ክቡር አቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ ዶክመንተሪ ተመረቀ

አካለወርቅ ሀብተወልድ

ጥር 1 2013 አ.ም በክቡር አቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ዶክመንተሪ በብሄራዊ ቴአትር ተመርቋል፡፡የዚህ ዶክመንተሪ ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰር እዝራ እጅጉ ሲሆን ፕሮዲዩሰር ደግሞ አቤል እንዳቅሙ ነው፡፡ በዚህ ዶክመንተሪ ስራ ላይ በቪድዮ ቀረጻ እና በኤዲቲንግ አቢይ ተመስገን ውበቱ እና አንተነህ ዘለቀ ተሳትፈዋል፡፡

በእለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት በትምህርት ሚኒስቴር የስርአተ-ትምህርት ጀነራል ዳይሬክተር ክቡር ዶክተር ቴዎድሮስ ሸዋርገጥ ሲሆኑ እርሳቸውም ባደረጉት ንግግር የባለውለታዎችን ተሞክሮ በዲቪዲ እና በኦድዮ ሲዲ ማቅረብ ለአዲሱ ትውልድ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህ የምረቃ ስነ-ስርአት ላይ ለኢትዮጵያ ታላቅ ውለታ የዋሉ ባለውለታዎች ታድመው ስለ ክቡር አቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከታደሙት መሃልም ክቡር ደጃዝማች ወልደሰማእት ገብረወልድ ፣ ክቡር ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው ፤ አቶ አሰፋ አደፍርስ እና የመሳሰሉት ነበሩ፡፡

በእለቱ በክቡር አቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሙዚቃዊ ድራማ የቀረበ ሲሆን ለምረቃ ስነ-ስርአቱም ትልቅ ድምቀት የሰጠ ነበር፡፡

የዚህ ስራ ደራሲና አዘጋጅ አየሁ ሞላ የአሉላ አባ ነጋን ታሪካዊ ቴአትር ጽፎ ያዘጋጀ ሲሆን ‹‹ከአክሱም ጫፍ አቁማዳ›› የተሰኘውንም ሙዚቃዊ ቴአትር ያቀረበ ነው፡፡ በዚህ ሙዚቃዊ ድራማ ላይ በአድዋ ቴአትር ላይ የተወኑ ወጣቶችም ሙያዊ አቅማቸውንና ለእናት ሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር ያሳዩበት ነው፡፡

የእለቱ መድረክ መሪ ጋዜጠኛ ቤርሳቤህ ጌቴ ስትሆን ፕሮፌሽናሊዝምን በተከተለ መልኩ የመድረክ መሪነት ሚናዋን ተወጥታለች፡፡ በዚህ የምረቃ ስራ ላይ በማስተባበር ትልቅ ድርሻ የነበራቸው ሜቲ ቢራሳ ፤ ጸጋ ታሪኩ እና ሳምራዊት ተወልደ ነበሩ፡፡


ክቡር አቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ ሀገራቸውን በትምህርት ሚኒስትርነት፣ በእርሻ ሚኒስትርነት፣ እንዲሁም በፍርድ ሚኒስቴር በማገልገል ሙሉ አቅማቸውን ለሀገራቸው ያዋሉ ታላቅ ባለውለታ ናቸው፡፡ እኒህ ሰው በንጉሱ ዘመን የመሬት ይዞታ ማሻሻያ በ1956 ለንጉሱ ያቀረቡ ሲሆኑ በልዩ ልዩ የአውሮፓ ሀገራት በአምባሳደርነትም የሰሩ ናቸው፡፡

ዶክመንተሪውን የሰራው ድርጅት ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ከተመሰረተ 17 አመት የሆነው ሲሆን፣ በተለይ ‹‹ታሪክን በሲዲ›› በተሰኘው ፕሮጀክቱ ይታወቃል፡፡ የታላላቅ ኢትዮጵያውያንን ግለ-ታሪክ በሲዲ እያሳተመ የሚገኘው ይህ ድርጅት እስከ ዛሬ የ40 ግለሰቦችን ግለ-ታሪክ በ4 አመት ጊዜ ውስጥ አሳትሞ ለምረቃ ስነ-ስርአት እንዲበቁ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም 10 መጽሀፎችን ወደ ድምጽ በመቀየር ባህር ማዶ ለሚገኙ አድማጮች አቅርቧል፡፡ እስከዛሬ ካሳተማቸው ውስጥም የጸሀፌ-ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ፣ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ፣ የንጉስ ምኒሊክ ፣ የጃገማ ኬሎ እንዲሁም የልጅ እንዳልካቸው መኮንን ታሪክ እና የሌሎችም ይገኙበታል::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *