አስታጥቃቸው ይሁን ፋንታ

አስታጥቃቸው ይሁን ፋንታ ዕውቅና ቢሰጠው ስንል ታሪኩን አቅርበናል

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን፣ መዝገበ-አእምሮ (የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል።

ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች፣ በመጽሐፍ፣ በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት 4 ዓመታት ከ5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መጽሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።

በሚድያና ኪነ ጥበብ ዘርፍ የሕይወት ታሪካቸው ከሚሰነድላቸው መካከል አስታጥቃቸው ይሁን ፋንታ ይጠቀሳል። አስታጥቃቸው ታሪኩን ለተወዳጅ ሚድያ ፈቅዶ የሰጠ ሲሆን ፅሑፉንም ዕዝራ እጅጉ እና አይናለም ሀድራ እንደሚከተለው አጠናክረውታል።

በ1976 ዓ.ም ነው… ጋሽ ተስፋዬ ገሰሰ ” ሀገር ፍቅር ሲለመልም” ብሎ ‘የዛሬይቱ ኢትዮጵያ’ ጋዜጣ ላይ አንድ ጽሁፍ አሰፈረ፡፡ የጽሁፉ ይዘት ተስፋ፣ አድናቆትና ደስታን አዝሏል ፡፡ ተመስገን… ጎሽ… ለቲያትር ወርቃማ ጊዜ መጣላት፤ አይናችን ድንቅ ነገር አየ ሲልም ስሜቱን ገለጸ፡፡

ነገሩ የሆነው “ሣልሣዊው ባልንጀራ” የተሰኘው ተውኔት በሀገር ፍቅር ቴአትር ለዕይታ በበቃበት ጊዜ ነው፡፡ “ሣልሳዊው ባልንጀራ” የአንጋፋው የኪነ-ጥበብ ሰው አስታጥቃቸው ይሁን ሥራ ነው፡፡ በወቅቱ ጋሽ ተስፋዬ ገሰሰ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት ክፍል ኃላፊ ነበር፡፡ ታዲያ በአስታጥቃቸው ሥራ እጅግ በመደሰቱና በመደነቁ በጋዜጣው ካሰፈረው ጽሁፍ ባሻገር አስታጥቃቸው ወደ ሃገረ አሜሪካ በማቅናት የ’ ዪጂን እኒል ቴአትር ማዕከል’ አውደ ጥናት ላይ እንዲሳተፍ ከአሜሪካን ኤምባሲ ጋር ሁኔታውን አመቻችቶለት ለአንድ ወር ቆይታ አድርጎ ተመልሷል። ይህም አስታጥቃቸው አቅሙን እንዲረዳ በእጅጉ ጠቅሞታል፡፡
በአንድ ወቅት ደግሞ የ’ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ’ ፐብሊኬሽን ላይ ሰለ ኢትዮጵያ ወጣት የቴአትር ደራስያን በወጣው ሕትመት ነባሮቹን ፀጋዬ ገ/መድህን፣ መንግስቱ ለማ ወዘተ እያለ ከዘረዘረ በኋላ ስለ ዘመኑ ወጣት ጸሐፊ ደግሞ “There’s an upcoming generation yet, rearing its head outstanding of this young generation are ‘Astatkachew Yihun and Fiseha Belay Yimam.”እያለ ይቀጥላል…..በጽሁፉ አስታጥቃቸው ይሁን በሥራቸው ከተመሰገኑ ጸሃፌ ተውኔቶች ውስጥ ተካቷል፡፡

እንዲህ በሃገር ውስጥም በውጭ ጸሃፍትም ስሙ የተነሳው አስታጥቃቸው ይሁን ቀዳሚው ሥራው የሆነው “የህሊና ፀፀትን” ( “ሣልሳዊው ባልንጀራ”፣ አንቺን አሉ ፣ዘር አዳኝ እና ሌሎች 60 ተውኔቶችን ደርሷል፡፡

አስታጥቃቸው ይሁን፣ በዋናነት ከቴአትር ድርሰት አጻጻፍ በተጨማሪም በትወናና በመድረክ ዝግጅት ጥበብ ከዚህም አልፎ በሥራ ኃላፊነት ለ40 ዓመታት አገልግሏል፡፡

      ትውልድ

አስታጥቃቸው የጎጃም ፍሬ ነው፡፡ ም/ጎጃም ደጀን ወረዳ ድባብዜብ ማርያም ደብር ነው ውልደቱ። ጥቅምት 16 2018 ዓ.ም 68ተኛ የልደት በዓሉን አክብሯል፡፡ ይህም ማለት ትውልዱ በጥቅምት 1950 ዓ.ም ነው ማለት ነው።

የአርበኛው ይሁን ፈንታ እና የወ/ሮ የንጉሥ ነሽ የሻነው ልጅ አስታጥቃቸው ይሁን፣ ውልደቱ በገጠሩ ይሁን እንጂ እድገቱ ግን (በቤተሰብ የቦታ ለውጥ ምክንያት) በድሮ ስያሜው ከፋ ጠቅላይ ግዛት በጅማ አካባቢ ነው።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በደጀን ወረዳ ‘ ደጀን 1ኛና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ተከታትሏል።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በጅማ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀቀ፡፡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በጥሩ ውጤት በማለፉም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1971 ዓ.ም ገባ ። የትምህርት አቀባበል ላይ ጥሩ እንደነበርም ይነገራል ።

       አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

በ1971 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው እነ አቦነህ አሻግሬ፣ ተፈሪ ኣለሙ( ከተፈሪ ጋር እንዲያውም አንድ ዶርም ነበሩ)፣ በላይነህ አቡኔና( አንድ ክፍል ነበር የሚማሩት) አሰፋ ወ/ሰንበት ሌሎችም አብረውት ነበሩ፡፡ አንድ ዓመት ፍሬሽማን ከጨረሰ በኋላ የቲያትር ጥበብ ማጥናት ፈልጎ ወደ ትምህር ክፍሉ በምርጫው ገባ፡፡ አስታጥቃቸውና ጓደኞቹ በቴአትር ጥበባት ዘርፍ 2ኛው ባች ናቸው፡፡

በመጀመሪያው ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታው በባህል ማዕከል ከፍተኛ ተሳትፎ ነበረው፡፡ እንቅስቃሴውን የተመለከቱ ሰዎች ታዲያ ወደ ቲያትር እንዲገባ ሃሳብ ይሰጡት ነበር፡፡ በጊዜው የቲያትር ትምህር ክፍል ኃላፊ የነበረው ሚስተር ጆርጅም የቲያትር ጥበብን እንዲያጠና በጎ ተጽዕኖ እንዳደረገበት አስታጥቃቸው ይናገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በልጅነት የትምህርት ህይወቱ በቦይ ስካውት፣ በድራማና ሙዚቃ ክበብ እንዲሁም በክርክር ክበብ የነበረው ተሳትፎ ለትምህርት ዝንባሌው አስተዋጽኦ እንዳለውም አስታጥቃቸው ይናገራል፡፡

በኋላም በቴአትር ጥበባት ዘርፍ ለ4 ዓመታት ትምህርቱና ተከታትሎ በ1974 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ በቴአትር ጥበባት ተመረቀ፡፡ “ቀባሪ ያጣ በድን” በኋላ “የህሊና ጸጸት” ተብሎ የተሰየመው ተውኔት የመመረቂያ ሥራው ነበር፡፡

የሥራ ህይወት

ከምረቃ በኋላ ሀገር ፍቅር ቲያትር ባለሙያ ሆኖ ተቀጠረ።1975። አርቲስቱም መድረኩም በፍቅር ተቀበሉት፡፡ በአገር ፍቅር የመጀመሪያ ሥራው የተመረቀበት “ቀባሪ ያጣ በድን” የተሰኘው ተውኔት ነው፡፡ በወቅቱ ርዕሱ በሳንሱር ምክንያት አያልፍም ተብሎ “የህሊና ፀፀት” በሚል ተተክቶ ለመድረክ በቃ፡፡ ከዚያ በኋላም ብዙ ተውኔቶችን ደርሷል፡፡ በተቋሙ በትወና፣ በቲያትር ድርሰት ጽሁፍና በኋላም በቲያትር ክፍል ኃላፊነትም አገልግሏል፡፡ ከ1990 ዓ.ም እስከ 1995 ዓ.ም የሃገር ፍቅር ቲያትር ቤት ሥራአስኪያጅ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ የኢትዮጲያ ደራሲያን ማህበር ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በመሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በ1997 ዓ.ም ደግሞ ብሔራዊ ቴአትር ገባ።ብሔራዊ ቲያትር በነበረበት ወቅት በ2ኛ ደረጃ ባጠናው መሠረት እንደ ኢትኖግራፈር የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች ባህል ወግና ልማድ ባጠቃላይም ትውን (Performing Arts) ጥበባቸውን እቦታው ድረስ ሄዶ በማጥናት ወደ ብሔራዊ ቲያትር መድረክ በማምጣት ለህዝብ የማስተዋወቅ ሥራን ሠርቷል፡፡ ካጠናቸው ብሔረሰቦች መካከል መኤነት፣ በርታ፣ አገው፣ ባስኬቶና ኢሮብም ይገኙበታል፡፡

ሃገር ፍቅር ለ22 ዓመታት አገልግሎ በ2010 ዓ.ም ከዚያው ከብሔራዊ ቲያትር ጡረታ ወጣ፡፡

አስታጥቃቸው በሙያ ቆይታው በዋናነት በቴአትር ድርሰት አጻጻፍ እንዲሁም በትወናና በመድረክ ዝግጅት ብዙ ሠርቷል። በዝግጅት ሙያው እምብዛም ባይገፋበትም በቴአትር ድርሰት አጻጻፍ ግን እጅጉን ሄዷል፡፡ ድርሰቶቹ ለህትመት ባይበቁም በመድረክ፣ በቴሌቪዥን መስኮትና በሬዲዮ ለሕዝብ ዓይንና ጆሮ ደርሰዋል፡፡ የተለያዩ የቲያትር ሙያተኞች እንደሚሉትና ሥራዎቹም እንደሚመሰክሩት አስታጥቃቸው አንቱ ከተባሉ የአፍሪካ የቴአር ደራሰያን ተርታ የሚሰለፍ ነው፡፡ ለዚህም ከላይ ያነሳነው የጋሽ ተስፋዬ ምስክርነትና የ’ካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ’ ፐብሊኬሽን ላይ የወጣው ሕትመት የሚጠቀሱ ምስክርነቶች ናቸው፡፡

አስታጥቃቸው የሙሉ ጊዜ ተውኔቶችን ለተለያዩ ፕሮፌሽናል መድረኮች አብቅቷል። ከእነዚህ መካከል ሁለቱን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው የጻፋቸው፡፡

በኬንያ በተዘጋጀው የአፍሪካ የቴአትር ፌስቲቫል በብሔራዊ መድረካቸው ላይ “Love And Peace” የተሰኘው የአስታጥቃቸው ሥራ ቀርቧል። ከተመልካቹም ጥሩና የሚያስገርም ምላሽ ነበረው።

በወቅቱ በኬንያ ብሔራዊ ቴአትር ከነበሩት የጆሞ ኬንያታ ዩኒቨርስቲ ምሁራንና ታዳሚዎች ጋር ከትርኢት በኋላ ባደረገው ውይይት ‘ምን ያህል ተውኔቶችን እስካሁን ጽፈሃል?’ የሚል ጥያቄ ቀርቦለት ‘ ሙሉ ጊዜዎቹ፣ ባለአንድ ገቢሮቹና አጫጭር ተውኔቶቹ ባጠቃላይ ተደምረው ወደ 60 አካባቢ ይሆናሉ ብሎ የሰጠውን ምላሽ ማመን አቅቷቸው ” ለመሆኑ ሀውልት ቆሞልሃል?” ሲሉ ነበር የጠየቁት ። ለዚህም በጊዜው አብረውት የነበሩት የኢትዮጵያውያን ልዑካን አባላት ምሥክሮች ናቸው።

ከተውኔቱ ባለፈ አስታጥቃቸው በአጭር ልቦለድ ጽሑፍም ተሳትፏል፡፡ በሙያው ኬንያ አሜሪካና ቻይናን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በማቅናት ልምድ ቀስሟል ልምዱንም አካፍሏል፡፡ ። ከተለያዩ ሙያተኞችም ጋር መገናኘት ችሏል ። በአሜሪካን ሃገር በተካሄደው በዩጂን እኒል የቴአትር ተቋም መቶኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ በተቋሙ የተገኘውም አስታጥቃቸው ይሁን ፈንታ ነው፡፡

አስታጥቃቸው፣ እንዲህ በዘርፉ አገልግሎ ከ40 ኣመታት በኋላ ጡረታ ወጥቷል ፡፡ ዛሬ ለመጻፍ ቢያስብም የትኛው ተመልካች ይሰማኛል ብሎ ስለሚጨነቅ ሥራውን ገታ አድርጓል፡፡
በሌላ በኩል ግን ከጊዜ በኋላ ከገጠመው የስኳር ህመም ጋር እየታገለ ነው፡፡

የሚገርመው ከ60 ስራዎቹ ውስጥ አሁን በእጁ ያሉት 30 የስክሪፕት ፅሑፎች ናቸው፡፡ ለዚህም ባለውለታው ጽሁፎቹን ካሉበት ከየሰዎች እጅ ሰባስቦ ያመጣለት ያሬድ ገብረስላሴ ነውና አስታጥቃቸው ያሬድን እጅግ ያመሰግነዋል፡፡

ተውኔቶቹና ሌሎች የድርሰት ሥራዎቹ ያሉት ለህትመት በቅተው ማየት የዘወትር ህልሙ ነው፡፡

     የቤተሰብ ህይወት

አስታጥቃቸው ይሁን ትምህርቱን አጠናቆ ስራ በጀመረ በሁለተኛው ዓመት ትዳር መስርቶ ከወ/ሮ ሙሉ መኮንን 3 ልጆችን አፍርቷል፡፡ (ምግባር አስታጥቃቸው፣ መልካም አስታጥቃቸውና ዮርዳኖስ አስታጥቃቸው)፡፡

ምስክርነት

ኪሮስ ኃይለስላሴ

አስታጥቃቸው ጎጃም ተወልዶ ጅማ በማደጉ የሁለት አካባቢ ባህል ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ አማርኛ ቋንቋንም ጥሩ አድርጎ ያውቀዋል፡፡ ጥሩ የቋንቋ ችሎታ አለው፡፡ ተዋናይ ነው ፣ ገጣሚ ነው አጫጭር ልቦለዶችን ይጽፋል በዚህ አደንቀዋለሁ፡፡ አስታጥቄ ቶሎ ሰውን አምኖ መቅረብ ይቸግረዋል፤ ለሳቅም ይዘገያል፡፡ ከቀረበ ግን መልካም ሰው ነው፡፡ በተረፈ ግን ትወና ይችላል በተለይ ትራጀዲ….ኮሜዲም ይችላል፡፡ በጽሁፍም ሁለቱንም ይጽፋል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካፈራቸው የቲያትር ምሁራን እንደ አንዱ የሚቆጠርም ነው። መድረክ ላይ ያልወጡም በርካታ ድርሰቶች አሉትና ወደ ፊት ቢያመጣቸው እላለሁ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *