የ5 አመት እቅዳችን እውን ሆነ -እግዚአብሄር የተመሰገነ ይሁን

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ‹‹ታሪክን በሲዲ›› የተሰኘውን ፕሮጀክት በጀመረ ልክ በ12 ወሩ ታህሳስ 1 2010አ.ም የጸሀፌ-ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድን የህይወት ታሪክ በዲቪዲ አውጥቶ አስመረቀ፡፡ ይህ ቀን ለድርጅታችን ታሪካዊ ሊባል የሚችል ቀን ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያውያን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት አድርገን እንደምንሰራ ለራሳችንም ለሰውም ቃልኪዳን የገባንበት ጊዜ ስለነበር ነው፡፡በጊዜው ተወዳጅ ከታህሳስ 1 2010አ.ም በፊት የ4 ባለውለታዎችን ታሪክ በኦድዮ አሳትሞና አሰራጭቶ ነበር፡፡ የፀሀፌ-ትእዛዝን ታሪክ በዲቪዲ ሰርቶ ሲያስመርቅ ግን የመጀመርያው የምረቃ መርሀ-ግብር ሊባል የሚችል ነው፡፡

ተወዳጅ ከታሪክ ምሁራን፣ ከመገናኛ ብዙሀን ሰዎች ፣ ከሌሎችም ታሪክ ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር ቀዳሚ ትውውቁ የጀመረው ከዚህ ከታህሳስ 1 ቀን በኋላ ነበር፡፡ በዚህ ቀን ኤምሪተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴን ጨምሮ በርካታዎች በራስ ሆቴል አዳራሽ ታድመው ነበር፡፡ የወቅቱን ሁኔታ የሚያስታውሱ ታሪካዊ ምስሎችን እንዳየሁት ከሆነ አዳራሹ ሙሉ ሰው ነበረው፡፡ መቀመጫ ወንበር እንኳን ማግኘት አዳጋች ነበር፡፡ ደጃዝማች ወልደሰማእት ገብረወልድን የመሰሉ አሁንም በህይወት ያሉ ታላቅ ሰው በዚህ እለት ታድመው ዘጋቢ ፊልሙን ሲመለከቱ ነበር፡፡ በጊዜው ተወዳጅ ታሪክን በሲዲ ለመስራት በሰው ሀይልም ፣ በፋይናንስ አቅምም ገና ብትሆንም ብዙ የአጭር እና የረጅም ጊዜ እቅድ በመሰነቅ ህልሟን እውን ለማድረግ ተነሳስታ ነበር፡፡

የተወዳጅ ሚድያ ዋና ስራ አስፈጻሚና መስራች እዝራ እጅጉ በዚህ እለት ለሚድያዎች በሰጠው መግለጫ በ5 አመት የ32 ሰዎችን ታሪክ በሲዲ የመስራት እቅድ ይዘናል ብሎ ነበር፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያውያን ታሪክ ላይ አተኩሮ ለመስራት ቃልም ገብቶ ነበር፡፡ እንግዲህ ተወዳጅ የአክሊሉን 72 ደቂቃ የፈጀ ታሪክ ሰርቶ በዲቪዲ ካቀረበ በኋላ ብዙዎች ታላላቆች ‹‹ መልካም ያድርግላችሁ›› ብለው መርቀውት ነበር፡፡ በእለቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ዳይሬክተር ዶክተር በለጠ ብዙነህ በክብር እንግድነት ታድመው የተወዳጅ ሚድያን ሙከራ አድንቀዋል፡፡ እንዲሁም ደራሲና ሀያሲ ዳንኤል ወርቁ ዘጋቢ ፊልሙ የተሰራበትን መንገድ አድንቆ አጭር ገለጻ አቅርቧል፡፡

እንግዲህ ይህን አጭር ማስታወሻ ያቀረብነው አንድ ሀሳብ ሲታቀድና ሲፈጸም እንዴት እንደሆነ ለማሳየት ነው፡፡ ህልምንስ እውን ማድረግ ይቻላል ወይ? የሚለውን ለማሳየት ነው፡፡ የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ ነውና መነሻችንን ለማሳየት በማሰብ ጭምርም ነው፡፡ ከአምስት አመት በፊት የሰራናቸው ሲዲዎች ቁጥር 5 ብቻ ነበር፡፡ ዛሬ የ45 ሰዎችን ታሪክ ሰርተን ለገበያ አውለናል፡፡ በ2010 አብረውን የሚሰሩት ባለሙያዎች ቁጥር 6 ነበር፡፡ በ5 አመት ጊዜ ውስጥ ከ32 በላይ ባለሙያዎች በተወዳጅ የታሪክ ፕሮጀክት ተሳትፈዋል፡፡ ተወዳጅ ከዚህ የምረቃ ስነስርአት በኋላ 15 የምረቃ መርሀ-ግብሮችን እውን ያደረገ ሲሆን አራት መጽሐፍት አዘጋጅቶ ለአንባቢ አቅርቧል፡፡

በተጨማሪም አስር መጽሐፍት ወደ ድምጽ በመቀየር ለትረካ እንዲመቹ አድርጎ አቅርቧል፡፡ ዳግም ከ2013 ጀምሮ የዊኪፒዲያ ፕሮጀክትን በመቅረጽ የ300 ኢትዮጵያውያን ታሪክ ሰንዶ በድረ-ገጽ እንዲጫኑ አድርጓል፡፡ ይህንኑንም ስራ በኢንሳይክሎፒዲያ በማዘጋጀት የመጀመርያውን በጠንካራ ሽፋን የወጣ መዝገበ-አእምሮ መጽሀፍ አሳትሞ አስመርቋል፡፡ ያቺ የአክሊሉ ሀብተወልድ ዲቪዲ የተመረቀችባት ቀን በብዙ ምክንያት መነሻ ነበረች፡፡ መነሻ ሳይኖር መድረሻ አይኖርም፡፡ ይሄ ሁሉ ስኬት የመጣው ግን እግዚአብሄር ሀይል ሰጥቶን ስለሰራን ነው፡፡ ሀይል ሰጪ አምላክ አሁንም አብሮን አለ፡፡ ክብር ለጌታ ይሁን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *