ሰሎሞን አባተ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን የባለሙያዎችን የሕይወት ታሪክ ሰንዶ በማስቀመጥና በማሰራጨት፣ በመፅሐፍ ላይ እንዲታተም በማድረግ የባለሙያዎች አበርክቶ ተዘንግቶ እንዳይቀር የበኩላችን እየተወጣ ይገኛለን፡፡ እስከዛሬ ከ 400 በላይ በሚድያ እና በኪነ ጥበብ ሙያ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ጨምሮ ሌሎችም ታሪካቸው በመረጃ ቋታችን ላይ እንዲቀመጥ አድርገናል፡፡ ስለ እነርሱ ለማወቅ በተፈለገ ጊዜም ፣ታሪካቸው በቀላሉ መገኘት እንዲችል የዲጂታል አማራጮችን በማቅረብ የታሪኰቹ ተደራሽነት ዕውን እንዲሆን ሁሉን አመቻችተናል፡፡

ታሪኮቹ በጥራዝ መልክ ተሠንደው ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑም ቅፅ አንድ እና ቅፅ ሁለት መዝገበ አእምሮን እያንዳንዳቸውን በ600ገፅ አድርገን አዘጋጅተን፣ አሳትመን ፣ አስተዋውቀን እና አስመርቀን ሀገራዊ ኃላፊነታችንን ተወጥተናል፡፡ አሁንም የስነዳ ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን የመማክርት አባላት እንዲሰነዱ ስምምነት የደረሱባቸው ባለሙያዎችን እያፈላለግን መሥራታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

በቅፅ ሁለት የሕይወት ታሪካቸው መዝገበ አእምሮ ላይ ከተሰነደላቸው መካከል ሰሎሞን አባተ ይጠቀሳል፡፡ ዕዝራ እጅጉ እና ሂላሪያ ተስፋዬ ታሪኩን እንደሚከተለው ሰንደውታል፡፡

ሰሎሞን አባተ በ1999 ዓ.ም. ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄዶ የቅርብ ወዳጆቹን ሰላም ለማለት ዋሺንግተን ዲ.ሲ. ወደሚገኘው የአሜሪካ ድምፅ (ቪኦኤ) ጎራ አለ። ድምፁን የወደዱት ኃላፊዎች በኮንትራት ቅጥር መጀመሪያ በዘጋቢነት፣ በዜና አቅራቢነትና በፕሮግራም አስተዋዋቂነት እንዲሠራ አስቀሩት። እዚያው ቪኦኤ በኮምፕዩተር ዲቪዥን ውስጥ ሌላ የሥራ ዕድል አገኘና ሁለቱም ጋ መሥራት ቀጠለ። የቋሚ ቅጥር ማስታወቅያ ሲወጣ ተወዳድሮ መጀመሪያ በዓለምአቀፍ ብሮድካስተርነት፣ ከዚያም በማኔጂንግ ኤዲተርነት፣ ቀጥሎም የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት ኃላፊ ሆኖ ሠርቷል።

ሰሎሞን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለሁለተኛ ጊዜ ሄዶ ኑሮውን እዚያ ከማድረጉ ቀድሞ በአክሽን ኤድ ተቀጥሮ ኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤትን (ሃፕኮ)ን ተቀላቀለ። ወቅቱ ኤችአይቪ በዓለም ዙሪያ በአስፈሪ ሁኔታ የተሠራጨበት፣ ኢትዮጵያም በቫይረሱ ሥርጭት በዓለም 3ኛ ደረጃ ላይ የነበረችበት ነበር። በዚህ ተቋም ለአራት ዓመታት በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነት ሲያገለግል፥ ለሀገሪቱ መገናኛ ብዙኀንና የጥበባት ባለሞያዎች ኤችአይቪ/ኤድስን፣ ጫናዎቹንና ምላሾቹን በተመለከተ ሰፊ ትምህርትና ሥልጠና እንዲሰጥ አድርጓል።
ሃፕኮ ከመግባቱ በፊት የ“ዕለታዊ አዲስ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሠርቷል። ይህም በኢትዮጵያ የህትመት ታሪክ የመጀመሪያው በሣምንት ሰባት ቀን የሚወጣና የመጀመሪያው ባለሙሉ/ዝርግ ፎርማት የግል ጋዜጣ ነበር።

መስከረም 1/1993 ዓ.ም. በመጀመሪያው የሙከራ ዕትም ለንባብ የበቃውና ከ120 በላይ ጋዜጠኞችና ሠራተኞችን የያዘው ጋዜጣ በአንድ ወቅት ሕወሓት ውስጥ የተፈጠረውን የመከፋፈል ታሪክ የሚዘግብ ሰበር ዜና ይዞ ወጣ። ለዜናው ሽፋን የሰጠ ብቸኛ ሚድያ በመሆኑም በተከታታይ ትዕዛዞች በ25 ሺህ ቅጅ ተሠራጨ። ሆኖም ይህ ዜና ለጋዜጣው መቋረጥ ምክንያት ሆነ። አልፎም “የፖለቲካ ይዘት ያለው አንዳችም ዘገባ ከእንግዲህ በጋዜጣው ላይ እንዳይወጣ” የሚል ትዕዛዝ ከአሳታሚው ተላከ። በዚህ “መሠረታዊ የጋዜጠኛነት ነፃነትን በሚጋፋ ጫና” የተነሳ ሰሎሞን ይህንኑ በመልስ ደብዳቤ ገልፆ ሥራውን መልቀቁን አሳወቀ። እርሱንም ተከትሎ ሌሎችም የሙያ አጋሮቹ የሥራ መልቀቂያ አስገቡ።

ከዚህ በኋላ ሰሎሞን በራሱ የማስታወቂያና የህትመት ድርጅት ላይ አተኮረ። በመካከልም በደረጀ ደስታ አነሳሽነትና ዋና አዘጋጅነት በጋራ በመሠረቱት ‘ዘ-ፕሬስ’ የተሰኘና በቪዥን ኢንፎርሜሽንና ፕሮሞሽንስ ድርጅት የሚታተም ጋዜጣ አማካሪ በመሆን ያገለግል ነበር።

ነገር ሁሉ መነሻ አለውና፥ የጋዜጠኛነት ሙያ ፍቅር ከልጅነቱ ጀምሮ የነበረው ሰሎሞን መነሻው እንዲህ ነው፥ መጋቢት ወር 1955 ዓ.ም. በቀድሞ ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ወናጎ ከተማ ነው የተወለደው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ወናጎ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማረ።

በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ትርምስ የተነሳ ወላጅ አባቱን በሞት በመነጠቁ፥ ቤተሰቡም ለመለያየት ተገደደ። በ1967 ዓ.ም. አዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩ አክስቱ (የእናቱ ታላቅ እህት) ወሰዱት። በዚያው ዓመት ተቋርጦ የነበረ የ6ኛ ክፍል ትምህርቱን ቀጥሎ በጠብመንጃ ያዥ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን፥ ፈለገ ዮርዳኖስ፣ በኋላም አዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተምሮ በ1972 ዓ.ም. አጠናቀቀ።

የ16 ዓመት ወጣት ሳለ በመጀመሪያው ዙር የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ወደ ሐረርጌ ዘምቶ ለ6 ወራት አገልግሏል። ከዛም ሲመለስ ይኖርበት በነበረው ቀበሌ በሰባት ተከታትይ ዙሮች አስተምሯል። በተለያዩ የወጣት ማኅበር እንቅስቃሴዎችም ይሳተፍ ነበር። ከልጅነት የነበረውን ጋዜጠኛ የመሆን ሕልም የሚያሳካበትን ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝቶ በ1974 ዓ.ም. ወደ ያኔዋ ሶቭየት ኅብረት ሄደ።

ሚንስክ ከተማ የሚገኘው ቤላሩስ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በዓለምአቀፍ ጋዜጠኛነት የመጀመሪያው ባች ተማሪ ሆነ። ከሃያ ሰባት አገሮች የተላኩ ወጣቶች በገቡበት ኮርስ ብቸኛ ኢትዮጵያዊ ነበር። በዛም በህትመት ሚድያ ስፔሻላይዝ አድርጎ፣ ማስተርስ ዲግሪውን በከፍተኛ ማዕረግ ተቀብሏል።

ለመመረቂያው “የኢትዮጵያ የህትመት ታሪክ አጀማመርና ዕድገት” በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ጥናት በዩኒቪርሲቲው ኮሚሽን ተመርምሮ በማዕረግ ሲጸድቅ፣ ቅጂው “ለማገናዘቢያ/ረፈርንስ” እንዲያገለግል ሞስኮ ወደሚገኘው ላማኖሰቭ ዩኒቨርሲቲ ተልኳል።

ለጋዜጠኛነት ፋካልቲ “ሜሪዲያን” በሚል ስያሜ የመጀመሪያውን የሰሌዳ ጋዜጣ ፈጥሮ ከማዘጋጀት አልፎ ሚንስክ የውጭ ቋንቋዎች ጥናት ተቋም ሩሲያኛ ቋንቋን ከተማረ በኋላ ቋንቋውን የማስተማር ዲፕሎማ አግኝቷል፤ በማስተርጎምም ያገለግል ነበር። ከትምህርቱ በተጓዳኝም በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ይሣተፍ ነበር።

ሰሎሞን ከሩሲያ እንደተመለሰ ያኔ በማስታወቅያ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መምሪያ ተመድቦ በዜና እና መዋዕለ ዜና ዋና ክፍል ከፍተኛ ሪፖርተር ሆነ። በጣቢያው ዜና፣ ዕለታዊ፣ ሣምንታዊና ልዩ ዘገባዎችን፣ ወቅታዊ ፕሮግራሞችን ብሎም የመስክ ሥራዎችን ይሸፍን ነበር። ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ከተውጣጡ ባለሞያዎች ጋር በጦር ቀጠና ሪፖርተርነት ኤርትራ ተመድቦ ከአሥር ወራት በላይ ሠርቷል።

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “ሰዎች ምን ይላሉ?” የሚል ፕሮግራም ጀምሮ ለሦስት ዓመታት ገደማ በመምራትም ይታወቃል። ይህ ፕሮግራም የተጀመረው በ1983/84 ዓ.ም በመጣው የፖለቲካ ለውጥ ምክንያት ሰዎች ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲያንሸራሽሩ ነበር። በፅሁፍና በድምፅ የሚደርሱ መልዕክቶችን ማስተናገድ፣ ማቀናበርና ማቅረብ የሰሎሞን ሥራ ነበር።

“መቶ ሃያ (120)” የተሰኘው የመረጃና መዝናኛ (ኢንፎቴይመንት) ይዘት ያለው ሣምንታዊ የሁለት ሰዓት የመፅሄት ዝግጅት ሲነሳም የሰሎሞን ስም አብሮ ሳይጠቀስ አይቀርም። ይህ መሰናዶ በቴሌቪዥን ጣቢያው የሚቀናበሩና የሚዘጋጁ የንግድ ማስታወቂያዎችን የማውጣት አዲስ ባህል የጀመረና ያሳየ ነው።

በኢቲቪ ቆይታው ከሠራቸው ሥራዎች መካከልም በ1985/86 ዓ.ም. አካባቢ ተቋሙ፣ እንዲሁም በጠቅላላ መገናኛ ብዙኃኑ ከአዲሱ የኮምፕዩተር ቴክኖሎጂ ጋር በአካል እንዲተዋወቁና እንዲሠሩበትም ያበረከተው አስተዋፅዖ ይጠቀሳል። በወቅቱ በተከፈተና ዳስ (Data Access Systems – DAS) በሚባል የግል ማሠልጠኛ ሙሉ ሥልጠና ከወሰደ በኋላ፥ ከማሠልጠኛው ኃላፊዎች ጋር ተነጋግሮ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ የኢትዮጵያ ሬድዮ፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ባልደረቦች ሙሉ የኮምፕዩተር ሥልጠና እንዲያገኙ አስችሏል።

በኢቲቪ 6 ዓመታት ከ7 ወር ገደማ የቆየው ሰሎሞን፥ በአንድ ወቅት በሚድያ ተቋማቱ ውስጥ ገንኖ የነበረው የፖለቲካ ድባብ ምቾት ስለነሳው፣ ምንም እንኳ ቤቱንና ሥራውን ቢወድድና በጥቂት ጊዜ ውስጥ ዕድገት የሚያገኝበት ዕድል እንደነበረ ቢያውቅም፣ ያንን ትቶ 1987 ዓ.ም. ግንቦት ከኢቲቪ ለቀቀ። ይህን ሲወስን ግን ቀጣይ ማረፊያውን አያውቅም ነበር።

በዚህ ወቅት ነበር ከአማረ አረጋዊ በደረሰው የስልክ ጥሪ “ሪፖርተር” ጋዜጣ እየተመሠረተ ስለመሆኑ የተነገረውና አሣታሚውን የሚድያ ኮምዩኒኬሽንስ ሴንተርን የተቀላቀለው። ጋዜጣው ካዛንችስ በነበረው ቢሮ ውስጥ ሲጀመር ሰሎሞን የመጀመሪያው ምክትል ዋና አዘጋጁ ነበር። በሂደትም ፅሁፍ የሚያበረክቱ፣ የሪፖርተሮችና የሠራተኛ ቁጥር አደገና ሥራውን በማስፋት ተነባቢ፣ ተዓማኒና የሚከበር ጋዜጣ መፍጠር ቻሉ። ሰሎሞንም በዚህ ውስጥ ዘገባዎችንና ጽሁፎችን በማዘጋጀትና በአርትኦት፣ ቃለመጠይቆችን በማድረግ ሠርቷል። የገፅ ዲዛይንና የኮምፕዩተር ቅንብር፣ የህትመትና የሥርጭት ክትትል ሥራዎችን ያከናውን ነበር። በድርጅቱ ውስጥ ለአራት ዓመታት ሠርቶ በ1990 ዓ.ም. ለቀቀ።

ቪዥን ኢንፎርሜሽንና ፕሮሞሽንስ (VIP) የሚባል የማስታወቅያና የህትመት ድርጅት የከፈተው ከዚህ በኋላ ነበር። ይህ ድርጅት ለትልልቅ የንግድ፣ አንጋፋና ስመ ጥር ለሆኑ፣ የተለያዩ ምርቶችን ለሚያመርቱና ከውጭ ለሚያስገቡ ተቋማት የማስታወቅያና የማስተማርያ ሥራዎችን የሚሠራ ነው። በዚህ ድርጅት ጋዜጣዎችና መፅሔቶችን አትሟል፤ ትልልቅ ሃገራዊ ክንዋኔዎችን አሰናድቷል፣ በአደባባይ መድረኮች ዝግጅቶች ላይ በንቃት ተሣትፏል።

በሙሉ ሙያዊ ህይወቱ በከተማና በገጠር፣ ከጦር ቀጣና እስከ ድርቅና ሌሎችም የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች፣ ከጎዳና እስከ ቤተመንግሥት፣ በሃገር ውስጥና በውጭም እየተሠማራ የኖረውና በህትመት፣ በኤሌክትሮኒክስና በዲጂታል የመገናኛ ብዙኃን ዘርፎች፣ በኦዲዮ-ቪዥዋል መሣሪያዎችና በኮምፕዩተር አጠቃቀም የካበተ ክህሎትና ልምድ ያለው ሰሎሞን ሙያዊ የጥናትና ምርምር ተቋም የመመሥረት ምኞትና ሃሳብ እንዳለው ይናገራል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም ጋዜጠኛነትን ለአጭር ጊዜ አስተምሯል። አዲስ ዘመን፣ ሩሕ፣ ቁምነገር መፅሔት፣ አዲስ አድማስ በተለያዩ ደረጃዎችና ጊዜዎች ሙያዊ እጆቹ የነካካቸው ናቸው። በኢትዮጵያ ሬድዮም የአየር ጊዜ እየተከራየ በተለያዩ ጊዜዎች ዝግጅቶን አቅርቧል። ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ይሠራ በነበረ ጊዜና በኋላም ለክልሎችና ሌሎችም ወጣት ጋዜጠኞች ሥልጠናዎችን ሰጥቷል፤ ኮስሞስ ኦዲዮ-ቪዥዋል ማሠልጠኛ በሚባል የግል ተቋም ውስም አስተምሯል።

ከጋዜጠኛነቱ ዓለም ባሻገር በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ በአዲስ አበባና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ውስጥ ሠርቷል። በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የማርኬቲንግና የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆኖ አገልግሏል። ከባለሙያዎች ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ማርሻል አርትስ ፌዴሬሽን አደራጅ ኮሚቴ በማቋቋምና የብሄራዊ ፌዴሬሽኑ መሥራች ፕሬዚዳንት በመሆን ሠርቷል። የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽንም የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሆኖ አገልግሏል። የሃገሪቱን የመጀመሪያ የካራቴ ብሄራዊ ቡድን መርቶ አቡጃ ላይ ተካሂዶ በነበረው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ በዘርፉ ሃገሪቱ በተጨማሪ የስፖርት ዘርፍ እንድትሣተፍ አድርጓል። አትሌቶቹ ሜዳልያዎችን ይዘው ተመልሰዋል። ካይሮ ላይ በተካሄደ አካባቢያዊ የካራቴ ጉባዔ ላይም የኢትዮጵያን ቡድን መርቶ ተሣትፏል። የኢትዮጵያ ስካውት ማኅበር በመንግሥት ደረጃ ዕውቅና እንዲያገኝም የድርሻውን አድርጓል፤ የብሄራዊ ማኅበሩ የውጭ ግንኙነቶች ኮሚሽነር ሆኖም የማኅበሩ የበላይ ጠባቂ በነበሩት የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ተሾሟል።

ሰሎሞን በጋዜጠኛነት ሙያና ሌሎችም በተሠማራባቸው የአገልግሎት ዘርፎች በሃገር ውስጥ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ኬንያን ጨምሮ ተጉዞ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ተከታትሏል። በሩስያ የባህል ማዕከል የሩሲያኛ ቋንቋ መምህር ሆኖ ወደ ሦስት ዓመት ገደማ አገልግሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *