን ነው። የሆነው ግን በዋዛ አልነበረም። “ይህ ዕድል የረዥም ጊዜ ጸሎቴ መልስ ነውና የአባታችንን ታሪክ በዚህ መልኩ እንዲሰናድ ስላደረጋችኹ ከልቤ ጐንበስ ብዬ አመሰግናለኹ!” ትላለች ሁለተኛ ልጁ ካቢው መኮንን። ተወዳጅ ሚዲያን የሚመራው እዝራ እጅጉም፣ መጽሐፉን ግሩም አድርጎ በማሰናኘት የዘመናት ህልሟን እውን አደረገው። ካቢው ታሪኩ በመጽሐፍ እንዲሰነድ ስታደርግ፣ ትልቁ መሻቷ ለእናቷ ለወይዘሮ ሠናይት የወንድዐጥርና ለመኮንን ተማሪዎች ሁሉ ገጸ በረከት እንዲሆን ነው። ይኼው ሁሉም ዛሬ ሆነ። የሀገር ዋርካው፣ ታላቁ መምህርም፤ ታሪክን በጠመኔ ከሀገሩ ሠሌዳ ላይ አጻፈ።
በተማሪዎቹ የተከበረ
መኮንን ሸገኔ በተማሪዎቹ የሚወደድ ፣ ዘመን ተሻጋሪ መምህር የሚባል ነው። እውቀት ያስጨበጣቸው ተማሪዎቹ የእርሱ ነገር አይሆንላቸውም። ትልቅ ቦታ አድርሷቸዋልና ሊዘነጉት አይሹም። በመኮንን ሸገኔ ተምረው ትልቅ ቦታ ከደረሱት መካከል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ፣ ገነት አየለ፣ ንጉሴ አየለ፣ ደራሲ ጌታቸው በለጠ ፣ አማረ መላኩ ፣ ታዬ በላቸው፣ ዶክተር አለማየሁ ጎሹ ፣ ማንያዘዋል እንደሻው ይገኙበታል።
ለመኮንን ሸገኔ ቅዳሜ ነሐሴ 16 2018 ዓ.ም በዳላስ የሚገኘው የአርአያ ሰው ሽልማት ፋውንዴሽን መኮንን ሸገኔ የሚል የሽልማት ዘርፍ በመሰየም እውቅና እንዲያገኝ አድርጓል። የመኮንን ሸገኔ ቤተሰቦችም በሽልማት አሰጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ታድመው ደስታቸውን ገልፀዋል። ተወዳጅ ሚድያ እና ካቢው መኮንን ሸገኔ የመኮንን ሸገኔን ታሪክ ለትውልድ ለማስቀረት በአንድ ሀሣብ እና በአንድ ልብ እየሠሩ ይገኛሉ።