ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ ታሪካቸው ተሰነደ
በቀጣዩ አመት ጥቅምት 2019- 72ኛ አመት ይሞላሉ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣ መዝገበ-አእምሮ ( የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች ፣በመፅሀፍ፣በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል።በተለይ ጉግል ላይ ታሪካቸው ሲፈለግ የማይገኝ ሰዎች አሁን የሙያ አበርክቷቸው በቀላሉ ኢንተርኔት ላይ በግልፅ ተቀምጦ ይገኛል።
ባለፉት 4 ዓመት ከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መፅሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።
ከእነዚህ ውስጥ የሚድያ ሰዎችም፣ የቴአትር ባለሙያዎች ይገኙበታል። አጠቃላይ 74 ከፍተኛ የሚድያ አመራሮች፣ሚኒስትሮች ፣ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የግል ሚድያ መሥራቾች፣ዋና አዘጋጆች እና መካከለኛ አመራሮች ተካተዋል። 35 ያህሉ በዋና ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ያሉ ሲሆን የሁሉም ታሪክ በተሟላ ደረጃ ለመሰነድ ተችሏል።በተጨማሪም በሳይንስ፣ በመምህርነት ፣በምህንድስና እና በሌሎችም ዘርፎች ውስጥ ያሉ ሰዎችን ወደ አንባቢ እያመጣን እንዲታወቁ ጥናትና መረጃ ማድረግ ለሚሻም ተደራሽ ስናደርግ ቆይተናል።
የእነዚህን ሰዎች ታሪክ ሰንዶ ለአንባቢ ተደራሽ ማድረግ ፈታኝ ቢሆንም አሳክተነዋል። በዚህ ተግባራችንም ተጠናክረን እንቀጥላለን።
በዚህ ፅሑፍ ታሪካቸው የሚሰነደው የፕሮፌሰር ማስረሻ እርሳቸውም በሳይንስ ዘርፍ ትልቅ አሻራ ያኖሩ ናቸው። ፕሮፌሠር ማስረሻ ፈጠነ፡- ለሳይንስ፣ ለጥናታዊ ጽሑፍና ለአገር ልማት የተኖረን ሕይወት በተግባር ያሳዩ ናቸው። ይህ እኛ የሰነድነው ታሪካቸው እኛ በጠየቅናቸው መሠረት የእርሳቸውን ይሁንታ ያገኘ እና ረቂቁንም የተመለከቱት መሆኑን ማሳወቅ እንወዳለን። ለዚህም ለእርሳቸው ልባዊ ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን።
ጆን ዘለቀ በላይ እና ዕዝራ እጅጉ ታሪካቸውን እንደሚከተለው አጠናክረውታል።
መግቢያ
ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ በኢትዮጵያ ስመ ጥር ከሚባሉ ሳይንቲስቶች፣ የትምህርት ሰዎችና አካደሚክ መሪዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ከአራት አሥርት ዓመታት በላይ ባስቆጠረው ሙያቸው ለእጽዋት ኢኮፊዚዮሎጂ፣ ለብዝሃ ሕይወት አስተዳደር፣ ለአካባቢ ሳይንስ፣ ለግብርና ምርምር፣ ለከፍተኛ ትምህርትና ለሳይንስ ፖሊሲ የጎላ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በጥናታዊ ጽሑፋቸው፣ በአመራራቸው፣ በማስተማርና በተማሪ የማማከር ሥራቸውና በተቋም ግንባታ ጥረታቸው ለሳይንሳዊ እውቀት መስፋፋትና የኢትዮጵያን ሳይንሳዊና የትምህርት እውቀት አድማስ ለማስፋፋት ባደረጉት ጥረት ትልቅ እውቅና አግኝተዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሠር፣ የዩንቨርስቲው የምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የመጀመሪያው አደራጅ ፣ የዓለም አቀፍ ሳይንሳዊ አካዳሚዎች መረብ ፕሬዚዳንት ሆነው በማገልገል ሕይወታቸውን ሙሉ ሳይንስን ለአገራዊ ልማት አገልግሎት እንዲውል ትልቅ አስተዋጾ አድርገዋል። በሥራቸው በአገር ውስጥና በውጭ አገራት በሚገኙ በብዙ ትውልድ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጭዎችና ተቋማት ላይ ተጽእኗቸውን አሳርፈዋል።
የሕይወትና የትምህርት ጉዞ
ማስረሻ ፈጠነ ጥቅምት 4 /1947 ዓ.ም. መርጡለ ማርያም ኢትዮጵያ ተወለዱ። ገና በለጋነት እድሜያቸው ጀምሮ ለተፈጥሮ ሳይንስ ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው ሲሆን በኋላ ስመ ጥር ወደ ሆኑበት የስነ-ሕይወት ሳይንስ ሙያ እንዲያመሩ ያደረጋቸው ጠያቂ ባሕሪይ ነበራቸው።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ የትምህርት ዘርፍ በ1974 ዓ.ም አገኙ። ከዚያም በመቀጠል በዚሁ ተቋም በ1977 ዓ.ም. በሳይንስ ማስተርስ ዲግሪ በቦታኒ የትምህርት ዘርፍ አገኙ። ቀጥሎም ለእጽዋት ሳይንስና አካባቢ ጥናትና ምርምር እያደገ በሄደው ፍላጎታቸው ምክንያት ጀርመን አገር በሚገኘው በዳርምስታት ዩንቨርስቲ የዶክትሬት ጥናታቸውን ተከታትለው በታህሳስ 1983 ዓ.ም. ፒኤችዲያቸውን በእጽዋት ኢኮፊዚዮሎጂ፣ በተለይ እጽዋት ከአካባቢያቸው ጋር ባላቸው መስተጋብር ላይ በመሥራት አግኝተዋል።
የትምህርት ጉዟቸውን በመቀጠል በእጽዋት የምግብና የውሃ ፍሰት ቅብብሎሽ ላይ አተኩረው በሠሩበት በጀርመን አገር ባይሮይት ዩኒቨርሲቲ የድኅረ-ዶክትሬት ጥናታቸውን ተከታትለዋል። ይህ ቆይታ በእጽዋት ሳይንስ ለተከተሉት ምርምር መሠረት የጣለ፣ ከመስኩ ባለሙያዎች ጋር ያስተዋወቃቸው እና ለነበራቸው ዓለም አቀፍ የምርምር ትብብር በር የከፈተ ነበር።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማስተማር፣ የምርምር እና የአስተዳደር አገልግሎት
የፕሮፌሰር ማስረሻ የትምህርትና የሕይወት ጉዞ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቀዳሚ ከሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅርበት የተቆራኘ ሆኖ እናገኘዋለን። በረዳት-ምሩቅ (Graduate Assistant) በ1975 ዓ.ም.ግልጋሎታቸውን ጀምረው፣ በነበራቸው ሙያዊ መሰጠት፣ ብቃትና ምሁራዊ አበርክቶ ምክንያት በትምህርታዊ ማዕረጎች ሳያቋርጥ ከፍታን እያገኙ መጥተዋል። ፕሮፌሠር ማስረሻ ከውጭ አገር የዶክትሬት ጥናታቸው ወደ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ከተመለሱ በኋላም በሰጡት አገልግሎት በ1986 አ.ም ረዳት ፕሮፌሠር፣ በ1990 ተባባሪ ፕሮፌሠር እንዲሁም በ1995 የሙሉ ፕሮፌሠርነት ማዕረግ አግኝተዋል።
በመምህርነትና በተመራማሪነት ቆይታቸው፣ ፕሮፌሠር ማስረሻ ፈጠነ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች በመጀመሪያ ዲግሪና በድኅረ ምረቃ ዲግሪ በሥነ-ሕይወት፣ በእጽዋት ፊዚዮሎጂ፣ በኢኮሎጂ/ስነ-ምሕዳርና፣ በአካባቢ ሳይንስ አሰልጥነዋል። የማስተማር ዘዴያቸውም ምሁራዊ ልሕቀት፣ ሳይንሳዊ ጠያቂነትና በተማሪዎች መካከል በጥልቀት ማሰብን የማሳደግ ባሕሪይ ያለው ሆኖ ይታወቃል። በመማሪያ ክፍል ከሚሰጡት ትምህርት ባሻገር በሥርዓተ- ትምህርት ቀረጻና የትምህርታዊ ፕሮግራም ማስፋፊያ ላይ ጉልህ አበርክቶት አድርገዋል።
የጥናታዊ ጽሑፍና ምርምር አስተዋጽኦዎችና ውጤቶች
የፕሮፌሠር ማስረሻ የጥናትና ምርምር ሙያ በቀዳሚነት በእጽዋት ኢኮ-ፊዚዮሎጂ፣ በአካባቢ ሳይንስ፣ በብዝሃ ሕይወት አስተዳደር፣ በደን ስነ-ምሕዳር፣ በድርቅ መቋቋም፣ በአግሮ-ፎረስትሪና በዘላቂ የተፈጥሮ ሐብት ቁጥጥር ላይ ያተኮረ ነው። የምርምር ውጤታቸው ከመቶ አርባ በላይ በሆኑ ዓለም አቀፍ የምርምር መጽሄቶች እና የስብሰባ ሕትመቶች የታተሙ ሲሆን በሥራቸው የተለያዩ ሳይንሳዊ የመፍትሔ ሀሳቦችን አቅርበዋል። ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ ከእጽዋት የድርቅ መቋቋም አቅም፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የመኖር፣ የደን ተክሎችን መልሶ ማብቀል፣ የብዝሃ ሕይወት አስተዳደርና የስነ-ምሕዳር ዘላቂነት ጋር የተያያዙ ናቸው።
እስካሁን በቆዩበት ሙያቸው በጀርመን፣ በስዊድን፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ኖርዌይ እና በሌሎች አገራት የሚገኙ ግንባር ቀደም ተቋማትን ትብብር ባካተቱ በአገራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ የገንዘብ ድጋፍ ባገኙ ጥናታዊ የፕሮጀክት ሥራዎች ላይ በመሪነትና በተመራማሪነት ተሳትፈዋል። እነዚህ የትብብር ርዕሶች ድርቅ ተቋቋሚ ማሽላ ዝርያዎች ላይ፣ የእንሰት ሥነሕይወታዊ ባሕሪና የእንሰት አጠውላጊ ባክቴሪያ ላይ፣ የኢትየጵያ የደን ዛፎችን መልሶ ማብቀል፣ የአፍሮ-አልፓይን ሥነ-ምሕዳር እና የተፈጥሮ ሐብት ዘላቂ ቁጥጥርን ያካትታሉ።
ፕሮፌሠር ማስረሻ ከድርጅቶች ለምሳሌ፡- ከጀርመን ምርምር ፋውንዴሽን፣ ዲኤኤዲ፣ ቮልስዋገን ፋውንዴሽን፣ ሲዳ፣ ዩኔስኮና ልዩ ልዩ የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ተቋማት የምርምር ፕሮጀክት ድጋፍ አግኝተዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ በአካባቢያዊና ግብርና ዘርፈ ጥናታዊ ጽሑፍና ምርምር ላይ እንድትታወቅ ረድተዋል።
አማካሪነትና የሰው ሐብት አቅም ማብቃት ማሳደግ
ከፕሮፌሠር ማስረሻ ዘላቂ አብርክቶት መካከል አንዱ ወጣት ሳይንቲስቶችን ለማማከር ያላቸው መሰጠት ነው። ለበርካታ አሥርት ዓመታት በልዩ ልዩ የትምህርት መስኮች፣ ለምሳሌ፡- በእጽዋት ብዝሃ ሕይወት፣ በአግሮ-ፎርስትሪ፣ በአካባቢ ሳይንስ፣ በሰብል ማሻሻል፣ በደን ስነ-ምሕዳርና የአየር ንብረት መላመድ ላይ የሠሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የማስተርስና የዶክትሬት ተማሪዎች አማክረው ለውጤት አብቅተዋል። ከቀድሞ ተማሪዎቻቸው መካከል ብዙዎቹ በኢትዮጵያና በውጭ አገራት የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሠሮች፣ አጥኝዎች፣ የመንግሥት አማካሪዎች፣ የልማት ባለሙያዎችና የሳይንስ መሪዎች ሆነዋል።
በከፍተኛ ትምህርት፣ በጥናታዊ ጽሑፍና ምርምር ሥራ አመራርነት
ፕሮፌሠር ማስረሻ ፈጠነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት እና የድሕረ ምረቃ ዲን ሆነው ሲያገለግሉ ምርምርና የድሕረ ምረቃ ትምህርትን በማሳደግ ሥራ ላይ የባለ ርእይ አመራርነት ስጥተዋል። የምርምር ምክትል ፕሬዚደንት ጽ/ቤቱን እንደ አዲስ አደራጅተው ለጥናታዊ ጽሑፍና ምርምር ቁጥጥር፣ ለዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ማሕበረሰብ አገልግሎት ተጠሪ የሆኑ ዳይሬክቶሬቶችን አቋቁመዋል። የባዮ-ቴክኖሎጂ፣ የኢትዮጵያ ውኃ ሐብት ተቋምና የልማትና ፖሊሲ ጥናታዊ ምርምር ተቋማትን እንዲመሰረቱ አድርገዋል። በዚህም የዩንቨርስቲውን የጥናታዊ ጽሁፍና ምርምር ድባብ በመቀየር ላይ ዋነኛ ሚና ተጫውተዋል። በአመራራቸው የጥናታዊ ጽሑፍና ምርምር ጥራትን፣ የድሕረ ምረቃ ትምህርትና ስልጠናን፣ የፈጠራ ሥራንና የእውቀት ማመንጨት ጥራትን ለማሳደግ አስፈላጊ ተቋማዊ ለውጦችን አምጥተዋል።
በጣም ተጠቃሽ ከሆኑት ውጤቶቻቸው መካከል አንዱ የድህረ ምረቃ ትምህርት መስፋፋትን ማመቻቸታቸው ነው። በእርሳቸው ጊዜ በርካታ አዳዲስ የማስተርስና የፒኤችዲ ፕሮግራሞች የተጀመሩ ሲሆን የዶክትሬት ተመዝጋቢዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። ይህም የኢትዮጵያን ከፍተኛ ትምህርት ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጻኦ አድርጓል። እንዲሁም ጭብጥ ተኮር ምርምርን (Thematic Research) በሚመለከት፤ መመሪያ በማዘጋጀት፣ ለተመራማሪዎችና ለምርምር ቢሮ ኃላፊዎች ስልጠና በመስጠት በተግባር ላይ እንዲውል ፈር ቀዳጅ ሚና ተጫውተዋል።የምርምር ማበረታቻን መመሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ በማውጣትና በማጸድቅ በተመራማሪዎች ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥረዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስና አካዳሚክ ሕትመት
ከ1999 እስከ 2004 እ.ኤ.አ ባለው ጊዜ ውስጥ ፕሮፌሠር ማስረሻ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ዳይሬክተርና ዋና አርታኢ በመሆን አገልግለዋል። በዚህ ኃላፊነት ላይ በነበሩበት ጊዜ በፕሬሱ በሚታተሙ የሕትመት ውጤቶች ላይ ጉልህ የሆነ እድገት በሕትመት ቁጥርና ስብጥር አስመዝግበዋል። በዚህ ወቅት በአንባቢያን ዘንድ እጅግ ተወዳጅና ተፈላጊ የሆኑ ለታሪክ ጥናትና ለህብረተሰብ ምርምር ከፍተኛ አስተዋጾ ያላቸው መጻሕፍት ታትመዋል። የፕሮፌሠር ማስረሻ ጥረት በኢትዮጵያ የምሁራዊ እውቀት ስርጭትና የአካደሚክ ሕትመት እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው።
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ግንባታ
ፕሮፌሠር ማስረሻ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ምሥረታና ዝግጅት ላይ ታሪካዊ ሚና ተጫውተዋል። የሳይንስ አካዳሚ ሀሳብ ለአርባ አመት ያህል የቆየ ቢሆንም አካዳሚውን ማቋቋሙን በኢትዮጵያ ምሁራን መካከል አገራዊ የሳይንስ አካዳሚ እንዲቋቋም ውይይት እንዲካሄድ በማድረግ ያስጀመሩት ፕሮፌሠር ማስረሻ ናቸው። ይህም የአካዳሚውን መመስረቻ መነሻ ሃሳብ (concept note) ከማርቀቅ ጀምሮ ውይይቱ እርሳቸው በፈጠሩት የኢሜይል ግሩፖች በ2001 ዓ.ም አንዲካሄድ በማድረግና ተከታታይ ሰብሰባዎችን በመምራት አገራዊ ኮንፍራንስ በማዘጋጀት፣ በመጨረሻ በ2002 አካዳሚው በኦፊሲኤል እንዲቋቋም ትልቅ አስተዋጾ አድርገዋል።
ፕሮፌሠር ማስረሻ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በ2002 አ.ም በይፋ ሲመሠረት የመጀመሪያው ምክትል ፕሬዚደንት ሆነዋል። በኋላም፣ ከ2006 እስከ 2012 ዓ.ም በሥራ አስፈጻሚነት ያገለገሉ ሲሆን አካዳሚውን ወደ ጎላ እድገትና ተቋማዊ መጠናከር መርተዋል። በዚሁ ጊዜ የአካዳሚውን ዋና ዋና ሳይንሳዊ ፕሮግራሞች ከመምራት ባሻገር፣ አገራዊና ዓለም አቀፍ ኮንፍራንሶችን አዘጋጅተዋል፣ ትኩረት በሚሹ አገራዊ ችግሮች ላይ የስምምነት ጥናቶች እንዲካሄዱ መርተዋል፣ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ግንባር ቀደም አካዳሚዎች ጋር የአጋርነት ስምምነቶች እንዲደረጉ አመቻችተዋል፤ የወደፊት ሳይንቲስት ትውልዶችን ማነቃቃትን ዓላማው ያደረገ በአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነ የሳይንስ ማዕከል እንዲቋቋም አድርገዋል።
አገራዊና ዓለም አቀፍ የሳይንስ አመራርነት
የፕሮፌሠር ማስረሻ አሻራ ከኢትዮጵያ ባሻገር የሰፋ ነው። በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ላይ በአመራር ስፍራዎች ያገለገሉ ሲሆን ሳይንስን፣ ፈጠራንና በመረጃ የተመሠረተ ፖሊሲ አወጣጥን ማጠናከርን ዓላማ ያደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶች አካል በመሆን አገልግለዋል። በአካዳሚ አባልነት በ2002 የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አባልና፣ በ2008 ደግሞ የአፍሪካ ሳይንስ አካደሚ አባል በመሆን ተመርጠዋል። በኋላም፣ በኢንተር-አካደሚ ፓርትነርሽፕ (አይኤፒ)፣ በሳይንስ አካደሚዎች ዓለም አቀፍ መረብ፣ የአይኤፒ ፖሊሲ ጣምራ-ሊቀ-መንበር (Co-chair)) በመሆን በሒደትም የአይኤፒ ጣምራ-ፕሬዚደንት (Co President) በመሆን አገልገለዋል።
በሙያቸው ባገለገሉበት ዘመን፣ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ትብብር በማድረግ በስፋት ሠርተዋል። ከእነዚህም መካከል፡- ዩኔስኮ፣ ሮያል ሶሳይቲ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ናሽናል ሳይንስ አካደሚ፣ የአፍሪካ ሳይንስ አካደሚና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ዪኒቨርሲቲዎችና ጥናትና ምርምር ተቋማት ይገኙበታል። በተለያዩ ድርጅቶች ለምሳሌ በአካባቢ ተቆርቋሪዋች መድረክ ፣ በፎረም ፍር ሶሻለ ስተዲስ -በባሕር ዳር ዩንቨርስቲ የአመራር ቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል። ከተለያዩ ትቋማትም ሽልማቶችን አግኝተዋል።
አበርክቶትና ቀጣይነት ያለው ተጽእኖ
የፕሮፌሠር ማስረሻ ሙያ የሳይንስ ልሕቀት፣ የተቋማዊ አመራር፣ የሕዝብ አገልግሎት አስደናቂ ጥምረትን የሚወክል ነው። በአጥኝነታቸው በእጽዋት ሳይንስ፣ በሥነ-ምሕዳርና በአካባቢ ዘላቂነት ላይ እውቀትን አስፋፍተዋል። በትምህርት ሰውነታቸውና አማካሪነታቸው ቁጥራቸው የበዛ ተማሪዎችን አስተምረዋል። በአካዳሚክ መሪነታቸው፣ በተቋማት ላይ ሁለንተናዊ ለውጥ በማምጣትና የጥናትና ምርምር አቅማቸውን በማጠናከር ላይ እገዛ አድርገዋል። በሳይንስ ጠበቃነታቸው በኢትዮጵያና በአፍሪካ መረጃን መሠረት ያደረገ ውሳኔ አሰጣጥንና የሳይንስ ባሕልን አሳድገዋል።
ማጠቃለያ
ፕሮፌሠር ማስረሻ ፈጠነ ብዙ ሥራዎችን ካከናወኑ የኢትዮጵያ ሳይንቲስቶችና አካዳሚክ መሪዎች መካከል የሚቆሙ ናቸው። ለጥናትና ምርምር፣ ለማስተማርና ለሕዝብ አገልግሎት ያደረጉት የእድሜ ዘመን አገልግሎት በአገሪቱ የሳይንስና ትምህርት መልክዓ ምድር ላይ ዘላቂ ምልክት ትቷል።
በርእያቸው፣ በአመራራቸውና በትጋታቸው ጠንካራ የሳይንስ ተቋማት እንዲገነቡ፣ የወደፊቱ ምሁራን ትውልዶች እንዲሰለጥኑ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው ጥናታዊ ጽሑፍና ምርምር እንዲስፋፋና ሳይንስ በአገር ልማት ላይ ያለውን ሚና በማሳደግ ላይ እገዛ አድርገዋል። አበርክቶታቸው እውቀትንና ፈጠራን ለማኅበረሰብ መሻሻል ለመጠቀም ለሚጣጣሩ አጥኚዎች፣ የትምህርት ሰዎች፣ ተማሪዎችና ፖሊሲ አውጭዎች የሁልጊዜ ማነቃቂያዎች በመሆን ያገለግላሉ።