ሐይማኖት ዘለቀ

አዲሷ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሐይማኖት ዘለቀ ወርቅነህ ማናቸው?

           (ከዕዝራ እጅጉ)

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣ መዝገበ-አእምሮ ( የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች ፣በመፅሀፍ፣በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል።በተለይ ጉግል ላይ ታሪካቸው ሲፈለግ የማይገኝ ሰዎች አሁን የሙያ አበርክቷቸው በቀላሉ ኢንተርኔት ላይ በግልፅ ተቀምጦ ይገኛል። ባለፉት 4 ዓመት ከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መፅሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።

ከእነዚህ ውስጥ የሚድያ ሰዎችና የቴአትር ባለሙያዎች ይገኙበታል። አጠቃላይ 74 ከፍተኛ የሚድያ አመራሮች፣ 50 በላይ የፊልምና የቴአትር ባለሙያዎች ፣ሚኒስትሮች ፣ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የግል ሚድያ መሥራቾች፣ዋና አዘጋጆች እና መካከለኛ አመራሮች ተካተዋል። 35 ያህሉ በዋና ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ያሉ ሲሆን የሁሉም ታሪክ በተሟላ ደረጃ ለመሰነድ ተችሏል። የእነዚህን አመራሮች እና የሚድያ ሰዎች ታሪክ ሰንዶ ለአንባቢ ተደራሽ ማድረግ ፈታኝ ቢሆንም አሳክተነዋል። በዚህ ተግባራችንም ተጠናክረን እንቀጥላለን።

በዚህ ፅሑፍ የሙያ ታሪካቸው የሚሰነድላቸው በሚድያው ዐለም 27 ዓመት የሠሩትና በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በመሆን በፓርላማ የተሾሙት ወይዘሮ ሐይማኖት ዘለቀ ናቸው።

ወይዘሮ ሐይማኖት፣ ከዜና አገልግሎት እስከ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊነት የሠሩ ባለሙያ ናቸው።ዕዝራ እጅጉ የሙያ ታሪካቸውን እንደሚከተለው አጠናክሮታል።

ወይዘሮ ሐይማኖት በሚድያው ዘርፍ ከ20 ዓመት በላይ የዘለቁ ባለሙያ ሲሆኑ በህዝብ ግንኙነት እና በጋዜጠኝነት የራሳቸውን አሻራ ለማስቀመጥ የሞከሩ ባለሙያ ናቸው። እርሳቸው ከሪፖርተርነት እስከ ጀነራል ዳይሬክተርነት በመድረስ በሁሉም የሥራ እርከኖች ያለፉና የሥራ ብቃታቸውም የተመሰከረላቸው ናቸው። አገርአቀፍ የሆኑ የኮምዩኒኬሽን ስትራቴጂዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ የሚነገርላቸው ወይዘሮ ሀይማኖት ዘለቀ ይህን ጥረታቸውንም አጠናክረው ቀጥለውበታል።

የትምህርት ሁኔታ

ወይዘሮሐይማኖት፣በሶሲዮሎጂ( ማህበረሰብ ጥናት) ከኢንድራ ጋንዲ ናሽናል ኦፕን ዩኒቨርሲቲ በሰኔ 2009 እኤአ ማስተርሳቸውን ማጠናቀቅ ችለዋል።
ቀደም ብለውም በ1992 እንደ ኢትዮጵያ ቀመር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋዎችና ሥነ -ፅሑፍ ቢኤ ዲግሪ መያዝ ችለዋል።

   ወደ ሥራ ዓለም

ወይዘሮ ሐይማኖት፣ የሥራ ዓለምን የተቀላቀሉት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን በ1991 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ሲሆን እዚያም በአዲስ አበባ ዴስክ ማኔጅመንት በሪፖርተር መደብ ዜና በማሰባሰብ አቅማቸውን አሳይተዋል።2 ዓመት በሪፖርተርነት ካገለገሉ በኃላም በ1993 በከፍተኛ ሪፖርተርነት መደብ የፕሮጀክት ዜናዎችን በማቀድና አገራዊ የሚመጥኑ ዜናዎችን ፅፎ በመሥራት ለዜና ያላቸው ክህሎት እምን ድረስ እንደሆነ አሳይተዋል።

       የሥራ ዕድገት

ወይዘሮ ሐይማኖት ፣ ለሥራ ያሳዩት ትጋት ግምት ውስጥ ገብቶ ወደ ረዳት አዘጋጅ መደብ ያደጉ ሲሆን በ1995 ዓ.ም በዚህ ኃላፊነት ዜናዎችን በመሥራት፣ኤዲት በማድረግ፣ ለዜና የሚሆኑ እቅዶችን ለይቶ በማውጣት፣ በቂ ገለፃ ለአዳዲስ ባለሙያዎች በመስጠት አቅጣጫ እንዲያገኙ እስከ የካቲት 1998 ዓ.ም ቆይተዋል።

    እንደ ኤዲተር

ወይዘሮ ሐይማኖት ፣በዚያው በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የነበራቸውን አቅም አጠናክረው ሙሉ ኤዲተር ሆነው ዜና እየሠሩም የሌሎች ሪፖርተሮችን ሥራ እያቃኑም፣ ተገቢውን የመምራት ሥራ እያከናወኑ አንድ ዓመት ዘልቀዋል።

 ወደ አዲስ መሥሪያ ቤት

ወይዘሮ ሐይማኖት በ1999 ሐምሌ ወር ላይ የኮምዩኒኬሽን ሚኒስቴርን በመቀላቀል የሬድዮና የቲቪ ቡድን መሪ በመሆን ለ 2 ዓመት አገልግለዋል። በዚህ መሥሪያ ቤት ሳሉም የኮምዩኒኬሽን ምርምሮችን በመሥራትና በማስተባበር ይሠሩ ነበር። በተለይ በስክሪፕት ፅሑፍና ዳይሬክቲንግ፣ በኤዲቲንግ እና በዶክመንተሪ እና በቲቪ ፕሮዳክሽን ተግባራት የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ ተልዕኮ በአግባቡ መወጣት ችለዋል።

ዕድገት ወደ ጀነራል ዳይሬክተርነት

በ2001 መጋቢት 10 ወይዘሮ ሐይማኖት ዘለቀ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳይ ጀነራል ዳይሬክተር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን በተለይም የኮምዩኒኬሽን ስትራቴጂዎች በመንደፍ የጎላ አሻራ ማኖራቸው በስፋት ይነገርላቸዋል። ለዓለም አቀፍ እና ለአገር ውስጥ ሚድያ ቪድዮዎች፣ፖስተርና ብሮሹሮች፣ የህትመት ውጤቶችን በማዘጋጀት የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ አደራ መወጣት ችለዋል።

ወይዘሮ ሐይማኖት በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ፣ ፕሮጀክት ፕሮፖዛሎችን በመንደፍ ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግም የጎላ ድርሻ ነበራቸው። በሚድያው ዘርፍ የምኒተሪንግ እና የግምገማ ተግባራትንም ሲያከናውኑ ሌሎች ባለሙያዎችንም መርተው የሚድያ እና የኮምዩኒኬሽን ሥራን የበለጠ ሙያዊ ለማድረግ የተቻላቸውን አድርገዋል። በእርሳቸው ክፍል አስተባባሪነት የሚደረጉ የሁነት መርሀ- ግብሮች በተሟላ ብቃት እንዲከናወኑም የመሪነት አቅጣጫ አስቀምጠዋል። ወይዘሮ ሐይማኖት በኮምዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት እስከ ህዳር 2008 አጠቃላይ ለ 6 ዓመት ማገልገል ችለዋል።

    ወደ ኢቢሲ

በ2008 ህዳር ላይ ወደ ኢቢሲ በመምጣት የኦንላይን እና ሞኒተሪንግ ዲፓርትመንት በመግባት ለ8 ወራት አገልግሎት ሰጥተዋል። ኢቢሲ ሳሉም በትርጉም፣እና በአለም አቀፍ የሞኒተሪንግ ሥራዎች ላይ ተሠማርተው በቂ አቅም አሳይተዋል። በተለይም በወቅታዊ የመንግስት ተግባራት ላይ ትንታኔዎችን በማቅረብ ሲተጉ ቆይተዋል።

ወይዘሮ ሐይማኖት ያላቸው ጥረት ታይቶም የኒው ሚድያ ወይም የማህበራዊ ሚድያ ክፍል አስተባባሪ ሆነው በዚያው በኢቢሲ ሰኔ 2008 ላይ እንዲያገለግሉ ኃላፊነት ተሰጣቸው። በጊዜው እንደ ፌስ ቡክ ያሉ ፈጣን ማህበራዊ ሚድያዎች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩበት ጊዜ ስለነበር በኢቢሲ ስር ለነበሩት ዲጂታል ፕላት ፎርሞች ይዘት ማዘጋጀት ወይዘሮ ሐይማኖት ከሚመሩት ክፍል የሚጠበቅ ነበር። ባለሙያዋ ወይዘሮ ሐይማኖትም ያላቸውን የካበተ ልምድ በመጠቀም የመንግሥትን አቅጣጫ በማስቀመጥ በማህበራዊ ሚድያ ላይ ምን ዓይነት መልዕክት መተላለፍ እንዳለበት መንገዶችን አመላክተዋል። ሌሎች ባለሙያዎችም በኒው ሚድያ ላይ ያልተቆጠበ አቅማቸውን አውጥተው እንዲሠሩ ወይዘሮ ሐይማኖት የበኩላቸውን አድርገዋል።

ወይዘሮ ሐይማኖት ዘለቀ፣በሐምሌ 2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮምዩኒኬሽን ምክትል ኃላፊ በመሆን ለአንድ ዓመት ሠርተዋል።
በሰኔ 2011 የአዲስ አበባ አስተዳደር የፅዳት ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅ በመሆን ለ 4 ዓመት አገልግለዋል።

ወ/ሮ ሐይማኖት ዘለቀ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት በም/ቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የኮሚኒኬሽን ዘርፍ መሪ በመሆን እያገለገሉ ነበር።

ጥናታዊ ሥራዎች

Major Research activity
“Ethiopian Women Journalist Status in the Media” Research Publication – June 2003, Ethiopian Journalism Review, a quarterly Journal of Ethiopian News Agency, Brana Printing Press.
“How to Organize and Manage Events” –May 2010 – a training paper which is organized for the training of the federal and Regional public Relation heads.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *