ደበበ እሸቱ

ደበበ እሸቱ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ ፤ በስነጽሁፍ ፤በቴአትር እና በፊልም አስተዋጽኦ ያደረጉ ባለሙያዎችን እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስካሁን የሰነድናቸው ብቻ ሳይሆኑ በተከታታይ የበርካቶችን የህይወት ታሪክ ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ከዚህ ቀደም የ180 የሚድያ ሰዎችን ታሪክ መዝገበ-አእምሮ በሚል መጽሀፍ ማውጣታችን ይታወሳል፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ደግሞ ቅጽ 2 የሚድያ እና የጥበብ ሰዎችን ታሪክ በመጽሀፍ መልክ እናወጣለን፡፡ በቅጽ 2 ላይ ታሪካቸው ከሚሰነድላቸው የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች መካከል አርቲስት ደበበ እሸቱ ይነሳል፡፡ ጋሽ ደበበ ከልጅነቱ አንስቶ በጥበብ ሙያ የዘለቀ ሲሆን ባለፉት 55 አመታትም በዚህ በሚወደው ሙያ ላይ ቆይቷል፡፡ ጋሽ ደበበ እሸቱ የህይወት ታሪኩን እንድንሰንድ ፈቃዱን ስንጠይቀው በአክብሮት ተቀብሎ ያስተናገደን ሲሆን ሌሎችም ታላላቅ ባለሙያዎችም ይልመድባችሁ ማለት እንወዳለን፡፡ እዝራ እጅጉ እና አይናለም ሀድራ የአርቲስት ደበበ እሸቱን ታሪክ ሰንደውታል፡፡

ትውልድ፣ እድገትና ትምህርት

አርቲስት ደበበ እሸቱ በ1934 ዓ.ም ተወለዱ። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪ እያሉ ቲያትር የመስራት ዕድሉ ገጥሟቸው ነበር።በወቅቱ ግን የህይወት ዘመናቸው ከቲያትር ስራ ጋር ግን የተቆራኘ ይሆናል ብለው አስበው እንደማያውቁ ነው ክቡር ዶክተር አርቲስት ደበበ እሸቱ የሚናገሩት። ከዛ በመቀጠል የአብራሪነት ስልጠና ለመውሰድ እጩ መኮንን ሆነው የኢትዮጲያ አየር ሀይልን ተቀላቀሉ። የቲያትር ነገር እዛም ተከተላቸውና የአየር ሀይል የመዝናኛ ክፍሉ ላይ በመሳተፍ ቲያትር ሰርተዋል።

ይሁንና ትምህርቱን የመቀጠል ሀሳባቸውን ቀይረው ትምህርት አቋርጠው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ። ከአየር ሃይል መልስም በፖስታ ቤት ስራ ተቀጠሩ።በአየር ሃይል የጀመሩትን ትምህርት ማቋረጣቸው እንደ ክህደት ይቆጠር ነበርና በስራ ላይ ሳሉ ፖሊሶች ሊይዟቸው እንደሆነ ሲረዱ አምልጠው ወደ ደብረብርሃን አመሩ። በደብረብርሃን የሚገኘው መምህራን ማሰልጠኛ ገብተው ስልጠናውን መከታተል ጀመሩ።በመሃል የተማሪዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ይነሳና እርሳቸውም ይቀላቀላሉ።በወቅቱ ተማሪዎቹ ተሰባስበው ተቃውሟቸውን ቅሬታቸውን ለማሰማት አዲስ አበባ ድረስ በእግራቸው መጥተው እንደነበር ይናገራሉ።በዚህ ሰበብም ለቅጣት ተዳርገው የፖለቲካ እስረኛ ሆነው ጎሬ ተላኩ።

ከጎሬ ቆይታ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ፐርፎርሚንግ አርትስ መማር ጀመሩ።እ.አ.አ በ1965 ደግሞ ወደ ሃንጋሪ በማቅናት የቲያትር ጥበብን ተማሩ። ክቡር ዶክተር አርቲስት ደበበ እሸቱ በሃንጋሪ ቆይታቸው ካገኙት ትምህርት በላይ የሃገራቸውን ልጆች እነ ተስፋዬ አውላቸው፣ ጌታቸው ደባልቄ፣ አስካለ አመነሸዋ፣ እትዬ አስናቀችና ሌሎች ቀደምት አንጋፋ ሙያተኞችን በማየት ብዙ እውቀት ማግኘታቸውን በንግግራቸው ያነሳሉ።

የስራ ሕይወት

ክቡር ዶክተር አርቲስት ደበበ እሸቱ በልጅነታቸው በቲያትር የመቀጠል ሃሳቡ አይኑራቸው እንጂ አንጋፋዎቹ ሙያተኞች ቲያትር ሲሰሩ እያዩ ነው ያደጉት።በክዋኔ ወቅትም መጋረጃ ያዥ ሆነው አገልግለዋል። እርሳቸውም ገና በብላቴንነታቸው እቤታቸው ቡና ሲፈላና ቤተሰብ ጎረቤት ሲሰበሰብ ነጠላ ጋርደው ያዩትን ቲያትር ያሳዩ ነበር።ያ እርሾ አድጎ ዛሬ አንቱ አስብሏቸዋል።ደራሲ፤ ተርጓሚ፤ አዘጋጅ፤ ተዋናይ፤ መድረክ መሪና ሁለገብ አርቲስት ደበበ እሸቱ የቲያትርን ስራ በቀድሞው ክሬቲቭ አርት ሴንተር ባሁኑ ባህል ማዕከል በይፋ ከጀመሩ ወዲህ ለኢትዮጲያ ኪነ ጥበብ በርካታ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ተሳትፏቸውም ከፍ ያለ ነው።

ጋሽ ደበበ ከ40 በላይ ተውኔቶች ላይ ተሳትፈዋል። ከተወኑባቸው ቴአትሮች መካከል እናት ዓለም ጠኑ፣ ዋናው ተቆጣጣሪ፣ የአዛውንቶች ክበብ፣ ኪንግ ሊር፣ ዳንዴው ጨቡዴ፣ ያላቻ ጋብቻ፣ ናትናኤል ጠቢቡ፣ የቬኒሱ ነጋዴ፣ የከርሞ ሰውና ጠልፎ በኪሴ የሚሉት ይገኙበታል።
የመንግስቱ ለማን “ጠያቂ”፣የተስፋዬ ገሰሰን “ተሐድሶ”፣የአያልነህ ሙላትን “ሻጥር በየፈርጁ”፣የነጋሽ ገብረማርያምን “የአዛውንቶች ክበብ” እና የዊልያም ሼክስፔርን “ሊር ነጋሲን” ጨምሮ 28 ተውኔቶችን አዘጋጅተው ለዕይታ አቅርበዋል።

በፊልም ስራም የተለያዩ በኢትዮጵያውያን የተዘጋጁ የሀገር ውስጥ ፊልሞችን ጨምሮ “Shaft in Africa”፣”The African spy”፣”The Sailor from Gibraltar”፣”A Season in Hell”፣”Zelda”፣”The gravedigger”፣”The grand rebellion”ና “Red Leaves” በሚሉት ላይም ተሳትፈዋል። በስነፅሁፍ ዘርፍም ከተዋናይ ሀሁ፤ የባሩድ በርሜል፤ድብልቅልቅ የመድረክ ተውኔት፣ ያልታመመው በሽተኛ፣ የደም እንባንና ሌሎችንም ስራዎች ወደ አማረኛ ተርጉመዋል።

አበርክቶዎችና ተሳትፎዎች

ክቡር ዶክተር አርቲስት ደበበ እሸቱ የአፍሪካ መድረክ ባለሙያዎች ማህበር መስራች ፣የዓለም ኮንቴምፖራሪ ቴአትር ኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባል፤ የዓለም አቀፍ ቴአትር ኢንስቲቲዩት የአፍሪካ አስተባባሪና የኢትዮጵያ ተጠሪ፤በብሔራዊ ቴያትር የፕሮግራምና ፕሮዳክሽን ሀላፊ፤በሀገር ፍቅር ቴአትር የኪነጥበብ አገልግሎትሀላፊና፣በራስ ቴአትር ዋና ስራ አስኪያጅነት፣ በአትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በርካታ ማህበራዊ፣ የልማትና እርዳታ አገልግሎቶችን ላይ አስተባባሪ፣ የሰላምና እርቅ ኮሚቴ አባል፣ የጌርጌሴኖን የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል አምባሳደር፣ በኩላሊት ሞት ይብቃ አምባሳደር በመሆን አገልግሏል እያገለገለም ይገኛል። ከተጠቀሱት ባሻገር በሌሎች በርካታ ማህበራዊ ግልጋሎቶችም ላይ ተሳትፎ አድርገዋል እያደረጉም ይገኛሉ።ከዛም ባሻገር በተለያዩ የአለም ክፍሎች በመዘዋወር ጽሁፎችን ያቀርባሉ፡፡ ወርክ ሾፖችንም ይሰጣሉ።ጋሽ ደበበ መረጃ ፈልገው ወደ እርሳቸው ለሚሄዱ ጋዜጠኞች፣ ተማሪዎችና የኪነጥበብ ሰዎችም አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ በማድረግ ይታወቃሉ።

ሽልማቶች

ለአፍሪካ ቲያትር ባደረጉት አስተዋጽኦ የዚምባብዌን ማላካይት አዋርድ ወስደዋል፣ ጣይቱ ኢንተርቴንመንት በዋሽንግተን ዲሲ በቲያትር ዘርፍ የህይወት ዘመን ተሸላሚ አድርጓቸዋል፡፡ በአትላንታ ጂኦርጂያ የከተማው ምክር ቤት ለአለም ቲያትር ባደረጉት አስተዋጽኦ ኖቬምበር 24ን የደበበ እሸቱ ቀን በሚል ሰይሞላቸዋል፡፡ የኢትዮጲያ ባህል ሚኒስትርም ለኢትዮጲያ ፊልም እድገት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሸልሟቸዋል፡፡ በጉማ አዋርድም የህይወት ዘመን ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ እ.አ.አ በ2015 በቫንኮቨር አለማቀፍ ፊልም ፌስቲቫልም በምርጥ መሪ ተዋናይ ዘርፍ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በዚህ አመት በ2015 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሃገራቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሸልሟቸዋል።

የቤተሰብ ሁኔታ

ክቡር ዶክተር አርቲስት ደበበ እሸቱ በ1964 ዓ.ም ነው ከወ/ሮ አልማዝ ደጀኔ ጋር ትዳር የመሰረቱት። በትዳር ህይወታቸውም 4 ልጆችንና 8 የልጅ ልጆችንም አፍርተዋል።

መዝጊያ

ይህ አቋም የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *