ሰይፉ ፋንታሁን የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ተሸላሚ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣ መዝገበ-አእምሮ ( የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች ፣በመፅሀፍ፣በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት 4 ዓመት ከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መፅሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።

ከእነዚህ ውስጥ የሚድያ ሰዎችም ይገኙበታል። አጠቃላይ 74 ከፍተኛ የሚድያ አመራሮች፣ሚኒስትሮች ፣ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የግል ሚድያ መሥራቾች፣ዋና አዘጋጆች እና መካከለኛ አመራሮች ተካተዋል። 35 ያህሉ በዋና ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ያሉ ሲሆን የሁሉም ታሪክ በተሟላ ደረጃ ለመሰነድ ተችሏል። የእነዚህን አመራሮች ታሪክ ሰንዶ ለአንባቢ ተደራሽ ማድረግ ፈታኝ ቢሆንም አሳክተነዋል። በዚህ ተግባራችንም ተጠናክረን እንቀጥላለን።


በዚህ ፅሁፍ የህይወት ታሪኩን የምናቀርብለት ሰው ሰይፉ ፋንታሁን ሲባል ወደ ራሱ የግል ሚድያ ከገባ 29 ዓመቱን አስቆጥሯል። ከሆሊዉድ ጋዜጣ እስከ ኢትዮ ኤፍኤም 107.8 የተጓዘበት መንገድ አስተማሪ ሆኖ ስላገኘነው ታሪኩን ሰንደናል። ዕዝራ እጅጉ ተአማኒነት ያላቸው የሰነድ እና የምስል መረጃዎችን በመያዝ ታሪኩን አጠናክሮታል ። በቅርቡ በአሜሪካ የሚደረገው የኣፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ተሸላሚ ከሆኑት አንዱ የሚድያ ሰው አንዱ ሰይፉ ሲሆን የህይወት ታሪኩንም ታነቡ ዘንድ ተጋብዛችኋል።


ሰይፉ ፋንታሁን፣ ጷግሜ ወር 1968 በአዲስ አበባ በጋንዲ ሆስፒታል ተወለደ። ወላጅ አባቱ አቶ ፋንታዬ ብዙነህ ሲባሉ እናቱ ደግሞ ወይዘሮ አለሚቱ ሰንደቁ ይባላሉ። ሰይፉ ባሳደጉት አጎቱ ማለትም በእናቱ ወንድም በአቶ ፋንታሁን ሰንደቁ የሚጠራ ሲሆን የአዲስ አበባ ዕድገቱም ልደታ “ቢርሞ ሜዳ” ከሚባለው አካባቢ ነው።የሰይፉ ወላጅ አባት አቶ ፋንታዬ ብዙነህ በ 1970ዎቹ ግድም ያረፉ ሲሆን እርሳቸውም ባቡር በመንዳት ሥራ ላይ የተሠማሩ ነበሩ።

ሰይፉ ፋንታሁን ፣በልጅነቱ ከአካባቢው ልጆች ጋር ኳስ እየተጫወተ ያደገ ሲሆን ለኪነ ጥበብ ልዩ ፍቅር ያደረበት ገና በልጅነቱ ነበር። የቅርብ ቤተሰቦቹ እንደሚናገሩት ሰይፉ ዝንባሌውን በተመለከተ ከሌሎች የቤተሰብ አባላት ያየው ነገር ሳይኖር በተፈጥሮው ክህሎትን የታደለ ነው።

የሰይፉ ወላጅ አባት አቶ ፋንታዬ ብዙነህ እና እናቱ ወይዘሮ አለሚቱ ሰንደቁ በሐረር ይኖሩ የነበር ሲሆን ቤተሰቡም በሆቴል ቤት ሥራ ላይ ተሠማርቶ ነበር።

ሰይፉ ምንም እንኳን አዲስ አበባ ተወልዶ የልጅነት ጊዜውን ቢያሳልፍም ሐረርም ይመላለስ ነበር ። ሐረር በሄደበት ጊዜም የኪነ -ጥበብ ፍቅሩን ለመወጣት ሙከራ አድርጓል ።

ሰይፉ አዲስ አበባ ሳለ ልደታ አካባቢ የሚገኘው ተስፋ ኮከብ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ተምሯል።የት/ቤቱ የሥነ ፅሁፍ ክበብን ይመሩ የነበሩት ደግሞ የታገል ሰይፉ ወላጅ እናት ወ/ሮ ሠናይት ሙልጌታ ነበሩ። እርሳቸው ሰይፉ ለኪነ- ጥበብ ያለውን ልዩ ክህሎት በመመልከት ከልጃቸው ታገል ሰይፉ ጋር ለገዳዲ ሬድዮ ጣቢያ እንዲሄድ ሁኔታዎችን አመቻቹለት። ወይዘሮ ሠናይት በዚያን ጊዜ ተሰጥዖ የታደሉ ታዳጊዎች ወደ መድረኮች እንዲመጡ ይጥሩ ነበር።ታገልም ከወላጅ እናቱ የተሰጠውን ትዕዛዝ በመቀበል ሰይፉን ወደ ለገዳዲ ሬዲዮ ጣቢያ ወስዶ ያሰተዋውቀዋል። ሰይፉም የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሆኖ የመጀመሪያ የሬዲዮ ሥራውን በለገዳዲ ሬዲዮ በትምህርት በሬዲዮ ጀመረ። ታገል እና ሰይፉ በልጅነታቸው “ቢሪሞ ሜዳ “ላይ ኳስ ተጫውተዋል። በጣም ፈጣን እና ቀልጣፋ መሆኑንም ታገል መስክሮለታል።

ሰይፉ በልጅነት ዕድሜው ማለትም ከ1982 ዓ.ም አንስቶ መኖሪያውን ሐረር ያደረገ በመሆኑ እዚያም የጥበብ ፍቅሩን እንዲወጣ ያስቻለው ዕድል ተፈጠረለት።

“ሀረር ላይ ኖሯል። ፀጉሩ ግጥም ያለ ነበር፣ ጥበብ ከልጅነቱ ጀምሮ የኖረበት ነው። ገና በልጅነቱ የቀይ መስቀል ድራማዎች ላይ ይሰራ ነበር።” በማለት የሐረሩ መምህር መክብብ አስራት ምስክርነቱን ይሰጣል።

ሰይፉ በዚያን ጊዜ፣የቤተክርስቲያን ቴአትሮችን ፅፎ አዘጋጅቷል። ከእነ አበባው መላኩ ጋርም ተውኗል።በ 1980ዎቹ ሐረር ላይ የነበሩ የአማተር ክበቦች ላይ የነቃ ተሳትፎ ነበረው። ግጥምም ይፅፍ ነበር፣ትወና ላይ በጣም ጎበዝ፣ ተዋናይነቱም በብዙዎች የተመሰከረለት ነው።

በተለይ ኮሜዲ ገፀ -ባህሪያት ላይ የተዋጣለት ነበር። ለዓላማው ፅኑ ነው አንድ ነገር አደርጋለሁ ካለ ያደርጋል። የኢቲቪ 120 የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ከእነ እንግዳ ዘር ነጋ ጋር ጭውውቶችን ይሰራ ነበር። ከዛ በኃላም ከእነ ሱራፌል እና ተመስገን ጋር የሙዚቃ ዝግጅት ያቀርብ ነበር።

መምህር መክብብ እንደሚናገረው”ሰይፉ ምስጋናም ወቀሳም የማያስደነግጠው በነገሮች የማይሰበር ጠንካራ ሰው ነው ሲል ይመሰክርለታል።

ሰይፉ አይጥ እና ሊጥ በተለየ ሁኔታ መጥላቱን አብሮ አደጎቹ ይመሰክራሉ።

“…በልጅነቱ የሚያደንቃቸው ታላላቅ ሰዎች ዛሬ አብረውት ይሠራሉ፣ ይሄ በጣም ትልቅ ስኬት ነው። ሰይፉ ወርቅ ፀባይ ያለው ትሁት ሰው ነው ሲል መስክሮለታል መምህር መክብብ አስራት።

ሙሉጌታ አክሊሉ ሰይፉን ከሐረር ጀምሮ ያውቀዋል። ወደ ኃላ ተጉዞ ምስክርነቱንም ሲሰጥም፦

” ሐረር የቦቴ ሰፈር ልጅ ነው። ብራና የኪነ-ጥበብ ቡድን ውስጥ ይሳተፍ ነበር፣
ማዕዶት የቤተክርስቲያን የቴአትር ክበብ የሙሉ ሰዓት ቴአትሮችን በጋራ እንሠራ ነበር፣ ከሐረር እስከ አ.አ ቴአትሮችን ይዘን መጥተን ሀገር ፍቅር እና ብሔራዊ ቴአትር ከእነ አበባው መላኩ ጋር መድረኮችን ሠርተናል ። ሐረር ላይ ከአዲስ አበባ የሚመጡ አርቲስቶችን የማስተባበር ስራ ይሰራ ነበር፣ሰዎችን የማሳቅ ልዩ ችሎታም ነበረው፣ የፀጉሩ ሉጫነት ወደ ራሰ በራነት ይቀየራል የማይባል ነበር፣እራሱ ሰይፉ ያዘጋጀው ድራማ ላይ አባት እና ልጅ ሆነን እንደሠራን አስታውሳለሁ ይላል ሙሉጌታ።

ሰይፉ ከልጅነቱ ጀምሮ ለጥበብ እና ለጋዜጠኝነት ፍቅር ነበረው።ሥራ አይንቅም ሁሌም አብሮ ለመሥራት ዝግጁ ነበር። ለዚህም ማሳያ አጃኢባ ያሲን የተባለች ሁለት እጆች ስለሌላት በወላጆቿ ተጥላ የነበረች እና በህይወት ተርፋ በእግሮቿ ብዙ ሥራዎችን ትሰራለች። ይህን ታሪክ ወደ ሰይፉ እንዲደርስ ያደረገው ደግሞ ሙልጌታ ነበር። ሰይፉ እንዲህ ላሉ ጉዳዮች በትኩረት ጊዜ ሰጥቶ ይሰራል በማለት ሙልጌታ ለሰይፉ አድናቆት ይቸረዋል።

አስፋው ሰንበቶ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሐረሪ ክልል ጽ/ቤት ኃላፊ ነው። ስለ ሰይፉ ሲመሰክርም፦

” ሰይፉ፣የቀይ መስቀል በጎ ፍቃደኛ አገልጋይ ነበር። የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ድራማዎች ላይ ይሳተፍ ነበር፣ሰይፉ ጨዋታ ይችላል፣ ያስቃል፣ እስክስታም ይጨፍር ነበር።ሰይፉ የጥበብ ራእዩን አሳክቷል። ያኔ በልጅነቱም ሰብአዊ ድጋፉ ከፍተኛ ነው። ደም ልገሳ እና ማህበረሰብ ተኮር ተግባራት ላይ ከፊት ተሰላፊ እና ሲሠራም ደከመኝን ፈፅሞ የማያውቅ ነው።ቴአትሮቹንም ሲሠራ የሚከፈለው ክፍያ አልነበረም።”በማለት ስለ ሰይፉ ተናግሯል ።

“ሆሊውድ እና ሰይፉ ፋንታሁን ” ሲል ጋዜጠኛ ዕዝራ እጅጉ በፃፈው የግል ማስታወሻ እንዲህ ይላል፦

“……የ1989 አዲስ ዓመት ሲገባ የ 12ኛ ክፍል ማትሪክ ወሳጅ ነበርኩ፡፡ በቦሌ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ቤት የሚኒ ሚድያ ሊቀመንበር ነበርኩ፡፡ የኢቲቪው ፋንታሁን ኃይለማሪያም አንድ ሰይፉ የሚባል ልጅ አለ ላስተዋውቅህ ብሎ ፒያሳ ቲሩም አካባቢ ቀጠረኝ። ያኔ ሰይፉ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተዋወቅኩ።
በ17 ዐመቴ አካፑልኮ ቤይ ፊልምን ለቦሌ ሀይስኩል ተማሪዎች መተርጎም ጀምሬ ነበር ጥቅምት 11 1989 ። ሆሊዉድ ደግሞ የዚያን ሰሞን ነበር አንድ ተብላ የተጀመረችው።

ሰይፉ ፋንታሁን እና ተመስገን አፈወርቅ ሆሊዉድ ጋዜጣን መሠረቱ፡፡ በጊዜው ሁለቱ ዕድሜያቸው ከ 22 አይዘልም፡፡

ሆሊዉድ ስትጀመር በ 15 ቀን የምትወጣ ጋዜጣ ነበረች።
ሰይፉ እስከማውቀው ድረስ የጋዜጣው ባለቤት ሲሆን ሆሊዉድ ላይ እንድሳተፍ ዕድሉን የከፈተልኝ ነው፡፡ በዐመቱ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን እየተከታተልኩ ደግሞ ፒያሳ እየመጣሁ ለሆሊዉድ የሚሆኑ ዜናዎችን እተረጉም ነበር፡፡ ሰይፉም እየከፈለኝ እሠራ ነበር፡፡ ያኔም የጋዜጣ ባለቤትነት እንደ ትልቅ በሚቆጠርበት ዘመን ሰይፉ በ 22 ዐመቱ የጋዜጣ አሳታሚ ነበር፡፡ እንዴት በትጋት ይሠራ እንደነበርም አልዘነጋውም፡፡ የፊያሜታውን ዳዊት ከበደ ወየሳንም የዚያን ሰሞን ነበር ያወቅኩት፡፡
ለፊት ገፅ የሚሆኑ ዜናዎችን እንድተረጉም ይሰጠኝ ነበር። ሰይፉ ብር ስጠኝ እንጂ ስለው በዚህ ወር ብዙ አልሠራንም እያለ ትንሽ ብር ሲሸጉጥልኝ ትዝ ይለኛል።

ብቻ ሰይፉ በመዝናኛ ኢንዱስትሪ ላይ ቀዳሚ አሻራ በማሳረፍ ታሪክ ያነሳዋል፡፡ ሁል ጊዜ ከትህትና የተነሳ እኔ ምን ሰርቼ ቢልም ከሆሊዉድ ተነስቶ የሬድዮ ጣቢያ ባለቤት የሆነበት ትልቁ ሚስጥር የሥራ ሠው ስለሆነ ነው፡፡ ይህን ጥረቱን ደግሞ ከ 1989 ጀምሮ ሳጤን ነበር፡፡ ሆሊዉድ ምን አይነት ይዘት እንደነበራት ለማወቅ ከዚህ ፅሁፍ ጋር የተያያዘዉን የጋዜጣዋን ቅጂ ይመልከቱ፡፡ እና ወዳጃችን ሰይፉ ብዙ ሰው ስለ ጋዜጣ በማያውቅበት ፣ጋዜጣን አሳትሞ ማሰራጨት ፈተና በሆነበት ጊዜ ሆሊዉድን ለህትመት ሲያበቃ ነበር፡፡ በዚህ አደንቀዋለሁ፡፡

ሰይፉ በጋዜጣ፡ በሬድዮ እና በቲቪ በ ሶስቱም ሚድየሞች በመስራት ማዝናናት እንደሚቻል አሳይቷል፡፡ ከሆሊዉድ በፊት ደግም ሞገድ ላይ የጥበበ ዐምድ ላይ ይፅፍ ነበር። ሰይፉ፣ የበጎ ሰው ሽልማት የ 2014 የሚድያ ዘርፍ ዕጬ በነበረ ጊዜ ለሽልማት ድርጅቱ የህይወት ታሪኩን የምሠራው እኔ ስለነበርኩ ብዙ የሥራ ታሪኮቹን ሳሰባስብ ነበር።

ያኔ የተረዳሁት ነገር የሰው ልጅ ትልቅ ጥረት ካሳየ ካሰበበት ቦታ ሊደርስ እንደሚችል ነው፡፡ የሚድያ ሥራ ፈጣሪዎች ቁጥራቸው ትንሽ በሆነበት ሀገር የእነ ሰይፉ ታሪክ ብዙ ያስተምራል፡፡ ታሪክ ሰናጅ ስለሆንኩ ለምፅፈው ሁሉ የሰነድ ማስረጃ አብሮኝ ነው፡፡ የጋዜጣ ታሪክ የሚፃፈው ጋዜጣ ላይ የሚፅፍ ሰው ስለ ሁኔታው ሲናገር ብቻ ነው፡፡ የጥንቱ ወዳጄ፣ አሠሪ ሰይፉ ለመዝናኛው ኢንዱስትሪ ላበረከትከው አስተዋፅኦ መሸለም ሲያንስህ ነው ሲል ዕዝራ እጅጉ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

የመክብብ አስራት ትዝታ ስለ ሰይፉ

እዝራ፥ የሆሊውድ ነገር ከተነሳ አንድ ምሥጢር ላውጋህ። ሐረር እያለ እኔ ቤት ይመጣና ሁሌ እንደምናደርገው የልባችንን እንጫወታለን። አንድ ዕለት መጣና፦

” አዲስ አበባ ልሄድ ነው!” ይለኛል።
“ምንም ሳናወራበት በድንገት? እና ምን ለመሥራት ዐሰብክ?” ግራ ገብቶኝ ጠየኩት።
” ባክህ በቅርቡ አሜሪካ ሆሊዉድ ነው የምታገኘኝ!” ሲል ከት ብዬ ስቄ ሽኘሁት። ከወራት በኋላ ደወለልኝ።
“ባለፈው ሆሊዉድ እሄዳለሁ ስልህ ስቀህ ነበር አይደል?” አለኝ።

“ያንተ ነገር እኮ አይታወቅም ልሄድ ነው እንዳትለኝ?!” ስለው በተራው ስቆብኝ፣
“ባክህ ሆሊዉድ መሄድ ቢያቅተኝ፣ ‘ሆሊዉድ’ የሚል ጋዜጣ ማሳተም ጀመርኩ። ልኬልሃለሁና አንብበህ አስተያየት ስጥ!” ያለኝ አይረሳኝም። ሰይፉ አንድ ነገር ከወሰነ ፈጽሞ ወደ ኋላ አይልም። ሐረር ላይ 1982 ዓ.ም ለዓመታዊው የቀይ መስቀል በዓል ለህዝብ የሚታይ ድራማ ሠርተን ነበር። ያኔ ዕድሜው ዐሥራ ዐራት ቢኾነው ነው። ድርሰቱም ዝግጅቱም የእኔ ስለነበር ገጸ- ባሕርያቱን የመምረጥ መብቱ ስለነበረኝ እረኛ አድርጌ መደብኩት። የክብር እንግዳው የሐረርጌ ክፍለ ሀገር ኢሠፓ ጽ/ኃላፊው ነበሩ። እርሳቸውን ጨምሮ በሳቅ የአዳራሹን ተመልካች ፍንድት ነበር ያደረጋቸው። ያን ጊዜ ከተወኑት ውስጥ ነፍሱን ይማርና መስፍን ጌታቸው እና ዛሬ ትንታግ ተንታኝ የኾነው ጋዜጠኛ ዐቢይ ደምለው ይገኙበት ነበር። በእዚህ እጋጣሚ ሦስት የብዙዎች ጥያቄዎችን አረጋግጬ ልለፍ፤
፩- አንዳንዶች በዕድሜው ላይ ይከራከራሉ። እሱም በራሱ ስለሚቀልድ ሰባ ዓመት የሚመስላቸው አይጠፉምና የሰይፉን ዕድሜ ተወዳጅ ሚድያ ካቀረበው ጋር ማመሳከር ቢችሉ፤
፪- ፀጉሩን የመለጡት አዲሶች ይመስሉኛል። (ሃሃሃሃሃ) ሐረር እያለ ፀጉሩ ከግንባሩ ድፍት ያለ ሉጫ የሚሉት ዓይነት ነበረ። ነበረ ኾኖ ተመልጦ ቀረ እንጂ! አዲስ ስንገናኝ “ከክቡር ገና ቀንተህ ነው መላጨት የጀመርከው!?” እለው ነበር፤ ለካ ጉዳዩ ሌላ ኾኖ ነው።
፫- ብዙዎች መተወን የሚችል አይመስላቸውም። ሐረር ላይ ከኛ ጋር ያልተወነበት መድረክ የለም። አንዴ ከአስረስ በቀለ ጋር ከአዲስ አበባ ጋብዘናቸው ብዙ ከተሞች ላይ ስናሳይ፣ ድንገት ጅግጅጋ ከተማ ላይ አስረስ ካልዘፈንኩ ይለኛል። ማይኩን ይዞ ወጣ። ሙዚቀኞቹ ” ብርቱካን ትርንጎ መሳይ’ የሚለውን ማጀብ ቀጠሉ። አስረስ በምርጥ ድምፁ አዳራሹን አናጋው! ሽልማት በሽልማት ይኾናል። ከመድረክ ጀርባ ኾኖ ሰይፉ ያያል። በቅናት መንፈስ ማይኩን ይዞ ወደ መድረክ ወጥቶ መዝፈን ሲጀምር አስረስ ደንግጦ ቆመ። ለካንስ እየዘፈነ የነበረው ከጀርባ ኾኖ ሰይፍሻ ነበር። ተመልካቹን በሳቅ አንፈራፈረው። እናም ልጃችን ከልጅነቱ ጀምሮ ነው ጥበብ የጠራችው ለማለት ነው! የእሱ ገጠመኞች ብዙ ቢኾኑም ለዛሬ ይብቃኝ!

የሰይፉ የሚድያ ጅማሮ (ከ1989-2018)

ሰይፉ ፣ከ1986-1989 ባሉት 4 ዓመታት በልዩ ልዩ ጋዜጦች ላይ ፅሑፎችን በማበርከት፣ ለ120 ፕሮግራም የሚሆን ድራማዎችን በመፃፍና በመተወን የጥበብ ፍላጎቱን ሲወጣ ነበር። ከእንግዳዘር ነጋ፣ከአስረስ በቀለ እና ከሌሎችም ጋር በመተወን ብዙዎችን ዘና ሲያደርግ ነበር። ያኔ የተወነባቸው አጫጭር ጭውውቶች አልፎ አልፎ በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ ይታዩ ነበር። ሰይፉ፣ በዚያን ሰዐት ይህን ሁሉ ሲሠራ ገና 19 ዓመቱ ነበር።20 ዓመቱን ካከበረ በኃላ ግን የራሱን ድርጅት የመመሥረት ህልም ሰነቀ።

በጊዜው የሪፖርተር ጋዜጣ ለህትመት በቅታ በአንባቢያን ዘንድ ከበሬታን ያተረፈችበት ጊዜ ነበር። ወጣቱ ሰይፉም የሪፖርተር ጋዜጣ መሥራች አቶ አማረ አረጋዊ ዘንድ ቀርቦ እንዲህ አለ፦” እኔ አቶ አማረ የሪፖርተር ጋዜጣ አድናቂ ነኝ። ከፖለቲካ ውጭ የሆነ ጋዜጣ መጀመርም ፈልጋለሁ። ስለ ፊልም የሚያወራ ሆሊዉድ የተባለ ጋዜጣ እንዲኖረኝ እሻለሁ። ነገር ግን ለማሳተሚያም ሆነ ድርጅቱን ለማቋቋም ገንዘብ የለኝም “ሲል ሰይፉ በሀዘኔታ ፊት ሀሣቡን ገለፀ።

ወጣቶችን ማገዝ የሚሆንለት አቶ አማረ አረጋዊም አንተ ሆሊዉድን ጀምረው እንጂ ህትመቱን አታስብ እኔ እሸፍናለሁ ሲል ሞራል ሰጠው። ገንዘቡንም ወዲያው ሰጠው። የ21 ዓመቱ ሰይፉም በ1989 ዓ.ም የጋዜጣ ባለቤት ሆነ። ከጥቂት ወራት በኃላም አቶ አማረ ዘንድ ሄዶ፦” አሁን ማስታወቂያ ማግኘት ጀምሬያለሁ ። ሥራም ጥሩ እየሆነ ነው። ጋሽ አማረ አንተም ትልቁ ባለውለታዬ ነህ ሲል ” ሰይፉ የከበረ ምስጋናውን አቀረበ።

ሰይፉና አቶ አማረ ዛሬ የልብ ወዳጆች ናቸው። አልፎ አልፎም ምሣ ለመብላት እየተገናኙ ይጨዋወታሉ። አቶ አማረን ስለ ሰይፉ ጠይቄው ለዚህ ደረጃ መብቃቱ ያረካዋል። ሰይፉ በጋዜጣ፣በሬድዮ፣በቲቪ አቅሙን ያሳየና ከራሱ አልፎ ለሌሎችም የሥራ ዕድል የፈጠረ ታታሪ ሰው ነው ” ሲል አድናቆቱን ይቸረዋል።

ሰይፉ በታህሳስ 1989 ዓ.ም ሆሊዉድን ሲጀምር ተመስገን አፈወርቅ እና ብርሀኑ ድጋፌ አብረውት ነበሩ። በወቅቱ፣ ተመስገን እና ሰይፉ የፊልም ጉዳዮችን ፣ ብርሀኑ ድጋፌ ደግሞ የሙዚቃ ርዕሰ -ነገሮችን ለአንባብያን ያቀርቡ ነበር። ያኔ ብርሀኑ ድጋፌ፣ የውጭ መፅሔቶችን እንደ ልብ ያገኝ ስለነበር ሆሊዉድ የአንባቢያንን ቀልብ በቶሎ መያዝ ቻለች።

ሆሊዉድ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ለህትመት ስትበቃ ቅጂዋ 2000 ነበር። የምትወጣውም በ 15ቀን አንድ ጊዜ ነበር። ያኔ የጋዜጣው የንድፍ ሥራ ይሠራ የነበረው ፒያሳ ቲሩም አካባቢ ሲሆን ጥበበ ታምራትም በዲዛይን ሥራ አሻራ ነበረው። ኃላ ላይም የፊያሜታው ዳዊት ከበደ ወዬሳ የሆሊዉድን የገፅ ንድፍ ይሠራ ነበር።

ጋዜጣው የተጀመረ ሰሞን ሰይፉ ከአንድ ጋዜጣ 400 ብር ትርፍ ያገኝ ነበር። በሂደት እንደ ሼል ኢትዮጵያ ያሉ ተቋማት ስፖንሰር ሆነው ከመጡ በኃላ የድርጅቱ ገቢም አደገ። ሰይፉ መጀመሪያ መኖሪያው ሰሜን ሆቴል አካባቢ አጎቱ ጋር የነበረ ሲሆን ቀጥሎም ሊሴ ገብረማሪያም ተማሪ ቤት ፊት ለፊት የ250 ብር ቤት ተከራይቶ ይኖር ነበር። በመቀጠልም አለምነህ ዋሴ ይኖርበት የነበረውን ዳትሰን ሰፈር የሚገኝ ቤትን በ850 ብር ተከራየ። እያለ እያለ ሰይፉ ራሱን ለማሳደግ እና በሚድያው ኢንዱስትሪ ለውጥ ለማምጣት መትጋት ጀመረ።

በ1990 ግድም በኢቲቪ ፣ ኢቲቪ ሚዩዚክን የተሰኘ መሰናዶን ከብርሀኔ ንጉሴ ና ከሱራፌል ወንድሙ ጋር ማቅረብ ጀመረ። በዚህም ከተመልካች ጋር የበለጠ ቅርርብ መፍጠር ችሏል።

በ1992 ዓ .ም ኤፍ ኤም አዲስ 97 ነጥብ አንድ ሲጀመር ከዲጄ ዚ ጋር አዲስ ዜማን በመጀመር የራሱን የአየር ሰዓት ወስዶ መሥራት ጀመረ። ሰይፉ የበለጠ በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ላይ ተፅእኖ ማሳደር የጀመረውም በዚህ ወቅት ነበር። አዳዲስ የመዝናኛ ወሬዎችም የሚገኙበት የሬድዮ ፕሮግራም ለመሆን በቃ። ከ1992-2000 ለ 8 ዓመታት የዘለቀው በሰይፉ ይመራ የነበረው አዲስ ዜማ በየዕለቱ እያደገ አድማጭን ለመቆጣጠር በቃ።

በ 2000 ዓ.ም ሸገር ሬድዮ ሲጀመር ሰይፉም “ታዲያስ አዲስ” በተሰኘ አዲስ የመዝናኛ ፕሮግራም በአዲስ መልክ የአድማጭን ጆሮ ለመያዝ ጣረ። ሸገር በሄደበት ጊዜ ሰይፉ የ11 ዓመት የመዝናኛ ሚድያ ልምድ አካብቶ ስለነበር ሥራው ብዙም ፈታኝ አልሆነበትም። ሸገር ከመግባቱ ቀደም ብሎ በ 1996 “መዝናኛ “ጋዜጣን ከፍ ባለ ደረጃ ጀምሮ አንባቢያንን ለመሳብ ቻለ።

ሰይፉ ፣በአንድ በኩል ሸገር ላይ “ታዲያስ አዲስ”ን እየሠራ በሌላ ደግሞ ኢቤኤስ ላይ ሰይፉ በኢቢኤስን በመጀመር ላለፉት 15 ዓመታት ተመልካቹን እያዝናና ይገኛል። ሁሉም የሬድዮም ሆነ የቲቪ ፕሮግራሞቹ፣በዩቲዩብ ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር ያላቸው ሲሆኑ ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀምሮ ሌሎች ታዋቂ ሰዎችንም በፕሮግራሙ ላይ ማቅረብ ችሏል።

ከ2009 ጀምሮ ደግሞ ከሁለት አጋሮቹ ጋር በመሆን ኢትዮ ኤፍ ኤም _107.8 ለማቋቋም ችሏል።

የሚድያ ሰው ሰይፉ ፋንታሁን ባለፉት 29 ዓመታት በሚድያው ኢንዱስትሪ ላይ ያለ አንዳች ዕረፍት እየሠራ ስኬታማ ሥራ ፈጣሪ የሚድያ ሰውና ባለቤት ለመሆን ችሏል። በ 13 ዓመቱ ለገዳዲ ላይ የጀመረው ጥረት ኢትዮ ኤፍ ኤም ላይ አድርሶታል። በመጠነኛ ካፒታል አንድ ብሎ የጀመረው ሆሊውድ ጋዜጣ ወደ ሬድዮ፣ከዛም ወደ ኢቲቪ፣ ቀጥሎም ወደ መዝናኛ ጋዜጣ አቃርቦታል። ሐረር ቀይ መስቀል አሀዱ ያለው በጎነቱ ለሜቄዶንያም ተርፏል።

የሰይፉ ነገር…..

(በረከቱን አንውሰድበት)

            ከአበበ ፈለቀ

ከሰይፊሻ ጋ ከ30 አመታት በላይ የጸና ጓደኝነት አለን። አብረን ብዙ አሳልፈናል፣ እድገቱን ጉዞውን አይቻለሁ። በስኬትና በስበዕናቸው ከምኮራባቸው ጥቂት ወዳጆቼ ውስጥም አንዱ ነው።

ሰይፉ በሰፊው ሊተነተን የሚችል፣ ‘የስኬት መርሆች’ን ለማስተማር የሚበቃ የህይወት ጉዞ አሳልፏል። ውጤታማነትን በአቋራጭ ሳይሆን በጥረት የጨበጠ ነው። ከሁሉም በላይ እግዚአብሔር የሰጠው የሙያ ክህሎቱ (talent) ወሳኝ ቢሆንም በየጊዜው ራሱን እየለወጠ፣ እያሳደገ የመጣ፣ በአንድ ቦታ ያልቆመ ሰው ነው። ከጊዜ፣ ከዘመን፣ ከቴክኖሎጂና ከሁኔታዎች መለዋወጥ ጋ አብሮ በመለወጥና በማደግ ራሱን ከዘመን ጋር እያቀናጀ መጥቷል።

ለረጅም ዓመታት ሳያቋርጥ (consistently) በዚህ ሙያ ላይ ስራዎችን ማቅረብ መቻል ከባድ ነው። ሰይፉ ሁለገብ ነው። ከሁሉም በላይ ፅናትና አይሰበሬነት (resilience) አለው። የሚጎርፉለት አድናቆቶች አላሰከሩትም፣ በስራዎቹ የሚመጡበት የትችት ውርጅብኞች እሱ ከፈለገው፣ ካቀደው፣ ከተለመው የፕሮግራም ቅርጽ፣ ይዘት፣ እና የአቀራረብ ዘዬ ዝንፍ አላጀረገውም። ይልቁንም በዛው ባሰበው መንገድ የተሻለ ስራ ለመስራት በየጊዜው ራሱን ለማሳደግ (continious improvment) መጣርን መርጧል። ከሁሉም በላይ ሰይፉ ራሱን ሆኖ ነው የኖረው። የማንነት ቀውስ (Identity crisis) የለበትም፣ የዝና ጠኔ አልጎበኘውም። ራሱን መሬት አውርዶ በትህትና (humility) የሚኖር ሰው ነው።

ባለፈው ለሜቄዶን ያ ድጋፍ የሚሰባሰብበትን መድረክ ከማመቻቸቱ ጋ ተያይዞ ስሙ ደጋግሞ ሲነሳ አይቻለሁ። ሰይፉ ሌላው የማንነቱ መገለጫ ለሰው በጎ ማሰቡ፣ በጎ ማድረጉ እና በሰወች ደስታ መደሰቱ ነው። መድረክ ላይ ወይም ቲቪ ላይ ከሚታዩት በጎ ተግባራቱ ጀርባ፣ ህዝብ የማያውቃቸው፣ እሱም የማያወራቸው፣ (እንዲወሩም የማይፈልጋቸው) በርካታ በጎ ተግባራትን ድምጹን አጥፍቶ ማድረግ የሰይፉ የረጅም ዘመን ስበዕና ነው። ለሰይፉ በጎ ማድረግ ስራ አይደለም። እድልና አጋጣሚ ሲገኝ የሚደረግ ነገርም አይደለም። ካሜራ ሲበራ፣ ሰው እንዲያይ የሚደረግ የእዩኝታ ተግባርም አይደለም። ለሰይፉ በጎ ማድረግ የህይወቱ አንድ አካል ነው። በሰው ደስታ ደስ ያሚለው ሰው ነው። ሲያደርግ እኔ ምን አተርፋለሁ አይልም።

የማድረጉ፣ የበጎነቱ፣ በሰወች ደስታ የመደስቱ ምስጢር ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋ ያለው ቅርርብ ነው። ሰይፉ እግዚአብሔር ከየት አንስቶ የት እንዳደረሰው አልዘነጋም። እናም ለሁሉም ነገር “ክብሩን አምላክ ይውሰድ” ከሚሉ ሰወች አንዱ ነው። ለሰው በጎ ሲያረግ ከአምላኩ ጋ የሚነጋገርበት፣ ምስጋናውን የሚያቀርብበት፣ በረከቱን የሚረከብበት መንገድ ነው። እናም ሰሞኑን የተያዙ ሰዋዊ ምስጋናወች፣ ሽልማቶች፣ እውቅናወች የመስጠቱ ሃሳብ፣ ምንም እንኳን የሚወዱትንና የሚያከብሩትን ሁሉ (እኔን ጨምሮ) የሚያስደስት ሃሳብ ቢሆንም፣ ሰይፊሻ የሚፈልጋቸውም፣ የሚደሰትባቸውም ሃሳቦች እንዳልሆኑ አውቃለሁ።

እናም ለሰይፉና እሱን ለመሰሉ ሰው ስለሆኑ ብቻ በጉ ለሆኑ፣ ስለተደረገላቸው ከአምላካቸው ጋ በበጎነት ለሚነጋገሩ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ለማክበር ሰውን ላከበሩ ሁሉ፣ ምድራዊውን ጭብጨባ ሰጥተን የእግዛብሔርን በረከት አንውሰድባቸው። ይልቁን እግዚአብሔር አብዝቶ ጉልበቱን፣ አቅሙን፣ ቸርነቱን፣ መሻቱንና በረከቱን ጨምሮ ጨማምሮ፣ አብዝቶ እንዲሰጣቸው በጽሞና እንጸልይላቸው እላለሁ።

አምላክ ለሁላችንም በጎ የማሰብ፣ በጎ የመሆን እና በጎ የማድረግን ጸጋ ያልብሰን።

በበጎ አድራጊነት ሥራው ምስጋና የሚቸረው ሰይፉ ለታይታ የማይጓጓ፣ ስለ ራሱ እንዲነገርለት የማይሻ እንደሆነ የቅርቦቹ ይመሰክራሉ። ሰብዕናው ለሌሎች መድረስን ያስቀድማል። ያለውን የሚድያ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ግምት ውስጥ በማስገባት ለመቁጠር የሚያዳግቱ በጎ ተግባራትን አከናውኗል። ይህም ርካታ ይሰጠዋል እንጂ ሌሎች እንዲያወሩለት አይሻም። ሰይፉ የሕይወት ታሪኩ እንዲሰነድ በተወዳጅ ሚድያ የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ተጠይቆ እኔ ምን ሰርቼ? በሚል ትህትና ይለፈኝ ብሎ ነበር። እኛም መረጃዎችን አሰባስበን ታሪኩን ሳናወጣው አቆይተን ነበር። አሁን ግን ጊዜው ስለሆነ የሰይፉን ታሪክ ከተሟላ መረጃ እና ብዙም ካልታዩ ምስሎች ጋር እነሆ አስነብበናል። ቀሪ መረጃዎችን በቀጣይ የምናካትት ይሆናል። የዝግጅት ክፍሉ ይህን ፅሁፍ ለማጠናከር የቅርብ ሰዎችን እና ተአማኒነት ያላቸውን ምንጮች ያነጋገረ ሲሆን መረጃ የሰጡንን ሁሉ ልባዊ ምስጋናን ማቅረብ እንወዳለን።

በተለይም መምህር መክብብ አስራት፣ አቶ አማረ አረጋዊ፣ አቶ በዛብህ ተክሉ

ነፍሱን ይማረውና ዳዊት ከበደ ወዬሳን እናመሰግናለን ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *