የመንገዶች ባለውለታ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣ መዝገበ-አእምሮ ( የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች ፣በመፅሀፍ፣በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል።በተለይ ጉግል ላይ ታሪካቸው ሲፈለግ የማይገኝ ሰዎች አሁን የሙያ አበርክቷቸው በቀላሉ ኢንተርኔት ላይ በግልፅ ተቀምጦ ይገኛል።
ባለፉት 4 ዓመት ከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መፅሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።
ከእነዚህ ውስጥ የሚድያ ሰዎችም፣ የቴአትር ባለሙያዎች ይገኙበታል። አጠቃላይ 74 ከፍተኛ የሚድያ አመራሮች፣ሚኒስትሮች ፣ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የግል ሚድያ መሥራቾች፣ዋና አዘጋጆች እና መካከለኛ አመራሮች ተካተዋል። 35 ያህሉ በዋና ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ያሉ ሲሆን የሁሉም ታሪክ በተሟላ ደረጃ ለመሰነድ ተችሏል።በተጨማሪም በሳይንስ፣ በቱሪዝም፣ በሥራ ፈጠራ፣ በመምህርነት ፣በምህንድስና እና በሌሎችም ዘርፎች ውስጥ ያሉ ሰዎችን ወደ አንባቢ እያመጣን እንዲታወቁ ጥናትና መረጃ ማድረግ ለሚሻም ተደራሽ ስናደርግ ቆይተናል።
የእነዚህን ሰዎች ታሪክ ሰንዶ ለአንባቢ ተደራሽ ማድረግ ፈታኝ ቢሆንም አሳክተነዋል። በዚህ ተግባራችንም ተጠናክረን እንቀጥላለን።
አሁን በዚህ ጽሑፍ ታሪካቸውን የምንሰንደው የኢንጂነር አባሻውል ወልደማሪያምን ነው። እርሳቸው በቀድሞ ስሙ አውራ ጎዳና በሚባለው መስሪያ ቤት ከመሀንዲስነት እስከ ዋና ሥራ አስኪያጅነት ሠርተዋል። በአውራጎዳና ታሪክም ሁለተኛው ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። የእርሳቸውን ታሪክ ለመሰነድ ስናስብ ቀዳሚ ትብብር ያደረጉልን የሚድያ ሰዎቹ ኤልያስ ተክለወልድና አቶ ሳምሶን ወንድሙ ናቸው። በተለይ አቶ ሳምሶን ከኢንጂነር አባሻውል ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለእኛ እንደሚሆን አድርገው ስለሰጡን ልባዊ ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን። ሁለተኛ ልጃቸው ዶክተር አይዳም ቀና ትብብር በማሳየት፣ ሰነድና ፅሑፎችን በመስጠት ለመጣጥፉ ተሳክቶ መቅረብ የበኩሏን አዋጥታለች። በነገራችሁ ላይ አባሻውል ህይወታቸው ካለፈ ዛሬ ጷግሜ 4 2018 ዓ.ም 6 ዓመት ሞላቸው። ህይወታቸው ሲያልፍ 91 ዓመታቸው ነበር።
ታሪክ ሰናጆቹ ቤርሳቤህ ጌቴ እና እዝራ እጅጉ ደግሞ ታሪኩን እንደሚከተለው አጠናክረውታል።
የአቶ አባሻውል ወ/ማርያም የሕይወትና የሙያ ጉዞ
የሰው ሕይወት አንድ ቀጥተኛ መንገድ አይደለም። አንዳንዴ ሕልም ወደ ሌላ ሕልም ይመራል፤ አንዳንዴም የጀመረው መንገድ ሳይጠናቀቅ ሌላ የሕይወት ጥሪ ይመጣል። አቶ አባሻውል ወ/ማርያም የሕይወት ጉዞም ከዚህ የተለየ አልነበረም። ከልጅነት ዘመናቸው ጀምሮ በትምህርት፣ በሙያ፣ በአመራርና በሀገር አገልግሎት የተዘረጋው የሕይወታቸው መንገድ ብዙ ማቆሚያዎችን ቢያልፍም፣ የሙያ ፍቅራቸውና የማገልገል ፍላጎታቸው ግን በአንድ አቅጣጫ ቀጥሎ መጥቷል።
አቶ አባሻውል ወ/ማርያም፣ በብዙዎች የባለሥልጣኑ መ/ቤት ሠራተኞች ዘንድ በሚገባ የሚታወቁ ሰው ናቸው። በተቋሙ ታሪክ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከዋና ሥራ አስኪያጅነት ዘመናቸው ከሁለት አስርተ ዓመታት በኋላም እንኳ ለሙያቸውና ለቀድሞ መ/ቤታቸው ያላቸው ፍቅር እየጎለበተ መምጣቱ ነው በብዙዎች ዘንድ ልዩ የሚያደርጋቸው።ባለሙያ የሚፈለገው በሥራ ዘመኑ ብቻ አይደለም። ዕውቀትና ልምድ የሚያረጁ ነገሮች አይደሉም። ይህንንም አቶ አባሻውል በሕይወታቸው በተግባር ያሳዩት ሰው ናቸው።
ከሐረር የተነሳው ጉዞ
አቶ አባሻውል ወ/ማርያም ህዳር 28 1921 ዓ.ም. በሐረር ከተማ ተወለዱ። አባታቸው አቶ ወልደማሪያም ወልደጊዮርጊስ እናታቸው ደግሞ ወይዘሮ መሳይ ዋልተንጉሥ ይባላሉ።ልጅነታቸውን በዚያው ከተማ ካሳለፉ በኋላ በ1934 ዓ.ም. የመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባን ረገጡ። ከዚያም ዘመናዊ ትምህርታቸውን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ጀመሩ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት ቀጠሉ።
የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ አንድ ሴሚስተር ብቻ በቀራቸው ጊዜ ግን የሕይወታቸውን አቅጣጫ ሊቀይር የሚችል ሌላ ጥሪ ተሰማቸው። የአየር ኃይል ጀት አብራሪነት።
የበረራ ሕልም ትምህርታቸውን ለጊዜው እንዲያቋርጡና የአየር ኃይል ግቢን እንዲቀላቀሉ አደረጋቸው። የአብራሪነት ኮርሱን በመከታተል ካጠናቀቁ በኋላም የበረራ ሥራቸውን ጀመሩ።
ነገር ግን ሕይወት ለእርሳቸው አንድ መንገድ ብቻ አልመደበችላቸውም። ከአንድ ወር የበረራ ሥራ በኋላ ወደ ትምህርታቸው ተመለሱ። የቀድሞ የትምህርት መንገዳቸውን እንደገና በመያዝም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።
የጀመሩት የበረራ ጉዞ ምናልባት ለአጭር ጊዜ ነበር፤ ነገር ግን የሕይወታቸው ትልቁ ጉዞ ገና ከፊታቸው ነበር።
ጉዞ ወደ አሜሪካ
በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ለመክፈት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በሂደት ላይ ነበሩ። ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ከዊንጌት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተመረቁ ተማሪዎችም ከእንግሊዝና ከአሜሪካ የሚላክ ፈተና እንዲወስዱ ዕድል ተፈጠረ።
አቶ አባሻውል ይህንን ፈተና በማለፋቸው አዲስ የሕይወት ገጽ ተከፈተላቸው፤ አቅጣጫቸውም ወደ አሜሪካ ሆነ።
በዌብር ስቴት፣ ኦሃዮ አንድ ዓመት ትምህርት ከተከታተሉ በኋላ በካንሳስ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ። በዚያም የትምህርት ጉዞቸውን በመቀጠል የድህረ ምረቃ ትምህርትን ለአንድ ሴሚስተር ተከታተሉ።
ከዚያም በኢሊኖይ በሚገኝ የሀይዌይ ተቋም በተግባራዊ ሥልጠናና በሥራ አንድ ዓመት አሳለፉ። ይህ ጊዜ የተማሩትን በመጽሐፍ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሥራ ላይ በመፈተን የሙያ ልምዳቸውን የገነቡበት ወቅት ነበር።
የድህረ ምረቃ ዕቅዳቸውን ለማሳካት ያደረጉት ጥረት ግን በታሰበው መልኩ አልተሳካም። ምክንያቱም ከሀገር ቤት የመጣው ጥሪ ከትምህርታቸው ዕቅድ የበለጠ አስቸኳይ ነበር።
በወቅቱ የአውራ ጎዳና ባለሥልጣን ከፍተኛ የሰው ኃይል ፍላጎት ነበረበት። በተለይም የተማሩና የሙያ እውቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በአስቸኳይ ያስፈልጉ ነበር። በኋላ የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁበት ዕድል እንደሚመቻችላቸው ተገልጾላቸው፣ እርሳቸውና እንደርሳቸው የድህረ ምረቃ ትምህርቱን ሲከታተል የነበረው አቶ ሙሉጌታ ሥነ ጊዮርጊስ በ1947 ዓ.ም. በወርኃ ጥር ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
የመሐንዲስነት ዘመን
ከአንድ ወር በኋላ አቶ አባሻውል በአውራ ጎዳና ባለሥልጣን መ/ቤት በመሐንዲስነት ተቀጠሩ። በዚያ የጀመሩት ሥራ በሙያቸው የረጅም ዘመን ጉዞ መሠረት ሆነ።
መ/ቤቱ በአስተዳደርና በቴክኒክ ክፍሎች ተዋቅሮ የተለያዩ ሥራዎችን ያከናውን ነበር። እርሳቸውም ከአቶ ሙሉጌታ ሥነ ጊዮርጊስ ጋር በቴክኒክ ክፍሉ ተመደቡ።
” መንገድ የልማት መሠረት ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ መብራት፣ የአየርና የባህር መገናኛዎች፣ እንዲሁም የሕንጻ ኮንስትራክሽን የመሳሰሉት ሥራቸውም ሆነ አገልግሎታቸውን ለማዳረስ ብሎም አጥጋቢ ውጤት ሊሰጡ የሚችሉት የመንገድ መገናኛ ሲኖር ነው፡፡ መንገድ ለማሕበራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ለፖለቲካዊ ዕድገትና ዓላማ መሳካት ቀዳሚ ፈር ቀዳጅ ነው፡፡ አንድ አገር በኢኮኖሚ ሊራመድ የሚችለው ጤናማና የተማረ ሕዝብ ከመልካም አስተዳደር ጋር ሲኖር ነው፡፡ የጤናና የትምህርት ተቋሞች ሊስፋፉ የሚችሉት የመንገድ መገናኛ ሲስፋፋ ነው፡፡ አስተዳደር ሊሻሻል የሚችለው ጤናው የተጠበቀና የተማረ ንቁ ሕዝብ ሲኖር ነው፡፡ ስለዚህ በትክክል ሲባል እንደኖረው መንገድ የደም ሥር ነው፡፡ በሰውነት ውስጥ ደም ካልተንቀሳቀሰ ሰውነት በድን ይሆናል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገትም አይኖርም ማለት ነው፡፡”
ይላሉ አቶ አባ ሻውል መንገድን ሲገልፁ።
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሥራ እየሰፋ ሲመጣ አዳዲስ የሥራ ክፍሎችን ማቋቋም አስፈላጊ ሆነ። በዚህም አቶ አባሻውል ከአሜሪካ ከመጣ አንድ ባለሙያ ጋር በመሆን የማቴሪያል ክፍል እንዲቋቋም አደረጉ። ለጥቂት ዓመታትም በዚያው ክፍል አብረው ሠሩ።
በዚህ ሂደት የትምህርት ዕውቀታቸውን ከተግባራዊ ሥራ ጋር አጣመሩ። ልምድ እያከማቹ፣ ኃላፊነት እየጨመረላቸው መጣ። በመጨረሻም የባለሥልጣኑ መ/ቤት ረዳት ዋና መሐንዲስ ሆነው ተመደቡ። በኋላም የዋና መሐንዲስን ቦታ ተክተው እንዲሠሩ ተደረገ።
ይህ የሥራ ሂደት ከአንድ የሙያ ዕድገት በላይ ትርጉም ነበረው። በተቋሙ ውስጥ ኃላፊነት ከአሜሪካውያን ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እየተሸጋገረ የመጣበት የለውጥ ሂደት ነበር። እርሳቸውም በዚህ ሂደት የራሳቸውን ድርሻ ተወጡ።
” በባለሥልጣን መ/ቤቱ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኜ ከ1958 ዓ.ም እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ያገለገልኩት እኔ ነበርኩ፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኜ እንድሠራ ኃላፊነቱ ከተሰጠኝ በፊት በመሥሪያ ቤቱ በተራ መሐንዲስነት እስከተለያዩ የኃላፊት ቦታዎች ለአሥራ አንድ ዓመታት ስለሰራሁ ከብዙ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ጋር በቅርብ ተዋውቄያለሁ፡፡ የመሥሪያ ቤቱንም ችግር ተረድቼ ነበር፡፡ ስለዚህ ትኩረቴ የነበረውን ችግር ለማቃለልና መሥሪያ ቤቱንም በተቻለ ወደዘመናዊ አሠራር ለማሸጋገር ነበር፡፡
ይህን ለማድረግ ደግሞ ትዕግስትና ዘዴ እንደሚያስፈልገው ተረዳሁ፡፡ የሠለጠነ የሰው ኃይል፣ መሣሪያና አስፈላጊ ዕቃዎች እንዲሟሉ ለማድረግ ከፍ ያለ ጥረት የሚያስፈልገው ነበር፡፡
ስለዚህ ከሁሉ አስቀድሞ መሠረት የሆነውን የመሥሪያ ቤቱ መዋቅር፣ የሥራ አመዳደብ፣ የሥራ ዝርዝር፣ ለየሥራ መደብ አስፈላጊ የሆነውን የዕውቀት ደረጃና የሥራ ልምድ፣ የደመወዝ ስኬልና የሠራተኛው ጥቅማ ጥቅሞች ወቅቱን የተከተለ ጥናት ተደርጎ እሥራ ላይ መዋል በግድ አስፈላጊ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ጉዳዩን ለቦርድና ለሚመለከታቸው የዓለም ባንክ ሰዎች በማቅረብ፣ በማስረዳትና በማሳሰብ አስፈላጊው በጀት ከዓለም ባንክ ከተገኘ በኋላ በአሠራሩ በቂ ልምድ ያለው PAS (ፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን ሰርቪስ) የተባለ አማካሪ ኩባንያ (ኮንሳልታንት) በዓለም አቀፍ ውድድር አሸንፎ ከተመረጠ በኋላ አስፈላጊ የሆኑትን ጥናቶች አካሄዶ ውጤቱን አቀረበ፡፡ ጥናቱንም የሚመለከታቸው የመሥሪያ ቤቱ ባልደረቦች በግልና በጋራ በዝርዝር ተመልክተው አስተያየት ከሰጡበት በኋላ በመጨረሻ ለቦርድ ቀርቦ የመሥሪያ ቤቱ ሕግ አማካሪዎችም ተመልክተውት አስፈላጊ የሆኑ እርማቶች ሁሉ ከተደረጉ በኋላ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡”
አስራ ሦስት የአመራር አመታት
በባለሥልጣኑ መ/ቤት ያሳለፉት 11 ዓመታትና በውጭ ሀገር ያገኙት የሁለት ዓመት ተኩል የሥራ ልምድ በድምሩ ወደ 13 ዓመት የሚጠጋ የሙያ ጉዞ ፈጠረ። ይህ ልምድ በ1958 ዓ.ም. የአውራ ጎዳና ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሆኑ አበቃቸው።
ከመሐንዲስነት የጀመረው ጉዞ ወደ ከፍተኛ አመራር ደረጃ ደረሰ። እርሳቸውም ይህንን ኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ መ/ቤቱን መርተዋል።
ይህ የአመራር ዘመን በተቋሙ ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የሙያና የአመራር ሚናቸውን በማጠናከር ላይ የነበሩበት ወሳኝ ወቅት ነበር። አቶ አባሻውልም በዚህ ታሪክ ውስጥ ስማቸውን በግልጽ አስቀምጠዋል።
ከ1966 ዓ.ም. በኋላ እርሳቸው በተለያዩ ድርጅቶች በሙያቸው አገልግለዋል። የሥራ ቦታቸው ቢቀየርም፣ የሙያ ልባቸው ግን ከጀመሩበት ተቋም አልተለየም።
ዓመታት አለፉ። የሥራ ዘመናቸው ቀጠለ። ተቋማት ተቀየሩ፣ ኃላፊነቶችም ተለዋወጡ። ነገር ግን አቶ አባሻውል ከቀድሞ መ/ቤታቸው ጋር የነበራቸው ትስስር አልተቋረጠም።
እንደገናም ሕይወት ወደ ቀድሞ መንገዳቸው መለሰቻቸው።
አቶ አባሻወል በመንገድ ሥራ ላይ ጣሊያኖች የነበራቸውን ሚና ሲናገሩ ” ጣሊያኖች በኢትዮጵያ ከ1928 ዓ.ም እስከ 1933 ዓ.ም ባሉበት ጊዜ በርካታ መንገዶችና ድልድዮች መሥራታቸው የተረጋገጠ ነው፡፡ በዚያን ዘመን መንገድ የሚሠራው በአብዛኛው በሰው ጉልበት ነበር፡፡ መሣሪያም ቢኖር ካሚዮን፣ ሩሎ፣ የድንጋይ መሠርሠሪያ፣ ማፈንጃና ወፍጮ የመሳሰሉት ናቸው እንጂ እንዳሁኑ ዘመን ከባድ መሣሪያዎች እንደ ዶዘር፣ ግሬደር፣ ስክሬፐር፣ ኤክስቫተር፣ ሎደርና ገልባጭ መኪናዎች አልነበሩም፡፡ ስለዚህ መንገዶች ኮንቱር (የመሬትን አቀማመጥ) ተከትለው ጠመዝማዛና መሠረቶችም ለጊዜው ሊጠቀሙበት በሚችለው ዓይነት በትላልቅ ድንጋዮች በእጅ ተነጥፈው ነበር የሚሠሩት፡፡ በ1943 ዓ.ም አውራ ጎዳና መሥሪያ ቤት ሲቋቋም ጣልያን ከለቀቀ አሥር ዓመት ሆኖት ነበር፡፡ ስለዚህ አሥሩን ዓመት ጣልያን የሠራቸው መንገዶች በቂ ጥገና ባለማግኘታቸው በአብዛኛው ከባድ ብልሽት ደርሶባቸው ነበር፡፡ በዚህም ላይ ጣልያኖች ተሸንፈው ሲሸሹ አብዛኛውን ድልድዮች አፈራርሰዋቸው ነበር፡፡
ስለዚህ እንደ አሰብ ያሉ መንገዶች ደርሶ መልስ በሳምንታት የሚቆጠር ጊዜ የሚወስድ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ እንዲሁም ሌሎችም ነባር መንገዶች መኪናዎች በየቦታው እየተሰባበሩ ለመድረስና ለመመለስ ከሳምንታት እስከ ወራት የሚፈጅባቸው ጊዜ ነበር። በመሆኑም አውራ ጎዳና ባለሥልጣን ሲቋቋም የመጀመያ ሥራው መሥሪያ ቤቱን ከማቋቋም ጋር ነበሩ የተባሉትን ከአገልግሎት ውጭ የሆኑትን መንገዶች በተገኘችው ውስን በጀት መሠረቶቻቸውን አጠናክሮና በተቻለ ስፋትም ጨምሮ በመሥራት ትራፊክ መንቀሳቀስ እንዲችል ማድረግ ነበር፡፡ በመሆኑም በጣልያን የወረራ ዘመን የተሰሩ መንገዶች በከፍተኛ ደረጃ ተበላሽተው ስለነበር የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ከተቋቋመ ጀምሮ ባሉት ዓመታት አብዛኛዎቹ እንዲሻሻሉና በአዲስ መልክ እንዲሠሩ በመደረጉ ነው አገልግሎት ሊሰጡ የቻሉት፡፡” ብለዋል።
አባሻውል ከቤተሰብ ፍቅር እስከ መንገድ ሥራ ትውስታ
የአባሻውልን ሕይወት ለመረዳት የሥራ ታሪካቸውን ብቻ ማየት በቂ አይደለም። ከመንገዶች፣ ከሙያዊ ሥራዎችኛ ከሕዝብ ጋር ካደረጉት ግንኙነት በስተጀርባ ቤተሰባቸውን በጥልቅ የሚወዱ፣ ልጆቻቸውን የሚያዳምጡና በአክብሮት የሚያነጋግሩ አባት ነበሩ። የልጃቸው የዶክተር አይዳ አባሻውል ትዝታዎችም ይህንን የአባሻወልን ሌላ ገጽታ በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው።
ዶክተር አይዳ አባሻውል የቤተሰቡ ሁለተኛ ልጅ ነች። አባሻወልና ባለቤታቸው ወይዘሮ በለጥሻቸው ሦስት ሴቶች ልጆች ያሏቸው ሲሆን፣ ሦስቱም በናዝሬት ትምህርት ቤት ነበር የተማሩት። የልጆቹ የልጅነት ትዝታ ግን ከኦሊምፒያ ሰፈር ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነበር። በወቅቱ አካባቢው እንደዛሬው የተገነባና የተጨናነቀ አልነበረም። ብዙው ቦታ ባዶ መሬት፣ እንደ ሜዳ የሚታይ አካባቢ ነበር። አባሻውል በዚያ አካባቢ መሬት ገዝተው ቤት ሰርተው ገቡ። ይህ ቤት ለአባሻውል ብቻ የመኖሪያ ቦታ አልነበረም፤ ለሦስቱ ሴቶች ልጆች የልጅነት ዓለም፣ ለቤተሰቡም የፍቅርና የትውስታ ማዕከል እንጂ።
ዶክተር አይዳ አባቷን ስታስታውስ በመጀመሪያ የሚመጣላት ነገር ርህራሄያቸውና ልጆቻቸውን የሚያዳምጡበት መንገድ ነው። አባሻውል በባህሪያቸው ጸጥተኛ ሰው ነበሩ። “ልጆቹን በቀላሉ የሚያዳምጥ፣ ሀሳባቸውን የሚቀበልና እንደ ትንንሽ ልጆች ሳይሆን እንደ ትልቅ ሰዎች የሚያነጋግራቸው አባት ነበር። በቀላሉ አይቆጣም፤ ልጆቹም ከእሱ ጋር ሳይፈሩ ሀሳባቸውን ይናገሩ ነበር።” ብላለች።
እናታቸው ወይዘሮ በለጥሻቸው ግርማ ደግሞ ከእርሱ በተለየ መልኩ ማህበራዊ ሕይወትን የሚወዱ፣ ሰዎችን መገናኘትና በማህበራዊ ዝግጅቶች መሳተፍ የሚሰምርላቸው ሴት ናቸው። በሁለቱ መካከል የነበረው ፍቅር ጥልቅ ነበር። ወይዘሮ በለጥሻቸው የሕፃናት ማዋያ በመክፈት ወላጅ የሌላቸውን ልጆች በመንከባከብና በጊዜው በሀገሪቱ ያልተለመደውን የመዋእለ ህፃናት አሰራር ለሀገሬው በማስለመድ ፈር ቀዳጅ ናቸው ማለት ይቻላል። የኋላ ኋላ በዘመነ ደርግ ልፋታቸው ሁሉ ከንቱ ሆኖ ሊወረስባቸውና እርሳቸውንም ለእስር ዳረጋቸው እንጂ።
የተሳሰረ የፍቅር ትውስታ
ከወይዘሮ በለጥሻቸው ግርማ አንደበት፦
” ከአባሻውል ጋር ያለኝ ትውውቅ ከቅርብ ዘመድነት የተነሳ ነው። የመጀመሪያው የተገናኘንበት ጊዜ ግን እንደ አንድ ትንሽ ክስተት ቢጀምርም፣ በኋላ ላይ ወደ ሕይወቴ የተለየ ትርጉም ያለው ትዝታ ሆኖ ቀርቷል።
በወቅቱ በፈረንሳይ ትምህርት ቤት ሊሴ እማር ነበር። በዚያ የሚማሩ ትንንሽ ልጆች ነበሩ፤ እኔም ከእነሱ ጋር በቅርብ እገናኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የልጆቹ እናት ልጆቿን እንድጠብቅላት ትጠይቀኝ ነበር። አባታቸውም አቶ ዘነበ ሃይሌ ይባላሉ፤ በወቅቱ በመንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ኃላፊነት የነበራቸው ሰው ነበሩ።
አባሻውልን ለመጀመሪያ ጊዜ በደንብ ያየሁት ከዚህ የተነሳ ነው። አንድ ቀን በስፖርት ሜዳ ላይ ስፖርት እየሠራሁ ነበር። እኔ ስፖርቴን ልጨርስ ስል አንዲት ጓደኛችን ተጠርታ ወደ እኔ መጣችና አንድ ሰው እንደሚፈልገኝ ነገረችኝ። እኔም ሮጬ ሄጄ ከሩቅ አየኋቸው።
በዚያ ጊዜ እንደ ዘመድ እንደምታውቀው ተነግሮኝ ነበር። ስለዚህ ቀርቤ እጄን ዘርግቼ ሰላምታ ሰጠሁት፣ ከዚያም ተሳሳምን። ያኔ ነው አባሻውልን ለመጀመሪያ ጊዜ በዓይኔ ያየሁት።
በኋላ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ የተገናኘነው በሌላ አጋጣሚ ነበር። ትምህርት ቤት በሌለበት ቀን ብዙ ጊዜ በአያቶቼ ቤት እቆይ ነበር። በዚያ ወቅት አክስቴ ልጆቿን ይዛ መጣችና ለሽርሽር እንድንወጣ ጋበዘችን። እኔና እህቴም አብረናት ሄድን።
ወደ ደብረ ዘይት፣ ቢሾፍቱ ሄደን ራዕይ ሆቴል ደረስን። ምሳ ለመብላት ተቀምጠን ሳለ አባሻውልም በዚያ ነበር። ያኔ እህቴን አቀራረብኳትና ይህ ሰው ዘመዳችን እንደሆነና በትምህርት ቤት ተዋውቀን እንደነበር ነገርኳት። እሷም እንደ ዘመድ ተቀበለችው። ከዚያም አባሻውል ተጠርቶ መጣና አብረን ምሳ በላን።
እነዚያ ቀናት ግን እኔ ከአባሻውል ጋር ሌላ ዓይነት ግንኙነት እንደሚኖረኝ አላሰብኩም ነበር። እርሱን እንደ ዘመድ ነበር የማየው።
በኋላ ግን በተለያዩ የቀን ግብዣዎችና የጓደኞች ስብሰባዎች እየተገናኘን መጣን። በዚያን ጊዜ የተማሪዎች የቀን ድግሶች፣ ቲ-ፓርቲዎች እና የምረቃ ዝግጅቶች ይካሄዱ ነበር። እኛም እንደ ተማሪዎች በእነዚህ ዝግጅቶች እንገናኝ፣ እንዝናና እና እንመለስ ነበር።
አባሻውል በወቅቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር። እህቴም የራሷ የፍቅር ግንኙነት ነበራት። ያ ሰው ዩኒቨርሲቲ ይማር ነበር፣ ትምህርቱንም አጠናቆ በኋላ ወደ አሜሪካ ሄደ። እኛም በምረቃ ዝግጅቱ ተገኝተን ደስታችንን አጋርተን ነበር።
እነሱ ግን ቃል ኪዳናቸውን አጠናቀው በኋላ እርሱ ወደ አሜሪካ ሄደ። እህቴም ትምህርቷን ጨርሳ የሚያስተምርበት ቦታ ስለተገኘላት ወደ አሜሪካ ለመሄድ ዝግጅት ጀመረች።
ይህ ሁኔታ ለአባሻውል ግን ሌላ ትርጉም ነበረው። እህቴ ከሀገር ለመውጣት ዝግጅት ላይ መሆኗን ሲያውቅ፣ እርሱም ወደ ቤተሰቡ ሄዶ ሽማግሌ ለመላክ ፍላጎቱን አሳየ።
ያኔ በቤተሰብ ውስጥ ትንሽ ማመንታት ተፈጠረ። ታላቂቱን ልጃቸውን አሁን አግብተው ለሌላዋ ልጃቸው ደግሞ በዚያው ጊዜ የጋብቻ ጉዳይ መነሳቱ ቤተሰቡን አስብቶ ነበር። በተለይም የቤተሰብ ግንኙነት፣ የሽማግሌዎች ምክርና የልጆቹ ፍላጎት በአንድ ላይ ተመዝነዋል።
በመጨረሻ ግን በቤተሰቦችና በሽማግሌዎች ስምምነት ጉዳዩ ወደፊት እንዲሄድ ተወሰነ። እኔም ከዚያ በፊት አባሻውልን እንደ ዘመድ እንጂ እንደ የወደፊት ባለቤቴ አይቼው አላውቅም ነበር።
አባሻውል ግን ስሜቱን በቀጥታ ለመናገር የወሰነው ያኔ ነበር። በአንድ ቀን ከእህቴ ጋር ተገናኝቼ ሳለሁ እርሷ ጉዳዩን አነሳችልኝ። አባሻውል እንደሚወደኝና እንዲያገባኝ ፍላጎት እንዳለው ነገረችኝ።
እኔ ግን በዚያን ጊዜ ገና ተማሪ ነበርኩ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ገና አልጨረስኩም ነበር፤ አንድ ዓመት ይቀረኝ ነበር። ስለዚህ ትምህርቴን ሳልጨርስ ማግባት እንደማልፈልግ ነገርኩት። እርሱ ግን ትምህርቴን እንደምጨርስ በማመን ቢያንስ ቃል እንድገባለት ጠየቀኝ።
እኔም በዚያን ጊዜ ፈጣን ውሳኔ መስጠት አልፈለግሁም። “ላስብበትና እነግርሃለሁ” ብዬ መለስኩለት። ከዚያም ተለያየን።
ከዚያ በኋላ ግን ግንኙነታችን በስልክ ቀጠለ።
በዚያን ዘመን እንደዛሬው በነፃነት ስልክ ማውራት ቀላል አልነበረም። ስለዚህ አንዳንዴ ተደብቄ እናገረው ነበር። እርሱም ይደውልልኝ ነበር፤ ስልኩን ዘግቶ ሲያበቃ እርሱ እንደነበር እገምትና እኔም መልሼ እደውልለት ነበር። ይህ ሁሉ እየሆነ የ1950ዎቹ መጨረሻ ደረሰ። እኔም ትምህርቴን ጨርሼ የሕይወቴን ቀጣይ ደረጃ ለመወሰን የምችልበት ጊዜ ደረሰ።
በመጨረሻም የቤተሰቦችና የሽማግሌዎች ውይይት ወደ መልካም ውሳኔ ደረሰ። እኔም ከአባሻውል ጋር የሚኖረኝን የሕይወት ጉዞ ለመጀመር ፈቃደኛ ሆንኩ።
የቀለበት ሥነ-ሥርዓቱም በልዩ ሁኔታ ተከናወነ። ሁለታችንም እህቶች በአንድ ቀን ቀለበት ተደረገልን። ያ ቀን በሕይወቴ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ቀን ነበር። ቀደም ሲል እንደ ዘመድ የማውቀው ሰው በቀስታ ወደ ሕይወቴ የሚገባ የትዳር አጋር ሆኖ ተለወጠ። የመጀመሪያው ትውውቃችን፣ የተደጋጋሚ መገናኘታችን፣ የስልክ ውይይቶቻችን፣ የቤተሰቦች ምክርና የሽማግሌዎች ስምምነት ተደራርበው ወደ አንድ የሕይወት ውሳኔ አደረሱን።”
ወይዘሮ በለጥሻቸው እንዳስታወሱት ትውውቃቸው በዘመድነት ስሜት ተጀምሮ፣ በወዳጅነት ተሻግሮ፣ በመጨረሻም ወደ ትዳር የተለወጠ የሕይወት ጉዞ ነበር። ዛሬ ያንን ዘመን ሲያስታውሱ፤ በእነዚያ ቀናት የተከናወኑ ትንንሽ ክስተቶች እንኳን በሕይወታቸው ትልቅ ቦታ እንዳላቸው ይገነዘባሉ።
ልጆችን የፈተነው ዘመን
የቤተሰቡ ሕይወት በድንገት የተለወጠው ደርግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ነበር። አባሻውል ለስምንት ዓመታት የታሰሩ ሲሆን ባለቤታቸው ወይዘሮ በለጥሻቸው ደግሞ ለአንድ ዓመት ያህል ታስረዋል። ይህ ለሦስቱ ሴቶች ልጆች በተለይ ከባድ የሕይወት ዘመን ሆነ።
አይዳ በዚያን ጊዜ ገና ታዳጊ ነበረች። የአባቷ መታሰር በልጅነቷ ላይ ጥሎት የሄደው ትዝታ እስከ አሁን ድረስ ከእሷ አልተለየም። አባት ከቤት መራቁ ብቻ ሳይሆን፣ እናትም ለእስር መዳረጓ ቀላል አልነበረም።
አባሻውል የታሰሩበት ቦታ ዛሬ በዩኒቲ ፓርክ ውስጥ ሙዚየም የተሰራበት በቤዝመንት ውስጥ በነበሩ ማሰሪያዎች ውስጥ ነበር። አይዳ ስለዚያ ዘመን ከአባቷ ብዙ ነገር እንዳልጠየቀች ታስታውሳለች ” እሱም ስለ እስር ቤቱ ብዙ አይናገርም ነበር። ግን
በዚያ ወቅት ከእሱ ጋር የነበሩ የቅርብ ሰዎች መካከል አንዱ ተወስዶ መገደሉ ደግሞ በአባቴ ላይ ጥልቅ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር። ይህ ትዝታ ከእስር ዘመኑ ጋር ተያይዞ በልቡ ውስጥ ቀርቶ ነበር።”
አባሻውል የጻፋቸው የዕለት መዝገቦችና ደብተሮችም አሁን በዶክተር አይዳ እጅ ይገኛሉ። እሷ ገና ሙሉ በሙሉ ማንበብ እንዳልጀመረች ትናገራለች፤ ነገር ግን እነዚህ ደብተሮች የአባቷን ውስጣዊ ዓለም፣ ያሳለፈውን ጊዜና ያልተነገሩ ትዝታዎችን ሊያሳዩ እንደሚችሉ ታምናለች። ስለዚህም በጥንቃቄ ልታነባቸው ተዘጋጅታለች።
ስምንት ዓመታት ረጅም ጊዜ ናቸው። ለአንድ አባት ከልጆቹ ርቆ ማሳለፍ ደግሞ ከቀናትና ከወራት በላይ የሚመዘን ጉዳይ ነው። ሆኖም አባሻውል ከእስር ከተፈቱ በኋላ የሥራ ሕይወታቸውን እንደገና መቀጠል ቻሉ። መንግሥት እንደገና ፈልጓቸው ከካሳ ገብሬ ጋር በመሆን በገጠር መንገዶች ላይ ለመሥራት ችለዋል። ከጂቲዜድ (GTZ) ጋርም የሥራ ግንኙነት ነበራቸው። ይህ ሁሉ የሚያሳየው በሙያው ላይ የነበራቸው ትልቅ ቁርጠኝነት እና እውቀቱ ከእስር ዘመን በኋላም እንዳልጠፋ ነው።”
የአባሻውል የእስር ዘመን ሲያበቃ ልጆቹ ሁሉም ወደ ውጭ ሄደው ነበር። አይዳም በአሜሪካ ትምህርቷን ቀጠለች። በመጀመሪያ ለሕክምና ትምህርት የሚያስፈልገው የገንዘብ አቅም እንኳን እንዳልነበራት ታስታውሳለች። የመግቢያ ፈተናውን ወስዳ ተቀባይነት ብታገኝም፣ የገንዘብ እጥረት መሰናክል ሆኖባት ነበር።
በዚያ ጊዜ አባቷ የሰጧት ምክር ከዛሬም በላይ በአእምሮዋ የተቀረጸ ነው። ከቃላቷ ውስጥ “አይቻልም” የሚለውን ቃል እንድታስወግድ ነገሯት። ሁሉም ነገር ይቻላል፤ የሚያስፈልገው ማመንና መጀመር ነው። ከዚያ በኋላ የሚመጣውን ሁኔታ እያየች መንገዷን እንድታስተካክል አበረታቷት።
ይህ ምክር ለአይዳ የትምህርት ምክር ብቻ አልነበረም። በአባቷ ሕይወት ራሱ የተፈጸመ እምነት ነበር። ስምንት ዓመት እስርን አልፈው ከዚያም ወደ ሥራው ተመልሰው፣ በድጋሚ የመንገድ ሥራዎችን የቀጠሉ ሰው ናቸውና “መጀመር” የሚለውን ቃል በሕይወታቸው አሳይተዋታል።
አይዳም በዚህ ምክር መሰረት ሕክምናን ተምራ ከጨረሰች በኋላ በህብረተሰብ ጤና (Public Health) እና በፕሪቨንቲቭ መድኃኒት (Preventive Medicine) ላይ ስፔሻላይዝ አደረገች።
እህቶቿም የራሳቸውን የሙያ መንገድ ተከተሉ። ሳባ አባሻውል ቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ተምራ በሂዩስተን ከተማ የኤርፖርት ሲስተም ኃላፊ በመሆን ለብዙ ዓመታት ሠርታለች። በዚያ መስክ በቴክሳስ የታወቀች ሰው መሆኗን አይዳ በኩራት ታስታውሳለች። ምስራቅ ደግሞ ኮምፒዩተር ተምራ ከኦይል ኩባንያ ጋር ሠርታለች። በኋላ ሁለቱም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በአዲስ አበባ መኖራቸውን አይዳ ነግራናለች።
“ሀገርን ሊቀይር የሚችለው ሰው ነው!! ሰውን በእውቀት መገንባት ነው ለሀገር ወሳኝ ይለን ነበር አባታችን።”
#ዳግም ወደ መንገዶች ባለሥልጣን
በ1985 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከተቋቋመ በኋላ፣ ተቋሙ የተመደበለትን ዓላማ በተፈለገው መልኩ ለማሳካት አሠራሩን ውጤታማና ቀልጣፋ ማድረግ እንዲቻል አደረጃጀቱን እንደገና ማጥናት አስፈላጊ ሆነ።
በዚህ ወቅት እርሳቸው በድጋሚ ተጠሩ። የብዙ ዓመታት የሙያ ልምዳቸው፣ የአመራር ችሎታቸውና የተቋሙን ታሪክ በውስጥ የሚያውቁበት ልምድ በዚህ ወቅት እጅግ ጠቃሚ ሆነ።
የተቋሙን አደረጃጀት እንደገና በማጥናት ሥራውን በአስተባባሪነት እንዲመሩ በመንግሥት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ተቀበሉ። ሥራውንም በመምራት ለተገኘው ውጤት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበረከቱ።
ይህ ለእርሳቸው የሥራ ቦታ መመለስ ብቻ አልነበረም። አንድ ባለሙያ ከዓመታት በኋላ ያከማቸውን ዕውቀትና ልምድ ለሌላ ትውልድ የሚያስተላልፍበት የሕይወት ዙር ነበር።
በየክልሉ የገጠር መንገዶችን በኃላፊነት የሚያስተዳድሩ የገጠር መንገዶች ባለሥልጣን መ/ቤቶች እንዲቋቋሙ መንግሥት በወሰነበት ወቅትም፣ እርሳቸው ከGTZ ጋር በመተባበር እነዚህን ተቋማት ለማቋቋም በተካሄዱ የተለያዩ ጥናታዊ ሥራዎች ላይ ተሳተፉ።
በአውራ ጎዳና ባለሥልጣን የአቶ አባሻውል የሥራ ተሞክሮ
በዚያን ዘመን ከተሞች እንደአሁኑ በስፋት ባልተስፋፉበትና የመንገድ ሥራዎችም ከአሁኑ በተለየ ሁኔታ በሚከናወኑበት ወቅት፣ አውራ ጎዳና ባለሥልጣን ለራሱ ኃይል በሚያከናውናቸው የመንገድ ሥራዎች የሚመደበውን በጀት በጥንቃቄ በመጠቀም በተቻለ መጠን የተወሰኑ መንገዶችን ለመሥራት ጥረት ያደርግ ነበር። የሥራው ዋና ትኩረትም ለሠራተኞች የተለየ ምቾት መፍጠር ሳይሆን፣ የተመደበውን ገንዘብ በአግባቡ ተጠቅሞ የመንገድ ሥራውን በማከናወን የተወሰነ ርቀት ለመድረስ ነበር።
ይህ ሲባል በዚያን ዘመን ለካምፕ አሠራር ከፍተኛ ወጪ ይወጣ ነበር ማለት ሳይሆን፣ በአንጻሩ የነበሩት የኑሮ ወጪዎች ዝቅተኛ መሆናቸውና በየአካባቢው የነበረው ሕዝብም የመንገድ ሠራተኞችን እንደቤተሰብ በመቀበል ይረዳቸው ስለነበር ትልቅ ችግር አይፈጠርም ነበር።
“ሌላው የአውራ ጎዳና መሥሪያ ቤት ወደፊት በዓለም ደረጃ እንዲራመድ ለማድግ ብዙ የትምህርት ብቻ ሳይሆን የሥራ ልምድም ያላቸው ባለሙያዎች ያስፈልገው ነበር፡፡ ይህን ለማሟላት በአገር ውስጥ ብቻ በቀላሉ የሚፈታ ጉዳይ ስላልሆነ ተፈላጊውን የሥራ ልምድ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ማካሄድ እንዲቻል የበጀት ጉዳይ ሊፈታ የሚችለው በዓለም ባንክ ብድር ነበር፡፡ መንግሥት ለመንገድ ሥራ ከዓለም ባንክ ብድር ሲጠይቅ ባለሙያዎችንም የሥራ ልምድ እንዲያገኙ ለሥልጠናው የሚያስፈልገውን ፈንድ በብድሩ ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ በግድ አሳማኝ የሆነ ጥያቄ ይዞ መቅረብ ያስፈልግ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት የዓለም ባንክ በቂ ፈንድ ስለፈቀደ ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ ባለሙያዎች በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች የሥራ ልምድ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ከፍተኛ ትምህርትም ለማግኘት ችለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት አውራ ጎዳና ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ለሌላም የአገሪቱ መሥሪያ ቤቶች የሥራ ልምድ ያላቸው የባለሙያ ምንጭ ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡”
አቶ አባሻውል በአውራ ጎዳና ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ከ1947 እስከ 1966 ዓ.ም. ባሳለፉት የሥራ ዘመን፣ በተለይም ዋና ሥራ አስኪያጅ ከመሆናቸው በፊት ያሳለፉትን አሥራ አንድ ዓመታት እጅግ የሚያስደስታቸው የሥራ ዘመን እንደነበር ይገልጻሉ። በዚህ ወቅት የተማሩትን የምሕንድስና ሙያ በተግባር ላይ አውለው ውጤቱን ማየታቸው እጅግ ያስደስታቸው ነበር። ከሠራተኞችም ጋር የቀረበና የመግባባት ግንኙነት እንደነበራቸው ያስታውሳሉ።
” እኔ በተለየ መልኩ የማስታውሰውና መሠረት የጣለ ሥራ ነው ብዬ የማስበው የኢትዮጵያ ባለሙያዎች በሁሉም የአውራ ጎዳና ሥራ ዘርፍ ከበቂ የትምህርትና የሥራ ልምድ ጋር እራሳቸውን ችለው የባለሥልጣኑን አጠቃላይ ሥራ ለመሥራትና ለመምራት ፣ በኮንትራት የሚሠሩትንም በበላይነት ለመቆጣጠር መቻላቸው ነው፡፡ ለዚህም መሠረት የሆኑት ከላይ የተገለጹት ተግባራት ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡”
ከሥራው ባሻገር የገጠሩ አካባቢዎች ያኔ እንደአሁኑ በከፍተኛ ሁኔታ ያልተራቆቱ መሆናቸው፣ የነበራቸው ደንና የተፈጥሮ ውበት እንዲሁም የአካባቢው ሕዝብ የነበረው የዋህነትና ደግነት በጣም ያስደስታቸው ነበር። በዚህም ምክንያት የከተማ ኑሮ እስከዚያ ድረስ አያጓጓቸውም ነበር።
እንደአቶ አባሻውል ገለጻ፣ ይህ የሥራ ዘመን የመሥሪያ ቤቱን አሠራር ከታች እስከ ላይ በደንብ እንዲያውቁና በምሕንድስና ሙያቸውም በቂ የሥራ ልምድ እንዲያካብቱ ዕድል የሰጣቸው ጊዜ ነበር። ዋና ሥራ አስኪያጅ ለመሆንም የግል ምርጫቸው አልነበረም፤ የነበራቸው ዕቅድ አገራቸውን ለተወሰነ ጊዜ በምሕንድስና ሙያቸው ማገልገል ብቻ ነበር።
ነገር ግን ከ1958 እስከ 1966 ዓ.ም. በዋና ሥራ አስኪያጅነት ያሳለፉት ዘመን ከቀደመው የሥራ ሕይወታቸው በተለየ ሁኔታ ብዙ ጭንቀትና ጫና የነበረበት ጊዜ ነበር። ያቀዷቸውን የሥራ ዕቅዶች በተግባር ማዋል ቀላል አልነበረም። ሆኖም በወቅቱ የተከናወኑትን ሥራዎች ሲመለከቱ፣ ያደረጉት ጥረት ከንቱ እንዳልነበረ መገንዘባቸውን ይገልጻሉ።
የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት የዕድገት ሂደት
አቶ አባሻውል የመንገዶች ባለሥልጣን ለዛሬ ደረጃው እንዲደርስ አስተዋጽኦ ያደረገውን የታሪክ ሂደት ሲያስታውሱ፣ ተቋሙ ችግሮች ሳይገጥሙት በቀጣይነት ይሻሻል ነበር ቢሆን ኖሮ አሁን ካለበት የበለጠ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችል እንደነበር ያምናሉ።
እንደገለጹት፣ ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙ እንደገና ተሻሽሎ ከተቋቋመ በኋላ ዋና መንገዶችን በአስፋልት ማሻሻልና መሥራት፣ አዳዲስ መንገዶችን መገንባት፣ የመሥሪያ ቤቱን አሠራር በኮምፒዩተር የተደገፈ የማኔጅመንት ሲስተም እንዲኖረው ማድረግ እና የመንገድ ጥገናን ለመደገፍ የራሱ የሆነ ገቢ እንዲኖረው የRoad Fund አሠራር ለመጀመር የተወሰዱ እርምጃዎች ተቋሙ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው።
በተለይም የ10 ዓመቱ የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም በመንገድ ልማትና በጥገና ላይ ተግባራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አድርጓል። እነዚህ ለውጦች ተደማምረው የመንገዶች ባለሥልጣን በወቅቱ ከነበረው የበለጠ የተደራጀና የተሻለ አቅም ያለው ተቋም እንዲሆን አስተዋጽኦ እንዳደረጉ አቶ አባሻውል ያስረዳሉ።
“የአውራ ጎዳናን አሠራር ለማሻሻልም ሆነ በጀት እስኪፈቀድለት ድረስ መሥሪያ ቤቱ ላከናወናቸው ሥራዎች መሳካት ሊታወሱና ሊመሰገኑ የሚገባቸው በጊዜው የነበሩ የባለሥልጣኑ ሠራተኞች ናቸው፡፡ የሠራተኛውን ትብብር፣ በዱር በገደሉ ምቾትና ጥቅሙን ሳያስብ ለራሱ ከሚያስበው በላይ ለመሥሪያ ቤቱ በማሰብ፣ ጉልበቱን ሳይቆጥብ የተጀመረ ሥራ ለመጨረስ እስከ ሌሊቱ በመብራት እየሠራ እስከ መጨረሻው ለራሱ ጎጆ እንኳን ሳይሠራ ዕድሜውን የጨረሰ ብዙ ነው፡፡ ሠራተኛው ሲገናኝ የሚወያየው ስለመንገድ ሥራና ጥገና ነው፡፡
መንገዶች በብዛት እንዲሠሩ ከምኞትም በላይ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡” ይላሉ።
አባሻውልን ለማስታወስ የሚነሳው ትዝታ ከአንድ ሰው የግል ሕይወት ታሪክ ብቻ የሚጀምር አይደለም። እርሱን ለማወቅ የዘመኑን የልማት ጉዞ፣ የመንገድ ግንባታውን እና በዚያ ዘመን በነበረው አስቸጋሪ የሥራ ሁኔታ ውስጥ የተወጧቸውን ተግባራት ማየት ያስፈልጋል። አባሻውል ከእነዚህ ትውስታዎች መካከል በልዩ ሁኔታ የሚታወሱ ሰው መሆናቸውን የተሰጧቸውን ምስክርነቶች ሰምቶ ማረጋገጥ ይቻላል።
ከሙያዊ ሕይወታቸው በፊትም የአባሻውል ሕይወት ከቅርብ ሰዎቻቸው ጋር የተሳሰረ ነበር። ከእርሳቸው ጋር በልጅነት የተቀራረቡት ደጃዝማች የአባሻውል የትውልድ ቦታና የልጅነት ታሪክ በትዝታ ውስጥ በልዩ ሁኔታ ይጠቅሳሉ። የተወለደበት ቦታ ሐረር ኤጀርሳ ጎሮ መሆኑና በሀረር ስላሴ ቤተክርስቲያን ቀዳሽ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ አሰብ የሚወርደው መንገድ ከተሠራበት ዘመን ጋር የአባሻውል ስም በጥብቅ ይያያዛል። መንገዱ በሰሜን አካባቢዎችና በአፋር በኩል አልፎ ወደ አሰብ የሚደርስ ሲሆን፣ በወቅቱ ለንግድና ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ትልቅ ጠቀሜታ የነበረው መስመር ነበር። ቀደም ሲል ረጅም ጊዜ የሚፈጅበት ጉዞ ይህ መንገድ ከተሠራ በኋላ በእጅጉ እንደቀለለና የሚወስደው ጊዜም ወደ አንድ ቀን ተኩል ያህል እንደቀነሰ ደጃዝማች ወልደሰማእት ይናገራሉ።
” ይህ መንገድ የጉዞ ርቀትን ብቻ ያሳጠረ አልነበረም፤ የንግድ ሸቀጦችን፣ ነዳጅንና ሌሎች አስፈላጊ ጭነቶችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ለማጓጓዝ የሚያስችል ዋና የንግድ መስመር ሆኖ አገልግሏል። በዚህም መንገድ የተገነባው መሠረተ ልማት በወቅቱ ከነበረው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነበር።
እንደ አባሻውል ያሉ ባለሙያዎች በዚያን ዘመን ቀላል ባልነበረ የቴክኒክ ሥራ ውስጥ ትልቅ ኃላፊነት ይሸከሙ ነበር። የመንገድ አቅጣጫን መለካት፣ የመሬትና የአፈር ሁኔታን መመርመር፣ የመንገድ ዲዛይን ማዘጋጀትና ግንባታውን መከታተል የሥራቸው አካል ነበር። አባሻውልም በእነዚህ የቴክኒክ ሥራዎች የተለየ ብቃት ነበረው።”
በአዲስ አበባ–ቢሾፍቱ መንገድ ዲዛይንና ተያያዥ የቴክኒክ ሥራዎችም የእርሳቸው ተሳትፎ የተሰራ መሆኑን አያይዘው ገልፀውልናል። ” በሥራው ውስጥ የነበረው የቴክኒክ ጥንቃቄ፣ በቁጥርና በስሌት ላይ የሚያደርገው ትኩረት እና ሥራውን ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው በኃላፊነት የመከታተል ልምዱ ከባልደረቦቹ ዘንድ ክብር አስገኝቶለት ነበር። የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ሲዘጋጁ የሚያስፈልገው ስሌትና ዝርዝር ጥናት ይደረግ ነበር። ከዚያም ፕሮጀክቱ ለዓለም ባንክ ይቀርብ ነበር። የዓለም ባንክ መሐንዲሶችም ሥራውን በዝርዝር ይመረምሩ ነበር። በወቅቱ በኢትዮጵያ በቂ የአካባቢ ኮንትራክተሮች አለመኖራቸው ምክንያት የውጭ ኩባንያዎችና ኮንትራክተሮች በግንባታው ይሳተፉ ነበር። ክፍያዎችም በተወሰነ የቁጥጥር ሥርዓት በቀጥታ ለኮንትራክተሮች ይፈጸሙ ነበር።” በሚል አስተዋፅኦዋቸውን አብራርተውልናል።
አባሻውል ብቻውን የሠሩ ሰው አልነበሩም ይልቁን ከእርሳቸው ጋር የሠሩ ባለሙያዎች በኋላ በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካና በሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ሄደው ሥራቸውን ቀጥለዋል። ይህ የሚያሳየው በሥራ ቦታቸው ሌሎችን በማፍራት ረገድ የነበራቸው ሚና ምን ያህል የጎላ መሆኑን ነው። በኋላም አባሻውል ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን በመምከር የሥራ ዘመናቸውኝ ቀጥለዋል። በተለይም ለታምራት ላይኔ በመንገድና በሀይዌይ ግንባታ ዙሪያ ምክር ይሰጡ እንደነበር ይታወሳል። በግንባታ ሥራ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ሰዎችም ከእርሳቸው ምክርና ልምድ ያገኙ ነበር። አባሻውል እውቀታቸውን በራሳቸው ውስጥ አስቀምጠው የሚቀሩ ሳይሆኑ፣ ለሌሎች የሚያካፍሉ ሰው ነበሩ።
አባሻውልን የሚያስታውሱት ሰዎች ስለ ሙያዊ ብቃታቸው ብቻ አይናገሩም። ስለ ሰብዓዊነታቸው፣ ስለ ትህትናና ሰዎችን በክብር የመያዝ ባህሪያቸውም ብዙ ይመሰከርላቸዋል። ደጃዝማች ወልደሰማእት አባሻወል በቢሯቸው ‘ኢንጅነር ወተቴ’ ተብለው ይጠሩ እንደነበረ ያስታውሳሉ።
” አባሻውል በተፈጥሮው ጸጥተኛና የተረጋጋ ሰው ነበር። በችግር ጊዜ በቀላሉ የማይደናገጥ፣ ነገሮችን በማስተዋል የሚመዝንና ከዚያም ውሳኔ የሚወስን ነበር። ለሠራተኞቹም ትዕዛዝ በጩኸትና በቁጣ አይሰጥም ነበር፤ በረጋ መንፈስ ያስረዳ፣ የሥራውን ኃላፊነት ያስታውስና ውጤቱን ይጠብቅ ነበር። ሠራተኞቹን እንደ ተራ ተቀጣሪዎች ብቻ አያያቸውም ነበር። እንደ ጓደኞቹ ይቀርባቸው ነበር። ይህ ባህሪውም ከሰዎቹ ዘንድ ፍቅርና ክብር እንዲያገኝ አድርጎታል። ሥራን በቁም ነገር የሚያይ፣ ሰውን ግን በሰብዓዊነት የሚያይ መሪ ነበር።”
መንገዶች በመሬት ላይ ብቻ አይሠሩም፤ በሰዎች ሕይወት ውስጥም አሻራ ይተዋሉ። አንድ መንገድ ከከተማ ከተማ፣ ከአካባቢ አካባቢ፣ ከንግድ ከንግድ እና ከሰው ከሰው ያገናኛል። አባሻውልም በሠሯቸውና በተሳተፉባቸው ሥራዎች፤ የመንገድ ሥራ ብቻ ሳይሆን፣ በሰዎች ልብ ውስጥ ባስቀመጡት ትዝታ የሚታወሱ ሰው ሆነው ቀርተዋል።
የአባሻውል የሙያ ብቃትና የአመራር ችሎታ በአቶ የሺጥላ ደምሴ አንደበት (
” አባሻውልን በሥራ ዓለም በቅርበት የማውቃቸው ሰው ነኝ። በወቅቱ እኔ በፐርሰኔል ክፍል ውስጥ እሰራ ነበር፤ አቶ አባሻውል ደግሞ ዋና ማኔጀር ነበሩ። በዚያን ዘመን አውራ ጎዳና ድርጅት በብዛት በውጭ አገር ኢንጂነሮች ይመራ ነበር። ከውጭ የመጡ ኢንጂነሮች በድርጅቱ ውስጥ ቁልፍ የሆኑ የሥራ ቦታዎችን ይይዙ ነበር። ከእነዚህ ጋር በመስራት የታወቁ ኢትዮጵያውያን ኢንጂነሮችም ነበሩ።ከእነዚያ ጥቂት ብቁ ኢንጂነሮች መካከል ግን አቶ አባሻውል በተለየ ሁኔታ ብሩህ፣ ብልህና በሙያቸው እጅግ የተዋጣላቸው ነበሩ።
በወቅቱ ከነበሩት የውጭ ኢንጂነሮች ጋር ተወዳድረው የዋና ኢንጂነርነትን ኃላፊነት መረከባቸው የእርሳቸውን የሙያ ብቃት የሚያሳይ አንዱ ትልቅ ምልክት ነበር።
የአውራ ጎዳና ሥራ ቀላል ሥራ አይደለም። አዲስ መንገድ መገንባት፣ የተገነቡትን መንገዶች ማሻሻል፣ ጥገና ማድረግና በየጊዜው ሥራዎችን መቆጣጠር የሚጠይቅ ሰፊ ኃላፊነት ነው። ይህንን ሰፊ ሥራ ለመምራት ደግሞ የኢንጂነሪንግ ዕውቀት ብቻ አይበቃም። አስተዳደርን፣ ፋይናንስን፣ ኢኮኖሚን፣ የሰው ኃይልንና የሥራ አደረጃጀትን መረዳት ያስፈልጋል። አባሻውል እነዚህን ሁሉ በሚገባ የሚያስተዳድሩ ነበሩ።
አንድ ድርጅት በትክክል ለመምራት ዕቅድ ማውጣት፣ ማደራጀት፣ መምራትና መቆጣጠር ወሳኝ ናቸው። የሰው ኃይልንና ቁሳቁስን በትክክለኛው ቦታ ማሰማራት፣ ተገቢውን ሰው ለተገቢው ሥራ መምረጥና የእያንዳንዱን ሰው ችሎታ በብቃት መጠቀም የአመራር ችሎታ ነው። አቶ አባሻውል በዚህ ረገድ እጅግ የተሻሉ ነበሩ።
በተለይ ሰውን የመምረጥ፣ ችሎታውን የመፈተሽና በትክክለኛው የሥራ ቦታ የማሰማራት ችሎታቸው የሚደነቅ ነበር።
ሥራን ሁሉ እራሳቸው ለመሥራት ከመሞከር ይልቅ፣ ትክክለኛውን ሰው በመምረጥ ኃላፊነት ይሰጡ ነበር። ይህም ሰዎችን በብቃት የመጠቀምና ሥራን በተገቢው ሰው የማስመራት ችሎታቸውን ያሳያል።
የመንገድ ፕሮጀክት ከኢንጂነሪንግ ሥራ ብቻ አይጀምርም። አንድ ፕሮጀክት ከመጀመሩ በፊት የኢኮኖሚ ጥናትና የአዋጭነት ጥናት ያስፈልጋል። መንገዱ ለአገሪቱ በኢኮኖሚ ምን ያህል ጠቃሚ ነው? ለንግድና ለልማት ምን ያህል አስተዋፅኦ ያደርጋል? የሚሉት ጉዳዮች ይጠናሉ። ከዚያም ፕሮጀክቱ ለዓለም ባንክም ሆነ ለመንግሥት ቀርቦ የፋይናንስ ድጋፍ ይፈለጋል።
ስለዚህ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆነ ሰው ኢንጂነሪንግን ብቻ ማወቁ አይበቃውም። የኢኮኖሚ ጥናትን መረዳት፣ የፋይናንስ ሥርዓትን ማወቅ፣ በጀትን በትክክል ማቀድና የተገኘውን ገንዘብ በብቃት መጠቀም አለበት። አባሻውል እነዚህን የተለያዩ የሥራ ገጽታዎች በማስተባበር ሥራን በትክክል የሚመሩ ነበሩ።
ከእርሳቸው ጋር በቅርብ ለመሥራት ያገኘሁት ዕድል ደግሞ በአስተዳደርና በሥልጠና ኃላፊነት ላይ በነበርኩበት ወቅት ነበር። በዚያን ጊዜ እርሳቸው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ይመሩ ነበር፤ እኔም በየዕለቱ ከእርሳቸው ጋር በሥራ እገናኝ ነበር። በአጠቃላይ በአውራ ጎዳና የሠራሁት ጊዜ አሥራ አንድ ዓመት ነበር። በዚህ ረጅም የሥራ ጊዜ ውስጥ አባሻውልን በቅርበት ለማየትና የአመራር ችሎታቸውን ለመመልከት ችያለሁ።
በስብሰባ ወቅትም በጣም የተረጋጉና በራሳቸው ዕውቀት የተማመኑ ሰው ነበሩ። በወቅቱ ከኢትዮጵያውያን ጋር የሚሠሩ የውጭ አገር ኢንጂነሮችም ነበሩ። እርሳቸው ግን በቋንቋ ችሎታቸው፣ በኢንጂነሪንግ ዕውቀታቸውና በአመራር ችሎታቸው ከእነርሱ ጋር በእኩልነት ይሳተፉ ነበር። ስብሰባዎችንም በብቃት ይመሩ ነበር።
እርሳቸው በጣም የተረጋጉ፣ የተዝናኑና በዕውቀታቸው ከፍተኛ እምነት ያላቸው ሰው ነበሩ። በቀላሉ የሚቆጡ ወይም ቁጣቸውን በሌሎች ላይ የሚያሳዩ አልነበሩም። እንዲያውም በሙያቸው ያላቸው ብቃትና በሰው አመራር ላይ ያላቸው ጥበብ በሥራ ቦታ የተከበሩና የተወደዱ አመራር እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
በአመራር ረገድ የሚለያቸው ሌላው ባህሪ ሥልጣንን በአግባቡ መመደብና ሰዎችን በኃላፊነት ማሳተፍ ነበር። በሥራ ውስጥ ሰው ሁሉ የራሱ ድርሻ እንዳለው ያምኑ ነበር። ስለዚህ ሥልጣንን ብቻቸውን ከመያዝ ይልቅ ለተገቢው ሰው ኃላፊነት ይሰጡ ነበር። ይህም ሰዎች በራሳቸው ችሎታ እንዲሠሩና የድርጅቱ ሥራ በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲከናወን ያግዝ ነበር።
ከአውራ ጎዳና ከወጡ በኋላም እርሳቸው ከሙያቸው አልተለዩም። በኋላ በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አማካሪ ሆነው ሠርተዋል። በወቅቱ የኮንስትራክሽን ሚኒስትር ለነበሩት ካሳ ገብሬ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል። በአውራ ጎዳና የነበራቸው ሰፊ ልምድና የሙያ ብቃት በመንግሥት በኩል እንደገና እንዲፈለጉ አድርጓቸዋል።
እኔም በዚያን ወቅት በኮንሰልታንሲ ውስጥ እሠራ ስለነበር በአጋጣሚ እንደገና አገኘኋቸው። እኛ የምንሠራው ከአውራ ጎዳና ጋር ግንኙነት ከነበራቸው ተቋራጮችና ከፕሮጀክቶች ጋር ነበር። በዚያም ወቅት አባሻውልን እንደገና በሥራ ላይ ለማግኘት ችያለሁ። እርሳቸው ለአውራ ጎዳናም እንደ አማካሪ አገልግለዋል።”
አባሻውል በተሰጣቸው ምስክርነት መሰረት ለየት የሚያደርጋቸው ነገር የሙያ ዕውቀታቸውን ከሰው አመራር ጋር ማጣመራቸው ሲሆን ሥራን ለማስፈጸም ዕውቀት ብቻ እንደማይበቃ ያውቁ ነበር፤ ትክክለኛ ሰውን መምረጥ፣ ለሰው ኃላፊነት መስጠት፣ ሥራን ማደራጀትና በመጨረሻም በጥበብ መወሰን የአንድ ብቁ አመራር መሠረቶች መሆናቸውን በሥራቸው ማሳየት የቻሉ መሆናቸውን እንረዳለን።
#ህልፈትና ቀብር
እኒህ ታላቅ ባለውለታ መንገዶች ባለሥልጣን አሁን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ አሻራ ያኖሩ፣ የመንገዶች ባለውለታ ልክ የዛሬ 6 ዓመት ጷግሜ 4 2012 ዓ.ም በ91 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም ራሳቸው ቆመው ባሰሩት በእንጦጦ ኪዳነምህረት ነበር።
#ማጠቃለያ
ዕውቀት የማያረጅበት ሕይወት
የአቶ አባሻውል የሕይወት ታሪክ ከአንድ መሐንዲስ ወይም ከአንድ የቀድሞ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሥራ ጉዞ በላይ ነው። ይህ ከትምህርት ወደ ሙያ፣ ከሙያ ወደ አመራር፣ ከአመራር ወደ ዳግም አገልግሎት የተሸጋገረ የአንድ ባለሙያ ረጅም የሕይወት ታሪክ ነው።
በዚህ ጉዞ ውስጥ የተለያዩ ምዕራፎች አሉ። የአብራሪነት ሕልም አለ፤ የትምህርት ጥረት አለ፤ የአሜሪካ ጉዞ አለ፤ የመሐንዲስነት ሥራ አለ፤ የአመራር ኃላፊነት አለ፤ ከዓመታት በኋላም ዳግም ወደ ተቋሙ ተመልሶ ማገልገል አለ።
እነዚህ ሁሉ ግን በአንድ የሕይወት መርህ የተሳሰሩ ይመስላሉ፤ ሙያን እንደ ሥራ ብቻ ሳይሆን እንደ አገልግሎት መመልከት።
ከዋና ሥራ አስኪያጅነት ዘመናቸው ከረዥም ጊዜ በኋላም በጥናትና በሙያዊ ሥራዎች ውስጥ መሳተፋቸው ይህንን ያሳያል። ዕውቀት በዕድሜ አይገደብም፤ ልምድም በሥራ መደብ አይወሰንም። ባለሙያ ለሀገርና ለተቋም ሊያበረክተው የሚችለው ዋጋ የሥራ ዘመኑ ካበቃ በኋላም ይቀጥላል።
ምናልባትም የአቶ አባሻውል ታሪክ የሚያስተምረን ትልቁ ነገር ይህ ይሆናል፤ የሰው የሥራ ዘመን ሊያበቃ ይችላል፤ የሙያ ዕውቀትና ለማገልገል ያለው ፍላጎት ግን ሞት እስካልገደበው ድረስ መቼም አያበቃም!!