ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን፣ መዝገበ-አእምሮ (የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ) ፕሮጀክቱ ለአገርና ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል።
ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች፣ በመጽሐፍ፣ በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ ሲሆን፣ ባለፉት 4 ዓመታት 5 ወራት ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻለና 600 ገጽ ባላቸው ሁለት የተለያዩ ጥራዞች ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።
በኪነ-ጥበብና መዝናኛ ዘርፍ ባለፉት 25 ዓመታት ጉልህ አሻራ ካኖሩት የጥበብ ሰዎች መካከል ሐረገወይን አሰፋ እንደ አብነት የምትጠቀስና በሙያ ትጋት የምትታወቅ ናት። በድርጅታችን ዐላማና ግብ አንጻር ገምግመን የሕይወት ታሪኳም ተሰንዶ ለትውልድ እንዲቀመጥ ስንጠይቃት ፈቃድዋን ሰጥታናለች። ስለዚህም፣ የሥራ ታሪኳንም ዕዝራ እጅጉና ዓይናለም ሀድራ እንደሚከተለው ሰንደውታል።
#የሐረግ ልዩ ክህሎት
የአንድን ሰው ችሎታ በወጉ ለመረዳትና አቅሙ እምን ድረስ እንደሆነ ለማወቅ በተለያዩ ተውኔቶች ላይ የሚያሳየውን ክህሎት ማንሣት መልካም ነው ይላል ቢኒያም ወርቁ፡፡
ሐረግም የሥራ ዘመኗ ሲፈተሽ፣ ‘ሮሚዮና ጁሊየት’ ላይ ሠርታለች፡፤ ‘ይግባኝ የሚል’ ቴያትር ላይ ስትጫወትም አውቃለሁ፡፡ ከዚያ ደግሞ ‘ከራስ በላይ ራስን’ ታያለህ፡፡ 4ተኛ ደግሞ ‘ንጉሥ ሊርን’ ብናመጣ ሁሉም ልዩ ልዩ ናቸው፡፡ ታዲያ ሐረግ በነዚህ ሁሉ ላይ በብቃት ተውናለች፡፡ ኮሜዲ ስትጫወት ሌላ ናት፤ ‘ይግባኝ’ ደግሞ መራራ ነው፤….ልትሞት ጥቂት ቀናት የቀራት፣ ቀናቷ በስቃይ የተሞሉ የካንሰር ታማሚን ወክላ ነው የምትጫወተው፡፡ እዚያ ደግሞ ሌላ ናት፡፡” ሲል ይገልጻታል- ቢኒያም ሐረግን፡፡
ሐረግ ፣አንዳንድ ጊዜ እንዲህ የተለያዩ ገጸ ባሕሪያትን ፣በተቀራረቡ ጊዜያት ፤ግን ደግሞ በተለያየ ስሜት እንደምትጫወታቸውም ቢንያም ያነሣል፡፡ እንዲህ ያለ ብቃት ካላቸው ልዩ ተዋናዮች መካከል እንደምትመደብም የሙያ አጋሯ ይናገራል፡፡
በትወና ዓለም ረዳት ገጸ-ባሕሪ ሲጫወቱ የሚደበቁ፣የሚጠፉ፣የማይሆንላቸው ተዋንያን አሉ። እርሷ ግን ዋናም ገጸ- ባሕሪ ትላበስ፣ወይም ረዳት፤በሁለቱም ድምቅ ብላ ትወጣለች- ይላል ቢንያም።
#ገዝፎ የመታየት ዐቅም
“ውበትን ፍለጋ” ላይ ሐረገወይን እንደ ረዳት ገጸ ባህሪ ሆና ብትቀርብም፤መድረክ ላይ ከዋናዎቹ ገጸ ባህሪያት ባልተናነሰ ገዝፋና ደምቃ ትታያለች፡፡ “ንጉሥ ሊር” ላይም ከነ አቦነሽ መንግሥቱ፣ አብራር አብዶና መንበረ ታደሠ ጋር ስትጫወት አጨዋወቷ አስደናቂ ነበር፡፡ ፈጽመህ ገጸ ባሕሪዋን ሳትረሳት በውስጥህ እንድትቀመጥ የማድረግ ልዩ ክህሎት የታደለች ናት -ይላል ቢኒያም ወርቁ፡፡
እንዲህ በሙያ አጋሯ የተደነቀችው አርቲስት ሐረገወይን አሰፋ በተመልካችም ዘንድ ተወዳጅነትን ካተረፉ ስመጥር ተዋንያን አንዷ ናት፡፡ በሙያዋ በቆየችባቸው 30 ዓመታት ሥራዋን አክብራና ወድዳ መሥራቷን የቅርቦቿ ሁሉ ይናገሩላታል።
#ትውልድ፣ ዕድገትና ጅማሮ
ተወልዳ ያደገችው በተለምዶ “ሰባራ ባቡር” እየተባለ የሚጠራው ሰፈር፣ በ1967 ዓ.ም ሚያዝያ 3 ቀን ነው፡፡ አባቷ አቶ አሰፋ አባይነህ፤ እናቷ ወይዘሮ ምንትዋብ በላይነህ ይባላሉ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችው ሉተራን ሚሽንና ዕድገት ፋና ነው፡፡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ ምኒልክ 2ኛ ደረጃ አጠናቅቃለች፡፡ ዛሬ የመድረክ ፈርጥ የሆነችበት የቴያትር ዝንባሌም የጀመረው እዚያ በአፍላው ዕድሜ ነው፡፡
ያኔ 10ኛ ክፍል ሳለች በድራማ ክበብ ውስጥ ፈራ ተባ እያለች የጀመረችው የመድረክ ሥራ ዛሬ በሙያዋ የአንቱታን ካባ ደርቦላታል።
#ኮሌታው
ለመጀመሪያ ጊዜ መድረክ ላይ ወጥታ ሰው ፊት የቀረበችው እዚያው ምኒልክ ትምህርት ቤት ግጥም በማቅረብ ነው፡፡ በዚያ ያሟሸችውን መድረክ በኋላ የተለያዩ ድራማዎችን ሠርታ ታይታባቸዋለች፡፡ አሐዱ ያለችበት ሥራዋ “ኮሌታው “የሚል እንደነበር ሐረገወይን ታስታውሳለች፡፡ በትምህርት ቤቱ ድራማዎች ላይ ስትተውን የመጀመሪያ ዳይሬክተሯ የነበረው ተስፋዬ ገብረሃና ነው፡፡ ተስፋዬና ጓደኞቹ ከነሐረግ ቀደም ይሉ ነበርና የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወጥተው እንኳን ፣ቴያትር ቤቶች በመሄድ የቀሰሙትን ልምድ ለነ ሐረግ ያካፍሉ ነበር፡፡
#ጉዞ ወደ ተስፋዬ ሲማ
የ2ኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ተስፋዬ ሲማ ጋ የቲያትር ኮርስ ወሰደች፡፡ ከዚያም ጋሽ ተስፋዬ አበበ ጋ አቅንታ “ይብላኝላት” የሚል ድራማ ሠራች፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ድራማውን ሊገመግም የመጣው አርቲስት ሥዩም ተፈራ ነበረና አቅሟን አይቶ ለሮሚዮና ጁሊየት ካስት አደረጋት፡፡
እንግዲህ ወጣቷ ሐረገወይን አሰፋ በዚህ ሁኔታ ወደ ትልቁ የቴያትሩን ዓለም ተቀላቀለች፡፡ ሐረግ ራሷ፣ሮሚዮና ጁሊየትን ስትሠራ ቴዎድሮስ ተስፋዬ እጅግ እንዳገዛት ታስታውሳለች፡፡ ሥራውን በብቃት የመሥራት ፍላጎትም ስለነበራት ስዩም ያነገራትን ሁሉ ያለ አንዳች ማዛነፍ ታደምጣለች፤ትተገብራለች፤ በዚህ በተወደደው በሮሚዮና ጁሊየት ላይ ጁሊየትን ሆና ተወነች። ተመልካችም ልባዊ አድናቆቱን አንዳች ሳይሰስት ቸራት።
#ለአዘጋጅ የማታስቸግር ጥንቁቅ ሙያተኛ
ቢኒያም ወርቁ፣ ሐረገወይን የተሰጣትን የቤት ሥራ በቅጡ ሠርታ የምትመጣ፤ ለአዘጋጅ የማታስቸግር፤ጥንቁቅ ሙያተኛ መሆኗን በሙሉ አንደበቱ ይመሰክራል ፡፡ ሐረግ ታዲያ ዛሬም እንደዚያው ናት፤በሥራዋ ቸልታ አታውቅም፡፡ ስክሪፕቷን ይዛ ለወራት ደጋግማ በመለማመድ ትታወቃለች፡፡ ይህም ጥሩ ጥንቃቄና ትጋት ትወናዋ ላይ ስኬትን እንድትጎናፀፍ አድርጓታል።
በ“ሮሚዮና ጁሊየት” ላይ ያሳየችው የላቀ ብቃት “ከራስ በላይ ራስ” ላይ እንድትሠራ ምክንያት ሆኗት፣ኋላም “ንጉሥ ሊር”ን ሠራች። እንዲህ እያለ ተዋናይነቱ ተሳካ፤እርሷም ቀጠለችበት፡፡ ሐረገወይን ወደ ትልልቅ ሥራዎችና መድረኮች በአጭር ጊዜ መምጣት የቻለች ተዋናይ ናት፡፡
“ሐምሌት” ላይ ከተወነች በኋላ “የሚዘፍኑ ቅጠሎች” የሚል የአውሮፓን ተረት በትረካና በቴአትር ሠራች፡፡ በዚህ ሥራ በኬንያና ካሜሩን በተካሄዱ 2 ዓለማቀፍ ፌስቲቫሎች ሠራች፡፡
#ወደ ቅጥር ዓለም
በ1990 ሜጋ ተጠርታ ስትቀጠር፣ የሜጋው ሥራ የመጀመሪያ የቅጥር ሥራዋ መሆኑ ነው፡፡አንቲገንን፣ የቬሎ ገበያና ፎዚያን(የቴዎድሮስ ተክለአረጋይ የቴሌቪዥን ድራማ ) ተጫወተች ፡፡ ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር የሜጋ ቆይታ በኋላ ብሔራዊ ቴያትር ማስታወቂያ ሲወጣ ተወዳድራ ገባች፡፡
በብሔራዊ ቴአትር የመጀመሪያ ሥራዋ ውበትን ፍለጋን ነው፡፡ መርዛማ ጥላ፣ ባቢሎን በሳሎን፣ ይግባኝ ፣ ፍቅር የተራበ፣ሕንደኬ፣ ንጉሥ አርማህ፣ እንግዳ፣ በትረ -አዳም፣ ግደይ ግደይ አለኝ፣ አጎቴ ቫንያ፣8ቱ ሴቶች(ረዳት አዘጋጅ ሆና ሠርታለች)፣ ዳንዴው ጨቡዴ፣ ባለ ካባና ባለዳባ የሚሉ ቴያትሮችን ሠርታለች፡፡
ሐረግ”ሕንደኬ እና ንጉሥ አርማህ ላይ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ገጸባሕርያትን ተጫውቻለሁ”ትላለች። ሐሳቧንም ስትቀጥል፦
“ሕንደኬ ላይ በቅድሚያ ሔሎፋዥን በመቀጠል ንግሥት ሕንደኬን የተጫወትኩ ሲሆን፣ ንጉሥ አርማህ ላይ መጀመሪያ የልዕልት ናፓታን ቀጥሎ ንግሥቲቷን ተጫወትኩ”ትላለች።
በተውኔቱ ዓለም በነበራት ተሳትፎ በሁለት ታሪካዊ ተውኔቶች ላይ የተለየ ታሪክ ሠርታለች፡፡
“ንጉሥ አርማህ”ና “ሕንደኬ” ላይ በሁለቱም ተውኔቶች በአንድ ጊዜ ሁለት ሁለት የተለያዩ ገጸ ባሕሪያትን ወክላ በጥሩ ሁኔታ መጫወት ችላለች፡፡
#ኪነት መለኪያ
ሐረገወይን ከነተፈሪ ዓለሙ፣ መኣዛ ብሩ፣ ፍቃዱ ተክለማርያም፣ ጌትነት እንየውና ነቢይ መኮንን ጋር በመሆን በአፍሪካ ጃዝ መንደር ረቡዕ ረቡዕ የሚያቀርቡት “ኪነት መለኪያ” የተሰኘ አንድ ፕሮግራም ትሠራ ነበር፡፡ በፕሮግራሙ አጫጭር ጭውውቶች፣ ግጥሞችና ታሪኮች ይቀርቡበት ነበር፡፡ ዝግጅቱን የሚለየው ታዳሚው እየተመገበ የወደደውን እየተጎነጨ ከመመልከት በቀር የሚከፍለው ክፍያ አልነበረም፤ተዋናዮችም የሚሠሩት ያለ ክፍያ ነበር፡፡
#የሐረገወይን የፊልም ተሳትፎ
ከቴአትሩ ባለፈ ሐረገወይን አሰፋ በፊልሙም አሻራዋን አሳርፋለች፡፡ አየለ እሸቱ ደርሶት ጥላሁን ታፈረ ያዘጋጀው “የበደል ጽዋ “የመጀመሪያ የፊልም ሥራዋ ነው፡፡ ያልተነካና፣ አማላዩ( በዚህ ላይ በካስቲንግም ተሳትፋለች)፣ ውበትን ፍለጋም ለታሪክ ይሰነድ በሚል በፊልም ሲሠራ፣ እሱም ላይ ተሳትፋለች፡፡ አልአዛር፣ ሰላዮቹ፣ ዙምራ፣ሃብትሽ ሃብቴ፣ አሸን ክታብ፣ ስውሩ ውጊያ፣ አስተውሎትና ሌሎች ላይ ሠርታለች፡፡ “ያልተኖረ” የሚል ፊልም ደግሞ በያዝነው ወር ኅዳር 15 2018 ለዕይታ ይበቃል።
#ተጨማሪ ሌሎች፦
የቴአትር ባለሙያው ሳሙኤል ተስፋዬ የሐረግን የትወና ችሎታ በእጅጉ ያደንቃል። መድረክ ላይ ራሷ ገዝፋ ሌሎችን ለማግዘፍ ወይም ለማድመቅ የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው። እርሷ መድረኩ ላይ አንጸባርቃ ሌሎችም እንዲያንጸባርቁ የምትሻ ልበ ቀና ተዋናይት ናት ሲል ይገልጻታል።በእርሱ አባባል፣ይህ ዐይነቱን ክህሎት ጥቂት ተዋናዮች ብቻ የሚታደሉት ነው።
ሐረግ ፣የተሰጣትን ገጸ ባሕሪያት በሙሉ በልዩነት ከፍ አድርጋ እንደምትሠራ ሳሙኤል ይናገራል።
ሐረገወይን ፣የቴዎድሮስ ራእይንም አገረ አሜሪካ ድረስ አቅንታ ሠርታለች፡፡ የቴአትር አንድ መቶኛ ዓመት ሲከበር ደግሞ” ሼክስፒር ኢትዮጲያዊ ነው” የተሰኘውን የመኣዛ ወርቁ አጭር ተውኔት ላይ ሠርታለች፡፡ እንደውም እዚያ ላይ የተጫወተችው የወንድ ገጸ ባሕሪን ተላብሳ ነው፡፡
ሐረገወይን በሬዲዮ ድራማዎችም የጎላ ተሳትፎ ያላት ናት፡፡የቀን ቅኝት(ፍቅርተን ወክላ) ፣ የደወል ድምጾች (ሲጳራን ሆና)፣ አዲስ አገር በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ በወቅቱ በድራማዎቹ በጎ ተጽዕኖ የተነሣም ሰዎች የተወነቻቸውን ገጸባህሪያት ስም በብዛት ለስያሜ ሲጠቀሙበት ተስተውሏል፡፡
ምንዱባን ፣ ጉንጉን፣ የአዳም ረታ በርካታ መጽሐፎችንና ሌሎች መጻሕፍትንም ከነ ተፈሪ ዓለሙ፣ ደጀኔ ጥላሁንና አንዷለም ተስፋዬ ጋር በመሆን ተርካለች፡፡
ሐረግ፣ከትወናው ባለፈም በሬዲዮና በቴሌቪዥን የተለያዩ ፕሮግራሞችንም ሠርታለች፡፡ ሸገር ሬዲዮ ላይ ከፀደንያ ገ/ማርቆስ ጋር “ዜማ ፍቅር”የሚል በፍቅር ሙዚቃዎችና የፍቅር ታሪኮች ላይ ያተኮረ ዝግጅት ለሰባት ዓመታት ታዘጋጅና ታቀርብ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ ደግሞ ሥነተዋልዶ፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና የቤተሰብ ጤና አጠባበቅ ላይ ያተኮረ ፕሮግራም ትሠራ ነበር፡፡
ትርታ ሬዲዮ ላይ “እኛና ቅዳሜ” የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም ከነ የኋላሸት ዘሪሁን፣ ይትባረክ ዋለልኝና ቤተልሔም ለገሠ ጋር ነበራት፡፡
ኤን ቢ ሲ ቴሌቭዥን ላይ “ከሐረግ ጋር”የተሰኘ ቶክሾው ታዘጋጅና ታቀርብም ነበር፡፡
ሁለገቧ ሐረገወይን አሰፋ ማስታወቂያዎችን ትሠራለች፤ትልልቅ መድረኮችን ትመራለች። በተጨማሪ የማኅበራዊ አገልግሎት ተሳትፎም አላት። የፓርኪንሰን በሽታ ሕሙማን አምባሳደር በመሆንም ወገኖቿን ታገለግላለች፡፡
#ማንያዘዋል እንደሻው ስለ ሐረግ
የቴአትር አዘጋጅና መምህር ማንያዘዋል እንዳሻው የሐረግን ልዩ ክህሎት ከሚያደንቁ አዘጋጆች አንዱ ነው። ማንያዘዋል እንደሚለው፣ ሐረግን ሲያዘጋጃት ቶሎ ሐሳቡን ትረዳለታለች። አንድ ገጸ ባሕሪን ቶሎ ተረድታ ተዋሕዷት ጥሩ ሥራ ይዛ መቅረብ ትችላለች።
ማንያዘዋል፣ የሐረገወይን የመድረክ ላይ ድምፅ ተመልካችን የሚያረካ እንደሆነ ይናገራል። ድምፅዋ ከእነ ስሜቷ ጥርት ብሎ በግልጽ ይሰማል። ” ድምፅ ላይ የማደንቀው ሌላ ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማሪያም ነው፤ሐረግም ድምፅን ታድላዋለች።
ማንያዘዋል የሐረግን ዲስፕሊን ያደንቃል። “ለቴአትር ራሷን የሰጠች፣ ሙያውን የምታከብር” ሲልም ይገልጻታል። ማንያዘዋል፣እንግዳና ንጉሥ አርማህ የተባሉትን ቴአትሮች ሲያዘጋጅ ሐረግን ተከታትሎ እንዳስተዋለው፣ የአዘጋጅን ሐሳብ ቀድማ የምትረዳ ንቁ ነች።
በዚሁ ቴአትር ላይ በሠራች ጊዜ ከማንያዘዋል ጋር ሰፊ ውይይት አድርጋለች። የሐረግ አንዱ ችሎታ ፣ሐሳቡን ከያዘች በኋላ የራሷን አክላ ጥሩ ሥራ ይዛ መሜጣቷ ነው።
#ሼክስፒርን ከተጫወቱ ተዋናዮች ተጠቃሿ
ቢኒያም ወርቁ ስለ ሐረገወይን ሲናገር፣ መድረክ ላይ በሆነ ምክንያት በሌላ የምትተካቸው ተዋናዮች አሉ፤ ሐረግ ግን በፍጹም ከሚተኩት አይደለችም ፤ልዩ ናት፤ ታናሽ ታላቅን አክባሪ ፣ቂም የማትይዝ አብረዋት ለሚሠሩ የምትቆረቆር ነች፡፡ ሦስትና አራት የሼክስፒር ሥራዎችን መጫወት ከቻሉት ከነ ደበበ እሸቱ፣ ታምሩ ብርሃኑና ሌሎች ጥቂት ሰዎች መካከል አንዷና የታደለችም ናት፡፡
ክላሲክ፣ ሞደርን ፣ ትርጉም ወይም ታሪካዊ ተውኔት ፤ የቱም ሥራ ቢሰጣት መስላ ሳይሆን ሆና የመጫወት ብቃት ያላት፤ ሥራዋን -ወዳድ ተመልካችን አክባሪ፤መሆኗንም ቢንያም ይመሰክራል፡፡ እንደውም አንድ ጊዜ አብረሃት ከሠራህ ሁልጊዜ አብረሃት ልትሠራ የምትፈልግ ዓይነት ናትም ሲል ሀሣቡን ያጠናክራል።
ሐረገወይን በበኩሏ፣ በሕይወቴ የመጀመሪያ ዳይሬክተሬ ነው የምትለው ተስፋዬ ገብረሃና( ገና ምኒሊክ 2ኛ ደረጃ ትምህር ቤት ሳሉ ነው ትውውቃቸው) የተሰጣትን የቤት ሥራ ጥንቅቅ አድርጋ የምትሠራ፤ አልፋም ለሌሎች የምትተርፍ “አንደኛ” ብለን ከምናስቀምጣቸው ተዋንያን የምትመደብ ናት ይላል-ሐረግን ሲገልጻት፡፡
#ሐረግ መድረኩ ላይ ስትወጣ ድምቀት ይመጣል
ገነት አጥላው በ1990ዎቹ የሜጋ ኪነ -ጥበባት ማዕከል የቴአትር መምሪያ ኃላፊ ነበረች።በጊዜው ገነት ሐረግን ያየቻት “ከራስ በላይ ራስ “በተሰኘው የኃይሉ ፀጋዬ ኮሜዲ ቴአትር ላይ ነበር።ያኔ ደግሞ ሜጋ ተዋናይ ይፈልግ ስለነበር ፣ገነት ደግሞ ሐረግ “ከራስ በላይ ራስ”ላይ ያሳየችው ብቃት አስደንቋት፤ ሜጋ በቀጥታ እንድትቀጠር ማድረጓን ታስታውሳለች። ገነትን አላሳፈረቻትም፤ ሜጋ ከገባች በኋላ አንቲገን ላይ ጥሩ ትወና አሳየች።
“ይህች ተዋናይት ተቀጠረች”ማለቷን ገነት ታስታውሳለች። አንቲገን የሳህሉ ኪዳኔ ድርሰትና ዝግጅት ነበር።ሐረግ አንቲገን ላይ የሜጋን ሰዎች አስደምማለች።
ሐረግ፣ከጀማነሽ ሰሎሞንና ከዓለማየሁ ታደሰ ጋር ሥትሠራ ዕምቅ ክህሎቷን ያሳየችበት ጊዜ ነበር።
ገነት የሐረግን ሁለገብነት ታደንቃለች።
የበለጠ ያደነቀቻት ደግሞ፣ “ስምንቱ ሴቶች” ላይ ባሳየችው ልዩ የትወና ብቃት ነው።”ስምንቱ ሴቶች” ላይ ሐረግ ስትወጣ መድረኩ ድምቅ ማለት ይጀምራል። ገነት አጥላው ትወናን በጥልቀት ስለምታይ፣ ሐረግ ቴአትሩን ከፍ ስታደርገው አስተውላለች። በዚህም “ከልብ አድናቆቴን እገልጻለሁ”ስትል ምስክርነት ትሰጣለች።
“ሐረግ ጥሩ ቁመና፤ ብቃትና ግርማ ሞገስም አላት” በማለት ገነት አድናቆቷን ትገልጻለች።
ሐረግ”እንግዳ”ቴአትር ላይም ልዩ ክህሎቷን እንዳሳየች ገነት በሙሉ ልቧ ትመሰክራለች።
አንጋፋውና ስመ-ጥሩው፤ የቴአትር አዘጋጅ ተስፋዬ ገብረማርያም ደግም እንዲህ ይላል፦”እኔ ሐረግን ሳስብ ቀድሞ የሚመጣብኝ መድረክ ላይ ያላት ግርማ ሞገስ ነው፤ እዚያ ላይ ከብዙ ተዋንያን መሐል ግዘፍ ነስታ ቀልብ ትስባለች። ለዚህም መሰለኝ እርሷ የተጫወተችባቸው ተውኔቶች ላይ አጨዋወቶቿ የማይዘነጉኝ። እንቅስቃሴዎቿ፤ የሰውነት እንቅስቃሴዋ ሆነ፣ የድምጽዋ ቅላጼ ቀልብ የመሳብ ኃይል አላቸው። በእንግሊዝኛ ካሪዝማቲክ(ሞገስ ያላቸው) እንደሚባሉት ናት።
ስለምትጫወታቸው ገጸባህርያትም የምትከሥተው ምስል፥ ይህንን የምታሳይበት በራስ መተማመን የሚደንቁኝ ናቸው። ከእርሷ ጋር መሥራት ምንጊዜም የደስታ ምንጭ ነው።” በማለት ሙያዊ ክህሎት የተቸራት ባለሙያ
መሆኗን ይመሰክራል።
ሌላኛው የቴአትር ባለሙያ ሳሙኤል ተስፋዬ፣ የሐረግን የትወና ችሎታ ያደንቃል። መድረክ ላይ ራሷ ገዝፋ ሌሎችን ለማግዘፍ ወይም ለማድመቅ የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው። እርሷ መድረኩ ላይ አንጸባርቃ ሌሎችም እንዲያንጸባርቁ የምታግዝ ልበ ቀና ተዋናይት ናት ሲል ይገልጻታል።ይህ ዐይነቱን ክህሎት ጥቂት ተዋናዮች ብቻ የሚታደሉት ነው።
ሐረግ የተሰጣትን ገጸ ባሕሪያት በሙሉ በልዩነት ከፍ አድርጋ እንደምትሠራ ሳሙኤል ያሰምርበታል።
የዚህ ሁሉ ሥራ ባለቤት ሐረገወይን አሰፋ “የቴአትር ምርጥ ተዋናይት”በሚል በሸራተን አዲስ በተካሄደ ዝግጅት ላይ ሽልማት አግኝታለች።
በነገራችን ላይ ሐረግ ዕድለኛም ናት። ዕድለኝቷ ቸርነቷ በቀደደው ሽንቁር የገባ ነው። በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ሎተሪ ደርሷታል፡፡ ይህን ሎተሪ የገዛችው ሎተሪ ለመሸጥ የሚኳትኑት ሻጭ ግዙኝ ያሉት ሁሉ ዝም ሲላቸው አዝና በገዛቸው ነው ባለዕድል ሆና፣ ዛሬ የምትኖርበትን ቤት የገዛችው፡፡
ሐረገወይን አሰፋ፣በሙያዋ ትልቅ ሥራ መሥራቷን ታላላቅ ባለሙያዎች ቢመሰክሩላትም ሐረግ ግን ትኅትናዋ ይቀድማል። “ይሄን ሠራሁ፤ ያንን ከወንኩ፤ የማለቱ ልማድ የላትም። ይሁን እንጂ ሥራዎቿን ለመቁጠር ብዙ ናቸው። የዚህ ታሪክ ሰናጆች ሐረግ በትወናውና በመዝናኛው ዘርፍ አንድ አሻራ አኑራለች ብለን ብዕር ከወረቀት ስናዋህድ በጥናት የተረጋገጠ ማስረጃ ይዘን ነው። ቴአትርና ፊልሞቿን ተመልክተን፤ የሬድዮ ድራማዎቿን አድምጠን ነው። ሐረግ ግን እግዚአብሔር አቅምና ጉልበት ከሰጣት በመክሊቷ ከዚህ በላይ የመሥራት ሕልምና ራእይ ሰንቃለች። የራስዋ የማስታወቂያ ድርጅት ስላላትም በአንድ በኩል ኑሮን ለማሸነፍ እየሠራችና ቤተሰብ እየመራች፤በሌላ በኩል ደግሞ በጥበቡ ሙያ ደምቃ ለማብራት ያለመታከት ራሷን ታዘጋጃለች።
አርቲስት ሐረገወይን አሰፋ፦
- የተጫወተችባቸው ቴአትሮች
❖ ሮሚዮና ጁልየት
❖ ሐምሌት
❖ ንጉሥ ሊር
❖ አንቲገን
❖ የሚዘፍኑ ቅጠሎች (የሕፃናት ቴአትር) በካሜሮንና በኬኒያ ኢንተርናሽናል የቴአትር
ፌስቲቫሎች ላይ የቀረበ
❖ ጋብቻና ፍቺ (በቴሌቭዥንና በመድረክ የቀረበ)
❖ ጠለፋና አስገድዶ መድፈር (በቴሌቭዥን እና በመድረክ የቀረበ)
❖ ዳንዴው ጨቡዴ
❖ ግደይ ግደይ አለኝ
❖ መርዛማ ጥላ
❖ በትረ አዳም
❖ ባቢሎን በሳሎን
❖ አጎቴ ቫኒያ
❖ ቶፓዝ
❖ ንጉሥ አርማህ
❖ ይግባኝ
❖ ሕንደኬ
❖ የቴዎድሮስ ራእይ (በአሜሪካን ሀገር መድረኮች የቀረበ)
❖ ውበትን ፍለጋ
❖ ከራስ በላይ ራስ
❖ ሼክስፒር ኢትዮጵያዊ ነው
❖ እንግዳ
❖ 8ቱ ሴቶች (ረዳት አዘጋጅ)
❖ ባሎችና ሚስቶች - ፊልሞች
❖ ዙምራ
❖ የበደል ጽዋ
❖ ድፍረት
❖ አማላዩ
❖ ውበትን ፍለጋ
❖ ናዲያ
❖ ሀብትሽ ሀብቴ
❖ እናፋታለን
❖ ሰላዮቹ
❖ ስውር ውጊያ
❖ አልዐዛር
❖ ያልተነካ - የቴሌቪዥን ድራማዎች
❖ እጮኞቹ
❖ የቬሎ ገበያ
❖ ፎዚያ
❖ ዳና
❖ በመሐል
❖ ሳሎኑ
፡
#
- የቴሌቭዥን ድራ