(ከዕዝራ እጅጉ) ክፍል 5
ትዝታ 1
በ1989 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማትሪክን ከመውሰዴ በፊት በኢቲቪ የሚታየውን “አካፑልኮ ቤይ” ፊልም ለትምህርት ቤታችን የሬድዮ አድማጮች አቀርብ ነበር፡፡ ከተመሠረተ ገና ሁለተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው ፋና ሬድዮ የትርጉም ሥራዬን አስመልክቶ እንግዳ ሊያደርገኝ ስቱድዮ ጋበዘኝ፡፡ በጊዜው ቃለ ምልልስ ያደረገልኝ መስፍን አሸብር ነበር፡፡ በሥራዬ ሁሉም የፋና አባላት ማኔጅመንቱን ጨምሮ ደስተኞች ነበሩ፡፡
በወቅቱ ሙልጌታ ገሰሰን፣ ወልዱ ይመስልን ፣ሴኮቱሬ ጌታቸውን ሌሎቹንም መተዋወቄን አስታውሳለሁ፡፡
ሙሉጌታ ቃለ ምልልሱን ካደመጠ በኃላ እሁድ እሁድ ለሚሠራጨው “አብረን እናረፋፍድ” መሰናዶ የትርጉም ሥራውን በተከታታይ ያቅርብ ሲል ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ‘ታዳጊዎችን መንገድ ማስያዝ እና ማነቃቃት ‘አለብን ሲልም ሙልጌታ ሀሣብ አከለበት፡፡ ከዚያም ለተከታታይ 3 ሳምንታት በፋና የፊልሙን ትረካ ማቅረቤን አልዘነጋውም፡፡ በጊዜው የመሰናዶው አዘጋጆች እነ ነቢዩ ጥዑመልሣን ይህን የሚዘነጉት አይመስለኝም። እኔም ሞራሌ ተነቃቅቶ አካፑልኮ ቤይን በመፅሐፍ አሳትሜ ማቅረብ አለብኝ ከሚል ውሳኔ ላይ ደረስኩ፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት እና ተመስጋኝ ሙልጌታ ነበር፡፡
ትዝታ ሁለት
በ1992 ዓ.ም ወደ ሥራ አለም ገና እንደገባሁ በ347 ብር የተቀጠርኩበት መሥሪያ ቤት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ልሳን የነበረው ‹‹አዲስ ልሳን›› ጋዜጣ ነበር፡፡ በመስከረም ወር ተቀጥሬ በህዳር ወር አንድ ዜና አቀድኩ፡፡ ይህም የፋና ሬድዮ 5ኛ አመት ክብረ-በአልን በተመለከተ ዜና እንድሠራ ነበር፡፡ እኔም በቀጥታ ወደ ፋና ደውዬ የዋና ሥራ አስኪያጁን የአቶ ሙልጌታ ገሰሰን ፀሀፊ መላክ የአብስራ ዘሩን አገኘኋት፡፡ መላክም ከአቶ ሙልጌታ ገሰሰ ጋር ቀጠሮ ይዛልን ጉዞ ወደ ፋና ተጀመረ፡፡ በመሠረቱ ወደ ሥራ ዓለም ለመግባቴ ቀደም ብሎ ገና ሀይስኩል እያለሁ ፋናን አውቀው ስለነበር ቤቱ አዲስ አልሆነብኝም፡፡ እናም ፋና ከደረስኩ በኋላ ፣ አቶ ሙሉጌታን ቃለ-መጠይቅ አደረግኩት፡፡
ትዝታ 3
ሙሉጌታ በ1993 ፋናን ከለቀቀ ወዲህ ብዙም ሚድያው አካባቢ አላየውም ነበር፡፡ የመጀመሪያው የፋና ሥራ መሪ እንደመሆኑ በፋና ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ አምናለሁ፡፡
በእኔ እምነት አቶ ሙልጌታ የፋና የመጀመሪያው የሥራ መሪ በመሆኑ ብቻ ከፋና መጥፋት አለበት ብዬ አላምንም፡፡ በተሰጠው ኃላፊነት አንድ አሻራ ማስቀመጡ አይቀርም፡፡ ለ12 አመታት ፋና የምስረታ በአሉን ሲያከብር ሙሉጌታን መጥቶ አላየሁትም፡፡ ምናልባት ውጭ ሀገር ሄዶ ይሆን? እያልኩ እጠይቅ ነበር፡፡ ለማንኛውም በ2012 ሙሉጌታ ገሰሰ ሞባይል ላይ ደውዬ ለፋና 25ኛ አመት ላነጋግረው እንደምፈልግ ነገርኩት፡፡ በተለይ ደግሞ የዚህን ቤት ./የፋናን/ ታሪክ የመሰነድና ለትውልድ የማስተላለፍ እቅድ እንዳለኝ አጫወትኩት፡፡ በሀሣቡ ተስማማ፡፡ ከዚያ ደግሞ በቀጥታ ስርጭት ገብቶ ከአዳነ አረጋ እና ከምህረት ዮሴፍ ጋር ያደረገውን ቆይታ ልብ ብዬ አደመጥኩት/ተመለከትኩ/፡፡ በጣም በሳል ሰው ነው፡፡
ትዝታ አራት
የሚድያ ሰዎች የሕይወት ታሪካቸው የሚሰነድበት “መዝገበ አእምሮ” መፅሐፍ ላይ ታሪክህ ቢሰነድ መልካም ነው ስል የዛሬ 3 ዓመት ሙልጌታን ጠየቅኩት፡፡’ እኔ ምን ሠርቼ!’ ሲል ታሪኩን ለመስጠት ሳይፈቅድ ቀረ፡፡ ብዙ ተደዋወልን በጄ ሳይል ቀረ፡፡
ከሳምንት በፊት ማለፉን ስሰማ ማመን ተሳነኝ።እናም ዛሬ ነሐሴ 4 2017 የእሱን የማስታወሻ ዝግጅት መድረክ ስመራ እና ለዝግጅቱ አንዱ ተባባሪ ስሆን ብዙ ሀሳቦች ውስጤ ይመላለስ ገባ፡፡ ለሚወዳችሁ እና ለምትወዱት፣ ክብር ለምትሰጡት ሰው ምን ላድርግለት ስትሉ በሆነ መንገድ የውስጣችሁን ታደርጉለታላችሁ፡፡ በዚህም ውስጣችሁ ይረካል፡፡ ሙሌ፣ እንዲሁ ቀለል ያልክ አለቃ ስለሆንክ እወድሀለሁ፡፡አብረን ባንሠራም አንተ በፈጠርከው የፋና ሲስተም ብዙ ተሠርቼ አሁን የሆንኩትን ሆኛለሁ፡፡ነፍስ ይማር ሙሌ !!!!