ሻምበል ገድሉ ኃይሉ (1924-2002)

ፓሊስና እርምጃው ጋዜጣ 65 ዓመቱ ተከበረ

*ሻምበል ገድሉ ኃይሉ ከፖሊስና እርምጃው መሥራቾች አንዱ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን፣ መዝገበ-አእምሮ (የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል።

ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች፣ በመጽሐፍ፣ በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት 4 ዓመታት ከ5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መጽሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።

ቅፅ 3 መዝገበ አእምሮ መፅሐፍ ፣ከ20 በላይ ዘርፎች ይኖሩታል። ከእነዚህም ዘርፎች አንዱ አስተዳደር እና ሚሊተሪ የሚለው ይገኝበታል። በዚህ ዘርፍ ታሪካቸው መፅሐፉ ላይ ከሚካተትላቸው ለአገሩ የሠሩ ባለሙያዎች ውስጥ ሻምበል ገድሉ አንዱ ናቸው። ሻምበል ገድሉ በሚሊተሪ እና በልዩ ልዩ መሥሪያ ቤት ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ያገለገሉ ነበሩ። ሻምበል ገድሉ ኃይሉ “ፓሊስና እርምጃ ” ጋዜጣ በጥቅምት 23 1953 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕትመት ሲበቃ ከጋዜጣው የእድገት ጠባቂዎች መካከል አንዱ ነበሩ። የሻምበል ገድሉን ታሪክ ቤተሰባቸውን በማስፈቀድና ማረጋገጫ በማግኘት ለመሰነድ በቅተናል። ይህን ታሪክ ስንሰንድ ትብብር ላደረገልን ለልጃቸው ለእስክንድር ገድሉ ማመስገን እንወዳለን።በተጨማሪም ቤተልሔም ገድሉ እና ኢየሩሳሌም ገድሉንም አመስግነናል። ዕዝራ እጅጉ ታሪኩን እንደሚከተለው ሰንዶታል።

        ትውልድ እና ልጅነት

ሻምበል ገድሉ ኃይሉ ከአባታቸው ከክቡር ፊታውራሪ ኃይሉ ይግዛው እና ከእናታቸው ክብርት ወይዘሮ አበበች ወሠኔ ሰኔ 19 ቀን 1924 ዓ.ም በሸዋ ክፍለ ሐገር በወጨጫ አውራጃ ተወለዱ።

ለክብርት ወ/ሮ አበበች ወሠኔ ብቸኛ ልጅ የሆኑት ሕፃን ገድሉ ኃይሉ ገና ከእናታቸው አብራክ እንደተከፈሉ በአራስነታቸው በአያታቸው በደጃዝማች ወሠኔ ትርፌና በክብርት ወ/ሮ ደስታ ጫጫ ቤት ተወስደው በልዩ ትኩረትና እንክብካቤ የጨቅላነት እድሜያቸውን በልዩ ቅምጥልና እንክብካቤ እንዲያሳልፉ ሆኖ እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰም በዘመኑ ሥርዓቱ በሚፈቅደው መሠረት መደበኛ መምህር ተመድቦላቸው የአማርኛ ትምህርታቸውን በማቀላጠፍ ዳዊትም ያጠናቀቁት ገና እጅግ በለጋነታቸው እድሜ ነበር።

              ትምህርት እና ውትድርና

እድሜያቸው ለዘመናዊ ትምህርት እንደደረሰም፣ በቀድሞው ተፈሪ መኮንን ት/ቤት በአዳሪነት ተመዝግበው የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመፈፀም ከአያት ቅድመ- አያት ሲወርድ ሲዋረድ እንደቆየው ሐገርን በውትድርና መስክ የማገልገል ፍላጎት ስላየለባቸው በአባዲና ፖሊስ ኮሌጅ የ2ኛ ኮርስ የእጩ መኮንንነት ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ 1943 ዓ.ም በምክትል የመቶ አለቃነት ማዕረግ ተመርቀዋል።

በፖሊስ ሠራዊት የአገልግሎት የሥራ ዘመናቸውም በሬዲዮና ጋዜጣ ክፍል (ማስታወቂያ ክፍል) ተቋሙን ካቋቋሙትና ካደራጁት እንዲሁም ከመሩት ጥቂት ሰዎች መካከል ዋነኛው ሰው በመሆን በተጨማሪም በትርጉምና በጣት አሻራ፣ ምርምራ ክፍል ኃላፊነት እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች በጣቢያ አዛዥነት በስፖርት እንዲሁም በሙዚቃ መምሪያ ኃላፊነት አገልግለዋል። ሠራዊቱንም በመወከል በእግር ኳሱ መስክ በብሔራዊ ደረጃ ለኦሜድላ ቡድን የተጫወቱና በአምበልነትም ቡድኑን በመምራት ውጤትም ማስገኘት የቻሉ የተዋጣላቸውና የተወደዱ ወጣት ስፖርተኛና ቆፍጣና ወጣት መኮንን ነበሩ።

     ፖሊስና እርምጃው

በአገራችን የህትመት ታሪክ ውስጥ ስመ-ጥር የነበረውን ፓሊስና ርምጃው ጋዜጣ ሲመሠረት ትልቅ አሻራ ካኖሩት መካከል ሻምበል ገድሉ አንዱ ናቸው። ጋዜጣዋ የዕድገት ጠባቂ ብላ ካስቀመጠቻቸው ቁልፍ ሰዎች አንዱ የ29 ዓመቱ ሻምበል ገድሉ ነበሩ። ጄነራል ጽጌ ዲቡ የሥራ መሪ የነበሩ ሲሆን ሻምበል ገድሉም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በብቃት የተወጡ ነበሩ።

በግል ምክንያት ወጣቱና ቆፍጣናው መኮንን ከፖሊስ ሠራዊት በስንብት በሻምበልነት ማዕረግ እስከተለዩበት ጊዜ ድረስ ሠራዊቱን ደከመኝ ወይም ይህ ቀረብኝ ሳይሉ በፍፁም ታታሪነት ቅንነትና ልባዊ ፍቅር ያልተገደበና ሁለ ገብ የሆነ ተሰጥኦዋቸውን ለሠራዊቱ አገልግሎት በከፍተኛ ንቃትና ትጋት ያበረከቱ ንቁ መኮንን ነበሩ።

            ከፖሊስ ሠራዊት በኃላ

ሻምበል ገድሉ ኃይሉ፣ ከፖሊስ ሠራዊት ስንብት በኋላ በቱሪስት ድርጅት በወህኒ ቤቶችና አስተዳደር፣ በቱሪስት ኮሚሽን በመሬት ይዞታና አስተዳደር ሚኒስቴር፣ በአክሱም የፊልም ድርጅት፣ በግብርና ሚኒስቴር፣ በቡናና ሻይ ልማት ሚኒስቴር፣ እንዲሁም በእጣንና ሙጫ በአዲስ አበባ በጅማ በወሎና በጎንደር ክፍለ አገራት በመዘዋወር ያበረከቱት አገልግሎት በአብይነት የሚጠቀስ ሲሆን ያከናወኗቸው የሥራ ድርሻዎችም በክፍል መምሪያ ኃላፊነት፣ በአስተዳደሪነት፣ በሥራ አስኪያጅነትና በዋና ዳይሬክተርነት እስከ ሚኒስትር ዴኤታ ድረስ የረጅም ዘመን ህዝባዊና መንግሥታዊ አገልግሎታቸውና ሀገራዊ ግዴታቸውን የተወጡ ዜጋ ነበሩ።

   ቤተሰብ

ሻምበል ገድሉ፣ ለእናታቸው ብቸኛ ልጅ ቢሆኑም ልዑል እግዚአብሔር በዘር አብዝቶ የባረካቸው አስራ አንድ ለወለዱዋቸውና 2 ለሚያሳድጓቸው በድምሩ የ 13 ልጆች አባትና ለአስር የልጅ ልጆች አያት ለመሆን የበቁ እድለኛ ሰው ነበሩ።
ሻምበል ገድሉ ኃይሉ ቀና አሳቢ ቸርና ትሁት የተቸገረን መርዳት የማይሰለቻቸው ሐገራቸውንና ባህላቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ የሚያከብሩና እጅግ የሚያፈቅሩ ታላቅ ሠው ነበሩ።

          አገርን በንቃት ማገልገል እና መታሠር

ለአገራቸውና ለሕዝባቸው እድገትና መሻሻል ያላቸን ራዕይ ለማስተዋወቅና ለመተግበር ጊዜን ገንዘብን ጉልበትና ህልውናቸውን ሳይቀር ምክንያትና መሸሸጊያ ሳያደርጉ ለረጅም ጊዜ በተለያዩ አቅጣጫዎች በአገርም ውስጥ ሆነ በውጭ የተለያዩ ጥረቶችንና ክንዋኔዎችን ፈጽመዋል።

ከ1953 ዓ.ም ከታህሳሱ ግርገር አንስቶ የተደጋገመ የእስር እንግልት ተቀብለዋል። በታህሳስ 1953 ዓ.ም ልዑል አልጋወራሽ አስፋው ወሰን ኃይለ ሥላሴ አባታቸው ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከስልጣን ተነስተው በህግ የተደነገገ ንጉሣዊ ሥርዓት ይሆን ዘንድ በመስማማት በሬዲዮ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያስተላልፉ የተዘጋጀውን የልዑሉን የመግለጫ መልዕክት በአካል በመገኘት እንዲቀበሉ እንዲቀርፁና በኋላም እንዲተላለፍ ካደረጉት ከፖሊስ ሠራዊት የተወከሉት ሁለት መኮንንኖች መካከል አንዱ ሻምበል ገድሉ ኃይሉ ሲሆኑ ከክቡር ዘበኛ ደግሞ ሻምበል አስራት ደፈረስ ነበሩ።

አንባቢውም ጋዜጠኛ ዳምጤ አሰማኸኝ “አለቀ ደቀቀ” በሚል ርዕስ ማንበቡ በታሪክ ሲታወስ ይኖራል። በኋላም በዚሁ ሙያዊ ተሳትፏቸው ላጭር ጊዜ በእሥር ቆይተው በነፃ በመለቀቅ ወደ መደባዊ ተግባራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። በመቀጠልም ከጊዜ ወደ ግዜ ግንዛቤያቸውን በወቅቱ በነበሩት በዋና ዋና የአገሪቱ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ጋዜጦች የሰላ ትችትና ምልከታቸውን በድፍረት ለአንባቢያን ያቀርቡ ሰለነበረ ይኼም በየጊዜው ለእስር አጋልጧቸዋል።

በተለይ ደግሞ 1966 ዓ.ም የዘውዱን አገዛዝ ከሥልጣን በማስወገድ የባላባትና የመሣፍንት የመኳንንት ዘር የተባሉትን በማንነታቸው ጭምር በፍረደ ገምድልነት ከርቸሌ እንዲወርዱ ከተደረጉት ሰዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ 4 ዓመት ከስድስት ወር ያለፍርድ በግፍ 1967-1971 ዓ.ም ታስረው በመጨረሻም ተለቀዋል።

በመሬት ይዞታና አስተዳደር ሚኒስቴር በዋና ዳይሬክተርነት፣ እስከ ሚኒስቴር ዲኤታ ደረጃ ማዕረግ ከደረሱበት መስሪያ ቤትም እንዲባረሩ የተደረገበት አንዱና ዋነኛ ምክንያት በወቅቱ “አድሐሪ አቆርቃዥ “የሚል ታፔላ ከተለጠፈበት ወገን የተገኙና የተፈረጁም ሠው በመሆናቸው እንጂ ምንም የሠሩት ወንጀል ኖሮ አልነበረም።
ከ10 ዓመታት በላይ ከፍተኛ ትጋትና ቅንነት ካገለገሉበት የሥራ መስክ በ1966 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ነበር እንዲሰናበቱ የተደረገው።

ኮሎኔል ዳንኔል አስፋው ሻምበል ገድሉን በደህንነቶች አሳግቶ እቢሮው ለረጅም ሰዓታት ካቆያቸው በኋላ በከፍተኛ ዘለፋና ፉከራ በህይወታቸው ላይ እርምጃ እስከመውሰድ እንደዛተባቸውና እንደ ዘመዶቻቸው እንደ መኳንንቱና መሳፍንቱ ሁሉ እርሳቸውንም ወደ ከርቸሌ እንደሚያወርዳቸው ለዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በቃለ ምልልስ መልክ መናገራቸው ቢገለጽ አግባብ ያለው ይሆናል።
እገድላለሁ ባዩም ኮሎኔል ዳንኤል ብዙም ሳይቆይ ከዚህ ዓለም በመሰናበቱ ምክንያት ከተዛተባቸው የግድያ ዛቻ እግዚአብሔር ጠብቆ 4 ዓመት በላይ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ የተመሰቃቀለውን ህይወታቸውን መስመር ለማስያዝ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ተሳክቶ ከሰባት ዓመት በኃላ በግብርናና በቡናና ሻይ ልማት ሚንስትር፣ በእጣንና ሙጫ፣ ወደ ጅማ በበቃ ጎንደር ወሎና አዲስ አበባ በመዘዋወር በሥራ አስኪያጅነት ማዕረግ አገራቸውን እና ህዝባቸውን አገልግለዋል።

      ጉዞ ወደ ባህር ማዶ

ልጆቻቸው ወደ ሚኖሩበት ወደ ሰሜን አሜሪካ 1991 ዓ.ም በመሄድ የስደት ህይወታቸውን ተጎዳኝተዋል። በደረሱበት ቦታ ሁሉ ፀንቶ መቆም ሁኔታን መቀበልና መልሶ መቋቋም የማይከብዳቸው ብርቱና ጽኑ ሠው በመሆናቸው የአሜሪካንም አዲስ ህይወት ጋር ተቀላቅሎና ተሳልጦ ለመኖር ግዜ ያልወሰደባቸው ጀግና ሰው ነበሩ።

እንደ ታላላቆቹ አያትና ቅድም አያቶቻቸው ሁሉ ታላላቅ ሐገራዊና መንግሥታዊ የአስተዳደር ቦታዎችን በመሸፈን እና በጀግንነትም የተከፈሉትን ታላላቅ የመስዋዕትነቶችን ዋጋ እያዩና እየሰሙ እንዳደጉ ሰው እርሳቸውም የሐገርና የህዝብ ጉዳይ እጅግ የሚያሳስባቸውና የሚያስጨንቃቸውም ሰው ነበሩ።

በመሆኑም፣ በተለያዩ ጊዜ ከተገበሯቸው የተለያዩ ክንዋኔዎች አንዱና ዋነኛው ብዙ ጊዜያቸውን ሰጥተው የተንቀሳቀሱበት የሞአምበሳ ድርጅት ዋና ጸሐፊ በመሆን በሰሜን አሜሪካ ኸረንደን ቨርጂንያ ላይ የተመሠረተው ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ክፍላተ አህጉራት እንቅስቃሴ ያደርግ የነበረ ድርጅት ውስጥ ከነ ዶ/ር ጌታቸው መካሻ ከነ ክቡር አፈ-ንጉሥ ተሾመ ኃይለማሪያም እንዲሁም ዶ/ር ለይኩን ብርሐነኑ ሌሎችም ጋር በመሆን ከፍተኛ ጥረትና ተልኳቸውን በመወጣት አገልግለዋል።

የድርጅቱም ዓላማ እንደነ ጃፓን እና ታላቋ ብሪታንያ ለአገራችን ሞገስ የነበረው የዘውድ ሥርዓት በህግ በተደነገገ ሥርዓት እንዲኖርና ወደ ቀደመው ክብራችን እንመለስ ዘንድ የሚያምን ድርጅት ነበር። በታህሳስ 1953 ዓ.ም ልዑል አልጋወራሽ አስፋው ወሠን ኃይለሥላሴ እንዲናገሩ የተደረገውን ጽንሰ ሃሳብ ሻምበል ገድሉ ለአገርና ለወገን ይጠቅማል በማለት እስከ እለተ- ህልፈታቸው ድረስ ይሄንን ገቢራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ምኞታቸው እንደነበርና ይኼንንም በከፍተኛ የዓላማ ጽናት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት የጣሩ መሆናቸውን ያሳያል።

በዚህም የኃላፊነት ጊዜያት ልዑካንን በመምራት እና ድርጅቱን በተለያየ ቦታ ለማዋቀር በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን እስከ ደብረ ብርሀንና ሌሎችም በወቅቱ ሊያሳስርና ሊያስገድልም በሚችሉ ቦታዎች ለህይወታቸው ሳይሳሱ ተንቀሳቅሰዋል።

እንዲህ ያለውም ስብእና ሁሌም የሚስተዋልባቸው ልበ- ሙሉነት እና ዋጋ ለመክፈል አለመፍራትን የሚያመለክት ነው።

የመጨረሻዎቹ ጊዜያት

ሻምበል ገድሉ ኃይሉ፣ በደረሰባቸው የጤና መታወክ ምክንያት የመጨረሻ ዘመናቸውን በጤና መታወክ ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው የመላው ቤተሰቦቻቸውና የባለቤታቸው ፍቅርና እንክብካቤ ሳይለያቸው በተወለዱ በ78 ዓመታቸው በሠሜን አሜሪካ በፌርፋክስ በቨርጅንያ ጥቅምት 9 ቀን 2002 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።

አስከሬናቸውም በፌርፋክስ ሚሞሪያል ፓርክ በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል።

      በመጨረሻም

ሻምበል ገድሉ፣ ኃይሉ በጣም ቅን መንፈሰ ጠንካራ እና ላመኑበት ዓላማ በፍጹም ወደኋላ የማይሉ፣ ለተበደለ ጠበቃና ተቆርቋሪ፣ ለጋስ ገና ከጠዋቱ ጀምሮ ልዑል እግዚአብሔር ሞገስን ያለበሳቸው ልዩ የሠው መውደድ የነበራቸው በተሠማሩበት የሥራ መስክ ሁሉ ትጉና ውጤትን ለማዝመዝገብና ልዩነትን ለማሳየት እጅግ የሚጥሩ የነበሩና ማስመዝገብም የቻሉ ሰው ነበሩ። በሥራ ዘመናቸውም በማንኛውም ግዜና ሠዓት የገጠማቸውን እያንዳንዷን ክስተት በማስታወሻነት መዝግቦና ሰንዶ የማስቀመጥ ልምዱ የነባራቸው ሰው ብልህ ሰው ነበሩ።

ገና ከወጣትነትና ከጎልማሳነት ዘመናቸው ጀምሮ ያማረ ተክለ ሰውነት ታክሎበት በዘመናዊነት፣ በቆፍጣናነት፣ በስፖርተኛነት እንዲህም በተሽቀርቃሪነት የታወቁና እጅግም የተወደዱ ዕድለኛ ሰው ነበሩ።

ከሻምበል ገድሉ ኃይሉ ቤተሰቦች የቀረበ መደምደሚያ እና ምሥጋና

የ“መዝገበ አዕምሮ” አሳታሚ የተወዳጅ ሚድያ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ያልተሰነዱና ትኩረት ያልተቸራቸውን በባትሪ እየፈለገ እውቅናን ለመስጠትና ታሪክን በመሰነድ እየተገበረ ላለው ታላቅና ድንቅ ስራ ልባዊ ምሥጋና አድናቆታችንን እንገልፃለን።

እቴጌ ጣይቱ ጋር በስተቀኝ በኩል የቆሙትና እንደገናም በቀኝ በኩል ከእቴጌ ጀርባ ካባ ለብሰው የቆሙት ወይዘሮ የሺመቤት ተሠማ ሣህሉ ይባላሉ። የንጉሥ ወልደጊዮርጊስ ሚስት ሲሆኑ የፊታውራሪ ኃይሉ ይግዛው የናታቸው የወ/ሮ አህሉሽ ኃይሉ እናትና አያታቸው ናቸው። ወይዘሮ የሺመቤት ተሰማ እናታቸው ወይዘሮ የውብዳር ኃይለማሪያም ገብሬ ናቸው። የደጃዝማች ብጡል ኃይለማሪያምና የደጃዝማች ውቤ ኃይለማሪያም እህት ናቸው።

ደጃች ውቤ ደሞ የእቴጌ ጥሩወርቅ አባት ሲሆኑ የአጼ ቴዎድሮስ ሚስት የልዑል አለማየሁ እናት የነበሩ ናቸው። እዚህ ፎቶግራፍ ላይ ያሉት በሙሉ ለምሳሌ እራስ ወሌና ራስ ጉግሳ የደጃዝማች ብጡል ኃይለማሪያም ልጅና የልጅ ልጅ ናቸው። ጉግሳ ወሌ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ባል ነበሩ።

ጣይቱ ብጡል የምኒሊክ፣ ወይዘሮ የሺመቤት ተሰማ የንጉስ ወልደጊዮርጊስ ወይዘሮ አሰለፈች ወልደሃና የወሮ ደስታ ብጡል ልጅ ከጣይቱ በስተግራ በኩል ያሉት ደግሞ የግርማዊ ጃንሆይን ወንድም የሆኑት ደጃዝማች ይልማ መኮንን አግብተው ነው ልዕልት የሻሽወርቅ ይልማ የሚወለዱት። የራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ሚስትና የነ ክቡር እንዳልካቸው መኮንን የእንጀራ እናት መሆናቸው ነው። የልዕልት ሣራ ግዛው እናት ወሮ ሙሉመቤት ሐይሉና ወሮ አህሉሽ ሐይሉ የክቡር ፊታውራሪ ሐይሉ ይግዛው እናት ጋር እትማማች ናቸው። በቀጥታ አጎት መሆናቸው ነው። እንደሚታወቀው ልዕልት ሳራ ግዛውም የልዑል መኮንን ሚስት እና የእነ ልዑል ወሠንሠገድ ወዘተ እናት መሆናቸው ነው። እነ ደጃዝማች አያሌው ብሩ እነ ደጃዝማች መስፍን ገመች እነ ደጃዝማች ገሠሠ ወልደ ሃና በሙሉና ሌሎችም እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ የተሳሰሩና የተዋለዱ የቅርብ ቤተሰቦች ናቸው። ይሔ ጥናት የብዙ ግዜ ውጤት ነው። በነ ክቡር ደጃዝማች ወሠኔ ትርፌ በኩል ያለውንና ሌላውን ሳንነካ ነው፡፤ ከላይ ያለው የሻምበል ገድሉ ሐይሉ በአባታቸው በፊታውራሪ ሐይሉ ይግዛ እናት በክብርት ወሮ አህሉሽ ሐይሉ እናት በኩል ብቻ ያለ ሐረግ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *