ሰሎሞን አምባቸው

ሰሎሞን አምባቸው

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ሥራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡

ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ? የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡

ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 185 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር የፊልም ሰዎች ታሪክን አሰባስበናል። በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከሚሰነድላቸው መካከል ጋዜጠኛ ሰሎሞን አምባቸው አንዱ ነው።ሰሎሞን በፖሊስና ህብረተሰብ መሠናዶ ይታወቃል ።ባለፉት 25 ዓመታት በሚድያው ዓለም የዘለቀው ሰሎሞን ዛሬም ለሚድያ ሙያ የተለየ ፍቅር አለው። ቦጋለ ተስፋዬ የህይወት ታሪኩን እንደሚከተለው ሰንዶታል።

ልጅነት

ውልደቱ ከውቢቷ ባህርዳር ከ 50 አመታት በፊት ወስዶን 1965ን ያስታውሰናል።’’እትብቴ የተቀበረባት ውብ ከተማ’’ ይላታል ሶል ባህርዳርን። ምንም እንኳ ባህርዳር ለ 3 አመታት ብቻ ቢቆይም፤አብዝቶ የሚጠራት ፤ከልጅነቱ ትዝታ ጋር እጅጉን የተቆራኘችውን በቢሪሞ ሜዳ ነው። ሮጦ የፈነጨባት፣ኳስ እንደልቡ የተጫወተባት፣የአራዶች መፍለቂያ የመተሳሰብና ደግነት ምንጭ የሚፈልቅባት መንደር ነች “የሚላት የሸገሯን ልደታን ነው።

የልደታ ልጅ ‘’ልደትዬ ብሎ ሲምል ማር ከአፉ ይፈሳል“ ይላል ሰለሞን ሰፈሩንና ሰፈሩን ልጆች ሲገልጻቸው።

“ያላየን የለም እንጂ ያላየነው የለም’’ ባይም ነው።

ልደታን ከኳሱ እና ከልጅነት ትዝታዎቹ ባሻገር ፊደልና ሀሁ የቆጠረባትን በልደታ ቤተክርስትያን ውስጥ የነበረችው የየኔታ ጌጡ ቄስ ትምህርት ቤት መቼም ከእዝነ ህሊናው አይጠፉም።

“አቡጊዳ፣መልእክተ፣ወንጌልና ዳዊት ማንም አይደርስብኝም“ ነበር የሚለው ሰለሞን “በስነ ምግባር የተቀረጸው በዚያ እንደሆነ የሚናገረው በኩራት ነው።“መምህር ጌጡ ጋር ፊደል በምንቆጥርበት ጊዜ አባዬ ተዘራ የምትባል የአእምሮ በሽተኛ ነበረች ። ሲፈልጋት ታጫውተናለች ሲያሻት እያለቀሰች ታባርረናለች።መሞቷን የሰማሁት ትልቅ ሆኜ በቴሌቪዥን መቅረብ ከጀመርኩ በኋላ ነበር።የልደታ ልጆች ሁላችን አዘንን ።ግን የት ለቅሶ እንድረስ? አባዬ ተዘራ ….ቀበጢና…ዘመድ አልነበራትም። እኔና አብሮ አደጎቼ የልጅነት አጫዋቻችንን ለቅሶ በልተን ቀረን። ለልደታ ሰፈር ቡቱ ቡትቱ ነበረች አባዬ ተዘራ።“…….የሚለው ጋዜጠኛ ሰለሞን አምባቸው ስለልደታ የልጅነት ህይወቱ ተናግሮ አይጠግብም።

የቄስ ትምህርቱ በማእረግ ካጠናቀቀ በኋላና በቀኝ እጁ የግራ ጆሮውን መያዝ ሲችል 1972 እድሜው ለትምህርት ደረሰና ባልቻ አባ ነፍሶ ትምህርት ቤት ከጓደኞቹ ጋር አንደኛ ክፍል ገባ። በልጅነቱ ወታደር መሆን ይፈልግ የነበረው የዚያን ጊዜው ህፃን፤ ከአመት አመት አንደኛ እየወጣ በትምህርቱም ተሸላሚና እና ደሀ እናቱን በወላጆች ቀን የሚያስከብርም ነበር አሉ።“ብዙ ድጋፍ የነበራቸው የሀብታም ልጆች አብረውኝ ይማሩ እንጅ አንደኛ የምወጣው እኔ ነበርኩ።ታዲያ ወላጆች ቀን ሲከበር የእኔ እናት መድረክ ላይ ተጠርታከእሻማ ቀሚሷ ስትሸለም ማየት እጅግ ያስደስተኝ ነበር።ያን ጊዜ የሀብታም ልጆች ጓደኞቼ ይሄ ደሀ ልጅ እንዴት ይበልጣችኋል? እየተባሉ እንደሚገረፉ ይነግሩኝ ነበር። “የሚለን ሰለሞን እናቱን አብዝቶ ያመሰግናል።

“ክብሯን አውርዳ ፣አይሰሩም የተባሉ ስራዎችን ሁሉ ሰርታ አባትም እናትም ሆና ያሳደገችኝ ምርጧ እናቴ“ ይላታል።

የባልቻ አባ ነፍሶ ትምህርት ቤት ቆይታው ሰለሞን በትምህርት ጉብዝናው ብቻ ሳይሆን በእግር ኳስ፣በስእልና በግጥም የነበረው ፍቅርና ችሎታ በጓደኞቹ ዘንድ ይነሳለታል።፤ የኳስ ችሎታውም ትምህርት ቤቱን ወክሎ ተጫውቷል።

ማርሽ ቀያሪዋ ሺልንጌ

በትምህርቱ ጎበዝ ተማሪና ወደፊት ወታደር መሆን ይፈልግ ለነበረው ሰለሞን አንድ የወደፊት እጣፋንታውን የሚቀይር የህይወት አጋጣሚ ተፈጠረ።ያ የህይወት ጥሪውን ያወጀው አጋጣሚ የ8ኛ ክፍል ተማሪ እያለ የአማርኛ መማርያ መፃሀፍ ላይ ያለው የፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ “ሺልንጌ“ የተሰኘ ልቦለድ ነበር።ልቦለዱ ድሬዳዋ ከተማ ላይ ፍራፍሬ ትሸጥ የነበረች አሳዛኝ ሴት አንድ ተሳፋሪ ሺልንጓን ሳይመልስላት በስህተት ይዞባት ሲሄድ “ሽልንጌን………ሽልንጌን……ሽልንጌን ……“ እያለች የምታለቅስን ምስኪን ሴት ታሪክ ያትት ነበር።

“ብዙም ባልበሰለ የልጅነት አእምሮዬ የታሪኩ አጨራረስ እጅግ አናደደኝ።ተኝቼም በህልሜ የማላውቃት ግን በህሊናዬ የሳልኳት ምስኪን እናቴን ምትመስል ሴት ሽልንጌን እያለች እየሮጠች፣ እየወደቀች እየተነሳች ባቡሩን ስትከተል ይታየኝ ነበር“የሚለው የ8ኛ ክፍሉ ተማሪ ሰለሞን አምባቸው የድርሰቱን ቀጣይ ክፍል ሁለት ብሎ ያለደራሲው ፍቃድ የራሱን ምናባዊ ፈጣራ ጨምሮበት ምስኪኗ ሴት ሺልንጓን አግኝታ ስትደሰት የሚያሳይ ታሪክ ፈጥሮ በየክፍሉ እየዞረ ማንበቡን ተያያዘው።

“ያን በማድረጌ ያቺ ምስኪን ሽልንጓን ያገኘች ያህል ተሰምቶኝ ደስታዬ ወደር አልነበረውም። ሁሉም ተደሰተ።አድናቂዎቼ በዙ።በተለይ ሳሚ ባርያው የምለው የምወደው ጓደኛዬ ከደስታው የተነሳ ሁለት ቀን ዝንቦ ሻይ ቤት የምወደውን ድንች በዳቦ ጋብዞኛል።“

ይሄኔ ነው እንግዲህ የማያውቀው ውስጡ የነበረው መክሊት ፈንቅሎት የወጣው “በርታ የሚሉ የሙገሳ ቃላት ከተማሪዎችና ከመምህራን ሲታከልበት ለካ የመፃፍ አቅም አለኝ የሚል ነገር ማሰብ ጀመርኩ“ ይላል ሰለሞን አምባቸው።

ልዩ ልዩ የልጅነት ክህሎቶች

የሰለሞን ክህሎት የእግር ኳስ እና የመጻፍ ብቻ አልነበረም፤ በእግሩ ኳስ ይጫወታል፣በእጁ ይፅፋል፣ በጣቶቹ ክራር ይደረድራል። ለሙዚቃ ከፍተኛ ፍቅር የነበረው ሰለሞን ከኮሜዲያ ሀብቴ ምትኩ ጋር የልጅነት ጓደኛሞች ነበሩና ሀብቴ ግጥምና የተለያዩ መነባንቦችን ሲያነብ ሰለሞን በክራር ያጅበው ነበር ።“በፖሊስና ህብረተሰብ የቴሌቪዥን ፕሮግራምም ቀርቦ በወቅቱ አነጋጋሪ በነበረው በሂቦንጎ ሙዚቃ ማይሚንግ ላይ ጊታር የመያዜ ሚስጢርም መነሻው ያ በልጅነቴ ክራር የመጫወት ልምድ ነው “ይላል ሶል።

‘’ሰለሞን አምባቸው ከልደታ’’!!

በ 1983 ዓ/ም የ 12ኛ ክፍሉን የጨረሰው ሰለሞን አምባቸው ወደ ስነ ጽሁፉ በማዘንበሉ ለዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ባይመጣለትም በተለያዩ ጋዜጦች ላይ መፃፍ ጀመረ። በተለይ ለሙዳይ፣ ለሩህ መጽሄቶች ጽሁፎችን በየጊዜው ይልክ ነበረ።በኢትዮጵያ ራዲዮ ይተላለፉ ለነበሩ የፖሊስ ፕሮግራሞች ደብዳቤዎችን ይልክ የነበረው ሰለሞን አንድ ቀን አንዲት ግጥም ፅፎ ወደ ሜክሲኮ አደባባይ ወደሚገኘው የፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ቅጥር ግቢ ዘለቀ።ጋዜጠኛ ሻምበል ግዛው ዳኜን አግኝቶ ወረቀቱን ከተቀበለው በኋላ ጥቂት አንብቦ

“እውነት ይህ ያንተ ነው? “ሲል ኮስተር ብሎ ጠየቀ

“አዎ የራሴ ነው “ በድንጋጤ ሰለሞን መለሰ።

“እርግጠኛ ነህ ያንተ ፅሁፍ ነው? “ጎርናናውና አስደንጋጩ የሻምበል ግዛው ድምጽ አይኑን ከወረቀቱ ላይ እንደተከለ መልሶ ጠየቀ።

“በዕውነት ራሴ ነኝ የጻፍኩት። ካላመኑኝ ሌላ ርእስ ይስጡኝና እዚሁ ጽፌ ላሳይዎ“ ወጣቱ ሰለሞን በፍርሀት ግን የራስ መተማመን ባለው ድምጸት መለሰ።

ሻምበል ግዛው ዳኜን በማየቴና ከሱ ጋር በማውራቴ ደስታዬ ወደር አልነበረውም።“ጎበዝ በርታ እሁድ ጠዋት ጠብቅ በራዲዮ እናቀርበዋለን“ ተብዬ ተመለስኩ የሚለው ሰለሞን “ጽሁፉን የሰጠሁት ሀሙስ ሲሆን እሁድ የአመት ያህል ራቀኝ። በተለይ ቅዳሜ ለሊት አልነጋ አለኝ።“

ሰለሞን ለሰፈር ልጆችና ለአካባቢው ነዋሪዎች ልደታ ነዋሪዎች አካሎ “እሁድ ጠዋት በፖሊስ ፕሮግራም ግጥሜ በሬዲዮ ይሰማል ስሙ ፣የሰማችሁ ላልሰማው አሰሙ ፣ግጥሜን ያልሰማ ምሬ አልምረውም መቃብሬ ላይ እንዳይቆም ፣ራዲዮ የሌላችሁም ብትሆኑ በየጎረቤቱና በየዘመድ አዝማዱ እየሄዳችሁ ስሙ“ ብሎ አወጀ።

እናቱም በየእድሩ “የልጄን ችሎታ እሁድ በሬድዮ ስሙት ብለው ተናገሩ። ልደታ በተለይ የደገፋ ሱቅ ሰፈር በአንድ እግሯ ቆመች።አይደርስ የለም እሁድ አምስት ሰአት ደረሰ ።ሰለሞን አምባቸው ከልደታ ያደረሰን ግጥም አለ ቀጥሎ ይቀርባል ብሎ ባለወርቃማ ድምጹ ጋዜጠኛ ሻምበል ግዛው ግጥሙን በሙዚቃ አሳምሮ በአየር ላይ ናኘው ።

“ከኔ ደስታ በበለጠ የእናቴና ጓደኞቿ ደስታ ይበልጥ ነበር።ብዙ ጓደኞቼ ወደቤታችን መጡ። ቡና ተፈላ ደስታም በቤታችን ሞላ“ይላል ሶል ስለዚያች ሰአት ሲያወራ ።ያ በሬዲዮ ስራው ቀርቦ ስሙ የተጠራው ልጅ ተነሳሽነቱ እየጨመረ መጣ። ስነ ጽሁፍም በሽልንጌ አሟሽታ በፖሊስ ግጥም አሳስቃ ጠቅልላ በውስጡ ቤቷን ሰራች።

ቀልድ የማያጡት አንዳንድ የልደታ ሰፈር አብሮ አደጎቹ ግን “ጥበብ ጠራችው “እያሉ አሹፈውበታል።

ሳሌም መፅሄት

ወቅቱ የለውጥ ጊዜ ነበር።መጽሄቶችና ጋዜጦች እንደጉድ የሚወጡበት ሁሉም አንባቢ የነበረበት ለብዙ ወጣት ጸሀፍት መንገድን አጋጣሚ የፈጠረ ወቅት ነበር። በሩህና በሙዳይ ጋዜጦች ላይ እጁን ያሟሸው ጋዜጠኛ ሰለሞን አምባቸው በወቅቱ ዝነኛ በነበረው ሳሌም መፅሄት ለመቀጠር አጋጣሚውን አገኘ።ጠንካራ ጸሀፊ መሆኑን በተለያዩ ፅሁፎች ቀድሞ ያውቁት ነበርና “በስንት ብር እንቅጠርህ?“የሚል ጥያቄ ቀረበለት ። ለደሞዝ አዲስ የነበረው ሰለሞን ምንም ሳይተነፍስ ከወዳጆቹ ጋር ተማከረ፤“ዝም ብለህ 700 በላቸው ተባልኩ“ የሚለው ሰለሞን በወቅቱ ትልቅ ብር የነበረውን 700 ለማለት ቢያመነታም በ 700 ብር ቅጠሩኝ ባለው መሰረት በሰባት መቶ ብር ወርሃዊ ደሞዝ በአዘጋጅነት ተቀጥሮ የጋዜጠኝነትን ጥሙን በደሞዝ ያወራርደው ጀመረ። በወቅቱ የስራ ባልደረባው የነበረው ሰይፉ ፋንታሁን“ ደሞዙ ሶስት መቶ ሀምሳ ብር ነበርም“ ይላል ።ሰለሞን በሳቅ መልክ እያስታወሰ። እናም ሰለሞን የመጀመርያ ወር ደሞዙን የተቀበለ እለት በልደታ ልጆች እንደ ጋርድነት ተከቦ ወደ ቤት መምጣቱን ያስታውሳል።“ብሩ በረከት ነበረውና ስንት ቀን ዘና ፈታ ብለን ተደሰትንበት መሰለህ ወይ ደግ ጊዜ“

ጉዞ ወደ ፖሊስ ሚዲያ

በሳሌም ጋዜጠኝነትን በርካታ ጽሁፎችን ለአንባቢ ያበረከተው ሰለሞን ስራውንና ድምጹን በራድዮና በቴሌቪዥን ለማቅረብ በማሰቡ በ1988 ዓ/ም ፖሊስ ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ከ35 ልጆች ተወዳድሮ 1ኛ በመሆን በጀማሪ ሪፖርተርነት ተቀጥሮ ስራ ጀመረ።

“እጅግ ከምወደውና የስነፅሁፍ ጉዞዩ መንገድ ቀያሽ ከሆነው ከሻምበል ግዛው ዳኜ ጋር የመስራት እድል ያጋጥመኛል ብዬ አላሰብኩም ነበር።ልሞክር በሚል ነበር የተወዳደርኩት። የህይወት አጋጣሚ ሆነና በጥሩ ውጤት አለፍኩኝ።“

“በወቅቱ የፖሊስና ህብረተሰብ የራዲዮ ፕሮግራም በጣም ተወዳጅና ተደማጭ ከነበሩት መካከል የመጀመሪያው ረድፍ ላይ ነበር። በጊዜው በቃለ መጠይቅ ከፈተኑኝ መካከል የቴዲ አፍሮ አባት ታዋቂው ጋዜጠኛና መድረክ መሪ ካሳሁን ገርማሞ አንዱ ነበር። “ካስሽ ብዙ ቆንጆና ልብ አንጠልጣይ የወንጀል ትረካዎችን ያቀርብ ስለነበር አውቀውም አደንቀውም ነበር።አጠር ያለ ተጫዋችና ቁጥብ ሰው ነበር ።የጠየቀኝን ጥያቄም አልረሳውም።“ይላል ሰለሞን በትዝታ ወደ ኋላ እየተጓዘ።

“ለምን ጋዜጠኛ መሆን ፈለክ? ጋዜጠኛ እዚህ ሀገር ብዙ ነው። ደመወዙም ከእጅ ወደ አፍ“ ካሳሁን ገርማሞ ጠየቀ

“ልሆን የምችለው እሱን ብቻ ነው“መለሰ ሰለሞን

“አንተ ወጣት ነህ።የፈለከውን መሆን ትችላለህ“ አለ ካሳሁን በአዘኔታ ወጣቱን እያየው።

“ከገንዘብም በላይ የምወደው ስራ ነው ጋዜጠኝነት“

“ውሳኔህን አከብራለሁ።እንኳን ደስ አለህ ፣ባልደረባችን ሆነሀል“

እናም ወጣቱ ጋዜጠኛ የልደቱ እለት መስከረም 1/1988 የፖሊስ ጋዜጠኛ ሆኖ ቀደም ሲል ይከፈለው ከነበረው ደመወዙን ቀንሶ በ350 ብር ተቀጠረ።

ጋዜጠኛ ሰለሞን አምባቸው በፖሊስና ህብረተሰብ የተለያዩ የወንጀል ትረካዎችን በመጻፍና በማዘጋጀት ለአንድ አመት ቆየ።በዚህ መሀል ሻምበል ግዛው ዳኜ ለአለቆቹ አንድ ሀሳብ አቀረበ።“ጋዜጣና ራዲዮ ያለው ፖሊስ ለምን የቴሌቪዢን ፕሮግራም አይከፍትም?“የሚል

ወቅቱ ደግሞ ጥሩ አጋጣሚን ይዞ መጥቶ ነበር።ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጽያ ቴሌቪዢን የቀን ስርጭት ሊከፍት ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ነበር።በርካታ ክፍት የአየር ሰአት ነበር።የትኛውም ተቋም ወይም ድርጅት ይህን አላሰበውም ነበር።ግዛው ደግሞ ያን ጊዜ የቴሌቪዥን ዜና አንባቢና ዝነኛ ስለነበር የአየር ሰአት ለማስፈቀድ አልከበደውም።በስተመጨረሻ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ታሪክ የመጀመርያው (out source) ፕሮግራም እሁድ 1989አ.ም ከረፋዱ 4፤00 ለሰላሳ ደቂቃ ፖሊስና ህብረተሰብ በሚል ርዕስ አየር ላይ ዋለ። በዚህ ታሪካዊ እለትም ሻምበል ግዛው ዳኜ፤ኮማንደር አበበ ሙልጌታና ሰለሞን አምባቸው ፕሮግራሙን ያስጀመሩ ታሪካዊ ጋዜጠኞች ሆነው ስማቸው በታሪክ ተጻፈ።

የፖሊስ እና ህብረተሰብ የቴሌቪዢን ፕሮግራም

በ90ዎቹ ትውልድ በአስተማሪነቱና በአዝናኝነቱ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ወንጀል ጠል ማህበረሰብ ለመፍጠር የራሱን አሻራ ጥሎ ያለፈው፤ በአቀራረቡ፤በሚያቀርባቸው እንግዶች ጥራት ጭምር ይወደድ የነበረውን የፖሊስና ህብረተሰብ የቴሌቪዢን ፕሮግራም የራሳቸውን አሻራ ካሳረፉ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ጋዜጠኛ ሰለሞን አምባቸው ነበር።

“በተለይ ተገደው በጉልበተኛ ወንዶች ተደፍረው ደማቸውን ጠርገው ቤት ውስጥ ታፍነው ይቀሩ የነበሩ ህጻናት ህግ ፊት ቀርበው ፍርድ እንዲያገኙ በማደፋፈር ፖሊስ ፕሮግራም ብዙ ሰርቷል።አዘጋጆቹ ላይ ብዙ ጫና ይደረግ ነበር።ጫናውን ተቋቁመን የህጻናቱ ደም ይታበስ ዘንድ የሰራነው ስራ ለዛሬው የህጻናት መብት መከበር የማእዘን ራስ ነበር“

ሰለሞን በጊዜው ከልምድ በስተቀር ይህ ነው የሚባል የጋዜጠኝነት ትምህርት ባይኖረውም በአጫጭር ስልጠናዎች ወስዶ ነበር ፖሊስ ፕሮግራምን የተቀላቀለው። ፤በቲቪ ለመታየት ብዙ ውጣ ዉረድ ማለፉን በትዝታ የሚያወጋው ሰለሞን “ኢቲቪ ነው የምሰራው የሚላቸው ጓደኞቹ መቼ ነው አንተ የምትታየው እያሉ ያስቸግሩት እንደ ነበር ይናገራል።“ ጓደኞቼ እንዲያምኑኝ ብዩ ካሜራ ማኖችን እየለመንኩ በአካል መታየት ባይፈቀድልኝም እጄን እያስገባሁ ይህ የኔ እጅ ነው እል ነበር።“ ይላል ያኔ የነበረውን በቲቪ የመታየት ጉጉት ሲያወራ።

ፕሮግራሙን ያስተዋውቀው የነበረው ታዋቂው ግዛው ዳኘ ብቻ ነበር።“ለመታየት አትቸኩሉ ሁሉም በጊዜው ይደርሳል።ስራችሁ ላይ ብቻ አተኩሩ። ያለጊዜው አየር ላይ ብትወጡ ትታበያላችሁ።ዝናን መሸከም የሚችል ስብእናን እስክትፈጥሩ ድረስ ስራችሁን ስሩ።“ ግዛው ዳኘ ይላችው እንደነበር እነሰለሞን ሁልጊዜም ያስታውሱታል።

ከእለታት አንድ ቀን ግዛው ዳኘ ለስራ ወደ ውጪ ሀገር በሄደበት ወቅት ለነሰለሞን አንድ ጥሩ አጋጣሚ ተፈጠረላቸው።በቴሌቪዥን ለመታየት ካላቸው ጉጉት የተነሳ እስከመቼ ነው ምስላችን በቴሌቪዥን የማይታየው? ብለው መጠያየቅ ጀመሩ። አስበውም አልቀሩ ሰለሞን አምባቸው እና አበበ ሙልጌታ “ እንሞክር እንሞክር “ተባብለው ዳይሬክተሩ ጋር በመሄድ በሚገባ አጥንተው ፕሮግራም ማስተዋውቁን አስቀርፀው አየር ላይ አዋሉት።

“የመጀመሪያችን አይመስልም ነበር። አንድ ፊደል እንኳን አልተሳሳትንም ነበር።ያለንን ልብስ አጥበንና ተኩሰን ሽክ ብለን ነበር የቀረብነው። የልደታ ሰፈር ዳግም ጉድ አለ።አንጀባዬ ጨመረ።ጋባዤ በዛ።ቴሌቪዢን ላይ የቀረብኩባትን ልብስ ሳልቀይር ከተማውን አስሳለሁ።….ላኮመልዛ ባንኮኒ ላይ ነገስኩበት….ይህ ሁሉ ሲሆን ሻምበል ግዛው ጉዱን አልሰማም “ሶል በትዝታ የኋሊት ተመለሰ።ዛሬ የሙያ አባቱ ሻምበል ግዛው በህይወት የለምና በትዝታ በተጓዘ ቁጥር አይኖቹ እምባ ያዝላሉ።

በዚህ መሀል የግዛው ዳኘ መምጫ ቀን ደረሰ።“ስሩም አትስሩም “ሳይለን ነው የሄደው።“ሲመጣ ምን ይለን ይሆን?ቤቱ ደግሞ የወታደር ቤት ነው።ህግ ህግ ነው ደንብ ደንብ ነው። ብቻ በጣም ጨነቀን።አንዴ ሆኗል የመጣው ይምጣ ብለን ተዘጋጅተን ጠበቅነው።

ግዛው ዳኜ መጣ።ድፍረቶቻችንን ሁሉ አስተባብረን ተቀበልነው።ትኩር ብሎ ሲያይህ ዝም ብሎ ያስደነግጣል።ቆፍጣና መኮንን ነበር።ቦሌ ስንቀበለው ከድንጋጤያችን ብዛት አበባ እንኳን እንደሚያዝ አላስታወስንም።

“እንዴት ናችሁ ልጆች?“….ሁልጊዜ እኛ ለሱ ልጆች ነን።

“ደህና ነን እንኳን ደህና መጣህ“

“ስራ እንዴት ነው?“ …ሻምበል ቀጥታ ወደ ገደለው ገባ…..በነገራችን ላይ ሰለሞን እንደሚናገረው “ወደ ገደለው “የሚለው አባባል መነሻው ፖሊስ ፕሮገራም ነው“የምናቀርበው የነፍስ ግድያ ወንጀል በመሆኑ ቀጥታ እከሌ እከሌን ገደለው ከምንል ትንሽ እናዋዛው በሚል እንኳን ሰው እግርና እግርም ይጋጫል የሚል መግቢያ እንሰራ ነበር።ሰው ደግሞ የሚፈልገው ማን ማንን ገደለ የሚለውን ዜና ነው። በዚህ የተነሳ ተመልካች ወደ ገደለው ግቡ ሲል ሀተታ ለሚያበዛ ሰው ወደ ገደለው ተባለ“ ይላል ሶል።

“ስራ ሰላም ነው“ሰምቶ ይሆን አበበና ሰለሞን በፍርሀት ተያዩ

“በናንተ እተማመናለሁ።ጥሩ እንደነበረም ሰምቻለሁ“

“ጉድ ፈላ ሰምቷል ማለት ነው“……ዝም ብለን አበበ እየነዳ ወደ ቤቱ አደረስነው“

“የኋላ ኋላ የቴሌቪዢን ሰዎች ልጆችህ እጅግ ጎበዝ ሆነዋል።ተኪ ልጆች አፍርተሀል ባለው አለሳልሰው የሰራነውን እያሳዩት ነገሩት።እንደፈራነው ሳይሆን ሻምበል እጅግ ተደሰተ።

“ድሮም እኮ መቻላችሁን አውቃለው ።ለሙያው ይበልጥ ጉጉት እንዲኖራችሁና ወረተኛ እንዳትሆኑ ነው። “አለን ሻምበል ልዩ ራትና አድርጎት የማያውቀውን ውስኪ እየጋበዘን።ከዚያ ቀን በኋላ አንተ ግባ አንተ ግባ መባባል ጀመርን።እንደውም ይውጣላቸው ብሎ ነው መሰል ብዙውን ጊዜ ለኛ ተወልን።ይኄው እስከዛ ያኔ በሰራነው ስራ ስማችን ሲጠራ ይኖራል።እናም እኛ ስለፕሮግራሙ በተጠየቅን ጊዜ ሁሉ ስሙን እናወድሳለን።“

ፍጥጫ ከነፍሰ ገዳዩ ጋር

“የመጀመርያ ስራውን ታስታውሳለህ ወይ ?“አልነው ሰለሞንን

“አዎ ትዝ ይለኛል።የራዲዮ ጋዜጠኛ ሆኜ እንደተቀጠርኩ ግዛው ነፍሰ ገዳይ ጋር ነበር“ የላከኝ ይላል ሰለሞን ።

“የቀድሞ ወታደር የነበረና በቦንብ 3 ሰዎችን የገደለ ሰው ጋር ፌዴራል ማረሚያ ቤት ሄድኩኝ ።ለሥራው ከተመደብኩ ጀምሮ ሌሊቱን ሙሉ ስጨነቅ ነበር ያደርኩት።ነፍሴ ፈራች ነፍሰ ገዳይ አይቼ አላውቅም ።ነበር“ የሚለው ሰለሞን ወቅቱን ሲያስታወስ እንዲህ ይላል

“የታሰረበት ፖሊስ ጣቢያ ደረጃው የጣውላ ነበር።ስትራመድበት ሆነ በተንቀሳቀስክ ቁጥር ይጮሀል።በዚያ ላይ ጨለማ ነው።በቀስታ ካልሆነ ምንም አይታይም።የጣውላው ወለል ላይ ሲራመድ የሚያስፈራ፤እግሩ አርቴፊሻል ስለነበር ከጣውላው ጩኸት ጋር ተደምሮ እጅግ የሚያስፈራ ሰው ወደ እኔ መጣ።

“ፍርሃቴ ጨምሯል ።ነፍሰ ገዳይ የተባለው ሰው ፊት ለፊቴ ቀረበ። ጥለህ እሩጥ እሩጥ አለኝ።ግን ድፍረቴን ሁሉ አስተባብሬ ቁጭ አልኩ።“ በትዝታ ፈገገ ሰለሞን።

“የምትጠይቀኝ ነገር ካለ ቀጥል“አለኝ ወንጀለኛው ኮስተር ብሎ።ምንም የፍርሀትም ሆነ የመጸጸት ስሜት አይታይበትም።

“ስምህን ማን ልበል አልኩት?“

“ስሜ ምን ያደርግልሀል።ከፈለክ ፖሊሶቹን ጠይቅ“ ነፍሰ ገዳዩ በሚያስፈራ ድምጽ መለሰ።

“እሺ ልጆቹን ለመግደል ምን አነሳሳህ?“ ብዙ ጋዜጠኞች ሲሉ የሰማሁት ጥያቄ ቀጠልኩ።

ሰውዬው ጉሮሮውን ጠራረገና በንዴት ድምፀት “እኔ ሰው አልገደልኩም አለ እግሩን አውጥቶ አሳየኝ። ሰው ሰራሽ እግር ።እናም እነዚያ አሳዳጊ የበደላቸው ለእናት ሀገሬ ስዋደቅ እግሬን ባጣ ቆማጣ እያሉ ይሰድቡኝ ጀመር ።ሀገሬ በጠላት ስትጠቃ ጥቃቷን አላይም ብዬ የነሱ አባቶች ጓዳ ተጎልተው እኔ ዘመትኩ።ልጆቹ ስድባቸውን ቀጠሉ።ቆማጣው ቆማጣው ይሉኝ ያዙ።ከትእግስቴ በላይ ሲሆን ለአደጋ ጊዜ ያስቀመጥኩትን ቦንብ ከቤት አምጥቼ ተካፈሉት ብዬ ወረወርኩባቸው….በቃ ልጆቹ ወደ መቃብር እኔ ወደእስር ቤት።

የሰለሞን ስራዎች በወፍ በረር

የክርስትና አባት

አንድ አስገራሚ ታሪክ በአንድ ወቅት ተሰምቶ ነበር። አዋሳ አከባቢ ነው።ወጣቷ የሰው ቤት ሰራተኛ ነበረች።እናም ተገዳ ትደፈርና እዚያው ቤት እያለች በድብቅ ልጅ ትወልዳለች ።ልጁን ለማሳደግ አቅም አልነበራትምና 11 ሜትር ጥልቀት ወዳለው የመጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ትጥለዋለች።ያልቆረጠው ነፍስ ይሆንና ልጁ የወደቀው ጉድጓዱ ጫፍ ላይ ነበር።ህጻኑ ጉድጓድ ውስጥ እንዳለ አምርሮ ይጮህ ጀመር።አንዲት ታዳጊ ወደ እርሱ መጥታ ድምጽ ታሰማና አንድ አዛውንት ወገባቸውን ታስረው ይገቡና የህጻኑ ህይወት ይተርፋል።ይህን ልብ የሚነካ ታሪክ ስፍራው ድረስ በመሄድ ሰለሞን አሳምሮ ሰራው። ብዙዎች የዚያን ተአምረኛ ሕጻን ታሪክ ዛሬም ያስታውሱታል።

“በአጋጣሚ ከጣሊያን ሀገር የመጣች አንዲት ኢትዬጵያዊ ሴት ታሪኩን ትከታተል ነበርና ልጁን ማሳደግ እንደምትፈልግ ገልጻልን አዋሳ ሄደን ልጁን ክርስትና አንስቼ አስረከብኳት።ዛሬ ልጁ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ አላውቅም።ግን ከሰራሁዋቸው ታሪኮች ሁሉ ያስደስተኛል።“ይላል ጨዋታ አዋቂው ጋዜጠኛ ሰለሞን አምባቸው።

ከፖሊስ መዝናኛ ፕሮግራሞች ጀርባ ያለው ሰው

በርካቶች ከመዝናኛ ፕሮግራሞች እኩል ይጠብቁት የነበረው የፖሊስ ፕሮግራም በይዘትና በአቀራረብ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን የቅርፅ ለውጥ ያደረገው ጋዜጠኛ ሰለሞን አምባቸው፤ አያሌ ስመጥር የሀገሪቱን ሰዎች በእንግድነት አቅርቧል። በተለይ በጊዜው ሊቃነ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ጳውሎስን በንግስ ወቅት በቁልቢ ገብርኤል ቤተክርስትያን ዙሪያ ስለሚደረገው ህገ ወጥ ተግባር ምላሽ እንዲሰጡ ያቀረበው ጥያቄና የጸረ ሙስና ኮሚሽነር የነበሩትን አቶ አሊ ሱሌይማንን “ኮሚሽኑ የኢሀዴግ ባለስልጣናትን አይነካም ተጽእኖ አለበት ይባላል “ሲል የጠየቀበት ፕሮግራም በድፍረቱ ይጠቀሳል።

ከጥላሁን ገሰሰ እስከ ማህሙድ አህመድ፤ ከሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን እስከ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር፤ እነ ታምራት ሞላን፤ ከአንጋፎቹ ሙዚቀኞችና ደራሲያን ጋር ቆይታ አድርጓል። እነ ሙሉዓለም እና ሰራዊት ፍቅሬ ባልና ሚስት ለሚመስሉን የ90ዎቹ ትውልዶች ፊት ለፊት ተጋፍጦ እውነቱን አፍረጥርጦታል።

“ብዙ ጊዜ ለቃለ መጠይቅ ቀጥረናቸው እምቢ የሚል እንግዳ አላጋጠመኝም። እያስፈራራችሁ ነው እንግዶችን የምትጠሯቸው እያለ ኮሜዲያን ደረጀ ሀይሌ ይቀልድብናል። ግን እውነቱ እሱ አይደለም። እንግዳህን አክብረህ ከሰራህ ሁሉም ፈቃደኛ ይሆንልሀል።ሰርተህ ማሳመን አለብህ።አቀራረብህም ወሳኝ ነው።እንደሱ ለመሆን ግን ችሎታና ክህሎት ይጠይቃል ።የፖሊስ ፕሮግራም አዘጋጆች ሚስጢር ይህ ነው።“ የሰለሞን አጭር ምላሽ።

ቴዲ አፍሮና ሰለሞን አምባቸው

ሰለሞን ከጋዜጠኞች ሁሉ በተለየ መልኩ ከድምጻዊ ከቴዲ አፍሮ ጋር ብዙ ግዜ ቃለምልልስ በማድረግ የሚስተካከለው የለም። የዚህም ምክንያት ብዙ ቢሆንም የአባቱ የካሳሁን ግርማሞ ጓደኛና የስራ ባልደረባ መሆኑና የቴዲም አድናቂ መሆኑ እንደጠቀመው ይነገራል።

በ1993ቱ አልበም ቴዲ ዝናው ሲናኝ፤ በ1994 አዲስ አመት ዋዜማ ላይ ቴዲ አፍሮና ሀይሌ ገ/ስላሴ ለመጀመርያ ጊዜ እንዲገናኙ በማድረግ ፤እንዲሁም በወቅቱ ቴዲ ላይ የሚወራውን አሉባልታ ፊት ለፊት ጠይቆ ቴዲ ነፃ አውጥቶታል። ሰለሞን ስለዚያች ቀን ሲያስታውስ ከጥያቄዎቼ መልሶቹ ይገርሙኛል ይላል። “በሀገራችን ባልተለመደ ሁኔታ ፖሊስ ባለበት ሀገር የምትሄደው በጋርድ ነው አሉ?“ ሰለሞን ይጠይቃል ።ተመልካቹ ይስቃል።ቴዲ አፍሮ ሳቀና መልስ ጀመረ

“የእኔ ዘፋኝነት ለሀገሬ ብቻ ነው።ወንዝ አልተሻገረችም።ከኔ አጠገብ ያለው ዝናው በአለም አቀፍ ደረጃ የናኘው ጀግናው ሀይሌ ገብረ ስላሴ በነጻነት በሚሄድባት ሀገር እኔ ማን ስለሆንኩ በጋርድ እሄዳለሁ?“የቴዲ አፍሮ ምላሽ ነበር።ተመልካቹ መጣም አጨበጨበ።ሰለሞን ጥያቄውን ቀጠለ።

“ሴቶች ጡት ላይና የማይገባ ቦታ ትፈርማለህ እየተባለ ነው።ይሄ ከባህላችን ውጭ የሆነን ተግባር እንዴት ልትፈጽም ቻልክ?“ደፋሩ ጋዜጠኛ ጠየቀ።ተመልካቹ ደነገጠ በሳቅን አወካ።ቴዲ ቀጠለ

“ይህን ላለማድረግ የሚያስፈልገው ኢትዮጵያዊ ሆኖ መገኘት ነው“ምላሹ በጭባጨባ ታጀበ።“በጥሩ ስነምግባር ያደኩ ኢትዮጽያዊ ነኝ።በልጅነታችን ሰው ፊት እንኳን እንድናወራ አይፈቀድልንም።እና ይህን አስነዋሪ ነገር ልፈጽም እችላለሁ?“የተመልካቹ ጭብጨባ ቀለጠ።

ከቴዲ ጋር በ1997 አዲስ አመት ስለቀነኒሳና ሀይሌ በወቅቱ ስለዘፈነው አልሆንልህ አለኝ ስለሚለው ዘፈን ለመጠየቅ ቴዲን እንግዳ ባደረገበት ወቅትም

“ይሄ ምርጥ ዘፈን እንዴት በአንድ ቀን ለመስራት አሰብከው “ሲለው ቴዲ በፍጥነት “መጀመርያ እኔ ለመዝፈን እነሱ ማሸነፍ ነበረባቸው.ብሎ ካሳቀኝ በኋላ …አየህ እኛ ከፊት ያለን አክብረን አናልፍም በፖለቲካውም ቢሆን ያለፈን መውቀስ ብቻ ነው።የቀደመውን አክብሮ መሸኘት ያስፈልጋል ። ቀነኒሳ ላይ የታየው ይሄው አንተን ጥሎ መሄድ አልሆነልኝም የሚል መልካም እሳቤ ስለሆነ ይህን ለትውልድ ለማስተላለፍ የሰራሁት ስራ ነው።ያሰብኩትም ተሳክቶልኛል። የሚለው ምላሹ አስገርሞኛል ይላል ጋዜጠኛ ሰለሞን አምባቸው።

የማይሚንጉ ሂቦንጎ ጉዳይ

“አንድ ወቅት የፖሊስ የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ የወቅቱ ዝነኛ ሙዚቀኛ የሂቦንጎ ዘፋኝ አርቲስት ስንታየሁ ሀዋሳ ለበዓል ስራ ቀጥሮን ባልታወቀ ምክንያት ቀረብን“ ይላል ሰለሞን። እናም ፕሮግራማችን ሊበላሽብን ሲል አንድ ሃሳብ መጣለት ።አብዛኛዎቹ የኛ ጋዜጠኞች በአንድ ወቅት የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች የነበሩ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ለጓደኞቹ አንድ ጥያቄ አቀረበ።

“የሙዚቃ መሳርያውን ከሙዚቃ ተጫዋቾች ተቀብለን ሂቦንጎን በማይሚንግ ለምን እኛ ጋዜጠኞች አናስመስለውም?“ አልኩኝ

“እንዴት?“ የስራ ባልደረቦቹ

“ይሆናል ያልኩት ሁሉ አስረዳሁ ሁሉም ቀስ በቀስ ተቀበለኝ ከዚያ በኋላ ሂቦንጎን መድረክ ላይ ሙዚቃ መሳርያ ኪቦርዱ፤ድራሙ፤ሳክሱ ሁሉም ተይዞ እኔም በልጅነቴ እነካካት የነበረችው ክራር ጠቅማኝ ጊታር አንግቤ ሂቦንጎን አስነካነው“ ይላል ስለ ፈጠራው በትዝታ ሲያወሳ።

የሰለሞን አበርክቶዎች

ሰለሞን ለየት ከሚያደርገው ነገር አንዱ ብዙ ጊዜ ከበላይ አለቆቹ ጋር የሚያጣላው እስረኛ ወይም ወንጀለኛም ይሁን ተጠርጣሪ ቃለመጠይቅ ሲያደርግ መጀመርያ የታራሚውን ፍቃድ መጠየቅ ያስፈልጋል በሚል ያልተለመደ አስራር ማስለመዱ ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ እስረኛው ፍቃደኛ ቢሆንም ካቴና ከእጁ ላይ ሳያወልቅ መጠየቅ የለበትም በሚል እስረኛም ሆነ ታራሚ ካቴና ከእጃቸው ላይ ሳይፈታ ቃለመጠይቅ ያለማድረጉ ሰለሞን በፖሊስና ህብረተሰብ ፕሮግራም ላይ ያስለመደው የስራ ባህል መሆኑን የስራ ባልደረቦቹ ያወጉለታል።

“ሰለሞን አዳዲስ ፕሮግራሞች አስጀምሯል፤የፖሊስና ህብረተሰብ ፕሮግራም ተወዳጅ ሳቢ እንዲሆን የመዝናኛ ፓኬጆችን ቀርፆ የሚፈራውን የፖሊስ ፕሮግራም፤ ተወዳጅ አድርጎታል፤ፈለጠው ቆረጠው ከሚባልበት አዘጋገብ ተወጥቶ ትውልድ በስነምግባር እንዲቀረፅ ፤ህብረተሰቡ ወንጀልን በባለቤትነት በጋራ እንዲከላከል የበኩሉን ሚና ተጫውቷል“ የቅርብ ጓደኛውና ባልደረባው የኮማንደር አበበ ሙሉጌታ አስተያየት ነው።

ይሁን እንጂ ሰለሞን ስለፕሮግራሙ ተወዳጅነት ዘወትር ሲጠየቅ“ ውጤቱ የጋራ ነው“ ሲል በጨዋነት ይመልሳል።

“የፕሮግራሙ ስኬት የእኔ ወይም የእከሌ ነው ሊባል አይችልም ።የጋራ ውጤት ነው።እኛ በቴሌቪዥን ስለምንታይ ሊሆን ይችላል።ከኛ ጀርባ የነበሩ ቅን ፣ብርቱና ጎበዝ ባልደረቦቻችንን ውጤት እጅግ ከፍተኛ ነበር።የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ እንዲባል ነው።ይህ ማለት ግን በልዩነት የሚነሱ የሉም ማለት አይደለም“ የሚል ነው ምላሹ።

ጠንቋዮችን የማይፈራው ሰሎሞን

“በህይወቴ ፈርቼ የማላውቀው ጠንቋዮችን ነው።ስራቸው በጣም ያበሳጨኛል።የብዙ ሰዎችን ህይወት አመሳቅለዋል።ብዙ ትዳር ችግር ውስጥ ወድቆ ልጆች ተበትነዋል።ጠንቋዮች ርህራሄ የላቸውም።ብዙ ሰውም ሆነ ጋዜጠኞች ስለእነሱ መስራት ይፈራሉ።የሆነ ነገር ይደርስብናል ብለው ይሰጋሉ። በተደጋጋሚ የጠንቋይ ክስ ሲመጣ የሚሰጠው ለእኔ ነው።ስራውንም የምቀበለው በደስታ ነው።“

“ዋናው ምክንያቴ በእውነተኛው አምላክ ላይ ያለኝ እምነት ነው። ይህ ማለት ከሀጥያት የፀዳሁ ነኝ ለማለት አይደለም።ሁሉንም የሀጢያት አይነቶች የምፈጽም ደካማ ሰው ነኝ። ቢሆንም ሰይጣን በሀጢያቴ እያስፈራራ እንዲጫወትብኝ አልፈቅድለትም።ስለዚህ እኔ ጋር ሲደርስ ጉልበቱ ቄጤማ ይሆናል።ፕሮግራሙን ስሰራም የሚኖረውን ፈተና ስለማውቅ በደንብ ጸልዬ ነው።ስሰራም በሚያስተምር መልኩ ነው። በጠንቋይ መገዛት ምን ያህል ሞኝነት መሆኑንም በሚገልጥ መልኩ እሰራዋለሁ።ብዙዎች ሊያስፈራሩኝ አለፍ ሲልም በገንዘብ ሊደልሉኝ ሞክረዋል።ግን ፍጹም አልቻሉም።የስኬቴም ምስጢር ይሄ ነው።“

“ሰይጣን ነጻ ስጦታ የለውም።ገንዘብ ሰጥቶ ሰላምህን ይወስዳል።ሀብት ሰጥቶ ትዳርህን ያፈርሳል።ጥሩ ስራ ሰጥቶ በረከትህን ይቀማሀል።ይሄ ቀድሞ ስለገባኝ በእነዚህ ነገሮች ስለመሸነፍ አስቤ አላውቅም።ከሶስት በላይ የሆኑ ገንዘብ ቲፎዞ ሀብት ጉልበት የነበራቸው ጠንቋዮችን ፕሮግራም ሰርቻለሁ።ብዙዎች በእኔ ፕሮግራም ተምረው ነጻ ወጥተዋል።በዚህም እጅግ እኮራለሁ።ዛሬም ያለምንም ስጋት የምኖረው ውስጤ ምንም ፍርሀት ስለሌለ ነው።“ ይላል ሰለሞን አምባቸው በአንድ ወቅት ከሀገር አልፎ በአለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጽያዊያንን ጉድ አስኝቶ ስለነበር ስራው ሲያወራ።

ስራና ፈተና

ሰለሞን አደገኛ ውሳኔ በሚሹ ቦታዎች ሄዶ የሰራና ስራን የሚያስቀድም ጋዜጠኛ ነበር። በተለይ አደገኛ የወንጀል ታሪኮችን በምርመራ መልክ በመያዝ በስራዎች ተስፋ ሳይቆርጥ እስከ መጨረሻው ይዞ በመሄድና የፍርድ ውሳኔያቸውን ለህዝብ በመግለጽ ይታወቃል።

ለነፍስ አደገኛ ከሆኑ ወሮበሎች እና የወቅቱ አደገኛ ከነበሩ የሜርኩሪና የፎርጅድ ዶላር ነጋዴዎች ጋር ህይወቱን ለስራው አሳልፎ ሰጥቶበታል፤ ዛቻና ማስፈራርያዎች ስራውን ወደኋላ የሚመልሱ ቢሆንም ሰለሞን ግን ያን ሁሉ በጥናት አልፏል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ

“የህዳሴው ግድባ ስራ ከተበሰረ ገና አንድ አመቱ ነው። የአዲስ አመት ልዩ ዝግጅት እዚያ ለመስራት እቅድ አወጥተን ተፈቀደልን። በወቅቱ የትኛውም ፕሮግራም ይህን አላሰበም።ቀድመን ፕሮግራም ለመዘርጋት ወደ ቤኒሻንጉል ያመራነው እኔና የፕሮግራሙ አዘጋጅ ቅኑ አለቃዬ ኮማንደር መኮንን ጋርጠው ነበር። ፋማጾሬ ምትባል ስፍራ ስንደርስ መኪናችን ምን እንደነካት ሳናውቅ ከገደል ገደል መገለባበጥ ጀመረች።ስንቴ እንደተገለበጠች ባናውቅም በተአምር ነፍሳችን ተረፈ። ከሁሉ በጣም የተጎዳሁት እኔ ብሆንም ጉዳቴን ችዬ ፕሮግራሙ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ።“የሚለው ሰለሞን ያስገረመውን እንዲህ ይገልጻል።

“ግድቡን ኮንትራት ይዘው የሚሰሩት የሳሊኒ ዋና ሀላፊ አስጠራኝና “ምንድን ነው የምትሰሩት?“ ብሎ ጠየቀኝ።

እኔም “አዲስ አመት ስለሆነ ሰራተኛውን ቢያንስ ለግማሽ ቀን እንኳን አደረሳችሁ ብለን በሙዚቃ ለማዝናናት ነው “አልኩት።

ስራ አስኪያጁ በመገረም እያየኝ በሀሳቡ በጣም ተደነቀና የሚከተለውን አለኝ።

“የሀገራችሁ ፖሊስ በጣም ሀብታም ነው ማለት ነው“ ሲለኝ ደነገጥኩና

።እንዴት?“ ስል ጠየኩት።

“ሁሉንም ሰራተኛ ለግማሽ ቀን ስራ ለማስፈታት ቢያንስ ፖሊስ ለሳሊኒ 20 ሚሊዮን ብር ሊከፍለኝ ይገባል“ብሎኝ እርፍ።የምለው ጠፋኝ። በእርጋታ ሀሳባችን ማስረዳት ጀመርኩ።የኋላ ኋላ ስራ አስኪያጁ ሀሳቤን ተረድቶ እረፍት የሆኑ ሰራተኞችን ብቻ አዝናንተን ተመለስን“ሲል አውግቶናል።

የዋህ ጊዜ

“የኛ ጊዜ የዋህ ዘመን ነበር።አንድ ተጠርጣሪ በተያዘ ማግስት ቃለ መጠይቅ ማድረግ ነበር።አሁን ሳስበው ለራሴ ንስሀ እገባለሁ።ቃለ መጠይቅ አድርገን ካቀረብነው በኋላ ነጻ ይውጣ ይታሰር ብዙ አያስጨንቀንም ነበር።የብዙ ሰው ህይወት አበላሽተናል ብዬ አስባለሁ።በኋላ ግን ተውነው።ወንጀለኛ ተብሎ ካልተፈረደበት በስተቀር አያቀርብም።“

“ሌላው የሚያስቀኝ ነፍሰ ገዳይን ቃለ-መጠይቅ ስናደርግ የገደለበትን መሳሪያ የምናስይዘው ጉዳይ ነው።መጥረቢያ ከሆነ መጥረቢያውን አስይዘን ቆንጨራም ቢላዋም ጠመንጃም ከሆነ አስይዘን ነው የምንጠይቀው።ሰውዬው የመረረው ነፍስ ያጠፋ ነው ።በያዘው መሳሪያ ቢለንስ። አስበነው አናውቅም።አሁን ስናስበው ያስቀናል።የዋህ ጊዜ።የጋዜጠኝነት ሙያና ስነምግባርን ስናውቅ ግን ሁሉንም ተውነው ።ሥራችንንም በእውቀት መስራት ጀመርን።

የማይረሳቸው አስገራሚ ወንጀሎች

በ 18 አመታት የፖሊስና ህብረተሰብ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ቆይታው አያሌ አስገራሚና አስቂኝ እንዲሁም የሚያስደነግጥ ወንጀሎችን ሰምቷል ዘግቧልም።ከነዚህም መካከል

 ደንበኛውን ገድሎ ሬሳቸው ላይ መደብ ሰርቶ ለአመታት መደቡ ላይ ሲቅም የነበረው ጠንቋይ

 አባቱ በመኪና አደጋ ሞተውበት በበቀል ተነሳስቶ ገዳዩ መኪና ከቆመበት ፖሊስ ጣቢያ በሌሊት ተደብቆ ገብቶ መኪናውን አመድ ስላደረገው ጎረምሳ

 ሰው ቤታቸው ቀብረው፤ የቀበሩትን ረስተው ቤቱን ሽጠው ገዢው ቤቱን ለማደስ ሲቆፍር ከ 13 አመታት በኋላ የተያዙት ባልና ሚስት ጉዳይ

 አስገራሚው የሎተሪ አዟሪውና የሎተሪ ቆራጩ ጉዳይ፤መኪና ደርሶት አልሰጥህም የተበላው ወጣት

 ሚስቱን እና ውሽማዋን በብረት ዘነዘና የገደለውና አንድ ወቅት በከተማው አነጋጋሪ የነበረው የወተት አላቢው ታሪክ

 ባለስልጣን ነኝ እያለ ባለስልጣናትን ሳይቀር እያሰረና እየሾመ የከረመው ወንጀለኛ

 አሜሪካ እወስዳችኋለሁ እያለ ከ14 በላይ ሴቶችን በተለያየ ክልሎች ስላገባው ወጣት

 በሳር የሰሩትን አስከሬን በአዲስ አባባ አደባባዮች አጋድመው የሰው ሀገር ሰው አስከሬን መሸኛ እያሉ ሲያጭበረብሩ ስለተያዙ ከሳሾች

 ጎማ ሰርቆ ሲያንከባልል ከእጁ አምልጦ የፖሊስ ጣቢያ ግቢ የገባበት ሌባ ታሪክ

 በር ሰብሮ ገብቶ ማር ሲልስ ሰክሮ የተገኘው ሌባ

 ሞቷል ተብሎ በቤተሰባቸው እድር ተበሉ በኋላ ስለመጣው ወጣት

 አገባሻለሁ ብሎ ድግስ ካስደገሳት በኋላ የውሀ ሽታ ስለሆነውና ቤቱ ሲኬድ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ስለተገኘው ደፋር አባወራ……….እጅግ ባለ ብዙ ገጠመኝ ነው ሰለሞን።

ባለ 3 ማስተርስ

ሰለሞን ለትምህርት ያለው ፍቅር መነሻው ከቁጭት ነው።እንደ አጀማመሩ ቢሆን ሩቅ መድረስ ይችል እንደነበር ይናገራል።በጊዜ ከምስኪን እናቱ መስተቀር ሁነኛ ረዳት ስላልነበረው የዩኒቨርሲቲ ውጤት እንዳይመጣለት ይጸልይ እንደነበር ይናገራል።ፀሎቱን ፈጣሪ ሰማና ውጤት ሳይመጣለት ቀረ።ይሁን እንጂ ጋዜጠኛ ከሆነ በኋላ ትምህርቱን በዲፕሎማ አሟሸ።ቀጠለ ዲግሪ ማስተርስ።

 መጀመሪያ ከአዲስ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነትና ኮምዩኒኬሽን ማስተርስ ዲግሪውን አገኘ።

 ሁለተኛ ከኢትዮጽያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሊደር ሺፕና ጉድ ገቨርናንስ ለሁለተኛ ጊዜ ማስተርስ ዲግሪውን አገኘ

 ለሶስተኛ ጊዜ/ይህ መጠይቅ በተደረገበት ወቅት/ በኢትዮጽያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት በማስተርስ ዲግሪ በመማር ላይ ይገኛል።

“ዛሬ ወትሮ እየጓጓሁለትንና ያጣሁትን ትምህርት ተበቅየዋለሁ።እስካለሁ ድረስ ትምህርት አላቆምም።ለኔ መማር ደስታን ከሚፈጥሩልን ተግባራት መካከል ነው።“እሱ እንደተናገረው።

ሰለሞን አምባቸው አሁን

“ሁለት ጸጉር ያለው ጋዜጠኛ ሲበር ወደ ሚዲያው እመለሳለሁ የሚለው ጋዜጠኛ ሰለሞን አምባቸው በፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።

ሰለሞን አምባቸው ከሞዴል ባለቤቱ ከወይዘሮ ኤደን አብዱ ጋር በትዳር ተጣምሮ የሁለት ወንድና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *