ሚስተር ራፋት ሙሳዐድ (1906-1960)

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን የባለሙያዎችን የሕይወት ታሪክ ሰንዶ በማስቀመጥና በማሰራጨት፣ በመፅሐፍ ላይ እንዲታተም በማድረግ የባለሙያዎች አበርክቶ ተዘንግቶ እንዳይቀር የበኩላችን እየተወጣ ይገኛለን፡፡ እስከዛሬ ከ 400 በላይ በሚድያ እና በኪነ ጥበብ ሙያ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ጨምሮ ሌሎችም ታሪካቸው በመረጃ ቋታችን ላይ እንዲቀመጥ አድርገናል፡፡ ስለ እነርሱ ለማወቅ በተፈለገ ጊዜም ፣ታሪካቸው በቀላሉ መገኘት እንዲችል የዲጂታል አማራጮችን በማቅረብ የታሪኰቹ ተደራሽነት ዕውን እንዲሆን ሁሉን አመቻችተናል፡፡

ታሪኮቹ በጥራዝ መልክ ተሠንደው ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑም ቅፅ አንድ እና ቅፅ ሁለት መዝገበ አእምሮን እያንዳንዳቸውን በ600ገፅ አድርገን አዘጋጅተን፣ አሳትመን ፣ አስተዋውቀን እና አስመርቀን ሀገራዊ ኃላፊነታችንን ተወጥተናል፡፡ አሁንም የስነዳ ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን የመማክርት አባላት እንዲሰነዱ ስምምነት የደረሱባቸው ባለሙያዎችን እያፈላለግን መሥራታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

በቅፅ 3 በትምህርት ዘርፍ መዝገበ አእምሮ ላይ የሕይወት ታሪካቸው ከሚሰነድላቸው መካከል ሚስተር ራፍት ሙሳዐድ ናቸው፡፡ ሚስተር ራፋት ፣የዛሬ 56 ዓመት ሕይወታቸው ያለፈ የኢትዮጵያ የትምህርት ባለውለታ ሲሆኑ በትውልድ ግብፃዊ በዜግነት ደግሞ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ ቤርሳቤህ ጌቴ እና ዕዝራ እጅጉ የሕይወት ታሪካቸውን እንደሚከተለው አጠናክረውታል፡፡

ሚስተር ራፋት ለኢትዮጵያ ትምህርት የዋሉት ውለታ

ሚስተር ራፋት ሙሳዐድ በ1906 በግብፅ የተወለዱ ግብፃዊ ሰው ናቸው። በዜግነት ደግሞ ኢትዮጵያዊት አግብተው የኢትዮጵያ ዜግነትን ያገኙ የአገር ባለውለታ ናቸው። ከግብፅ ይልቅ በእንግሊዝ ሀገር ነበር ረዥሙን የትምህርት ቆይታ ያሳለፉት። ጣሊያን ከኢትዮጵያ እንደወጣች በ1934 ዓ.ም በአፄ ኃይለሥላሴ ጥያቄ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በትምህርት ሥርአቱ ውስጥ ለ27 ዓመታት ያገለገሉ ናቸው። የመጀመሪያ የሥራ ጊዜያቸውን በዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት በዳይሬክተርነት የጀመሩት ሚስተር ራፋት በመቀጠል በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ለረዥም አመታት አገልግለዋል። በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ትምህርት ቤት(በኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ) ፣በወሊሶና በአምቦ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣በሰላሌ አበራ አስፋወሰን ትምህርት ቤት እና በአዳማ አፄ ገላውዴዎስ ትምህርት ቤት በተለያየ ጊዜ ትምህርት ቤቶቹን ከማቋቋም ጀምሮ እንግሊዘኛ መምህር በመሆንና በዋናነት በዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
አቶ ንጉሴ አምቦ ለዚህ የሕይወት ታሪክ አዘጋጅ እንደተናገሩት ሚስተር ራፋት ዝምተኛ ግን ተማሪን በሥነ ምግባር የሚያንፁ መምህር ነበሩ ብለዋል፡፡ አቶ ንጉሤ በ 1956 የኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ ሚስተር ራፋትን እንደሚያውቁና ትልቅ ባለውለታ መሆናቸውን መስክረዋል፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ባልነበሩባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤት ማቋቋም ማለት ትልቅ መፍትሔ ነው ለወዳጆችም ለተማሪውም። ለምሳሌ በፍቼ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባልነበረበት ጊዜ ተማሪዎች ስምንተኛ ክፍልን ጨርሰው የዘጠነኛ ብሔራዊ መግቢያ ፈተና ካለፉ በደብረብርሀን ወይም በደብረዘይትና በወሊሶ መሄድ ይጠበቅባቸው ነበር። ይህ ደግሞ በተለይም በእርሻ ሥራ ለሚተዳደሩ ወላጆች አስቸጋሪ ነበርና ትምህርት እስከማቋረጥ ይደርሱ ነበር። በመሆኑም ትምህርት ቤት የማቋቋም ሚና ቀላል አልነበረም።
ሚስተር ራፋት እንዲጀመሩ ያደረጓቸው ትምህርት ቤቶች የወሊሶ፣ የአምቦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤቶችንና የሰላሌ አስፋወሰን ትምህርት ቤትን ሲሆን በዚህ ትምህርት ቤት ለዘጠኝ አመታት ሲያገለግሉ፤ በተማሪዎቻቸውና በትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ዘንድ የነበራቸው አክብሮትና ፍቅር በእጅጉ ከፍ ያለ ነበር። ከወቅቱ ተማሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት መጋቢ መርዕድ ለማ  እንዲህ ይገልጿቸዋል።

“በወቅቱ የትምህርት ቤታችን ዳይሬክተር የነበሩት የግብፅ ተወላጁ ሚስተር ራፋት ሙሳዐድ ጠንካራ የትምህርት ቤት አስተዳዳሪ የነበሩ በተማሪውና በቀሪው የትምህርት ቤት ማህበረሰብ ዘንድ ታዋቂና ተወዳጅነት ያተረፉ አንጋፋ ሰው ናቸው።ተማሪዎች ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት ጀምሮ በት/ቤቱ ቅጥርግቢ እንድንገኝ ይጠበቅብን ነበርና ከነበረው ጥብቅ ሥርዐት የተነሳ በተለያየ ምክንያት ያረፈድን እንደሆነ ሚስተር ራፋት አንበርክከው ይቀጡን ነበር። ” ብለው ለህግና ሥርዐት ያላቸውን ቁርጠኝነት መስክረውላቸዋል። መጋቢ መርዕድ “የተጠራ ህይወት” በተሰኘው መፅሀፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት “በጣም የሚገርመኝ ራፋት ሙሳዐድ በመቅጣትም ጭምር የሚታወቁ መምህር ቢሆኑም እንኳን እጅግ እናከብራቸውና እንወዳቸው ነበር። ታዲያ አንድ ወቅት ከትምህርት ሚኒስቴር በተፃፈ ደብዳቤ ዝውውር አግኝተው ናዝሬት ወደሚገኘው ዐፄ ገላውዴዎስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሆነው እንዲሄዱ መወሰኑን በሰንደቅ ዓላማ ሠልፍ ላይ ተሰማ።እጅግም ልባችን አዘነ” ተማሪው ለሚስተር ራፋት የነበረው አክብሮትና ፍቅር በእጅጉ ከፍ ያለ ስለነበር  የሰሙት ነገር ልባቸውን ሰበረ። እንዳዘኑም አልቀሩ ቅሬታቸውን ይዘው በአፄ ኃይለሥላሴ ፊት ቀረቡ። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለባለስልጣን ቀብር ደብረሊባኖስ ገዳም መሄዳቸውን የሰሙት ተማሪዎች ቅሬታቸውን ለማቅረብ ከፍቼ ተነስተው በእግራቸው ሀያ ኪሎሜትር ተጉዘው ጫገል በምትባል የደብረሊባኖስ መገንጠያ ጋር የምትገኝ ስፍራ ደረሱ። ጃንሆይ አይተው እንዳያልፏቸው የኢትዮጵያን ሰንደቅ  ዐላማ ይዘው ነበር የቆሙት። በዚህ መንገድ ለንጉሱ ስሞታቸውን በማቅረብ ሚስተር ራፋት ከአበራ አስፋውወሰን ትምህርት ቤት እንዳይነሱ ለመጠየቅ የበቁት ምን ያህሉን የተወደዱ ለመሆናቸው አንዱ ምስክር የሚሆን ነው።

ቀዳማዊ ኃይለስላሴም የተማሪዎቹን ቅሬታ አንድ ሰው መጥቶ ያስረዳኝ በማለታቸው አንደበተ ርቱዕ የነበረው የቄስአምባ ወጣት ተመርጦ በንጉሱ ፊት ቀረበ። “ግርማዊ ሆይ! እኛ ከሥላሴ አውራጃ ከአበራአስፋወሰን ትምህርት ቤት የመጣን ተማሪዎች ነን።ተወዳጅ የሆኑት ዳይሬክተራችን ሚስተር ራፋት ሊወድቅ የተቃረበውን ትምህርት ቤታችንን እያሳደሱልን ሳሉ በድንገት ተቀይረው ሊሄዱብን ስለሆነ እንዳይሄዱብን ለእርስዎ ለጃንሆይ አቤት ለማለት ነው የመጣነው” ሲሉ የተማሪውን ስሞታ ሲያሰማ ንጉሱም ” ትምህርት ቤታችሁ ይታደስላችኋል ዳይሬክተራችሁም አይቀየሩባችሁም። አሁን እናንተ ወደ ትምህርትቤታችሁ ሂዱ ብለው ተስፋ ሰጥተውን ለተማሪዎቹ አንድ አንድ ፓኬት ብስኩትና አንድ ብር ሰጥተው አሰናበቱን። ይሔ ዜና ሲሰማም እንደ ፅልመት ጠፍቶ የነበረው ተስፋችን ቦግ ብሎ ሲበራ ታየን።” ሲሉ የተጠራ ህይወት በተሰኘው መፅሀፋቸው ላይ አስፍረዋል።

ተፈጸመ ነገሩ ተፈጸመ፤ አሃሃ!!
ተፈጸመ ነገሩ ተፈጸመ
ደስ ይበልህ ተማሪ ደስ ይበልህ፤አሃሃ
ደስ ይበልህ ተማሪ ደስ ይበልህ … እያሉ እያዜሙም ወደ መጡበት ተመለሱ። ፍቼ በተማሪ ጭፈራ ደመቀች። ንጉሱ ተማሪውን ለማረጋጋት ያህል በዚህ ቃል ቢሸኟቸውም የሚስተር ራፋት ወደ አፄ ገላውዴዎስ መዛወር አይቀሬ ነበረና በአንዱ ፀሀያማ ጠዋት ትላልቅ እንግዶች በተገኙበት በሰንደቅ ዓላማ ሰልፍ ላይ ሚስተር ራፋት ንግግር አድርገው ሽኝቱ ተከናወነ።

ሚስተር ራፋት ከሰላሌ ፍቼ (አበራ አስፋወሰን ትምህርት ቤት) በኋላ በ1955 በአዳማ አፄ ገላውዴዎስ ትምህርት ቤት በመዛወር ለአምስት አመታት አገልግለዋል።
ከወይዘሮ የሺመቤት አበበ ጋር ትዳር በመመስረት ሰባት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን ከመጀመሪያ ልጃቸው እዝራ ራፋት ጀምሮ በቅደም ተከተል አሊስ፣ኤልሳቤጥ፣ሰሎሞን፣ዮሀንስ፣ዮሴፍና ማርቆስ የተሰኙ ልጆችን ነው ያፈሩት።
ሚስተር ራፋት ሙሳዐድ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርአት ውስጥ በቀናነትና በታማኝነት ያገለገሉ ፣ ትውልድ በማፍራት ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የሀገር ባለውለታ ሲሆኑ በሐምሌ 1/1960 ዓ.ም ከዚህ አለም ድካም አርፈዋል።የእርሳቸው ሕይወት ያለፈበትን 57ኛ ዓመት አስመልክቶም ይህን የሕይወት ታሪካቸውን በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች ዛሬ ሐምሌ 24 2017 ዓ.ም ሰንደነዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *