ጋሽ ሀይሌ ገብሬ እንኳን ለ71 ኛ አመትዎ በሰላም አደረስዎ

ሀይሌ ገብሬ

ተወዳጅ የሚድያና የኮሚኒኬሽን ማእከል ለሀገር ውለታ የሰሩ ሰዎችን የልደት ቀን ምክንያት በማድረግ በማህበራዊ ሚድያ ከ300 ቃላት እስከ 400 ቃላት በሚሆን መልኩ ስለ ባለልደቱ ይጽፋል፡፡ አሁንም የድርጅታችን ተባባሪና ደጋፊ የሆኑት ጋሽ ሀይሌ ገብሬ በዛሬው እለት 71ኛ አመታቸውን በማክበራቸው እንኳን ደስ አለዎ ማለትን እንወዳለን፡፡ ……..

በእለተ-ፋሲካ ፣ሚያዝያ 23 1940 ይህም ሲባል የዛሬ 71 አመት የተወለዱት አቶ ሀይሌ ገብሬ በዛሬው እለት ሚያዝያ 23 2010 71ኛ አመታቸውን ይዘዋል፡፡

ጋሽ ሀይሌ ገብሬን ያወቅኳቸው ከ19 ቀን በፊት ነበር፡፡ ዛሬ ቃለ-መጠይቅ ባደረግኩላቸው ቀን 71ኛ አመታቸውን ያከብሩ ነበርና ለምን በተወሰኑ ቃላት እኒህን ሰው አልገልጻቸውም? ስል ወሰንኩ፡፡

ጋሽ ሀይሌ በመንግስት ስራ ውስጥ በተለይ ደግሞ በሀገራችን የህብረት ስራ ዩኒየኖችን በመምራት ሚና አበርክተዋል፡፡ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከዛሬ 25 አመት ቀደም ብሎ ሲመሰረት ከመስራቾቹ አንዱ ናቸው፡፡

በአሁኑ ሰአት ሞርዶኮፍ ኃ.የተ.የግ.ማ የተሰኘ በቡና ላይ የተሰማራ ድርጅት ከፍተው በመስራት ላይ ናቸው፡፡ ጋሽ ሀይሌ ሩሲያ ሀገር በማቅናት በማስተርስ ደረጃ ተምረዋል፡፡ ከህይወት ውጣ ውረድ ብዙ ተምረዋል፡፡

በተወለዱበት የቦረና አስተዳደር በልጅነታቸው ከብት ጠብቀዋል፡፡ጋሽ ሀይሌ እስከ 6ኛ ክፍል በሲዳሞ ከተማሩ በኋላ በመቀጠልም ሲዳሞ በሚገኘው የራስ ደስታ ዳምጠው ተማሪ ቤት ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡

ጋሽ ሀይሌ በ1965 ወደ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ገብተው ተምረዋል፡፡ በ1966 የህብረት ስራ ዩኒየን ትምህርትን በሀዋሳ ከተማሩ በኋላ ወደ ስራ አለም ይሰማራሉ፡፡ ከ1966-1971 ከሰሩ በኋላ በ1971 ለትምህርት ወደ ሩሲያ አቀኑ፡፡ ከሶቭየት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ይዘው በ1977 ተመለሱ፡፡

ከ1977-1985 ድረስም በመምህርነት ማገልገላቸውን ነግረውኛል፡፡ ገና በልጅነት የህብረት ስራ ዩኒየን ውስጥ የገቡት አቶ ሀይሌ ‹‹የሀገራችን የህብረት ስራ ዩኒየን አባት›› ቢባሉ ያንስባቸዋል፡፡ ከበርካታ የህብረት ስራ ዩኒየኖች በስተጀርባ ወይም ጎን ጋሽ ሀይሌ አሉ፡፡ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ዩኒየንን የመሰረቱት እርሳቸው መሆናቸው ይታወቃል፡፡


ጋሽ ሀይሌ በመቀጠል ወደ ፌደራል በማቅናት በፌደራል መንግስት የህብረት ስራ ኮሚሽን ውስጥ በኮሚሽነርነት በትጋት ማገልገላቸውን ይናገራሉ፡፡ በዚህ ኮሚሽን ውስጥ ባገለገሉበት ዘመን ህጎችን ከማውጣት አነስቶ የሰው ሀይልን እስከ ማደራጀት ያለውን ተግባር በማከናውን የትውልድ ሀላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡ ከዚህ ኮሚሽን ስኬት ጀርባ ወይም ጎን ያሉት አቶ ሀይሌ ለመሆናቸው ብዙ ሰው ሊመሰክር ይችላል፡፡ ለ5 አመታት ያህል ይህን ኮሚሽን በጥሩ ሁኔታ መምራታቸውን ይናገራሉ፡፡ የህብረት ስራ ዪኒየን አዋጅ እንዲወጣ ማድረጋቸው አቶ ሀይሌን ያረካቸዋል፡፡

ጋሽ ሀይሌ አጠቃላይ ለ33 አመት በሀብረት ስራ ዪኒየን ውስጥ ካገለገሉ በኋላ በ1999 ጡረታ ስለወጡ ወደ ራሳቸው ስራ መግባት ነበረባቸው፡፡ አቶ ሀይሌ ‹‹ድሮም እወደው የነበረው ከደሃ ጋር መስራት ነበር የራሴንም ስሰራ እንደዛው ነው የሚል ሀሳብ ይዘው ነበር፡፡ ከ1999 አነስቶ ጋሽ ሀይሌ ኦርጋኒክ ቡናን እያመረቱ ወደ ውጭ ሀገር ይልካሉ፡፡ አብረዋቸውም ከ300 በላይ ገበሬዎች ይሰራሉ፡፡

ጋሽ ሀይሌ ትዳር የመሰረቱት በ1967 ነው፡፡ ባለቤታቸውም ወይዘሮ ድንብላል እንዳለ ይባላሉ፡፡ አቶ ሀይሌን ስለባለቤታቸው ስጠይቃቸው ጥንካሬዋን አደንቃለሁ ይላሉ፡፡ አቶ ሀይሌና ወይዘሮ ድንብላል 6 ሴት ልጆችን የወለዱ ሲሆን ስማቸውም ምስራቅ ሀይሌ፣ትዝታ ሀይሌ፣ ታሪኳ ሀይሌ ፣ብሩክታዊት ሀይሌ ፣ትንሳኤ ሀይሌና ረቂቅ ሀይሌ ናቸው፡፡ መልካም ዘመን ለቤተሰቡ…. ተባረኩ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *