ጋዜጠኛ  ዕዝራ  እጅጉ በግለ ታሪክ ዘርፍ ዕውቅና  ተሠጠው

ቴክሳስ ዳላስ የሚገኘው አድዋ የታሪክና የባህል  ህብረት  በዘንድሮው 8ኛው የአርአያ ሰው ሽልማት በግለ ታሪክ ዘርፍ ጋዜጠኛ  ዕዝራ እጅጉን ልዩ ተመስጋኝ አድርጎታል።

ጋዜጠኛ ዕዝራ  ፣ ጸሀፌ ትዕዛዝ አክሊሉ  ሀብተወልድን የመሠሉ የሀገር ባለውለታዎችን የህይወት ታሪክ በሲዲና በዲቪዲ  ያሳተመ ሲሆን ይሄንኑ ታሪክ በእንግሊዝኛ  አዘጋጅቶታል።

በተጨማሪም  ከ 20ዐ9 አንስቶ ባለፉት 7 ዓመታት የ 45 ሠዎችን ታሪክ በሲዲ ሠርቶ  ለማስመረቅ ችሏል።

በተጨማሪም፣ በአገራችን  ታዋቂ የሆኑ እንደ ማማ በሰማይ ፤ ማህሌት የአክሊሉ ማስታወሻ፤ የመሳሰሉት 30 የሚጠጉ መጽሀፎችን ወደ ድምጽ በመቀየር ማንበብ ለማይችሉ ሰዎች እዝራ እና ድርጅቱ መላ ዘይደዋል፡

ከዚህም ባሻገር፣ የታዋቂ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ በባለታሪኮች እና በልጆቻቸው አሰሪነት ተጠይቆ 14 መጽሀፎችን አዘጋጅቷል፡፡ 

ከእነዚህም መካከል የአንኮበሩ ሰው በጂኒቫ ፤ወደ ራስ መመለስ ፤ኢትዮጵያ በድህነት ማነቆ ስር ፤ማሩ አበበ የልማት አርበኛ ዳዊት ያቺን ሰአት ፤ የኮለኔል ይልማ መንግሥቱ  የህይወት ትዝታዬ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡  በተጨማሪም በመዘጋጀት ላይ ያሉ የጀነራል አሰፋ አየነ ፤ የደጃዝማች የማነ ሀሰን ፤ ኢትዮጵያዊ በአትላንታ  እና መዝገበ አእምሮ የሚድያ እና የስነጽሁፍ ሰዎች ታሪክ ይገኝበታል፡፡ እዝራ ታሪክን የሚሰንድበት የራሱ ድረገጽ፤ ፌስቡክ እና ዩቲዩብ ያለው ሲሆን ወደ ፊት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በ10 አመት ጊዜ ውስጥ በአንድ ገጽ ብቻ ታሪካቸውን ጽፈው እንዲልኩ እየጣረ ይገኛል፡፡   

እዝራ እጅጉ በአሁኑ ሰአት ሙሉ ጊዜውን በግለሰቦች ታሪክ ላይ አተኩሮ  እየሰራ ሲሆን ወደፊትም አጠናክሮ የመቀጠል ግብ አለው፡፡

በዘንድሮው 8ኛው የአርአያ ሰው ሽልማት 16 የሚሆኑ  ባለውለታዎች ዕውቅና የሚያገኙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የቱሪዝም አባት አቶ ሀብተስላሴ ታፈሰ ፣አርኪቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ፣ጸሀፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፣ ዶክተር  እንዳለጌታ ከበደ እና ሌሎችም  ይገኙበታል ።

የአርአያ ሠው ሽልማት  ሰኔ 13   2016   በዮድ አቢሲኒያ  በታላቅ ስነስርአት ይከናወናል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *