ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣ መዝገበ-አእምሮ ( የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች ፣በመፅሀፍ፣በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል።
በተለይ ጉግል ላይ ታሪካቸው ሲፈለግ የማይገኝ ሰዎች አሁን የሙያ አበርክቷቸው በቀላሉ ኢንተርኔት ላይ በግልፅ ተቀምጦ ይገኛል።
ባለፉት 4 ዓመት ከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መፅሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።
ከእነዚህ ውስጥ የሚድያ ሰዎችም፣ የቴአትር ባለሙያዎች ይገኙበታል። አጠቃላይ 74 ከፍተኛ የሚድያ አመራሮች፣ሚኒስትሮች ፣ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የግል ሚድያ መሥራቾች፣ዋና አዘጋጆች እና መካከለኛ አመራሮች ተካተዋል። 35 ያህሉ በዋና ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ያሉ ሲሆን የሁሉም ታሪክ በተሟላ ደረጃ ለመሰነድ ተችሏል።በተጨማሪም በሳይንስ፣ በመምህርነት ፣በምህንድስና እና በሌሎችም ዘርፎች ውስጥ ያሉ ሰዎችን ወደ አንባቢ እያመጣን እንዲታወቁ ጥናትና መረጃ ማድረግ ለሚሻም ተደራሽ ስናደርግ ቆይተናል።
የእነዚህን ሰዎች ታሪክ ሰንዶ ለአንባቢ ተደራሽ ማድረግ ፈታኝ ቢሆንም አሳክተነዋል። በዚህ ተግባራችንም ተጠናክረን እንቀጥላለን።
አሁን ታሪካቸውን የምንሰንድላቸው ሰው ህይወታቸው ካለፈ 3 ዓመታት ተቆጠሩ። በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራም አሳርፈዋል። ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ። ተወዳጅ ሚድያ ከቤተሰባቸው የተገኘውን መረጃ፣ እንዲሁም ልጆቻቸው ረቂቁን ተመልክተው የሰጡትን ህጋዊ ማረጋገጫ እና ይሁንታ መሠረት በማድረግ የሕይወት ታሪካቸውን አቅርበናል። ታሪኩንም ዕዝራ እጅጉ ሙላት ሰንዶታል።ይህ ፅሑፍ በዚህ መልኩ እንዲቀርብ አስተዋፅዖ ላደረጉት ለጋሽ ደረጀ ገብሬ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን።
፨፨፨፨፨፨፨፨፨ ፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
በቁጥር የሚተመን ጊዜ አቶ ዘሪሁን አስፋውንና የሱን መሰሎች በኖሩበት ዘመን ውስጥ የፈጸሙትን ተግባር ቁልጭ አድርጎ አያሳይም፡፡ መሽቶ በመንጋት የተፈጥሮ ኡደት የሚመላለስ ቀን፣ ሳምንት፣ ወርና ዓመት እየተባለ ቀን ቆጥሮ ዘሪሁን ጥቅምት 10 ቀን 1944 ዓ.ም. በደሴ ተወልዶ 71 ዓመት ኖሮ ለየካቲት 28 አጥቢያ አረፈ ብሎ መናገር አቶ ዘሪሁንን (ወንድማችንን፣ ጓደኛችንን፣) አይገልጸውም፡፡ ዘሪሁንን ለመግለጽ ከቀንና ዘመን ቁጥር በላይ የሆኑ እጅግ በርካታ ሥራዎች አሉት፡፡ ዝርዝራቸውን በአጭር በአጭሩ ከማቅረባችን በፊት ግን አባቱ አቶ አስፋው ጉበናንና እናቱን ወይዘሮ ስህንጉበናን የወንድማችን የሆነውን እንዲሆን መሠረቶች ናቸውና ስማቸውን በክብር እናነሳለን፡፡
1.ትምህርት
ወጣቱ ዘሪሁን በደሴ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በመምህር አካለወልድ ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃውን ደግሞ በወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ተማረ፤ በወ/ሮ ስህን ትምህርት ቤት ከመደበኛ ትምህርቱ በተጨማሪ የትምህርት ቤቱ የኪነጥበብ ክበብ አባል ሆኖ በትያትር ትወና፣ በሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነት በመሳተፍ በኋለኛው ዘመኑ እድሜውን ሙሉ ለዋኘበት የሥነጽሑፍ ሙያ መሠረቱን እንዳደላደለለት የሚታወቅ ነው፡፡
በ1962 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በልዑል በእደማርያም የመሰናዶ ትምህርት ቤት መማር ከጀመረ በኋላም የጥበብ ጥሪውን ተከትሎ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማእከል አባል በመሆን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮት የነበረውን ኪነጥበባዊ ተግባሩን ገፍቶበታል፡፡
በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ ክፍለትምህርት ከ1963-1965 የሦስት ዓመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ካጠቃለለ በኋላ በወቅቱ አስፈላጊ በነበረው የዩኒቨርሲቲ አገልግሎት መርሀግብር በመሳተፍ በኤርትራ ጠቅላይ ግዛት በከረን ከተማ አንድ ዓመት ያህል አስተምሮና ግዳጁን ተወጥቶ ተመልሷል፡፡ ከዚያም በኋላ በ1967 በታወጀው የዕድገት በኅብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ
ተሳታፊ በመሆን በአድዋ እና አካባቢው ተመድቦ ግዳጁን ተወጥቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲ አገልግሎትና በእድገት በኅብረት ዘመቻ ምክንያት ለሦስት ዓመታት ያቋረጠውን ትምህርት ለመማር ቢሞክርም ወቅቱ በልዩ ልዩ የፖለቲካ ኃይሎች ቁርቁስና ትርምስ፣ ነጭ ሽብር፣ ቀይ ሽብር ምክንያት ተረጋግቶ መማር ባለመቻሉ በአርሲ ክፍለሀገር በአሰላ ከተማ አሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አማርኛናእንግሊዝኛእያስተማረ ዓመት ያህል ቆይቶ ተመለሰ፡፡ ያቋረጠውንም ትምህርት በሚገባ አጠናቅቆ በ1970 በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ፡፡ የሁለተኛ ዲግሪውንም ከዚሁ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የውጭ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ ትምህርት ክፍል ከ1973-1975 ተከታትሎ በሥነጽሑፍ የማስተርስ ዲግሪ ተቀበለ፡፡
2.ሥራ
አቶ ዘሪሁን አስፋው ገና በጠዋቱ በመምህርነትና በሥነጽሑፍ አድባር የተጠራ ሰው ለመሆኑ ከዚህ ቀጥሎ የሚቀርቡት ዝርዝሮች ጠቋሚዎች ናቸው፡፡ በልጅነቱ በትምህርት ቤት የኪነጥበብ ክበብ የጀመረውን ንቁ ተሳታፊነት ቀስበቀስ እያሳደገና እያጠነከረ የሕይወቱ ድርና ማግ ያደረገ፣ በጥልቅ ተመልካችነትም ሥነጽሑፍን የተጠበበ፣ የመረመረ፣ የሔሰ፣ ያገራችን አንጋፋና ወጣት ተመራማሪዎችም ሆኑ ፈጣሪዎች በረቂቁ የአስተሳሰብ መንገድና ያሠራር ብልሃታቸው ያስገኙትን ትሩፋት አንጥሮ ለማሳየት ዘወትር የሚተጋ ነበረ፡፡ከላይ እንደተጠቆመው፣ የአቶ ዘሪሁን አስፋው ዋነኛ ጥሪ መምህርነት በተለይም የሥነጽሑፍ መምህርነት በመሆኑ፣ በበርካታ ቦታዎች በመምህርነት አገልግሏል፡፡ የመጀመሪያውን የማስተማር ሥራውን የጀመረው ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ በዩኒቨርሲቲ አገልግሎት በከረን፣ በአድዋም በመሠረተ ትምህርት፣ የአርሲ ክፍለሀገር በአሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአማርኛና በእንሊዝኛ መምህርነት ነበር፡፡
የመጀመሪያ ዲግሪውን ካጠናቀቀ በኋላ ደግሞ ያኔ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር በነበረው የዓለማያ ግብርና ኮሌጅ በረዳት ምሩቅነት ደረጃ በ1971 ዓ.ም ተቀጥሮ እስከ ሌክቸረርነት ደረጃ በማደግ እስከ 1975 ዓ.ም ድረስ በመምህርነትና በተከታታይ ትምህርት አስተባባሪነት አገልግሏል፡፡
ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ሕይወቱ እስካለፈበት ዕለት ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀድሞው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ ( በአሁኑ ስሙ የአማርኛ ቋንቋ ሥነጽሑፍና ፎክሎር) ክፍለ ትምህርት ውስጥ በተለያዩ ማዕረጎችና የኃላፊነት ደረጃዎች አገልግሏል፡፡ ይህም ማለት፡
·
ከ1976 – 1986 በሌክቸረርነት
·
ከ1986 – 1993 በረዳት ፕሮፌሰርነት
·
ከ1993 ጀምሮ ሕይወቱ እስካለፈበት ድረስ በተባባሪ ፕሮፌሰርነት ሲያገለግል ቆይቷል፡፡
አቶ ዘሪሁን በተለይ በሥነ -ጽሑፍና ከሥነ-ጽሑፍ ጋር ተያያዥ የሆኑ ኮርሶችን ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ እስከ ከፍተኛው የዶክትሬት ዲግሪ ድረስ በማስተማር በርካታ ምሁራንን አፍርቷል፡፡ ካስተማራቸው ኮርሶች መካከልም፣ የሥነጽሑፍ መሠረታዊያን፣ የዝርውና ሥነግጥም ፈጠራ ድርሰት፣ የኢትዮጵያ
ሥነጽሑፍ ቅኝት፣ የህጻናት ሥነጽሑፍ፣ የሥነጽሑፍ ምርምር፣ የአማርኛ ሥነጽሑፍ ታሪክና ዕድገት፣ የሥነጽሑፍ ሒስ እንዲሁም የፎክሎር ቴዮሪ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ከማስተማር ሥራው ጎን ለጎን ያቶ ዘሪሁን አስፋው ተቀዳሚ ሥራ ጥናትና ምርምር
ነበር፡፡ በዚህ ረገድም በርካታ ተሳትፎና አበርክቶ የነበረው ሊቅ ነበር፡፡ ምርምርን ከማስተማር በተጨማሪ 143 የመጀመሪያ ዲግሪ ፣ 80 ማስተርስ ዲግሪ ፣ 20 የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎችን በምርምር ሥራዎቻቸው አማክሯል፣ እስከዛሬም በማማከር ላይ ነበር፡፡
እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና ዶክትሬት ተማሪዎችን የምርምር ሥራዎች በመገምገም፣ ዩኒቨርሲቲዎቹ የሥነጽሑፍ ትምህርት ክፍሎችን ሲያቋቁሙ መርሀግብሮቻቸውን በመገምገም፣ የጥናትና የአሠራር እንዲሁም የአተገባበር
ብልሃቶችን በማመላከት አስተዋፅኦ ማድረጉን የተጠቀሙ ሁሉ የሚመሰክሩት ነው፡፡
አቶ ዘሪሁን ተማሪዎችን በምርምር ከማገዝም አልፎ በግሉ ሠርቶ ያቀረባቸውና ለህትመት ያበቃቸው ብዙ ሥራዎች አሉት፡፡ ከሥራዎቹ መካከልም አምስት መጻህፍት፤
·
የሥነ-ጽሑፍ መሠረታውያን፣
·
ልቦለድ አዋጅና የቀደምት ደራስያን አጫጭር ትረካዎች፣
·
ሥነጽሑፍ ለማኅበራዊ ለውጥ ከፖፑሌሽን መገናኛ ማእከል ጋር፣
·
ከበዓሉ ግርማ እስከ አዳም ረታ፣ ሥነጽሑፋዊ ተሀዝቦት፣
·
በሥነጽሑፍና በፎክሎር ላይ የተሠሩ ዲግሪ ማሟያ ጥናቶች አጠቃሎዎች ስብስብ፣
ቀደሚዎቹ ናቸው፡፡
ከእነዚህ መጻሕፍ በተጨማሪ እጅግ በርካታ የምርምር ጽሑፎች በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ በታወቁ መጽሔቶችና መድበለ ጉባኤዎች ላይ ታትመውለታል፡፡
በምርምር ሥራዎቹ ያልተዳሰሱ ሥነጽሑፋዊ ርእሰ ጉዳዮች ቢኖሩ ምናልባት ጥቂቶች ሆነው በቀጠሮ ተራቸውን የሚጠብቁ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ መገመት የሚቻል ይመስላል፡፡ ያልታተሙትን የጥናት ሥራዎቹን በየጭብጣቸው አደራጅቶ ተከታታይነት ባላቸው ቅጾች ለማሳተም በማለም በዓይነት ባይነታቸው እያዘጋጀ እንደነበረ የሥራ ባልደረቦቹ ያውቃሉ፡፡
አቶ ዘሪሁን፣ከላይ የተጠቃቀሱትን የታተሙትንም ሆነ ገና ያልታተሙትን የምርምር ሥራዎቹን በበርካታ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባዔዎች ላይ አቅርቧል፡፡
በግል ማኅደሩና ከቤተሰብ ከተገኙት መረጃዎች ላይ መመልከት እንደተቻለው አያሌ ጥናትና ምርምሮቹን ካቀረበባቸው መድረኮች መካከልም ዋና ዋናዎቹ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሴት ደራስያን ማኅበር፣ የፖፑሌሽን ሜዲያ ሴነተር፣ ወሎ ዩኒቨርሲቴ፣ ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ፣ ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ፣ ማይነዝ ዩኒቨርሲቲ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
አቶ ዘሪሁን ከነዚህ የወል መድረኮች በተጨማሪ በግል ተጋብዞ ልምዱንና እውቀቱን ያካፈለባቸው መድረኮችም ነበሩ፡፡ ለአብነትም በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ፣ በኢትዮጵያ ሴት ደራስያን ማኅበር፣ የመገናኛ ብዙሃን ማሰልጠኛ ተቋም፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ እና በጀርመን ሀገር የሚገኘው የማይንዝ ዩኒቨርሲቴ ከብዙዎች ጥቁቶቹ ናቸው፡፡ እንዲሁም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደባህል እየተለመደ በመጣው የመትሐፍ ምረቃ ሥነሥርዓት ላይ በመገኘት ጎልማሶቹን ይበልጥ እንዲበረቱ፣ ወጣቶቹ ደግሞ በእውቀትና በልምድ እንዲበለጽጉ ሙያዊ ፍኖት በማሳየት በእጅጉ የሚተጋ ቸር መምህርና ተመራማሪ ነበር፡፡
አቶ ዘሪሁን በረጅም ጊዜ መምህርነቱ፣ በምርምር ሥራዎቹ፣ በነበረው ሰፊ ማኅበራዊ አገልግሎቱ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋሞች በርካታ የእውቅና የምስክር ወረቀቶች ተበርክቶለታል፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሂዩማኒቲስ የቋንቋዎች ጥናት፣ ጆርናሊዝምና ኮሚዩኒኬሽን ኮሌጅ፣ የአፍሪካ ሴቶች ደራስያን ማኅበር፣ የበጎ ሰው የሽልማት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር እና ሌሎችም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከጥናትና ምርምር መደበኛ መድረኮች አለፍ ሲልም አቶ ዘሪሁን ዕውቀቱንና ልምዱንን ለሀገር ልማትና ለኅብረተሰብ ንቃት ለማዋል ሳይታክት ይሠራ እንደነበር ቀደም ባሉት ዓመታት በራዲዮና በቴሌቪዥን ይሰጣቸው የነበሩ ገለጻዎችና ሙያዊ ማብራሪያዎች በምስክርነት ሊቆሙ ይችላሉ፡፡
አቶ ዘሪሁን፣የሥራ ተሳትፎውና ሙያዊ አበርክቶው በመደበኛ ሥራውና በመምህርነቱ ላይ ብቻ አልነበረም፡፡ በኮሚቴ አባልነት፣ በአማካሪነት፣ በሙያዊ ዳኝነት የተሳተፈባቸው ተቋማት እጅግ ብዙ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ
ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ፡-
·
የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ሥነጽሑፍ ትምህርት ክፍል ሊቀመንበር
(1986-1988)
·
የቋንቋዎች ተቋም ዲን (1988 – 1993)
·
የኢትዮጵያ ጥናትና
ምርምር ተቋም የቦርድ አባል (1988-1994)
የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም መጽሔት ኤዲሮሪያል ቦርድ አባል (1988-1994)
·
የ13ኛ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጥናት ጉባኤ የሥነጽሑፍ ዘርፍ ኮሚቴ ሰብሳቢ
·
የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና
ባህሎች አካዳሚ (ከአካዳሚ አደራጅ ኪሚቴ አባል እስከ ህይወት ዘመን አባልነት የደረሰ ተሳትፎ)
·
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል ህትመት ንዑስ ኮሚቴ አባል
·
በአ.አ.ዩ.
የትምህርት ጥራትና ምርምር ተቋም አማካሪ ቦርድ አባል (1994-95)
·
የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ መጽሔት ዋና ኤዲተር (2003-2007) ሆኖ አገልግሏል፡፡
ከላይ እንደተጠቆመው፣ አቶ ዘሪሁን በነበረው ሰፊ ዕወቀትና ልምድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውጭ ለሌሎች በርካታ ተቋማትና ድርጅቶች ሙያዊ አገልግሎት ከመስጠት የማይታክት ምሁርም ነበር፡፡ እንዲህ አይነት ሙያዊ አበርክቶ ከሰጠባቸውና በግል ማኅደሩ ተመዝግበው ከሚገኙ በመቶዎች ከሚቆጠሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ድርጅቶች መካከልም በጣም ጥቂቶቹ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡- CRDA,
Populationa Media Center, CODE-Ethiopia, HANDICAP, የትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት፣ USA Peace Corps-Ethiopia፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ሜጋ ኪነጥበባት ማዕከል፣ የጀርመን ባህል ማዕከል፣ የጀርመን አካዳሚክ ልውውጥ አገልግሎት (DAAD)፣ የስነ ጥበባትና መገናኛ ብዙኃን የሽልማት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ ባለሙያዎች ማህበር፣ የኢትዮጵያ የአእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡
አቶ ዘሪሁን በሀገር ውስጥ ካበረከታቸው ምርምሮችና ሙዊ አገልግሎቶች በተጨማሪም፣ በዓለም አቀፍ መድረኮችም ተሳትፎው ጉልህ ነበር፡፡ ከነዚህ መካከልም ዩኤስ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ እንግሊዝና ጀርመን የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
አቶ ዘሪሁን የእሱ ብቻ ሆኖ የሚታወቅ ልዩ ባህርይ አለው፡፡ የማስታወስ ችሎታ! ከልጅነት እስከ አዛውንትነት እድሜው ያለፈባቸውን ሁነቶች፣ አብረው የተማሩትን ሰዎች፣ በልዩ ልዩ አጋጣሚ የተዋወቃቸውን ግለሰቦች ከብዙ ዓመታት በኋላም ቢሆን ሲያጋጥሙት በስማቸው ጠርቶ ያናግር እንደነበረ ጓደኞቹ ያውቃሉ፡፡ በመምህርነት ተመድቦ ባገለገለባቸው ቦታዎች ሁሉ ካስተማራቸው ተማሪዎች ውስጥ ድንገት ቢያጋጥሙት በስማቸው ሲጠራ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ በተለይ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያስተማራቸውን ተማሪዎች ስም፣የተመካሪዎቹን ጥናት በርእስ ሳይቀር በዝርዝር
የሚያስታውስ፣ የሥራ ባልደረቦቹን መንፈሳዊ ቅናት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ሰብእና ነበረው፡፡
የሥራ ባልደረቦቹን እንደወንድምና እህት፣ ተማሪዎቹን እንደጓደኛ ያይ የነበረው አቶ ዘሪሁን ከመልካም ሥነምግባሩና ሥልጡን ከነበረው ሰብእናው ሳይሰስት እንዳካፈለ፣ በቸርነት ኖሮ፣ ቸር እንደሆነ፣ በኑሮ ሂደት የሚያጋጥሙትን አንዳንድ አስከፊ ድርጊቶችና አጋጣሚዎች በሆደ ሰፊነት፣ ቀለል አድርጎ በማየት፣ በፈገግታና በዝምታ እንዳለፈና እንዳሳለፈ፣ በሥራ አካባቢ በማናቸውም አግባብ በሚፈጠር እንከን ኃይለቃል ሳይወጣው አክብሮ እንደተከበረ በጓደኞቹ “ዘሪቾ”፣ በተማሪዎቹ “ጋሽ ዘሪሁን” እንደተባለ ኖሮ፣ 2015 ዓ.ም. መዝለል ተስኖት ይኸው አካላዊ ፍጻሜው ሆነ፡፡
አቶ ዘሪሁን፣ ከሕይወት አጋሩ ከወይዘሮ የትምወርቅ አክሊሉ ጋር ለ40 ዓመታት በትዳር ኖረው አንዲት ሴትና ሦስት ወንዶች አፍርተዋል፤ የልጅ ልጆችንም አፍርተዋል።
ይሁንና አንዱ ልጃቸው ከዓመት በፊት ቢያልፍም በሦስቱ ልጆቹና በባለቤቱ እንዲሁም በወዳጅ ዘመዶቹ፣ በጓደኞቹና በተማሪዎቹ፣ ሰው አላፊ ጠፊ ነውና ከሁሉም በላይ በሥራዎቹ ሐውልትነት ሲታወስ ይኖራል፡፡ እግዚአብሔር ነፍሱን ያሳርፍልነ፣ ይማርልን፡፡
#ሕልፈተ ሕይወትና ሥርዓተ ቀብር
ምሁሩ እስከ ዕድሜያቸውመግፊያ ድረስ በቤታቸው በምርምርና በሥራ ላይ የነበሩ ሲሆን፤ ሰኞ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም (በፈረንጆቹ March 6, 2023) በድንገት ባደረባቸው ሕመም በተወለዱ በ71 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ሥርዓተ ቀብራቸው ረቡዕ፣ የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ባልደረቦቻቸው፣ ደራሲያን፣ አድናቂዎቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በታላቅ ክብር ተፈጽሟል። የተቀበሩትም በካቴድራሉ ሰሜናዊ ምሥራቅ አቅጣጫ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራቸው ከነበሩት ከታዋቂው ፕሮፌሰር አብርሃም ደመወዝ አጠገብ ነው።