ፕሮፌሰር ብሩክ ሀይሉ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ፕሮፌሰር ብሩክ ሀይሉ ይጠቀሳሉ፡፡
እኒህ ሰው በአሁኑ ሰአት የናሁ ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሲሆኑ ቀደም ብሎም በአሜሪካን ሀገር ጋዜጠኝነትን ያስተማሩ ሰው ናቸው፡፡ በናሁ ቲቪ ዲፕሎማሲያዊ ማእዘን የተሰኘ መሰናዶ አየር ላይ የሚያውሉ ሲሆን የጋዜጠኝነት ሙያ በፕሮፌናል ደረጃ እንዲሰራ ከሚሹት መካከልም አንዱ ናቸው፡፡ ሞሊቶ ኤሊያስ እና እዝራ እጅጉ የህይወት ታሪካቸውን ሰንደውታል፡፡
ውልደትና እድገት
ፕሮፌሰር ብሩክ ሀይሉ በሻህ ከኢንጅነር አባታቸው ከአቶ ሀይሉ በሻህ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ሮዛ ተረፈ ሀምሌ 26 1948 ዓ.ም በአዲስ አበባ ነው የተወለዱት።ለቤተሰባቸው 3ኛ ልጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ብሩክ ከመዋዕለ ህፃናት እስከ 1ኛ ክፍል በናዝሬት ትምህርት ቤት እንዲሁም ከ 2ኛ ክፍል እስከ መሠናዶ በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ተምረዋል።
ብሩክና “እድገት በህብረት” ዘመቻ
የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በደርግ መንግስት በታወጀው የእድገት በህብረት ዘመቻ ወደ ትግራይ በማቅናት ለአንድ አመት ተኩል አገልግለዋል።
ከዘመቻ መልስ
ፕሮፌሰር ብሩክ ከዘመቻ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኃላ 1969 ዓ.ም ወደ ተመደቡበት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመግባት በፖለቲካ ሳይንስ እና አለማቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያዙ።
የስራ ህይወት
ፕሮፌሰር ብሩክ በነበራቸው ጥሩ ነጥብ እና ተሳትፎ ምክንያት ከዩኒቨርሲቲው ጥያቄ ቀርቦላቸው እዚያው አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህር ሆነው በመቀጠር ለ 20 አመታት ማስተማር ችለዋል። ከዚህ በኋላ ፕሮፌሰር ብሩክ ባገኙት የውጭ የትምህርት እድል ወደ ጀርመን በማቅናት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአንጋፋው Leipzig university በፖለቲካል ሳይንስ እና አለማቀፍ ግንኙነቶች እንዲሁም የ ማስተርስ ዲግሪያቸውን ከዚሁ ዪኒቨርስቲ PhD በ International Political Communications አግኝተዋል። ለትምህርት በሄዱበት ጀርመን ሀገር በጀርመንኛ ቋንቋ ለ 4 አመታት ማስተማርም ችለዋል።
ወደ ሀገር ቤት
ከጀርመን መልስ በ አዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እንዲሁም የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርቶችን ለአመታት አስተምረዋል፡፡ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞችንም አስተምረዋል፡፡
ኃላፊነት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ
ፕሮፌሰር ብሩክ በማስተማር ስራቸው ላይ እያሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የውጭ ግንኙነት ሀላፊ ሆኖ ተሾሙ። በዚህ ክፍል ውስጥም ለ 3አመት ተኩል አገልግለዋል፡፡ በዚህ ኃላፊነት ላይ እያሉ በዩንቨርሲቲው ለ26 አመታት ተቋርጦ የቆየውን የክብር ዶክትሬት ዳግም መሰጠት እንዲጀምር ማስቻላቸው ጎልቶ የሚነገርላቸው ስራ ነው። በጊዜውም ለደራሲ ከበደ ሚካኤል እና ለደራሲ ሀዲስ አለማየሁ የክብር የዶክትሬት ዲግሪ እንዲሰጥ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ፕሮፌሰር ብሩክ በፖለቲካል ሳይንስ ፣በአለማቀፍ ግንኙነት እንዲሁም በአለማቀፍ ሚዲያ ጥናት ዘርፎች ረጅም አመት የማስተማር ልምድና እውቅናን ያተረፉ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ምሁር ናቸው።
የውጭ ሀገር የስራ ልምድ
ፕሮፌሰር ብሩክ በተለያዩ የውጭ ሀገር ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማስተማር እድል ያገኙ ሲሆን። በሰሜን ካሮላይና በሚገኘው የ A&T state university፣ በ ሜሪላንድ ዩኒቨርስቲ (UMGC)፣በ center for african study፣በ Venovich የአመራር ትምህርት ቤት ፣በ ኦሃዮ ዩኒቨርስቲ ፣በ አክሮን ዪኒቨርስቲ ፣በCarnegie mellon የህዝብ ፖሊሲ ትምህርት ቤት፣በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ የኤሊዮት የአለማቀፍ ጉዳዮች እንዲሁም ኦሃዮ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በሚገኘው የስክሪፕስ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ውስጥ ተባባሪ እንዲሁም የሙሉ ጊዜ መምህር በመሆን አገልግለዋል።
ዲፕሎማትነት እና የ UN ግልጋሎት
ፕሮፌሰር ብሩክ ኢትዮጵያን በመወከል በአሜሪካና በፈረንሳይ-ፓሪስ በዲፕሎማትነት ያገለገሉ ሲሆን፣ከ2002-2008 ዓ.ም ባሉት አመታት ፦ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና አምባሳደር በUN ዩኔስኮ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል ። በዚህ ወቅትም የዩኔስኮ የቦርድ አባል ሆነው ጥንታዊው የሐረር ጀጎል ግንብ በቅርስነት እንዲመዘገብ ፣የአክሱም ሀውልት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው። ፕሮፌሰር ብሩክ ሀይሉ በተለያዩ አገራዊና አለማቀፍ ተቋማት ያዳበሩትን ልምድ በመጠቀም ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ የዳያስፖራ ምክር ቤቶች እና የምርምር ተቋማት ላይ በአባልነትና በአመራርነት ለአመታት የዜግነት ድርሻቸውን ሲወጡ ቆይተዋል።
ፕሮፌሰር ብሩክ በአለም ፣በአፍሪካና በምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ዙሪያ ትንታኔ እንዲሰጡ በአለማቀፍ ሚዲያዎች ከሚመረጡ ምሁራን አንዱ ናቸው።- በተለይም ስለ አፍሪካ -አሜሪካ ግንኙነት ፣አፍሪካ -ቻይና ግንኙነት እና የመሳሰሉት በተመለከተ ሰፋ ያለ ሙያዊ ትንተናን በመስጠት ይታወቃሉ። ከሀምሌ 2008 እስከ ጥቅምት 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ብቻ በአማርኛ፣እንግሊዝኛ፣ጀርመንኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ወደ 100 የሚጠጉ ቃለ-መጠይቆችን ለተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ የሚዲያ ኢንዱስትሪ ውስጥ ጉልህ አሻራ በማበርከት ላይ የሚገኙት ፕሮፌሰር ብሩክ በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፖለቲካል ሳይንስ እና አለማቀፍ ግንኙነት የትምህርት ክፍል በመምህርነት ፣በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ በአማካሪነት እንዲሁም የፖለቲካል ሳይንስ ተቋም የቦርድ አባል በመሆም እያገለገሉ ይገኛሉ። የካበተው ልምድ ወደ ሚዲያው ኢንደስትሪ በተለያዩ ሀገራት በዲፕሎማትነት፣በመምህርነት እና በአማካሪነት በመስራት የካበተው የፕሮፌሰር ብሩክ ልምድ ወደ ሚዲያው ኢንደስትሪ መጥቶ የሚታይ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።
ከ 2008 ዓ.ም ጀምሮ በ አሜሪካ ድምፅ ሬድዮ(VOA) አማርኛ ፕሮግራም እንዲሁም ከ 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለአመታት በእንግሊዘኛ ቋንቋ ትኩረቱን በኢትዮ-አሜሪካ ግንኙነት፣የተባበሩት መንግስታት፣የአፍሪካ ፖለቲካ እና ሚዲያ ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ሰፋ ያሉ ውይይቶች እና ፖለቲካዊ ትንተናዎችን ሲሰጡ ቆይተዋል። ትንታኔ ከሰጡባቸው ሚድያዎች መካከልም አልጀዚራ እና የአሜሪካ ድምጽ ይገኙበታል፡፡
ናሁ ቴሌቪዥን እና ፕሮፌሰር ብሩክ
ፕሮፌሰር ብሩክ ሀይሉ የናሁ ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ ሲሆኑ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ቋሚ መልዕክተኞች የሚጋበዙበት “ዲፕሎማሲያዊ ማዕዘን” የተሰኘ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ቋሚ መልዕክተኞች የሚጋበዙበት የቴሌቪዥን ፕሮግራም እንዲሁም “የዲያስፖራ ድምፅ” የተሰኘ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በማዘጋጀት ይታወቃሉ። ፕሮፌሰር ብሩክ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ እንግሊዘኛ፣ጀርመንኛና ፈረንሳይኛ አቀላጥፎ የሚናገሩ ሲሆን መሰረታዊ የጣሊያንኛ ቋንቋን ለመልመድ ችለዋል።
መዝጊያ
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ የቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ፕሮፌሰር ብሩክ ሀይሉ በሚድያው ዘርፍ ካሉት መካከል በቂ የአካዳሚክ እውቀት ካላቸው ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ጋዜጠኝነትን በባህር ማዶ በማስተማራቸውም አለም የደረሰበትን የሚድያ ደረጃ በወጉ ይገነዘባሉ፡፡ በመሆኑም የሚድያን ተግባር በፕሮፌሽናል ቅርጽ ለማስኬድ የእርሳቸው ጉልህ አስተዋጽኦ ማስፈለጉ ግድ ነው፡፡ በየጊዜው በሚድያው ጉዳይ ላይ በሚደረጉ መሰናዶዎች ላይ እርሳቸው ይታደማሉ፡፡ ልምዳቸውንም ያካፍላሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ አብረዋቸው የሰሩ አፋቸውን ሞልተው እንደሚመሰክሩላቸው ወጣት ለማገዝ ወደ ኃላ አይሉም፡፡ በቅንነት ሀሳብ ሲሰጡ ፈጽሞ የሚሰስቱ አይደሉም፡፡ ትልቅ እመርታ ሊያሳይ የሚገባው የሚድያ ኢንዱስትሪ ደግሞ እንደ ፕሮፌሰር ብሩክ አይነት ሰዎች ያስፈልጉታል፡፡ ነገር ግን ሁሉ የሚጀምረው ሰውን ከማውቅ ነውና የእርሳቸውን ታሪክ ሰንደን አስቀምጠናል፡፡ እርሳቸው ለሚሰሩት ሙያን የማሳደግ ተግባርም እውቅና መስጠት እንሻለን፡፡