ሜሮን ጌትነት
ተወዳጅ ሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ማእከል በሚድያው ዘርፍ ልዩ አሻራ ያላቸውን እና የነበራቸውን ባለሙያዎች ታሪክ እየሰነደ ሲያቀርብ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደም የ180 የሚድያ ሰዎችን የህይወት ታሪክ መዝገበ አእምሮ በሚል ርእስ በመጽሀፍ ማውጣታችን ይታወሳል። አሁን ደግሞ በቀጣይነት የ200 የጥበብ እና የሚድያ ሰዎችን የህይወት ታሪክ አሰባስበን በአንድ መጽሀፍ አድርገን ለማውጣት መሰናዶ አጠናቀናል።
አሁን በዚህ ጽሁፍ የህይወት ታሪኳን የምናይላት ገጣሚ እና ተዋናይት ሜሮን ጌትነት ናት፡፡ ሜሮን ጌትነት በተጨማሪም የቴአትር ጥበባት ምሩቅም ነች፡፡ በአሁኑ ሰአት መኖሪያዋን በባህር ማዶ ያደረገችው ሜሮን ዛሬም የኪነጥበብ ፍላጎት እንዳላት ይነገራል፡፡ የሜሮንን ታሪክ እንደሚከተለው ሰንደነዋል፡፡
ሜሮን ጌትነት በምሥራቅ ሀረርጌ አሰበ ተፈሪ /ጭሮ/ ከተማ ሰኔ 10 ቀን 1975 ዓ.ም ተወለደች። በወላጆችዋ የሥራ ዝውውር ምክንያት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በተለያዩ የሃገሪቷ ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውራ የተማረች ሲሆን ይህም 1ኛ ክፍልን ወለጋ ሻምቡ አንደኛ ደረጃ፤ 2ኛ እና 3ኛ ክፍልን በአዲስ አበባ ህብረት በልጅነት፤ 4ኛ ክፍል በአራት ኪሎ ቅድስት ስላሴ፤ 5 ኛ ክፍልን በጠመንጃ ያዥ፤ 6ኛ ክፍል በአሰበ ተፈሪ ቁጥር አንድ፤ 7ኛ እና 8ኛ ክፍል በእውቀት ፋና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በአብዮት ቅርስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቃለች።
ከዚያም በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በማርኬቲንግ ክፍል በዲፕሎማ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል በዲግሪ የተመረቀች ሲሆን የሁለተኛ ዲግሪዋንም በዚሁ ትምህርት ክፍል በቴአትር ለልማት /Theatre for Development/ ተከታትላለች።
ይህ በተለያዩ አካባቢዎች የማደግና የመማር አጋጣሚ ከሰዎች ጋር በቶሎ የመግባባትና ወዳጅነት የመፍጠር እንዲሁም ከአካባቢና ሁኔታዎች ጋር በፍጥነት መላመድ እንድትችል ያገዛት ሲሆን ለኪነጥበባዊ ምልከታዎቿና ለፈጠራ ዝንባሌዋ መሰረት ሆኗታል።
የ7ኛ ክፍል ተማሪ በነበረችበት ወቅት በት/ቤቱ ውስጥ ይዘጋጅ በነበረ የግጥም ንባብ መድረክ ላይ ግጥም ማንበብ የጀመረችው በመምህራኖችና በተማሪዎች ይሰጥ የነበረው የፈጠራ አድናቆትና ድጋፍ አጓጉቷት እንደነበረ ታወሳለች፤ በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ቆይታዋም በሚኒሚዲያ፣ በስነተዋልዶ ጤናና በቀይ መስቀል ክበቦች በመሳተፍ እንዲሁም በስነጽሁፍ ውድድሮች ትምህርት ቤቷን ወክላ በመወዳደር፣ በማሸነፍና በመሸለም የኪነጥበበ ጉዞዋን የጀመረችው ሜሮን የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ በነበረችበት ወቅት በጋሽ አበራ ሞላ የወጣቶች ፕሮጀክት አማካኝነት የኢትዮጵያንና የጃፓንን ግንኙነት በሙዚቃ ለማጠናከር በተደረገ ውድድር ተመርጣ ወደ ጃፓን ተጉዛለች። በቆይታዋም ቶኪዮ በሚገኝ የሙዚቃ ት/ቤት የድምጽ ስልጠና በመውሰድ በጃፓንኛ ያቀነቀነች ሲሆን ከዝነኛ የጃፓን ድምጻዊ ጋር በመሆን ዝግጅቷን በተለያዩ ከተሞች ተዘርዋውራ ስታቀርብ ከመቆየቷም በተጨማሪ በጃፓንኛ ነጠላ ዜማ ሰርታለች። ቲቪ አሳሂ በተባለ የቴሌቭዥን ጣቢያም ለአራት ወራት ያህል የተላለፈ አጠቃላይ ጉዞዋን የተመለከተ ሳምንታዊ ፕሮግራም ሰርታለች። “ይህ አጋጣሚ መክሊቴን ፍለጋ ከቆፈርኩባቸው ቦታዎች አንዱና የልጅነት ጀብዱዬ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ሌላ ታላቅ አጋጣሚ ፈጥሮልኝ አልፏል” ትላለች። ይሄውም፡-
ከጃፓን ለአባቷ የምትጽፋቸው ደብዳቤዎች በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ታትመው ሲወጡ የስነጽሁፍ ዝንባሌዋን ያጤኑ የወቅቱ የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበር መስራቾች፥ ለማህበሩ አባልነት አጯት። ወደ ሀገሯ ስትመለስ በማህበሩ ይዘጋጅ በነበረው “ግጥም በማለዳ” የግጥም ንባብ መድረክ ደግሞ ስራዎቿን ለታዳሚ ለማቅረብ ዕድል ብቻ ሳይሆን፤ የመድረክ መሪነት ሙያ የጀመረችበትና ወደ ትወና አለም ለመግባት ዕድል ያገኘችበት ሆኖ ከጥበቡ ማህበረስብ ጋር በማለዳ እንድትተዋወቅ አጋጣሚ ፈጥሮላታል። ግጥሞቿን በበርካታ መድረኮች፣ መገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከማቅረብ ባሻገር በ1999 ዓ.ም “ዙረት” የተሰኘ የግጥም መድበል አሳትማ ለንባብ አብቅታለች። በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ውክልናም የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወጣት ጀግኖች ተሸላሚ በመሆን በወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ከነበሩት ከክቡር ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ እጅ የሜዳሊያ ሽልማት ተቀብላለች።
ሜሮን ከሁለት እስከ አምስት አመታት ያህል በመድረክ ላይ በቆዩ የሙሉ ሰአት ቴአትሮች ላይ በመሪ ተዋናይነት ሰርታለች። እነዚህም
ፍሬሽማን፣ ትሩፋልዲኖ፣ መስተፋቅር፣ ሰማያዊ ዓይን በሃገር ፍቅር ቴአትር፤
እልባት በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ፤
ቅጥልጥል ኮከቦች በብሄራዊ ቴአትር ናቸው። በአንድ ቀን ሁለት የተለያዩ ቴአትሮችን በሁለት ተለያዩ መድረኮች ላይ ለአመታት የተጫወተች ሲሆን በ2ኛው የተስፋ ኢንተርፕራይዝ ሃገር አቀፍ የቴአትር ፌስቲቫል የሴት ኮከብ ተዋናይት ዘርፍ ተሸላሚ ሆናለች። በአሜሪካም በሚኔሶታ ግዛት የፍሪንጅ ቴአትር ፌስቲቫል ላይ ተሳትፋ ኢትዮጲያዊት ገጸ ባህሪ ወክላ በመጫወት የሀገሯን ባህል አስተዋውቃለች።
“የቴሌቭዥን ድራማዎች ከተመልካች ጋር የበለጠ እንድተዋወቅ አድርገውኛል” የምትለው ሜሮን ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2006 ዓ.ም በተከታታይነት በኢትዮጲያ ቴሌቭዥን ሲተላለፉ በቆዩ ገመና አንድ፣ ገመና ሁለትና ዳና በተሰኙ ሳምንታዊ ድራማዎች ላይ ተወዳጅ ገጸ ባህሪያትን ወክላ በመጫወት ትታወቃለች።
አንድ ዕድል፣ ፊደል አዳኝ፣ ኤልዛቤል፣ የእግር ዕጣ፣ ዱካ፣ ይሉኝታ፣ቤተልሄም፣ ሄሎ ኢትዮጵያ፣ ዲፕሎማት፣ ጊዜ ግዙን፣ የተከፈለበት፣ ትራፊኳ እና ድፍረት የተወነችባቸው ፊልሞች ሲሆኑ የተከፈለበት በድርሰት፣ በዝግጅትና በፕሮዲውሰርነት ተሳትፋለች። በዚህም በኢትዮጲያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል የተመልካች ምርጫ ፊልም አሸናፊ እንዲሁም በቤተልሄም ምርጥ ረዳት ሴት ተዋናይት ዘርፍ ተሸላሚ ሆናለች። ከሃገር ወጪም በጀርመን የበርሊን ፊልም ፌስቲቫልና በአሜሪካ የሰንዳንስ ፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ተገኝታ በድፍረት ፊልም “የ2014 መታየት ያለባቸው የተመረጡ ተዋንያን” ዝርዝር ውስጥ ተካታለች።
በሬዲዮ ድራማ የዘመን ችግኞች እና ቀጭን ፍቅር በተሰኙ ተከታታይ ድራማዎች ላይ በትወና፤ ቃና ዜማ የተሰኘ ሳምንታዊ የመዝናኛ ፕሮግራም (ራዲዮ ፋና) በአዘጋጅና አቅራቢነት ለሁለት አመታት ሰርታለች።
የኢትዮጵያ ሚሊኒየም አከባበርን ጨምሮ የበርካታ ሃገራዊና ማህበራዊ ፕሮግራም መድረኮችን በቀጥታ ስርጭቶች ከመምራት በተጨማሪ የኢትዮጲያ አይዶል እና የኢቲቪ የጥያቄና መልስ ውድድሮችን በማቅረብ ለአምስት ዓመታት ያህል ሰርታለች ።
በማህበራዊ ሃላፊነቶችም የበጎ ፈቃድ አምባሳደር በመሆን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ የሰራች ሲሆን
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተመራቂ ሀኪሞች አምባሳደር (ሶስት ዓመታት)፤
የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሲየሽን አምባሳደር (ሁለት ዓመታት)
የቢቢሲ ወርልድ ትረስት የወጣቶች ጤና አምባሳደር (አንድ ዓመት)
የሴቭ ዘ ችልድረን ያለእድሜ ጋብቻና የህጻናት ጤና አምባሳደር በመሆን (አንድ ዓመት) አገልግላለች።
እኤአ በ2010 በአሜሪካ የመጀመሪያው የፕሬዘዳንት ኦባማ የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያ ተወካዮች አንዷ በመሆንም ተሳትፋለች ።
ሜሮን ጌትነት ባለ ትዳርና የሁለት ሴት ልጆች እናት ስትሆን “ቤተሰብ መስርቶ ልጆች ማሳደግ ከሃገራዊና ማህበራዊ ሃላፊነት እኩል ነው” ትላለች። በአሁኑ ወቅት ከምትሰራቸው የማስታወቂያ ስራዎችና ፅሁፎች በተጨማሪ በአዳዲስ የኪነጥበብ ስራዎቿ ለመመለስ በዝግጅት ላይ ትገኛለች።