ተፈሪ ዓለሙ


የድምፁ ግርማ ሞገስ ልጅ ዐዋቂውን የሚገዛው፣ የሠራው ሁሉ የሚዋጣለት፣ ተወዳጁ የጥበብ ሰው ተፈሪ ዓለሙ በ 1956 ዓ.ም. ተወልዶ፣ ዕድገቱም አዲስ አበባ ነው፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በመስፍነ ሐረር ት/ቤት እና አርበኞች፣ ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መድኃኔዓለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተምሯል፡፡ በወጣትነቱ በትምህርት ቤት ክበባት እና በቀበሌ ኪነት በነበረው ተሳትፎ ሙዚቃ ሲሞካክር በወቅቱ ያዩት ሁሉ ዘፋኝ ይሆናል ብለው ያስቡ ነበር፡፡ እንደውም ባደገበት አዲሱ ቄራ አካባቢ ቄራ መሐሙድ ይሉት ነበር፡፡ እሱም ቴአትር ተምሬ የቴአትር ሰው እሆናለሁ የሚል ሐሳብም አልነበረው፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ስድስት ኪሎ ግቢ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ እያለ ግን በባህል ማዕከል በነበረው ተሳትፎ የተለያዩ ድራማዎችን የመሥራት ዕድል ገጠመው፡፡ በቆይታው “ዳንዴው ጨቡዴን” እና “ሰርቆ በኪሴን” ጨምሮ ሌሎች ድራማዎችን ሠርቷል፡፡ በእነኚህ ሥራዎች ዕውቅናና ተወዳጅነትን ማትረፍ ችሏል፡፡ በዚያው የቴአትር ትምህርትን መርጦ መማር ቀጠለ፡፡
በትምህርት ክፍሉ ስለሚዲያ በሚወስዱት ኮርስ ላይ ለትምህርቱ ማሟያ የሠሩት ሥራ በመምህራቸው በመወደዱ፤ እሱ፣ መኣዛ ብሩና መንበረ ታደሰ በኢትዮጵያ ሬዲዬ እሑድ ፕሮግራም ላይ በሳምንት 25 ብር እየተከፈላቸው እንዲሠሩ ምክንያት ሆነ፡፡
ትምህርቱን በመከታተል ላይ እያለ የሬዲዮ ፕሮግራሙን እያዘጋጀ፣ ጎን ለጎን ቴአትርም ሲሠራ ቆይቷል፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ባህል ሚኒስቴር ሃገር ፍቅር ቴአትር ቤት መድቦት በጀማሪ የቴአትር ኤክስፐርትነት ሥራ ጀመረ፡፡ በወቅቱ የሕጻናት ቴአትር ጅማሮ ነበርና በዘርፉ ዐሻራውን አኑሯል፡፡
በሃገር ፍቅር ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ቴአትር የሠራው የብርሃኑ ዘሪሁንን “ጣጠኛው ተዋናይ”ን ነው፡፡ በሃገር ፍቅር ከ1975 እስከ 1990 ዓ.ም. በነበረው ቆይታ ከተዋናይነት እስከ የቴአትር ቤቱ ሥራ አስኪጅነት ባሉት የሐላፊነት ቦታዎች አገልግሏል፡፡
በሃገር ፍቅር ቴአትር ሥራ አስኪጅነት ለስድስት ዓመታት ሲያገለግል በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ያሉ ቢሮክራሲያዊ አካሄዶች የሙያተኛውን የፈጠራ ሥራ እንዳይረብሹ የሚያደርጉ አሠራሮችን በመከተል የበኩሉን አበርክቷል፡፡ ከበላይ አካል በተሰጠው ትዕዛዝም ሙያተኞችን አስተባብሮ ቴአትር ቤቱ የሕዝብ ሆኖ ራሱን ማስተዳደር እንዲችል መንገድ አመላካች ጥናትም አስጠንቶ አቅርቧል፡፡
ከ1990 ዓ.ም. በኋላ ወደ ራስ ቴአትር ተዛውሮ ለአንድ ዓመት ከአገለገለ በኋላ ትንሣኤ የኪነ ጥበባት አማካሪ ኢንተርፕራይዝን አቋቁሞ የግሉን ሥራ ጀመረ፡፡ በ1992 ዓ.ም. የመኣዛ ብሩ አደይ ኢንተርፕራይዝ እና የተፈሪ ዓለሙ ትንሣኤ ኢንተርፕራይዝ በጋራ ተወዳጁን ሸገር ኤፍ ኤም 101.1 የሬድዮ ጣቢያን መሠረቱ፡፡ በሬድዮ ጣቢያው ዛሬም ድረስ ድንቅ ፕሮግራሞችን ለአድማጭ እያደረሱ እንደተወደዱ ዘልቀዋል፡፡

ተፈሪ እና ሬድዮ


የሬድዮውን ሥራ በውል ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ የሬድዮ ድራማዎችን በመጻፍ እና በመተወን፣ ልዩ ልዩ መጻሕፍትን በመተረክ፣ መጣጥፎችን ተፈጥሮ በቸረችው ማራኪ ድምፁ በማንበብ፣ የጨዋታ ሰዓትን፣ የአዘቦት ቀንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለማድመጥ በጉጉት እንድንጠብቀው አድርጓል።
ተፈሪ ዓለሙ ለመናገር አይፈጥንም፤ ከመናገራቸው በፊት ተጠንቅቀው ከሚያስቡት ወገን ይመደባል፡፡ ለሥራውም ካለው ክብር የተነሣ በሚገባ እንደሚዘጋጅ የሙያ አጋሩ ኪሮስ ሃ/ሥላሴ ይናገራል፡፡
ለሙዚቃ ያለው መረዳት እና የማስታወስ ችሎታውም የሚደንቅ ነው። ምናልባትም በሬድዮ ጣቢያው አየር ላይ የሚውሉትን ዘመን አይሽሬ የሙዚቃ ሥራዎች አድምጠን ከተደነቅንባቸው ተፈሪ ለሙዚቃ ያለው ጥልቅ ፍቅር እንዲሁም ዘፈኑን እና ግጥሙን ቀድሞ ማወቁ ለዝግጅቱ ሳይጠቅመው እንዳልቀረ ማንያዘዋል እንደሻው ይመሰክራል።


የትወና ተሳትፎ


ተፈሪ የተወነባቸውን ጠልፎ በኪሴ፣ ባልቻ አባነፍሶ፣ አሉ፣ ምሽት፣ አንቲገን፣ አንበሳ ግቢ ነበርኩ፣ የጫጉላ ሽርሽር፣ ዳንዴው ጨቡዴ፣ ክፍተት እና ሌሎች በርካታ የሙሉ ጊዜ ቴአትሮችን ያየ ሰው በጥበቡ ውስጥ እንዴት ባለ ከፍታ መራመድ እንደሚቻል ከተፈሪ ዓለሙ የትወና ብቃት ማየት ይችላል፡፡
ተፈሪ ዓለሙ ቢሮክራትና ተረቱ (1971 ዓ.ም.)፣ የመቅደላ ስንብት (1972 ዓ.ም.)፣ ጠልፎ በኪሴ (1973 ዓ.ም.)፣ ባልቻ አባ ነፍሶ (1977 ዓ.ም.)፣ የቬኑሱ ነጋዴ (1978 ዓ.ም.)፣ ኦቴሎ (2008 ዓ.ም.) ጨምሮ ከ20 በላይ ቴአትሮች ላይ በተዋናይነት ተሳትፏል፡፡
የፌዝ ዶክተር፣ ዐይነ ሞራ፣ ጫጉላ ሽርሽር፣ ጽናት በመሳሰሉትና በሌሎች ሥራዎች ላይም በዝግጅት ተሳትፏል፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ እንደሆነ በሚነገርለት “ጎበዜ”በተሰኘ የሕፃናት ቴአትርም ላይ በትወና መሳተፉ አይዘነጋም።
ተፈሪ በፊልሙ ዘርፍ ከ“አስቴር” ጀምሮ በነበረው ተሳትፎ ከበርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎች ጋር ሠርቷል፡፡
“ስንብት” (1972 ዓ.ም.)፣ “ሥሉስ ምኞት” (1973 ዓ.ም.) እና “ግደይ ግደይ አለኝ” (1974 ዓ.ም.) የሚሉት ደግሞ በአዘጋጅነት ከተሳተፈባቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የቻርልስ ሊ “ባሻ ሽብሩን”፣ የአንቷን ቼኮቭ “ለፈስፋሲት”ንና ሌሎች ሥራዎችንም ወደ አማርኛ ተርጉሟል፡፡
ተፈሪ ዓለሙ ከሠራቸው በርካታ የቴሌቪዥን ድራማዎች “ዳንዴ ጨቡዴ” (ጸጋዬ ገብረ መድኅን)፣ “ገመና 2” (አዜብ ወርቁ)፣ “ደርሶ መልስ” (መኣዛ ወርቁ)፣ “እንፋሎት” (ተፈሪ ዓለሙ) እና “The call” ይጠቀሳሉ፡፡
ምንም እንኳን በቁጥር መግለፅ አስቸጋሪ ቢሆንም እሱ የተወነባቸውን በርካታ የቴሌቪዥን ድራማዎችን ስንመለከትም ሆነ የሠራቸውን ፊልሞች ስናጤን፤ “እውነትም ለትወና የተፈጠረ ሰው ነው እንድንል ያደርገናል” ይላሉ በትወና ብቃቱ የሚደመሙት ማንያዘዋል እንደሻው እና ኪሮስ ሃ/ሥለሴ።


ተፈሪ ለኅትመት ያላበቃቸው በርካታ ጽሑፎች አሉት። “የካፍያ ምች“ የተሰኘው የግጥም መድብል መጽሐፉ ግን በብዙዎች ዘንድ የተወደደለት የግጥም ስብስብ ነው ። ከመጽሐፍም አልፎ በድምፅ (ኦድዮ) ተሰንዶ እናገኘዋለን።
የብዙ ተሰጥኦ ባለቤት የሆነው ከያኒው የቋንቋ ችሎታውም የላቀ ነው። በውጭ ሀገር ቋንቋ የተጻፉ ተውኔቶች እና መጻሕፍትን ወደ አማርኛ ይተረጉማል፤ ደግሞም ያዘጋጃል።
ለሙያው ያለውን ክብር በነገር ሁሉ በሥነሥርዓት መግለፅ የሚወደው ተፈሪ በቀጠሮ ሰዓት ላይ ቀልድ አያውቅም። ስለጊዜ ያለው ጥብቅ አቋሙና ይኸው ባሕርይው አብረውት በሚሠሩትም ሆነ በቤተሰቦቹ ዘንድ እንደባህል መቆጠር የቻለ ድንቅ ልማድ ሆኖለታል።


ሰዋዊ ባሕርይ


ተፈሪ ከውጭ ለሚመለከተውም ሆነ በቴሌቪዥን መስኮት ላየው ሰው ኮስታራ እና አስፈሪ ይምሰል እንጂ፣ ቀርበው ላዩት ሰዎች ሁሉ ጨዋታ ዐዋቂ እና ተግባቢ፣ እንደውም እሱ እስኪመጣ የሚናፈቅ፣ ሲለይም የሚያባባ እንደሆነ፣ ታዋቂዋ አርቲስት ሐረገ ወይን አሰፋ ትናገራለች።
ቤተሰባዊ ሕይወት
ሀገር ፍቅር ቴአትር ሳለ በዘመናዊ የሙዚቃ ውዝዋዜ አብራው ትሠራ ከነበረችው አዜብ በላቸው ጋር በትዳር ተጣምሮ፣ አራት ልጆችን ያፈራ ጥሩ አባት እና መልካም ባልም ነው፤ ጥበበኛው ተፈሪ ዓለሙ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *