ዶክተር አርቲስት ትዕግስት ልኡል ሰገድ

ዶክተር አርቲስት ትዕግስት ልኡል ሰገድ

ዶክተር ትዕግሥት ልኡልሰገድ በአዲስ አበባ ከተማ ከአባቷ ከአቶ ልኡልሰገድ ጎበና እና ከእናቷ ከወይዘሮ አዛለች ጸጋዬ እንደ ኢትዩዽያን አቆጣጠር ( እ.ኢ.አ.) በ1959 ዓም ተወለደች።

ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያለውን ትምህርቷን በሊሴገብረማሪያም ፣በአፄ ፋሲልና በኢትዮጵያ ትቅደም ትምህርት ቤቶች ተከታትላለች።

ትዕግሥት አብዛኛውን የልጅነት ጊዜዋን ያሳለፈችው አዲሱ ገበያ እና አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ በተባሉ ስፍራዎች ነበር።

ዶክተር ትዕግስት በ1979 አ.ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች በዓመቱ በ1980 እ.ኢ.አ. የዛሬ 36 ዓመት በሁለተኛ አባቷ ኮሎኔል ይልማ ተሾመ አማካኝነት ከእህቶቿና ወንድሞቿ ጋር በመሆን ወደ አሜሪካን ለመምጣት ችላለች።

“ትጋት የሁልጊዜ ዋና መርሔ ነው “

የምትለው ትእግስት የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዋን ያገኘች ሲሆን ሶስተኛ ዲግሪዋን ደግሞ በአማራጭ የጤና ሳይንስ ( ALTERNATIVE MEDICINE) በተባለው የህክምና ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪዋን ለማግኘት ችላለች፡፡ ይህንን የከፍተኛ ትምህርት እንድትማር ምክንያት የሆናት ደግሞ የአባቷ ህመም ነበር። ይህንንም ክስተት ወደ መፍትሔ ቀይራው በተማረችው ትምህርት ከአባቷ አልፎ ለብዙዎች ተርፋለች። ህሙማንን ቤታቸው ድረስ በመሄድ ለብዙዎች እርዳታን ለግሳለች።

ትዕግስት፣ ከተማረችው ትምህርት ባሻገር በማህበረሰባችን ውስጥ ብዙም ያልተለመደ የሥራ ዘርፍ የሆነውን የእንስሳት ህክምና እና ማቆያ ተቋም በመክፈት በአትላንታ ኢትዮጵያን ዘንድ በፈር ቀዳጅነቷ ትጠቀሳለች። በዚህም የህክምና ተቋም ውስጥ ለእንስሳት በሚደረጉ የህክምና፣ የቀዶጥገና፣ የክትባት እንዲሁም የማስዋብ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ የሀገሩዋ ልጆችና የሌሎች ሀገርዜጎችን አሰልጥኖ በመቅጠር ለብዙዎች የስራ እድል ከፍታለች።

በዚህም ተግባር ላይ ለአመታት ተሰማርታ ቆይታለች።

ዶክተር ትዕግስት ልኡልሰገድ፣ በአትላንታ ማህበረሰብ ዘንድም የተመሰገነች ብቻ ሳትሆን በሚሰጣት የስራ አደራ ሁሉ የተጣለባትን በአግባቡ የምትወጣ ጠንካራ ሴት ነበረች፡፡

ዶክተር ትዕግስት ከህይወት አጋሯ ከጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ መከባበርና መግባባት የተሞላበትን መልካም የትዳር ጊዜ አሳልፈዋል ፡፡

የብርታቷ ማሳያ አንዱ በሆነው ጣና ማርት ውስጥ ልዩ ልዩ የጥበብ ምሽቶችን በማዘጋጀት፣ የመጽሐፍት ምርቃቶችን በስፍራው እንዲከናወኑ በማድረግ ልዩ ልዩ የኪነጥበብ ስራዎችን ታበረታታም ነበር። ከአንድ አመት ተኩል በፊት ማለትም በጥምቅት 29 2015 ከዚህ አለም በሞት የተለየውን የህይወት አጋሯን ካጣች በኃላ ትዕግስት የዳዊትን ወዳጆች አስተባብራ ሁለቱን ሚድያዎች : አድማስ ሬዲዮና ድንቅ መጽሄትን ለማስቀጠል ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል ያደረገችው ጥረት እጅግ የሚደነቅ ነው ፡፡ አድማስ ሬዲዮን ከአንድ አመት ተኩል በላይ፤ ድንቅ መጽሔትን ደግሞ ለ15 እትሞች ያህል እያሳተመች መዝለቋ የጠንካራነቷ ማሳያ ነው፡፡

የዶክተር ትዕግስት የደግነትና የማህበራዊ ሥራ አገልግሎት እንዲህ በቀላሉ ተዘርዝሮ የሚያልቅ ባይሆንም በጥቂቱ ለመዘርዘር ያህል አትላንታ በሚገኘው የሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፌዴሬሽን ውስጥ የቦርድ አባል በመሆን ስለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም የቻለችውን ያህል ሰብካለች፤ ዘፍናለች፤ የገንዘብ ድጋፍን በማድረግ በርካቶችን ደግፋለች።

ትዕግስት፣ የሰዎች ህይወት ተሻሽሎና አድጎ ማየት ደስታን የሚፈጥርላት ነገር ነው። የብዙዎችን ህይወት ለመለወጥ በማሰብም ከ50 በላይ ሰዎችን ከኢትዮጵያ ስፖንሰር በማድረግ ወደ አሜሪካ እንዲመጡ አድርጋለች። ማምጣት ብቻም ሳይሆን ላብዛኛዎቹ የሥራ እድልንም ፈጥራለች።

በዚህ ብቻ ያላበቃው የዶክተር ትዕግስት ደግነት እና ለበጎአድራጎት ስራዎች ያላት ልበ ቀናነት ኢትዮጵያ በሚገኘው በሜሪጆይ ሲስተር ዘቢደር ስር ያሉ አረጋውያንን እና ህጻናትን በመርዳት በኩል የቻለችውን ሁሉ ህይወቷ እስኪያልፍ ድረስ ስታደርግ ቆይታለች። ወደ ሀገሯ በመመለስም በተማረችው ሙያ ከፍተኛ ክሊኒክ በመክፈት ወገኖቿን ስታገለግል ነበር።

ትዕግስት፣ ከልጅነቷ ጀምሮ ለሙዚቃ ልዩ ፍቅር ነበራት። ማንጎራጎርም በጣም ትወድ ነበር። ይህንን ፍላጎቷንም እውን ለማድረግ ሥራዋ፣ ትምህርቷ እና ንግዷ አላስቆሟትም ነበር። ይልቁንም በፍላጎቷ በይበልጥ በመግፋት በ1993 ዓ.ም እ.ኢ.አ. “ይገርማል ” የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበሟን ለአድማጮቿ አድርሳለች። በመቀጠልም የተለያዩ ነጠላ ዜማዎችን ወደ አድማጭ ተመልካች አድርሳለች። ትዕግስት የብዙ ሙያ እና የተሰጥዖ ባለቤትም ነበረች።

ዶክተር ትዕግስት በመልካም እና በሰፊ ቤተሰብ መሀል በፍቅርና በመተሳሰብ የኖረች ሲሆን 6 ወንድሞችና 7 እህቶች አሏት።ከወንድሞቿና እህቶቿ የወጡ ልጆች ትዕግስትን አክስታችን ሳይሆን እናታችን “ማሚ” በማለት ነበር የሚጠሯት። እንዲህሞ ብለው እንዲጠሯት ያስቻላቸው ለእነርሱ ያላት ፍጹም ፍቅር እና እንክብካቤ ነበር።

ትዕግስት በስጋ ለሚዛመዷት ብቻ ሳይሆን ደግነቷ፣ ለሁሉ ደራሽ መሆኗ የአትላንታ ነዋሪና አብረዋት ይሰሩ የነበሩት ሁሉ የሚመሰክሩት ጉዳይ ነው፡፡

ዶክተር ትዕግስት ለልኡልሰገድ ሚያዚያ 19፣ 2016 እ.ኢ.አ.( April 27, 2024) በስራ ገበታዋ ላይ እያለች በደረሰባት አደጋ ምክንያት ከዚህ አለም በሞት ተለይታናለች።

የትግስት ድንገተኛ ህልፈት ቤተሰቡዋን ብቻ ሳይሆን እንደ ተወዳጅ ቤተሰብ የሚያዩዋትን የአትላንታ ነዋሪዎችን እንዲሁም በኢትዮጵያ ድጋፍና እንክብካቤ የምታደርግላቸው ወገኖችና ወዳጅ ዘመዶችን በእንባ ያራጨ ጥልቅ ሃዘን ፈጥሯል። ዶክተር ትዕግስት በተሰማራችበት መስክ ሁሉ ውጤታማ፣ ታታሪ ሠራተኛ፣ የጥበብ ሰው፣ ብርቱና መልካም አርአያ የሆነች ሰው ነበረች።

ሆኖም ፣መኖርና ወደማይቀረው ሞት መሄድ ከአዳም ዘመን ጀምሮ የነበረ ሲሆን በምድር ላይ እያሉ እንደ እህታችን ዶክተር ትዕግስት ሁሉንም ነገር በስኬትአከናውኖ ወደ አምላክ መሄድ እጅግ መታደል ነው!!

የተኖረ ህይወት! የእህታችንን ነፍስ በደጋጎቹ በነ አብርሃም እቅፍ ያኑርልን!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *