ቴዎድሮስ ገብሬ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)

ቴዎድሮስ ገብሬ (ተ/ፕ) በዓለም ታላላቅ የምርምር መጽሔቶች ላይ በርካታ ጥናቶችን ለንባብ ያበቃ የሥነ-ጽሁፍ ተመራማሪና መምህር ነው፡፡ ስመ ጥር በሆኑት “ብላክ ዌል”፣“ካላሉ”እና “ኖርዝ ኢስት አፍሪካን ስተዲስ” ካቀረባቸው ምርምሮች በተጨማሪም በአማርኛ ቋንቋ “በይነ-ዲስፕሊናዊ የሥነ-ጽሑፍ ንባብ” የሚል መጽሐፍና በርካታ ጥናቶችን ለአንባብያን አቅርቧል፡፡

 ቴዎድሮስ ከአገሩ ሳይወጣ በጥልቅ ንባቡና ምርምሮቹ ጆናተናን ከለርና ሜሪ ሮዛሪዎን ከመሰሉ የዘመናችን የሥነ-ጽሁፍ ሊቃውንት አድናቆትን ያተረፈ ስኬታማ ኢትዮጵያዊ ምሁር ነው፡፡ 

በዚህ መነሻም ድርጅታችን ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሥነ-ጽሁፍ፣ በቴአትር ፣በፊልም እና በሚድያ ዘርፎች የተለየ አስተዋጽኦ  ያላቸውን ኢትዮጵያዊያን የሕይወት ታሪክ ለመሰነድ የጀመረው ፕሮጀክት አንድ አካል ሆኗል፡፡ ይህ ግን በቀላሉ የተሳካ አይደለም፡፡ ቴዎድሮስ ገብሬ (ተ/ፕ) እንደ አንድ መምህርና ተመራማሪ መገለጤ ባስተማርኳቸው ተማሪዎች ስኬትና በምሰራቸው ጥናቶች ከፍታ እንጂ በእኔ ሰዋዊ የሕይወት ጉዞ መሆን የለበትም የሚል ጽኑ ዕምነት አለው፡፡ይሁንና ማስረሻ ፈጠነ (ፕ/ር) ባደረጉት ጥረት በራሱም ባይሆን በተማሪዎቹና ባልደረቦቹ ምስክርነት የቴዎድሮስ ገብሬ የሕይወት ታሪክ እንዲህ ተሰንዷል፡፡

ተወዳጅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ዓላማችንን በመረዳት የዚህን ታዋቂ መምህርና ተመራማሪ የሕይወት መንገድ እንድንሰንድ ለተባበሩን ሁሉ ምስጋና ያቀርባል፡፡ 

ከቀድሞ የቴዎድሮስ ገብሬ (ተ/ፕ) ተማሪዎች አንዱ የሆነው ደራሲና ጋዜጠኛ ይነገር ጌታቸው/ማዕረግ/ የጽሁፉን አርትዖት በመሥራትና የመጣጥፉን ሁለተኛ ክፍል (አስተርዮ ቴዎድሮስን) ሙሉ በሙሉ በማዘጋጀት ላደረገው አስተዋጾ በእናንተ በአንባብያን ስም ክብረት ይስጥልን እንላለን፡፡

 በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ  የሥነ-ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት መምህር አገኘሁ አዳነ ድልነሣሁ የቴዎድሮስ ገብሬን ምስል በስኬች ሰርቶ ስላስረከበን ብቻ ሳይሆን በቴዎድሮስ ላይ ሀሳቡን ስለሰነዘረ ምስጋናችን ወደር የለውም፡፡ ወዳጃችን ሲሳይ ጫንያለውም የቴዎድሮስን ታሪክ በእንዴት ያለ መልኩ ማደራጀት እንዳለብን ጥልቅ ሀሳብ ስለለገሰን ሲስ ባለበት እናመሰግነዋለን፡፡  

ይህ ጽሁፍ በሁለት ክፍሎች የተዋቀረ ነው፡፡ ቀዳሚው በአብዮት ዘመን ተወልዶ አብዮት የታጠነውን የጨርቆሱን ብላቴና ያስታውሳል፡፡ ተማሪውንና መምሕሩን ቴዎድሮስን ይፈልጋል፡፡ሁለተኛው ክፍል ግን ከዚህ ይለያል፡፡ ሰዋዊውን መሠፈሪያ ትቶ ረቂቁን ምሑራዊ ፈለግ ይከተላል፡፡ በዓለም ዓቀፍ የምርምር መጽሔቶች ስሙ ስለሚጠቀሰው፤ሀሳቡ እንጂ እርሱ ስለማይታየው ቴዎድሮስ ያትታል፡፡ 

ዕዝራ እጅጉ (ዋና አዘጋጅ)

መልካም ንባብ፡፡

ኀሠሣ ቴዎድሮስ

ቴዎድሮስ ገብሬ ውልደቱ 1966 ዓ.ም ነው፡፡ ንጉሳዊው ሥርዓት በቃህ ተብሎ ወታደራዊው መንግሥት መጣሁ በሚልበት፤ የቀድመው ልማድ ተሽሮ አዲሱ ፍኖት በሚጠረግበት-ዘመን፡፡ ማሕበራዊ ምስቅልቅሉ፣ ነጭና ቀይ ጥለት የለበሰው የአገሬው ሽብር ሁሉ የትዝታው አካል ናቸው፡፡ በደም በተዋጀው የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ውስጥ አዲስ አበባ ጨርቆስ ሰፈር የተወለደው ቴዎድሮስ ብዙም ጨዋታ የሚስበው ታዳጊ አልነበረም፡፡ እስከ ዘጠኝ ዓመቱ ከእኩዮቹ ጋር እየዋለ ኳስ ቢጫወትም ኋላ ላይ ግን የጓደኞቹም መንገድ ግድ አልሰጠው፡፡ 

ይልቁኑ ልብ-ወለዶችን እያሳደደ ማንበብ ጀመረ፡፡ታሪክና ፍልስፍናን ይፈልስ ያዘ፡፡  ኳሱን ራቀ፤  ብሽሽቁን ሸሸ፡፡ የራሱን ዓለም በልኩ የሰራ መሰለ፡፡ ታናሽ ወንድሙ እንዳለ ገብሬ የቴዎድሮስ አብሮ አደጎች መጽሐፍቱ ናቸው ይላል፡፡

 ደስታውም ንዴቱም የሚቀዳው ከእነርሱ ነው፡፡ መጽሐፍት ያነባል፤ የራዲዮ ድራማ ያደምጣል፡፡ በልኩ የሚሟገተው ባያገኝም ከንባቡና ከማድመጡ ያገኛቸውን ጉዳዮች ይዞ ያወራል፡፡ እንዳለ ታላቅ ወንድሙን እንደ ልጅ ቤተ-ዘመድ ቤት እንኳን የመሄድ ፍላጎት ያልነበረው እንደሆነ ያስታውሳል፡፡“እኛ አውዳመትን አስመልክተን በየቤቱ ስንዞር እርሱ ፍላጎት አልነበረውም፡፡ በኋላ ጉትጎታው ሲበዛበት አክስታችን ቤት መሔድ ጀመረ፡፡ ለዚያውም እርሷ ቤት መጽሐፍት አለ ተብሎ!” 

የቴዎድሮስ ገብሬ ልጅነት ካለ መጽሐፍት የሚታሰብ አይመስልም፡፡ የታሪክ ተመራማሪውና ኀያሲው ብርሃኑ ደቦጭም በዚህ ሀሳብ ይስማማል፡፡ ብርሃኑና ቴዎድሮስ ትውውቃቸው የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ነበር፡፡  ደገኛ ቦታ ሲውሉ፡፡ ደገኛ የተባለው ሥፍራ ያየኔው ወመዘክር የአሁኑ ብሄራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሐፍት ኤጀንሲ ነው፡፡ሁለቱ ታዳጊዎች ከመንደራቸው ርቀው ይጓዛሉ፡፡ መሄዳቸው እንደ እኩዮቻቸው በኳስ ጨዋታ ሰፈራቸውን ለማስጠራት አይደለም፡፡ ማቅናታቸው እንደ አብሮ አደጎቻቸው ለውሃ ዋና አልያም ለድብድብ ሆኖ አያውቅም፡፡ ሰርክ ልማዳቸው ንባብ ነው፡፡ ከጨርቆስ ተነስተው ሼህ መንደፈርን አልፈው ብሄራዊ ይደርሳሉ፡፡ ሲያነቡ ውለው ስለ መጽሐፍት እያወሩ ሰፈራቸው ይመለሳሉ፡፡ 

ቴዎድሮስ  የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው ፃድቁ ዮሃንስ እና ፈለገ- ዮርዳኖስ  ትምህርት ቤቶች ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ዳግማዊ ምኒሊክ ፡፡ ታናሽ ወንድሙ “ልክፍት” ሲል የሚጠራው የቴዎድሮስ የንባብ ፍቅር የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኖም ከሰፈሩ ሲርቅ ባሰ እንጂ አልቀነሰም፡፡ እንዳለ እንደሚያስታውሰው ታላቅ ወንድሙ ለምሣ ተብሎ የሚሰጠውን ገንዘብ ጾሙን እየዋለ መጽሐፍት ይገዛበት ነበር፡፡ “በእርግጥ እንደቤተሰብ መጽሐፍ ከገዛሁ ጾሜን ብውልስ የሚለው የቴዎድሮስ ሐሳብ የሚደገፍ አልነበረም፡፡ ኋላ ላይ ግን አባታችን ነፃነቱን ሰጠው፡፡ ድንበሩን አከበረለት፤አስከበረለት፡፡” 

ብርሃኑ ደቦጭ የቴዎድሮስ የታዳጊነት ዘመን ንባብ ‘ይሄን መጽሐፍ አንብቤዋለሁ ለሚል ዝና  አልነበረም“ ይላል፡፡የትኛውን መጽሐፍ ለምን እና እንዴት ማንበብ እንዳለበት ገና በእዚያ እድሜው የሚያውቅ ጥንቁቅ ስለመሆኑም ያስታውሳል፡፡ በእርግጥም የታዳጊው ቴዎድሮስ ለንባብ መሸፈት የአንድ ወዳጁ ትውስታ ብቻ አይደለም፡፡ የረጅም ጊዜ ጓደኛው አብነት መንግሥቴ ትዝታ እንደውም ለፊት ፈገግታን ይለግሳል፡፡ “የበዓሉ ግርማ ኦሮማይ በዳግም ሕትመት ለአንባብያን ሲበቃ አዲስ አበባ በመጽሐፉ ወሬ ተመታች፡፡ 

ብዙዎች ተቀዳድመው ለመግዛት በየመደብሩ በር ተገኙ፡፡ ብላቴናው ቴዎድሮስም ያለችውን ገንዘብ ይዞ ሊገዛ ተሰለፈ፡፡ከመኻል ግን አንድ ያልጠበቀውን ድምጽ ሰማ፡፡ ዘበኛው ነው፡፡ “ተራ ይዘህ ልትሽጥ ነው አይደል ?! ውጣ” አለው፡፡ ታዳጊው ለራሴ ላነበው ነው ቢል የሚያምነው አላገኘም፡፡ ውጣ… ውጣ… ተባለ፡፡ እጅ አልሰጠም፡፡ ሰለፈኞቹም በትህትናውና በልጅነት ፊቱ ላይ ጨክነው አልጨከኑም፡፡ገዝቶ ወደ ቤቱ ሔደ፡፡” 

ቴዎድሮስ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ያጠናቀቀው በ1983 ዓ.ም ነው፡፡ ይሁንና ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከመግባቱ በፊት ለሦስት ዓመታት ያህል ንባብን ሕይወቱ አድርጎ ሊዘልቅ ሞክሯል፡፡በዚህ ወቅትም በሀገርአቀፍ ህዝብና ቤት ቆጠራ በረዳት ካሪቶግራፊነት እንዲሁም በአስተባባሪነት ተሳትፏል፡፡ ይህም ሆኖ ግን የትምህርቱን ነገር እርግፍ አድርጎ አልተወውም፡፡ በ1987 ዓ.ም የኮተቤ መምህራን ኮሌጅን ተቀላቀለ፡፡ምርጫው የማይጠበቅ አልነበረም፡፡ የልጅነት ሕልሙን ሊኖር የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ገባ፡፡

በኮሌጁ ለ4 ዓመታት አብሮት ያሳለፈው አብነት መንግሥቴ ቴዎድሮስ ኮተቤ የገባው እንደ ብዙዎቹ ተማሪዎች ሊማር ብቻ አልነበረም ይላል፡፡ ይልቁንስ ትልልቅ የሥነ-ጽሁፍ ድርሰቶችንና ኀልዮቶችን አንብቦ ስለነበር ብዙ ነገሮች ላይ መምሕራኑን መሞገቱን ያስታውሳል፡፡ 

“በኮሌጅ እያለን ባሉን እረፍት ጊዜያት አንዳንዴም ትምህርቱን እያስተጓጎለ ወደ ወመዘክር ቤተ-መጽሀፍት በመሔድ ከሚማረው ትምህርት ጋር ተያያዥነት በሌለው ንባብ ይጠመድ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡በዚህም ወቅት ንባቡ ታላላቅ የዓለም ሥነ-ጽሁፍ ስራዎችን፣ የፍልስፍ፣ የሥነ-ልቦና የካልቸራል አንትሮፖሎጅ እና ሌሎች የሒውማኒቲ እውቀት ዘርፎችን በወጉ አጥንቷል፡፡”

በይነ-ዲስፕሊናው የሥነ-ጽሁፍ አተያዩን በወጉ የገፈበት ከዚያ ወዲያ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የያኔው ቴዎድሮስ የአማርኛ ሥነ-ጽሁፍን በስነ-ልቡና ንድፈ ሐሳቦች በጥልቀት ለመመርመር ብዙ ጥሯል፡፡ ፍልስፍናዊ ሀሳቦችን እየተዋሰ ኢትዮጵያዊ ድርሰቶችን ለማጠየቅ የሔደበትም መንገድ ለእኩዮቹ ብቻ ሳይሆን ለመምህራኑም እንግዳ ሆኗል፡፡ቴዎድሮስ ወዲህ በክፍል ውስጥ ውጤቱ ተወዳጅና መነጋገሪያ መሆኑ ባይካድም የእርሱ ቀልብ ግን ከወመዘክር ለመራቅ አልተቻለውም፡፡ ከኮተቤ ብሔራዊ እየተጓዘ ለልጅነት ቤቱ ስብሃት ማድረሱን ቀጠለ፡፡ ለልብስና ጫማ የሚሠጠውን ገንዘብ መጽሐፍ እየገዛበት የንባብ አምሮቱን ሊቆርጥ ከጊዜው ጋር ነጎደ፡፡ 

ይኼኛው ቴዎድሮስ ተማሪና የተመራማሪነት አምሮት ያለው ብቻ አልነበረም፡፡ ይልቁኑስ ያደረ የደራሲነት ፍላጎቱም አብሮት ነበር፡፡ ግጥሞችንና አጭር ልብወለዶችን እየፃፈ ለጓደኞቹ ማስነበቡን ቀጠለ፡፡ ፀሐፌ-ተውኔትነቱም የቀደመ እንጂ አዲስ አልነበረም፡፡ በዚያ የአፍላነቱ ዘመን የቀድሞው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ከሰተብርሃን አድማሱን(ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች እኩዮቹ የተወኑባቸውን ቴአትሮች ጽፏል፡፡  ይህ ግን የራስ ፈለግን ለማሰስ የተሄደ እርቀት እንጂ መድረኮችን እየፈለጉ ከዝና ማማ ላይ ለመድረስ መታገል አልነበረም፡፡  ለዚህም ነው ቴዎድሮስ የአፍላነት ዘመን ድርሰቱ ተወዶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ለመድረክ ይብቃ ሲባል አልፈልግም የሚል አስገራሚ መልስ የሠጠው፡፡

እንዲህ ያለው የቴዎድሮስ በራስ ዛቢያ እየተንቀሳቀሱ ለቀሪው ዓለም ጀርባን መስጠት ብርቅ ጠባዩ አይደለም፡፡ በአፍላነቱ ዘመን ስብሃት ገብረእግዚአብሔርን እንደሚወደው የሚያውቁ ወዳጆቹ ስብሀትን አግኝተናል እናስተዋውቅህ ቢሉት  ”እኔ ጉዳዬ ከድርሰቱ እንጂ ከእርሱ አይደለም“ ሲል እምቢታውን ገልጿል፡፡ በጎልማሳነቱ ዘመንም በዓለም የሥነ-ጽሁፍ ጥናት ውስጥ ስሟ የገነነው ደራሲና ተመራማሪ  ሜሪ ሮዛሪዎ በምርምር ሥራው ተደማ፤አዲስ አበባ በመጣች ወቅት ልታገኘው ብትፈልግ ባለቤቴን ልልካት እችላለሁ እኔ ግን አይመቸኝም ሲል መልሷል፡፡

የዚህ አይገመቴ ጠባዩ ቁንጮ ግን ፓስፖርት ኑሮት አለማወቁ ነው፡፡ ለምን? ፓስፖርት ከያዘ በወዳጅ ዘመድ ግፊት ለሚያማልሉት የውጭ አገር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥ ሊገደድ ነዋ! ፍርሃቱም እሱ ነው፡፡ቴዎድሮስ ከኢትዮጵያ መውጣት አይፈልግም፡፡ እሱን ደግሞ በጋንቤላ መምህራንና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርነቱ ወቅት እንግሊዝ አገር የመማር ዕድል ይመቻችልህ ሲባል አልፈልግም ብሎ አረጋግጧል፡፡

ብርሃኑ ደቦጭ የረጅም ዓመታት ጓደኛውን ሲያስብ አንዱ የሚደንቀው ነገርም ይኼ ነው፡፡ ከአገሩ ሳይወጣ ፣የታላላቆቹን የምዕራቡ ዓለም ዩኒቨርስቲዎች ደጃፍ ሳያረግጥ በጥልቅ ንባቦቹ ብቻ ዘመኑን ዋጅቷል፡፡ በእርግጥም ቴዎድሮስ በአገሬው የሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ልማድ ውስጥ ብቻ ለማለፍ ሞክሮ ቢሆን ዛሬ የምናወራለት እርሱነቱ መፈጠሩ ያጠያይቃል፡፡ የአብነት ገለጻ ይበልጥ ግዙፍ ይነሳል፡፡ 

“በንባብ ውስጥ ራሱን ያገኘ፤ራሱን የሰራ እንጂ የቅድመ  ምረቃም ሆነ የድህረ ምረቃ ትምህርት ተሞክሮው በእውቀቱና በአስተሳሰቡ ላይ የጎላ ተጽዕኖ የፈጠሩበት ሰው አይመስለኝም፡፡ ገና የመጀመሪያ ዓመት የኮሌጅ ተማሪዎች ሳለን  ከሚቶሎጅ፣ከፍልስፍና፣ከሥነ-ልቡና፣ከአንትሮፖሎጂ እንደውም ለሥነ-ጽሁፍ ተዛምዶ ይኖራቸዋል ተብሎ ከማይታሰቡ  እንደ ፊዚክስ ካሉ ዲስፒሊኖች  ቴዎሪ ወስዶ ለሥነ-ጽሁፍ ማናበቢያና መተንተኛ ይጠቀም ነበር፡፡ ለምሣሌ የሠይፉ መታፈሪያን ግጥም በquantum Physics ንድፈ ሀሳብ ለመተንተን ሞክሯል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ቴዎድሮስ ቀድሞም ቢሆን የ literary interpretation  እና የ literary philosophy አተያይ እንደነበረው እማኝ ይሆናሉ፡፡ በአሁን ዘመን ሥራዎቹ ላይ ላቅ ይል ካልሆነ፡፡ …ገና የአንደኛና የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች እያለን የሚያነሳቸው ሥነ-ጽሑፋዊ ጉዳዮች ከበርካታ ዓመታት በኋላ በትላልቅ የሥነ-ጽሑፍ ጆርናሎች ላይ በዐቢይ ርዕሰነት ሲወሱ ማየቴም ይህንን ድምዳሜዬን ይበልጥ ያጠናክረዋል፡፡” 

የቴዎድሮስ የኮሌጅ ቆይታ ከፍ ተብሎ እንደተጠቀሰው በጥልቅ ንባብ ብቻ የታጀበ  አይደለም፡፡ በትምህር ቤት በሚሰጡት የቤት ሥራዎች ላይ ያቀርባቸው የነበሩ ጽሁፎቹ ዛሬም ኪናዊ ኅሩይ ናቸው፡፡ማስረጃችን የሦስተኛ ዓመት ተማሪ እያለ ያቀረበው ”ተርም ፔፐር“ ነው፡፡ ይህ ጥናት በአዳም ረታ “ማኅሌት” መድብል ውስጥ ከተካተቱ  አጫጭር ታሪኮች አንዱ የሆነውን “ኤልዛቤል” በመውሰድ ከዘመናዊ አተራረክ አንፃር ቃኝቷል፡፡ 

ጽሁፉ በጊዜው ለመምህሩ ብቻ  የቀረበ ቢሆንም ኋላ ላይ ግን ትኩረትን ሳበ፡፡አስተውሎቱና ኀሰሳው ከፍ ያለ  ነበረና በ1992 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ጥናት ሊቃውንት በጋር ባሳተሙት የምርምር መጽሔት ላይ ተካተተ ፡፡ 

ቴዎድሮስ የኮተቤ ተማሪነቱ ቆይታው ከፍ ብለን የጠቀስነውን ዓይነት ዘመን ተሻጋሪ ሥነ-ጽሁፋዊ ልህቀት እንዳለው ቢያረጋግጥም እርሱ ግን የሚረካ አልነበረም፡፡  ወደ መጀመሪያ ድግሪ ማሙያ ጽሁፉ እንለፍ ፡፡ ይህ  ጥናቱ   በዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ” ልብ ወለድ “እንደወረደ” (stream of consciousness) ሥነ-ጽሑፋዊ አንፃር  ላይ ያተኮረ ነው፡፡ እዚህ ላይ በሥራውና በራሱ ላይ የነበረውን መተማመን የሚያሳይ አንድ ነገር እንጥቀስ፡፡ ቴዎድሮስ ጥናቱን ካጠናቀቀ በኋላ ክፍለ-ትምህርቱ ፈታኝ መምህራንን በሚመድብ ሰዓት ጥያቄ አነሳ፡፡ የእኔን መመረቂያ ጽሁፍ የሚፈትኑ ሰዎች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መሆን አለባቸው አለ፡፡ 

ሙግቱ ከውጤት ይልቅ ለማወቅ ያለውን ጉጉት ያሳያል፡፡ ቴዎድሮስ በሚያውቁትና በሚያውቃቸው መምህራን ቢፈተን ከፍተኛ ውጤት እንደሚያገኝ እርግጥ ነበር፡፡ እርሱ ግን ከውጤቱ በላይ ያስተማሩት መምህራን ደጋግመው የሚያነሷቸውን ትላልቅ የሥነ-ጽሁፍ ሰዎች በእዚያ ዕድሜው ለመሞገት ጓጓ፡፡ ይሁንና ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በመሆኑም ብዙዎች እንደጠበቁት የኮተቤ ቆይታውን ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ደመደመ፡፡ 

ከዚህ በኋላ ያለ ሕይወቱ ወደ ጋምቤላ ይወስደናል፡፡ የጋምቤላ መምህራንና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህር ሆነ፡፡የወዳጆቹ ስጋት አንጋፋ መምህራን ያሉት የኮተቤ መምህራን ኮሌጅ የጠበበው ቴዎድሮስ ገብሬ በጋምቤላ የሚኖረው ቆይታ እንዴት ይሆናል? የሚለው ነበር፡፡ እርሱ ግን ብዙም ግድ አልሰጠውም፡፡ ከዓለሙ እንደራቀ ባሕታዊ በመጽሐፍት ብቻ ተከቦ በዚያች የበርሃ ገነት ኑሮን ለመደ፡፡ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንሲ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተርና የቀድሞው የቴዎድሮስ ገብሬ ተማሪ ወንድወሰን አንዱአለም ወቅቱን እንዲህ ያስታውሰዋል፡፡

‹‹…..በዚያ ግቢ ውስጥ ከብዙዎች ጋራ የማይገናኝ፤በእዚያ አስቸጋሪ በረሃ በጣም ፈታኝ በሆነ የአየር ፀባይ ውስጥ ያለ ማቋረጥ የሚያነብ፤በሌላ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ጭምር ስሙ የሁል ጊዜ መነጋገሪያ የሆነ፤ምሽት በሆነና  ስለ አስተማሪዎች በተነሳ ቁጥር ስሙ እየተነሳ የረጅም ሰዓት አጀንዳ የሚሆን  አንድ ሰው ነበረ … ቴዎድሮስ ገብሬ የሚባል፡፡›› ይላል ወንድወሰን

የጋምቤላው “ባይተዋር” እንደ ሌሎች ባልደረቦቹ የባሮ ወንዝ  ነፋሻማ ዓየር አላጓጓውም፡፡ ዛፍ ስር ተቀምጠው ካርታ እንደሚጫወቱት፣ስስ ልብስ ለብሰው በብስክሌት እንደሚቀዝፉት እኩዮቸ ሊሆን አልዳዳውም፡፡ ይልቁኑስ በእዚያ በርሃ ሥነ-ጽሁፍን ሊያጠምቅ እንደመጣ “ባሕታዊ” ማስተማር ጀመረ፡፡ ተከታይ አላጣም፡፡ ብዙዎች ስለ ሥነ-ጽሁፍ ለማወቅ  ጉጉት አደረባቸው፡፡ 

በሥፍራው ከነበሩት “ደቀ-መዛሙርት” አንዱ የሆነው ወንድወሰን አንዱአለም ቴዎድሮስ የሥነ-ጽሁፍ መምህር ቢሆንም ዝናው ግን ከክፍለ ትምህርቱ ከፍ ያለ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ “በግቢው ተማሪዎች፣ በአካባቢው ነዋሪዎች፣ በክልልና በከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጭምር የሚወደስ የሚከበርና የሚፈራ የብዙ ጊዜ አጀንዳ የሆነ ሰው እንደነበር እኔ ምስክር ነኝ ”ይላል፡፡ “ብዙዎች በእርሱ በመማራቸው ራሳቸውን እንደ እድለኛ ይቆጥራሉ፡፡ ዛሬም ድረስ  በተለያየ ደረጃ ላይ ሆነው ስሙን ሲያነሱት መስማትም የተለመደ ነው”፤ሲልም ይደመድማል፡፡ ፡ 

የበርኻው የሥነ-ጽሁፍ መምህር ሕይወቱ አማናዊ ነው፡፡ በእርሱ ውስጥ ዛሬ ለነገ መሸጋገሪያ ብቻ አይደለችም፡፡ ጋምቤላ ሁኖ ስለነገው ደጋግሞ ማሰቡ ባይቀርም መምህርነቱን ግን ወዶታል፡፡ ኮተቤ ላይ ለተለየው ወዳጁ ይፅፍለት የነበረው ደብዳቤም ይህን ያረጋግጣል፡፡ ቴዎድሮስ ለአብነት ይልካቸው በነበሩ ደብዳቤዎቹ ላይ ተማሪዎቹ ለውጥ እያመጡለት መሆኑን ፈተናውንና ውጤታቸውን ኮፒ እያደረገ በመላክ ደስታውን ይገልጽ ነበር፡፡ ከአብነት ትውስታ ጥቂት እንዋስ፡፡ ”ቴዎድሮስ ማስተማር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለተማሪዎቹ ፍጹም ክብር አለው፡፡ ይህ ማለት ሰፊ ዝግጅት ከማድረግ አንስቶ ለተማሪዎቹ ሳይሰስት ያለውን ሁሉ እያካፈለ በሚኖራቸው ውጤት መደሰትን ይጨምራል ፡፡“ 

በእርግጥም እንዲህ ያለው  የመምህሩ ቴዎድሮስ ገብሬ ጠባይ በእርሱ ሥር ያለፉ ተማሪዎቹ ሁሉ ትዝታ ሳይሆን አይቀርም፡፡  “በይነ-ዲስፕሊናዊ የሥነ-ጽሁፍ ንባብ” የተሰኘውን  መጽሐፍ ካነበበ በኋላ ለሥነ-ጽሁፍ ጥናት እጁን የሰጠው የአለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዳይሬክተሩ አገኘሁ አዳነ የስድስት ኪሎን ደጃፍ ከረገጠ በኋላ በሩቅ ያወቀውን ሰው በቅርብ ሲያገኘው የተሰማውን ስሜት እንዲህ ይገልፃል፡፡ “ሰውዬው አዋቂ ብቻ ሳይሆን ስስት የሌለበት፣ ጥንቅቅ ያለ ምሑር፣ የተማሪን ጥቂት ጥረት በደግነት አግዝፎ የሚያበረታ አባት መሆኑን እመሰክርለታለሁ።” የአገኘሁን አስተያየት ሌላው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አንጋፋው የቴአትር መምህር አሰፋ ወርቁም ይጋራዋል፡፡ 

የሥነ-ፅሁፍ ዕውቀቱ ያስገርማል፡፡ የማስተማር ዘዴው ለተማሪዎች ከፍ ያለ ነፃነትን የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ በየሳምንቱ በሚሰጣቸው የቤት ሥራዎች ብቁ እንድንሆን ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል፡፡ ቴዎድሮስ ለእኔ የስነ-ፅሁፍን ምንነት ለመረዳት፣ አቅጣጫዎችን በይበልጥ እንዳውቅ፣ ያደረገኝ ሰው ነው፡፡ 

የቀድሞ ተማሪው ይነገር ጌታቸው ቴዎድሮስ ማሰብን የሚያበረታታ የተለየ መምህር እንደሆነ ያስረዳል ፡፡ “የአገሬው ዘመናዊ ትምህርት ከሞላ ጎደል የሰጠሁህን ሰፍረህ መልስ  የሚል ”ብድራዊ“ መንገድን የሚከተል ነው፡፡ እርሱ ግን ለጠየቀው ጥያቄ ምላሹ እውነትም ይሁን ሀሰት እንዴት? የሚለውን ጉዳይ ተማሪዎቹ እንዲያስረዱት ያበረታታል፡፡ይነገር መምህሩን ሲያስብ የፈላስፋው ዘረዓያቆብን አባባል ይስታውሳል፡፡ ”ትምህርት ያልተሟላን ሰውነት መሙያ ከሆነ፤ ለእሱ ተግባር  በልኩ የተፈጠረው  ቴዎድሮስ ገብሬ ነው“፤ ይላል፡፡ 

ብርሃኑ ደቦጭ ቴዎድሮስን ጎበዝ መምህርና ብርቱ ተመራማሪ ብቻ ሳይሆን የተማሪዎቹን ስኬት እንደራሱ የሚቆጥር ደግ ሲል ይጠራዋል፡፡ “ያስተማራቸው ልጆች ጥሩ ውጤት ካመጡ እዚያው እንዲቀጠሩ ብዙ ይጥራል፡፡ በዚህ ብቻ ግን አያቆመም፡፡ ለአዳዲስ ባልደረቦቹ መብትና ጥቅምም የእርሱን ያህል የሚታገል የለም፡፡”የመምህሩ ቴዎድሮስ አስተዋጾ በእርግጥም በመማሪያ ክፍል ብቻ የሚሰፈር አይደለም፡፡

የሚዲያ ባለሙያው ዘካርያስ ብርሃኑ ጎበዙም ሆነ ሰነፉ ተማሪ ስለቀድሞ መምህሩ በአድናቆት የሚያወራው አንድ ነገር ስለመኖሩ ይገልፃል፡፡  እሱም ዕውቀትና መልካምነትን አጣምሮ መያዙ ነው፡፡  የጋምቤላ ተማሪውና የዛሬው ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊ ወንድወሰን አንዱአለም ምስክርነትም ከዚህ ጋር ይስማማል፡፡ ወንድወሰን ዲፕሎማውን ከጨረሰ በኋላ የሥራውን ዓለም አሐዱ ብሎ የጀመረው በጋምቤላ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባለች አነስተኛ የገጠር ቀበሌ መምህር በመሆን ነበር፡፡ ይሁንና የቀድሞ መምህሩ ያለውን ሥነ-ጽሁፋዊ መረዳት በወጉ ያውቅ ስለነበር በቻለው አቅም ሁሉ ሊረዳው ደፋ ቀና ማለቱን ቀጠለ፡፡ እንዲማር አብዝቶ ጎተጎተው፡፡ 

አንዱአለምም ይሁንታውን ሰጥቶ በጂማ ዩኒቨርስቲ የክረምት መርሃ ግብር ለመማር ተመዘገበ፡፡ ቴዎድሮስ ግን ለተሻለ ነገህ ወደ አዲስ አበባ መጥተህ አድቫንስ ስታንዲንግ ብትማር ይሻላል አለው፡፡ ምክሩ ለማለት ያህል ብቻ አልነበረም፡፡ መምህሩ ለራሱ ከማትበቃው ደሞዙ ላይ ለትራንስፖርት  ልኮ የቀድሞ ተማሪውን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዲመዘገብ ረዳው፡፡ አላበቃም፡፡ ትምህርት ከጀመረም በኋላ የኪስ ገንዘብ እየሰጠ አስተማረው፡፡ ዛሬ ወንድወሰን የቀድሞ መምህሩን አሁን ለደረሰኩበት ደረጃ ያደረሰኝ ሌላኛው አባቴ ነው ይላል፡፡

የቴዎድሮስ እንዲህ ያለው ደግነት በተማሪዎቹ ውስጥ ጎልቶ ይስተዋል እንጂ ለሚያውቁት ሁሉ ግን የተለመደ መሆኑን የረጅም ጊዜ ወዳጁ ብርሃኑ ደቦጭ ይናገራል፡፡ እማኝ የሚጠራው ራሱን ነው፡፡ “ባንድ ወቅት ስልኬ እክል ገጥሞት ለተወሰነ ጊዜ ብጠፋበት አዲስ ስልክ ገዝቶ ሲፈልገኝ አገኘሁት”፤ይላል፡፡ ተማሪው አገኘሁ አዳነም በሕይወት ውጣውረድ ውስጥ ሁሉ አብሮ የሚደክም እውነተኛ ወዳጅ ይለዋል፡፡   

ቴዎድሮስ ገብሬ በጋምቤላ መምህራንና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሰፊ ተቀባይነትና አንቱታን ቢያተርፍም እርሱ ግን ራሱን ለማሳደግ የበርሃዋን ገነት መሰናበት ነበረበት፡፡ በመሆኑም በ1995 ዓ.ም ሁለተኛ ዲግሪውን ለማጥናት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ተቀላቀለ፡፡አንጋፋዎቹ መምህራን አሁንም ከጠያይሞቹ ሕንፃዎች ስር አልጠፉም፡፡ዮናስ አድማሱ (ዶ/ር) ስመ ገናና ናቸው፡፡ ፍቃደ አዘዘ(ዶ/ር) ዘመናትን ከኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ጋር እንደ ጅረት ተጉዘዋል፡፡

ቴዎድሮስ በጋምቤላ ቆይታው የመጣለትን በእንግሊዝ አገር የመማር ዕድል አንዱንም ያሳለፈው የኮተቤ መምህሩን  ማስፈራሪያ ተቋቁሞ እንደሚገኝ ለማሳየት ነበር፡፡  የመጀመሪያ ዲግሪ መመረቂያ ጽሁፍ አማካሪው ተማሪውን ሲሰናበተው   ”አንተ ጎረምሳ በዚህ ጥጋብህ ከቀጠልክ እነዚያ ሽማግሌዎች ይሰብሩሀል ተጠንቀቅ አለው፡፡“የቅኔው ፍች የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አንጋፋ  የሥነ-ጽሁፍ መምህራን ለእንዲህ ያለው ድፍረትህና ልማድ አፍራሽነት ቦታ የላቸውም ተጠንቀቅ የሚል ነበር፡፡ ወቅቱ ደረሰና ሁለቱ ወገኖች ተገናኙ፡፡“ሰባሪና ተሰባሪ” ተፋጠጡ፡፡

ዮናስ አድማሱ(ዶ/ር)የተማሪያቸውን የቴዎድሮስ ገብሬን ማንነት ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ ወደዱት፤እንዲያሻው እንዲያስብ እንደፈለገው እንዲሞግት ዕድሉን ሰጡት፡፡ እርሱም አከበራቸው፡፡ የተማሪና መምህር ግንኙነቱ በጦፈ ክርክር ተተካ፡፡ ትናንት “ሰባሪህ” ይሆናሉ የተባሉት አንጋፋ መምህራን በምርቃቱ ሰሞን እዚህ ቅር አሉት ፡፡ 

ዮናስ ጠንከር ያለ ምስክርነት ፃፉ፡፡ ፍቃደ አዘዘ(ዶ/ር) ከጎኑ ቆሙ፡፡ ይሁንና በተቋማዊ አሰራር ችግር ምክንያት የሁለቱ ምኞት በቶሎ የሚደርስ አልሆነም፡፡ ዮናስ ተበሳጩ፡፡ ሥራዬን እለቃለሁ ብለው ተቆጡ፡፡  ፍቃደ አዘኑ፡፡ ልጁን ማጣት የለብንም ብለው ተሟገቱ፡፡አምሮታቸው ትክክለኛ ተተኪን ፍለጋ ብቻ አይመስልም፡፡ ይህ ሰው ለነገው የኢትዮጰያ ሥነ-ጽሁፍ ጥናት አስፈላጊ እንደነበር እርግጠኞች ነበሩ፡፡ አሰልቺ የመሰለው ውስጣዊ ክርክር ከዘጠኝ ወራት በኋላ እልባት አገኘ፡፡ቴዎድሮስ ገብሬ በአገሪቱ ስመ-ጥር ዩኒቨርስቲ የሥነ-ጽሁፍ መምህር ሊሆን ጉዞ ጀመረ፡፡    

እዚህ ላይ ግን በኮተቤ ከነበረውም በላይ ያወዛገበውን  የሁለተኛ ድግሪ ማሟያ ጥናት ሳያነሱ ማለፍ ንፉግነት ነው፡፡   ንትርኩ ልማድ ከማፍረሱ ነበር፡፡ የተመረጡ የአማርኛ ልብወለዶችን ከርዕይ መነጠቅ አንፃር ሲተነትን ግርታው ናረ፡፡ ትልልቅ የፍልስፍና እና የሥነ-ልቡና ንድፈ ሀሳቦችን ተመርኩዞ ድርሰቶቹን መፈተሸ ያስኬዳል አያስኬድም ተባለ፡፡ዘገየ እንጂ ወደ ሰፊው አንባቢም መድረሱ አልቀረም፡፡ የሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጥናቱን ያካተተው “በይነ-ዲስፕሊናዊ የሥነ-ጽሁፍ ንባብ” መጽሐፍ በ2001 ዓ.ም ለንባብ ሲያበቃ ዝምታ የዋጠው የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ጥናት አንዳች ነገር እንደወደቀበት ተናወጠ፡፡ 

ጋዜጣ ላይ የክርክር አጀንዳ ሆነ፡፡አድናቆቱም ዘገየ እንጂ አልቀረም፡፡ የአማርኛ ሥነ-ጽሁፍ ጥናትን ቀያሪነቱ ታወጀ፡፡ ቴዎድሮስ በእዚህ ሥራው ላይ ዮናስ አድማሱን አልዘነጋቸውም፡፡ “ተቀመጥ በወንበሬ ተናገር በከንፈሬ ያለከኝ አንተን አመሰግንሃለሁ ”ብሎ ስብሃት አደረሰ፡፡ አላቆመም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተነባቢ በሆነው የምርምር መጽሔት ላይ ጥናቱ ሲታተምም የአማርኛ ሥነ-ጽሁፍ ባለውለታውን- ዘከረ፡፡ 

“በይነ-ዲስፕሊናዊ የሥነ-ጽሁፍ ንባብ” መጽሐፍ የተለያዩ የጥናት መስኮችን ያጎራበተና አንዱን ከአንዱ ያዋደደ ነው፡፡ የሥነ-ሥዕል መምህሩ አገኘሁ አዳነ እንደሚለው ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ብቻ ሳይሆን ለዘመነኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ሥዕልም ውለታን ትቷል፡፡ “የስድሳዎቹ የዘመን ምልክቶች እነ ሶሎሞን ደሬሳ፣ ክፍሌ ብጽአት፣ ግርማ ኪዳኔ፣ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር እና በሰባዎቹ ግድም ደግሞ እነ ስዩም ወልዴ የደከሙበትን ነገረ-ሥዕል በምዕተ ዓመቱ መባቻ ቴዎድሮስ ገብሬ የካሰው [የሚክሰው] ይመስላል፡፡” የአገኘሁ ምሥክርነት አላበቃም፡፡ 

የሥነ ሥዕል ዓለም ሓቲታዊ አንጻር ባለቤት ቸግሮት ብቅ ጥልቅ በሚሉ የጊዜው ጥራዝ ነጠቅ “ሙያተኛ ነን” ባዮች ሲወጣ ሲወርድ፣ ቴዎድሮስ ገብሬ የተባለ መፍትሄ እንደመጣለት የሚመሰክሩ፣ በሥነ ሥዕል ጉዳይ ላይ የተሠሩ የቅርብ ጊዜ ጥናቶቹ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። “አካል በሥነ-ጽሑፍ ውስጥ”፣  “የነገሮች መቃ(የ)(ለ)ጥ፣ የበቀለ አሻራዎች” እና “በቀለ መኰንን በብሔራዊ ትዕምርት ፍለጋ ውስጥ” የሚሉት መጣጥፎችም ለእዚህ ጠንካራ አብነት ይሆናሉ፡፡ 

የቴዎድሮስ ከሥነ-ጽሁፍ ያለፈ አስተዋጽዖ (በቀጣዩ ክፍል በስፋት ተዳሷል) በመገናኛ ብዙሃንም ላይ ያረበበ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቲቪ መዝናኛ ቻናል ሥራ አስኪያጁ ዘካርያስ ብርሃኑ የቀድሞ መምህሩ ስለራሱ አያውራ እንጂ ተማሪዎቹ ግን በኢትዮጵያ ሥነ/ኪነ-ጥበብ ውስጥ የጎላ አስተዋጾን እያበረከቱ ነው ይላል፡፡ ቴዎድሮስም የዳር ተመልካች አለመሆኑን ይጠቅሳል፡፡ ለዚህ ደግሞ እማኙ ዘካሪያስ በኃላፊነት የሚመራው ጣቢያ “ፍቅር እስከ መቃብር” ልብወለድን ወደ ቴሌቪዥን ድራማ ለመቀየር እያደረገ ባለው ጉዞ የቀድሞ መምህሩ ለስክሪፕት አዘጋጆች፣ ለዳይሬክተሮች፣ለተዋንያን ወዘተ በሥነ-ጽሁፍና ፊልም ላይ ያለውን ተክህኖ (Mastery) እያካፈለ እንደሆነ ያነሳል፡፡

 የሚድያ ሰው ዘካሪያስ ቴዎድሮስን ሲገልጸው አንድ ትልቅ መምህር ሀገራችን እንዳፈራች በማሰብ ነው፡፡ ዘካሪያስ የሰጠን ምስክርነት ተጨምቆ ሲቀርብ እንዲህ ነው፡፡

‹‹……በከፍተኛ የትምህርት ዓለም ቆይታዬ ካጋጠሙኝ እጅግ ድንቅና ልዩ መምህራን አንዱ ቴዎድሮስ ገብሬ ነው።በእውቀትና በስነምግባር ሞልቶ የተረፈው ሰው የሱን ያህል አላየሁም።እሱን ማወቄና በእሱ መማሬ በሕይወቴ ካጋጠሙኝ እጅግ መልካም አጋጣሚዎች አንዱ ነው፡፡ 

ስለ እሱ የአካዳሚክ ድንቅ ሰውነት ማንም የሚያወራው በመሆኑ ብዙ ማለት አልፈልግም ።ይልቅስ በሚዲያዎች ላይ ያለው አስተዋጽኦ ብዙም የሚታወቅ አይመስለኝም።ይህም የሆነው እሱ በሚዲያዎች ላይ የመቅረብ ፍላጎት ስለሌለው ነው።ስላደረገውም፣ ስላስደረገውም መልካም ውለታ እንዲነገርና እንዲጻፍ አይፈልግም።ጎልተውና ሰምረው በወጡ በርካታ የሥነጥበብ የሚዲያ ሥራዎች ጀርባ የቴዲ ተማሪ የሆኑ ጋዜጠኞች እንዳሉ ጥርጥር የለውም።በየሚዲያው ያሉ እሱ ያስተማራቸው ጋዜጠኞች በወሳኝ ሰዓት  አብዝተው ይፈልጉታል።በተለይ አምኖ በገባበት እርዳታ ከባለቤቱ በላይ እንቅልፍ ሲያጣ ማየት ያስገርማል።የሚደረግለት ምስጋና እና ቃል እስኪያጣ ድረስ በምክርና ዕውቀት ያጠግበዋል።

በ2005 በሬድዮ ፋና በተዘጋጀው ታላቅ ሀገር አቀፍ የግጥም ውድድር የቴዲ ሚና ትልቅ ነበር።›› በማለት ዘካርያስ ምልከታውን አስቀምጦ ነበር፡፡

የሚድያ ሰው እና በለባዊ ኢንተርናሽናል ት/ቤት የሀገረ በቀል እውቀት ዲፓርትመንት መስራች የሆነው ሚካኤል አለማየሁ/ የእናኑ ልጅ/  ቴዎድሮስን መምህሩ ተመራማሪውና ተጋዳሊው ቴዎድሮስ ገብሬ ሲል ይገልጸዋል፡፡ ሚካኤል ቴዲን ለመግለጽ ቃላት ቢያጥረውም እኔ ላይ በጎ ተጽእኖ በመፍጠሩ ላመሰግነው ወዳለሁ ይላል፡፡ ሚኪ ጋር ያሉት ሀገር በቀል አስተሳሰቦች በዋናነት በቴዲ የተቃኙ እና የመምህሩ አሻራ ያረፈባቸው ናቸው፡፡ ሚካኤል ምስክርነቱን ሲሰነዝር፦

‹‹ሥነ ጽሑፍ ጥንተ ተፈጥሮ በይነ – ዲሲፕሊናዊ ነው። እዚህ  ተፈጥሮው ላይ መሠረት ያረገ በይነ- ዲስፕሊናዊ የሆነ ንባብ ፣ ትምህርትና ምርምር ይፈልጋል። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ንባብ ትምህርትና  ምርምር ከበይነ – ዲስፕሊናዊ አንጻር አሁን ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ጥያቄውንም መሠረት አድርጎ ጥናት ማረግ የሚመለከተን ሰዎች የቤት ስራ ነው።

የሥነ ጽሑፍ ንባብ ትምህርትና ምርምር በይነ – ዲስፕሊናዊ መሆን እንዳለበት በተጨባጭ ካሳዩ ምሁራን አንዱ እና ዋንኛው ቴዲ ነው ፡፡ በተለየ ሁኔታ ለእኔ እሱ ነው። ” በይነ- ዲሲፕሊናዊ የሥነ ጽሑፍ ንባብ ” መጻሕፉን ፣ በምርምር መጽሔቶች ላይ ያሳተማቸውን ጽሑፎችና በክፍል ውስጥ የሚሰጣቸው ትምህርቶች ዋንኛ እና አንዱ መሆኑን ይመሰክራሉ።

ቴዎድሮስ ገብሬ የሥነ ጽሑፍ ንባብ ፣ ትምህርትና ምርምር  ተጋዳሊ ነው። ከነባሩ የሥነ ጽሑፍ ንባብ ትምህርትና ምርምር ልማድ  ያወጣን ተጋዳሊ ነው። ለዚህም ” የሃያኛው ክፍለ ዘመን የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ማስተማሪያ መጻሕፍት ሁኔታ ፤ ታሪካዊ – ሒሳዊ ቅኝት ” የሚለውን ጥናቱን ዋቢ አረጋለሁ።

ከሥነ ጽሑፍ የበይነ -ዲሲፕሊናዊ ባህር ጋር ያገናኘ ድልድይ ነው – ቴዎድሮስ ገብሬ።›› በማለት ሚካኤል ሀሳቡን ይገልጻል፡፡

ቴዎድሮስ  መገለጥ የሚፈልገው በግላዊ ኑሮው አይደለም፡፡ እንደ አንድ መምህርና ተመራማሪ  በሥራዎቹ ተጽዕኖና በተማሪዎቹ ስኬት ደስታውን ይሰፍራል፡፡ ይህም ሆኖ ግን የቅርብ ወዳጆች በቤተሰባዊ ሕይወቱም ስኬታማ እንደሆነ ይመሰክራሉ፡፡ አብነት መንግሥቴ ከቴዎድሮስ ጀርባ ያለችው ሴት የስኬቱ ሁሉ ምንጭ ናት ይላል፡፡ ይህንን ደግሞ ያረጋገጠው ከማንም ሳይሆን ከራሱ ነው፡፡

 “ቴዎድሮስ የትዳር አጋሩ እመቤት ወርቁን (ቴዎድሮስ በሚጠራበትና ወዳጅ ዘመድም እርሱን ተከትሎ በሚገለገልበት መጠሪያ ስሟ ኤሟ) ኤሟ በእኔ ሕይወት ውስጥ wild pearl ነች ይላል፡፡ wild pearl” ንጽሕናን ከድንቅነት ከማጣመሩም በላይ የሚገኝበት መንገድም በእድል ብቻ ነው- ከስንት አንዴ፡፡ እዚህ ላይ “በይነ ዲሲፕሊናዊ የሥነ- ጽሁፍ ንባብ” በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ባlቤቱን ያመሰገነበትን መንገድና የመጽሐፉን አበርክቶ ለእርሷ ማድረጉን እናክልበት፡፡” 

እመቤት የመጀመሪያ ድግሪዋን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሕግ ትምህርት ሁለቱን የሁለተኛ ዲግሪዎቿን ደግሞ ከአሜሪካን ዩኒቨርስቲዎች በIntellectual Property Law እና በInternational Development ብታጠናም ለሥነ-ጽሁፍ ግን እጅጉን ቅርብ ናት፡፡ እንደውም የቴዎድሮስ የቅርብ ወዳጆች እርሷ የምታነሳቸው ፈታኝ ጥያቄዎች ጥናትና ምርምሮቹ ይበልጡኑ ስል እንዲሆኑ አግዘውታል ይላሉ፡፡ 

አብነት መንግሥቴም በሀሳቡ ይስማማል፡፡ “ኤሟ የአንድ ሴትና የጥንድ ወንድ ልጆች አባት ያደረገችው የሚወዳት ሚስቱ ብቻ ሳትሆን ቴዎድሮስን ቴዎድሮስ እንዲሆን በማድረግ ሒደት ውስጥ ትልቅ ሚና ያላት ሴት ናት” ይላል፡፡ “የእርሱ ጥናቶች አካዳሚያዊ ዕድገት ለማግኘት አልያም ለገንዘብ ተብለው የሚሰሩ አይደሉም፡፡ ይህ ደግሞ በመምሕር ደሞዝ ቀርቶ በሌላውም ቤተሰብ በኩል ቢሆን ኢኮኖሚያዊ ጫናን እንዲሚፈጥር ጥርጥር የለውም፡፡ ኤሟ ግን የእርሱን ጫና መርጣ ቴዎድሮስን በልኩ እንድናገኘው ያደረገች ብርቱ የትዳር አጋር ናት፡፡”

አስተርዮ ቴዎድሮስ

አንዳንድ ሰው በጊዜ አይለካም፡፡ በስፍራ አይወሰንም፡፡ ይልቁኑስ መንፈስ ሆኖ ሁሉም ጋር ያረባል፡፡ ሥጋ ለብሶ ረቂቅ ይሆናል፡፡ ፍሬድሪክ ሔግል ናፖሊዎን ቦናፓርቲን ባየበት ቅጽበት የተሰማው ስሜት ጥሩ መንደርደሪያ ሳይሆነን አይቀርም፡፡ “የዘመናችንን ነፍስ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ሽምጥ ሲጋልብ አየሁት፤ በእርግጥም ሁሉም ነገር አንድ ሰው ላይ ተጠራቅሞ በፈረስ ጀርባ  ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ሲገን መመልከት ስሜትን ይነካል፡፡”የሄግል ገለፃ ድንበር አፍራሽ ነው፤የሚታይን በማይታይ፤ የማይታይን በሚታይ የሚተካ፡፡ 

የቴዎድሮስ ትውልድ አይነተኛ መልኩ አርምሞን መራጭነቱ ነው ፡፡ አብዮት ከሚሉት ምንትስ በኋላ የአደባባይ ሰውነት ቦታ አጥቷል፡፡ቁዘማና መብሰልሰሉ ከራስ ጋር ሆኗል፡፡ ወደ ውስጥ ወደራስ ብቻ መጓዝ ለእልፎች ታድሏል፡፡ ይህ ጉዞ ስውር ዳናዎችን ይተው ካልሆነ የሚታይ የሚዳሰስ አይደለም፡፡ ረቂቅ ነው፡፡ በመልከአ ልቡና ላይ የሚደረግ ነውና አሰሳውም ከፍ ይላል፡፡ ስለ ቴዎድሮስ ገብሬ  በጥቂቱ ለማውራት ስንሞክር ሌለኛው አንፃር ይህ ይመስላል፡፡ቴዎድሮስ አንድም ሄግል ናፖሊዎን በገለፀበት መንገድ ይበየናል፡፡ ይህም ሰጋ ለበስ ረቂቅነቱ ነው፡፡ ቴዎድሮስ የሥነ-ጽሑፍ መምህር ብቻ ሳይሆን ራሱም ሥነ-ጽሁፍ ነው፡፡ 

ሥነ-ጽሁፍደግሞየታሪክ፣የፍልስፍና፣የሚቶሎጅ፣የኪን፣የሥነ-ልቡና…ወዘተ ማደሪያ ነው፡፡ በመሆኑም ቴዎድሮስና ሥነ-ጽሁፍ ድንበር ሽረው ይዋሃዳሉ፡፡ አንዳቸው በአንዳቸው ውስጥ ያድራሉ፡፡ አካላዊነት ይከስማል፡፡ ሰውነት ወደ ሥነ-ጽሁፍ ጽንሰ ሀሳብነት (ገጸ-ባሕሪ መሆንንም ይጨምራል) ያድጋል፡፡ ምንድን ነው? ምን አይደለም? ይከተላል፡፡ ቴዎድሮስ ገብሬ እንደ ሰው ምን ዓይነት ነው? ከሚል ክርክር ተላቆ የሥነ-ጽሁፍ ወሰን የት ድረስ ነው?  ጥያቄ ይመጣል፡፡ 

ቴዎድሮስ ባለፉት 20 ዓመታት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቆይታው ከ22 የሚልቁ ጥናታዊ ጽሁፎችን ለንባብ አብቅቷል፡፡ “በይነ-ዲስፕሊናዊ የሥነ-ጽሑፍ ንባብ” የተሰኘ የአንድ ብዙ የሆነ መጽሐፍን ለአንባቢያን አድርሷል፡፡ እነዚህ ጥናቶች ወሰናቸው እጅጉን ሰፊ ነው፡፡ ከፍ ብለን እንደጠቀስነውም ቴዎድሮስን ረቂቅ የሚያደርጉትም ይመስላሉ፡፡ ከሥነ-ማኅበረሰብ እስከ ሥነ-ልቡና፣ ከታሪክ እስከ ፍልስፍና ይዘልቃሉ፡፡ ፊዚክስን በሚቶሎጅ ፣ ሳይንስን በሃይማኖት ይሞግታሉ፡፡ ወዲህ የተክለሃይማኖትን ገድል በጆሴፍ ካምቤል የተጋድሎ ሚዛን ይሰፍራሉ፡፡ ወዲያ የልብ ወለድ ድርሰቶችን ከታሪክ መጻሕፍት በላይ ሀቀኛ የዘመን ምስክር ያደርጋሉ፡፡ 

ቴዎድሮስ ገብሬ ከሰፊው አንባቢ ጋር የተገናኘው በ2001 ዓ.ም ለንባብ ባበቃው “በይነ-ዲስፕሊን የሥነ-ጽሁፍ ንባብ” መጽሐፉ ቢሆንም ከዚያ ቀድም ብሎ ግን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ መነጋገሪያ መሆኑ አልቀረም፡፡ በሁለት ምክንያቶች፤ ቀዳሚው ትልቁ የሥነ-ጽሁፍ መምህር ዮናስ አድማሱ (ዶ/ር) በተማሪያቸው ከመደነቃቸው ይመነጫል፡፡ ዮናስ ለተማሪዎቻቸው የሰጡትን የቤት ሥራ ሲያርሙ እንግዳ ጉዳይ ገጠማቸው፡፡ ሁለተኛ ዲግሪውን ማጥናት ከጀመረ ቀናት ያስቆጠረው ቴዎድሮስ ገብሬ ያቀረበው ጽሁፍ ግራ አጋባቸው፡፡ አስጠሩት፤ “ይህን ጽሁፍ አንተ ነህ የሠራኸው እንዳልል ሀሳቡ በፍጹም በአንተ ደረጃ ያለ ተማሪ የሚያቀርበው አይደለም፡፡ አይ የአንተ አይደለም እንዳልል እንዲህ አድርጎ በአማርኛ የሚጽፍ የውጭ አገር ዜጋ የለም፡፡ እስኪ ንገረኝ?” አሉት፡፡ የራሱ መሆኑን  አስረዳቸው፡፡

የአማርኛ ሥነ-ጽሁፍ ጥናት ባለሟሉ ዮናስ በቀጣይ ቀን ክፍል ውስጥ ያወሩት ስለምንም አልነበረም፡፡ “ይኼውላችሁ ልጆች አንድ ነገር ልንገራችሁ፤”አሉ፡፡ “አውሮፕላን መብረር የሚችለው በተፈቀደለት ከፍታ ብቻ ነው፡፡ ከዛ በላይ ከወጣ ራሱን ለአደጋ ያጋልጣል፡፡ ስለሆነም ከተፈቀደላችሁ ከፍታ በላይ  ወደ ላይ ስትወጡ ተጠንቀቁ፤”፡፡ ዮናስ ተማሪያቸውን እያሰቡ ክፍል ውስጥ ይህን ይበሉ እንጂ ያንን ያረሙትን ጥናት ግን ለሚያከብሯቸው ወዳጆቻቸው ሁሉ ማካፈላቸው አልቀረም፡፡

በመሆኑም ቴዎድሮስ ገብሬ ገና የሁለተኛ ዲግሪውን ትምህርት በጀመረ በጥቂት ወራት ውስጥ ስሙ በሥነ-ጽሁፍ ትምህርት ክፍሉ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ምሁራን ዘንድ ይታወቅ ያዘ፡፡ ከእነዚህ መካከል የወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት እንድርያስ እሸቴ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ጥቁሮች በተማሪነት እንኳን ለመግባት በሚቸገሩበት የአሜሪካን ዩኒቨርስቲ ውስጥ በመምህርነት ያገለገሉት፤ የኢትዮጵያን ኪንና ሥነ-ጽሁፍ በወጉ ያጠኑት የፍልስፍናው ሊቅ እንድርያስ በሚመሩት ግቢ ውስጥ እየተማረ ያለ “ልጃቸውን” መጨረሻ ለማየት መጓጓታቸው አልቀረም፡፡

ስለሆነም  ቴዎድሮስ  የሁለተኛ ድግሪ መመረቂያ ጽሑፉን  ሲያቀርብ ባልተለመደ መልኩ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ተገኙ፡፡ ቀኑ ለተማሪው ቴዎድሮስ ብቻ ሳይሆን ለመምህሩ ዮናስም ዕረፍት መስጠቱ የሚቀር አይመስልም፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቀድሞ መማሪያ ክፍሎች (OCR) ያልበቃቸው የቴዎድሮስ ገብሬ ሀሳቦች ከዚያ ወዲያ ከልካይ አልነበራቸውም፡፡ በተማረበት ሥፍራ መምህር ተባለ፡፡ በጌታቸው ኃይሌ (ፕ/ር) እና ዮናስ አድማሡ (ዶ/ር) ትጋት ወደፊት የተጓዘው የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ጥናት ሦስተኛውን መሪ አገኘ፡፡

የእርሱ ዘመን እውቀት ማዕከል አልባ ነው፡፡ እንደ አባቶቹ በበሩ ከሚያልፍ ጅረት ቀድቶ ከመጠጣት  ከፍ ይላል፡፡ ብዙ እውነቶች ብዙ መንገዶች በሚታዩበት የዓለም የሥነ-ጽሑፍ ጥናት ውስጥ ራሱን ካልቃኘ የተቸካይነቱ ዕዳ ግለሰባዊ ብቻ አይመስለኝም፡፡ የአገሩን ሥነ-ጽሁፍ ይዞት እስከመሞት ይደርሳል፡፡ እዚህ ሥፍራ ላይ በነባሩ መንገድ ስለማይዳኝ ብቻ ከሥነ-ጽሁፍ ትምህርት ቤቱ ተገፍቶ የኖረውን አዳም ረታ ቴዎድሮስ ገብሬ ባይደርስለት ኑሮ አሁን የቆመበት ቦታ ላይ ይገኝ ነበር? ብሎ መጠየቅ ያሻል፡፡ ከ“ማሕሌት” እስከ “የስንበት ቀለማት” የተንጣለለው የአዳም “ቤተ-ሙከራ” ሁነኛ ባለሙያ ባያገኝ ኖሮ ኦናነቱ መልሶ አያፈርሰውም ነበር? ወይ ብሎ ማሰብም ይገባል፡፡

ቴዎድሮስ ገብሬ አስቀድመን እንዳየነው የሁለተኛ ዲግሪ ጥናቱን ከሌሎች ጉዳዮች ጋር አጣምሮ “በይነ-ዲስፕሊናዊ የሥነ-ጽሁፍ ንባብ” በማለት ለአንባቢ ያቀረበው በ2001 ዓ.ም ነው፡፡ ወቅቱ ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ለሆነው የአገሬው “አካዳሚያዊው” ምልከታም የብራ መብረቅ የሚባል ሳይሆን አይቀርም፡፡ ድንገት ወድቆ እልፎችን የሚያስደነግጥ፡፡ 

“የእኔ ሥፍራ የቱ ጋር ነው?” የሚያስብል፡፡ ቴዎድሮስ በዚህ ሥራው የበርካታ የጥናት መስኮችን ድንበር እያፈረሰ አንድ ላይ ቀይጧቸዋል፡፡ መጓተት የሚቀናቸውን “ዲስፕሊኖች” በሥነ-ጽሁፍ አርቋቸዋል፡፡ ሃይማኖት ፀረ-ሳይንስ ነው መባሉን ሽሮ እምነትን ሳይንሳዊ አድርጎታል፡፡ ልብወለድን አተርኮ የልቡና ጠባሳችንን ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል፡፡  ዮናስን እንዲህ ያለው ልህቀቱ ሳይሆን አይቀርም ሦሰተኛ ድግሪውን ጨርሶ እርሱ ክፍል እየገባሁ እስክማር እጓጓለሁ እንዲሉ ያደረጋቸው፡፡ ሞት ቀደማቸው እንጂ! 

ቴዎድሮስ ማንም የማይነቀንቃቸውን የአገሬው ምሁራን በመጽሐፉ ማነጋገሩ የቀደመ ቢሆንም ባሕር ማዶ የታወቀው ግን “Myth and Sexuality: A Mythopoeic Reading of Le’tum Aynegallign” የተባለ ጥናቱን ካቀረበ በኋላ ነው፡፡ ይህ ወቅት ሁለት “ጎረምሶች” አንድ ላይ የገጠሙበት ይመስለኛል፡፡ ቀዳሚው ማሳያዬ የሁለቱ ሰዎች ትውውቅ ነው፡፡ ቴዎድሮስ ገና በአፍላነቱ ዘመን ብሔራዊ ቤተ-መጽሐፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ እየገባ ሲያነብ ያገኛቸው የነበሩ አሮጌ መጽሐፍት  የነተበ የእጅ ጽሑፍ ያለባቸው ነበሩ፡፡

 እነዚህ ጽሑፎች በ1950ዎቹ አጋማሽ ወጣት የነበረው ስብሃት ገብረእግዚአብሄር ያሰፈራቸው ናቸው፡፡ የቴዎድሮስና  ስብሃት ትውውቅ መጽሐፍ ላይ ነው፡፡ ትልቁ ጸሐፊ ያነበባቸውን መጻሕፍት በነፍስ ጥቅሻ ትልቁ የሥነ-ጽሁፍ ሰውም ከዓመታት በኋላ አግኝቷቸዋል፡፡ ይህ መንገድ ቴዎድሮስና ስብሃት በልቡና እንዲጎራበቱ ማድረጉን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን የስብሃት ገብረእግዚአብሔርን ሥራዎች የዘመናት ቅኔ ለመፍታት ቴዎድሮስ ገብሬ የሚባል ሰው በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ጥናት ታሪክ ውስጥ መጠበቅ ነበረበት፡፡ 

ስብሃት ገዳማዊውን የአገሬው “ጥበበ ቃል” ልማድ የበጠበጠ “ጎረምሳ” ከተባለ፤ቴዎድሮስም የቀደመው የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ጥናት የጠበበው አቻው መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ አንዳንዴ እንደውም የዘመንን ግንብ አፍርሰው አብነት ትምህርት ቤት እንዳለ ተማሪ ቅኔ የሚነጣጠቁ ሁላ ይመስላሉ፡፡ ማስረጃችን የቴዎድሮስ ጥናት ነው፡፡ እማኛችን ደግሞ “ሌቱም አይነጋልኝ” የተባለ “ተናዋሪ”፡፡ 

ቴዎድሮስ ገብሬ ለዘመናት በአገሬው አንባቢ ውግዝ ተብሎ የኖረውን ድርሳን አንስቶ “የፍቅር እስከ መቃብር” አቻ “የአደፍርስ” እና “ከአድማስ ባሻገር” እኩያ ያደርገዋል፡፡ ይህ ሽግግር በአንባቢው ልቡና ውስጥ ሚታዊ መልክ የሚኖረው ይመስላል፡፡ ከሴተኛ አዳሪነት  ለቅድስና እንደመጠራት ያለ ሃይማኖታዊ ገድል፡፡ ቴዎድሮስ “ሌቱም አይነጋልኝ”ን   በኢትዮጵያ ጥንታዊ ድርሳናት ውስጥ ፈልጎ ያሳየናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልኩን በርብሮ ይገልጥልናል፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ አመጽ፤ከዚህ በላይ “ጉርምስና” እና አፍራሽነት ከየት ይመጣል?! 

የቴዎድሮስ አመጽ ግብታዊ አይደለም፡፡ ትርጉም አለው፤ ታሪክ አለው፡፡ ፋይዳው የትናንትን ሕመም ማወቅ የዛሬን ሽረት መመኘት ነው፡፡ “ሌቱም አይነጋልኝ” ለዘመናት ፀያፍ የሆነን ነገር በአደባባይ የሰበከ ድርሳን ነበር፡፡ በቴዎድሮስ “ቤተ-ሙከራ” ውስጥ ሲያልፍ ግን ሕመማችን መሆኑ ተረጋገጠ፡፡ ውቤ በርሃ ለለውጥ ያጎፈሩ ኢትዮጵያዊያን ስፍራ ነው፡፡ ለአርነት የጋበዝነው ትምህርት ከራሳቸው ያኳረፋቸው፤ ዝመና ያልነው ነገር መቀበሪያ የሆናቸው-የአብዮቱ ትውልድ አምሳዮች፡፡ ኦ! ስብሃት ለአብ ገብረእግዚአብሔር በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ስናነውርህ ኑረናልና ይቅርታህን እንለምናለን ማለት ይኖርብን ይሆን ? 

“Myth and Sexuality: A Mythopoeic Reading of Le’tum Aynegallign” በነባሩ የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ጥናት ላይ እንዲህ ያለ “አብዮታዊ” እርምጃ ሲወስድ በውጩ ዓለም ያሉ ምሁራንም ለአገሬው ሥነ-ጽሁፍ ጆሮ መስጠታቸው አልቀረም፡፡ ለዚህ ደግሞ ጆናታን ከለር (Jonathan culler) አብነት ይሆናል፡፡ ከለር የዘመናችን የሥነ-ጽሁፍ ጥናት መሠፈሪያ ተደርገው ከሚቆጠሩ ጥቂት ምሁራን አንዱ ነው፡፡ ይህ ሰው ከፍ ብዬ የጠቀስኩትን የሥነ-ጽሁፍ ምርምር ካነበበ በኋላ ለአጥኝው ያለውን አድናቆት ገልጿል፡፡ በእርግጥ እንዲህ ያለ አጋጣሚ ለቴዎድሮስ ገብሬ አዲስ አይደለም፡፡ ጥቁር አሜሪካዊቷ  የቴክሳስ ዩኒቨርስቲ አንጋፋ ምሁርና ታዋቂ ደራሲ ሜሪ ሮዛሪዎም በተጠቀሰው ጥናት መደመሟ አልቀረም፡፡ 

ቴዎድሮስ አውቆትም ሆነ ሳያውቀው በሚያነሳቸው ጥናቶች ውስጥ እጅጉን ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ አንድም በርዕሰ ነገር አንድም ነገሩን ለማጥናት በሚሔድበት መንገድ፡፡ ለያይተን እንመልከተው፡፡ ኢትዮጵያ “ከክበረ-ነገስት” ወዲህ ይህ ነው የሚባል አገሩን የሚያኖር ውል ያሰረች አይመስልም፡፡ የዶናልድ ሌቪንን ቃል ልዋስና የድሕረ አብዮቷ ኢትዮጵያ ከትናንቷ የተፋታች በመንፈስ ግርግር የምትናጥ ከሆነች ውላ አድራለች፡፡ ጉዳዩ የነባሩን ሚት መጤንን አስፈላጊነት፤ የውል ልቡናችንን ቁስል መሻርን ግዴታነት ይጠይቃል፡፡

ቴዎድሮስ ገብሬ በአንድ በኩል ራሱም የአብዮቱ ልጅ ነው (1966 ነው ውልደቱ)፡፡ ሕፃንነቱን ያሳለፈው በደም የተሸመነን የአገር ምንትስ ተከናንቦ ነው፡፡ ይህ እጣ ፋንታ የእርሱ ብቻ ሆኖ አልቀረም፡፡ ዛሬም የልጆቹ ዘመን ያንን ያስንቃል፡፡ በመሆኑም በበርካታ ጥናቶቹ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ዳግም ያጤናል፡፡ ከወል እብደታችን ብንወጣ ብሎ መፈወሻ ፍለጋ ይባዝናል፡፡ በእኔ የንባብ ምልከታ ተከታዮቹ ሰባት ጥናቶች ጉልህ ጠባያቸው ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡

1)የነገሮች መቃ(የ)(ለ)ጥ፤የበቀለ አሻራዎች፣ 2) The Representation of Nation and National Identity in Modern Literature, 3) Ethiopia and Ethiopianness in Modern Amharic literature,4) Period,History, and Literary art: Historicizing Amharic Novels,5) Abbay and Nile ;Tsegaye’s Romantic Obsession, 6) የስንበት ቀለማት ድኅረ ቃል 7) ሐቲተ በእነተ እብደት፡ ሥነ-አዕምሯዊ የሥነ-ጽሁፍ ንባብ.

እነዚህ ጥናቶች በቁጥር በርካታ ቢባሉም ያላቸው ሚና ቤተ-ሙከራዊነት ይመስለኛል፡፡ አንድን መድኃኒት ለማግኘት መባዘን፡፡ ቴዎድሮስ ለመጨረሻ ጊዜ ባስነበበን የበቀለ መኮንን ሥዕሎች ቅኝት ላይ መድኃኒት ያለውን እንዲህ ይነግረናል፡፡ “በደም የተሸለመው የወል ትውስታችን በሕመም የተመታው የጋራ ልቡናችን ሽረቱም የሚገኘው በጋራ ከሚከናወን የፈውስ ሥርዓት (collective Catharsis) ነው ብዬ አምናለሁ፡፡”

የቴዎድሮስ ገብሬን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አስቀድሜ እንደገለጽኩት በአንድ በኩል ከጥናት ፍሬ ነገሩና የቆሰለን የወል ልቡናን ከማከም ጋር ቢተሳሰርም በሌላ መልኩ ከጥናት ፈለጉ ይቆራኛል፡፡ ይህ ማለት በእርሱ ጥናት ውስጥ ሰፊ ግዛትን ይዘው የሚገኙት አንድምታ፣ ፍካሬ እና ትርጓሜ  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ የተለመዱ ከመሆናቸው ይቀዳል፡፡ ቴዎድሮስ የውጭ ምሁራንን ለሐሳቡ መደገፊያ ይጠቀም ይሆናል እንጂ ምልከታና መራቀቁ ፈጽሞ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡

እንደ ቀደሙት የአገሬው ሊቃውንት በምናቡ ሽቅብ ወጥቶ “ለቴክስቱ” ትርጓሜ ይጽፋል፡፡ አንድምታ ያዘጋጃል፡፡ በፍካሬው በጸሐፊውና አንባቢው መኻል ያለን ሥፍራ ይሞላል፡፡ ወጥ ድርሰቱን ወደ ሌላ ደረጃ ያሸጋግራል፡፡ ቴዎድሮስ እንዲህ ያለ ተግባሩን ”continuation of creativity” ይለዋል፡፡ ሚናው አዲስም ጥንታዊም ነው፡፡ አዲስነቱ በዘመናዊው ሥነ-ጽሁፋችን ውስጥ አንድምታና ትርጓሜ ቦታ ከማግኘታቸው ይገናኛል፡፡ ጥንታዊነቱ ልማዱን በቀደመው የቤተ-ክርስቲያን ትምህርት ውስጥ ከመመልከታችን ይመነጫል፡፡ እዚህ ላይ የቴዎድሮስ ሚና  “ኒዎ” ደብተራነት (Neo Debtra) መሆኑ ይገለጥልናል፡፡ 

“ደብተራው“ቴዎድሮስ በአንድምታና ትርጓሜ የማይደርስበት “ዲስፕሊን” የለም፡፡ The Genius Loci of Addis Ababa በተሰኘ ጥናቱ የእኛዋን አድባር በዘመናዊው የሥነ-ምድር ጥናት (Modern Geography) ውስጥ ይበይናታል፡፡”አካል በአማርኛ ሥነ-ጽሁፍ ውስጥ“ በሚል የምርምር ሥራው ከማሕሌት እስከ ስንበት ቀለማት ልብወለዶች የተዘረጋውን የአዳም ረታ ኢ-ንቁ አዕምሮ ግዛቱ ያደርገዋል፡፡ ስፍራ ነጠቃው አንድም የደራሲውን ልቡና ተራራና ሸለቆ መውጣት ይጠይቃል ፡፡አንድም  በራስ ልቡና ላይ ሳይሰለቹ መጓዝን ይፈልጋል፡፡

ቴዎድሮስ ሁለቱን ጉዳዮች ካጣመረ በኋላ ሥነ-ጽሁፋዊ መበያዎችን (literary motifs) መሰላሉ አድርጎ ከፍታው ላይ ይወጣል፡፡ድርሰቱን እንደ አዲስ ያዋልዳል፡፡ በዚህ መንገድም ተጨቋኞቹን ገፀ-ባሕርያት ማኅሌትና ዘውዴ መከወኛ(ከ ይጠብቃል) ሳይሆን ከዋኝ ያደርጋቸዋል፡፡ ከአብዮተኛ ያስተካክላቸዋል፡፡ተግባራቸው ወንዳዊውን ሥርዓት እንዴት እንደገነደሰ ያስረዳል፡፡የቀደመው ሥነ-ጥበብ መናድና የወንዳዊውን ዓለም መናጥ ያስከትላል፡፡   

የቴዎድሮስ ኢትዮጵያዊ መልክ “ሐቲተ በእንተ እብደት፡ ሥነ-አዕምሯዊ የሥነ-ጽሁፍ ንባብ” በሚል ምርምሩ ላይም ጎልቶ ይታያል፡፡ሙግቱ  የኢትዮጵያዊያን የአዕምሮ ሕመም መነሻና መድረሻ ላይ ነው፡፡ እብደት መሠፈሪያው ባሕል ከሆነ ኢትዮጵያዊ የሆነው እብደታችን ኢትዮጵያዊ ሕክምና ያስፈልገዋል ያላል፡፡ስጋቱ ትምህርታችን የአሜሪካን ስነ-አዕምሯዊና ስነ-ልቡናዊ ጉዳዮች በሚተነትኑ መጽሐፍት እየተሰጠ የእኛ ሽረት ከየት ይገኛል የሚል ነው፡፡   

የበርሃው ባሕታዊ የጥናት መንገድ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን ግላዊም ጭምር ነው፡፡ የእርሱ ጥናቶች የራሱ በሆኑ ልዩ ልዩ ጌጦች ያሸበረቁ ናቸው፡፡ አንድም በቋንቋው ልህቀት አንድም በያዘው ኃልዮት፡፡ ከቋንቋ አንፃር የቴዎድሮስ ዐረፍተ ነገሮች እንደ ግጥም ቤት የሚመቱ እንደ ሙዚቃ ”ሪትም“እና ምት ያላቸው  ስሜት ቆንጣጭ ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር ጥናቶቹ ራሱ እንደ ሥነ-ጽሁፍ የመቆጠር አቅም ያላቸው በሙዚቃዊ ቋንቋም ለመለካት የቀረቡ መሆናቸውን መገንዘብ ያሻል፡፡ (ምናልባት በተማሪነቱ ዘመን የተውኔትና ልብ ወለድ ደራሲ ስለነበር ከዛ የወረሰው ይሆናል)፡፡ እዚህ ላይ  የውጭ ቃላትን ወደ አማርኛ የሚመልስበት መንገድና የግርጌ ማስታወሻ አጠቃቀሙን እናክልበት፡፡ 

ቴዎድሮስ ገብሬ በእኔ የንባብ ልማድ በየትኛውም የውጭ የስነ-ሰብ ምሁር ንድፈ ሀሳብ አይሰፈርም፡፡ የእገሌ ደቂቅ ነውም አይባልም፡፡ ይልቁኑስ ነገ በወጉ ሊጠና የሚገባውን ሥነ-ጽሁፋዊ “ቴዎሪና ሜቶዶሎጅ”  እየተከለ ያለ ይመስላል፡፡ ምናልባት የዓለም ሥነ-ጽሑፍ ጥናት ፈር አስያዦቹ ጆናታን ከለር እና ሜሪ ሮዛሪዎ አምሳ ዓመት ያልሞላው “ወጣት” (ለእንደሱ ዓይነት የሥነ-ጽሁፍ አጥኝ ዕድሜው ገና የሚባል ስለሆነ) ላይ ያዩት ነገርም ይኼ ሳይሆን አይቀርም፡፡

መዝጊያ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡  

ሀገራችን ብዙ ያልተነገረላቸው መምህራን ይዛለች፡፡ መምህር የሁሉም ሙያ አባት ቢሆንም ተገቢውን እውቅና እና ክብር ሲያገኝ ብዙም አይስተዋልም፡፡  ሌሎችን ያበቃል፤ እንደሻማ ቀልጦ ያስተምራል ነገር ግን በስተፍጻሜ ይዘነጋል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ጥሩ ምስክርነት እያላቸው ነገር ግን ወደ ህዝብ ላልደረሱ ሰዎች ሁሌም ጋሻ ነው፡፡  ካሉበት ቦታ ወጥተው ስራቸው  እና የህይወት ተሞክሯቸው ለአደባባይ እንዲበቃም ይጥራል፡፡

መምህር ቴዎድሮስ ገብሬ በተማሪዎች የሚከበር ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ የስነጽሁፍ መንገድ አዲስ መንገድ ያመለከተ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከመምህር የሚጠበቅ ነው፡፡ መምህር አዲስ ስልት ፈጣሪ፤ ያልተሄደበትን መንገድ ሞካሪ ነው እንጂ በባህላዊ መንገድ የሚነጉድ አይሆንም፡፡ ከላይ የህይወት ታሪኩን ያየንለት ሰው ቴዎድሮስ ገብሬ ጥልቅ ንባቡ አዲስ እይታ እንዲመለከት አግዞታል፡፡ ይህ ጥረቱ ደግሞ መና ሆኖ አልቀረም፡፡ በታላላቆቹ መምህራን ሳይቀር መደነቅ የቻለ ነበር፡፡ ታዲያ እንዲህ አይነት የሰላ ሂስ መሰንዘር የሚችሉ ሊቆች ምነው ቢበዙልን፡፡

ተወዳጅ ሚድያ በቅርቡ በሚታተመው መዝገበ-አእምሮ ውስጥ የመምህር ቴዎድሮስን ታሪክ ለመካተት ስንወስን ከላይ የተቀመጡት ጉዳዬች አሳማኝ ሆነው ስላገኘናቸው ነው፡፡ ባደረግነው ምርምር መምህሩ ሊመሰገን እና ሊሸለም የሚገባው ነው፡፡ ምክንያቱም አዲስ መንገድ አመለክቷል፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎችን ለታሪክ ማስቀመጥ ትልቁ ሃላፊነታችን ስለሆነ ይህንኑ አደራ ተወጥተናል፡፡   ይህ መጣጥፍ በጋዜጠኛ ይነገር ጌታቸው አርታኢነት በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ አዘጋጅነት ዛሬ ታህሳስ 13 2016 በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች የተቀመጠ ነው፡፡ በዚህ ጽሁፍ ላይ ሀሳብ ካለዎት በ0911416678 መሰንዘር ይችላሉ፡፡

4 thoughts on “ቴዎድሮስ ገብሬ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)

  1. ቴዲን የሚመጥን ቆንጆ ጽሑፍ ነው። እናመሰግናለን!
    ከጥቂት የፊደል ግድፈቶች በቀር

  2. ከላይ ያለውን ታሪክ ያነበብሁት ዩ ቲዩብ ተመልክቼ በመምህሩ ምጡቅ እውቀትና ንግግር ተደንቄ ለካ ጥቂትም ቢሆን በዘመን መተላለፊያ ” ሰው” አናጣም የሚል የአእምሮ ወረት ያዝሁ። በጣዕሙ ደስ አለኝ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *