ጎርፍነህ ይመር

ጎርፍነህ ይመር

በጊዜ ደለል ተውጠውና ቀልጠው እንዳይጠፉ ስንል የአቅማችንን ቆፍረን ከምንዘክራቸው ባለሙያዎች እንዱ ነው። ዝምተኛ፣ ግልጽ፣ የሙያ ስነ-ምግባርን በልኩ ሰፍቶ የለበሰ ፣ሚዛናዊ፣ ፍትሕ የሚወድ እና ብዙ ብዙ ነው ይሉታል የሙያ አጋሮቹና ባልንጀሮቹ የአንጀታቸውን በአንደበታቸው አውጥተው ለዚህ ዕንቁ ባለሙያ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ። ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ለሀገራቸው ከልብ ለሰሩ ባለሙያዎች ታላቅ አክብሮት አለው፡፡ ይህን አክብሮቱንም ለመግለጽ የህይወት ታሪካቸውን በማውጣት ትውልድ እንዲማርባቸው ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ቀደም በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽና በብሎጉ የበርካታ ባለሙያዎችን የህይወት ታሪክ እያፈላለግን ስናወጣ ነበር፡፡ ከእነዚህ ሙያዎች አንዱ ደግሞ የሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሙያ ነው፡፡ ታሪካቸው ተጽፎ መነበብ፣ መደመጥና መታየት ካለባቸው ጋዜጠኞች አንዱ ጋዜጠኛ ጎርፍነህ ይመር ነው፡፡ ጎርፍነህ ብዙ ያልተነገረለት፣ ነገር ግን ብዙ የሰራ ባለሙያ ሲሆን ታሪኩም ለብዙዎች የሚያስተምር ነው፡፡

ይህ ዕንቁ ባለሙያ ታዲያ ከትውልድ ሀገሩ ባሻገር ሰማይ ሰንጥቆ ከጀርመን አለምአቀፍ የጋዜጠኝነት ማሰልጠኛ ተቋም ዲፕሎማ ሲያገኝ በፖላንድና ሌሎች ሀገራትም የጋዜጠኝነት ሙያን ተምሯል። በሙያ ብቃቱ ብቻ በብዙ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ዘመን የማይገረስሰው ጊዜ ደርሶ የማይከሰው ፅኑ ማንነቱን እና አድናቆቱን አትሟል። በስፖርት ጋዜጠኝነቱ ዝነኛ የነበረ ሲሆን ውብ ዜማ በሚያወርደው ድምጹ ፣ ልዩ ስልት ባለውና ሚዛናዊ በሆነው ብዕሩ ያለከልካይ ተደላድሎ ተቀምጧል።

ከስፖርቱ ባሻገር በሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በቀጥታ ተሳትፎ በኢትዮ- ሶማሌና በቀይ ኮከብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ ላይ በግንባር ተሰልፎ በከርከበት፣ አልጌና፣ናቅፋ ሌሎች ግንባሮች ከተባራሪ ጥይት የተረፈ ተስፋን ፣ ከመሳሪያ ፉጨት መካከል የተጨበጠ መረጃን ሰብስቦ ለህዝብ አሰምቷል። አንጋፋው የሬዲዮ ጋዜጠኛ ጎርፍነህ ይመር። ዕዝራ እጅጉና ባንቺአየሁ አሰፋ የጎርፍነህን ታሪክ ከልዩ ልዩ ምንጮች በመውሰድ ታሪኩን አጠንክረው አቅርበውታል ይህ ጽሁፍ በዚህ መልኩ እንዲቀርብ ጋዜጠኛ ቅጣው ንጉሴ ላደረገው ትልቅ አስተዋጽኦ ምስጋናችን ወደር የለውም፡፡

ለኪነ-ጥበብ ዝንባሌ ነበረው

” ማን ይናገር የነበረ

ማን ያርዳ የቀበረ ” ነውና

ስለጋዜጠኛ ጎርፍነህ ይመር የሙያ ባልደረባውና አብሮ አደጉ የአሜሪካን ድምፅ ጋዜጠኛ መለስካቸው አምሃ ከጋዜጠኛ ቅጣው ንጉሴ ጋር ባደረገው ቆይታ እንደተናገረው ጋዜጠኛ ጎርፍነህ በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ በቀድሞው ተፈሪ መኮንን ትምህርትቤት አካባቢ በሚገኝ ኮስትራ በተሰኘ መንደር በ 1946 ዓ.ም ከእናቱ ከወ/ሮ ባጀባ ወልደሚካኤል እና ከአባቱ አስር አለቃ ይመር ይፍሩ ነው የተወለደው ይላል።

ይህ የኮስትራ መንደር ቡቃያ በጋዜጠኝነት ሙያው ላይ ለብዙ ዓመታት በፍቅር ፈሶበታል። ከስሙ ስንነሳም ጎርፉ ሙያዊ ስነምግባርና የስራ ክህሎት ሆኖ በስክነት ሲወርድ ለ3 አስርት ዓመታት ታይቷል። እንደማንኛውም የአዲስ አበባ ልጅ ስፖርት ወዳድ ሲሆን ዳር ቆሞ ከመታዘብ በዘለለ በጨዋታውም ይሳተፍ ነበር። እግርኳስም ይወዳል። በተጨማሪም፣ ለኪነ-ጥበብ ከፍተኛ ዝንባሌ ነበረው። ብዙ ችሎታዎች ያሉት እና ጥሩ ጸሐፊ ከመሆኑ የተነሳ ግልጽ ሀሳቦችን በአጭርና ቀላል ቋንቋ የሚጽፍ ሲሆን በቤተክርስቲያን ዙሪያ (እንጦጦ መካነየሱስ) በሚዘጋጁ ስራዎች ላይ ትልልቅ ገጸ-ባህሪያትን ወክሎ ትያትሮች ይተውን ነበር ይላል አብሮ አደጉ ጋዜጠኛ መለስካቸው አምሃ።

ብስራተ-ወንጌል ተቀጠረ

ፍልቅልቁ እና ትንታጉ ጎርፍነህ ይመር፣ የሀገራችን ኢትዮጵያ የረዥም ዘመናት ዘውዳዊ የአገዛዝ ስርዓት ግብአተ- መሬቱ ተፈጽሞ አብዮታዊ ወታደራዊ ስርዓቱ ዙፋን ለመቆናጠጥ በሚያደርገው ትንቅንቅ ወቅት 1966 ዓ.ም ነበር የ 12ኛ ክፍል ትምህርቱን ያጠናቀቀው ። ፈተና ወስዶ ብዙም ሳይቆይ የእንጦጦ መካነ-የሱስ አባልና ተሳታፊም ስለነበር የብስራተ- ወንጌል ሬዲዮ ጋዜጠኞችን መልምሎ ስልጠና ለመስጠት ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት በቀላሉ ተፈትኖ ለስልጠናው አለፈ፡፡ ለ2 ወራት ያህልም ስልጠናውን ወስዶ ከፍተኛ የመመረቂያ ስራን ከሰሩት መካከልም አንዱ ነበር። በተዋረድ የመጡትን ምርጫዎች አልፎ በቀድሞው ብስራተ-ወንጌል ( Middle wave) በአሁኑ FM ተብሎ በሚጠራው የምስራች ድምፅ ሬዲዮ በ 1967 ዓ.ም በጋዜጠኝነት ሙያ ተቀጠረ ። በዚህ ሬዲዮ እንደ እድገት በህብረት ዘመቻ ያሉ ወቅታዊና ሀገራዊ ዜናዎችን በማንበብ፣ ስፖርት እና ሌሎች በርካታ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት፣በአጭር ጊዜ ውስጥ በፍጥነት የገሰገሰ ባለሙያ ነበር።

በበርካታ ቋንቋዎች በአለምአቀፍ ደረጃ በሰፊው ይሰራጭ የነበረው ብስራተ- ወንጌል በደርግ መንግስት እስከተወረሰበት 1969 ዓ.ም ወርሀ መጋቢት ገደማ ድረስ አገልግሎ በኋላ የኢትዮጵያ ሬዲዮን ሊቀላቀል ችሏል። በኢትዮጵያ ሬዲዮ በሪፖርተርነት ፣ በስፖርት ፣በመዝናኛ እስከ ኃላፊነት ደረጃ ድረስም አገልግሏል።

ቆይቶም በ 1992 ዓ.ም FM ADDIS 97.1 ሲቋቋም በመጀመሪያ ምክትል አስተባባሪ ቀጥሎም ዋና አስተባባሪ በመሆን ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለየበት መጋቢት 8 1999 ዓ.ም ድረስ ለ 32 ዓመታት በሙያው አገልግሏል። በዚህ የአገልግሎት ዘመኑ ከስታዲየም እስከ ጦር ግንባር ከቤት እስከ አደባባይ ብራናውን ዘርግቶ ብዕሩን ወድሮ በየመስኩ ፣ በየበረሃው ፣ ቆላ ደጋውን በስራው ተሰማርቷል። ወቅታዊ መረጃዎችን በቅርበት ለህዝብ አቀብሏል። እንደ ኃላፊነት በአለቃነትና እንደ ሙያ በጋዜጠኝነት ሰርቷል።

አያጋንንም

የሙያ አጋሩና የቀድሞው የጠረጴዛ ኳስ ተጫዋቹ የሔራልድ ጋዜጠኛ የነበረው ሰለሞን በቀለ ከጎርፍነህ ይመር ጋር የነበረው ትውውቅ ከ 1979 ዓ.ም ወዲህ እንደሆነ ለፍቅር ቤት ቲዩብና ለጋዜጠኛ ቅጣው ንጉሴ ገልጾ ስለ ጎርፍነህ እንዲህ ሲል አክሏል ፣ ‹‹….ጎርፍነህ የሙያ ልምዱን ለሌሎች የሚያጋራ ፣ ነገሮችን የማይረሳ የማስታወስ ችሎታው የሚደንቅ ፣ የሚፈልገውን ወይም ሊናገር ያሰበውን በግልጽ የሚያስረዳ ፣ ለስራው ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ፣ ጽሑፎቹ ምስል መከሰት የሚችል አቅም ያላቸው ሲሆኑ ጨዋታ ምን ላይ እንደደረሰ ለማወቅ ከተፈለገ ቴሌቪዥን ከማየት ይልቅ ጎርፍነህን መስማት ግልጽ እንዲሆን ያግዛል። መረጃዎችን እያጣቀሰ ሲናገር ስለ ስፖርት ተጨባጭ የሆነ እውቀት ለመያዝ ይረዳል። ሚዛናዊ ነው። አያጋንንም ። እርሱ የትኛውም ቦታ ላይ ቢቆም ወገንተኛ አይደለም። እንደሙያ ማስተላለፍ ያለበትን ያስተላልፋል የትም ቢሆን ጋዜጠኛ ነው›› ሲል ሰለሞን ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡

እ.ኤ.አ. በ 2000 ሲድኒ ላይ በተካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮን ላይ ተገኝቶ የሰራው ዘገባ በስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ የማይዘነጋ ነው። በየቤቱ ቡና እየጠጣ ፣ በአውቶቡስ ተሳፍሮ እየተጓዘ እያለ ሲዲኒ ላይ ከተገኘው የስፖርት ቤተሰብ እኩል ጨዋታውን ለመታደም ችሎ ነበር። ጎርፍነህ ምንምኳን በስፖርቱ ዘርፍ የሚታወቅ ቢሆንም ሁለገብ ባለሙያ መሆኑ ግን አይዘነጋም። በኢኮኖሚው ዘርፍ የሰራቸው ስራዎቹ እስካሁን ከአእምሯችን አልጠፋም የሚሉ ባለሙያዎችም አሉ።

ጎርፍነህ በቀይ ኮከብ ዘመቻ

እርሱ በርካታ ቁምነገር ያዘሉ ፕሮግራሞችን ፣ መዝናኛዎችን አዘጋጅቷል ። ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ዳጎስ ያለ መረጃን ይዞ ሰፋፊ ትንታኔዎችን አቅርቧል። ጥሩ ድምፅ ያለው ዜና አንባቢም ነበር። የራሱ የሆነ የሥነጽሑፍ ስልት እና የአሰራር ብልሀትም አለው ይባልለታል ጋዜጠኛ ጎርፍነህ ይመር።

በ 1970ዎቹ መጨረሻ በጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ መሪነት በቀይ ኮኮብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ ወቅት በተደረገው የጋዜጠኞች ዘመቻ ከተሳተፉት መካከል አንዱ ነበር ጎርፍነህ ይመር ። በወቅቱ በዘመቻው ላይ አብሮት የተሳተፈው ጋዜጠኛ ታደሰ ገ/ማሪያም ከቅጣው ንጉሴ ጋር በነበረው ቃለ-መጠይቅ ስለ ዘማች ጋዜጠኛ ጓዱ ሲናገር ከጎርፍነህ ጋር ያልወጡት ተራራ ያልወረዱት ቁልቁለት ያልተሰለፉበት ግንባር እንደሌለ ያነሳል። በሁለቱ መንግሥታት ማለትም በደርግና ኢህአደግ ወቅት በተደረጉ አውደውጊያዎች ሁሉ የራሱ የሆነ የጦር ሜዳ ሚና ያለው ጋዜጠኛ ሲሆን ከታደሰ ጋር በመሆን በአልጌና ፣ከርከበት ፣ በአቆርዳት እና ናቅፋ ማዘዣ ጣቢያ የጦር ግንባር ላይ በመሳተፍ የዜና ሽፋን ሰጥቷል።

በማህበራዊ መሰረተልማት የመስክ ስራ ላይም በመዘዋወር የዘገበ ሲሆን በትላንቷ የሀገራችን ሰሜናዊ ክፍል በአሁኗ ሀገረ- ኤርትራ ብዙ ቦታዎች ላይ የእግሮቹ ዱካዎች እትም አሉ። በራሱ ተነሳሽነት ኤርትራውያን በወቅቱ ስለነበረው ጦርነት የተሰማቸው ለማወቅ ሲል በገበያ ስፍራ ፣ ሰው በተሰበሰበበት ከታደሰ ጋር በመሆን የህዝብ አስተያየት ሰብስበዋል። በዚህም ከአለቃቸው በዓሉ ምስጋና እንደተቸራቸው አይዘነጉም።

ስራውን በዘፈቀደ አሊያም በአቦ ሰጥ ሳይሆን አስቦ አሰላስሎ በትኩረት የሚሰራ ለመሆኑ ማሳያ የሚሆነው ከጋዜጠኛ ታደሰ ገብረማርያም ጋር አብረው የሰሩትን ለቅጣው እንዲህ ያስተውሳል ” በሀገሪቱ ትልልቅ የሆኑ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ የጋዜጠኛ ስምሪት ሲደረግ እኔና ጎርፍነህ አብረን ነበርን። ታዲያ ትልቁ የሸበሌ ወንዝ መልካዋከና ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀት ሲመረቅ የዜና ሽፋን ለመስጠት ስንሄድ በሰነዘርናቸው የተደራጁ ጥያቄዎቻችን ምክንያት እንዲህ ያለ መልስ ለማግኘት መቻላችንን አልዘነጋውም ይላል። ነገሩ እንዲህ ነው ይህን ፕሮጀክት ለመገንባት ያስጠኑት ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ሲሆኑ አጥኝው ደግሞ አንድ የፈረንሳይ ኩባንያ ነበር። ደርግ ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል ከአለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ይጠይቃል። ታዲያ የአለም ባንክን ዘወትር በሚዘውሩት ኃያላኑ ሀገራት አዙሪት ሳቢያ ገንዘቡን ኢትዮጵያ ማግኘት ከፈለገች ወንዙ ድንበር ተሻጋሪ ነውና ከሶማሊያ ጋር ስምምነት ትፈጽም ካልሆነ ገንዘቡን እርሱት አለ። የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ያለመደብንን እንዴት? አልደራደርም ሲል መራር ሀሞቱን ዋጠ። ከሶቪዬት ህብረት በረዥም ጊዜ የክፍያ አማራጭ ተጠቅሞ ፕሮጀክቱን ጨርሶ አስመረቀ። ጉዟችንም በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ዜና ለመስራት ነበር ” ይላል። እንግዲህ አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል ማለት ይህ ነው።

ያላየው የጦር ግንባር የለም የሚባልለት አንጋፋው የሙያ ሰው ጎርፍነህ ይመር ከቀይ ኮከብ ዘመቻ በተጨማሪ በኢትዮ ሶማሌ ጦርነት ጊዜ ከወታደሩ ጋር ግንባር ድረስ ገስግሶ በርካታ ዘገባዎችን ሰርቷል። ውድቀትና ድል ፣ ዕድልና ገድል አብረውትም ነበሩ። ከወታደሩ እኩል በርካታ ስቃይና እንግልቶችን አሳልፏል። ለወራቶች መሳሪያ እና እሳት እያፏጨበት የወታደሩን አካሄድና የጦርነቱን ሁናቴ በዘገባ ሰርቷል። በስራዎቹም የራሱን ቀለምና አሻራ አሳርፏል። እዚህ ቦታ ብለው ሊመድቡት የማይቻል ሁሉንም የሆነ ባለሙያ ነው። ምንምኳን እንጨት ሆኖ ከጭስ ፣ ሰው ሆኖ ከስህተት ፣ ብረት ሆኖ ከዝገት የጸዳ ባይኖርም በተቻለው አቅም ግን ህይወትን በቀላል መንገድ የሚፈልግ ስለስራው አብዝቶ የሚጨነቅ ስለራሱ እንዲህ ነኝ ብሎ የማይናገር ውሸትና ማጋነንን አብዝቶ የሚጠላ ፍትሕን ፈላጊ ነው ይሉታል ወዳጆቹና አድናቂዎቹ።

ቁምነገረኛ

ጎርፍነህ ፣እጅግ በጣም ግልጽ በወሬ ሳይሆን በተግባር የሚኖር ባለሙያ ነው። የለበሰውን አውልቆ የሚሰጥ ተጫዋችና ቁምነገረኛ እንኳን ተጫውቶ ስቆ ሳቁ ያስቃል ይላሉ። በሙያው ሰርቶ ህይወቱን ማሸነፍ እንጂ በተለያዩ ጉዳዮች እጆቹን ሰዶ ጥቅም የሚያሳድድ አልነበረም። በስራ ዘመኑ ሁለት መንግስታትን ያየ ሲሆን ከየትኛውም ፖለቲካዊ አጀንዳ ጋር እራሱን አያያይዝም። በሙያው ከሚሰጠው እድገት ጋር ተያይዞ ለሰዎች ጀርባ የማይሰጥ ፣ በራሱ መንገድ ከሁሉም ሰው ጋር አብሮ የመኖር አቅም ያለው ፣ የሰዎችን አቅም በአንክሮት አይቶ ያላቸውን ውስጣዊ አቅም የሚያውቅ ነው። ግብዝነት የሌለበት ፍትሐዊነትን ከልቡ የሚወድ የሙያ ሰውና በሙያውም ሚዛናዊ ነው ሲሉ ወዳጆቹ ይስማሙበታል። ለዚህም አርካይቭ ውስጥ የሚገኙ ስራዎቹ ህያው ምስክሮች ናቸው።

ጋዜጠኛ ጎርፍነህ ይመር በብስራተ ወንጌል የጀመረው የጋዜጠኝነት ሙያ በስነምግባርና በሙያ ብቃት እየካበተ ሄዶ በሪፖርተርነት ፣ ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢነት ፣ ዜና አንባቢነት ፣ ትልልቅ የመስክ ላይ ፕሮጀክት ተሳታፊነት እና ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ድረስ በሙያው ሀገሩንና ህዝቡን በብዙ ዘርፍ እንዲያገለግል እድል አመቻችቶለታል። FM ADDIS 97.1 በሰዎች ዘንዳ እስካሁን ተወዳጅ ሆኖ እንዲዘልቅ የራሱን ያላሰለሰ አስተዋጽኦ አድርጓል። ማንነቱ ከጨለማ በገዘፈ ዝምታ ውስጥ ተውጦ እንደሻማ እየቀለጠ ለትውልድ ሲያበራ ቆይቶ አልፏል። ሲያነብ ያገኛቸውን ቁልፍና ጠቃሚ ሀሳቦች ለይቶ በመያዝ የሚገለገልበት ሲሆን የድምፅ አወጣጥ ውበቱ በልምድና በንባብ የተገራ ነው የሚሉም አሉ።

የጎርፍነህን የመጨረሻዎቹ ጊዜያት

የጎርፍነህ ባለቤት ወይዘሮ ጸሀይ ጸጋዬ ለዚህ ህይወት ታሪክ አዘጋጅ እንደተናገረችው ጎርፍነህን ያወቀችው ያወቀችው ከዛሬ 40 አመት በፊት ሽሮ ሜዳ ነበር፡፡ ከዚያም ጎርፌና ጸሀይ ትዳር መስርተው ሁለት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ቤዛ ጎርፍነህ እና አደይ ጎርፍነህ፡፡

ወይዘሮ ጸሀይ ጎርፍነህን ስትገልጸው ሙያውን ከልብ የሚወድ ህመም ቢሰማው እንኳን ስራ ከመሄድ የማይቦዝን ታታሪ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቤት ሆኖ እንኳን ሬድዮ እያደመጥ ይህ እንዲህ መሆን የለበትም በማለት ስራዎች በትክክለኛው መንገድ እንዲሰሩ ያደርግ እንደነበር ጸሀይ ትመሰክራለች፡፡

ጸሀይ ባለቤቷ ሙያውን ከልብ እንደሚወድ እንጂ በምን ጉዳይ እንደሚበሳጭ እንደማታውቅ ትናገራለች፡፡ ይሁንና በስራ ሁኔታው አልፎ አልፎ በስጨት የሚልበት አጋጣሚ እንደነበር አትዘነጋውም፡፡

ባለቤቱ ጸሀይ ፣ የጎርፍነህን የመጨረሻዎቹ ጊዜያት ስታስታውስ ጨጓራውን አሞት ነበር ትላለች፡፡ ከዚያም የህክምና ባለሙያዎች በሰጡት መረጃ መሰረት የሀሞት ከረጡት እንዳለበት ተነገረው፡፡ ከዚያም በጥቁር አንበሳና በሌሎችም የህክምና ተቋማት ህክምና ተከታትሎ መጋቢት 8 1999 በ53 አመት እድሜው ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል፡፡

ባለቤቱ ፀሀይ ፀጋዬ ጎርፍነህ ህይወቱ ባለፈ ጊዜ ከጎኗ የነበሩ የጎርፍነህን ወዳጆች ማመስገን ትሻለች፡፡ በተለይ አይዞሽ ጎርፍነህ ቢያልፍም እኛ አለን በማለት በሁለንተናዊ ድጋፍ ያልተለዩ ሰዎችን ማመስገን ትፈልጋለች፡፡

እነርሱም መለስካቸው አምሀ ፣ሰለሞን በቀለ፣ ቴዎድሮስ በቀለ፣ ግርማ ነጋሽ ፣ ጸጋ ቁምላቸው ፣ ሰሎሜ ደስታ ፤ ቅጣው ንጉሴ ፣ አበበ ፈለቀንና ይፍቱስራ ቱጂን ማመስገን ትወዳለች፡፡

ይንበርበሩ ምትኬ ስለ ጎርፍነህ ይመር የሰጠን ምስክርነት

ጎርፍነህ ይመርን የማውቀው ገና ተማሪ ሳለ ነበር፡፡ ትዝ እንደሚለኝ ሁለ-ገብ እውቀትን የታደለ የሙያ ሰው ነበር፡፡ከስፖርት ባሻገር የተለያዩ ማህበራዊ ፕሮግራሞችን በመስራት ይታወቃል፡፡ ጎርፌ አመለካከቱ በጣም መጠቅ ያለ ለሰው ልጅ ትልቅ አክብሮት ያለው ነው፡፡ 32 አመት በዚህ ሙያ ሲያገለግል ብዙዎቹ መመስከር ይችላሉ- ጎርፌ ታላቅ ጋዜጠኛ ነው፡፡ አንድን ፕሮግራም በቀጥታ ስርጭት ላይቭ ሲሰራ ይችልበታል፡፡ ጎርፍነህ የተሰማውን ፊት ለፊት በመናገር ይታወቃል፡፡ መለማመጥ የሚሉትን ነገር ብዙም አያውቅም፡፡ቢሆንም ግን የምንረዳው ሰዎች እንረዳዋለን፡፡ ጎርፍነህ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ በቀላሉ የማይፋቅ አሻራ ያኖረ በተለይ ደግሞ ለኤፍኤም አዲስ 97 ነጥብ አንድ ትልቅ መሰረት ያኖረ ነው፡፡ ለዚህም ያለኝን ትልቅ አክብሮት ገልጻለሁ፡፡ ነፍሱን በገነት ያኑር፡፡

ቅጣው ንጉሴ ስለ ጎርፍነህ ይመር

ጋዜጠኛ ጎርፍነህ ይመርን የማውቀው ከ1981 ዓ/ም በፊት እንደብዙው አድማጭ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የስፖርት ዘገባዎችንና ብሔራዊ ቡድናችን ከሌሎች አገሮች ጋር ሲጫወት በቀጥታ ስርጭት ሲያቀርብ ነው። በ1981 ዓ/ም አ.አ.ዩ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ እያለሁ ቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም ላይ ለመሳተፍ ስመላለስ በአካል አወቅኩት፡፡ በ1992 ዓ.ም በኤፍ ኤም 97 ነጥብ አንድ ምስረታ አካባቢ ተወዳድሬ ተቀጥሬ ስገባ የጣቢያው ም/አስተባባሪ አለቃዬና ኤዲተሬ ሆኖ በደንብ የማወቅ ዕድል ገጠመኝ። አንባቢ በመረጃ የተሞላ ጋዜጠኝነትን ከስሜት ውጪ በመሆን መስራት ብቻ ሳይሆን በተግባር እየሰራ የሚያስተምር አስደማሚ የማስታወስ ችሎታ ያለው ታላቅ ወንድም ነበር። ራሱን ማስተዋወቅ የማይፈልግ ነገር ግን ወጣት ጋዜጠኞች ወደፊት እንዲመጡ የሚታገል ነበር። በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለይ የስፖርት ጋዜጠኞች የሙያ ስነምግባርን ከእርሱ ቀስመዋል። ለእኔም አርአያና መካሪ ታላቅ ወንድም ነበር።

ሰሎሜ ደስታ ስለ ጎርፍነህ ይመር

‹‹መጋቢት 8 ቀን 1999 ዓ.ም ለሽሮሜዳው ልጅ፣ ለረጋው የስፖርት ዘጋቢ፣ የአማርኛ ቋንቋ ክፍል የፕሮግራም ኃላፊ በነበረ ጊዜ አለቃዬ፤ ለኤፌም አዲስ 97.1 አጋሬ፣ ለልጆቹ የሚንሰፈሰፈው፣ ባለቤቱ ፀሐዬን ጠርቶ ለማይጠግበው፤ ዳማ መጫወት እጅግ ለሚያፈቅረው ትሁቱ ጎርፍነህ ይመር ሙሉ ቀን አልነበረም፡፡ ለቤተሰቦቹና ለእኛም ጎርፌ ጎድሎ አጎደለን፡፡

ቀኑ ደግሞ ቅዳሜ ወደ ዘጠኝ ሠዓት ተኩል ገደማ ነበር፡፡ በኢትዮጵያን ኮንስዩመር ፕሮቴክሽን አሶሴሽን ጽ/ቤት የቦርድ ስብሰባ ላይ ነበርኩ፡፡ ምናላቸው ስማቸው ደወለልኝ፤ ሠላምታውንና የደወለልኝ ሠው እንደነበር ለማረጋገጥ ያቀረበውን ጥያቄ አከታትሎ ተናገረ፡፡ ማንም እንዳልደወለልኝ ስነግረው ‹‹ጎርፌ ሆስፒታል መግባቱን ታውቂ ነበር?›› ሲል ጠየቀኝ ‹‹አላውቅም ምን ሆነ ብዬ?›› ከመቀመጫዬ ተነሳሁ፡፡ መደንገጤን የተረዳው ምናላቸው ‹‹አሞት ሆስፒታል ነው ብለውኝ ነው አረጋግጬ እደውላለሁ›› ብሎ ስልኩን በፍጥነት ዘጋ፡፡

ጥያቄው ግን ‹‹ሆስፒታል ገብቶ ነበር፤ አረፈ›› የሚል መልዕክት ያላው ሆኖ በማግኘቴ ማልቀስ ጀመርኩ፤ ስብሰባው ተቋረጠ፡፡ አብረውኝ የነበሩት ሠዎች ወደ ምናላቸው ስልክ ደወሉ፡፡ ድንጋጤዬ ስላስደነገጠውና እቅጩን ለመናገር መቋቋም ስላቃተው እንጂ ‹‹አርፏል ወደቤት ውሰዷት›› ሲል አሳወቃቸው፡፡ በጎርፌ የመጨረሻዎቹ ሠዓታት አብሬው ባለመሆኔ ባስታወስኩት ቁጥር እጅግ ይቆጨኛል፡፡

እሱ የዘገበውን የሲድኒ ኦሎምፒክ አሁንም ድረስ ሌላ ሠው እንደዘገበ ተደርጎ ሲጠራ ስሰማ በቲፎዞ መውደድና በቲፎዞ መጥላት በተለመደበት የእኛ ሀገር የሚጠበቅ ነው በማለት ለፈጣሪ እተወዋለሁ፡፡

ጎርፌ ስሜተኛ አይደለም፡፡ በሳል የስፖርት ዕውቀቱና የማስታወስ ችሎታው ልዩ ነው፡፡ የኤፍኤም አዲስ 97.1 ልጃችን ዳግማዊ ታሪኩ የሚዲያ የፈጠራ ችሎታ ካበረከታቸው ትሩፋቶች አንዱ የጎርፌን የስፖርት ትንታኔና ግምገማ ችሎታ ያወጣበት ነበር፡፡ ዛሬ በተለያዩ መረጃዎች እንደሚነገረው የስፖርት ትንታኔን የጀመረው ፍስሀ ተገኝ አልነበረም፡፡ ዳግማዊ ተረኛ ሆኖ የዕለቱን ስርጭት ሲመራ እንደ እንግዳ ይዞት ገብቶ ትንታኔ እንዲሰጥ ያደርገው ነበር፡፡ ይኽ አቀራረብ እየተወደደ ሲመጣ በሌሎች አስተናጋጅ ተረኞች ወቅትም ዳግማዊ ጥያቄውን ይዞ ጎርፌን ለትንታኔ መጋበዙ ፈር ቀዳጅ ነበር፡፡

ጎርፌ በሌሎችም ጉዳዮች የታሪክ አርካይቭ ባለቤት ነበር፡፡ ቀልድ ያውቃል፡፡ ነገሮችን በማስታመም ለመያዝ ይሞክራል፡፡ እኔ በቀጥታ አካፋን አካፋ ስል እሱ ደግሞ አካፋውን አካፋ ለማለት ምሳሌ ያበዛል፡፡ ነገሮችን በመሳቅ ለማለፍ ይሞክራል፡፡ ነገሮችን ለማለዘብ የሚያደርገው ግን ስሜቱን በውስጥ በማመቅ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በተለይ የ97 ምርጫን ተከትሎ በእጅጉ ጎድቶታል፡፡ ያላደረገውን ተግባር እንዳደረገ በማድረግ የሕይወት እንጀራ በሰጣቸው ጥርሶች ተነክሷል፡፡ አስረድቶ ለማሳመን ዕድሉን የሰጠው የለም፤ ‹‹ሞቱ አሳዝኗቸው እግዚአብሄር ያጥናችሁ አላሉም›› ፡፡

ዛሬም ድረስ የዘለቀውና ኢህአዴግ በዘረጋው የመዋቅር ጥናትና ድልድል ሽፋን በተደረገው ምደባም በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ሬዴዮ የፕሮግራሞች ኃላፊ፤ እንዲሁም የኤፍኤም አዲስ 97.1 ጣቢያ ም/አስተባባሪ ለሆነው ጎርፌ የተሰጠው የሥራ ደረጃ የኢትዮጵያችን የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ማሳያ ነው፡፡ ተናግሮ ያልወጣለት ጎርፌ በእነዚህ ምክንያት ስሜቱን አምቆ በአገራችን አባባል ቆሽቱ አሮ በተፋጠነ በሽታ ሊለየን ቻለ፡፡ ቤተሰቡንና እኛ ወዳጆቹን የሚያሳዝነንም ይኸው ነው እንጂ በተወለድን ቀን እንደምንሞትና ማንም ከዚህ እንደማይቀር ይታወቃል፡፡

ፍቅሩን ያልጠገቡት፤ አሁንም ድረስ እንደልጅነታቸው ሲጠሩት ‹‹አባቱ›› የሚሉት ሕጻናት ልጆቹ አድገው በተለይ ሊሊዬ ተምራ ዲግሪዋን የያዘች ዕለት ግን ጎርፌ እንዳልሞተ እራሴን አሳመንኩ፡፡ ዛሬም ግን ተመልካች ቢያገኙ የዚህ በስፖርቱ እና በሚዲያው ዘርፍ አሻራውን ያሳረፈው ጎርፍነህ ይመር ልጆች ማረፊያቸው እንዲሟላላቸው ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ጎርፌ ተወልዶ ያደገበትና በውርስ የወሰደው የቤተሰቡ ቤት ከሽሮ ሜዳ ወደ እንጦጦ ኪዳነምህረት የሚወስደው የማስፋፊያ መንገድ ሲሰራ ፈርሷል፡፡ በምትኩ ገደል ላይ ያረፈ ቦታና አነስተኛ የገንዘብ ግምት ቢሰጣቸውም መሬቱን ለማስተካከል ወይም ረጅም ‹ቤዝመንት› ለማሰራት እንኳን የማይበቃውን ገንዘብ ይዘው ከአምስት ዓመት በላይ በኪራይ ቤት እንዲቀመጡ ተገደዋል፡፡ ጎርፌን ለማስታወስና ለመዘከር የቤተሰቡንም የመኖር ዋስትና ማመቻቸት ከሁሉም የሚጠበቅ ነው፡፡ ያኔ ነው ሲታወስ ይኖራል የሚለው መረጃ ተሟላ የምንለው፡፡››

ሰሎሜ ደስታ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ባልደረባና የኤፍኤም አዲስ 97.1 የመጀመሪያ አስተባባሪ የነበረች

ይፍቱስራ ቱጂ ስለ ጎርፍነህ ይመር

ጎርፍነህ ይመር በየፕሮግራሞቹ ላይ አስተያየት ይሰጣል። ሳይቆጣ በእርጋታ ምክር ይለግሳል። የሚበረታታውን ያበረታታል። በሚሰራው ፕሮግራም ላይ በጋዜጠኞቹ እምነት ሲያድርበት ደግሞ የራሳቸው ፕሮግራም አርታኢ እንዲሆኑ በተዘዋዋሪ ኃላፊነት ይሰጣል። ጋዜጠኛውም ስራውን በጥንቃቄ እንዲሰራ ያግዘዋል።

ኤልሳቤጥ ሳሙኤል ስለ ጎርፍነህ ይመር

ጋሽ ጎርፍነህ በጣም ጥሩ የሚባል አለቃ ሁላችንንም እኩል የሚያይ አለቃ ነበር፡፡ የኤፍ ኤም አዲስ 97 ነጥብ አንድ ሃላፊ በነበረ ጊዜ አንድ ጋዜጠኛ የራሱን እምቅ አቅም እንዲያወጣ የሚጥር መልካም አለቃ ነበር፡፡ ጋሽ ጎርፍነፍ ጥሞና ሰጥቶ የሚያዳምጥ በሳል ሰው ነው፡፡ ጋዜጠኛውንም የት ወጣህ የት ገባህ ብሎ የሚያጨናንቅ ሳይሆን ስራን ብቻ ማእከል አድርጎ የሚያሰራ መሪ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

ቤዛ ጎርፍነህ ስለ አባቷ

አባቴ ማለት ለእኔ በጣም መልካም አባት ፤ በስስት የሚያየኝ ማለት ነው፡፡ አሁን ግን የለም፡፡

አደይ ጎርፍነህ ስለ አባቷ

አባታችን በጣም መልካም ሰው ነው፡፡ በህይወት ውስጥ መልካም ነገሮችን ብቻ ነው የሚመለከተው፡፡ ታሞ እንኳን ስለስራው አብዝቶ የሚጨነቅ ሰው ነው፡፡ አባቴ ለራሱ ምንም ያልኖረ ነው፡፡ ትንሽ ቆይቶ የሚፈልጋቸው ነገሮች ተሳክተው ብናይ ደስ ይለኝ ነበር፡፡

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አዕምሮ የመማክርት ቡድን አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ የጋዜጠኛ ጎርፍነህ ይመርን የህይወት ታሪክ በጽሑፍ ለመሰነድ የሚረዳንን ግብዓት በቀላሉ እንድናገኝ የረዳንን የፍቅር ቤት ቲዩብና ጋዜጠኛ ቅጣው ንጉሴን በባለ ታሪኩና በተወዳጅ ሚዲያ ስም እያመሰገንን ታሪኩን እንዲህ እናሳርገው። የሰው ልጅ አፈር ነህና ወደአፈር ትመለሳለህ የተባለ ቢሆንም ስም ግን አይሞትም ይባላል ። ህያው የሚያደርገው አንድ ነገር አለና። ይኸውም ስራው ነው። በጎ የሰራም በበጎ ነገሩ ህያው ሆኖ ይኖራል፡፡ ጋዜጠኛ ጎርፍነህ ይመር በህይወት ዘመኑ በበጎነት ህያው የሚያደርገውን የእረፍተ ስራ ሰርቶ ለትውልድ ቀለሙን ትቶ አልፏልና በስፖርት አፍቃሪዎችና በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ከሞት የላቀውን ህይወት ያገኘ ባለሙያ ነው። በተለይ በስፖርት ጋዜጠኝነት ዘርፍ በቀላሉ የማይዘነጋ ቀለም ያኖረ ሰው ነው፡፡ ጎርፍነህ ይመር ህይወቱ ካለፈ 15 አመት አለፈው፡፡ ነገር ግን ስለ እርሱ ምን ያህል ሚድያዎች ዘግበዋል ብንል ቁጥሩ ትንሽ ነው፡፡ እኛም ከተወቃሽነት የማንድን ቢሆንም አሁንም አልረፈደምና የኢትዮጵያ የሚድያ ሰዎች በሚዘከርበት አለም አቀፍ የመዝገብ ዝርዝር ውስጥ ጎርፍነህን አካተነዋል፡፡ መዝገበ-አዕምሮ የሚድያ ሰዎች ታሪክ ቅጽ 2 ላይ የጎርፍነህ ይመር ታሪክ ይነበባል፡፡

እኛ እንደተወዳጅ ሚድያ አሻራ ያኖረና ጥሩ ምስክርነት ያለው ባለሙያ ታሪኩ በዝርዝር ቢጻፍ ደስ ይለናል፡፡ ደስ ይለናል ብቻ ሳይሆን የድርጅታችንም አላማ ይህ ነው፡፡ ጋሽ ጎርፍነህ በእኩያ ባልደረቦቹና በታናናሾቹ በበጎ መልኩ የሚገለጽ ብዙዎችን ለስኬት ያበቃ ነገር ግን ይህ ሁሉ ብዙም ያልተወሳለት ሰው ነው፡፡ እኛ እንደተወዳጅ ሚድያ ጎርፍነህን እናክብር በሚል አንድ እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ የጎርፍነህን ህይወትና ስራ ለአዲሱ ትውልድ የሚያሳውቅ ሲሆን መድረኮችንም አዘጋጅተን የእዚህን ታላቅ ሰው ስም ከፍ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተዘጋጅተናል፡፡ የጎርፍነህን አየር ላይ የዋሉ መሰናዶዎች፣ በተለያዩ ጊዜ የተነሳቸውንም ምስሎች በዚህ ህይወት-ታሪክ ጽሁፍ ውስጥ አካተናል፡፡ተጨማሪ አስተያየት ያላችሁና ታሪኩ ላይ ማከል የምትፈልጉ በኢንቦክስ ላኩልን፡፡ ታላቅ ክብር ለጋሽ ጎርፍነህ / ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ እና በባንቺአየሁ አሰፋ የተሰናዳ ነው፡፡ዛሬ ሰኞ ግንቦት 29 2014 አ.ም በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ እና ብሎግ ላይ ይህ ህይወት ታሪክ ወጣ፡፡ ይህን ጽሁፍ እንድንጽፍ ትልቅ እገዛ ላደረገልን ለቅጣው ንጉሴ ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *