ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ እሸቱ

ተወዳጅታሪክ ተወዳጅ ይታወቃል።ና ኮምዩኒኬሽን፣ መዝገበ-አእምሮ (የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል።

ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች፣ በመጽሐፍ፣ በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት 4 ዓመታት ከ5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መጽሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።

መዝገበ አእምሮ ቅጽ ሁለት ላይ ታሪካቸው ከተሠራላቸው የቴአትር ባለሙያዎች መካከል ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ እሸቱ ይገኝበታል ። የሥራ እና የሕይወት ታሪኩን ዕዝራ እጅጉ እንደሚከተለው በስፋት ሰንዶታል።

መንደርደሪያ

አንድን ጉዳይ ከያዘ ካሳበበት ከዳር ሳያደርስ ምንም ምክንያትም ይሁን ኃይል አያቆመውም፡፡ ነገርን ጀምሮ መተው እና አይሆንልኝም በቃኝ ብሎ ተስፋ መቁረጥን በፍፁም አያውቅም፡፡ ትወናን አጥብቆ ይወዳል፡፡ ለተማሪዎቹ አዲስ ነገር ለማሳወቅ ዘወትር የሚጥር ጎበዝ መምህርም ነው፡፡ የራሱን ዕይታ መፍጠር የሚችል ድንቅ መራሄ ተውኔትም ነው፡፡ ተስፋዬ እሸቱ፡፡ ገና ከልጅነት ዕድሜው፣ ከጨቅላነቱ አንስቶ ለመድረክ፣ (ክዋኔ) ለጥበብ፣ እንደተፈጠረ ውስጡ የነገረው (የተገነዘበ) እና የጥበብ ሰው ለመሆንም አጥብቆ ሲሰራ፣ ሲለፋ እና ሲጥር የኖረ ሰውም ነው፡፡ ይህም ልፋቱ፣ ጥረቱ እና ትጋቱ ቀደም ብሎ ሊሳካ ይችል እንደነበርም ይናገራል፡፡

በአደገበት አካባቢ ተለምዶዓዊ አጠራር ጓያ ብለው የሚጠሩት ትምህርት ቤት ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያለም ይሁን ኋላ መርዓዊ ሁለተኛ ደረጃ ገብቶ ሲማር ማትሪክ በጥሩ ውጤት አልፎ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ቴአትር እንደሚማር እና ተዋናይ እንደሚሆን ውስጡ ይሰማው እንደነበር እና ይህንንም በእርግጠኝነት ይናገር እንደነበር ያወሳል፡፡ ነገር ግን ይህ እርግጠኝነትም ይሁን ተዋናይ የመሆን ህልሙ ባሳበበት ግዜ አልተሳካም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በ1993 ዓ.ም በህይወቴ እጅግ ካስደነገጡኝ እና አሳዛኝ ከነበሩ ክስተቶች ሁሉ የማይረሳው ብሎ ከሚጠቅሳቸው ገጠመኞች አንደኛው በመከሰቱ ነበር፡፡ ይኸውም ከላይ በተጠቀሰው 1993 ዓ.ም የወሰደው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤቱ 2.8 በመምጣቱ ምክንያት ወደ ዩኒቨርሲቲ የመግቢያ ውጤት ሊያመጣ ባለመቻሉ ነበር፡፡ ይህ አጋጣሚ ለእርሱ፣ ተስፋዬን እጅግ ታታሪ እና የደረጃ ተማሪ እንደነበር ለሚያውቁ የአካባቢው ነዋሪ ሁሉ፣ ለቤተሰቡ፣ አብረውት ለተማሩት ጓደኞቹ እና በተለይም ለወላጅ አባቱ መምህር እሸቱ ሀብቱ እጅግ አስደንጋጭ እና ቅስም ሰባሪ ነበር፡፡

ተስፋዬም ይህንን ወቅት ሲያስታውስ “መላው ቤተሰቡ ‹‹ሾክ ሆነ!›› ቤተሰባችን ከፍተኛ ድንጋጤ እና ሀዘን ተጭኖት ያየሁበት የመጀመሪያው አጋጣሚ ነበር፡፡ በተለይ አባቴን በዛ ልክ አዝኖ እና ተክዞ፤ በዛ ልክ ተሰብሮ አይቼው አላውቅም፡፡” ይላል፡፡ ነገር ግን ይህ ክስተት ከህልሙ ሊመልሰው አልቻለም፡፡ ካሳበው ቢዘገይም ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ቴአትር መማሩም ይሁን ተዋናይ መሆኑ አልቀረም፡፡

ውልደትእናእድገት

ተስፋዬ የሁለተኛ ደረጃ መምህር ከነበሩት አባቱ ከአቶ እሸቱ ሀብቱ እና ከእናቱ ከወይዘሮ ሙሉቀን አሳየ ሀምሌ 2 1978 ዓ.ም ምዕራብ ጎጃም በምትገኘው ዱር ቤቴ ከተማ ነው የተወለደው፡፡ ነገር ግን አንድ ዓመት እንኳ ሳይሞላው አባቱ በስራ ምክንያት ከባህዳር ከተማ 35 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደምትገኘው መርዓዊ ከተማ በመዘዋወራቸው ኑሮው እና ዕድገቱ በመርዓዊ ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ በመርዓዊ “ሽንብራ ትምህርት ቤት” የተማረ ሲሆን፤ ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍልን ደግሞ በ”መርዓዊ ጁኒየር ትምህርት ቤት” (በአካባቢው የተማሪዎች ዘልማድ “ጓያ” ትምህርት ቤት እያሉ ይጠሩታል፡፡) የተማረ ሲሆን ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍልን ደግሞ በ”መርዓዊ መሰናድዖ ትምህርት ቤት” በአሁኑ አጠራር “ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ ፈንቴ ትምህርት ቤት” ተከታትሏል፡፡
“ሽምብራ” እና “ጓያ” ትምህርት ቤቶች
ተስፋዬ እሸቱ ሽምብራ ትምህርት ቤት ገና የአራተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ነው በወላጆች ቀን ለተማሪዎች መዝሙር በማቅረብ የክዋኔ ህይወቱ የጀመረው፡፡ በዚህም አቅርቦቱ በመደመም የምስጋና እና የአድናቆት ደብዳቤ ከትምህርት ቤቱ ተበርክቶለታል፡፡ እዛው ሽምብራ ትምህርት ቤት እያለ ወደ ስድስተኛ ክፍል ሲደርስ ቅልጥፍናውን እና ዕንቅስቃሴውን በመቀጠል በዕረፍት ቀናቸው እና በዕረፍት ሰዓታቸው ላይ በመኖሪያ ግቢያቸው ውስጥ የሰፈሩን ልጆች አስተባብሮ ድራማ ያዘጋጅ እና ያቀርብ ነበር፡፡ ታዲያ እነዛን ክዋኔዎች ለመመልከት ተመልካች ሳይከፍል አይገባም ነበር፡፡ ክፍያውም ቆርኪ ነበር፡፡ ቆርኪ እያስከፈለ ያሳይ የነበረውን ክዋኔ በመቀጠል፤ ዓይነቱን ደግሞ በመቀየር የበዙትን የሰፈሩን ልጆች የሚያሳትፍ እና በርካታ ተመልካች ያለው ውድድርም ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ ውድድሩም የሰፈር ኦሎምፒክ ነበር፡፡ ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡ ተወዳዳሪዎችም እንደየደረጃቸው ስባሪ ሸክላዎች ላይ ጭቃ እና የሲጋራ ልጣጭ ወረቀት በማጣበቅ የተሰሩ ሜዳሊያዎችን ይሸለሙ ነበር፡፡ እነዚህ ውድድሮች ከሰፈሩ ነዋሪዎች “ማድጋችን ተሰበረ”፣ “እንስራዎቻችን አለቁ” የሚሉ በርካታ ስሞታዎችን አስከትለውም ነበር፡፡ ስሞታዎቹ ቢደጋገምም ወላጆቹ ግን ከተግሳፅ ያለፈ ጫና ግን አያሳድሩበትም ነበር፡፡
ተስፋዬ እሸቱ ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍልን ወደተማረበት ወደ መርዓዊ ጁኒየር ትምህርት ቤት በእነሱ አጠራር ወደ ጓያ ትምህርት ቤት ከተዛወረ በኋላ በጣም ውጤታማ ዕንቅስቃሴዎችን ያደርግ ነበር፡፡ ለኋለኛው የክዋኔ ህይወቱም እጅጉን ጠንካራ መሰረት ነበር ለማለትም ያስችላል፡፡

በጓያ ትምህርት ቤት የእግር ኳስ ውድድር ሲካሄድ በኮሜንታተርነት እግር ኳሱን በቀጥታ ካቀረበ በኋላ በነጋታው ደግሞ ይህንን ውድድር ላልተመለከቱ ሰዎች እንደገና በዘጋቢነት ውድድሩ ምን ይመስል እንደነበር ድራማዊ በሆነ መንገድ ያቀርብ ነበር፡፡ በዚህ ወቅትም ነበር ለመጀመሪያ ግዜ በትምህርት ቤታቸው የድራማ እና የስነ-ፅሁፍ ክበብ መስርተው መስራት የጀመሩት፡፡ ያን ግዜ ነው ታዲያ ሲ.ቢ.ኤም የተባለ የዕርዳታ ድርጅት ወደ ትምህርት ቤታቸው መጥቶ ፀረ-ኤች አይ ቪ ኤድስ ፕሮግራም ያዘጋጀው፡፡ በዚሁ ፕሮግራም ላይም አንድ መምህራቸው ተላላፊ በሽታዎችን ገፀ-ባህሪ አድርገው ቴአትር ፅፈው መሪውን ገፀ-ባህሪ ተስፋዬ እንዲጫወተው አድርገው በመምህራን እና በተመልካች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን አስገኝቶለታል፡፡ በዚሁ ወቅት ነው ታዲያ በህይወቱ የተሸለመው የመጀመሪያው ትልቁ ሽልማት የተከሰተው፡፡ ይኸውም አንዲት ሴት መምህሩ በዛን ወቅት ታዋቂ የነበረውን የድምፃዊ አበበ ተካን “ሰው ጥሩ” የተሰኘ ዘፈን በርካታ ተመልካች በተገኘበት መድረክ ላይ እንዲጫወት ያደርጉት እና እዛው በቴፕ ሪከርደር ይቀዱታል፡፡ በክዋኔው በጣም የተደነቁት የዕርዳታ ድርጅቱ ሰዎችም ስድስት ብር ይሸልሙታል፡፡ ይህም የህይወቱ የመጀመሪያው ትልቁ ሽልማት ሆኖ አልፏል፡፡ ይህንን ወቅት ተስፋዬ እንዲህ ያስታውሰዋል ፦

“ከዛን ቀደም ብሎም ሽምብራ ትምህርት ቤት መዝሙር ስናቀርብ አሁን በትክክል ባላስታውሰውም ሳንሸለም ግን አልቀረንም፡፡ ይሄኛው ግን ይለያል፡፡ ፐርፎርማንሱን ራሱ አስታውሰዋለሁ፡፡ ድምፅ ማጉያው ከአቅሜ በላይ ሆኖ እየተንዳገድኩኝ ሁሉ ነው ያቀረብኩት ግን አስገራሚ ነበር፡፡ ስድሰት ብር ተሸለምኩኝ፤ የመጀመሪያ ልጅ ስለሆንኩኝ ለወንድሞቼ ሸሚዝ እና ቁምጣ ገዛሁላቸው፤ ያኔ ኦፔራ የሚባል ቁምጣ ነበር እሱን ገዛሁላቸው፡፡”

በስድስት ብር የተጀመረው የሽልማት ጉዞው አላበቃም ሁለተኛ ደረጃ ሲገባም በስራዎቹ ኮከብ ተብሎ ተሸላሚ ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡

መርዓዊ፣ “መረዋ” እና ተስፋዬ እሸቱ
ሌላኛው የተስፋዬ እሸቱ ትውስታ ላይ ወርቃማ ሆኖ የተቀመጠው ዘመን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የነበረበት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ግዜ ከቀድሞው በተጠናከረ ሁኔታ በርካታ ኪነ-ጥበባዊ ክዋኔዎች ለመድረክ አብቅቷል፡፡ በትምህርት ቤቱ በዕረፍት ሰዓት እና ተማሪዎች በሚለቀቁበት ሰዓት ለተማሪዎቹ የተለያዩ ትረካዎችን ያቀርብ ነበር፡፡ ሚኒ ሚዲያ ፕሮግራሞችን እያዘጋጀ ያቀርብም ነበር፡፡ ኋላ ላይም “መረዋ” የኪነ-ጥበብ ቡድን ሲመሰረትም በመሪነት አገልግሏል፡፡ ለመጀሪያ ግዜ ቴአትር ይዞ ከመርዓዊ ከተማ ርቆ የተጓዘውም በዚህ ወቅት ነበር፡፡ ወቅቱ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ነበር፡፡ ከመምህራኖቻቸው አንደኛው ይህንኑ የተመለከተ ቴአትር ፅፈው በተባበሩት መንግስታት ፍርድ ሸንጎ ስለ ኢትዮጵያ የሚከራከረውን ጀግናውን ኢትዮጵያዊ ወጣት ወክሎ እንዲጫወት ተስፋዬን ይመድቡታል፡፡ እርሱም ጥሩ አድርጎ ይጫወተዋል፡፡ ቴአትሩንም ይዘው ወደ ትውልድ ከተማው አቸፈር ዱር ቤቴ ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ ተስፋዬ ይህንንም አጋጣሚ በትዝታ እንዲህ ያስታውሰዋል፡፡

“ያ አጋጣሚ የሚደንቅ ነው፡፡ ጉዞ ወደ አቸፈር ጀመርን፡፡ ያ ለእኔ ለመጀመሪያ ግዜ በመንግስት መኪና የተሳፈርኩበት አጋጣሚ ነበር፤ እሱም ብቻ አይደለም ለመጀመሪያ ግዜ የሆቴል ምግብ የቀመስኩትም ያኔ ነው፡፡ አቸፈር ደርሰን ቴአትሩን አሳይተን ስንጨርስ ደግሞ ሚሪንዳ ተከፈተልን፤ ይሄም ለእኔ የመጀመሪያ ነው፤ ለመጀመሪያ ግዜ ሚሪንዳ የጠጣሁባት አጋጣሚ ያቺ ናት፡፡ አሁንም ድረስ ትዝ ትለኛለች፡፡”

የመርዓዊ እና የተስፋዬ እሸቱ የቴአትር ጣፋጭ ትዝታ በዚህ ብቻ አይገታም፡፡ የወቅቱ ባህልና ቱሪዝም መስሪያ ቤት በዛን ግዜ የነበሩትን የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ የቴአትር ባለሙያዎች ድጋፍ ሰጪ በማድረግ ከዋና ዋና ከተማዎች ወጣ ባሉት አነስተኛ ከተሞች ላይ የኪነ-ጥበብ ማዕከላትን ያቋቁሙ ነበረ፡፡ በመርዓዊ ከተማም የኪነ-ጥበብ ቡድን ማቋቋም ፈልገው ተስፋዬን ያማክሩታል፡፡ እርሱም በደስተኛነት በወቅቱ ከነበሩት እኩዮቹ ጋር በመሆን “መረዋ” የተሰኘውን ክበብ በመመስረት ከተማውን ለቆ እስከወጣበት ግዜ ድረስ በኃላፊነት ሲመራ ቆይቷል፡፡ ሲመሰረት አንድ ከበሮ ብቻ የነበረው “መረዋ” ከሃያ ብር መዋጮ በመነሳት እያደገ ሄዶ ሙሉ ባህላዊ ባንድ እና የተለያዩ የቴአትር ቁሳቁሶች እንዲኖሩት ያስቻለ የቡድን መሪ ነበር፡፡ በመረዋ ቆይታውም ሁለገብ ባለሙያነቱ እጅጉን አይሎ የወጣበት ግዜ ነበር፡፡ ሁሉንም ክዋኔዎች ይሞክር ነበር፡፡ ቴአትር ይፅፋል፣ ያዘጋጃል፣ ይተውናል፣ ሴቶች ባልነበሩ ግዜ የሴት ገፀ-ባህሪያትን ወክሎ ሁሉ ተጫውቷል፣ መድረክ ያስተዋውቃል፣ ይዘፍናል፣ ይወዛወዛል፣ ባህላዊ ከበሮም ይጫወት ነበር፡፡ ለሁለገብ የክዋኔ ሕይወቱ ሌላኛው ትልቁን አሻራ ያሳረፈው “መረዋ የኪነ-ጥበብ” ቡድን ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይኸው ቡድንም ከእነ ተስፋዬ ዘመን በኋላም እስከ አሁን ድረስ ዘልቆ ለበርካታ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች መፍለቂያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከኪነ-ጥበብ ቡድንነት ወደ ባህል ማዕከልነት አድጓል፡፡

በ መረዋ የኪነ-ጥበብ ቡድን እንደ አዲስ መነሳሳትን የፈጠረለት እና ወደ ሙያው የበለጠ ጠንክሮ እንዲዘልቅ ያደረገው አንድ ልዩ አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የወቅቱ የምዕራብ ጎጃም ዞን ባህልና ቱሪዝም መስሪያ ቤት በዞን ደረጃ ባዘጋጀው የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ላይ ምዕራብ ጎጃምን ወክለው ባቀረቡት ቴአትር ሁለተኛው ኮከብ ተዋናይ በመሆን ሰማንያ ብር ተሸለመ፡፡ ይህን ልዩ አጋጣሚ አንዲህ እያለ ያታውሰዋል፡፡

“በግዜው ያቀረብነው ቴአትር “ዛየደ እና ስልኩ” የተሰኘ ጓደኛችን የፃፈው ቴአትር ነበር፡፡ እኔ የዛየደን ዘመድ ሆኜ ተጫወትኩኝ፡፡ ሁለተኛ ወጥቼ ሰማንያ ብር ተሸለምኩኝ፡፡ እኔን ያስደሰተኝ ሰማንያ ብሯ አይደለችም፡፡ አንደኛ የወጣው ኑረዲን ኢሳ ነበር (ኑረዲን ኢሳ “ዒሻራ” የተሰኘው የግጥም መድብል ደራሲ ነው፡፡) ኑረዲንን የማውቀው በልጅነቴ ነው እንዴት ያለ ድንቅ ተዋናይ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ እኔ ሳድግ እንደ ኑረዲን ነው መሆን የምፈልገው እል ነበር፡፡ እነ ኑረዲን እኛ ገና ጓያ ትምህርት ቤት እያለን ከባህዳር ቴአትር ይዘው ይመጡ ነበር፤ ያኔ ታዲያ ለማስታወቂያ የሚጠቀሙበት ፖስተር የሚሰሩበት ጨርቅ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ ይቆሽሽባቸው ስለነበር እኛ እናጥብላቸዋለን፡፡ የምናጥብላቸው ታዲያ ቴአትር በነፃ ለመግባት ነበር፡፡ ታዲያ ከሽልማቱም በላይ ያስደሰተኝ ፀጉሬን እያሻሸ ‹‹አንቺ እንዴት ያለሽ ጎበዝ አክተር ነሽ ወደፊት ትልቅ ቦታ ትደርሻለሽ` አለኝ›› ታዲያ ያኔ የተሰማኝን ደስታ መቼም አልረሳውም፡፡”

መረዋ የኪነ-ጥበብ ቡድን ተሳትፎውን በማሳደግ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ በክልል ደረጃ በተዘጋጀው ኤች አይ ቪ ኤድስ ላይ ባተኮረ ፌስቲቫል ላይ ምዕራብ ጎጃምን በመወከል በተስፋዬ እሸቱ የተዘጋጀ ቴአትር ይዞ በመቅረብ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ ታዲያ የተስፋዬ እሸቱ እና የመርዓዊ እንዲሁም የመረዋ ፍቅር እና ፈንጠዚያ እንደታሰበው በፌሽታ ሊጠናቀቅ አልተቻለውም፡፡
ተስፋዬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተከታተለባቸው አራት ዓመታት የበለጠ ወደ ኪነ-ጥበቡ በመሳብ ከቀለም ትምህርቱ ወደ ኋላ ስለቀረ ይሁን ባልታወቀ ምክንያት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ የመልቀቂያ ውጤት ሳይሳካ ቀረ፡፡

“እኔ አሁን ነው በደንብ የማስታውሰው ከዘጠነኛ ክፍል በኋላ ጥበቡ በጣም ሳበኝ፡፡ ከአባቴ ጋርም በዚህ ምክንያት በተደጋጋሚ ፀብ ሆነ፡፡ በእርግጥ ጥበብ በጣም ይወዳል፡፡ ያበረታታኝ ነበር፣ ቴሌቪዥን ያለበት ይዞኝ እየሄደ ቴሌቪዥን ያሳየኛል፣ እቤት ውስጥ ልብ ወለድ ይዞ እየመጣ ያነብልናል፡፡ ነገር ግን ከዛም በላይ ወደ ትምህርቱ እንዳተኩር ይፈልግ ነበር፡፡ በእርግጥ እርሱ የናዝሬት ልጅ ነው፤ ከናዝሬት መጥቶ ነው አቸፈር እናቴን አግብቶ የተጠቃለለው፡፡ እኔ ግን የገጠር ልጅ ነኝ ከገጠር ብቸኛው መውጫ ደግሞ ትምህርት ነው፡፡ አስታውሳለሁ ማትሪክ ብንወድቅ ምንድን ነው የምንሆነው ስንባባል እራሳችንን እናጠፋለን የምንል ልጆች ሁሉ ነበርን፡፡ ታዲያ ምን ደርጋል ከአንድ እስከ ሰባት ከወጣነው ልጆች መሃል ሁሉም ለዲግሪ ሲያልፉ እኔ ብቻ ወደኩኝ፡፡ ያሳዝናል ቤተሰቤ በዚህን ያህል “ሾክ” ሲያደርግ አይቼው አላውቅም! የአባቴ ደግሞ የተለየ ነበር! ተስፋቸው ሁሉ በነነ፡፡”
በህይወት ዘመኔ ሁሉ ሁለተኛ አማራጭ የሚባል ነገር ይዤ አላውቅም የሚለው ተስፋዬ ይህ ባይሆንልኝ ይህን አደርጋለሁ ብዬ አላውቅም ይላል፡፡ አንድ ነገር ከያዘ በዛው ጉዳይ እስከመጨረሻው መዝለቅ እንጂ አማራጭ ይዞ መንቀሳቀስ የማይሆንለት ተስፋዬ የማትሪክ ውጤቱ አልሳካ ሲል በቀጥታ ያመራው ወደ ጎንደር መምህራን ኮሌጅ ነበር፡፡ እዛም ገብቶ የታሪክ ትምህርትን ተከታትሏል፡፡ በጎንደር ቆይታውም ቴአትርን አልተዋትም ነበር ከሥነ-ፅሁፍ ተማሪዎች ጋር በመሆን ቴአትር እያዘጋጀ ያቀርብ ነበር፡፡ ካቀረባቸው ተውኔቶች መሃልም የአፄ ቴዎድሮስን ገፀ-ባህሪ ወክሎ የተጫወተው አይረሴ እንደነበር ይናገራል፡፡ ቴአትርን አለመተውም ብቻም አይደለም ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ቴአትር እንደሚያጠናም በእርግጠኝኘት ይናገር እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በመቀጠልም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴአትር ለመማር ሲጓዝም ከጎንደር መምህራን ኮሌጅ በከፍተኛ ውጤት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኖ ነበር የተመለሰው፡፡

አዲስአበባዩኒቨርሲቲበትምህርትበመምህርነትእናበኃላፊነት

ተስፋዬ እሸቱ ከጎንደር መምህራን ኮሌጅ እንደተመለሰ በቀጥታ ያመራው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነበር፡፡ አሁንም ቴአትር ተምሮ ተዋናይ ለመሆን፡፡ ነገር ግን ይህ ህልሙ እንደቀደመው ግዜ ሁሉ ወዲያውኑ ያለ ተግዳሮት ሊሳካለት አልቻለም፡፡ በዩኒቨርሲቲው በገጠመው የአሰራር መመሪያ መሰረት በቅድሚያ ወደ ታሪክ ትምህርት ክፍል ዘልቆ ለማማር ግዴታ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ተስፋ መቁረጥን ፈፅሞ የማያውቀው ተስፋዬ በታሪክ ትምህርት ክፍል ለአንድ ዓመት ተምሮ እንደለመደው 4.0 ነጥብ ዓመታዊ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ዓመቱን አጠናቀቀ፡፡ በታሪክ ትምህርት ክፍል ለወርቅ ተሸላሚነት ታጭቶ ለማዕረግ ሲጠበቅ እርሱ ግን በቀጥታ ያመራው ወደ ህልሙ ደጃፍ ነበር፡፡ ሌላውን ነገር እርግፍ አድርጎ በመተውም ትምህርት ክፍል በመቀየር በ19998 ዓ.ም ለረጅም ግዜ ሲናፍቀው ወደ ነበረው ቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ተቀላቀለ፡፡ በመጨረሻም የዕድሜ ዘመን ህልሙ ጋር ተገጣጠሙ፡፡ ከስጋ ሞት በኋላም እንኳ በህያው ስም እና ክብር ነፍስ ዘርተው በጋራ ሲወሱ ለመዝለቅ ተማምለው ጉዞኣቸውን ጀመሩ፡፡ ይህ ጉዞም አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

ተስፋዬ እሸቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት በትምህርት ዓለም ቆይታውም ከዛ ቀደም እንደነበሩት የትምህርት ዘመን ቆይታዎቹ ሁሉ ጠንካራ እና ባለ ከፍተኛ ውጤት ተማሪም ነበር፡፡ ይኸው ከፍተኛ ውጤቱ እና ትጋቱ ነበር በቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ውስጥ ወዲያውኑ በመምህርነት እንዲቀጠር ምክንያት የሆነው፡፡ በዚሁ ትምህርት ክፍል የትምህርት ክፍሉ ለ 4 ዓመታት ዳይሬክተር በመሆንም አገልግሏል፡፡ በዚሁ ኃላፊነቱ ጊዜ በርካታ ተግባሮችን ያከናወነ ሲሆን ከእነዚህም መሃከል ዩኒቨርሲቲው በግዜው በነበረው አሰራር ቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል በእየ ዓመቱ 40 ተመዝጋቢ ተማሪዎች ከሌሉት ማስተማር አይችልም ነበር ይህንንም ቁጥር ዩኒቨርሲቲውን አሳምኖ የምዝገባ ቁጥሩ ወደ 20 ተማሪ እንዲወርድ አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በታሪክ ጭምር የሚመሰገንበት ስራው “ኑ እስኪ ቴአትር እንይ” የተሰኘው በ2007 ዓ.ም እና በ2008 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ግዜያት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የተካሄደው ሳምንታዊ የቴአትር ፌስቲቫል ነው፡፡ በእነዚህ ፌስቲቫሎች ላይ 10 ያህል ትላልቅ ቴአትሮች በነፃ ለተመልካች የቀረቡ ሲሆን፣ ከአስር በላይ ታላላቅ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ተዘክረዋል፣ በርካታ ጥናታዊ ወረቀቶች እና ወርክሾፖችም ቀርበዋል፡፡ ታዲያ ለመጀመሪያ ግዜ ይህ ፌስቲቫል ሲዘጋጅ ተስፋዬ እሽቱ በራሱ ተነሳሽነት ሃሳቡን በማመንጨት እና ወደ አንድ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ድረስ በመሄድ በጀት በመለን እና መምህራንን፣ ተማሪዎችን እና ባለሙያዎችን በማስተባበር በትልቅ ትግል ፌስቲቫሎቹ እንዲካሄዱ ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ ፌስቲቫሉ ላይ ከቀረቡት ቴአትሮች መሃከልም በመራሄ ተውኔት አባተ መኩሪያ በተዘጋጀው “ኦቴሎ” ቴአትር ላይ የ “ቃሲዮ” ን ገፀ-ባህሪ ወክሎ ሲጫወት የታላቁ ግሪካዊ ሶፎክለስ ድርሰት የሆነውን “አንቲገን” ቴአትርን ደግሞ በማዘጋጀት ለመድረክ አብቅቷል፡፡

ሁለተኛ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ “ካልቸራል ስተዲስ” ያገኘው ተስፋዬ አሁን ደግሞ በዛው ዩኒቨርሲቲ በ “ፎክሎር” ሶስተኛ ዲግሪውን እየተማረ ሲሆን በመስራት ላይ የሚገኘው የጥናት ወረቀቱም በታላቁ ኢትዮጵያዊ የትውፊታዊ ክዋኔዎች አባት ፍስሃ በላይ ይማም ህይወት እና ስራዎች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡

የአዲስአበባዩኒቨርሲቲየባህልማዕከል

ተስፋዬ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መጥቶ ገና የታሪክ ተማሪ እያለ የተለያዩ ወጎችን እና ግጥሞችን በማቅረብ ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ የተዋወቀውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርቲ የባህል ማዕከል በስራ አስኪያጅነት እየመራው ይገኛል፡፡ በተለይም በ 2016 ዓ.ም ከ 10 ዓመታት በላይ ተቋርጦ የነበረውን ሳምንታዊ የኪነ-ጥበብ ምሽት በድጋሚ በማስጀመር በርካታ ወጣት እና ታዳጊ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እንዲጠቀሙበት ክፍት እንዲሆን አድርጓል፡፡ በኪነ-ጥበብ ምሽቱም ከ30 በላይ አንጋፋ እና ወጣት የጥበብ ባለሙያዎች በመገኘት የሙያ እና የህይወት ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ሆኗል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃም ለመጀመሪያ ግዜ ከአምስት በላይ ዩኒቨርሲቲዎች የተሳተፉበትን የዩኒቨርሲቲዎች ባህል ማዕከላት ፌስቲቫል እንዲዘጋጅም በማድረግ ከሃሳብ ከማመንጨት ጀምሮ ከፍተኛውን የመሪነት ድርሻ ተወጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ባህል ማዕከሉ ከረጅም ዘመናት በኋላ በዘመናዊ መልክ ታድሶ አግልግሎት እንዲሰጥ ከፍተኛውን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

የአባተ መኩሪያ አስተዋፅፆ በ “ሜጫ” ህይወት ውስጥ
“…ጋሼ ተሰፋዬ እሸቱ እባላለሁ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር መምህር ነኝ…”
“….ይመችሽ! አባተ እባላለሁ፡፡ የቴአትር ተማሪ ነኝ…”
ይህች ድራማዊ ቃለ-ተውኔት የመሰለች ምልልስ ታላቁ መራሄ ተውኔት አባተ መኩሪያ እና ተስፋዬ እሸቱ (ረ/ፕ) በነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) አስተዋዋቂነት በተዋወቁበት የመጀመሪያዋ ቀን፣ የመጀመሪያዋ ቅፅበት ላይ የተለዋወጧት የመጀመሪያዋ ምልልሳቸው ናት፡፡ ያ የኢትዮጵያ የምንግዜውም ታላቅ መራሄ ተውኔት፣ ከአስናቀች ወርቁ እስከ መሰረት መብራቴ፣ ከ ወጋየሁ ንጋቱ እስከ ደበበ እሸቱ፣ ከተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ) እስከ ተስፋዬ እሸቱ (ራሱ ባለ ታሪኩ) ድረስ ባለው ረጅም የዘመን ርቀት እልፍ አዕላፍ የመድረክ ዕንቁዎችን ያዘጋጀ እና ወደ ብቃታቸው ጣራ ያደረሰ፣ አሉ የተባሉ ታላላቅ ፀሃፌ-ተውኔቶችን ሁሉ ድርሰቶቻቸውን ከወረቀት ወደ መድረክ ከሃሳብ ወደ ህይወት በተዓምራዊ ጥበብ የቀየረ፣ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር ታሪክ ውስጥ የራሱ የሆነ የዝግጅት አሻራ ያሳረፈው ጠቢብ በዕድሜው የመጨረሻ አስርተ ዓመታት ላይ ለተዋወቀው ወጣቱ ጀማሪ የዩኒቨርሲቲ መምህር በመጀመሪያ ቀን ትውውቅ በፍፁም ትህትና እና ለጥበብ ካለ አክብሮት በመነጨ ልቦና “የቴአትር ተማሪ ነኝ” በማለት ትውውቁን ጀምሮ ወጣቱን በአንዲት ቃለ-ምልልስ የህይወት ዘመን ትምህርት ቸረው፡፡ ወጣቱ ተስፋዬ እሸቱም ለመማር ልቡ ክፍት ነበር እና በገጠመው ያልተጠበቀ ምላሽ ሳይደናገጥ፣ ግራ ሳይጋባ እና ሳይሸሽ ይልቁንም ቀድሞ ባሳየው ‹‹ጄስቸር›› ሸምቀቅ በማለት ከዚህ የህይወት መምህሩ ጋር በመጣበቅ መራሄ ተውኔት አባተ መኩሪያ ህይወቱ እስካለፈችበት ግዜ ድረስ የልብ ወዳጅ፣ የቅርብ ጓደኛ፣ ቤተሰብ እና የዘለለት ተማሪ በመሆን ዘለቀ፡፡

ከጋሽ አባተ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቁት በ2001 ዓ.ም ተስፋዬ ልክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቆ እንደወጣ ነበር፡፡ በዛን ወቅት ለስድስት ወራት ያህል የግማሽ ግዜ ሰራተኛ ነበረ እንጂ ገና ቋሚ ቅጥር አልነበረም፡፡ በመሃልም የምስራቅ አፍሪካ የቴአትር ፌስቲቫል እንዳለ ይሰማ እና በቀጥታ ወደ ባህር ዳር በማምራት ለክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ በዚህ ፌስቲቫል ላይ እንሳተፍ የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡ ጥያቄውም ተቀባይነት አግኝቶ በጀት ተመድቦለት ወደ ሰባ የሚጠጉ የገጠር ልጆችን ይዞ መጥቶ፤ በባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት ላይ የሚያተኩር ሙዚቃዊ-ትውፊታዊ ተውኔት በፌስቲቫሉ ላይ አቀረበ፡፡ በወቅቱ ከተለያዩ ዓለማት መጥተው በታደሙት ታዳሚያን ዘንድ እጅግ ከፍተኛ አድናቆትን አግኝቶ ነበር፡፡ ጋሽ አባተም ቴአትሩን ተመልክቶ ተደስቶ ስለነበር ተስፋዬ ነብዩ ባዬን (ረ/ፕ) እንዲያስተዋውቀው አደረገ፡፡ በዛው ወዳጅነታቸው ፀና፡፡

“የጋሼ የመጀመሪያ ስራ ጠዋት እኔ ጋር መደወል ነበር”
ይላል ተስፋዬ ጋሽ አባተ መኩሪያን ሲያስታውስ፡፡
“ጠዋት ጠዋት የሚያደርገው ነገር ቢኖር ሁለት ሶስት ግዜ ባለበት ጎርደድ ጎርደድ ማለት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ከዛ እኔ ጋር መደወል ነበር፡፡ ክፍለ ሀገር እንደሆነ ያለሁት እያወቀ እንኳ ይደውልልኝ ነበር፡፡ ይህንን ነገር ለምጄ፤ ካለፈ በኋላ ለርጅም ግዜ ተቸግሬ ነበር፡፡ ሁልግዜም ጠዋት ጠዋት ስልኩን እጠብቅ ነበር፡፡”
እያለ ስለ ቅርበታቸው በተመስጦ የሚያነሳው ተስፋዬ በነበራቸው ለዘጠኝ ዓመታት ያህል የዘለቀ ወዳጅነት ሁሉን ነገር ከጋሽ አባተ እንደተማረ ይናገራል፡፡ በተለይ የቴአትር የዝግጅት ጥበብን በደንብ እንደቀሰመ እና በተለይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተዋንያን ያሉበት ቴአትር ማዘጋጀት እንዲወድ ያደረገው እና በምርጫውም ከትወናው ወደ ዝግጅቱ የበለጠ እየተማረከ ለመሄዱ መነሳሳት እና ሰበበ ምክንያት የሆነው ጋሽ አባተ መኩሪያ እንደሆነ አበክሮ ያነሳል፡፡
በጥብቅ ቁርኝት እንደ እኩያ በጓደኝነት ከጋሽ አባተ ጋር አብሮ የኖረው ተስፋዬ እሸቱ ከጋሽ አባተ መኩሪያ ዕረፍት በኋላ ህይወት እጅግ ከብዶት እንደነበር ይናገራል፡፡ በህይወቴ የገጠሙኝ ከባድ ሀዘኖች ሶስት ናቸው የሚለው ተስፋዬ የመጀመሪያ ብሎ ሚያነሳው ከባድ ድንጋጤ እና ሀዘን ያቺ ማትሪክ የወደቀባትን ወቅት ሲሆን፤ ወርሃ ህዳር አስራ ዘጠነኛው ቀን 2006 ዓ.ም ደግሞ ተስፋዬ ሁለተኛው ብሎ የሚያነሳው እና የማያውቀው ዕንግዳ ስሜት ለመጀመሪያ ግዜ እንደተሰማው የሚያነሳበት ወቅት ነው፡፡ አባቱ መምህር እሸቱ ሀብቱ ህልፈታቸው የተሰማበት ወቅት፡፡ ተስፋዬ ይህን ግዜ ሲያስታውስ እንዲህ በማለት ነው፡፡
“አባት የሚሞት አይመስለኝም ነበር፡፡ እኔ ያኔ ትልቅ ሰው ነኝ ማስተርስ ሁሉ ይዣለሁ ግን ዕንግዳ ነው የሆነብኝ ምክንያቱም ሁሉ ነገራችን ነበር አባቴ፡፡ ለእኔ እና ለቤተሰቦቼ እጅግ ከባዱ ግዜ ነበር፡፡ ከባድ ድንጋጤ እና ሀዘን የወረረን ወቅት ነበር፡፡ ያንን ግዜ ለመቀበል በጣም ከብዶኝ መራር ሀዘን እና መሰበር ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡”

ሌላው ለማገገም እጅግ ከባድ የሆነብኝ እና ጥልቅ ሀዘን የሚባል የደረሰብኝ ግዜ ብሎ የሚያስታውሰው የመራሄ ተውኔት አባተ መኩሪያን ህልፈት ወቅት ነበር፡፡
“ያኔ ሁሉ ጨለመብኝ፣ ግራ ገባኝ፣ ወዲህ ብዞር፣ ወዲህ ብዞር ምንም አላገኘሁ ብዙ ነገሬን ጋሼ ተቆጣጥሮት ስለነበር እርሱ በሌለበት መኖር ለእኔ እጅግ ከባድ ነበር፡፡”
በማለት ያሳለፈውን ከባድ ግዜ ያስታውሳል፡፡
ተስፋዬ በአንድ ወቅት የልጅነቱ መሰረት ወደ ሆነችው የምዕራብ ጎጃሟ መርዓዊ ከተማ ጋሽ አባተን በግብዣ መልክ ይዞት ሄዶ ነበር፡፡ ግብዣውም ትውፊታዊ ተውኔት ያሰራቸው ወጣቶች የቴአትር ፌስቲቫል አዘጋጅተው ጋብዘውት ስለነበር ጋሽ አባተን በክብር ዕንግድነት ይዞት ሄዶ ነበር፡፡ በጉዞኣቸው ወቅትም አካባቢውን አይቶ ይህ አካባቢ ምን ይሰኛል ሲል ጋሽ አባተ ተስፋዬን ይጠይቀዋል ተስፋዬም ሜጫ ይባላል ሲል ይመልስለታል፡፡ ጋሽ አባተም አንተ “ሜጫ” ነህ በቃ ሲል ይህንኑ ቅጽል ስም ያወጣለታል፡፡ እስከመጨረሻውም በዚህ ስም ሲጠራው ኖሯል፡፡ ብዙ ወዳጆቹም ከጋሽ አባተ በመቀበል “ሜጫ” ሲሉም ይጠሩታል፡፡
“አሁንም ድረስ ሰዎች ሜጫ ሲሉኝ ደስ ይለኛል፤ ጋሼ የጠራኝ ይመስለኛል፡፡”
በማለት ተስፋዬ የህይወት መምህሩን በፍቅር ያስታውሳል፡፡
ተጨማሪ ትምህርቶች እና ዋና ዋና የስራ ውጤቶች

ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ እሸቱ “ሜጫ” ቴአትርን ከነፍሱ መውደድ ብቻም አይደለም ከቴአትር ውጪ መኖር የሚችል ዓይነት ሰው አይደለም፡፡ ይህንን የሚወደውን ሙያ ከሀገር ውስጥ ትምህርት በተጨማሪ በተለያዩ ሀገራት እየተዘዋወረ የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስዷል፡፡ አሜሪካን ሀገር በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሚቺጋን “አፍሪካን ፐሬዚደንሺያል ስኮላርሺፕ” ለስድስት ወራት ያህል ተከታትሏል፡፡ ይህ ስኮላርሺፕ የተሳካው ከዚህ ቀደም አሜሪካን ሀገር ለ ሶስት ተከታታይ ጊዜያት ያገኛቸው የትምህርት ዕድሎች በቪዛ መከልከል ምክንያት ከከሸፉ በኋላ ነው፡፡ በተለይ ኦሪጎን ዩኒቨርሲቲ ሰጥቶት የነበረው የቴአትር ዝግጅት የ ፒ.ኤች.ዲ ሙሉ ስኮላርሺፕ በቪዛ መከልከል ምክንያት መክሸፉ በግሌ ህይወቴ ላይ ከደረሱ ነገሮች ሁሉ በድንጋጤ ስብርብሬን ያወጣው አጋጣሚ ነው ይላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ሀገራት እየተዘዋወረ ትምህርቶችን ቀስሟል፡፡ በጣሊያን ሀገር ላማማ ኡምብሪያ የዳይሬክቲንግ ወርክሾፕ ለ አስር ቀናት ያህል፣ በፖላንድ የአስራ አምስት ቀናት ኤክስፐርመንታል ቴአትር ወርክሾፖች የሚጠቀሱ ሲሆን በሙያ ህይወቴ ትልቁ እመርታ እና ከስኬቶቼ አንዱ እና ትልቁ ብሎ የሚጠቅሰው ፈረንሳይ ሀገር የተከታተለውን ወርክሾ ነው፡፡ ይህ ወርክሾፕ የተካሄደው በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2016 ዓ.ም በፈረንሳይ ኖርማንዴ ሲሆን፤ መጠሪያውም “ዶመን ላ ቦዲዬ” ይሰኛል፡፡ ተስፋዬ በቅድሚያ የወላጅ እናቱን ታሪክ በተውኔት መልክ በአማርኛ ፅፎት ወደ እንግሊዝኛ ተርጉሞ ልኮላቸው ነው ወደውት እና መርጠውት የሄደው፡፡ ለሙሉ ወርክሾፑ ማስተማሪያ የነበረውም ይኸው የተስፋዬ ተውኔት ሲሆን መጨረሻ ላይም ለተመልካች ቀርቧል፡፡ በዚህ ወርክሾፕ ላይ የቴአትሩ ረዳት አዘጋጅ በመሆንም ጭምር ተሳትፏል፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ተውኔቶች ላይ በትወና እና በዝግጅት የተሳተፈ ሲሆን በተለይም “ሙከራዊ (Experimental)” የቴአትር ዝግጅት አቀራረብን እንደሚመርጥ ይናገራል፡፡ ከሰራቸው ስራዎች መካከልም የመጀመሪያ ፕሮፌሽናል ቴአትሩ “ዘወልድ” የተሰኘ ሲሆን ድርሰት እና ዝግጅቱ የራሱ ነው፡፡ ይህን ቴአትር ከጋሽ አባተ መኩሪያ ጋር በመሆን ከአስር በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ዞረው አሳይተውታል፡፡ ሌላኛው ትልቁ ስራው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር የተጀመረበት መቶኛ ዓመት በተከበረበት ግዜ አዘጋጅቶ ለተመልካች ያቀረበው “የካሳ ፈረሶች” የተሰኘው ሙከራዊ ቴአትር አንዱ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ በ2014 ዓ.ም ለታላቁ የአድዋ ድል መታሰቢያ የሰራው “አድዋስ” የተሰኘው ሙዚቃዊ ቴአትርን ደግሞ ከስራዎቼ ሁሉ ትልቁ ሲል ይጠቅሰዋል፡፡

ማሳረጊያ

ተስፋዬ በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ ግዜ ከሚከውናቸው ጥበባዊ ተግባራት ባሻገር በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ባህል ማዕከል በስራ አስኪያጅነት እያገለገለ ይገኛል፡፡ ወደ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብሎም “በመሃል” በተሰኘ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ከድምፃዊ ፀሐይ ዮሐንስ እና ከተዋናይት ሀረገወይን አሰፋ ጋር በተዋናይነት እየተሳተፈ ይገኛል፡፡ በፍፁም ተስፋ መቁረጥ የማያውቀው እና አንድ ነገር ለማድረግ አስቤ ሳላደርገው ምንም ነገር የሚያስጥለኝ አይኖርም ከጀመርኩኝ ሳልጨርስ ማረፍ አልችልም ማለትን የሕይወቱ መርህ አድርጎ የኖረው ረዳት ፕሮፈሰር ተስፋዬ እሸቱ “ሜጫ” ይህንን ሁሉ በነፃነት ለማድረጉ እና በስራ ገበታው አንድም ቀን ሳይረበሽ ሁልግዜም በሙሉ ኃይል እና ጉልበት ስራዎቹን እንዲያከናውን የሚያስችለው አንድ ነገር እንዳለ ይናገራል፡፡ ይህም ኃይልና ብርታቱ ትዳሩ ነው፡፡

“በህይወቴ ትልቁ ስኬቴ ትዳሬ ነው፡፡ ሁልግዜም ደስተኛ ነኝ! ይህንን ለማለት ያህል አይደለም የምለው፡፡ እግዚያብሄር ይወደኛል ብዬ የምለው አንደኛ በጣም በፍቅር ከተሞላ ተወዳጅ ከሆነ ቤተሰብ መውጣቴ፣ ሁለተኛ የምወደውን ሙያ እየሰራሁ መኖር መቻሌ እና ሌላው ትልቁ ነገር በትዳሬ ደስተኛ መሆኔ ነው፡፡ ምንም ነገር ቢኖርህ በህይወትህ ደስታ ከሌለህ ሁሉ ነገር ዋጋ ቢስ ነው፡፡ ከባለቤቴ ጋር አይቸግረንም፣ አንጣላም ማለት አይደለም፡፡ ሊቸግረን ይችላል፣ ልንጋጭ እንችላለን ነገር ግን አሁንም ድረስ ገና አዲስ ፍቅር እንደጀመርንበት ግዜ (አዲስ አንደተጣበሱ ጥንዶች) ነው ፍቅራችን፡፡ በዚህ በጣም ዕድለኛ ነኝ! ለዚህም ይመስለኛል ደስታ ርቆኝ የማያውቀው፡፡ በእነዚህ ነገሮች ሁሌም እግዚያብሄርን አመሰግነዋለሁ!”

ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ እሸቱ “ሜጫ” እንዲህ በምስጋና እንዲሞላ እና ደስተኛ ህይወት እንዲኖረው ካደረገቺው የትዳር አጋሩ ከወ/ሮ ልደት ደበበ ጋር ትዳር ከመሰረቱ አምስት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ለወደፊቱ ለመስራት የሚያልማቸው ብዙ ሙከራዊ ቴአትሮች እንዳሉ የሚናገረው ተስፋዬ ዋነኛው የወደፊት ዕቅዱ ግን እንደ ህይወት መምህሩ ታላቁ መራሄ ተውኔት አባተ መኩሪያ እስከመጨረሻው እየተማሩ ኖረው እየተማሩ መሞት እንደሆነ ይናገራል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *