ጋሽ ገ/የሱስ ሃ/ማርያም 16 መጻህፍትን በጉራጊኛ፣ በአማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋንዎች መጻሕፍትን በመጻፍ ይታወቃሉ፡፡ የታሪክ ጸሀፊ፣ ደራሲ እና ገጣሚ ናቸው፡፡ ደራሲ ገ/የሱስ ለንባብ ካበቋቸው መጽሐፍት “ከንቱ ኑሮ”፣ “ጉዱና ታሪኩ”፣ “የመዓዛ ጉዞ”፣ “አርዕስት ስጡልኝ”፣ “የኅብረት እንቅስቃሴ”፣ “የጫሙት ሽካ” (በጉራግኛ)፣ “ተኬትነት አጂነት አገኪ” (በጉራግኛ)፣ “ያቃተተች ሕይወት”፣ “The Gurague and Their Culture”፣ “አይ ማሞ”፣ “አደራው” (የተኬትነት አጂነት አገኪ የአማርኛ ትርጉም)፣ “የአካላት ሤራ”፣ “ትንሣኤ ወይንስ ስንብት”፣ “ጉዞ 1” እና “ጉዞ 2”። ሌላው ነሁቸው የተሰኘ በማህበረሰቡ ሥነ ቃልና ባህል ላይ ያተኮረ (የዌግና የበድራ) መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡
“ደራሲ”፣ “የልማት ሰው”፣ “የባህል ተቋም መስራች”፣ “ገጣሚ” (በተለይ በጉራግኛ ጥሩ ገጣሚ ናቸው) የሆኑት ጋሽ ገብረ ኢየሱስ ተወልደው ያደጉት ጐማረ “ድርቦ” በሚባል ደጋማ መንደር ሲሆን ልጅነታቸው በዘመኑ እንደነበሩ የጉራጌ ልጆች በእረኝነት እና ከከብት ጥበቃው ጎን ለጎን ሣር ማጨዱም፣ እንጨት በመልቀም እና በእርሻ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ነበር፡፡ ከፊደል ቆጠራ እስከ ሦስተኛ ክፍል በመደርቾ፣ ከመደርቾ ደግሞ ዠምቡወረ፣ ከዚያም ወደ እምድብር በመሄድ የሰባተኛ ክፍል ትምህርታቸውን በ1942 ዓ.ም. አጠናቀቁ። ከእምድብር ወደ አዲስ አበባ በማምራት ተፈሪ መኰንን (ላዛሪስት ካቶሊክ ሚሲዮን)፣ ቀጥሎ ደግሞ ኮከበ ጽባሕ በመግባት ከመምህርነት ሥልጠና ጋር አቀናጅቶ ተምሮ ሲወጣ ለመጀመሪያ ጊዜ በመምህርነት የተመደበው ወሊሶ ነበር።
ጋሽ ገብረ ኢየሱስ ኃይለማርያም በድርሰቱ ብቻ ሳይሆን በትዳራቸው፣ በልጆቻቸውም ሆነ በሀገር ውስጥ እና በአለማቀፍ ተቋማት (አፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን) መስርያ ቤት ውስጥ ባሳለፉት የስራ ጊዜያት ስኬታማ ነበሩ፡፡
ባለፉት ስርአቶች በድርሰት ስራ ውስጥ ፈታኝ የነበረው ከአማርኛ ውጪ ባሉ ቋንቋዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ መጽሐፍ ማሳተም ያልተለመደ እና ከባድ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ፈተናው “የጫሙት ሽካ” (የጫሙት ወጥመድ) የተሰኘው፣ በኮርታዊና በጫሙት የፍቅር ሕይወት ላይ ያነጣጠረ የጉራግኛ ረዥም ልብ ወለድ ከጻፈ በኋላም፣ የጉራግኛ ቃልን በአግባቡ ሊገልጹ የሚችሉ ፊደሎች ስላልነበሩ ፊደሎቹን ለመቅረጽ የነበረው ውጣ ውረድ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ይህንን ፈተና በብቃት በመወጣታቸው በጉራጊና ስነ ጹሑፍ ሆነ የቋንቋ ጥናት ውስጥ ትልቅ አሻራ አኑረዋል፡፡ የሳቸው ፍኖት በመከተልም የተስፋዬ ጐይቴ፡ “ኬርጋት” “ጒራጌንደ” የክፍሌ ተመስገን “እልል በል ጉራጌ” ቪሲዲ እና “መርኸቱ” እንደዚሁም የጠና ካሣ አንደታ እና በክስታኔ ቤተ ጉራጌ ዘዬ የታተመው “የጉራግኛ፣ አማርኛና እንግሊዝኛ” መዝገበ ቃላት ሌሎችም መጽሐፎች ወደ ማህበረሰባችን ሲደርሱ የሳቸው መንገድ ጠራጊነት ከፍተኛ ነው፡፡
በጉራጌ ስነ ጹሁፍ ውስጥ በሳቸው ደረጃ ያሰበ፣ የተመራመረ፣ ታሪክን የሰነደ እና የጻፈ ሰው ማግኘት ይከብዳል፡፡ በተለይም ወደፉት በጥናት የሚዳብሩ ዝርዝር ሰነዶችን ሰንዶ በማስቀመጥ ታሪክ የማይረሳቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡
የጉራጌ ባህል ጉዳይ እጅግ ተቆርቋሪ እና አሳቢ በመሆናቸው በሀገራችን ባህል ማእከል ምስረታ ቀደምት የነበረው የጉራጌ ባህል ማእከል በመመስረት ሂደት ውስጥ ትልቁን ድርሻ ወስደዋል፡፡ በእርጅና ዘመናቸው ለጉራጌ ሚዲያ ኔትወርክ ምስረታ ላይ የአንበሳውን ድርሻ ወስደው ሰርተዋል፡፡ ደራሲ ገ/የሱስ ሃ/ማርያም በጉራጊኛ ቋንቋ በጻፉት ረጅም ልብወለድ ‹‹የጫሙት ሽካ›› እና ሌሎች 16 ያክል ድርሰቶችን ብቻ በመጻፋቸው ብቻ አይደለም የሚታወቁት፡፡ በሆቴል ኢንደስትሪው ዘርፍ እርሳቸው እና ቤተሰቦቻቸው ለለፉት 3 አስርት አመታትን በስኬት ተጉዘዋል፡፡
በተለይም በጤፍ እና በጤፍ ተዋጽኦ ላይ በሰሩት ስራ አለማቀፍ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ በባህል ማዕከል ደረጃ በሀገራችን ቀዳሚ የነበረው የጉራጌ ባህል ማዕከል ሲቋቋም በመስራችነት እና በኃላም በአመራርነት ሰርተዋል፡፡ በበጎ ፍቃድ ስራዎች ላይ ከወጣትነታቸው ጊዜ ጀምሮ በጉመር ወረዳ፣ በጉራጌ ራስ አገዝ ድርጅት ውስጥ ሆነ በጉራጌ ባህል ማእከል ውስጥ ትልቅ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡
ጋሽ ገብረ ኢየሱስ በድሜ ዘመናቸው ሁሉ ቅን ለሆነው አገልግሎታቸው እና በጉራግኛ ባህል፣ ቋንቋ እና ስነ ፁሁፍ ጉዞ ውስጥ ላበረከቱ አስተዋጽኦ ይህንን የኬር ሽልማት፣ የበጎ ሰው ሽልማት፣ ከጉራጌ ዞኖች እና ከሌሎች አካላት እውቅና ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
የዚህ ዝግጅት ጉራግኛ ቋንቋ የስነ ጽሑፍ ቋንቋ ለማድረግ የሚያስችል የአሠራር ስርአት ለመዘርጋት፣ ለማስተዋወቅ እና የስነ ጽሑፍ ሥራዎች የሚደመጡበት ቋሚ አውድ ለመፍጠር (እንዲኖር) የሚያስችል መደላድል ለመፍጠር ነው፡፡ ይህን ስራ ለማስጀመር ደግሞ መነሻችንን ጋሽ ገብረኢየሱስ ኃይለማርያም አድርገናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያችን ጋሽ ገብረኢየሱስ ለዘርፉ የከፈሉትን ዋጋ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡
በመሆኑም የዝያን ታላላቅ አባቶች ትውልድ የመጨራሻው ሰው እሳቸው እና በጣም ጥቂቶች ብቻ በመሆናቸው የአንጋፋዎቹን ስራ ወደእዚህኛው ትውልድ በምላት ለማሸጋገር ወይም ድልድይ ለመሆን የሚያስችል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡