መዓዛ ወርቁ ብርሃኑ


ጸሐፊ ተውኔት እና ዳይሬክተር


መዓዛ ወርቁ በመድረክ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን እና በህትመት ድራማ(comic-book) ድርሰት እና ዝግጅት ስራዎቿ በሀገር ውስጥ እና በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ በስፋት ትታወቃለች፡፡ በ1992ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቴአትር ጥበባት ሙያ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች፡፡ ስዊድን ሀገር ከሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦፍ ዌስት በ1998ዓ.ም በኢንተርካልቸራል አደልት ፔዳጎጂ ዲፕሎማዋን ሰርታለች፡፡ መዓዛ የኪነጥበብ ሙያ ስራን “ሀ” ብላ የተቀላቀለችው በትወና ይሁን እንጂ በአቀራረባቸውም ሆነ በይዘታቸው ከተለምዶው ወጣ ባሉ በሰው ልጆች ፍትሃዊነት፣ ሰብዓዊነት እና በአየር ንብረት ጥበቃ ላይ ትኩረታቸውን ባደረጉ የድርሰት እና የዝግጅት ስራዎቿ ጎላ ብላ ትጠቀሳለች፡፡


ትወና


መዓዛ የቴአትር ጥበባት ትምህርቷን እንደጨረሰች በባህርዳር ሙሉዓለም የባህል ማዕከል ተቀጥራ በ1993ዓ.ም ‹ባህር ማዶ› የተሰኘ በአቦነህ አሻግሬ ተፅፎ በአቢቹ ኃ/ማሪያም የተዘጋጀ የሙሉ ጊዜ ተውኔት ላይ ተውናለች፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ቴአትር ተቋም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ማህበር በነበረው የመኩሪያ ቴአትር ስቱዲዮ እና መዝናኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በቀረቡ ‹ጠለፋ› (60 መድረኮች በ1996ዓ.ም) እና ‹ባየ በሰማ› (20 መድረኮች በ1998ዓ.ም) አሳታፊ ተውኔቶች ላይ በትወና ሰርታለች፡፡ The Inspector General የኒኮላይ ጎጎል ተውኔት ሰለሞን ጋሻው ‹የፌደራሉ ገምጋሚ› በሚል ርዕስ ወደአማርኛ ተርጉሞ ባዘጋጀው ተውኔት ላይም በ2000ዓ.ም ለ8 ወራት በአዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽ መድረክ ላይ ተውናለች፡፡


ድርሰት እና ዝግጅት


‹ፎዚያ›(1994ዓ.ም) በፕሮዳክሽን ማናጀርነት ወደ ቴሌቪዥን ድራማ የተቀላቀለችበት 6 ክፍል ምጥን ድራማ ነው፡፡ አቋራጩ (በ1995ዓ.ም) 4 ክፍል ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በዝግጅት፣ ‹የቅርብ ሩቅ› በ1995ዓ.ም በሜጋ ኪነጥበባት ማእከል የተሰራ ባለ 2 ክፍል ድራማ ፅፋለች፡፡ በተለያዩ የሬዲዮ ጣቢያዎች የተላለፉ ከ20 በላይ አጫጭር የሬዲዮ የድራማዎችን ፅፋ አዘጋጅታለች፡፡
‹ዝነኞቹ› በ2004ዓ.ም በአዲስ አበባ ትያትርና ባህል አዳራሽ የቀረበ የመድረክ ተውኔት ስራዋ ነው፡፡ በ2004ዓ.ም ሁለተኛ የመድረክ ተውኔቷ በእንግሊዝኛ ቋንቋ Desperate to Fight በሚል ርእስ ፅፋ በሰንዳንስ ኢንስቲትዩት የምስራቅ አፍሪካ ቲያትር ፕሮግራም አማካኝነት ኬኒያ ማንዳ ደሴት ላይ በኬኒያ እና ዩጋንዳ ተዋንያን በአሜሪካው ዳይሬክተር ፊሊፕ ሂምበርግ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ይሄው ቲያትር በ2005ዓ.ም በኒውዮርክ ባርሺንኮቭ ቲያትር በአሜሪካውያን ተሰርቶ ለተመልካች ቀርቧል፡፡ በዚያው በ2005ዓ.ም በስዊድን ሀገር በአለምአቀፍ የሴት ፀሀፊ ተውኔቶች ኮንፍረንስ ላይ በንባብ ክዋኔ በስዊድናዊያን ተሰርቶ ስቶክሆልም ከተማ ላይ ቀርቧል፡፡ Desperate to Fight 2005ዓ.ም በኬኒያ ብሔራዊ ሚዩዚየም በክዋኒ ፌስቲቫል ላይ በኬኒያዊያን ተሰርቶ ለእይታ ቀርቧል፡፡ መዓዛ በ2007ዓ.ም ይሄንኑ ቲያትር ‹ከሰላምታ ጋር› በሚል ወደአማርኛ ተርጉማ እና አዘጋጅታ በጃዝአምባ/ጣይቱ ሆቴል/ እና በአፍሪካን ጃዝ ቪሌጅ /ጊዮን ሆቴል/ ለሁለት አመታት ለተመልካች አቅርባው ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡ በ2007ዓ.ም Desperate to Fight በዩጋንዳ ብሄራዊ ቴአትር በካምፓላ ኢንተርናሽናል ቲያትር ፌስቲቫል አማካኝነት ተሰርቶ ለተመልካች ቀርቧል፡፡ ይሄው የዩጋንዳ ፕሮዳክሽን ሩዋንዳ(2009ዓ.ም) እና ብሩንዲ(2010ዓ.ም) ለተመልካች ቀርቧል፡፡ Desperate to Fight በጀርመን ቋንቋ በቲያትራላይዝ ዶት ካምፓኒ ተተርጉሟል፡፡ በ2015ዓ.ም በአረብኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለካይሮ አለምአቀፍ የሙከራዊ የቴአትር ፌስቲቫል በግብጽ ባህል ማእከል ታትሞ ለንባብ በቅቷል፡፡ በሚሺጋን ዩኒቨርስቲ አሳታሚነት ከሌሎች 7 አፍሪካውያን ፀሀፊ ተውኔቶች ስራዎች Speaking Our Selves፡ New Plays by African women በሚል መፅሀፍ ታትሞ ከየካቲት 2017ዓ.ም አንስቶ ለንባብ ቀርቧል፡፡ በ2013ዓ.ም በጽሁፍ እና ዝግጅት ያቀናበረችው ‹ሼክስፒር ኢትዮጵያዊ ነው!› ተውኔት ለቲያትር 100ኛ አመት አከባበር በሸራተን አዲስ ሆቴል ታይቷል፡፡ መዓዛ በ2017ዓ.ም የፃፈችውን ‹እመጌቶች› የተሰኘ ተውኔት ከተለመደው ቴአትር ማሳያ ወጣ በማለት በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ፍንድቃ ባህል ማዕከል አዘጋጅታ አቅርባለች፡፡
መዓዛ ወርቁ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የፃፈቻቸው አጫጭር ተውኔቶች በአለምአቀፍ መድረኮች ላይ ቀርበውላታል፡፡ CrossRoads(2010 ዓ.ም) እና By the River(2012ዓ.ም) በክላይሜት ቼንጅ ፎር ቲያትር አክሽን ተተርጉመዋል፤ ተከውነዋል፤ ታትመዋል፡፡ By the River የተሰኘው ተውኔት Lighting the Way: An Anthology of Short Plays about the Climate Crisis(2013ዓ.ም) መፅሀፍ ስብስብ ውስጥ ተካቷል፡፡ ይሄው ተውኔት በጣሊያንኛ ቋንቋ ተተርጉሞ በኤሚሊያ ሮማ ቲያትር ፋውንዴሽን በ “Planet B Project” ሁነት በቼሴና፣ ቦሎኛ እና ሞዴና የጣሊያን ከተሞች በ2014ዓ.ም ታይቷል፡፡
መዓዛ ወርቁ በኢትዮጵያ ከሰራቻቸው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ስራዎች መካከል ‹አላውቅም አናውቅም› በ2017ዓ.ም በዴኤስቲቪ አቦል ቴሌቪዥን በ13 ክፍል የቀረበ ድርሰትና ዝግጅት አንዱ ነው፡፡ በ2017ዓ.ም በገርል ኢፌክት ኢትዮጵያ ተሰርቶ በአባይ ቴሌቪዥን በ16 ክፍል የተላለፈ‹የኛ› ድራማ ምእራፍ 6 መሪ ፀሀፊ እና የቅድመዝግጅት አማካሪ ሆና ሰርታለች፡፡ ደርሶ መልስ ተከታታይ የቴሌቪዠን ድራማ በ44 ክፍሎች በፋና ቴሌቪዥን የተላለፈ(2009-2012ዓ.ም) ተወዳጅ ስራዋ ነው፡፡ ‹አለሁ› በ16 ክፍሎች በ2012ዓ.ም በፋና ቴሌቪዥን የተላለፈ ሌላው ድራማ ነው፡፡ በተጨማሪም ዶክመንተሪዎች እና ማስታወቂያዎች ሰርታለች፡፡
ከመዓዛ ተከታታይ የሬዲዮ ድራማዎች መካከል ‹አልጋ በአልጋ› ባለ34 ክፍል 2002ዓ.ም ፣ ‹ህይወት መሰናዶ› ባለ24 ክፍል በ2003ዓ.ም እንዲሁም ‹ወፌ ቆመች› ባለ 40 ክፍል በ2008ዓ.ም በሸገር ኤፍኤም 102.1 ሬዲዮ የተላለፉ ስራዎቿ ናቸው፡፡ ‹ሰፈረ ፅዱ› ባለ 26 ክፍል የሬዲዮ ድራማ በ2009ዓ.ም እና ‹እርካብ› 24 ክፍሎች በ2010ዓ.ም በ5 የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ተተርጉመው በክልል የሬዲዮ ጣቢያዎች ተላልፈዋል፡፡ ከቢቢሲ ሚዲያ አክሽን ጋር በመተባበር የሰራችው ‹ንጋት› ባለ 12 ክፍል ድራማ ድርሰት እና ዝግጅት በ2014ዓ.ም ለአድማጭ ደርሷል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በቃና ታሌቪዥን በወር አንድ ጊዜ በመተላለፍ ላይ በሚገኘው ‹ዛሬን ከቃና› ፕሮግራም ላይ ‹በአንድ ዲንጋይ ሶስት ወፍ› ያለችውን ባለአንድ ሰው ተውኔት ለቴሌቪዥን እና ዲጂታል ሚዲያ ፅፋ በማዘጋጀት ላይ ትገኛለች፡፡


ጋዜጠኝነት


በ1995ዓ.ም የጋዜጠኝነት አጭር ስልጠና ወስዳ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፤ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ እና አቅራቢ ሆና ተቀጥራለች፡፡ በፋና ሬዲዮ የሳምንታዊ ድራማ ዝግጅት፣ ጥበባት አለም፣ የቋንቋ ለዛ፣ የአርብ መዝናኛ፣ የእሁድ ወጣቶች መዝናኛ እንዲሁም የእሁድ ዳሰሳ ፕሮግራም አዘጋጅ ሆና ሰርታለች፡፡ ፋና የጋዜጠኝነት ሀሁ ያወቅኩበትና የተማርኩበት ነው የምትለው መዓዛ ከ2000ዓ.ም ጀምሮ ሸገር ኤፍኤም 102.1 ሬዲዮ እንደተከፈተ ከጋዜጠኛ እማዋይሽ ዘውዱ ጋር በመሆን ‹አዲስ ሐበሻ› የተሰኘ የሴቶች የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ለ3 ዓመታት ሰርታለች፡፡ በ2003ዓ.ም ‹ሴት ናት› በሚል ርዕስ በ20 ሳምንታት በተደመጠው የሬዲዮ ፕሮግራም ላይም ሸገር ሬዲዮ ጋር በመተባበር አዘጋጅታ አቅርባለች፡፡
መምህርነት
መዓዛ በ2005ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል በትርፍ ሰዓት መምህርነት አገልግላለች፡፡


ተቋማት


መዓዛ መጀመሪያ በቅጥር ለ 7 ወራት ያገለገለችበት ተቋም ባህር ዳር የሚገኘው የሙሉአለም ባህል ማዕከል ነው፡፡ በሜጋ ኪነጥበባት ማዕከል ለሁለት አመታት(ከ1993- 1995ዓ.ም) በቴሌቪዥን ድራማ ጽሁፍ፣ ዝግጅት እና ማስተባበር ሰርታለች፡፡ በፋና ሬዲዮ ለ10 ወራት በአዘጋጅ መደብ ሰርታለች፡፡ ለ4 ዓመታት የምስራቅ አፍሪካ ቲያትር ተቋም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ማህበር የሆነው መኩሪያ ቴአትር ስቱዲዮ እና መዝናኛ ድራማቱል /Dramatool/ የተሰኘ የክዋኔ ጥበብ ባለሞያዎችን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አማካኝነት በሚያገናኘው ፕሮጀክት አስተባባሪ/co-ordinator/ ነበረች፡፡ ትኩረቱን ክዋኔ ጥበብ ላይ ባደረገው ‹መኩሪያ ቴአትር› በአማርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋ በየ3 ወሩ ይታተም የነበረው መጽሄት አዘጋጅ እና ፀሀፊም ሆና ሰርታለች፡፡


በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የኤድስ መረጃ ማእከል ማርች ፕሮጀክት ይታተሙ በነበሩ ‹ተወርዋሪ ከዋክብት›(ለፌደራል ፓሊስ አባላት)፣‹ጥቋቁር ነብሮች›(ለመከላከያ ሰራዊት አባላት) እና Life 101 (ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች) በሚዘጋጁት ተከታታይ ህትመት ድራማዎች/Comic Books/ ስክሪፕት ፅሁፍና የፈጠራ ድጋፍ በመስጠት 3ዓመታት(ከ2003 – 2007ዓ.ም) ሰርታለች፡፡ በጆንሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ኮምንኬሽን ፎር ሄልዝ ፕሮጀክት ላይም ‹እርካብ› ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ መሪ ፀሀፊ (head writer) እና የኮምኒኬሽን ውጤቶች ይዘት አማካሪ ሆና ከ2009- 2011ዓ.ም ሰርታለች፡፡


ሁነትና አመራር


መዓዛ የሰንዳንስ አሊሙናይ ከኢትዮጵያ ቴአትር ባለሞያዎች ማህበር ጋር በመተባበር ባዘጋጁት ወሰንን መሻገር አለምአቀፍ የክዋኔ ጥበብ ፌስቲቫል እና ኮንፍረንስ /Crossing Boundaries International Performing Arts Festival and Conference በፕሮግራም ዳይሬክተርነት ሁነቱን መርታለች፡፡ 11 ሀገራት የተሳተፉበት እና በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 6/ስድስት/ ልዩ ልዩ መድረኮች ላይ በተካሄደው ፌስቲቫል ላይ ሁነት በማቀድ፣ አለምአቀፍ ተሳታፊዎችን በመለየት እና በግንኙነት እንዲሁም በህትመት፣ ዶክዩመንተሪ ስራና እና የማስተዋወቂያ ስራዎች ይዘት ስራ ተሰርታለች፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በ2014 ዓ.ም እና በ2015 ዓ.ም ለተከታታይ ሁለት አመታት ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በማስጀመር እና በማዘጋጀት ሰርታለች፡፡ አዲስ አበባ፣ ሃዋሳ፣ አዳማ፣ ጂግጂጋ እና ባህርዳር ከተሞች ላይ በተካሄዱት ፌስቲቫሎች ፊልሞችን ከማሰራት አንስቶ የሁነት ቦታ እና የፕሮሞሽን ይዘት እና አይነት በመምራት የተሳካ ፌስቲቫል አካሂዳለች፡፡
ከኮቪድ-19 መምጣት በኋላ የተቀዛቀዘውን የቴአትር ጥበብ ለማነቃቃት በ2013ዓ.ም የተሰባሰበ ‹ስለቲያትር› የሙያተኞች ንቅናቄ መርታለች፡፡ የቲያትር 100ኛ አመት የሚያከብር መክፈቻ ዝግጅት በሸራተን አዲስ፣ የሚዲያ እና የባለሞያዎች ውይይት፣ እንዲሁም 43 የቴአትር ስራዎች የቀረቡበት ሀገር አቀፍ ፌስቲቫል በማዘጋጀት እና በመምራት ትታወቃለች፡፡ ስለቲያትር የቴአትር ሶሳይቲ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ሆኖ ከተመሰረተ 2014ዓ.ም ወዲህ የቦርድ ሰብሳቢ ሆና በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
መዓዛ ስራዎቿን ለተደራሲ የምታመርትበት ተቋም መዓዛ ፊልም ፕሮዳክሽን ኤንድ አርት ኮንሰልታንሲ መስራች እና ባለቤት ናት ፡፡


ሽልማት


መዓዛ ወርቁ በ2010 ዓ.ም በሙያዋ ላበረከተችው አስተዋጽኦ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ‹ሁለገብ ከያኒ› በሚል የእውቅና ሰርተፍኬት እና ዋንጫ ሰጥቷታል፡፡ በ2012ዓ.ም ‹ደርሶ መልስ› በተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ስራዋ በ10ኛው ለዛ አዋርድ ምርጥ በምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም የተመልካች ምርጫ ሽልማት አግኝታለች፡፡


ውልደት ፣ እድገት እና ቤተሰብ


መዓዛ ወርቁ የተወለደችው በታህሳስ 3 ቀን 1970ዓ.ም በአስመራ ከተማ ቲራቮሎ አካባቢ በሚገኘው አሜሪካ በ1943እ.አ.አ ለወታደራዊ ሬዲዮ ጣቢያ በገነባችው በኋላም የኢትዮጵያ ወታደሮች ካምፕ በነበረው ቃኘው ስቴሽን ነው፡፡ መዓዛ የአንድ ወር አራስ ሳለች ወላጆቿ በስራ ዝውውር ምክንያት ጠቅለልው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ መኖሪያቸውን አደረጉ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በጥበብ እድገት፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በኢትዮጵያ ትቅደም ቁ.1 ትምህርት ቤት ተምራለች፡፡ በትምህርት ጎበዝ ከሚባሉት ተማሪዎች ቀዳሚ የሆነቸው መዓዛ የዩኒቨርስቲ ነጥብ በማምጣት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ከተቀላቀለች በኋላ በልዩነት እየሰራችበት የምትገኘውን የቴአትር ጥበብ ትምህርት ተምራለች፡፡
መዓዛ የአማርኛ እና የታሪክ መምህራኖቿ ለተሰማራችበት ሙያ ተጽእኖ እንዳላቸው ብትናገርም፤ ለአስተሳሰቧ፣ ለማንነቷ እና ለሙያ ህይወቷ መሰረት የጣሉት አባቷ የመቶ አለቃ ወርቁ ብርሃኑ መሆናቸውን አጠንክራ ትገልጻለች፡፡ በ7ዓመት እድሜዋ ሀገር ፍቅር ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ ከነበረው ‹ፅናት› ቲያትር ጋር ያስተዋወቋት አባቷ ገና 10 ዓመት ሳይሞላት በሁሉም ቲያትር ቤቶች መድረኮች ላይ የነበሩ ትርዒቶችን አሳይተዋታል፡፡ ‹ነቃሽ› በአዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽ፣ ‹የዋርካው ስር ምኞት› በራስ ቴአትር እንዲሁም የተለያዩ የበኣል የሙዚቃ ዝግጅቶችን በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ታድማለች፡፡ መዓዛ ከንባብ እና መገናኛ ብዙኋን ጋር ቅርበት እንዲኖራት፣ ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ ድፍረት ልምምድ እንዲኖራት የተቃኘቸው በአባቷ ነው፡፡ በልጅነቷ የነበራትን የስዕል ዝንባሌዋ አድናቂ እና ደጋፊ ነበሩ፡፡ የጽሁፍ ልምምድ የጀመረቸውም በ1983ዓ.ም በነበረው የመንግስት ለውጥ አባቷ በተሀድሶ ቆይታ ላይ በነበሩ ጊዜ ለአባቷ በፃፈቻቸው ተከታታይ እና ረዣዥም ደብዳቤዎች እንደሆነ ታስታውሳለች፡፡ ደብዳቤዎቿ የነበረውን ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ በሳቅ እያዋዛች በመተረክ ትፅፈው ስለነበር በጦላይ ማሰልጠኛ በነበሩ የአባቷ ጓደኞች ዘንድ በጉጉት ይጠበቁ እና ይነበቡ ነበር፡፡ ከአደገች በኋላ መዓዛ ከድርሰት ስራዎቿ ውጪ ለወዳጅ ጓደኞቿ በምትፅፋቸው ዘለግ ያሉ አዝናኝ ደብዳቤዎች ትወደዳለች፡፡ በልጅነት የሰዎችን አረማመድ እና አነጋገር በማስመሰል የተለያየ ገጸባህሪ በመላበስ ጎረቤቶችን ስታነጋገር ባገኘችው ቀና ምላሽ ለምናብ ልምምድ የሚያግዝ ሰፈር ውስጥ እንዳደገች ትመሰክራለች፡፡


መዓዛ ከ1995ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 21 ዓመታት ከሙያ እና የህይወት አጋሯ ፕሮዲዩሰር ዘካሪያስ ካሱ ጋር በፍቅር እና በትዳር እየኖረች ትገኛለች፡፡ ሉሊያ እና ባሮክ ዘካሪያስ የተሰኙ አንድ ሴት እና አንድ ወንድ ልጆችንም አፍርተዋል፡፡
መዓዛ ወርቁን በሁሉም የማህበራዊ ትስስር ገፆች እንዲሁም በlemeazaworku@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *