ማህሌት ሰለሞን

ማህሌት ሰለሞን

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የቴአትር ፤ የፊልም እና የስነ-ጽሁፍ ባለሙያዎችን የህይወት ታሪክ ሲያወጣ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህንን ተግባራችንን በመቀጠል በቴአትር ዘርፍ አስተዋጽኦ እያበረከተች ስላለችው ማህሌት ሰለሞን እነሆ ብለናል፡፡

ትውልድ ፤ እድገትና ትምህርት

ደራሲ ፣ዳይሬክተር ና ተዋናይ እንዲሁም የትያትር መምህርት ወ/ት ማህሌት ሰለሞን መንግስቱ ውልደቷና እድገቷ በተለምዶ 5 ኪሎ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ ነው ፡፡ የቅድመ መደበኛ ትምህርቷን በቤቢላንድ ት/ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በምስካየሃዙናን መድሃኒያለም ገዳም ት/ቤት የተከታተለች ሲሆን በመቀጠልም በቀድሞ መጠሪያው እቴጌ መነን እየተባለ በሚጠራው በየካቲት 12 የ2ኛ ደረጃ ከፍተኛ ት/ቤት ውስጥ አጠናቃለች ፡፡ ማህሌት ከዚያም በአማርኛ ቋንቋ ስነጽሁፍ ጥናት ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ዲፕሎማዋን ያገኘች ሲሆን ከዚያም በመቀጠል ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የትያትር ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከያዘች በኃላ በዚያው በ6 ኪሎ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማስተር ዲግሪዋን በትያትርና ዲቨሎፕመንት ሰርታለች ፡፡

የስራ አለም

ማህሌት የስራ አለምን ስትቀላቀል ስራዋን ሀ ብላ የጀመረችው የመጀመርያ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ በቋንቋ መምህርነት በማገልገል ሲሆን ከዚያም ወደ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ወይንም እንጦጦ ቲቪኢቲ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተዛውራ እጅግ በርካታ ለሆኑ አመታት በመምህርነት በማገልገል ላይ ትገኛለች ፡፡ ማህሌት ከዚሁ የማስተማር ስራዋ ጎን ለጎን የአዲስ አበባ ዩንቨርሰቲን በመቀላቀል የትምህርት ደረጃዋን ለማሻሻል የቻለች ብቻ ሳትሆን በቀድሞው ‹‹የማለዳ ኮኮቦች›› የትወና ክህሎት የኢቢኤስ ቴሌቭዥን ሾውም ላይ በዋና ዳኛነት ለአመታት ያገለገለች መሆኗ ይታወቃል ፡፡ ከዚያም በማስከተል ማህሌት ሰለሞን የፊልም ፕዳክሽን የተባለውን የግሏን ድርጅት መስርታ የኢንተርቴይመንት ኢንዱስትሪውን መቀላቀል ቻለች፡፡ በዚሁ ድርጅቷ አማካኝነትም ቁጥራቸው እጅግ በርካታ የሆኑ ፊልሞች ውስጥ በአዘጋጅነት ፣በደራሲነት በተዋናይነትና የፕሮዲዩሰርነት ሚናዎች ወስዳ ከፍተኛ አስተዋፅኦዋን አበርክታለች ፡፡

የማህሌት ሰለሞን ፊልም ፕሮዳክሽን በአጠቃላይ ከ60 በላይ ፊልሞችን ተከታታይ የቴሌቭዥን ፣የሬዲዮ ድራማዎችን እንዲሁም የመድረክ ተውኔቶችን ለተመልካች ማቅረብ የቻለ እንጋፋ ድርጅት ነው፡፡በዚሁ ድርጅት አማካኝነት ማህሌት ከተሳተፈችባቸው ፊልሞች መካካል

  • ‹‹በቅዳሜና እሁድ›› የተሰኘ 22 ክፍሎች ባለሁለት ምዕራፍ የቴሌቭዥን ተከታታይ ድራማ ፁሁፍ አዘጋጅታ በኢሳት ቴሌቭዥን አቅርባለች፡፡
  • እየየም የተባለ ባለ 6 ክፍሎች አጭር ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ፅፍ በአንተነህ ሰይፉ አዘጋጅነት ለህዝብ እይታ አቅርባለች፡፡
  • በምርጫ ብቻ የተሰኘ ባለ10 ክፍሎች ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማን ፅፍ ና አዘጋጅታ በኢቲቪ እና በዋልታ ቴሌቭዥን አቅርባለች፡፡
  • እንነጋገር የሚል ባለ12 ክፍሎች የሬዲዮ ድራማ ፅፍ ና አዘጋጅታ በአንድ የሬድዮ–ጣቢያ ላይ እንዲተላላፍ አድርጋለች፡፡
  • የዲግሪ ማሟያ ፅሁፏን የሰራችው የፊልም ማስታወቂያዎች ላይ ሲሆን የማስተርስ መመረቂያ ፅሁፏን ደግሞ “theatre as atvet ” ወይም ቴአትር እንደ ቴክኒክ ና ሙያ በሚል ርዕስ ነው፡፡

ሙያን ማሳደግ

በእንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ት/ቤት ለ12 አመታት በመምህርነት አገልግላለች፡፡በተዋናይነት በተለያዩ ፊልሞች ላይ የሰራች ሲሆን ለምሳሌ “አይራቅ፣ልክ እንደኔ…….ወዘተ የሚሉ ፊልምች ተወዳጅነት አትርፎላታልከዚህ በተጨማሪ ማህሌት ሰለሞን በተለያዩ አለምአቀፍ የጥናታዊ ፅሁፍ ጀርናሎች ላይ ከአቶ ለአለም –እና ከሊድስ ዩንቨርሰቲ ፕሮፈሰር ጄን ፓልስትሮው ጋር በጥንድና በጋራ በመሆን ካሳተመቻቸው ጥናታዊ ስራዎች መሃከል

  • Ethiopian and European Influences on Teklehawariat Teklemaryam and His Play Fabula Yawreoch CommediaRreligious , Political and Cultural Dimensions
  • African Theatre Contemporary women
  • Yoftahe Nigusie and Ethiopian Modern Theater

ENN ቴሌቪዥን ላይ ይተላለፍ የነበረ ‹‹ዮጵ›› የሚል የባለተሰጥኦ ውድድር አዘጋጅታ ታቀርብ ነበር፡፡ በኃላም ወደ ናሁ ቲቪ ዞረ፡፡ አሁንም ደግሞ ኢቲቪ መዝናኛ ቻናል በመተላለፍ ላይ ይገኛል ፡፡ ከፊልም በተጨማሪ በኢቢኤስ ቴሌቭዥን ይተላለፍ የነበረውን ‹‹የማለዳ ኮኮቦች›› የተሰኘ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ላይ በዳኝነት አገልግላለች፡፡

ማህሌት ሰለሞን መምህርነቷን እንደምትወደው ትናገራለች፡፡ በዚህም ብዙ ሰው ማብቃት በመቻሏ እንደምትኮራ ትናገራለች ፡፡ በአሁኑ ሰአትም ተዋነይ የፊልም እና የትያትር ስልጠና ተቋም በመክፍት ሰልጣኞችን በብቃት በማሰልጠን ለኢንደስትሪው የበኩሏን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ትገኛለች። የምትወደውን ለሷ በሙያ የምታደንቀው ሰው ስትናገር ‹‹…መዓዛ ብሩን ብሆን ደስ ይለኛል›› ትላለች ፡፡ በመስራቷ የምትደሰትበት የእስካሁን ስራዋን ስትናገር ደግሞ‹‹ በቅዳሜ እና እሁድ›› የተሰኘው ድራማ እንደሆነ ትናገራለች፡፡

ወደፊት በደንብ መስራት ና መሳተፍ የምትፈልግበት ዘርፍ ደግሞ በኢትዮጵያ ፊልም ፖሊሲ ተግባራዊ ሆኖ ሙያውን የሚወዱ ሰዎች እንደፈለጉ በሙያው ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረግ ማስቻልና በሀገራችን ትምህርት ስርአት ውስጥ ቴያትርን ማካተት ምኞቷ እንደ ሆነ ትገልፃለች ፡፡ ማህሌት ሰለሞን ጠንካራ ሰራተኛ መሆኗን የሚያውቋት ሁሉ ይናገራሉ፡፡ በርግጥም ማህሌት እረፍት የለሽ ናት ፡፡ ማህሌት የሰው ልጅ ሁለት ነገሮች ለድርድር ማቅረብ የለበትም ትላለች የመጀመሪያው ነፃነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የአዕምሮ ሰላሙን ለማንም አሳልፎ መስጠትም ሆነ ለድርድር ማቅረብ አይጠበቅበትም ትላለች ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *