ሻምበል አክሊሉ ዘለቀ ንጉሤ

ሻምበል አክሊሉ ዘለቀ ንጉሤ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በሚድያ ዘርፍ ጉልህ አሻራ የነበራቸውን ሰዎች ታሪክ እየሰነደ በማስቀመጥ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም መዝገበ-አእምሮ በሚል ርእስ የ180 የሚድያ ሰዎችን የስራ እና የህይወት ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ለማስመረቅ መብቃቱ ይታወቃል፡፡ በቀጣይ ቅጽ 2 እትማችን ታሪካቸው ከሚካተት የሚድያ ሰዎች አንዱ ሻምበል አክሊሉ ዘለቀ ነው፡፡ ሻምበል አክሊሉ ከ50 አመት በፊት በጦር ሀይሎች ሬድዮ ፤በቲቪ የስፖርት ክፍል በኋላም በዜና አንባቢነት የዘለቀ ሚድያው ላይ ባለፉት 50 አመታት በወጉ የሰራ ጠንካራ ባለሙያ ነው፡፡ የዚህ ሰው ታሪክ ለትውልዱ ጠቃሚ መሆኑ ታምኖበት ታሪኩ እንዲህ ለመሰነድ ተዘጋጅቷል፡፡ እዝራ እጅጉ ታሪኩን እንደሚከተለው አጠናክሮታል

ሻምበል አክሊሉ ዘለቀ ንጉሤ ወደዚህ ዓለም የመጣው በ1945 ዓ.ም ነው፡፡ የተወለደው በመሀል አራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አጠገብ ካለው ዳግማዊ ሚኒልክ ሀውልት ፊት ለፊት ከሚገኝ ከባለ አንድ ፎቅ ቤት ውስጥ ነበር፡፡ አባቱ የምድር ጦር አባል የነበሩት መቶ አለቃ ዘለቀ ንጉሤ ፣ እናቱ ወይዘሮ ወርቅነሽ ወልደኢየሱስ ይባላሉ፡፡ በአራዳ ጊዮርጊስ ከወላጅ እናቱ ጋር ለ2 ዓመት ያህል ከቆየ በኋላ ወደ ለገሀር በመምጣት ቅዱስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ማርገጃ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ተቀመጠ፡፡

የፊደል ዘር መለየት ሳያውቁ ልጃቸው መማር የሚገባው መሆኑን የተረዱት እናቱ ወ/ሮ ወርቅነሽ ወልደ ኢየሱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን አትሮንስ ዘርግተው ያስተምሩ ከነበሩት ዓይነስውሩ ነገር ግን ልብ ብርሃን ካላቸው የኔታ ሀብተሚካኤል ዘንድ አቀረቡት፡፡ በጊዜው 4 ዓመት ሲሞላው ፊደልን ለመለየት የኔታ ሀብተሚካኤል ዘንድ የቀረበው አክሊሉ እጅግ ፈጣን በሆነ የትምህርት አቀባበል በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለዲቁና ደረጃ ሊበቃ ቻለ፡፡ ሳይማሩ እርሱ እንዲማር ከፍተኛ ማበረታታት ያሳዩት እናቱን ፊደል አስቆጥሮ ዳዊት ደጋሚ አደረጋቸው፡፡

አክሊሉ የመጀመሪያ ደስታዬን አግኝቻለሁ ብሎ ሳያበቃ ዘመናዊውንና ዓለማዊውን ትምህርት ለመቅሰም አቃቂ ሚሲዬን ትምህርት ቤት ገባ፡፡
የእንግሊዝኛ ፊደልን በግሪን ፕራይመር መለየት የጀመረው አክሊሉ ወደ ሺመልስ ሀብቴ ትምህርት ቤት ተዘዋውሮ 3ኛ ክፍል ከተቀመጠ በኋላ አስተማሪዎቹ ለትምህርት ያለውን ፍላጐትና ችሎታ መዝነው 5 ተማሪዎችን ሲመርጡ አንዱ አክሊሉ ነው ብለው ወደ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት አስገቡት፡፡

አክሊሉ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብቶ እስከ 8ኛ ክፍል ከተማረ በኋላ ባስመዘገበው ጥሩ ውጤት ኮከበ- ጽባህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቶ የመማር እድል አገኘ፡፡ በኮከበ- ጽባህ ትምህርት ቤት በቲያትርና በእግር ኳስ ጨዋታ ወደፊት የት ይደርሳል እስኪባል ድረስ ለትምህርት ቤቱ የበኩሉን ድርሻ አበረከተ፡፡ አክሊሉ፣ አንድም ጊዜ የውትድርና አባል እሆናለሁ ብሎ አስቦ አያውቅም፡፡ ጭርሱኑ ወታደር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሳያውቅ መቆየቱን ሳይሸሽግ ለጠየቁት ሁሉ ይናገራል፡፡

መገናኛ /ሲግናል/ የሚባል የጦር ክፍል አጠገብ ይኖሩ የነበሩትን አያቱን እማሆይ ወደርየለሽ አባ ተምሳስን ለመጠየቅ ይሄድ ስለነበር የመገናኛ /የሲግናል/ ወጣቶችን አለባበስና የራዲዮ ግንኙነት ሞርስ በሚባል መሣሪያ የወፍ ቋንቋ ነው እንዴ የሚለውን …… ምልክት ወረቀት ላይ ጭረው በእጅ ሲጠቀጥቁት ……. የሚለውን ድምጽ ተቀብለው ለአለቆቻቸው ሲያቀርቡ በመመልከቱ ከወጣቶቹ ጋር ለመቀላቀል ልቡ ሸፈተ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመጨረስ የማትሪክ ፈተና ሲጠብቀው እርሱ ቀድሞ ምድር ጦር መገናኛን በልጅ ወታደር ተቀላቀለ ፡፡ ፍቼ ማሠልጠኛ የእግረኛ ወታደራዊ ትምህርቱን ከተማረ በኋላ ሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ገብቶ ለ9 ወራት የመገናኛ /ሲግናል/ ትምህርቱን አጠናቅቆ ወደ ምድር ጦር መገናኛ ተመለሰ፡፡

በምድር ጦር መገናኛ ክፍል የራዲዮ ኦፕሬተርና የኤስ ኤስ ቢ አገልግሎት ከሰጠ በኋላ ወደ ወታደርና ዓላማው ጋዜጣ ክፍል ተዛወረ፡፡ ከ1964 እስከ 1966 የመጀመሪያው የስፖርት ፕሮግራም በኢትዮጵያ ራዲዮ አቅራቢ በመሆን በአስደማሚ ድምፁ በመቀጠል ከ1966 እስከ 1979 ዓ.ም የጦር ሀይሎች ራዲዮ ፕሮግራም የስፖርት ዋና አዘጋጅ ሆነ፡፡ የጦር ሀይሎች ሬድዬ አዘጋጅ በነበረበት ጊዜም በጊዜው አራተኛ ክፍለ ጦር የነበሩትን ኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያምን ቃለ -መጠይቅ ያደረገላቸው ሲሆን ከ 3 አመት በኋላም ኮሎኔሉ የደርግ ሊቀመንበር ሆነው መገኘታቸው ይገርመው ነበር፡፡ታዲያ ሻምበል አክሊሉ አንድ ጥያቄ ለመንግስቱ አቅርቦ ነበር፡፡ ከስፖርቶች የትኛውን ይወዳሉ ብሎ ፡፡ ኮሎኔሉም መልስ ሲሰጡ ቁመቴ አጭር ባይሆን ኖሮ ቦክሰኛ መሆን እፈልግ ነበር የሚል መልስ ሰጥተውት ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ከሟቹ ሰለሞን ተሰማ ጋር በመሆን የቴሌቪዥን የስፖርት ፕሮግራም በምክትልና እስከ ዋና አዘጋጅነት ሠራ፡፡ ሻምበል አክሊሉ በጊዜው 10ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ከአንጋፋው ሰለሞን ተሰማ ጋር በቀጥታ ስርጭት አስተላልፈዋል፡፡ ይህን ዘገባ ካቀረቡ በኋላ በደርግ ላይ ልዩ ቅስቀሳ አድርጋችኋል ተብለው ለእስር ተዳረጉ፡፡ በጊዜው ሰለሞን ተሰማ በህትመት ሚድያ እየሰራ የቲቪ ጋዜጠኝነቱን ተግባር ያከናውን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ቲቪ በጊዜው ብቸኞቹ የስፖርት ጋዜጠኞች የነበሩት ሰለሞን ተሰማ እና ሻምበል አክሊሉ ዘለቀ ነበሩ፡፡ ኋላ ላይ ሻምበል አክሊሉ ዘለቀ ከስር የሚመጡ የስፖርት ጋዜጠኞችን በማብቃት ዕድሉን ሰጥተዋል፡፡ ያኔ እነ ሻምበል አክሊሉን ተክተው ቦታውን የተረከቡት ጋዜጠኞች እነ ሰሎሞን ገብረእግዚአብሄር ፤እና ፀጋ ቁምላቸው ነበሩ፡፡ በመቀጠል ደግሞ አለሙ መኮንን መጣ፡፡ አለሙ መኮንን ቀደም ሲል የእግር ኳስ ተጫዋች ነበር፡፡ በጊዜው በኢቲቪ የውጭ የስፖርት ዜናዎች ይቀርቡ ነበር፡፡ በጊዜው የኢትዮጵያ ቲቪ መምሪያ ኃላፊ አቶ አለም መዝገበ ነበር፡፡ በኋላ ላይ አቶ አዛርያ ኪሮስ መጣ፡፡

ሻምበል አክሊሉ ዘለቀ በፍሪላንሰርነት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዜና አንባቢ በመሆን እስከ 1983ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ ድረስ ሞያዊ አስተዋጽኦ አደረገ ፡፡ ከ 1985 እስከ 1992 አሜሪካ ሎስ አንጀለስ ተዘጋጅቶ ለሚቀርበው “ኢትዮጵያን ሪቪው” እንግሊዝኛ መጽሔት የአፍሪካ ወኪል በመሆን የተራራቁትን ኢትዮጵያውያንን የሚያቀራርብ በትክክለኛ የዜና ዘገባ እውነትን ገሀድ በማውጣት የጋዜጠኝነት ተግባሩን አከናወነ፡፡ በዚያው በአሜሪካን አገር ለሚሠራጨው ብሥራት ሬዲዮ ኔት ወርክ እና ለመድህን ራዲዮ ጣቢያ የአፍሪካ ተጠሪ በመሆን አገለገለ፡፡ ሲዊዘርላንድ ጄኔቭ ይታተም ለነበረው አድማስ መጽሔት በተባባሪ አዘጋጅነት ሠራ፡፡ በ1997 ዓ.ም ተፎካካሪ ፖርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ሻምበል አክሊሉ ዘለቀ ንጉሤ የ “ሕብረት ተፎካካሪ አባላት ድምጽ በመሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ አይኑን ገለጠለት የተባለለትን ቅስቀሳ ሲያደርግ ኢህአዴግ ለእሥራት ዳረገው፡፡ ከዚህ በኋላ ቂመኛው ኢህአዴግ አክሊሉን ለሦስት ዓመት ያህል ያለ ሥራ ከቤቱ እንዲቀመጥ አድረገው፡፡

ከሦስት ዓመት ያለሥራ መቀመጥ በኋላ ሕያው ተስፋ ለሚባል የመንፈሳዊ ራዲዮ ጣቢያ አገልግሎት ከሰጠ በኋላ ሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የቀድሞው ሠራዊት አባላት ባቀረቡለት ጥያቄ መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ የቀድሞው የሀገር መከላከያና የፖሊስ ሠራዊት የሚለውን ስም ይዞ በባላገሩ ቴሌቪዥን እጅግ ከሚወደው ልጁ ጋዜጠኛ መሣይ አክሊሉ ጋር በመሆን ስሙ የጠለሸውን፣ ጡረታና ሕክምና ያጣውን፣ የቀድሞ ጦር መብቱ እንዲከበርልት በሞያዊ ብቃት አገልግሎት ሊሰጥ የቻለ የሠራዊቱ ድምጽ የተባለ ሥም ተቀይሮለት በዚያው በባለአገሩ ቴሌቭዥን ዜና አቅራቢነት መስራቱን ቀጠለ፡፡

ሻምበል አክሊሉ ዘለቀ ንጉሤ የሁለት ወንዶችና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ሆኖ ትንፋሹ እስኪቋረጥ ድረስ ከሠራዊቱ ማን ይለየኛለ ብሎ ዛሬም የሠራዊቱ ድምጽ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

  • ሻምበል አክሊሉ ዘለቀ የሠራዊቱን ተጋድሎ የሚያወሱ ሦስት የጦር ሜዳ መጽሐፍትን ተርኮ በሲዲ አቅርቧል፡፡
  • መንፈሳዊ መጽሐፍትን ማለትም ብሉይኪዳንና አዲስ ኪዳን በሲዲ ተርኮ ለወገኖቹ አበርክቷል፡፡
  • “ሰው ስንት ያወጣል” የሚል ከራሱ ግለ ታሪክ ጋር አዛምዶ በሠራዊት ቤት ያሳለፈውን የሕይወት መንገድ በመጽሐፍ አቅርቧል፡፡
  • ሻምበል አክሊሊ ዘለቀ ንጉሤ የየመንግሥታቱን አገዛዝ በመፈተሽና እውነትን ሲፈልግ ለሠራዊቱ ሲሟገት ተደጋጋሚ እሥራት ደርሶበታል፡፡
  • ሻምበል አክሊሉ እውነትን ፍለጋ ሲል በአፍሪካ በአውሮፖ በአሜሪካ የኡትዮጵያን ሠራዊት ጨዋነት ሀገር ወዳድነት ረሀብና እርዛትን ቻይነት በሚገባ ሰብኳል፡፡
  • የሕይወቴ መንገድ ባጭሩ ይህን ይመስላል የሚለው ሻምበል አክሊሉ ዘለቀ ንጉሤ ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ ለኢትዮጵያና ለወገኑ ሲል ደሙን ያፈሰሰውን አጥንቱን የከሰከሰውን ያለ ጡረታና ያለ ሕክምናተረስቶ የቀረውን የኢትዮጵያን የቀድሞ ሠራዊት ያከብርልኝ ይላል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *