ኪሮስ ሃይለስላሴ
ሁለ ገቡ የኪነጥበብ ባለሙያ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡
በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል የኪነጥበብ ባለሙያው ኪሮስ ሀይለስላሴ ይገኝበታል፡፡ ባለሙያው ኪሮስ በጥበቡ አለም ላለፉት 40 አመታት ሲቆይ ከትወና ጀምሮ በቴአትር አለም እና በፊልም ስራ ውስጥ ትልልቅ ሙያዊ አበርክቶ የሰጠ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ዝናሽ ካልአዩ የህይወት ታሪኩን ሰንዳዋለች፡፡
ውልደት እና እድገት
ኪሮስ ሃ/ስላሴ ትግራይ ክልል አድዋ አውራጃ ማይ ቅነጣል ወረዳ በምትባል የገጠር ከተማ ነበር ከአባቱ አቶ ሃ/ስላሴ ረዳ እና ከእናቱ ወ/ሮ ዘውዲቱ ገ/ዝጊ መጋቢት 27 1947 ዓ/ም የተወለደው ። ኪያ/ኪሮስ/ ወላጆቹ ተስለው ያገኙት የስስት ልጃቸው ነው። ወላጅ አባቱ ፖሊስ ስለ ነበሩ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ግዴታ ሆኖባቸው ከማይ ቅንጣል ወደ ውቅሮ ከተማ በመሄድ እዛው ትምህርቱን መከታተል ጀመረ።ብዙም ሳይቆይ ወደ አፅቢ ወንበርታ ተመለሰ።ቀጥሎም ስንቅ አጣ (ፍረወይኒ ) ወደ ምትባል ከተማ በመጓዝ የ3ኛ እና 4ኛ ክፍል ትምህርቱን ተከታተለ።
በመጨረሻም ወደ ውቅሮ ክልተ አውላዕሎ በመመለስ ከ4ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ትምህርቱን መማር ጀመረ ።በግዜው አብሮት ይማር ከነበረው ታዋቂው የትግርኛ ሙዚቃ አቀንቃኝ ኪሮስ አለማየሁ ጋር በመሆን በቦይስ ስካውት ክበብ ፣የትያትር እና የሙዚቃ ክበብ ላይ በንቃት በመሳተፍ ያለውን የኪነ-ጥበብ ተሰጥኦ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የተለያዩ ቀልዶችን በማቅረብ እና መድረክ በመምራት በወቅቱ የብዙ መምህሮቹ እና አብሮ አደግ ጓደኞች ቀልብ መግዛት የቻለ ልጅ ነበረ ።
ይሁንና የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና ሳይወስድ ትምህርቱን አቋርጦ ወደ አስመራ ተጓዘ። አስመራ የተወሰኑ ጊዜያት ያለትምህርት ካሳለፈ በኋላ ወደ አዲስአበባ መጥቶ ቋንቋ በመማር በካቶሊክ ካቴድራል ትምህርት ቤት ገብቶ ስምንተኛ ክፍል እንደ አዲስ ተምሮ ሚኒስትሪ ተፈትኖ በጥሩ ውጤት ሲያልፍ የትምህርቱ ላይ ጠነከረ፡፡ የዩኒቨርስቲ ውጤት አምጥቶም በ1972 ዓ/ም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብቶ በ1975 ዓ/ም በትያትር ጥበባት የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ።ኪሮስ በህግም የዲፕሎማ ምሩቅ ነው።
የስራ አለም
ኪሮስ ሃ/ስላሴ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመርቆ ከወጣ በኋላ በ 1976 ዓ.ም ወደ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሲመደብ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ደግሞ ወደ ሀገር ፍቅር ትያትር ቤት መደበው።በዚያ ስፍራም የፕሮግራም የፕሮዳክሽን ፣የመድረክ አርትስቲክ ማኔጀር በመሆን የስራውን አለም ግማሹን እድሜው በሀገር ፍቅር እንድያሳልፍ ምክንያት ሆኖቷል።ሀገር ፍቅር ይሰራ በነበረበት ግዜ ለወጣት ከያንያን እድል በመስጠት ያበረታታ እንደነበር ብዙዎች ይመሰክሩለታል፡፡ ተሻለ ወርቁ በአንድ ወቅት ለሚድያ በሰጠው ቃለ መጠይቅም ያኔ በልጅነታችን ትያትር ይዘን ወደ ተለያዩ ትያትር ቤቶች ስንሄድ እንኳንስ ሊቀበሉን ከበሩ ይመልሱን ነበር፡፡ ኪሮስ ይመራው የነበረውን ሀገር ፍቅር ትያትር ቤት ግን ስራችንን ተቀብለው እንደጀማሪ ባለሙያ አስተናግደውናል ።ምናልባትም እንደደከምነው ብዛት እና እንዳንኳኳነው በር አሱ ባይቀበለን ኖሮ ዛሬ ላይ በዚህ ሙያ ውስጥ ስለመዝለቄ እጠራጠራለሁ ሲል ይመሰክራል።
ከሀገር ፍቅር ከወጣ በኋላ ወደ ባህል እና ማስታወቂያ ቢሮ (ማዘጋጃቤት )በመሄድ የስነጥበባት ማስተባበሪያ ቡድን መሪ በመሆን በርካታ ስራዎችን ሰርቷል። ቀጥሎም የባህል መምሪያ ኋላፊ በመሆን አራቱን ትያትር ቤቶችን የአዲስ አበባ ሙዝየም ፣የአ/አ ቤተ መፃህፍትን ጨምሮ በማስተዳደር አገልግሏል።በመቀጠልም ከ1999 ዓ/ም ጀምሮ እስከ 2001 ዓ/ም የአ/አ ከተማ ሚሊንየም ምክር ቤት ፅሕፈት ቤት ዋና ዳይሬተር ሆኖ ሲሾም በግዜው ታቅደው የነበሩትን 22 ፕሮጀክቶችንም በማስፈፀም የማስተዳደር ችሎታውን አስመስክሯል ።በመጨረሻም ይሄን ስራ ለቆ ቀድሞ ወደ ነበረበት ወደ ባህል መምሪያ ተመልሶ 8 ወራትን ካገለገለ ቡኋላ እድሜው ሳይደርስ ቀድሞ ጡረታ ወጥቷል።
የመድረክ ትያትሮች
ኪሮስ ሃ/ስላሴ መድረክን የሚሞላ ሞገስ ያለው ድንቅ ባለሙያ እንደሆነ የሙያ አጋሮቹ ይመሰክሩለታል ።ሳልሳዊ ባልንጀራ፣ባልቻ ኣባነፍሶ፣የቬንሱ ነጋዴ፣አሉ እና ጠልፎ በኪሴን ጨምሮ ከ18 በላይ የሙሉ ጊዜ ትያትሮችን በትወና ተሳትፏል።
የቴሌቪዥን ድራማዎች
ገና ያኔ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጥቁርና ነጭ ከነበረበት ዘመን አንስቶ እስከ አሁኑ ቴክኖሎጂ በተራቀቀበት በዚህ ዘመን በርካታ ተከታታይ ድራማዎችን ሰርቷል።ገመና 1 እና 2 እንዲሁም ዳና ያየሰው ኪሮስን እና የትወና ብቃቱ አለማሰብ አይችልም። በቋንቋ ችሎታው አጃኢብ የተባለለት ኪሮስ በአማርኛ በቻ ሳይሆን በትግርኛም ጭምር ሓድጊ፣እዛ መሬት፣ፀዋር ልቢ የተሰኙ ተከታታይ ድራማዎች ላይ መተወኑ የብዙዎችን ቀልብ ለመግዛት ምክንያት ሆነውታል።ጣውንቶቹ ፣፣የመንታ እናት ደግሞ በአዘጋጅነት የተሳተፈባቸው ስራዎቹ ናቸው።
የፊልም ስራዎች
ከ16 በላይ ፊልሞች ላይ በትወና የተሳተፈው ኪሮስ ሰማያዊ ፈረስ፣ስጋ ያጣው መንፈስና ስላንቺ፣ በጥላሁን ታፈረ የተፃፈው 15ኛው ደቂቃ ኦፕሬሽን ዘመን የማይሽራቸው የፊልም ስራዎቹ ናቸው።ተተኪ ባለሙያዎች እንዲፈሩ ለጀማሪ ባለሙያዎች የነበረው ትልቅ ተስፋ ለማበረታታት ሲል ብዙ ግዜ ያለውን እውቀት እና ችሎታ ሳያይ ስለ ገንዘብ ውል ሳይጠይቅ እንዲሁ ስራውን ብቻ ተቀብሎ የሰራቸው በርካታ ስራዎች እንዳሉ እና ከነጭራሹም ሳይከፈለው የቀሩ ስራዎች እንዳሉ በመግለፅ ይህ ደግሞ ለሙያው ስላለው ክብር እንጂ ገንዘብ እንደማያስጨንቀው የሙያ ባልደረባው እና ጓደኛው ኩራባቸው ደነቀ ይናገራል፡፡
የሬድዮ ስራዎች
የድምፁ ጉልበት ብዙዎችን ይማርካል፡፡ ከያኒው ምስል እየከሰተ ማውራትም ሆነ መተወን ተክኖበታል።ከነ መአዛ ብሩ ፣ተፈሪ አለሙ፣መንበረ ታደሰ እና ሌሎች ጋር በመሆን የእሁድ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ መፃህፍት በመተረክ፣መጣጥፎች በማንበብ ፣ድራማዎችን በመስራት ኪሮስ የብዙ አድማጮች ትዝታ ሲሆን በሸገር ይተላለፍ የነበረውን የጥበብ መንገድ የተሰኘ ፕሮግራም ከባልደረባው ተስፋዬ ማሞ ጋር በመሆን ያቀርብ ነበር።
መድረክ መምራት
አንደበተ ርቱእ እና የተረት አባት እያሉ ጓደኞቹ ሲያሞካሹት ይሰማል።ለዚህም ይመስላል የተለያየ ይዘት ያላቸውን ከ166 በላይ የመራቸውን መድረኮች መለስ ብለን ስናጤናቸው አንደበተ ርቱእነቱ የሚያረጋግጡልን ናቸው።የድጋፍ ማሰባሰብያ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች፣የልማት ማህበራት ማሰባሰቢያ ሁነቶች፣እና ሌሎች ፋይዳ ያላቸው የህዝብ መድረኮች ላይ መድረክ በመምራት ኪሮስ ሃ/ ስላሴ ግንባር ቀደም ተሰላፊ ነው።ሮም ተወስዶ የነበረውን የአክሱም ሀውልት ሲመለስ፣የህዳሴ ግድብ ፣የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አስመልክቶ የመራቸው መድረኮች እና እያዋዛ ያስተላለፋቸው መልዕክቶች በቀላሉ የሚዘነጉ አይደሉም።
ሽልማት
በዋለበት ሁሉ ከልቡ ማገልገል መለያው ነው። ኪሮስ የታማኝነት ምልክት ነው ሲልም ተሻለ ወርቁ ይመሰክርለታል።በጥበቡ አለም ላበረከተው አስተዋጽኦም ሽልማቶችን ተበርክቶለታል። በምርጥ የትወና ብቃቱ ብዙዎቹን ይስማሙበታል።ለዚህም ማሳያ ይሆነን ዘንድ ጥቂቶቹን እንጥቀስ፡፡ ከጠቅላይ ሚኒሰቴር አብይ አህመድ ከፍተኛ የኪነጥበብ የህይወት ዘመን ተሸላሚ ተብሎ ተሸልሟል ።ከኢትዮ ፊልም አዋርድ ስላንቺ በተሰኘው ፊልም በምርጥ አጋዥ ተዋናይ ሽልማት ተበርክቶለታል ። ራክማኖቭ የትያትር ኮሌጅ በሰማያዊ ፈረስ ሸልሞታል፡፡ ከጉማ አዋርድ የህይወት ዘመን ተዋናይ ተሸላሚ ሲሆን ከተለያዩ ተቋማትም በርካታ የምስጋና ምስክር ወረቀቶች ተበርክተውለታል።
የትዳር ህይወት
ኪሮስ ምርጥ የኪነጥበብ ባለሙያ ብቻ ሳይሆን ምርጥ ባል እና አባትም እንደሆነ ቤተሰቦቹ ይናገራሉ። ሀገር ፍቅር ትያትር ቤት በተወዛዋዥነት ትሰራ ከነበረችው የሙያ ባልደረባው ወ/ሮ ፀዳለ ግርማ ጋር በ1978 ዓ.ም ትዳር መስርቶ ልጆች አፍርቶ ለቁምነገር ያበቃ ብርቱ ሰው ነው።
መዝጊያ
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ የቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ በሀገራችን ለኪነጥበብ ቅድሚያ ከሰጡ ባለሙያዎች አንዱ ኪሮስ ነው፡፡ ለሙያው ብዙ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ከኪነጥበብ ሰውነቱ ባሻገርም እንደ መሪም ያኖረው አሻራ ከትልቅ መዝገብ ላይ ስሙን እንድናሰፍር የሚያደርገን ነው፡፡ በሰራቸው ፊልሞችና መድረኮች ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ የሰራ ሰው ነው፡፡ ለዚህ አበርክቶው ደግሞ ልናመሰግነው ይገባል፡፡ ወጣቶች እንዲበረታቱ በማድረግ በኩል የእርሱ ሚና ትልቅ እንደነበር የያኔ ወጣቶች የዛሬ ጎልማሶች ይናገራሉ፡፡ ደግሞም ትክክል ነው ፡፡ ታላቅ ለታናናሽ እድል ሲከፍት ጥበብ ቀን ይወጣላታል፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች ከታሪክ መዝገብ ሲሰፍሩ አንደኛ ራሳቸውን ያበረታታል፡፡ ለካስ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረኝ እንዲሉ ያስችላል፡፡ ሁለትም አዲሱ ትውልድ ልምድ የሚቀስምበትን እድል ያገኛል፡፡ እነሆ ኪሮስ ላበረተከው አመስግነናል፡፡ ይህ መዝጊያ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተጻፋ ሲሆን የህይወት ታሪኩን በማሰናዳት ደግሞ ዝናሽ ካልአዩ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራት፡፡