ደበበ ሰይፉ

ዛሬ ሐምሌ 5 2015 በህይወት ቢኖር 73 ዓመቱን ያከብር ነበር

ደበበ ሰይፉ

በእዝራ እጅጉ

ደበበን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ወደድኩትnደበበ መምህሬ አልነበረም፡፡ በአካል የማየት ዕድሉም አልነበረኝም፡፡ ከደበበ ጋር ምንም ዓይነት የጋብቻም ሆነ የሥጋ ዝምድና የለኝም፡፡ ቤቱ የት እንደሆነ አላውቅም፡፡ ደበበን የሚያውቁ የቅርብ ሰዎች ስለ ደበበ ቀን ከለሊት አላጫወቱኝም፡፡ ብቻ ከልጅነቴ ከ1985 ዓ.ም. አንስቶ ‹‹ደበበ›› የሚለው ስም በሬድዮ ሲጠራ የሰማሁ ይመስለኛል፡፡ በ1985 ዓ.ም. የ8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ ከመውሰዴ ወራት በፊት ‹‹ልጅቱ የዘመነችቱ›› የሚለው የደበበ ግጥም በሬድዮ ማዳመጤን አስታውሳለሁ፡፡ እንዲህ ሆኖ ዕድሜያችን እያደገ ብስለትም ሲመጣ ደበበን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ወደድኩት፡፡

በተለይ በ1990 ዓ.ም. ወደ ዩኒቨርሲቲ ስገባ ‹‹ቴአትር ከጸሐፌ ተውኔቱ አንፃር›› የተሰኘውን የደበበን መጽሐፍ በአምስት ብር ሸምቼ ቤቴ ገባሁ፡፡ ጥቁር ሽፋን የነበረው ይህ መጽሐፍ ደበበን ይበልጥ እንድወደው አደረገኝ፡፡ አሁን ደበበ ውስጤ ሆነ፡፡ ወደ ሥነ ጽሑፍ ትምህርቱ ዘለቅ ብዬ ስገባም ደበበን የግድ ማወቅና በተለይም ሥራዎቹ ላይ ማተኮር ነበረብኝ፡፡ በቀዳሚነት ሥነ ግጥሞቹ ማረኩኝ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ወዳጄ የነበረው ደረጀ ጎሳዬ ሁሌ ስለ ደበበ ሥነ ግጥሞች ያወራኝ ስለነበር ተፅዕኖ ሊያድርብኝ ቻለ፡፡ ከዚያም ሒሳዊ ጽሑፎቹ ተናፋቂ ሆኑብኝ፡፡ የአንድን ሰው ሥራ ለማወቅ ሰውየው ያለፈበትን መንገድ ማወቅ ግድ ስለሚል፣ የደበበን ታሪክ ማጥናት ስጀምር ሰውየውን ይበልጥ ወደድኩት፡፡

በዚያን ወቅት ደግሞ ግለ ታሪኮችን እያሳደድኩ የማነብበት ሰዓት ስለነበር ስለደበበ በሬድዮ፣ በቲቪና በጋዜጣም ከተነገረ በጉጉት እከታተል ነበር፡፡ በተመስጦም አነብ ነበር፡፡ በ1992 ዓ.ም. የአዲስ አድማስ ባልደረባ በሆንኩ በ19ኛ ቀኑ ደበበ ሰይፉ መሞቱን ባልደረቦቼ እነ ነብይ መኮንን ሲያወሩ ሰማሁ፡፡ የምወደው ሰው እንዴት በአካል ሳላውቀው ይሞታል? ስል በቁጭት ለራሴ ተናገርኩ፡፡ ከዚያ በኋላም ደበበን ለማወቅ ዘልቆ ሥራዎቹን ለማጥናት ሁኔታዎች ሳይፈቅዱልኝ ቀርተው ደበበን በልቤ እንደያዝኩ ጥቂት ዓመታት አለፉ፡፡ ዳግም ደበበን የማውቅበት በጎ አጋጣሚ ወደ እኔ መጣ፡፡ ሕግ የተማረው የደበበ የመጨረሻ ታናሽ ወንድም አዶናይ ሰይፉ ወዳጄ ሆነ፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ የደበበን ሕይወትና ሥራ ለማየት ጥሩ አጋጣሚ ተፈጠረልኝ፡፡

አሁን ደበበ ውስጤ ሆነ

ደበበ ብዙ ሊነገርለት የሚገባ . . . ከ2005 ዓ.ም. አንስቶ ለ 8 ተከታታይ ዓመታት እሠራበት በነበረው የሬድዮ ጣቢያ በየዓመቱ የደበበ ሰይፉ የልደትና የሙት ዓመት ጊዜ አንድ የሬድዮ መሰናዶ ሳቀርብ ነበር፡፡ ደበበን በተፍታታ መልኩ እንዳውቅ ከወንድም እህቶቹ ጋር በቅርበት እንድወዳጅ በጎ በር የከፈተልኝ፡፡ አንድን ሰው ለማወቅ ያለፈበትንና የደረሰበትን በወጉ መገንዘብ ግድ ስለሚል ስለ ደበበም በእነዚህ ዓመታት አንድ ቁም ነገር ላውቅ ችያለሁ፡፡ ደበበ ብዙ ሊነገርለት የሚገባ፣ ሥራዎቹ ሊነሱለት ግድ የሚል፣ ሕይወት ታሪኩ በዘጋቢ ፊልምና በመጽሐፍ ሊሠራለት የሚገባ ታላቅ የአገር ባለውለታ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ማውራት ያስፈለገውም ደበበ ሰይፉ በሥጋ ባይኖር እንኳን ሥራዎቹ ህያው ናቸውና ሰውየው በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ቢታወስ፣ ቢዘከር መልካም ነው ለማለት ነው፡፡ እስከ ዛሬ በደበበ ዙሪያ ቃለ መጠይቅ ያደረግኩላቸው ስምንት ሰዎች ያስረዱኝ ነገር፣ ደበበ ብዙ መሥራት ሲችል ገና በ49 ዓመቱ ያለፈ ታላቅ ሰው መሆኑን ነው፡፡

የደበበ ትልቁ ሀብት መጻሕፍቶቹ ናቸው

ባለ ቅኔ ብለን ልንጠራው እንችላለን፡፡ ያስተማራቸው ደግሞ በሳልነቱን ደግመው ደጋግመው ያስረዳሉ፡፡ ደበበ ሲያስተምር ለተማሪዎቹ ስሜት ይጠነቀቃል፡፡ በጥሩ የማዳመጥ ስሜት ውስጥ ተማሪዎቹን ካላገኛቸው አጨናንቆ በማስተማር አያምንም፡፡ እርሱ ራሱ ጭንቀት አይወድም፡፡ ለዚህ ምስክርነቱን የሰጠኝ ተፈሪ መኰንን ነው፡፡ ተፈሪ ደበበን እንደ ታላቅ ወንድምና እንደ ቅርብ ጓደኛ ይመለከተዋል፡፡ ደበበ ቤት ቢኬድ ተፈሪ ይገኛል፡፡ ደበበ ተማሪን የማቅረብና ለተማሪ የማዘን በጎ ልማድ ነበረው፡፡ ይህ ልማዱ በሁሉም ተማሪዎቹ ዘንድ ይወደዳል፡፡ ከተፈሪ ባሻገር በአሁኑ ሰዓት በካናዳ የሚገኘው ገዛኸኝ ጌታቸው ከደበበ ቤት የማይጠፋ ነበር፡፡ እንደውም ገዛኸኝ የደበበ ሰይፉን ታሪክ በመጽሐፍ ለማሳተም ሥራ ጀምሮ ነበር የሚል ወሬ ሰምቻለሁ፡፡ ገዛኸኝ የት አድርሶት ይሆን?

ደበበ በአገራችን የሥነ ጽሑፍ ሥራ ውስጥ በተለይ በመደበኛ የሥነ ጽሑፍ ትምህርት ላይ ያበረከተው ሚና ሁል ጊዜም የሚነሳ ነው፡፡ የደበበ የጥናት ክፍል ውስጥ ላለፉት 8 ዓመታት ተመላልሼ የተረዳሁት አንድ ነገር፣ የደበበ ትልቁ ሀብት መጻሕፍቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህ የደበበ መጻሕፍቶች እንዲያው በመደርደሪያው ላይ የተቀመጡ ሳይሆኑ፣ በወጉ የተነበቡ ነበሩ፡፡ ገጣሚው ደበበ በአገራችን የሥነ ግጥም፣ የሥነ ጽሑፍና የቴአትር ጥበብ ታሪክ ውስጥ ዘለቅ አድርጎ ስላጠና የእርሱ የምርምር ሥራዎች ተወዳጅና ብስለትን የተላበሱ ነበሩ፡፡

ለቢዝነስ ዓለም ከቶ አልተጠራምና ፊቱን ወደ ጥበብ አዞረ

ደበበ ሰይፉ ሐምሌ 5 ቀን 1942 ዓ.ም. በይርጋለም ከተማ ተወለደ። ይርጋለም በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ጥንታዊ ከተሞች መካከል አንዷ ነች። ከሐዋሳ ከተማ በአጭር ርቀት ውስጥ ያለችው ይርጋለም ሲዳማ ውስጥ ዝነኛ ከሆኑ ከተሞች መካከል ግንባር ቀደሟ ናት፡፡ ከዚያም አልፎ ጥንት የደቡባዊ ኢትዮጵያ ሕዝብ መናኸሪያ ነበረች። ከ1940ዎቹ እስከ 1960ዎቹ ባሉት ዘመናት ከተለያዩ የደቡብ ከተሞች ተማሪዎች እየመጡ የመካከለኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚከታተሉባት ማዕከል ሆና ቆይታለች፡፡ ይርጋለም ኅብረ ሕዝብ ያለባት የኢትዮጵያ ምሳሌ ነች፡፡ እናም በዚህች ከተማ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ደበበ ሰይፉ ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ሰፊ ብርሃን ሰጥቶ ያለፈ የኪነት ፀሐይ ነበር፡፡ ደበበ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አዲስ አበባ ውስጥ በኮከበ ጽባሕ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት ካጠናቀቀ በኋላ፣ ቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ የሚታወቀው የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ሥነ ጽሑፍን ተምሮ በ1965 ዓ.ም. በከፍተኛ ማዕረግ ተመረቀ፡፡ ቀጥሎም በዚያው ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጽሑፍን ማስተማር ጀመረ፡፡

ደበበ ወደ ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ከመግባቱ አንድ ዓመት በፊት የቢዝነስ ትምህርትን ተምሮ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት የቢዝነስ ትምህርትን ሲማር ማስታወሻ የወሰደበትን ደብተር እንደተመለከትኩት ደበበ የ18 ዓመት ልጅ ሳለ የእንግሊዝኛ የእጅ ጽሑፉ ልቅም ያለና የሚያምር ነበር፡፡ ይህ ሰው ግን ለቢዝነስ ዓለም ከቶ አልተጠራምና ፊቱን ወደ ጥበብ አዞረ፡፡ ደበበ ሰይፉ ጥሩ አድርጎ ያነበበ ሐያሲ ብቻ ሳይሆን፣ ያለፉ ታሪኮችንም ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የሚሰጣቸው በሳል አስተያየቶች ከልብ የነበሩና ለለውጥ የሚያነሳሱ ነበሩ፡፡ ደበበ በሒስ ብቻ አይቆምም፡፡ ደግሞ ብዕር ከወረቀት ያወህድና ይገጥማል፡፡ ደበበ ሲገጥም ነፍሱ በአንዳች ሀሴት ትሞላለች፡፡ እነዛ ግጥሞቹ ወደ አንባቢው ወይም አድማጭ/ተመልካቹ ሲሄዱ ደግሞ ልብን የማረስረስ አቅም አላቸው፡፡

ደበበ የዛሬ 30 ዓመታት ለኅትመት ያበቃው ‹‹የብርሃን ፍቅር›› የሥነ ግጥም ድርሰቱ በብዙዎች የተደነቀለት ሥራ ነው፡፡ በተማሪነትና በአስተማሪነት ሳለ ሲጽፋቸው የነበሩት ግጥሞች ናቸው በብርሃን ፍቅር መድበል ውስጥ ሊካተቱ የቻሉት፡፡ ከዚህች መጽሐፉ በተጨማሪ በ1992 ዓ.ም. በሜጋ አሳታሚ ድርጅት አማካይነት ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ›› በሚል ርዕስ ሁለተኛዋ የሥነ ግጥም መጽሐፉ ለንባብ በቃች። ነገር ግን በዚህ ወቅት ደበበ በሕይወት የለም ነበር። ሥራዎቹ ዘለዓለማዊ ናቸውና እርሱ በሕይወት በሌለበት ወቅትም የትውልድ ሀሴት በመሆናቸው ይታተሙለታል። እናም ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ›› በምትሰኘው መጽሐፉም የደበበን የሥነ ግጥም ርቀትና ጥልቀት የምናይበት ሥራ ነው። ለዚህች ለደበበ መጽሐፍ አጠቃላይ ገጽታዋን በተመለከተ አስተያየት የጻፈው ታዋቂው ወገኛና የደበበ ጓደኛ የነበረው መስፍን ሀብተ ማርያም ነው። መስፍንም ስለዚህችው መጽሐፍ የሚከተለውን ብሏል።

‹‹ደበበ ሰይፉ በርዕስ አመራረጡና በሚያስተላልፋቸው ልብ የሚነኩ መልዕክቶች ብቻ ሳይሆን፣ በስንኞቹ አወራረድና የቤት አመታቱ በአጠቃላይ በውብ አቀራረቡ ተደራስያንን የሚመስጥ ገጣሚ ነው። ስለተፈጥሮ ሲገጥም ፀሐይና ጨረቃ፣ ቀስተ ደመናና የገደል ማሚቶ ያጅቡታል። ስለፍቅር ስንኞች ሲቋጥር የፍቅረኞችን ልብ እንደ ሥዕል ቆንጆ አድርጐ በቃላት ቀለማት ያሳያል። ክህደት ላይ እንደ አንዳንድ ገጣሚያን አያላዝንም። ይልቁንም ውበትና ሕይወትን አገናዝቦ ያውላችሁ ስሙት፣ እዩት፣ ማለትን ይመርጣል። እኔ እንደማውቀው ደበበ ሰይፉ በገጣሚነቱ ሁሌም ዝምተኛ ነው። አይጮህ፣ ጮሆም አያስበረግግም። ይልቁንስ ለዘብ ለስለስ አድርጐ ‹‹እስቲ አጢኑት›› ይለናል። ደግመን እንድናነብለት የሚያደርገንም ይኼው ችሎታው ነው፡፡››
ደበበ ሰይፉ በሥነ ግጥም ተሰጥዖውና በሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ጐልቶ ከሚነሱ ከያኒያን መካከል አንዱ መሆኑን ቀደም ያሉት ኃያስያን ጽፈውታል።

የደበበ ችሎታ በዚህ ብቻም አያበቃም። ደበበ የቴአትር ጥበብ መምህር ከመሆኑም በላይ በዘርፉ ውስጥ ግዙፍ የሚባል አስተዋፅኦ አበርክቶ አልፏል። ደበበ በመድረክ ላይ የሚሠሩ ቴአትሮችንና የቴአትር ጽሑፎችን የያዟቸውን ሐሳቦች በመተንተንና ሒስ በመስጠት ለዘርፉ ዕድገት የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። ደበበ ቃላትን መፍጠር ደስ ይለዋል፡፡ መጠሪያቸው በእንግሊዝኛ የሆኑ ሙያዊ ቃላትን ወደ አማርኛ ሲያመጣ አንዳች የደስታ ስሜት ሰውነቱን ይወረዋል፡፡ በአገራችን የሥነ ጽሑፍ ክፍለ ትምህርት ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ ሴራ፣ መቼት፣ ቃለ ተውኔትና ገጸ ባህርይ እየተባሉ የሚገለጹትን መጠሪያዎች በዋናነት የፈጠረው ደበበ ሰይፉ ነው፡፡

ደበበ ሰይፉ ለዚሁ ለቴአትር ትምህርት ዘርፍ ካበረከታቸው አስተዋፅኦዎች መካከል ለትምህርቱ መጐልበት ይረዳ ዘንድ በ1973 ዓ.ም. መጽሐፍ አሳትሟል። መጽሐፏ ‹‹የቴአትር ጥበብ ከጸሐፌ ተውኔቱ አንፃር›› የምትሰኝ ርዕስ የያዘች ሲሆን፣ በአገራችን የቴአትር ሙያተኞች እንዲበራከቱና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሰፊ ድርሻ አበርክታለች። ደበበ በዚሁ በቴአትር ዘርፍ ውስጥ የተጻፉ የንባብ መጻሕፍት ያለመኖራቸውን ክፍተት ተገንዝቦ ያንን ክፍተት ለመሙላት ሙያዊ ጥሪውን የተወጣ ባለሟል ነው። ደበበ ሰይፉ ጸሐፌ ተውኔትም ነው። በርካታ ተውኔቶችን ጽፎ ለመድረክ አብቅቷል። አንዳንዶቹ ደግሞ ለምሳሌ ‹‹ክፍተት›› የተሰኘው ተውኔቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለበርካታ ጊዜያት ታይቶለታል።

በዚህ ክፍተት በተሰኘው የደበበ የቴሌቪዥን ድራማው ላይ በመተወን ተፈሪ ዓለሙ፣ ዓለማየሁ ታደሰና ሙሉዓለም ታደሰ ድንቅ የሆነ ብቃታቸውን አሳይተውበታል። ደበበ ሰይፉ ከጻፋቸውና ከተረጐማቸው ተውኔቶች መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ከባህር የወጣ ዓሳ፣ እናትና ልጆቹ፣ እነሱ እነሷ፣ ሳይቋጠር ሲተረተር፣ የሕፃን ሽማግሌ፣ ማክቤዝና ጋሊሊዮ ጋሊሊ ይገኙበታል። ከእነዚህ ሌላም በ1973 ዓ.ም. ማርክሲዝምና የቋንቋ ችግሮቹ የሚል መጽሐፍ አሳትሟል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ በ1960 ዓ.ም. በታተመ የሦስት አጫጭር ታሪኮች መድበል ውስጥ አንዱ ሥራ የደበበ ነበረች፡፡

ደበበ በቀድሞው ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ መስፋፋት ዕገዛው ሰፊ ሆኖ ኖሯል። በኢትዮጵያ ሬድዮ ውስጥም የኪነ ጥበብ ዘርፍ ውስጥ ላሉት ፕሮግራሞች አማካሪ ሆኖ ሠርቷል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የቋንቋዎች ተቋም ጆርናል አሳታሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆኖ አገልግሏል። ደበበ ሰይፉ ከ1978 ዓ.ም. እስከ 1983 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ሊቀመንበር ሆኖ ሰፊ ድርሻ አበርክቷል። ደበበ ደራስያን ማኅበርን ሲመራ ‹‹ብሌን›› የተሰኘችውን የሥነ ጽሑፍ መጽሔት እንድትወጣ ሆኗል፡፡

ከዚህም በላይ በወቅቱ አያሌ የሙያው ባለቤቶች እንዲሰባሰቡ አድርጓል። ከውጭ አገሮች በተለይም ከሶቪየት ኅብረት ጋር ሙያዊ ድጋፍና ትብብር እንዲደረግ አድርጓል። ዛሬ በሕይወት የሌለው የሥነ ጽሑፍ መምህሩ ብርሃኑ ገበየሁ ስለደበበ ሰይፉ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል። ‹‹የደበበ አቀራረቡ ቀላልና የማያሻማ ነው። ድምፀቱ ደግሞ ሐዘን ከሰበረው ልብ የሚፈልቅ እንጉርጉ የአቀራረብ ቀላልነት ውበቱ ነው። ይርጋለምና ልጅነቱ በተናጋሪው ህሊና አንድም ሁለትም ናቸው፣ የማይፈቱ፤” እናም ይርጋለም ደበበ ሰይፉ ናት! ሌላኛው የሥነ ጽሑፍ መምህር የሆነው ወዳጄ ገዛኸኝ ጌታቸው፣ ደበበ ሰይፉ እንዳረፈ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር። ‹‹ዛሬ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ አንድ ለጋ ብዕር አጣ፣ ነጥፎ አይደለም ታጥፎ ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ የዋህ ሐሳብ አጣ። ከፍቶ አይደለም በኖ ተኖ እንጂ። ዛሬ ብዙዎቻችን ካወቅነው ብዙ ነገር አጣን። ካላወቅንም እሰየው፡፡ ከእንጉርጉሮና ከፀፀት ተረፍን፤›› ብሏል።

ደበበ ሰይፉ፣ ‹‹የብርሃን ፍቅር›› ቅጽ 1፣ ቅጽ 2 በመጽሐፉ ጠርዞ ትቶልን ሄዷል፡፡ በእነዚህም መጻሕፍት እንደምናየው፣ ደበበ በቀደመው ዘመን በአብዛኛው ገጣሚያን ይጠቀሙበት የነበረውን ረዥም ግጥምንና በዚህ ዘመን በአብዛኛው የሚዘወተረውን አጭር ግጥም በአንድ አጣምሮ በመምጣት ቀዳሚ ይመስለኛል። ከዚህም በተጨማሪ በቤት አመታት ጥበብ ላይ እጅግ በላቀና በጠለቀ ሁኔታ የፈጠረውን ልዩ ጥበብ የሥነ ግጥም ተመራማሪ የነበረው ብርሃኑ ገበየሁ ‹‹በቀበሮ ጉድጓድ›› በተሰኘ ግጥሙ ላይ በሰጠው ትንታኔ አስደማሚ ነገር ያሳየናል፡፡ ግጥሙን/በመጠኑ/ እንይ፡፡

በቀበሮ ጉድጓድ ቀበሮ መስሏቸው
በቀበሮ ጉድጓድ ቀበሮ መስሏቸው
ውሾቹ አጓሩ በዛ ጩኸታቸው
አየሩን በከለው
ምድሩን አገረኘው፣ ትፋት ድንፋታቸው!
አይ የውሾች ነገር
ማን በነገራቸው
ማን ባስተማራቸው
አንበሳ እንደሆነ የሚጠብቃቸው!
አንበሳ እንደሆነ የሚጠብቃቸው!
ደበበ በ1985 ዓ.ም. ግድም ሥራ መሄድ ካቆመ በኋላ ብዙም ከሰው ጋር የሚገናኝበት ዕድል አልነበረውም፡፡ ደበበ ከ1985 ዓ.ም. በኋላ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ባሉ ሰዎችና ሁኔታዎች ማዘኑን ቤተሰቦቹ ይናገራሉ፡፡ ደበበ ነገሮችን አብራርቶ ከመግለጽ ይልቅ ዝምታን መርጦ ለስድስት ዓመታት ለሚሆን ጊዜ ቤት ውስጥ ሊውል ችሏል፡፡ ደበበ በእነዚህ ቤት ውስጥ በዋለባቸው ጊዜያት ‹‹ደበበ እንዴት ነህ?›› ሲባል ደህና ብሎ ምላሽ መስጠት እንጂ የተብራራ ንግግር አይናገርም ነበር፡፡ ነገር ግን በጣም ለሚወዱት ወላጅ እናቱ ግን መልስ ይሰጥ ነበር፡፡

የደበበ የጥናት ክፍል

የደበበ የጥናት ክፍል ውስጥ ብትገቡ ሙሉ ክፍሉ በደበበ ሥራዎችና መጻሕፍቶች የተሞላ ነው፡፡ ጅምር ድርሰቶቹ፣ የወጣትነት ደብተሮቹ፣ ያልታዩ የመድረክ ሥራዎቹ በታይፕ ተተይበው ተቀምጠዋል፡፡ በተለይ በደምሳሳው ላነበው የሞከርኩት ደበበ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ የጻፋት አጭር ልብ ወለድ ነች፡፡ በዚያን ወቅት ማለትም በ1958 ዓ.ም. ደበበ የ16 ዓመት ልጅና የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡ ልብ ወለዱን ልብ ብዬ ሳነበው የደበበን የልጅነት በሳል የሥነ ጽሑፍ ክህሎት መረዳት ችያለሁ፡፡ ይህ ልብ ወለድ ምን እንደሚመስል የራሱን የደበበን የእጅ ጽሑፍ ስካን አድርጌ አቅርቤአለሁ፡፡ ምናልባት የሥነ ጽሑፍ አጥኚዎች ይህን ሥራ ቢያገኙ የደበበ ሥራዎች ከየት እንደሚጀምሩ ለማወቅ ይቻላቸዋል፡፡

የደበበ ድምፅ፣ ምሥልና ቪድዮ

በደበበ ላይ አንድ ደህና ታሪክ ለመሥራትና ይህን በሳል ሰው ለመዘከር ከሥራዎቹ ሌላ ሥነ ግጥም ሲያነብ የተቀዳቸው ድምፆቹና በቪድዮ የተቀረፁ ንግግሮቹ የግድ ጠቃሚ ናቸው፡፡ ደበበን ከእነ ሙሉ ክብሩ ልናውቀው የምንችለው የተሟላ ሥዕል ሲኖረን ብቻ ነው፡፡ ደበበ አንደበተ ርቱዕ ስለነበር ግጥም ሲያነብ ብንሰማው ደስ ይለናል፡፡ ደበበ ሒሳዊ መጣጥፍ ሲያቀርብ ማራኪ በመሆኑ ይህንንም ማየት ማድመጥ ብንችል አይከፋም፡፡ እስካሁን ደበበ ሥነ ግጥም እያነበበ የተመለከትኩት ‹‹ልቤ ተሸበረ›› የሚለውን ግጥሙን ብቻ ነው፡፡ ደበበ ከ1975 እስከ1983 ዓ.ም. በሬድዮና በቲቪ የተቀዳቸው ድምፆችና ቪዲዮች ካሉ ለአድናቂዎቹ በይፋ ቢቀርቡ የደበበ መንፈስ ራሱ ደስ ይለዋል፡፡ ጥልቅ ምርምር ለሚያደርጉ ሰዎችም የሚያበረክተው ሚና ትልቅ ነው፡፡

አንዳንድ ያልተነገሩ እውነታዎች ስለ ደበበ

መቼም ሁልጊዜ አዲስ ነገር መስማት የማይወድ የለም፡፡ ከደበበ ሕይወት ጋርም በተገናኘ አንዳንድ ብዙ ያልተባሉ ነገሮችን ብነግራችሁ ደስ ይለኛል፡፡ በቀዳሚነት ደበበና የማትሪክ ውጤቱን የሚለውን ብናይ፡፡ ደበበ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናውን የወሰደው በ1959 ዓ.ም. የ17 ዓመት ልጅ ሳለ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት የኮከበ ጽባሕ ተማሪ ነበር፡፡ ያገኘው ውጤትም እንዲህ ነበር፡፡ አማርኛ ‹‹ሲ››፣ እንግሊዝኛ ‹‹ቢ››፣ ሒሳብ ‹‹ኤ››፣ ታሪክ ‹‹ኤ››፣ የእንግሊዝኛ ሥነ ጽሑፍ ‹‹ሲ››፣ ባዮሎጂ ‹‹ሲ››፣ እንግዲህ ደበበ ማትሪክን ሲ አመጣ ሲባል ቆም ብላችሁ ማሰብ ትችላላችሁ፡፡ ወደ ደበበ የ8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ ደግሞ ስንመጣ በ14 ዓመቱ ሚኒስትሪ ወስዶ 96.6 ሊያመጣ ችሏል፡፡ ደበበ ወንድሞቹና እህቶቹ አንባቢ እንዲሆኑ ይፈልጋል፡፡ በተለይ ለታናናሾቹ መጽሐፍ እየገዛ ይሰጣል፡፡ ታናሽ እህቱ እሜቱ ሰይፉ እንደነገረችኝ፣ ‹‹ሥራ ፈተው ሲቀመጡ ከምትቀመጡ ለምን አታነቡም?›› ይላቸው ነበር፡፡ አበበም፣ አዶናይም የደበበን አርዓያነት ሁልጊዜም ይመሰክራሉ፡፡ ደበበ የምርምር ሥራዎቹን ለሊት ነበር ይሠራ የነበረው፡፡

የደበበ ሰይፉ 18ኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት ክፍል ከተወዳጅ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ጋር በመተባበር የደበበን 18ኛ ዓመት ዓርብ ሚያዝያ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. አስቧል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል ከረፋድ ጀምሮ በተካሄደው የገጣሚ ደበበ ሰይፉ የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ ደበበ ያስተማራቸው የቀድሞ ተማሪዎችና የአሁን ተማሪዎች ባልደረቦቹም የታደሙበት ነው፡፡ በዚሁ መታሰቢያ የደበበን ሕይወት የሚያሳዩ ምሥሎች በዐውደ ርዕይ ሲቀርብ ደበበን የሚያውቁት ትውስታና የ22 ደቂቃ ዘጋቢ ፊልም የመሰናዶው አካል ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው ለሁለት አሠርታት ግድም በጋዜጠኝነት ያገለገለ ሲሆን፣ የ 45ዕውቅ ሰዎችን ግለ ታሪክ በዲቪዲና በኦድዮ ሲዲ አሳትሟል፡፡ 11 መፅሐፎች ን አሳትሟል ‹‹እዝራ ተወዳጅ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን›› የተሰኘ የራሱ ድርጅት ያለውና የረዳት ፕሮፌሰር ደበበ ሰይፉ ታሪክንም በ 2011 በሲዲ ያሰናዳ ነው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው tewedajemedia@gmail.com ማግኘት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *