ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ከሰዎች የህይወት ታሪክ በተጨማሪ የተቋማት ታሪክ ብዙ የሀገር እውነት ይዟል ብሎ ያምናል፡፡ ይህን እምነቱን ለማራመድም የተቋማትን ሰነዶች እየመረመረ ፤ እያፈላለገ ለትውልድ ያቀብላል፡፡ በታህሳስ 1943 የዛሬ 72 አመት አንድ ብሎ የጀመረው የኢትዮጵያ የዩኒቨርሲቲ ታሪክ ብዙ ታሪካዊ ክስተቶች አሉት፡፡ ይህን የሀገር ሀቅ እዝራ እጅጉ ሰንዶታል፡፡
ዘመናዊ ትምህርት በሀገራችን የተጀመረው በዳግማዊ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት ነበር፡፡ የትምህርት ቤቱም ስም ዳግማዊ ምኒሊክ ይሰኛል፡፡ጊዜውም በ1899 ነበር፡፡ እርግጥ ነው ከዚህ ትምህርት ቤት ቀደም ብሎ የመጀመርያው የሙዚቃ ትምህርት ቤት መከፈቱ ይታወቃል፡፡ ዳግማዊ ምኒሊክም ሰኔ 26 1898 በጻፉት ደብዳቤ ልዩ ችሎታ ያላቸው ግብጻውያን መምህራን እንዲላኩላቸው ጠይቀው ነበር፡፡ በጠየቁት መሰረትም በሙሴ ሀና ሳሌብ የሚመራ 3 ግብጻውያን በጥር 1899 መጥተው በ1900 ተጀመረ፡፡ በጊዜው ይሰጥ የነበረው ትምህርት በይበልጥ ቋንቋ ላይ ነበር፡፡ ከሀገር ውስጥ ቋንቋ ከአማርኛ እና ከግእዝ ሌላ እንግሊዝኛ ፤ ፈረንሳይኛ፤ ጣሊያንኛ ስእል እንዲሁም የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡
ዳግማዊ ምኒልክ አሁን ያለበት ህንጻ ከመሰራቱ በፊት ትምህርቱ ይሰጥ የነበረው እሪ በከንቱ አካባቢ በሚገኘው በሙሴ ኢልግ ቤት ነበር፡፡ዳግማዊ ምኒሊክ በሌሎች ከተሞችም ተማሪ ቤቶች እንዲከፈቱ በማድረጋቸው በድሬደዋ ፤ በደሴ በሀረር ትምህርት ቤቶች ሊከፈቱ ችለዋል፡፡ በጠቅላላ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሀገራችን እስከተጀመረበት ጊዜ ድረስ 30 የሚጠጉ መደበኛ ተማሪ ቤቶች ነበሩ፡፡ በዛን ወቅት የነበሩ አጠቃላይ የተማሪዎች ብዛትም ወደ 5000 ይጠጉ ነበር፡፡
የእነዚህ ተማሪዎች ለዩኒቨርሲቲ ብቁ ሆኖ መገኘት ኮሌጅን በሀገራችን ለመጀመር እንደ ዋና ምክንያት የሚቆጠር ነበር፡፡ ጣሊያን ተሸንፎ ከሀገር ቤት በወጣ ልክ በ9 አመቱ ሀገራችን የመጀመሪያውን ዩኒቨርሲቲ ለመመስረት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጠች፡፡ ‹‹ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ›› በሚል ስያሜ ጥቅምት 23 1942 ዓ.ም ይህ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠ በኋላ ሀገራችን ወደ አንድ እድገት መገስገስዋ ታመነበት፡፡በታህሳስ 1 ፣1943 የዛሬ 72 አመት በይፋ ስራውን የጀመረው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሲጀመር 9 መምህራንን ነበሩት፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዩኒቨርሲቲ የገቡት ተማሪዎች ቁጥርም 72 ይጠጋ ነበር፡፡
ከእነዚህ ተማሪዎች ውስጥም 13ቱ በነሀሴ 1946 በዲግሪ ለመመረቅ ችለዋል፡፡ ከ13ቱ የመጀመሪያ ምሩቃን መካከል የህግ ምሁሩ አቶ ተሾመ ገብረማሪያም ይነሳሉ፡፡ ከ6 አመት ቀደም ብሎ ህይወታቸው ያለፈው አቶ ተሾመ ገብረማርያም ፣ የዩኒቨርሲቲ ትዝታቸውን ሲያወጉ ብዙ ቁምነገር የቀሰሙበት ማእከል እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ እኒህ ሰው በካናዳው የማክጊል ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ተከታትለዋል፡፡ በተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ከማገልገላቸው በተጨማሪ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ፣ ሚኒስትር ድኤታም ነበሩ፡፡ በደርግ ዘመነ መንግሥት ከሥልጣን ጓደኞቻቸው ጋር በእስር ቆይተዋል፡፡ ለረጅም ዓመታት በግል የሕግ አገልግሎት ይሰጡ ነበረ፡፡ አቶ ተሾመ ገብረማርያም ከ6ዓመት በፊት ለሥራ ናሚቢያ በሄዱበት ወቅት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ባለፉት 72 አመታት፤ 12 ሰዎች በፕሬዚዳንትነት መርተውታል፡፡ በ1943 ለመጀመሪያ ጊዜ ዩኒቨርሲቲውን በፕሬዚዳንት የመሩት ዶክተር ሉሲዮ ማት ናቸው፡፡ከእርሳቸው በመቀጠል ከ1954- 1961 ዩኒቨርሲቲውን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ልጅ ካሳ ወልደማሪም ናቸው፡፡ ይህም ልጅ ካሳ ወልደማሪያምን ዩኒቨርሲቲን በመምራት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ያደርጋቸዋል፡፡ በ1946 ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ 13 ተማሪዎች ሲመረቁ ዶክተር አክሊሉ ሀብቴም አንዱ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ሰአት በአሜሪካን ሀገር የሚኖሩት ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ ከ1961-1966 ድረስ 3ኛው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡ እርሳቸውም ከ13ቱ ምሩቃን አንዱ ነበሩ፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በፕሬዚዳንትነት ለረጅም አመታት በማገልገል ስማቸው የሚጠራው ዶክተር ዱሪ መሀመድ ናቸው፡፡ እርሳቸውም ከ1969-1977 እንዲሁም ደግሞ በድጋሚ ከ1985-1988 ድረስ ዩኒቨርሲቲውን በመሪነት አገልግለዋል፡፡ ዶክተር ዱሪ ህይወታቸው ካለፈ 10 አመት አልፎታል፤፤ ‹‹ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ›› በዚህ ስሙ እየተጠራ ለ11 አመት ከዘለቀ በኋላ፣ በ1954 ‹‹የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ›› ተባለ፡፡ይህን ስያሜ ካገኘ በኋላ ፣ ከዩኒቨርሲቲው የተመረቁት ወይዘሮ ሂሩት በፍቃዱ ዩኒቨርሲቲው ትልቅ የህይወት መሰረት አስቀምጦላቸው እንዳለፈ ይናገራሉ፡፡ በፖለቲካ ሳይንስና አለምአቀፍ ግንኙነት የተመረቁት ወይዘሮ ሂሩት በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በሌሎችም ታዋቂ መስሪያ ቤቶች ሰርተዋል፡፡
በ1954 የቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ፣ 2,047 ተማሪዎችን ሲመዘግብ ከእነዚህ ውስጥ በ6ኪሎ 536ቱ፣በእርሻ ኮሌጅ 224 ፣ በመሀንዲስ ኮሌጅ 167 ፣ በህንጻ ኮሌጅ 108 ፣ በጎንደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 261 ፣ በመንፈሳዊ ኮሌጅ ደግሞ 11 ተማሪዎች ተመዝግበው ነበር፡፡በዛን ጊዜ አንድ ተማሪ በዩኒቨርሲቲ ለመመዝገብ ከ50-59 ውጤት ማግኘት አለበት፡፡ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜም የጽሁፍና የቃል የመግቢያ ፈተና ይሰጥ ነበር፡፡ የያኔው የቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ሲመሰረት ፣ ከ216 በላይ እንግዶች በልደት አዳራሽ ታድመው ነበር፡፡ ፡ የዛሬ 61 አመት ታህስስ 9 ቀን ነበር ጊዜው ::
ግርማዊ ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ ገነተ- ልዑል ቤተ መንግስታቸውን ቀዳማዊ ኃይለ- ስላሴ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ያበረከቱበት ቀን ነው ታህሳስ 9 1954 :: ከቤተ- መጽሀፍት የተገኘው የጥሪ ካርድ ጃንሆይ የግል ርስታቸው የሆነውን ገነተ- ልዑል ቤተ-መንግስትን ዩኒቨርሲቲ ሲያደርጉት ትልቅ በዓል መደረጉን ይናገራል፡፡ የጥሪ ካርዱ እንዲህ ይላል፦‹‹……. ግርማዊ ንጉሰ-ነገስት ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ከስመ-ጥር አባታቸው ከልኡል ራስ መኮንን በውርስ ያገኙትን የግል ርስታቸውን ገነተ-ልኡል ቤተ-መንግስታቸውን ለዩኒቨርሲቲ በሰጡበት ቀን ሰኞ ታህሳስ 9 1954 ከጠዋቱ 4ሰአት ከ45 በገነተ-ልኡል ቤተ-መንግስት እንዲገኙ መጠራትዎንና ከበአሉም በኋላ በልደት አዳራሽ ምሳ መጋበዝዎን እናሳውቃለን፡፡ ልብስ ሞርኒንግ ኮት፡፡ በታይፕ ራይተር የተተየበውና ፣ከንጉሰ-ነገስቱ የልፍኝ አስከልካይ መዝገብ ቤት አቶ ገብረመድህን ባራኪ ያገኙት ባለ 3 ገጽ ሰነድ ላይ እነማን በቀሀስ ዩኒቨርሲቲ ምስረታ በአል ላይ እንደታደሙ ይነግረናል፡፡ በዚህ ሰነድ ላይ ማን ከማን ጎን ተቀምጦ ምሳ ይመገብ እንደነበር ሰነዱላይ ሰፍሮአል፡፡
ደግሞ ሌላም በምሳ ግብዣው ላይ የተገኙ ሰዎች ከስማቸው ጎን የራይት ምልክት ተደርጎአል፡፡ ላልተገኙት ደግሞ የኤክስ ምልክት ይደረጋል፡፡ በዚህ ግብዣ ላይ ከታደሙ ዋና ዋናዎቹ እንግዶች መሀልም ልዑል አልጋ ወራሽ፣ ራስ እምሩ ኃይለስላሴ ፤ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ፤ ክቡር ፀሀፌ- ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ እና ሌሎችም ተገኝተው ነበር ፡፡ በነገራችን ላይ የአዲስ አበባ ኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውን መምህራን ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያምና አቶ መሀመድ ዩሱፍ ናቸው፡፡ የቀሀስ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ሬጅስትራር ዶክተር ማርጋሬት ጂሌት ይባላሉ፡፡የዩኒቨርሲቲውን የትምህርት አይነቶች የሚገልጸውን ካታሎግ በመጋቢት ወር 1954 ታትሞ እንዲውጣ ትልቅ ሚና ያበረከቱ ሰው ናቸው፡
በሀገራችን የህክምና ትምህርት በ1950ዎቹ ሲጀመር የዛን ጊዜው የልኡል መኮንን ሆስፒታል ያሁኑ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የግንባታ ስራ ተጀምሮ ነበርና ለጤናው ዘርፍ አንድ መፍትሄ ተገኝቶ ነበር፤፤የሆስፒታሉን የግንባታ ስራ ያከናወነው የዩጎዝላቪያ ኩባንያ የሆነው ዩኒየን ኢንጂነሪንግ ነበር ኩባንያው የግንባታ ስራውን በ40 ወራት ውስጥ ያጠናቀቀ ሲሆን ለዚህም የሀገራችን መንግስት 15 ሚልዮን ብር ሊያወጣ ችሎአል፤፤ከታካሚዎች ባሻገር የህክምና ተማሪዎች እውቀት ሲቀስሙበት የነበረው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሀገሪቱ የዩኒቨርሲቲ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚናለማበርከት የቻለ ስለመሆኑ በብዙዎች ይመሰከርለታል፡፡ በአሁኑ ሰአት በህይወት የሌሉትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ፋክልቲ ቀደምት መምህር በመሆን ያገለገሉት፤ ፕሮፌሰር ጀማል አብዱልቃድር በርካታ ሀኪሞችን በማፍራት ታላቅ ውለታ የዋሉ ምሁር ናቸው፡፡
በውስጥ ደዌ ሀኪምነታቸው ስመ ጥር የነበሩት ፕሮፌሰር ጀማል በተለይ ከማስተማር ስራቸው ሌላ የዩኒቨርሲቲው የሜዲካል ጆርናል የበላይ ኃላፊ በመሆን ሰርተዋል፤ ከአዲስ አበባ ባሻገር በሀገራችን የዩኒቨርሲቲ መከፈት ታምኖበት በሰሜኑና በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ዩኒቨርሲቲ ሊመሰርት ችሎአል፡፡ ‹‹ባህር ዳር ፖሊ ቴክኒክ›› በዚህ መልክ ከተመሰረቱት መካከል አንዱ ነበር፡፡ታህሳስ 21 1954 የመሰረት ድንጋዩ የተቀመጠለት፣ባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ ባለፉት 61 አመታት ጊዜ ውስጥ በርካታ የእድገት ደረጃዎችን አልፎአል፡፡ መስከረም 19 1956 ላይ 250 ተማሪዎችን በመቀበል የማስተማሩን ስራ አሀዱ ያለው ‹‹ባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ››፣ ዛሬ በስኳር፣በጨርቃጨርቅ ፣ በኬሚካልና በሌሎችም የኢንዱስትሪ ዘርፎች በርካታዎችን በማፍራት ላይ ይገኛል፡፡
አቶ ገበየሁ አያሌው፣ በ1950ዎቹ በባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ ከተማሩት አንዱ ናቸው ፡፡እርሳቸው እንደነገሩን ፣ በዛን ወቅት ባህር ዳር ወንዶችን ብቻ ነበር ይቀበል የነበረው፡፡
በሂደትም ሴት ተማሪዎች መቀላቀላቸውን አቶ ገበየሁ ያስታውሳሉ፡፡ ተማሪ አልማዝ አርአያና ተማሪ አለሚቱ አብርሀም የመጀመሪያዎቹ የባህርዳር ሴት ተማሪዎች ነበሩ፡፡ በ1956 ባህርዳር ማስተማር ሲጀምር፣ 21 ኢትዮጵያውያን መምህራን የነበሩት ሲሆን የመጀመሪያው የባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ በክሪ አብዱላሂ ይባሉ ነበር፡፡ ‹‹ባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ›› ከተማሩት መካከል ታዋቂዎችን ጥቀሱ ብንባል በአሁኑ ሰአት በህይወት የሌሉት የናሳው ሳይንቲስት ቅጣው እጅጉን እንዲሁም ከፖለቲካው መስክ የሀገራችን የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ስዩም መስፍንን እናነሳለን፡፡
ከባህርዳር ወጥተን ወደ ጎንደር ስንገባ አንጋፋውን ‹‹ጎንደር ዩኒቨርሲቲ››ን እናገኛለን፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዛሬ 69 አመት ሲመሰረት፣ካፒታል በጀቱ 50ሺህ ብር ነበር፡፡ በ1961 ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 15ኛ አመት የምስረታ በአሉን ባከበረ ጊዜ 133 ወጣቶች ዲግሪና ዲፕሎማቸውን ተቀብለዋል፡፡ ሀምሌ 12 1946 የተመሰረተው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ በ63 አመት ውስጥ 30ሺህ የጤና ባለሙያዎችኝ አስመርቆአል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 200 የሚሆኑት በአለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በምርምርና በማስተማር ስራ ላይ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪዎች መካከል ፣ ፕሮፌሰር አታላይ አለም ይጠቀሳሉ፡፡
የመጀመሪያው የሀገራችን የቴክኖሎጂ ፋክሊቲ ኢምፔሪያል ኮሌጅ ኦፍ ኢንጂነሪንግ በሚል ስያሜ በ1945 በሜክሲኮ አደባባይ በሚገኘው አንድ ጥንታዊ ህንጻ ውስጥ ነበር የተመሰረተው፡፡በዚህ ተቁዋም ውስጥ የነበረው ፤በውጭ ሀገር የምህንድስና ትምህርታቸውን ለመከታተል ለሚችሉ ተማሪዎች የሚረዳ የ2አመት የመሰናዶ ትምህርት ነበር፡፡ ይህ ተቁዋም እንደ ኤሮፓ አቆጣጠር ከ1969 ጀምሮ ወደ 5ኪሎ ካምፓስ በመሸጋገር አሁን ባለበት ሁኔታ በ3 የምህንድስና ዘርፍ ማለትም በሲቪል ፣በኤሌክትሪክ በሜካኒካል ትምህርቱ በሀገር ውስጥ በሰፊው መሰጠት ተጀመረ፡፡ ኢንጂነር ሰይፉ ለማ በአሁኑ ሰአት የ83 አመት ሰው ናቸው፤፤ በ1955ሰኔ 24 ቀን ሀገራችን የመጀመሪያዎቹን የኤሌክትሪክ መሀንዲሶች ስታስመርቅ ኢንጂነር ሰይፉ አንዱ ነበሩ ፤፤
ኢንጂነር ሰይፉ 50 አመት በላይ ወደ ሁዋላ ተጉዘው ስለ መምህራኖቻቸው አስታወሱ ፤፤ በተለይ በዛን ወቅት በመብራት ሀይል መስሪያ ቤት የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ መሀንዲስ የሆኑት ኢንጂነር አሰፋ ጥላሁን ፤ ገና ተማሪ የነበሩትን እነ ሰይፉን ለማስተማር ይተጉ ነበር ፤ ጋና በ1949 ነጻነትዋን ከተቀዳጀች በሁዋላ በ1950 ፤ ስምንት ነጻ የአፍሪካ መንግስታትን ያገናኘ ስብሰባ አካሄደች፤ ሀገራችንም በአቶ አበበ ረታየልኡክ መሪነት በዚህ ጉባኤ ላይ ተሳትፋለች፤ በዚህ ጉባኤም ላይ ሀገራችን ለ50 የአፍሪቃ ወጣቶች ነጻ የትምህርት እድል እንደምትሰጥ አሳወቀች፤ በዚሁም መሰረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ የመጀመሪያዎቹ የነጻ ትምህርት እድል ተጠቃሚዎች በ1951 ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ፤ ከእነዚህ ተማሪዎች መካከልም ኬኒያዊው ኦሞጊ ካሌብ በ1952 የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የተማሪዎች ምክር ቤት ጸሃፊ በመሆን አገልግሎአል፤ በዚህ ወቅትም የሀገራችን ተማሪዎች ለአፍሪቃ ወንድሞቻቸው ያላቸውን በጎ እሳቤ አሳይተዋል ፤ከአፍሪካ ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች በቅኝ ግዛት ባልተገዛች ሀገር በኢትዮጵያ የተመሰረተው ‹‹ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ›› ከሁሉም የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች በእድሜ ትልቁ ወይም አንጋፋው ነው፡፡
72 አመት ብዙዎችን እውቀት በማስታጠቅ ዘልቋል፡፡ ባለፉት 72 አመታት 222000 ተማሪዎች ከዚህ አናጋፋ ተቋም ተመርቀዋል፡፡ ቀዳማዊ ሀይለስላሴም፣ በታህሳስ 10 1954 ባደረጉት ንግግር ‹‹….በዚህ ዩኒቨርሲቲ መመስረት አእምሮአችን ደስ አለው፡፡ ህሊናችንም ተነፈሰ›› ብለው መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ እርሳቸውም በዛን ወቅት ታሪካዊ ንግግራቸውን በመቀጠል፣ ‹‹ለእኛ ሀውልት የሚሆነን ድንጋይ አይደለም ፡፡የእኛ ሀውልት የትውልድ ጉልበት የሆነው ትምህርት ነው፡፡›› በማለት ንግግር አድርገው ነበር፡፡ እነሆ የዩኒቨርሲቲ ታሪክ ታህሳስ 2015 ላይ 72 አመት ሞላው፡፡