ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣ መዝገበ-አእምሮ ( የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች ፣በመፅሀፍ፣በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል።በተለይ ጉግል ላይ ታሪካቸው ሲፈለግ የማይገኝ ሰዎች አሁን የሙያ አበርክቷቸው በቀላሉ ኢንተርኔት ላይ በግልፅ ተቀምጦ ይገኛልደ ባለፉት 4 ዓመት ከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መፅሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።
ከእነዚህ ውስጥ የሚድያ ሰዎችም፣ የቴአትር ባለሙያዎች ይገኙበታል። አጠቃላይ 74 ከፍተኛ የሚድያ አመራሮች፣ሚኒስትሮች ፣ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የግል ሚድያ መሥራቾች፣ዋና አዘጋጆች እና መካከለኛ አመራሮች ተካተዋል። 35 ያህሉ በዋና ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ያሉ ሲሆን የሁሉም ታሪክ በተሟላ ደረጃ ለመሰነድ ተችሏል። የእነዚህን አመራሮች እና የሚድያ ሰዎች ታሪክ ሰንዶ ለአንባቢ ተደራሽ ማድረግ ፈታኝ ቢሆንም አሳክተነዋል። በዚህ ተግባራችንም ተጠናክረን እንቀጥላለን።
በዚህ ፅሑፍ የሙያ ታሪኩ የሚሰነድለት ባለሙያ መልካሙ ዘርይሁን ይባላል። መልካሙ የንጉሥ አርማህ እና የህንደኬ ደራሲ ሲሆን በቀጣዩ እሁድ ደግሞ የወህኑ አምባን ያስመርቃል። መልካሙ ማነው የሚለውን ለማወቅ ታሪኩን ዕዝራ እጅጉ እና አይናለም ሀድራ እንደሚከተለው ሰንደውታል።
ታሪክ ወዳድ ነው፡፡ ከታሪክም የእናት ሃገሩን የኢትዮጲያን ታሪክ ማወቅም ሆነ መከተብ ይስበዋል ፡፡
ገናና የነበረችው የጥንታዊት ኢትዮጵያ ታሪክ እና ሥልጣኔ፤ ከፋርስ፣ ከባዛንታይን፣ ከኦቶማን ቱርክ ጋር በንግድ የተሳሰረች፤ በጦር ሠራዊትም እጅግ ገናና የነበረችውን የሃገሩን ታሪክ ትውልድ እንዲያውቅለት ይናፍቃል ።
በቀይ ባሕር፣ በዘይላ፣ በአዱሊስ፣ በሕንድ ውቅያኖስ እስከ የመን ዳርቻ ድረስ የንግድ መስመሮች የነበሯት የገናናይቱ የኢትዮጵያ ታሪክ የጥበብ ስራዎቹ መነሻ ናቸው – ጋዜጠኛና ደራሲ መልካሙ ዘርይሁን ኣሥራት፡፡
የንጉሥ አርማህ እና የህንደኬ ታሪካዊ ተውኔቶች ፀሐፊ ነው፡፡ በአዲስ አበባ፣ በአውሮፓ እና በአሜሪካ የተለያዩ ከተሞች የታየ “የእኛ እድር” የተባለ ሳታየር ኮሜዲ ተውኔትም ለዕይታ አብቅቷል። ከዲያቢሎስ ጋር ድርድር የተሰኘ ረዥም ታሪካዊ ልብ ወለድም ጽፏል።
ፀሐፈ ተውኔት መልካሙ በታሪካዊ ተውኔቶቹ ኢትዮጵያ ከአረቡ ዓለም ጋር የነበራትን ግንኙነት ይመለከታል፡፡ ወደ አውሮፓ ተሻግሮ ሀገሩን ከታላቁ እስክንድር ጋር ያስተሳስራል። “ከዲያቢሎስ ጋር ድርድር” በተሰኘው ረዥም ታሪካዊ ልብ ወለዱም ኢትዮጵያን ከግብፅ ጋር ያስተያያል።
መልካሙ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ እና በሀገሪቱ የነበሩ ቀደምት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሽግግሮችን ማጥናት ላይ ያተኩራል ፡፡ ስራዎቹም የዚሁ የጥናቱ ውጤቶች ናቸው፡፡
ታሪካዊ ምርምሮችን፣ የፈጠራ ሥራዎችን፣ ዘጋቢ ፊልሞችን (ዶክመንታሪዎችን) እና የመድረክ ተውኔቶችን በማዘጋጀት የረጅም ጊዜ ልምድ አለው። ታሪካዊ የምርምር ውጤቶችን በልብ-ወለድ፣ በተውኔት፣ በሬዲዮ ፕሮግራም እና ዘጋቢ ፊልሞች መልክ በማቅረብ ጥንታዊ የኢትዮጲያን መልክ ለህዝብ በማድረስ ይታወቃል፡፡
በተለያዩ የአካዳሚክ ውይይቶች፣ የምርምር ልውውጦች እና ኮንፈረንሶች ላይ በመሳተፍም የኢትዮጵያን የታሪክ እውቀት ለማሳደግ በትጋት ይሰራል፡፡
ትውልድና ትምህርት
ይህ የታሪክና የጥበብ ሰው ትውልዱ በአዲስ አበባ በ የካቲት 27 1964 ዓ.ም ነው፡፡ ለአባቱ አቶ ዘርይሁን ኣስራት እና ለእናቱ ወ/ሮ ጥሩወርቅ ሙላት የመጀመሪያ ልጅ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በጆኔፍ ኬኔዲ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህር ቤት፤ 2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በዳግማዊ ሚኒሊክ 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል፡፡
ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ በትምህርት ቤቱ ጠንካራ እንቅስቃሴ የነበረው የቴአትር ክለብ ነበርና መልካሙ ከእነ ተስፋዬ ገብረሃና፣ ሐረገወይን አሰፋና ሌሎችም አርቲስቶች ጋር ተሳትፎ ያደርግ ነበር፡፡ በኋላ ሌሎቹ ጓደኞቹ ወደ ትወናው ሲያደሉ እርሱ ግን ወደ ጽሁፉ ገባ፡፡
የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ መጀመሪያ በማስ ሚዲያ የጋዜጠኝነት ማሰልጠኛ ተቋም በዲፕሎማ ቀጥሎም ከአ.አ.ዩ በጋዜጠኝነትና ኮምዩኒኬሽን በዲግሪ ተመርቋል፡፡
አቶ ዘርይሁን ኣስራት(አባት)
በዛሬ ማንነቱ ላይ አባቱ ትልቅ አሻራ እንዳላቸው ይናገራል መልካሙ፡፡ አቶ ዘርይሁን መልካሙ ልጅ እያለ በባህልና ስፖርት መ/ቤት ይሠሩ ስለነበር በርካታ ቴአትሮችን የመመልከት ዕድል ነበረው፡፡ አዳዲስ የሚወጡ ቴአትሮችን ከአባቱ ጋር በመሆን ብሄራዊ ቴአትር፣ ራስ ቴአትርና ሃገር ፍቅር እየገባ ያይ ነበር፡፡ ይሄ ልምዱ ወደ ቴአትሩ እንዳቀረበው ያነሳል፡፡
ከስራቸው ባህሪ የተነሳ ከቦታ ቦታ ይዘዋወሩ በነበረበት ጊዜም መልካሙ አብሯቸው በመሄድ የሃገሩን ታሪክና ባህል መመልከት ችሏል፡፡ በተለይም አባቱ አቶ ዘርይሁን በአክሱም ባህልና ቅርስ መ/ቤት ይሰሩ በነበረበት በአንድ ወቅት አክሱም አካባቢ የቅርስ ጥናት ይደረግ ነበር፤ አባቱ አጥኚ ቡድኑን ይመሩ ነበርና አብሮ ሄዶ እያንዳዷን ሂደት ይከታተል ነበር፡፡ የታሪክና የምርምር ፍቅር የወደቀበትም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሚያየው፣ በሚሰማውና በሚያነበው ነገር ነው፡፡
አቶ ዘርይሁን በወመዝክር ውስጥ የቤተ መፅሐፍት ባለሙያ ሆነው ያገለግሉ ነበርና ቤተሰቡ ለመጽሃፍትና ለንባብ እጅግ ቅርብ ሆኖ ነው የኖረው፡፡ አቶ ዘርይሁን የዛሬ 50 አመት ገደማ “The Inferno” የተሰኘውን መጽሃፍም ተርጉመው ለአንባቢያን አቅርበዋል።
ታዲያ በዚህ መልኩ ቀርጸው በበጎ ተጽዕኖ ላሳደጉት አባቱ እርሱም መጽሃፍ (ከዲያቢሎስ ጋር ድርድር) ጽፎ መታሰቢያነቱን ለእሳቸው አድርጓል፡፡
ታሪካዊ ሥራዎች እና የፈጠራ ውጤቶች
ታሪካዊ ልብ-ወለድ
ከዲያብሎስ ጋር ድርድር በ2013 ዓ.ም የታተመ።
ከዲያቢሎስ ጋር ድርድር አባይ ወንዝ ላይ ያተኩራል፡፡ አባይ ከተራ ወንዝነት ባለፈ
ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ስነጥበብ እንደሆነ ይተርካል፡፡ መጽሃፉ በአማዞን፣ መርከብ
መጻሕፍት፣ ኃሁ እና ጃፋር መጻሕፍት መደብሮች ይገኛል።
የመድረክ ተውኔቶች (Stage Plays)
ንጉሥ አርማህ (1991 ዓ.ም) በብሔራዊ ቴአትር ከ3 ዓመታት በላይ ለእይታ የበቃ
ታሪካዊ ተውኔት። ይህ ተውኔት ከ24 ዓመታት በኋላ በሐምሌ 2017
ዓ.ም በድጋሚ ለመድረክ በቅቷል)።
ሕንደኬ (2002 ዓ.ም) በብሔራዊ ቴአትር መድረክ የቀረበ ታሪካዊ ተውኔት።
የኛ ዕድር (2002 ዓ.ም ) የዕድርን ታሪክና ማኅበራዊ ፋይዳ በፈገግታ የሚመረምር
አስቂኝና አሽሙራዊ (ሳታይር) ተውኔት።
ዘጋቢ ፊልም (Documentary)
የመርካቶ ታሪክ (2000 ዓ.ም) ስለ አፍሪካ ታላቁ ገበያ መርካቶ የተሠራ ባለ 40
ደቂቃ ዘጋቢ ፊልም።
የፊልም ሥራ (2001 ዓ.ም)
የሕይወት ቅመም— ስክሪፕት ጸሐፊ እና ረዳት ዳይሬክተር
መልካሙ በተለያዩ መጽሔቶችና የድረ-ገጽ መድረኮች ላይ የታተሙ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸው ጽሑፎችንም አበርክቷል።
መልካሙ አሁንም ብዕሩ የኢትዮጵያን ታሪክ ለመንገር አይሰንፍም።
መጪው እሁድ ግንቦት16 ቀን፣ 2018 ዓ.ም. “ወህኒ አምባ” የሚል ሌላ ታሪካዊ ቴአትር በወጣቶችና ህጻናት ቴአትር ለዕይታ ያበቃል።
በመካከለኛ ኢትዮጵያ ዘመን የልዑላውያን ወህኒ ቤት በመባል ይታወቅ የነበረው ወህኒ አምባ፣ ለዘውድ ፉክክር የሚደረገውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቀረት፣ ባይቻል እንኳ ለመቀነስ ተብሎ ንጉሣውያን ቤተሰቦች ወይም ልዑላዊያንን በዚህ ወህኒ አምባ እንዲቆዩ ይደረግ ነበር።
ልዑላውያኑ ወገን ለይተው ለሥልጣን እንዳይሻኮቱ በወህኒ አምባ ማቆየት የኢትዮጵያ አንዱ ልዩ ታሪክ ነበር ይላል መልካሙ። በቦታው አካላዊ፣ ሃይማኖታዊና ሌላውንም ትምህርት ቀስመው ተራቸው ሲደርስ ከዚያ ተመርጠው እንዲነግሱ ይደረግ እንደነበረም መልካሙ ታሪክን ጠቅሶ ያነሳል፡፡
መልካሙ ይህንን ልዩ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያወሳ “ወህኒ አምባ“ የተሰኘ ቴአትር ለተመልካች አቅርቧል፡፡ እሁድ ከቀኑ 8 ሰዓት ፍላሚንጎ አጠገብ በሚገኘው ወጣቶችና ህጻናት ቴአትር መታየት ይጀምራል፡፡
ከተውኔት ዝግጅትና የታሪክ ምርምር ስራዎቹ ባሻገር መልካሙ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ሆኖ በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ሰርቷል፡፡ በናሁ ቲቪ የፈጠራ ጥበብ ዳይሬክተር እና የምርምር መሪም ነበር፡፡ በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልና በሬዲዮ ፋናም በሙያው አገልግሏል፡፡
የቤተሰብ ሁኔታ
መልካሙ ባለትዳና የልጆች አባት ነው፡፡ ለስራዎቹ ስኬት የባለቤቱ ወ/ሮ ትዕግስት ሚና ከፍ ያለ እንደሆነ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከመናገር አይቆጠብም፡፡ ህንደኬ ቴአትር ለእይታ የበቃ ሰሞን በመወለዷ ሴት ልጁን ህንደኬ ሲልም ሰይሟታል፡፡ አንዳንድ ወዳጆቹና የስራው አድናቂዎችም ለሴት ልጆቻቸው ህንደኬ ለወንድ ልጆቻቸው ደግሞ አርማህ የሚል ስም አውጥተዋል፡፡ ከዲያቢሎስ ጋር ድርድር መጽሃፍ ውስጥ አንድ ገጸ ባህርይ የሚወክለውን የንጉስ ፒያንኪን ስምም ለልጆቻቸው የተዋሱ አሉ፡፡