አለምጸሀይ በቀለ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በልዩ ልዩ ሙያ ላይ ሀገራቸውን ያገለገሉ ሰዎችን የህይወት ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በቴአትር ዘርፍ ታሪካቸው ከሚሰነዱት መካከል አለምጸሀይ በቀለ አንዷ ነች፡፡ አለምጸሀይ በቀለ ፣በአዲስ አበባ ከተማ ሰሜን ማዘጋጃ በ1954 ዓ.ም ተወለደች፡፡ ተማሪ ሳለች የትያትር ዕድገት ክበብ መኖሩን ከተማሪ ጓደኞቿ ሰምታ ወደዚያው አቀናች። አምባሳደር ትያትር እጩ ተዋናዮችን ይመለምል ስለነበር ከብዙ አመልካቾች መካከል ለማለፍ ችላ የእጩ ተዋናይ ኮርሱንም ለመውሰድ በቃች። ኮርሱን ከወሰዱት እጩ ተዋናዮች መካከል አንዷ በመሆንም አዲስ ተከፍቶ በነበረው ራስ ትያትር ሥራዋን ጀመረች።
ቀጥላም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትያትር የመማር ዕድል ስላገኘች የ 3 ዓመት ተኩል ኮርስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትያትር ጥበብ ፣ በሲኒማ ፕሮዳክሽንና ጥበብ ውስጥ የተለያዩ አጫጭር ኮርሶች፣ የተለያዩ የጥበብ ስልጠናዎችን ወስዳለች። በቴአትር ዲፕሎማም አግኝታለች።
አለምፀሐይ የቴአትር ጅማሮዋን ለራስ ቴአትር መክፈቻ ” አንድ ለአንድ ” በሚል ቴአትር የጀመረች ሲሆን አስከትላም ” ሁለት ክፍል ግብዣ ” የሚል የሙሉ ጊዜ ቴአትር ሰርታለች። ከ 30 ዓመታት በላይ በቴአትር ዘርፉ ስትቆይ ከ 35 እስከ 40 የሚደርሱ ቴአትሮችን በመሪ ተዋናይነት ተውናለች።
ከተዋናይነት ባሻገር በቴአትር ሀያሲነት ለብዙ ዓመታት ሰርታለች። አጭርና የሙሉ ሰዓት ቴአትሮችን በረዳት አዘጋጅነት ፣በአዘጋጅነት ፣ በዝግጅት መሪነት ፣ በዳይሬክተርነት ፣ በማማከር ፣ ስክሪፕት በመጻፍ ፣ ሀያሲ በመሆን እና በማስተማር በብዙ የኪነጥበብ ሙያ ለዓመታት አገልግላለች። ወደ ፊልሙ ዓለም በመግባት በአዲስአበባ መስተዳድር የሚታዩ አጫጭር ድራማዎችን ሰርታለች። የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎችን ዳይሬክት አድርጋለች። የጥላሁን ጉግሳን ቤቶች ፊልም ላይ በረ/አዘጋጅነት ተሳትፋለች። በቤቶች ዲራማ በርካታ ክፍሎችን ዳይሬክት አድርጋለች። በዳይሬክቲንግ ፣ በ ረ/አዘጋጅነት ፣ በማማከር ፣ ስክሪፕት ላይ በመሳተፍ (በመጻፍ)፣ በአዘጋጅነት ሰርታለች።
ስራዎቿም ዋና ዋናዎቹ፦ ገመና ቁጥር 1 ላይ በዋና የቴሌቭዥን ድራማ ተዋናይ ፣ ሁለት ክፍል ግብዣ ፣ የቴዎድሮስ እንባ ፣ ማክቤል ፣ የሉሊት ዲፕሎማ ፣ የመሸበት ይቅርታ ፣ ላጤ፣ የዋርካ ስር ምኞት ፣ ማለዳ ፣ አሻራ ፣ ቁርጥ ቀን፣ ትንታግ ፣ አማች ፣ የአና ማስታዎሻ ፣ የመሀን ቱርፋት ወዘተ. በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የሙሉ ጊዜ የመድረክ ስራዎች ላይ በ ረ/ዳይሬክተርነት እና በትወና ከሰራቻቸው መካከል
ሁለት ክፍል ግብዣ፣ ማለዳ፣ የአንድ ቀን እስረኞች፣ የአና ማስታወሻ፣Enesu Ensua፣ ላጤ ሲሆኑ የአጭር ጊዜ የመድረክ ትወና ስራዎች ደግሞ የምኞት እንጉርጉሮ ፣ፍለጋ፣ ሞላ፣ የአንድ ቀን እስረኞች ይጠቀሳሉ። በዳይሬክተርነት እና በትወና የተሳተፈችባቸው ደግሞ ቁርጥ ቀን፣ መርካቶ ፣ ወርቃማ ፍሬ፣ እልፍ ፣ ወንድ አይገባም ናቸው። አጫጭር የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ በዳይሬክተርነት የሰራች ሲሆን እነርሱም ፦ አፋልጉኝ ፣ቪዛው ፣ገበያ ማሞቂያ፣ የሱፍ፣እናት እና ሌሎችም ይገኛሉ። በቴሌቪዥን ተከታታይ ፊልም በ ረ/ዳይሬክተርነት እና በመሪ ተዋናይነት ሰርታለች። ከስራዎቿም የባህር በር ፣ ባለታክሲው ፣ቅብብልና ፎዚያ ይገኙበታል። ፍርሃትና ድንገተኛ የተሰኙ የቴሌቪዥን ድራማ ስክሪፕቶችን ጽፋለች። 4 ትምህርታዊ የሆኑ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ በዳይሬክተርነት ስትሰራ እነሱም ፦ አተርፍ ባይ ፣ ፍርሃት፣ መደበቂያውና ተጓዳኞቹ ናቸው። በሴቶች ላይ ያተኮረ አጭርና አስተማሪ ድራማ ሰርታለች። እነዚህም፦ክስተት ፣ የኔ ብቻ ፣ የስምወርቅ ፣ እንቆጳ ይጠቀሳሉ።
በክሬቲቭ አርት ሴንተር በመምህርነት ሙያ አገልግላለች። በአክሱም ፒክቸርስ መምህር ሆና ሰርታለች። በርካታ ተማሪዎቿም ጥሩ ሙያዊ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። የሙሉ ጊዜ ታሪካዊ ቴአትር በባህርዳር እና አዲስአበባ ያሳየች ሲሆን ከሳቢሳ ፕሮዳክሽን ጋር በመሆን የማስታዎቂያ ስራዎችንም ሰርታለች። በጥቅሉ ከ 30 ዓመታት በላይ በኪነጥበብ ዘርፉ ላይ አገልግላለች።