የወይዘሮ ቅድስት ጳውሎስ አጭር የህይወት ታሪክ
- የሕይወት ታሪክ ዝግጅት ፦ ዕዝራ እጅጉ
ክብርት ወይዘሮ ቅድስት ጳውሎስ ተድላ ሚያዝያ 9 ቀን 1944 ዓም በደሴ ከተማ ከአባታቸው ከፊታውራሪ ጳውሎስ ተድላ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ታእከማሪያም ስንቄ
ተወለዱ::ወሮ ቅድስት አብዛኛውን የልጅነት ጊዜያቸውን በአዲስ አበባ ከተማ በወላጅ አባታቸው በልዩ እንክብካቤ ያደጉና በአብሮ አደጎቻቸውም ዘንድ እጅግ የተከበሩና የተወደዱ ልጅ ነበሩ::
ወይዘሮ ቅድስት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አሜሪካን ሚሽን ተብሎ በሚጠራው ት/ቤት ቀጥሎም በካቴድራል ልደታ ማርያም ትምህርት ቤት ተከታትለዋል:: እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቅድስት ማርያም ወይም St Mary’s secondary school አጠናቀዋል። ከዚያም በመቀጠል
በአዲስ አበባ ንግድ ስራ ኮሌጅ በመግባት ከፍተኛ ትምህርት ጊዜያቸውን በብቃት አጠናቀው በ1965 ዓም ተመርቀዋል:: ከዚያም የስራ ዘመናቸውን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የበጀትና የፋይናንስ አናሊስት ባለሙያ ሆነው በመቀጠር ሙያዊ አበርክቶታቸውን ሰጥተዋል:: በዚሁምመስሪያ ቤት ለ25 አመታት በትጋትና በታማኝነት አገልግለዋል::
ወ/ሮ ቅድስት ጵውሎስ በዚህ ሁሉ የህይወት መንገዳቸው በወጥነት በመልካም ባህርያቸው በተግባቢነትና እና በማህበራዊ ክህሎታቸውው እጅግ የተመሰከረላቸው ሴት ነበሩ::
ወይዘሮ ቅድስት ጳውሎስ ከትምህርት ቤት አንስቶ ከተዋወቁት የፍቅር አጋራቸው ከአቶ ጥላሁን በሻህ ጋር በ1963 ዓም በጋብቻ ተጣምረው ባሳለፉት የፍቅርና የትዳር ህይወታቸው የ5 ልጆች እናትና የ15 የልጅ ልጆች አያት ለመሆን በቅተዋል::
ወ/ሮ ቅድስት ጳውሎስ በቤተሰባዊ ፍቅራቸው እጅግ የሚታወቁና የተመሰከረላቸው እንዲሁም ለአቋማቸው ሁልጊዜም ፅኑ የሆኑ ሴት ነበሩ:: በእግዚአብሔር ብዙ ቸርነትና በተሰጣቸው ልዮ የእናትነት ፀጋ ልጆቻቸውን በላቀ ስነ ምግባር አሳድገው ለታላቅ ቁምነገርና ለብዙ ፍሬ አብቅተዋል:: በዚህም በመልካም ስነ ምግባር ልጆችን የማሳደግ ተምሳሌትነታቸው በብዙ እናቶች መካከል እንደ አርአያ እንዲታዮ አድርጉዋአቸዋል::
ወይዘሮ ቅድስት ጳውሎስ በእርግጥም Selfless በሆነ የመስዋዕትነት ህይወት ቤተሰባችውን እየተንከባከቡ የፍቅር ሰውነታቸውን በተግባር ያስመሰከሩ ታላቅ ሴት ነበሩ:: ከወጣትነት ዕድሜ ጅምሮ የራሳቸውን ምቾትና ድሎት ወደ ጎን አድርገው ለልጆቻቸውና እና ለትዳራቸው ተሰጥተው የኖሩ ድንቅ እናት ነበሩ::
ዛሬ በህይወት የሌሉት ባለቤታቸው አቶ ጥላሁን በሻህንም ሕይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ ለትዳር አጋር የሚገባውን ግሩም እንክብካቤ በመስጠት የባለቤትነት ተግባራቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል::
እንዲሁም በመኖሪያ አካባቢያቸውም ሆነ በሥራ ቦታቸው የተቸገረን ለመርዳት ወይዘሮ ቅድስትን የሚቀማቸው አልነበረም።
ወ/ሮ ቅድስት ባላቸው መልካም ማህበራዊ ግንኙነት ብዙ መልካም ወዳጆች ያፈሩና እንዲሁም ትንሽ ትልቅ ሳይሉ ሁሉንም በማቅረብ አለኝታነታቸውን ያሳዮ ነበር::
ይህም ፈሪሀ እግዚአብሔር ያደረባቸው ደግ ርህሩህና መንፈሳዊ ሴት መሆኗቸውን በተግባር የገለፀ የስብዕናቸው ማሳያ ነበር።
ወይዘሮ ቅድስት ጳውሎስ አብረዋቸው በኖሩ የቅርብ ዘመዶቻቸውና ጉዋደኞቻቸው በብዙ መልክ ይገለፁ ነበር:: ከነዚህም የፍቅር ስሞች መካከል አባይ ቅድስት፣ ቅድስትዬ ሆዴ፣ ኪዲ፣ ኪዲዬ ተብለው እጅግ ባማረ የመወደድና እና የክብር ስም ይጠሩ ነበር ። ከሁሉ ሚገርመው የልጆቻቸው ጉዋደኞች ሳይቀር የሚጠሩአቸው ኪዲዬ በሚል የቁልምጫ ስም እንደነበር በፅኑ የሚታወስ ነው::
ወ/ሮ ቅድስትን ወዳጅ ዘመድና ጉዋደኞቻቸው በታማኝነታቸውና በሰው አክባሪነታቸው ሁልጊዜ ያስታውሱአቸዋል::
የራሳችውንም ሆነ የሌላውን ሰው ክብር ጠባቂ ከመሆን ብሻገር ሰውን በማንነቱ ብቻ የሚወዱ ግሩም ሴት ነበሩ:: ወሮ ቅድስት ለንፁህ ወዳጅነት ራሳቸውን የሰጡ የብዙዎች እህትና ወዳጅ በቤተሰባችውም ዘንድ ተናፋቂ እመቤት ሆነው ይታወሳሱ::
ወ/ሮ ቅድስት ዛሬ በስጋ ቢለዮንም በብዙ መልካም ስራቸውና ትዝታቸው በልጅቻቸውና በዘመዶቻቸው እንዲሁም በወዳጆቻቸው ልቦና ውስጥ ሁልጊዜ ሲታሰቡ ይኖራሉ::
ወ/ሮ ቅድስት ባደረባቸው ህመም ምክንያት በቤተሰባቸው ከፍተኛ እንክብካቤ ሲደረግላቸውና እንዲሁም አስፈላጊው የህክምና እርዳታ ሲታገዙ ኖረው በመጨረሻም ግንቦት 15 ቀን 2018 ዓም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል::
“ሰው በልቡ አምኖ ይፀድቃል በአፉም መስክሮ ይድናል” ተብሎ እንደተፃፈው የእግዚአብሔር ቃል በማያጠራጥር መልኩ በታመኑ ምስክሮች ፊት ጌታቸውን መስክረው ልባዊ የሆነ እምነታቸውን አፅንተው በመጨረሻው ሰዓት ወደ ጌታቸው ተሰብስበዋል::
ወይዘሮ ቅድስት ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓም ልጆቻቸው የቅርብ ወዳጆቻቸውና ዘመዶቻቸው በተገኙበት ስርዓተ ቀብራቸው በአሜሪካ ሜሪላንድ ተፈፅሟል።
ስለሁሉም የዘመን ባለቤት የሆነውን ታማኙን ጌታ ታላቁን ልዑል እግዚአብሔርን እጅግ አድርገን እናመሰግናለን:: ስለ ሁሉ ለእግዚአብሔር ለአምላካችን ክብርና ምስጋና ይሁንለት!!