ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን፣ መዝገበ-አእምሮ (የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች፣ በመጽሐፍ፣ በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት 4 ዓመታት ከ5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መጽሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።
ቅፅ 3 መዝገበ አእምሮ ከ20 በላይ ዘርፎች ይኖሩታል። በኪነጥበብና ትወና ዘርፍ ባለፉት 34 ዓመታት አሻራ ካኖሩት እና ታሪካቸውን ከምንሰንድላቸው መካካል አርቲስት ታምሩ ብርሀኑ ይገኝበታል። አርቲስት ታምሩ ለሙያው ጥልቅ ፍቅር ያሳደረ ባለሙያ ሲሆን በቴሌቪዥንና በፊቸር ፊልም ድርሰት የራሱን አሻራ አኑሯል። በትወና እና በተለይ በመድረክ ላይ ባሳየው ብቃት በባለሙያዎች ጥሩ ምስክርነት አግኝቷል። የመዝገበ አእምሮ የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ የቦርድ አባላት የአርቲስት ታምሩ ብርሀኑ ታሪክ ቢሰነድ ለትውልድ እንደሚጠቅም ተስፋ በማድረግ እኛም ሰንደዋል። ባለታሪኩን ታምሩን በማስፈቀድና የሰጠውን የፅሑፍ ማረጋገጫ በማጤን ታሪኩን በተወዳጅ ዲጂታል ሚድያዎች እንደሚሆን አድርገን አቅርበነዋል። የሙያ ታሪኩንም ዕዝራ እጅጉ እና አይናለም ሀድራ አጠናክረውታል።
“በህይወቴ ረፈደ የሚባል ነገር አላውቅም” ይላል አርቲስት ታምሩ ብርሀኑ
ሽጉጥ ባትታጠቅ ዝናር ባይኖራት
ጀማነሽ ጀማዬ የሴት ወንድ ናት
የተባለላቸው የብርቱዋ የጀግናዋ የወ/ሮ ጀማነሽ ገ/ሚካኤል 7ኛ ልጅ ነው አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ፡፡
በልጅነቱ በሞት የተለየው አባቱ ብርሃኑ ኃይሌ የህግ ባለሙያ እንደነበር ይናገራል፡፡
ጀግንነትን ብርታትን፤ ለትንሹም ለትልቁም የህይወት ፈተና እጅ አለመስጠትን ከእናቱ ከወ/ሮ ጀማነሽ ሳይወስድ አልቀረም፡፡
“ችግር በገጠመኝና ባዘንኩ ማግስት እንደውም ሀይሌ ይጨምራል” ይላል፡፡ ተሸንፎ መውደቅ፤ እጅ መስጠት ለታምሩ አይታሰብም፡፡ የህይወት ውጣ ውረድ ኩርኩም ቢያስከትልም አጎንብሶ መቅረት እርሱ ዘንድ ነውር ነው፡፡ ያስጎነበሰውን ችግር ለመጣል ይጥራል ጥሎም ይነሳል፡፡
አርቲስት ታምሩ እንዲህም ይላል፡- “ተገፍታችሁ ከሆነ ቆማችሁ የተገፋችሁበትን ነገር እያሰባችሁ አትማረሩ፡፡ ከፊት ለፊታችሁ ሌላ መንገድ አለና ሄዳችሁ እሱን ተጋፈጡ”፡፡
ታምሩ እንዲህ መናገር ብቻም ሳይሆን በህይወቱ ገጠመኞቹ በተግባር እንደተጠቀመበት ያነሳል፡፡
ምንም እንኳን የ14 ዓመት ልጅ እያለ በሞት ቢለዩትም ከጠበቃው አባቱ አቶ ብርሃኑ ሀይሌም ለመብት መቆምን መብትን ማስከበርን በቅጡ ተምሯልና በመብቱ ጉዳይ አይደራደርም፡፡ ከዚህ እልፍ ሲልም ስለሌሎች መኖርን በህይወቱ ስፍራ ይሰጣል፡፡ እንዲያውም ከራስ ይልቅ ለሌሎች መኖር የህይወት መርሁ እንደሆነ ይነገራል፡፡ “በአንተ ላይ እንዲደረግብህ የማትፈልገውን በሌሎች ላይ አታድርግ” የሚለውን አባባል የህይወቱ ቀዳሚ መርህ አድርጎታል፡፡
በጥበቡ አለም ከ34 ዓመታት በላይ አሳልፏል፡፡ ሁለገቡ አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ በቴሌቪዥን ድራማዎች፤ በቴአትሮች፣ በፊልምና በማስታወቂያ ሥራዎች ስሙ ጎልቶ ይነሳል፡፡ በትወና፣ በድርሰትና በዳይሬክቲንግ ከ58 በላይ ሥራዎችን አበርክቷል፡፡
የቴአትር ህይወት
አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ፣ በ1960 ዓ.ም አዲስ አበባ በተለምዶው ጣሊያን ሰፈር የሚባለው አካባቢ ነው የተወለደው፡፡ ከዚያም አስኮ አካባቢ ከቤተሰቡ ጋር ያደገ ሲሆን ገና በልጅነቱ አባቱ አቶ ብርሃኑ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እንዲሔድ ያደርጉት ነበርና መንፈሳዊ እድገቱም በዚያው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሆነ፡፡ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የነበሩ የእምነት አባቶች መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው የሥነፅሁፍ ሥራዎችን ታዳጊዎቹ እንዲሠሩ ያደርጉ ነበር እና በተለይም አባ አንጦኒዮስ አልቤርቶ ታምሩና ጓደኞቹን አጫጭር መንፈሳዊ ቴአትር ያሠሯቸው ነበር፡፡
ከዚያ በተጨማሪ የአርቲስት ታምሩ የእህቱ ባለቤት የነበረው አርቲስት ከበደ ደገፉ አዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ውስጥ በተዋናይነትና አዘጋጅነት ይሠሩ ነበርና በእርሳቸው ምክንያት በተደጋጋሚ ወደ ቴአትር ቤቱ እያቀና ቴአትሮችን የማየት እድል ነበረው፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ የቴአትር መድረክና ቴአትር እንደልብ የማየቱ እድል ተደማምረው ተደብቆ ብቅ ጥልቅ ይል የነበረው ተሰጥኦው ይበልጥ ለማውጣት የታምሩ ልብ ወደ ቴአትር መንደር ሸፈተ፡፡
በዚህ መሃል የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ እናት ወ/ሮ ጀማነሽ ልጃቸው ለቴአትር ያለው ፍቅር ስላላማራቸው አውቶሜካኒክስ ካልተማርክ ብለው ጨከኑ፡፡ ልቡ በቴአትር ቢረታም በብርታት በጀግንነት ያሳደጉትና ያስተማሩት እናቱን ቃል ማክበር ስለነበረበት በሐሳባቸው ሳይስማማ ተስማምቶ ጄኔራል ዊንጌት የሙያ ት/ቤት በመግባት 4 ዓመታትን ተምሮ በአውቶሜካኒክስም በዲፕሎማ ተመረቀ፡፡
ቀድሞም የተማረው የእናቱን ፍላጎት ለማሟላት ነበርና ዲፕሎማውን ለእናቱ አስረክቦ እርሱ የወደደው ቴአትር ቀጠለ፡፡
ከአውቶሜካኒክስ ትምህርት ላይ እያለ ሹልክ ብሎ ከታዋቂው ደራሲና አዘጋጅ ጋሼ መላኩ አሻግሬ ጋር ቴአትር ይሠራ ነበርና ከመድረኩ እምብዛም ርቆ አልራቀም፡፡ እናት ቢቆጡም አልሆነም አርቲስት ታምሩ ባገኘው ዕድል ሁሉ የቴአትር ሥራውን ቀጠለ፡፡ ከጋሼ መላኩ አሻግሬ እና ከሌሎች የሙያ አጋሮቹ ጋር በየክፍለሃገሩ ተዘዋውረው የአርሶ አደሮች ማሳ ሳይቀር የትራክተር ተሳቢ ላይ የመድረክ ገፅ በመገንባት ቴአትሮችን አሳይተዋል፡፡
በመድረክ ቴአትር ተዋናይነት
ይሄንን ተሳትፎውንና አቅሙን ያዩ ዳይሬክተሮች ዓይናቸውን ጣሉበት። በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ሮሚዮና ጁሊየትን እንዲሠራ አጩት በ29 ዓመቱ የ60 ዓመት ገፀ-ባህሪን ተጫወተ። ተሳካለትም፡፡
በመቀጠልም “አንድ ጡት” በተሰኘው ቴአትር ከነዓለምፀሐይ ወዳጆ፤ ተክሌ ደስታ፣ አስናቀች ወርቁ፣ ዘነበች ታደሰ (ጭራ ቀረሽ)፣ ጌትነት እንየው፣ ጥላሁን ጉግሳ እና ሌሎች አንጋፋ ሙያተኞች ጋር የመሥራት እድሉን አገኘ፡፡ የኃላ ኃላ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ እየተጋበዘ ቴአትሮችን ይሠራ ጀመር፡፡ ከዚያም በሳምንት እስከ አራት የተለያዩ ቴአትሮች ይሰራ እንደነበር ይታወሳል፡፡ እየተጋበዘ ሲተውን በነበረበት ወቅትም በመድረክ 75 ብር ይከፈለው ነበር፡፡ በሂደት ግን የሳምንት ክፍያው ቀርቶ ቋሚ ቅጥር ይሁን በመባሉ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ በ230 ብር የወር ደሞዝ ተቀጠረ፡፡
አርቲስት ታምሩ ብርሀኑ አንድ ጡት፣ ሮሚዮና ጁሊየት፣ ዩሊዮስ ቄሳር፣ የክፉ ቀን ደራሽ፣ ነጭ ጥቀርሻ፣ እስረኛው ንጉስ፣ ስርየት፣ ፅናት፣ የቼዝ አለም፣ አንድ ክረምት፣ ቁርጥ ቀን፣ ማክቤዝ፣ ባለትዳሮቹ፣ ሠማያዊ ዓይን፣ የሳቅ ጀምበር እና ሌሎችም ቴአትሮች ላይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ አብዛኛውን ዋና ገፀ-ባህሪያትን በመወከል ተጫውቷል፡፡
በፊልም ዳይሬክተርነት
*አስከሬኑ ፊልም
*ባለስልጣኑ ፊልም
*እናፋታለን ፊልም
- መለኞቹ የተሰኙ ፊልሞቹን በዋና ዳይሬክተርነት በማዘጋጀት ለአፍቃሪዎቹ አቅርቧል፡፡
ዶኩመንተሪ ፊልሞች
በታምሩ ብርሃኑ ባለቤትነት በሚመራው “ታምሩ ፕሮዳክሽን” አማካኝነት ከ25 በላይ ዶኩመንተሪ ፊልሞችን ስክሪፕት በማዘጋጀት፣ በዳይሬክተርነት፣ በተራኪነት/በአንባቢነትና አጠቃላይ ፕሮዳክሽኑን አጠናቆ ለደንበኞች አስረክቧል፡፡
በፊልም ተዋናይነት
አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ ኃይሌ ከመድረክ ሥራዎቹ በተጨማሪ በራሱ የድርሰት ስራዎች እና በተጋባዥ ተዋናይነት በተለያዩ ፊልሞች በመሪ ተዋናይነት ተውኗል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሠናይት፣ የዘማሪዋ ወፍ ህልም፣ ንስር፣ ሰማያዊ ፈረስ፣ ቀይ ስህተት፣ እጣ ፈንታ፣ ቃልኪዳን፣ መዘዝ፣ ሀማዊው፣ ማንነት፣ አስክሬኑ፣ ባለስልጣኑ፣ እናፋታለን፣ እምነት፣ ባለክራሩ፣ ብሌን እና እሁድ እለት የተሰኙት ፊልሞች ላይ አብዛኛውን በመሪ ተዋናይነት በመተወን የትዋና ተሰጥኦውን አስመስክሯል፡፡
በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ተዋናይነት
ከ30 ዓመት በፊት ዶክተሩ እና ግጥምጥም በቴሌቪዢን ተከታታይ ድራማ ትወና የተቀላቀለው አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ ከብዙ ዓመታት ቆይታ በኃላ “ግማሽ ጨረቃ”፣ “የሌሊት ጧፍ” እና “ግዛት” የተሰኙት ተከታታይ ድራማዎች ላይ የትወና ብቃቱን አሳይቷል፡፡
የሬዲዮ ድራማ
የሬዲዮ ድራማን በተመለከተ ከ12 በላይ አጫጭር እና ተከታታይ የሬድዮ ድራማዎች ላይ እንደሠራ ይናገራል፡፡
በደራሲነት
አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ የራሱ የሆኑ የተከታታይ ድራማ እና የፊልም ድርሰቶቹን ማለትም
አስከሬኑ
ሠው ለሰው (ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ የመጀመሪያ ደራሲ)
ባለስልጣኑ
እናፋታለን
መለኞቹ (የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ DOCUDRAMA) በደራሲነት ለህዝብ አቅርቦ ተወዳጅነትን አፍርተውለታል፡፡
እንዲሁም “ሆቴሉ” የተሰኘውን መስማትና መናገር በተሳናቸው ወጣቶች የቀረበ የመድረክ ተውኔት /MIME DRAMA/ በደራሲነት እና በአዘጋጅነት አቅርቧል፡፡
በፕሮግራም መሪነት
በተለያዩ መንግስታዊና የግል ተቋማት ልዩ ልዩ ከፍተኛ ዝግጅቶች ላይ ከብዙ በጥቂቱ ከ40 በላይ ፕሮግራሞችን በመድረክ መሪነት ሠርቷል፡፡
በማስታወቂያ ሥራዎች
የራሱ በሆነው የማስታወቂያ ድርጅቱ “ታምሩ ፕሮዳክሽን” አማካኝነት ላለፉት 18 ዓመታት ከ600 በላይ የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች፣ ከ800 በላይ የሬዲዮ ማስታወቂያዎች ስክሪፕት በማዘጋጀት፣ በተራኪነት /በአንባኒነት/፣ በዳይሬክተርነት እንዲሁም እንዳስፈላጊነቱ በመተወን ውጤታማ የሆኑ ማስታወቂያዎችን አጠቃላይ ዝግጅቱን በመስራት በተለያዩ ሚዲያዎች አስተላልፏል፡፡
ልዩ የበዓል የመዝናኛ ዝግጅቶች (በቴሌቪዥን የሚተላለፉ)
የመላው የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮችን በዓላትን ምክንያት በማድረግ በየበዓሉ ዕለት በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ዝግጅቶችን ከኢቲቪ፣ ፋና ቲቪ፣ ዋልታ ቲቪ እና ሌሎችም ጣቢያዎች ጋር በመተባበር ከ16 በላይ ልዩ የበዓል የቲቪ መዝናኛ የመዝናኛ ዝግጅቶችን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር በማዘጋጀት ለህዝብ አቅርቧል፡፡
ትምህርት
በአውቶሚካኒክስ ዲፕሎማ /ጄኔራል ዊንጌት/
በስነፅሁፍ ዲፕሎማ /ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ/
በቴአትር ጥበባት ዲግሪ /ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ/
ቢዝነስ ኮሚኒኬሽን ስልጠና ሰርተፍኬት /ከንግድ ሥራ ኮሌጅ/
የበጎ አድራጎት ሥራ
ሜሪ ጆይ የልማት ተራድኦ ድርጅት – ረዘም ላሉ ዓመታት በአምባሳደርነት እና አባልነት
ቸሻየር ኢትዮጵያ – በአምባሳደርነት
ካለን ብናካፍል የአዕምሮ ህሙማን፣ የአረጋዊያንና የህፃናት መርጃ ማዕከል – በአምባሳደርነት /ጎንደር/
በሜቄዶንያም አገልግሏል በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
በቦርድ አባልነት
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የስፖርት ክለብ በሆነው “ኦሜድላ” የስፖርት ክለብ በቦርድ አባልነት በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
ሽልማቶች
በተለያዩ ሀገራዊ ሥራዎቹ ከኢ.ፌ.ድ.ሪ ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ አህመድ እጅ 3 የዕውቅና እና የምስጋና ሰርተፊኬቶች፣ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እጅ ሽልማት እና ሰርተፍኬት፣ ከክብርት ከንቲባ አደነች አበቤ የታማኝ ግብር ከፋይ ሽልማትና የዕውቅና ሰርተፊኬት እንዲሁም በሙያውና በበጎ አድራጎት ሥራዎቹ ከ55 በላይ የእውቅና የምስጋና ሰርተፊኬቶች ከተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት በክብር ተበርክተውለታል፡፡
ቤተሰባዊ ህይወቱ
አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ በቤተሰባዊ ህይወቱ ሙሴ ታምሩ፣ አሜን ታምሩ፣ ማግድለን ታምሩ እና ሆሴዕ ታምሩ የተሰኙ አራት ልጆችን በእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳገኘ ይመሰክራል፡፡
ሁሌም ከታምሩ ብርሀኑ አንደበት በማይጠፋው ቃል
“ስለ ሁሉም ነገር እግዚአብሔር ይመስገን”!!!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!! የሚለውም ንግግር ከአንደበቱ አይጠፋም።