አቶ መስፍን ጣሰው

የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ተሸላሚው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ጣሰው ማናቸው?

     ዕዝራ እጅጉ-(ተወዳጅ ሚድያ)

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣ መዝገበ-አእምሮ ( የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች ፣በመፅሀፍ፣በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት 4 ዓመት ከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መፅሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።

ከእነዚህ ውስጥ የሚድያ ሰዎችም ይገኙበታል። አጠቃላይ 74 ከፍተኛ የሚድያ አመራሮች፣ሚኒስትሮች ፣ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የግል ሚድያ መሥራቾች፣ዋና አዘጋጆች እና መካከለኛ አመራሮች ተካተዋል። 35 ያህሉ በዋና ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ያሉ ሲሆን የሁሉም ታሪክ በተሟላ ደረጃ ለመሰነድ ተችሏል። የእነዚህን አመራሮች ታሪክ ሰንዶ ለአንባቢ ተደራሽ ማድረግ ፈታኝ ቢሆንም አሳክተነዋል። በዚህ ተግባራችንም ተጠናክረን እንቀጥላለን።
በዚህ ፅሁፍ የህይወት ታሪካቸውን የምናቀርብላቸው የሥራ መሪ አቶ መስፍን ጣሰው ይባላሉ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና የሥራ አስፈፃሚ ሲሆኑ የሥራ መሪዎችና አስተዳደር በሚለው ዘርፍ(category ) የሕይወት ታሪካቸውን እንደሚከተለው ሰንደነዋል።

“….የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀጥሬ እሰራለሁ ብዬ አንድም ቀን አስቤ አላውቅም።የሚያስደስተኝ ነገር በተሰማራሁበት ስራ ስኬታማ መሆን ነው።
ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ጊዜዬን፣እውቀቴን፣ጉልበቴን መስዋዕት አድርጌያለሁ።”የሚሉት አቶ
መስፍን ጣሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።

አቶ መስፍን ጣሰው በ1955 ዓ.ም በደብረማርቆስ ከተማ ተወለዱ። ትምህርታቸውንም እሰከ 12ተኛ ክፍል እዚያው ደብረማርቆስ አጠናቀው ወደ አ.አ መጡ። አ.አ.ዩ በመግባትም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ እና 2ኛ ዲግሪያቸውን አጠናቀዋል።

ሥራ የጀመሩት በኢትዮጵያ አየርመንገድ ውስጥ ረዳት መሀንዲስ በመሆን ነበር።ላለፉት 41 አመታት በአየር መንገዱ አገልግለዋል። ሌላ መስሪያ ቤትም እንዳልሰሩ ይናገራሉ።
በአየርመንገዱ የማይቋረጥ የ24 ሰዓት ሥራ ውስጥ ሙሉ ጊዜያቸውን በመስጠት የእርሳቸው ህይወት ላይ ቅዳሜ እና እሁድ የሚባል ነገር የለም። ሁልጊዜም ሥራ ላይ ናቸው። በ2022 የአየር መንገዱ ስራ አስፈፃሚ በመሆን ተሹመዋል። ከዛ በፊት በአየር መንገዱ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ውስጥ በአጠቃላይ 40 ዓመት በዚህ መስሪያ ቤት አገልግለዋል።

አቶ መስፍን ጣሰው ቀደም ሲል በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ በተለያዩ የሥራ ክፍሎች ውስጥ አገልግለዋል።
ከእነዚህም ውስጥ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ፣ በጥገናና ኢንጂነሪንግ እንዲሁም ኦፕሬሽን ዳይሬክተር በመሆን ሠርተዋል።
ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሥራ አመራር ቦርድአባል ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የከፍተኛ ድርሻ ባለቤት የሆነውና በምዕራብ አፍሪካ አገራት ውስጥ በስፋት የሚታወቀው የእስካይ አየር መንገድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ።
እስካይ አየር መንገድ በከባድ ኪሳራ የተዳከሙ የምዕራብ አፍሪካ አገራት አየር መንገዶችን ተክቶ በተለያዩ ባለሀብቶች በክፍለ አህጉሩ ያለውን የአየር ትራንስፖርት ክፍተት ለመሙላት የተቋቋመ አየር መንገድ ነው።
በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድም መቀመጫውን ቶጎ ሎሜ ባደረገው እስካይ ውስጥ 40 በመቶ ድርሻ በመያዝ ባለው ሰፊ የአየር ትራንስፖርት ልምድ ትርፋማ እንዲሆን እንዳስቻለው ይነገራል።

አቶ መስፍን ጣሰውም ይህንን አየር መንገድ በመምራት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲኖረው ያደረጉ ሲሆን ለስኬታማነቱ ተጠቃሽ ናቸው።

የአቬሽን ኢንደስትሪ ሥራ ላይ እገባለሁ የሚል ሃሳብም ምኞትም ሳይኖራቸው በአጋጣሚ የተቀላቀሉት ስራ በመጨረሻም በፍቅር የሚሠሩት ሥራ ሆኖ ተገኘ። ታታሪ እና ትጉህ ሠራተኛ መሆናቸው በተለያዩ መድረኮች ተመስክሮላቸዋል። ለምሳሌ በጋና አክራ በተካሄደው የአፍሪካን አየር መንገዶች በማስተሳሰር በሚል የግል ሽልማት አግኝተዋል። በሀገር ውስጥ ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እንደተቋም ሸልማት ተቀብለዋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተለያዩ መሠረተ ልማቶች በተቋሙ እየተገነቡ እንደሆነ እና ከዚህም በላይ አርቆ በማሰብ በርከት ያሉ ተግባራዊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ይናገራሉ። ይህ ኃላፊነት ለእሳቸው ትልቅ እድል እንደሆነና ከተቋሙ ሠራተኞች ጋር በመሆን ትልልቅ ተግባራትን ለማሳካት እንሰራለን በማለት ይገልፃሉ ። ማንም ሰው ጠንክሮ ከሰራ ያሰበበት ከመድረስ የሚያግደው ነገር የለም ብለውም ያምናሉ። አየርመንገዱ በርካታ ዓለም ዓቀፍ እውቅና እና ሽልማቶችን አግኝቷል።

ይህ የሚያሳየው ጠንካራ ሰራተኞቹ ከአስደናቂ የስራ ዲስፕሊን ጋር ምን ያህል እንደሚለፉ እና ታትረው እንደሚሰሩ ነው ይላሉ አቶ መስፍን። ኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የሚያቆየው ስራ እና ስራ ብቻ ነው በማለት የተቋሙን አሰራር ይመሰክራሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *