ወንድሙ ከበደ (1958-1999)

ወንድሙ ከበደ

ተወዳጅ ሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ማእከል በሚድያው ዘርፍ ልዩ አሻራ ያላቸውን እና የነበራቸውን ባለሙያዎች ታሪክ እየሰነደ ሲያቀርብ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደም የ180 የሚድያ ሰዎችን የህይወት ታሪክ መዝገበ አእምሮ በሚል ርእስ በመጽሀፍ ማውጣታችን ይታወሳል። አሁን ደግሞ በቀጣይነት የ200 የጥበብ እና የሚድያ ሰዎችን የህይወት ታሪክ አሰባስበን በአንድ መጽሀፍ አድርገን ለማውጣት መሰናዶ አጠናቀናል።

አሁን በዚህ ጽሁፍ የህይወት ታሪኩን የምናይለት ጋዜጠኛ ወንድሙ ከበደ ይባላል።በኢትዮጵያ ሬድዮ “ኢትዮጵያን እንቃኛት” በተሰኘው መሰናዶው ይታወቃል ። ወንድሙ ህይወቱ ካለፋ 17 ዓመት ያለፈው ሲሆን በሥራው ግን ምንጊዜም ይታወሳል። ሞሊቶ ኤልያስ እና ዕዝራ እጅጉ የህይወት ታሪኩን ሰንደውታል።

ወንድሙ ከበደ ሃይለሚካኤል ከአባታቸው ከአቶ ከበደ ኃይለሚካኤል እና ከእናታቸው ወይዘሮ ወርቄ አባተ ነሐሴ 24 ቀን 1958 ዓ.ም አዲስ አበባ ነበር ውልደታቸው።

የነፍስ ጥሪን ፍለጋ

ገና በልጅነታቸው የሬድዮ ፍቅር ልባቸው ላይ የገባ መሆኑን የሚያስታውሱት የአቶ ወንድሙ እህት አይናለም ከበደ ” ሬድዮ እንደልብ በማይገኝበት በዚያ ጊዜ ቤተሰቡን ሬድዮ እንዲገዙ በመወትወት ያስገዛ ነበር። ሬድዮዋን ጆሮው ላይ አድርጎ ይውላል። ባትሪ ሲያልቅ በድጋሚ ቤተሰብ ማስጨነቅ ይጀምራል። የሚሰማውን ይፅፋል። ይህ የሁልጊዜ ተግባሩ ነበር።”

አቶ ወንድሙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደጃዝማች በቀለ ወያ ትምህርት ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በ1971 ዓ.ም በኮልፌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለው አጠናቀዋል።

ሀረር የጦር አካዳሚ-የወጣቱ መዳረሻ

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ሀረር ወደሚገኝ የጦር አካዳሚ በመቀላቀል ወታደራዊ ስልጠናዎችን መውሰድ ችለዋል። በልጅነት እድሜያቸው ሬድዮ ማዳመጥ፣ጋዜጣ ማንበብና የተለያዩ ፅሁፎችን መፃፍ የነፍስ ጥሪያቸው የነበረው አቶ ወንድሙ ውትድርናን ከጋዜጠኝነት አስታርቀው ለመስራት መሰረታዊውን እውቀት መጨበጣቸው ላይ ትኩረት አደረጉ።

ጉዞ ወደ ሶቭየት ህብረት

በሀረር የጦር ትምህርት ቤት ወታደራዊ ስልጠናውን እየተከታተሉ የነበሩት አቶ ወንድሙ በ1975 ባገኙት የውጭ ሀገር የትምህርት እድል የቀድሞዋ የሶቭየት ህብረት አካል የነበረችው የአሁኗ ዩክሬን ውስጥ ወደሚገኝ ሉቦቭ ወደተሰኘ ከፍተኛ የወታደራዊ ኮሌጅ በመግባት የወታደራዊ ጋዜጠኝነት ትምህርትን ለሁለት አመታት ተከታትለዋል።

የሶቭየት የትምህርት ቆይታቸውን አጠናቅቀው ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ የጦር ሀይሎች ሬድዮ ጣቢያን በመቀላቀል መስራት ጀመሩ። በወቅቱ የጦር ሃይሎች ሬድዮ ጣቢያ ርዕዮተ-አለም(የፅሁፍ ክፍል) እና የድምፅ ክፍል ተብሎ በሁለት ዘርፎች ተከፍሎ ይሰራ የነበረ ሲሆን ጥሩ የፅሁፍ ችሎታ የነበራቸው አቶ ወንድሙ ወደ ፅሁፍ ክፍል በመቀላቀል በተለያዩ የዘመቻ ቦታዎች የሚገኙ ወታደሮችን እና አስተማሪ ታሪኮችን እጅግ በሚስብ እና ባማረ ቋንቋ በመፃፍ ለአድማጭ ጆሮ እንዲደርሱ በማድረግ ግዳጃቸውን ሲወጡ ቆይተዋል።

ጋዜጠኛ ወንድሙ በጊዜው ከኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ወታደራዊ ግንኙነት ስለነበራቸው እንደ ኩባ እና ራሺያ ያሉ ሀገራት ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ልምዶችን እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በዚሁ በርዕዮተዓለም ክፍል ውስጥ ሆነው ይዘግቡ ነበር።

ፈታኙ የጋዜጠኝነት ወቅት

ጋዜጠኛ ወንድሙ የተወሰኑ አመታትን በጦር ሃይሎች ሬድዮ ጣቢያ ካገለገሉ በኋላ በ1983 ዓ.ም የደርግ መንግስት ከስልጣን መወገዱ እውን ሆነ።በወቅቱ በተቀየረው መንግስት ሳቢያ ሬድዮ ጣቢያው የመበተን አደጋ አጋጠመው።

ይህ ወቅት እጅግ ፈታኝ ነበር።የሚወዱት ተቋም መፍረሱን ሲመለከቱ ዳግም ወደ ውትድርናው በመመለስ ወደ ጦላይ የጦር ማሰልጠኛ ተቋም በመግባት እና ለሁለት አመታት በመሰልጠን ወደ አዲስአበባ ተመለሱ።

ወንድሙ እና የኢትዮጵያ ሬድዮ

ከጦላይ ወታደራዊ ስልጠና ማዕከል በ1985 ዓ.ም ወደ አዲስአበባ የተመለሱት ወንድሙ ወትሮም ልምዱና ችሎታው ውስጣቸው አለና በኢትዮጵያ ሬድዮ በጋዜጠኝነት ሙያው በመወዳደር ለመቀጠር ብዙ ጊዜ ፣ተደጋጋሚም ሙከራ አላደረጉም።

የኢትዮጵያ ሬድዮን ከተቀላቀሉ በኋላ ቀድሞም በሚፅፏቸው ፅሁፎች ይታወቁ ስለነበረ እውቅናቸው በከፈተላቸው በር ተጠቅመው በቀላሉ የተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ፅሁፎችን በመፃፍ እና ለአድማጮች በማቅረብ ማገልገላቸውን ቀጠሉ።

ፀሀይ ተፈረደኝ እና ወንድሙ ከበደ

በኢትዮጵያ ሬድዮ ቤት በወቅቱ ‘በህይወት ዙሪያ’ የተሰኘ ፕሮግራም አዘጋጅ ከነበረችው እውቋ ጋዜጠኛ ፀሐይ ተፈረደኝ ጋር በመሆን የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችን እንዲሁም ኑሮን በተመለከተ በብዕር ስም የተለያዩ ፅሁፎችን ያዘጋጁ የነበረ ሲሆን ይህም ፕሮግራም በአድማጮች ዘንድ ተወዳጅነትን እንዳተረፈ ለሁለት አመታት የዘለቀ ነበር።

ጋዜጠኛ ወንድሙ ለጥቂት አመታት በተለያዩ የስራ ዘርፎች እና ሀላፊነቶች ካሳለፉ በኋላ በኢትዮጵያ ሬድዮ ለረጅም አመታት በአድማጮች ተወዳጅነት እንዳተረፈ የቆየውን ‘ኢትዮጵያን እንቃኛት’ የተሰኘ የሬድዮ ፕሮግራም አየር ላይ ከመዋሉ በፊት አስቀድሞ ጥሩ የአዘጋጅነት ብቃት ያላቸውን 3 ሰዎች ተመረጡ። ታዲያ ከነዚህ 3 ሰዎች አንዱ ወንድሙ ከበደ ነበሩ።

አቶ ወንድሙ የ’ኢትዮጵያን እንቃኛት’ ፕሮግራምን ከማዘጋጀት እና ከማቅረብ ባሻገር ኤዲተር በመሆንም ያገለግሉ እንደነበር በተቋሙ የታሪክ ማህደር በደማቅ የተፃፈ ታሪካቸው ነው።

ለስራቸው ካላቸው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ በወቅቱ ብዙም ያልተለመደውን ታሪካዊ ቦታዎችን በአካል በመሄድ ያዩትን እና የሰሙትን ነገር ለአድማጮቻቸው በአካል ተገኝተው የጎበኙ እስኪመስላቸው ምስል ከሳች ትንታኔዎችን ያቀርቡ ነበር።

ከነዚህም ስራዎቻቸው መካከል የማይረሳውና በብዙዎች ዘንድ እንዲታወሱ ያደረጋቸው ስራ አፄ ቴዎድሮስ ለነጮች እጅ አልሰጥም በማለት እራሳቸው ላይ ተኩሰው የሞቱበት ቦታው ድረስ በመሄድ ትልቅ ሀገራው ስሜት በአድማጮች ዘንድ እንዲጋባ ያደረጉበት ስራ መቼም የማይረሳ ነበር።

እንደአሁኑ ቴክኖሎጂ ባልረቀቀበት ጊዜ ከኋላ ቀር የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና ከጋዜጠኝነት ውጣ ውረድ ጋር እየተጋለጡ እስከ ኤዲተርነት ያገለግሉ የነበሩት ወንድሙ ትልቅ ችሎታ እንደነበራቸውም የተመሰከረላቸው ጋዜጠኛ ነበሩ።

ጋዜጠኛ ፀሀይ ተፈረደኝ ስለ ወንድሙ

“ከወንድሙ ጋር የተዋወቅነው 1978 ዓ.ም ጦር ሀይሎች ሬድዮ ጣቢያ ስንሰራ ነበር። በጣም ሰው አክባሪ፣ ስራውን የሚወድ፣ የቀረበው የሚወደው ሰው ነበር። በኋላ 1983 ኢህአዴግ ሲገባ ተቋማችን ተበተነ፤ተለያየን። እሱ ወደ ጦላይ ሄደ። እኔ 1985 ዓ.ም ኢትዮጵያ ሬድዮ ተቀጥሬ በነበረ ጊዜ በዚያው አመት ወንድሙም ከጦላይ ግዳጅ ተመልሶ ተወዳድሮ ኢትዮጵያ ሬድዮን ተቀላቀለ።

በድጋሚ አንድ ሚድያ ላይ የመስራት እድሉን ስናገኝ የተለያዩ ይዘቶችን በጋራ መስራት ጀመርን። ካነበብነው፣በህይወት ዙሪያ እና ጎረቤታሞቹን የመሳሰሉ ተዘዳጅ ዝግጅቶችን ተጣምረን ለአድማጮች ማድረስ ችለናል።”

የወንድሙ የስራ ላይ አጋጣሚ በፀሀይ ትውስታ

” ካነበብነው በመባል ይታወቅ የነበረው ዝግጅት ላይ በአንዷ ቀን ወንድሙ አንድ ታሪክን ያቀርባል። ታሪኩ በርካታ ባሎችን እያገባች ነገር ግን የምታገባቸው ባሎች ሁሉ የሚሞቱባት ሴትን ታሪክ ያነበበውን አጣቅሶ አቀረበ። በወቅቱ ታሪኩ ያልታሰበ ወከባ ፈጠረ። ‘ጥንቆላ እያቀረባችሁ ነው’ በሚል ብዙ ደረጃ ተደረሰ። በኋላ ግን ካነበብነው ላይ ያቀረብነው እንደሆነ በብዙ ጥረት አስረዳን።”

ባለቤታቸው ፀሀይ ይማም ስለመጨረሻዋ ጊዜ

” ከወንድሙ ጋር ያስተዋወቀኝ ኢቲቪ ነው። እኔ የድምፅ ባለሞያ ነበርኩ። በዚህ ምክንያት ለስራ መገናኘታችን አልቀረም። ተቀራረብን፣ ተዋደድን።፣ለ2 አመታትም በፍቅር ቆየን። በመጨረሻም ሰኔ 1 ቀን 1997 ዓ.ም ትዳር መስርተን ትዳራችን በአንድ ልጅ ደምቆልን ነበር።”

“..በጣም ስራ ይበዛበት ስለነበረ ውሎው የሩጫ ነበር። በዚያን ዕለትም ቀን ስራ ውሎ መጥቶ ምንም አይነት ህመም ሳይታይበት ነበር በድንገት ህይወቱ አልፎ ያገኘነው።”

ወታደርና ጋዜጠኛ ወንድሙ ከበደ በኢትዮጵያ ሬድዮ ብሎም በኢትዮጵያ የሚድያ ታሪክ ላይ አሻራቸው ጎልቶ ከሚታይ የሚድያ ባለሙያዎች ተጠቃሽ ነበሩ ። ጋዜጠኛ ወንድሙ የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ።

ጋዜጠኛ ወንድሙ ከበደ፣ በህዳር 6፣1999ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ ።

2 thoughts on “ወንድሙ ከበደ (1958-1999)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *