ልበ ሙሉው ሀይሉ ፀጋዬ

ልበ ሙሉው ሀይሉ ፀጋዬ ቴአትር የጀመረበት 40ኛ ዓመት

ሀይሉ ፀጋዬ

አራዳ ኤፍ ኤም ይህን ክብር በአሉን እያከበረለት ይገኛል ።

ሀይሉ ጸጋዬ፣ሰሜን ሸዋ ከደብረ ብርሃን ከተማ በስተ ሰሜን በምትገኘው ጥዳምባ ሚካኤል ነበር በ1954 ዓ/ም የተወለደው።ምንም እንኳን ወላጆቹ እናቱ ወ/ሮ ሙሉ እመቤት ወ/ማሪያም አባቱ ደግሞ ፊታውራሪ ሽፈራው ሳህሌ ይሁኑ እንጂ ያደገው ግን የእናቱ ታላቅ እህት (አክስቱ)ከሆኑት ወ/ሮ በላይነሽ ዘውዴ እና ከባለቤታቸው ፀጋዬ ወልዴ ጋር ነበር።ሀይሉ ፀጋዬ የተባለውም በዚህ ምክንያት ነው።

የተወለደው ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ከተማ ይሁን እንጂ ገና ከጨቅላ እድሜው ጀምሮ ነፍስ እስክያውቅ ድረስ ያደገው ናዝሬት ከተማ ነው።

እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ህፃን ብይ ሲወረውር ፣ኳስ ሲጫወት ያደገው ሀይሉ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ናዝሬት በቀዳማዊ ሀይለስላሴ ትምህርት ቤት ከ7_12 ክፍል ደግሞ በአፄ ገላውዲዮስ መርሃ ሙያ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል።

የህይወቱ ጥሪ በጥበቡ አለም እንዲኖር ተፈጥሮ ገና በማለዳ መንገድ አሳይተዋለች። እና የ8 ዓመት ታዳጊ ሆኖ ነበር በቤቱ ሆኖ ሲፅፋቸው ከነበሩት ግጥሞች በስነ ስርአት ሃሳቡን አደራጅቶ ለመጀመሪያ ግዜ የቋጠረውን የግጥም ስንኝ ያነበበው። ከዚያም 6ኛ ክፍል ላይ በሚማርበት ትምህርት ቤት ለተማሪዎች ግጥም ያቀርብ ጀመር።11ኛ እና 12ኛ ክፍል ሲደርስ ደግሞ ለቀበሌ ኪነት ግጥሞች እና ጭውውቶች እያዘጋጀ ያቀርብላቸው እንደነበር በአንደበቱ አጫውቶናል።

ለስነ ፅሑፍ ከፍተኛ ዝንባሌ የነበረው የያኔው ታዳጊ የከፍተኛ ትምህርቱን ማጠናቀቅ በነበረበት ጊዜ አልነበረም የጨረሰው ።ምክንያቱም በ1968 ዓ/ም የኢህአፓ ረብሻ በመፈጠሩ በወቅቱ 9ኛ ክፍል ስለ ነበር በድጋሚ በ1969 ዓ/ም 9ኛ ክፍል እንዲደግም ተደረገ። በ1972 ማትሪክ ወስዶ ካጠናቀቀ በኋላ አባቱ ውጭ ሀገር ሄዶ እንዲማር ይፈልጉ ስለ ነበር በ1973 ዓ/ም ውጤት እየተጠባበቀ የአባቱን የወፍጮ ስራ በምዘና እያገዘ ቆየ። ነገር ግን የውጭውን የትምህርት አለም ሳይሳካለት ሲቀር በ1975 ዓ/ም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተቀላቀለ።በትያትር ጥበባት ክፍል ገብቶ በ1977 ዓ/ም ተመረቀ።

የዩኒቨርስቲ ቆይታው

የ1975ዓ/ም የትያትር ጥበባት ክፍል ተማሪዎች ብዛታቸው 18 ነበሩ ።የገቡት ተማሪዎች ቁጥራቸው ሳይጎድል 18ቱ ተመርቀዋል።ለዚህ ስኬት ደግሞ ሀይሉ ፀጋዬ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል ።የዲፓርትመንቱ ተማሪዎች ህብረታቸው ጠንክሮ ለስኬት እንዲበቁ በማስተባበር እና የደከመውን በማገዝ ሁነኛ ሚና ተጫውቷል።በዩኒቨርስቲ ቆይታውም በርካታ ግጥሞችን በመፃፍ እና በድራማዎች ላይ በመተወን ይሳተፍ ነበር።ያኔ ፍስሃ በላይ ይማም የፃፈውን አልቃሽ እና ዘፋኝ ትያትርም በትወና እና በአዘጋጅነት ተሳትፏል።

ወርቃማ በሆነው የዩኒቨርስቲ ቆይታው “በሽተኞቹ” የተሰኘ የኮሜዲ ዘውግ ያለው ተውኔት ፅፎ አዘጋጅቷል።

በወቅቱ ያቀርባቸው የነበሩት ግጥሞች በሰዎች ዘንድ እውቅናን አስገኝተውለታል።በተለይ ደግሞ “አፈራረሳቸው”የተሰኘች ግጥሙ በወቅቱ ለነበሩ የጥበብ ወዳጆች አይረሴ ነበረች። በአጠቃላይ የሀይሉ ፀጋዬ ባች የተሳካለት ወርቃማ ትውልድ እንደነበር ዛሬ ላይ ያሉትን የያኔው ተማሪዎች የህይወት ስኬታቸውን አይተን መመስከር እንችላለን።

በዩኒቨርስቲ ቆይታው በአዘጋጅነት ፣በደራሲነት፣በገጣሚነት እና በተዋናይነት ይተጋ የነበረው ሀይሉ ፀጋዬ በ1977 ዓ/ም የመመረቅያ ፅሑፉን ኮሜዲ እና ኮሜድያን ላይ ትኩረቱን ያደረገው ተስፋዬ ሳህሉ ፣አበራ ደስታ ና ደበበ እሸቱ የተሳተፉበት ስራውን ምርጥ የመመረቅያ ፅሑፍ ሆኖ ለብዙዎች ለማጣቀሻ ግብአትነት እንዲሆን ምክንያት ሆኗል።

የሥራ ህይወት

በትያትር ጥበባት የመጀመሪያ ዲግሪውን ከማግኘቱ ጥቂት ቀደም ብሎ በ1977 ዓ/ም በሀገራችን በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ጠቅላላው የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ለሰፋሪዎች ጎጆ ቤቶችን ሲሰሩ ቆዩ።

ከዛ ከተመለሱ በኋላ ሀይሉን ጨምሮ ፍሰሃ በላይን እና ብርሃነመስቀል ታፈሰ የተባሉ ጓደኞቹን በወቅቱ እነማን እንደነበሩ የማያውቋቸው ሰዎች ቃለ መጠይቅ አደረጉላቸው። ከዩኒቨርስቲ እንደተመረቁም ሀይሉ ፀጋዬ ወደ የካቲት የፖለቲካ ትምህርት ቤት ገባ።

ለሁለት ወራት ያህል ስልጠና ከወሰደም በኋላ ከዩኒቨርሲቲው የተመረጡ ተማሪዎች በየሙያቸው በተለያየ ዘርፍ ሲመደቡ ሀይሉ ፀጋዬ በኢሰፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ በርእዮተ አለም መምሪያ ስር የባህልና ስፖርት ዘርፍ ኋላፊ ከነበሩት ደራሲና ገጣሚ አያልነህ ሙላት ስር የትያትር ክፍል ሀላፊ ሆኖ ተመደበ። በ1983ዓ/ም ኢህአዴግ እስኪገባም ፖሊሲ በማውጣት ጥናቶችን በመሥራት እና በአመራርነት ለ5ዓመት ከ 6 ወራት አገለገለ።

ሀይሉ ፀጋዬ የማንም ፓርቲ አባል ሆኖ አያውቅም ።ትላንትም ዛሬም።በሠራቸው ጥናቶችም ደስተኛ እንደሆነ ይናገራል።

ምናልባትም ጥናቶቹ ዛሬ ላይ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ከደራሲ እና ገጣሚ አያልነህ ሙላት ጋ አይጠፉም ይላል።

አያልነህ ሙላት የቅርብ አለቃ ሆኖህ እንደመስራት አስደሳች ነገር እንደሌለ የሚገልፀው ሀይሉ ፀጋዬ በዚያ ዘመን የፓርቲ አባል ሳይኮን ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ መሥራት እጅግ ከባድ ቢሆንም በነበረችው ጠባብ እድል ተጠቅሞ አባል ሳይሆን ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ገብቶ የሰራበት ዘመን እንደሚያስደስተው ደጋግሞ ያወሳል።ምክንያቱም በርካታ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ድራማዎችን የፃፈው እዛ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሆኖ ነበር።

ገና የ23 አመት ወጣት ሳለ ነበር እና ስራ የጀመረው። በተነቃቃ ጉልበት እና መሰጠት ነበር የሚሰራው ።ለዚህም የቅርብ አለቆቹ ራሱን በንባብ እንዲያሳድግ ያበረታቱት እንደነበር ይገልፃል።

በስራ አጋጣሚ በርካታ ቦታዎችን እየተዘዋወረ ያገለገለው የጥበብ ፈርጡ ሀይሉ ፀጋዬ በ1980 ዓ/ም መጨረሻ ላይ ኤርትራ ዘምቶ ማስታወቂያ ሚኒስቴር የሬድዮ ጣቢያ ውስጥ ያግዝ እንደነበር ይናገራል።ለዚህም አበርክቶው የጀግና ሜዳልያ ሲሰጡት አልቀበልም እንዳለ ይገልፃል።

የሬድዮ ድራማዎች

በ1976 ዓ/ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 3ኛ አመት ተማሪ ሆኖ የዘውገ በሽታ የተሰኘ የሬድዮ ድራማ ሰርቶ ነበር።የተማሪነት ህይወቱ እና የሬድዬ ድራማ ስራዎቹን ስያስታውስ ደግሞ ይህንን አጋጣሚ አልረሳውም ይላል።

“ቅዳሜ ላይ የኪነጥበባት ምሽት የሚል ፕሮግራም ነበር እና በወቅቱ የሶስተኛ አመት ተማሪ ሁኜ ነበር ስራዬን ይዤ ወደ ተቋሙ ያመራሁት። በወቅቱ የነበረው አለቃም ፅሑፉን አይቶ ለመገምገም ከሁለት ወራት በኋላ እንዲመለስ ቀጠረው።በረጅሙ ቀጠሮ የተናደደው ሀይሉ አይሆንም ብሎ በመከራከር ወደ 15 ከዛም ወደ ሶስት ቀነ ቀጠሮውን በማውረድ ስራውን ሰጥቶ ወጣ።በሶስተኛውም ቀን ተመልሶ ሲሄድ አለቃው ከወንበሩ ተነስቶ አቅፎ ሰላም እንዳለው እና ፅሑፉ ተባዝቶ እንዳገኘው ይገልፃል።ደግሞ ፅሑፉ በጣም ቆንጆ ስለሆነ በአማተር አይሰራም ፕሮፌሽናል ባለሙያዎች ናቸው የሚተውኑት በማለት የማዘጋጃ ቤት ተዋንያን ሱራፌል ጋሻው፣ወለላ አሰፋ፣አላዛር ሳሙኤል ካስት ተደርገው ተሰራ።ያኔ ለኔ እንዲህ ያለ ነገር መስማት ትልቅ ነገር ነበር።ድራማው ታድያ በ ሁለት አመት ውስጥም ከ30 ጊዜ በላይ እንደተደገመ ይናገራል።ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ ከወጣ በኋላም የወፍዋ ወጥመድ፣ከኔ ጋር ኑር፣ከፍቅር ባሻገር፣ ጋዜጠኛው፣ቅርጫው ፣የማዕበል ዋናተኞቹ፣ወደ ሃብት ጉዞ ፣የደወል ድምፆችእና ሌሎች ከአርባ በላይ የሚሆኑ የሬድዮ ድራማዎችን ሰርቷል።

ኢህአዴግ ከገባ በኋላ ምንም እንኳን እንደፈለገው በፈለገው ቦታ መስራት ባይችልም ከመንግስት ጫና እራሱን ነፃ በማውጣት ባመነበት መንገድ ተጉዞ ላለፉት 30 ዓመታት የሙሉ ጊዜ ፀሃፊ ሆኖ እየኖረ አለ።በነዚህ አመታት ግን ቀላል የማይባሉ ዋጋዎችን ከፍሏል።በወቅቱ የተመሰረተው የኢህአዴግ መንግስት በመደበው ስራ ላይ እሺ ብሎ ባለመቀበሉ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ይተላለፍ የነበረው “የፍቅር ጣኦቶች” የተሰኘ ድራማውን ስድስት ሳምንታትን እንደታየ ካድሬዎቹ አስቆሙበት ።ቀጥለውም” ህጋዊ በትር”የተሰኘ ትያትሩን በማዘጋጃ ቤት እንዳይታይ ገምግመው አስቀሩበት።

በአቋሙ የፀናው እና ለሙያው ክብር ያለው ከያኒው ግን ስራውን በእንቅፋት ብዛት አላቆመም። ይልቁንስ በርትቶ ሙያው ላይ በመስራት”ከራስ በላይ ራስ”የተሰኘ ትያትር ፅፎ በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት ስያሳይ እነሱም ሰልችቷቸው ተውት።

ሀይሉ ፀጋዬ “ስራ ወይስ እድል፣አደራው፣ጋዜጠኛው የፍቅር ጣዎቶች፣ሙግት፣ተበዳሪው፣ሞጋቾች እና ሌሎች ከ10የሚበልጡ የቴሌቪዥን ድራማዎችን ሰራ።

ቅርጫው፣ኮብላይ፣ወጥመድ፣ለእረፍት የመጣ ፍቅር፣መሃላ፣ ከራስ በላይ ራስ ፣ቤተሰቡ፣ቅድስተ ካናዳ እና ሌሎች የመድረክ ትያትሮችም ለጥበብ አፍቃርያን ያበረአተ ድንቅ ባለሙያ ነው።

አሁን ላይ ለመድረክ ያልበቁ ተፅፈው የተቀመጡ በርካታ ፅሑፎች እንዳሉት ይናገራል።

ሀይሉ ፀጋዬ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነው።ራህዋ ኋይሉ ፀጋዬ እና አማኑኤል ኋይሉ ፀጋዬ የተባሉ ልጆች አሉት ።በሴት ልጁ አማካኝነት አያት ሆኗል።ልጆቹም የሱ ሙያ እንደሚወዱለት እና እንደሚከተሉትም ጭምር ይናገራል።ወንድ ልጁ አማኑኤል የደወል ድምፆች የሬድዮ ድራማ ላይ ከሀረገወይ አሰፋ እና ከአባቱ ጋር በመሆን መተወኑ ይታወቃል።ሴት ልጁ ራህዋም “ሚስጢራዊ ምሽት”የተሰኘ ባለ 36 ክፍል የራድዮ ድራማ ፅፋና አዘጋጅታ ለህዝብ ከማቅረቧም በላይ “ሴቶቹ”የተሰኘው ተከታታይ ድራማ ደራሲም ናት።ሀይሉ ፀጋዬ ከደራሲነት ፣ከተዋናይነት ፣ከአዘጋጅነት በተጨማሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመምህርነትም አገልግሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *