ዮናስ አብርሀም
ፀሀፈ ተውኔት፤ ገጣሚ ፤ ደራሲና ጋዜጠኛ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ መዝገበ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ በዚህ ታሪክ ላይ ስማቸውና ሥራቸው ተሰንዶ መቀመጥ ይገባቸዋል ካላቸው ያላቸው ሙሉ አቅም አውጥተው ለህዝብና ለሀገራቸው በመስጠት ታሪክን ከታሪክ ፣ ባህልን ከባህል ፣ ህዝብን ከህዝብ ካስተዋወቁ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በመፍጠር ታሪክን ከሰነዱ ሀያል ብዕረኞች መካከል አንዱ ጋዜጠኛ ዮናስ አብረሃም ነው።
ዮናስ አብርሃም በአሁኑ ሰዓት በበርካታ ድራማዎችንና ተውኔቶችን እየጻፈ ያለና የጨረቃ ውል የተሰኘ የሬዲዮ ድራማ ድርሰቱን በቀድሞው መሥሪያ ቤቱ ፋና ሬዲዮ ላይ እየሰራ እንዲሁም በቅርቡ አየር ሰዓት ወስዶ ለመስራት እየተጋ ያለ ጋዜጠኛ ነው። በፀሐፌ-ተውኔት፣ ገጣሚነት፣ ደራሲነትና ጋዜጠኝነት እስካሁን በቆየባቸው ጊዜያት ሁሉ በሙያው ያበረከተው እውቀት፣ ያስጨበጠው ግንዛቤ ፣ ያስተማረው እምቅ እውቀት እልፍ አዕላፍ ነውና…ጽሑፉን እንዲታነቡ ተጋብዛችኋል።
ባንቺአየሁ አሰፋ እና እዝራ እጅጉ የዮናስ አብርሃምን ታሪክ እንደሚከተለው አጠናክረውታል፡፡ እርሱ የገሀዱን ዓለም ተጨባጭ እውነታ ከማይታየው ምናባዊ ሂደት ክዋኔ ያስታረቀ የፈጠራ ሀሳብ እና የምናብ ባለቤት ነው። ከሰፈር ተነስቶ እስከ ጠፈር የዘለቀ ከፍጡራን ንግግር አልፎ ተፈጥሮን በሹክሹክታ የሞላ ማልዶ ከጨረቃ ቡና የተጣጣ ሌት በፅልመት ከፀሐይ ወጥቶ የተሰጣ በቦታ የተከሰቱ ሁኔታዎችን በውብ ቃላት በለዛ አንደበት እያዋዛ የልብን በልብ ለቁምነገር የሰጠ ድምጸ መረዋ የባለ ብዙ ተሰጥኦ ባለቤቱ ጋዜጠኛ ዮናስ አብርሃም።
ትውልዳቸው ከሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ከሆኑ ወላጆቹ ይህም ማለት ከአሁኗ ኤርትራ በመዲናችን አዲስአበባ በሺህ ዘጠኝ መቶ ስድሳ አራት (1964) ዓ.ም ነበር የተወለደው። እድገቱ አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ሲሆን የአሁኑ መሰረቱ የተገነባው በዚሁ ቦታ ነበር። በልጅነቱ ካደገበት ቤት ፣ ከኖረበት ማህበረሰብ ፣ ከተማረበት ትምህርትቤት። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሆነበት ቡራቡሬ ህይወት ውስጥ ያለገደብ ሁሉም ተሰባስቦ በሚቦርቅበት ያለመደብ ከፊሉ በሸራ ከፊሉ በበረባሶ ከፊሉ ባዶ እግሩን በሚሄድበት ኑሮ ከሰውነት ሚዛን ላይ ወጥቶ ሰውን በማያቀልበት ወቅትና ቦታ ነበር ያደገው።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በመነን አስፋው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቤት የተከታተለ ሲሆን ቀጥሎ 2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአየር ጤና ተምሯል። በትምህርት ጊዜው ታሪክና ጂኦግራፊን እጅግ በጣም የሚወድ ተማሪ ሲሆን በተለይም ደግሞ ቋንቋ እና ንባብ ያስደስቱት ስለነበር በትምህርት ቤት ተሳታፊ እና ከእኩዮቹ ለየት ያለ ንቃት ያለው የእሳት ትንታግ ተማሪ ነበር።
የከባድ መኪና አሽከርካሪ የነበሩት አባቱ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለልጆቻቸው መጽሐፍቶችን በመግዛት እንዲያነቡ ሲያበረታቱ ሌሎችም የተማሩ የቤተሰብ ክፍሎች በመኖራቸው ዮናስ እንብዛም አልተቸገረም። ይሁን እንጂ ለንባብ ርሃቡ መጽሐፍቶቹ በቂ ባለመሆናቸው ከእነሱ ባሻገር ግድግዳ ልጦ ስኳርና ቡና ገልብጦ የሚያነብ ልጅ ስለነበር እንደ ንግርትም ሆኖ እናቱ በሚወዱት ጋዜጠኛ ዮናስ ገብረማርያም ስም ይጠሩት እንደነበር ይናገራል።
ይህ የንባብ ፍቅሩና ፍላጎቱ ገና በልጅነት ዕድሜው የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ነበር ወደ ለገዳዲ የትምህርት ማሳራጫ ሬዲዮ እንዲያቀና ያደረገው ። ስቱዲዮ ገብቶ ” እንደምን አላችሁ ተማሪዎች? እንደምን አሉ መምህር? ” በማለት ጣፋጭ የልጅነት አንደበቱን ለህፃናት ያስደመጠው ። በለጋ ጣቶቹ መካከል ጠጣር ብዕር የጨበጠው ። ከወደፊት እጣ ፋንታው ማይክራፎን ፊት ለፊት የተቀመጠው ።
ሬዲዮ እጅግ በሚከበርበት በዚያን ዘመን ዮናስ ሬዲዮን እንደ ተዓምር በሚቆጥርበት ወቅት ከየወረዳው ተሰብስበው ኳስ ከሚጫወቱ ልጆች ጋር እየተጫወተ በለምለሙ ሳር ላይ ደረታቸውን ደፍተው ሬዲዮ የሚያዳምጡ ሰዎችን ሲያይ በሚገረምበት ጊዜ ቀስበቀስ በደረቱ እየተሳበ በዚያች ትንሽዬ ቆርቆሮ ውስጥ የሚወጣውን ድምጽ ለመስማትና እሱም አንድ ቀን እንዲህ መሰማት እንደሚፈልግ በልቦናው አስቦ ነበር።
ታዲያ ዕድሜው ሬዲዮ ለማድመጥ ሲደርስና ስለራዲዮ ያለው ግንዛቤ ሲዳብር እነ ሀይሉ ፀጋዬ የሚጽፏቸውን ድራማዎች በማዳመጥ በወቅቱ አንጋፋ የተባሉ ጋዜጠኞች የሚያዘጋጇቸውን ፕሮግራሞች በመከታተል ለሬዲዮ ያለው ፍቅር እና የመደመጥ ዝንባሌ በውስጡ የተቀጣጠለው ያኔ ነበር ። ዮናስ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት (ሲደርስ ልዩልዩ ዓመታዊ መርሃግብሮች ሲኖሩ ተጋብዞ ስራዎቹን ያቀርባል፡፡ ከተማሪዎች ጋር በመሆንም መርሃግብር አዘጋጅቶ በመሳተፍ ኣሳልፏል፡፡ ቢሆንም ኪነጥበብ የነበረው እንቅስቃሴ አናሳ ስለነበር ድንኳን ሰብሮ አጥር ጥሶ በሌላ ወረዳ ላይ በተዘጋጀ መርሃግብር የወረዳው ኗሪ ነኝ በማለት በማያውቀው ወረዳ ተገኝቶ ኮሜዲያኑ ደረጀና ሀይሌ በተገኙበት ሥራዎቹን በደስታ አቅርቧል።
ይህ ጠይም ብዕረኛ በግሉ የጋዜጠኝነት ሙያን እየተማረ ጎንበጎን የሬዲዮ ድራማና ተውኔቶችን ጽፏል። ከነዚያ ስራዎችም አንዱ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የሚተላለፍ ሁለት ክፍል የሄደ ድራማው አንዱ ነበር። በኋላ በ(1987) ዓ.ም ፋና ሬዲዮ ተቋቁሞ የሥራ ቅጥር ማስታወቂያ ሲያወጣ ዮናስ የኢትዮጵያ ሬዲዮን ትቶ ወደፋና አዘገመ። ከአመልካች ቀድሞ በሚያምረው ድምጹ በወጣት ጉልበቱ እንዲሁም ቀድሞ በኢትዮጵያ ሬዲዮ በተላለፈው ድራማው የምዘና ስብስብ አልፎ ፋና ሬዲዮን ለማቋቋም በቃ። አቋቁሞም አቁሞ አላስቀረውም። ዮናስ አብረሃም ፀንቶ ወደፊት እንዲራመድና በሰዎች ልብ ውስጥ የማይነቃነቅ መሰረት እንዲኖረው አደረገ። በራሱ ፎርማትና የፕሮግራም ቅርጽ ልብ ለልብን ከልብ መስራት ጀመረ። ለዚህም ከሙያ መንትያው እማዋይሽ ዘውዱ ጋር እሩቅ ለመጓዝ አልሞ ተጣመደ።
አዲሱ የልብ ለልብ ዝግጅት ፋና ሬዲዮ ነፍስ ዘርቶ ሬዲዮ እንዲሆን አደረገው። ከ10 ዓመታት በላይ ያለማቋረጥ የተላለፈው እና በሰው ልብ ውስጥ ተዘርቶ የአንድን ልጅ ዕድሜ ያህል ያደገው የልብ ለልብ አዝናኝ የቁምነገር ትረካ በባለቤቱ ዮናስ አብርሃምና በድምጸ-ስርቅርቋ እማዋይሽ ዘውዱ በፋና ላይ ገነነ። ጋዜጠኛ ዮናስ አብርሃም በዚህ የልብ ለልብ ዝግጅቱ ላይ የሰውንልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የፍቅርን ልዕለ ሀያልነት የነፍስን የውዴታ መቃተት በመቃተት ውስጥ የሚመጡ ተግዳሮቶችን ኹነት የማይታየውን ስውር ሥርዓተ ስበት ፊደል ደርድሮ ቃል ሰድሮ እንኳን ያፈቀረን የልብ ሰው ይቅርና ያላፈቀረን በልቦና የሚያስፈቅር ብዕረኛ ሆነ።
አሁን ፋና ሬዲዮ ስሩ ቢማስ በእርግጥም መሰረቱን በልብ ለልብ ፕሮግራም ላይ ቆሞ ያገኘዋል። ሬዲዮን አክብረው ዝግጅቱን ወደው የሚሰሙቱ አድማጮቹ የልባቸውን ሀሳብ በወረቀት ጭነው በ2 ቀን 3 ዶንያ ያህል ልከዋል። “ያለ ባለቤቱ አይነድም እሳቱ ” እንዲሉት ነገር ዮናስ ፋና ሬዲዮን ትቶ በሄደበት ወቅት ልብ ለልብ በሌላ ባለሙያ እንዲቀጥል ቢደረግም ሳይሳካ ቀርቷል።
እንደወጣትነቱ በወጣትነቱ ወጣቶችን የሚመለከቱ የትኛዎቹንም ፕሮግራሞች ያለገደብ በልዩ ልዩ ይዘት ሰርቷል። በተለያዩ ደራሲያን በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፉ እና ለኢትዮጵያ ልጆች ይጠቅማሉ ያላቸውን የልጆች መጽሐፍት በሀገረኛ ቋንቋ በውርስ ትርጉም በመተርጎም አገልግሏል። በፋና መጽሔት በተለያዩ ክልሎች እየተዘዋወረ የሴቶችን ፣ ወጣቶችን ፣ ግብርና የተለያዩ ጉዳዮችን በመያዝ አስተምሯል እውቀት ከእውቀት አገናኝቷል። የማህበረሰብን ትውውቅ ፈጥሯል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አምላክ አገልጋዩን ይፈትናል ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን አገልጋዩን ጋዜጠኛ የገጠመው ይህ ነበር። እንደተለመደው በአንድ ወቅት ለሥራ ከከተማ የወጣው ዮናስ ከሄደበት ተመልሶ ቤቱ ለማረፍ ሲገሰግስ ሰው አልባ ወና ሆኖ አገኘው። አንድም ቤተሰብ የለም። ቤቱ በዝምታ ተውጦና ተለውጦ ሁለመናው የዘመድ አልቃሽ ቤት ሆኖ አገኘው። ነገሩን የተረዳው ዮናስ በሚወደው ሙያ ጉያ ለመወሸቅ ሲሮጥ ፋና ተመለሰ። ወቅቱ (1990) ነበር። ምክንያቱ ደግሞ
አሳርና አሰር የማያጣት ሀገራችን የልጅ ዶሴ ቀስቅሳ የሰሜን ኢትዮጵያን ተወላጆች ውጡልኝ ስትል ለፈፈች ። ምንም’ኳ እኛ ኢትዮጵያዊያን ነን ቢሉም የለም እናንተ ኤርትራዊያን ናችሁ በማለት ከልባቸው የማያወጧትን እናት ሀገራቸው ኢትዮጵያን በልባቸው አቅፈው ጓዛቸውን ሰብስበው በርካቶች ከእናት ሀገር ኢትዮጵያ ወደ ግልገሏ ሀገር ኤርትራ በግዴታ ተሰደዱ ።
የዚህ ስደት ሰደድ ነበልባል የዮናስን ነፍስና ስጋ ሳይገርፋት አላለፈም። የጋዜጠኛ ዮናስ አብርሃም ቤተሰቦች ከእናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ሀገራችሁ አይደለችም ተብለው ሌላ ሀገር ተሰጥቷቸው እንዲሰደዱ ተደርጎ ነበር። ይሄኔ ትንታጉ ጋዜጠኛ በወቅቱ ያለ ቤተሰብ ብቻውን የውኃ ላይ ኩበት ሆኖ ቀረ። ከሙያው በስተቀር የሚደበቅበት አንዳች ነገር አልነበረውም።
በሙያውም ቢሆን ስለሰላም ሰበከ እንጂ የተወለድኩባት ሀገር ያሳደገኝ ማህበረሰብ ክዶኛል ሲል አላላዘነም። መንግሥት ቤተሰቤን ነጥቆኛልና እኔም ሀገር የለኝም ብሎ ቁርሾ አላንቀራጨም። ጎራ ለይቶ ሚዛን አዛብቶ በሙያው መጥፎ ነገርን ለማድረግ አላሰበም። ይልቁንም ይህንን ሀሳብ ከላይ እስከታች እየተመላለሰ ጋዜጠኝነቱን ከፈጠራ ስራ ጋር እያዋሀደ ሀገሩንና ህዝቡን ይበልጥ አውቆ ለማሳወቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ስለእውነት በእውነት ጥረት አደረገ እንጂ። የሰላም ጋዜጠኛ በመሆን ጦርነት በሀገር ኢኮኖሚ ፣ በማህበራዊ አንድነትና ስነልቦና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት እና ኢትዮጵያዊነት የህዝብ ፍቅርና መደጋገፍ መሆኑን ከመቼውም ጊዜ በላይ በጨለማ ውስጥ በሥራዎቹ አጉልቶ አሳይቷል።
ዮናስ በዚህ ወቅት የደረሰበትን የስነልቦና ውደቀት እና ድቀት ተቋቁሞ በብዕሩ ከልብ በልብ ለልብ ሀገርና ማህበረሰብ ሰርቷል። ዮናስ አብርሃም እና በኤርትራ ሀገር ያለ ጋዜጠኛ ወንድሙ የአንድ ሀገር እና የአንድ እናት ልጆች አንድን ማህፀን የተጋሩ ሁለት ወንድማማች ጋዜጠኞች የተለያየ አቋም ይዘው ለሁለት ሀገር ሲሟገቱ እንደጠላት ሲተያዩ ሻዕቢያ እና ወያኔ ሲባባሉ ድፍን 20 ዓመታት ማሳለፋቸው የቅርብ ጊዜ የሦስት ዓመታት ዕድሜ ትዝታ ነው ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ
“ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም” እንዲሉ ቤተሰቡን ሀገር አልባ ያደረገው መንፈስ ዞሮ ከዮናስ ደረሰ። ዮናስ ከአዲስአበባ እንዳይወጣ ስራም እንዳይሰራ ታገደ። ይህ ታላቅ የሙያ ሰው ጎዳና ወጥቶ ወደቀ። ከመደበቂያው ከመሸሸጊያው ፋና ለቆ ለሦስት ዓመታት ያህል ያለቤተሰብ ያለስራ ሲንጓለል በየጎዳናው ዳር እየተንከላወሰ አሳዳሪ ሲያገኝ ከቤት ሲያጣ የትም ስጋውን እያሳረፈ ቀላል የማይባሉ ፈተናዎችን ለመረዳት ኖሮ ማለፍን የሚጠይቁ መከራዎችን ለማለፍ ተገደደ።
በ (1993) የፋና መኪና ዮናስን ባገኘው ጊዜ ለሥራ ትፈለጋለህ ብሎ እስኪወስደው ድረስ የፈለገው አልነበረም። አንጀቱን ያጠብቅበት እህል ጉሮሮውን ያረጥብበት ውኃ ሲያገኝ ፋና ገብቶ ጠረጴዛ ላይ የተከመረ ጋዜጣና መጽሔት መግፋት ጀመረ። ዮናስ እነዚያን ያሳለፋቸውን የሦስት ዓመታት ውጥንቅቶች በብዕሩ ወግቶ ወረቀት ላይ እያፈሰሰ ይቀንሳቸው እና እንባዎቹን በጥርሶቹ ነክሶ ይቀኛቸው ብሎም እንደ አንድት ሀገር አጀንዳ ይዞ ሲጽፍባቸው ቆይቷል። ጠንካራ ስብዕናን ለመገንባትና እውነትን በተግባር ለመኖር ሚዛናዊና የተረጋጋ ሰው እንዲሆን አስችለውታል። ወደፋና ከገባ በኋላ ለስራው ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ በመስራት እራሱን በስራ ጠምዶ በማያበራ ትግል ውስጥ ለዓመታት አሳልፏል። ” ያለ ሬዲዮ የምሞት ይመስለኛል ” የሚለው ዮናስ አብርሃም ሬዲዮ የምፈልገውን ያህል ሀሳብ የሚያስተላልፍበት ለመንገርና ለማስተማር የፈለገውን በቀላሉና አመቺ በሆነ መንገድ የሚያደርስበት ሚዲያው በመሆኑ አንድ ሰው ሳለ በአንድ የስራ ክፍያ የብዙ ሰዎችን ስራ ያለስፍር ሰርቷል።
ጠንካራው አይበገሬው የሀገር ልጅ ጋዜጠኛ ዮናስ አብረሃም በሬዲዮ ቋንቋ እና በሥነጽሑፍ ለዛ የትኛውንም ትምህርታዊ ፕሮግራም ቢሰራ በይዘቱ አስተማሪ ሳለ በአቀራረቡ ግን መዝናኛ ነው። ከሀዘን ጀርባ ያለን ሳቅ በማቅረብ አንገት ያስደፋን ጉዳይ በማቅናት ከጉዳዩ በተቃራኒ ያለውን በመጠቆም ወቅታዊን ጉዳይ የሚፈልገውን የመፍትሔ አቅጣጫ በማሳየት የአንድ ሰው ጉዳይ የየራሳችን የየቤታችን ጉዳይ አድርጎ ማምጣት እና ሁሉም ሰው ችግሩን የራሱ አድርጎ መፍትሔ እንዲፈልግ የሚያደርጉ ፕሮግራሞችን በራሱ ፎርማት በመቅረጽ ለዓመታት ሰርቷል።
ምንምኳን ዕውቅናን ያገኘው በልብ ለልብ ፕሮግራሙ ቢሆን ዓለም በፋና ፣ ፋና መጽሔት ፣ እና እንደ ትንንሽ ፀሐዮች ያሉ ትልልቅ ፕሮግራሞች ነበሩት። አሉትም። ዓለም በፋና የሬዲዮ ቱሪዝም ዝግጅቱ እጅግ ተወዳጅና አስገራሚ ሲሆን ሰዎች ሬዲዮን ከፍተው በተቀመጡበት ተራራ እየገፉ ሲያልባቸው ፣ ቁልቁለት ሲወርዱ ጉልበት ሲከዳቸው ፣ በሚያቋርጡት ጫካ መካከል የሚወርደው የቅዝቃዜ ስሜት በላያቸው ሲያርፍ ፤ አእዋፋት ለመብረር የሚሰብቁት ክንፍ ከከንፋቸው የተነቀለች አንድት ላባ የምታወጣው ድምጽ ፤ የንፋሱ አቅጣጫ ሳይቀር የቆሙበትን የአሸዋ እርጥበት ሲገርፈው ይሰማቸዋል። አጀብ አገር ብለው ተደምመዋል። እጃቸውን በአፋቸው ጭነው ለዓመታት በጉጉት አድምጠዋል ። አንጋፋ የተባሉ በሙያም በእድሜም ከዮናስ በላይ የሆኑቱ በታላቅ አክብሮት ተከታትለውታል። ተደምመውበታል።
የራቀውን ዓለም አቅርቦ ለህዝብ አሳይቷል። ህዝብን ከህዝብ መንግሥትን ከመንግሥት አቀራርቧል። በቱሪዝም ዘርፉ ሰዎች ለጉብኝት ያለቸውን ፍላጎት እንዲጨምር የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። የዓለማችንን ታሪክና ባህል ለህዝብ አስተዋውቋል። ዓለም በፋና ያልዳሰሰው ሀገር ያላሰሰው መንደር የለም። ሁሉም እግርና ዓይኑን ጆሮው ላይ አድርጎ በመጓዝ ተፈጥሮና ፍጥረታትን ጎብኝቷል። ጋዜጠኛ ዮናስ አብረሃም ከከተማ ሳይወጣ በመረጃዎች ብቻ ተጉዞ ዓለምን ያሳዬ ከሆነ ዘንዳ በአካል ተገኝቶ የመስራት ዕድል ቢያገኝና አጋጣሚው ቢመቻችለት ኖሮ በእርግጥም ከዚህ በላይ መስራት እንደሚችል እሙን ነው።
በሀገር ውስጥም ቢሆን ያልዞረበት የኢትዮጵያ ክፍል ያልረገጠው መሬት የለም። በእግሩ ባይጓዝ እንኳን በብዕሩ ሄዶ ቡና ማስፈላት ይችላል። ይህ የጉዞ ስራው ሀገሩን በደንብ እንዲያውቅ እና እንዲረዳ እራሱንና ማንነቱን እንዲወድ አመዛዛኝ እና ጠያቂ እንዲሆን አግዞታል። የሚኖረውም የሚሰራውም ያየውን እና ያመነበትን እውነት ብቻ ነው። የስራዎቹም መነሻ ያያቸው አካባቢዎችና የህይወት ውጣ ውረዶች የማህበረሰብ ታሪክና ባህሎቹ ናቸው። ዛሬ ሰሜን ተጉዞ ከሆነ በማግስቱ ደቡብ የሚዘልቅ የደቡቡን አቀብሎ በስተምስራቅ የሚያቀና የምስራቁን ሰጥቶ ለምራዕብ ተሸኝቶ የሚያድር ያለእረፍት የሚያገለግል ባለሙያ ነው። የኢትዮጵያ ሀገራችን ማህበራዊ ህይወትና የኢኮኖሚ መሰረተ- ልማት በዮናስ ብዕር ተቃኝቷል። እንደጋዜጠኛ እውነታውን ነግሮ እንደ ሥነ-ጽሑፍ ባለሙያ ምናቡን አክሎ በለዛ ተናግሮታል።
ደራሲው ዮናስ አብርሃም የሚያስታውሳቸው በፋና ሬዲዮ የተደመጡ ከ40 በላይ የሆኑ ድራማዎች ይኑሩት እንጂ ቅሉ በርካታ የረሳቸውና የማያስታውሳቸው ስራዎች አሉት። ምክንያቱም እርሱ ይሰራል አይቆጥርም። ይሰጣል አይጠይቅምና ነው። ሥራዎቹ ለህዝብና ለሀገር የተሰጡ በረከቶች ናቸው። ለድራማዎቹ የሚጠቀማቸው ርዕሶች ቃላቶች የተሸከሙት ጥቅል ሀሳብ ብቻውን ድራማ መሆን የሚችል ነው። ለምሳሌ ጥቁር ጽጌሬዳ ፣ የጉም ጅብ ፣ የእሾህ አጥር ፣ የወፍ ስጋ ፣ ሙሉ ጨረቃ፣ ኤሳው ፣ ከስራዎቹ እነዚህን ማንሳት ከማድጋው በገል እንደመጨለፍ ነው። እያንዳንዳቸው ርዕሶች እየሆነ ያለውን ሐቅ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ የነገሮችን ስር ከቅርንጫፉ አስተሳስረው ነገሩ የተቆረጠበትን የሚጠቁሙ ስል የሆኑና እና ስልት የታከለባቸው ናቸው።
ከጣቢያ ጋር በመሆን ልዩ ልዩ ቦታዎች ላይ ፊልድ በመጓዝ ሙዚቀኞች የሚሳተፉበት የመዝናኛና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃግብሮችን በመምራት ውይይት በማካሄድ የሬዲዮ ፕሮግራሞችን ሰርቷል። በራሱም እየተንቀሳቀሰ እንደ ህዳሴው ግድብ ፣ መልካም አስተዳደርና ሌሎች ፕሮግራሞች ላይ በስፋት ተሳትፏል። በማሳተፍ ላይም ይገኛል።
ዮናስ አብረሃም በ(2006) ዓ.ም ፈናን ለቆ ወደኢትዮጵያ ሬዲዮ አቅንቷል። በዚያ ቆይታውም መናፈሻ የተሰኘ የራሱ የምሽት ፕሮግራም ነበረው ። መናፈሻ ልክ እንደ ዓለምን በፋና ሁሉ የሬዲዮ ቱሪዝም የሚመስል ነገርግን አንድ መናፈሻ ውስጥ የሚሰራ ነበር። ዮናስ በምሽት ጨረቃዋን አምጥቶ ስትራመድ ኮቴዋን እስከ ማስቆጠር ፤ ለጨለማው ድምፅ ፈጥሮ እስከ ማዘመር በአድማጮች ጆሮ አልፎ በሀሳባቸው ቦታውን እስኪጋሩ ድረስ ጥበብ በተሞላበት ድንቅ ፕሮግራም በማዘጋጀት እና በማቅረብ ለሦስት ዓመታት ያህል አገልግሏል።
ከኢትዮጵያ ሬዲዮ በኋላ ደግሞ ወደ ብስራት ሬዲዮ ሲመጣ እጅግ አስደናቂ ተወዳጅና አዝናኝ የሆነ ልዩና በወቅቱ ያስፈልግ የነበረን ፕሮግራም ጀምሯል። ይህ ፕሮግራም ከልብ ለልቧ የውብ ድምፅ እመቤት እማዋይሽ ዘውዱ ጋር በጥምረት የሰሩት ከሰፈር ተነስተው መዳረሻቸውን ጠፈር ላይ የዘረጉበት ነው። በአብዛኛው የዕለት ተዕለት ማህበራዊ ህይወታችንን የሸፈና ከታች ተነስቶ እስከ ላይ ድረስ የቃኘ ጋዜጠኝነት ፣ ሥነጽሑፍ ፣ ሙዚቃ እና አባባሎቻችን ሁሉ ተስማምተው ትልቅ ውህደት የፈጠሩበት አስደናቂ ፕሮግራም ከአምስት ዓመታት በላይ ተደምጧል።
ያልገባበት ጓዳ ያልዳሰሰው ችግር ያላየው ብሶት በቤት ቢሆን በጎረቤት በቀበሌ ቢሆን በመሥሪያ ቤት በከተማ ቢሆን በገጠር የተሰወረ አንድም ለእሱ የለም። ሀገር እንዲያውቀው ፀሐይ እንዲሞቀው በማድረግ የመመረረ የህይወት ስቃይ ላይ ከመቆዘም ይልቅ ወይ ስቆበት እንዲያልፍ ብቻ ሳይሆን የችግሩን ሌላኛውን ክፍል እንዲያይና የእይታ መነጽሩን እንዲያሰፋ አድርጓል። ከሰፈር እስከ ጠፈር ተከታታይ የሆነ ድራማዊ ፕሮግራም ሲሆን በየዕለቱ ወቅታዊና ትኩስ የሆኑ አዳዲስ ጉዳዮችን ይዞ የሚወጣ ፕሮግራም ነው። ይህን ፕሮግራም በማዘጋጀትና በማቅረብ ከ 7 አመት በላይ ሰርቷል።
የዮናስ አንጋፋውና ትልቁ ትንንሽ ፀሐዮች ድራማ እማማ ጨቤ ለተከታታይ አምስት ዓመት ተኩል የሄደ ወደ 260 ገደማ የሚሆኑ ክፍሎች ያሉት በአይነቱም ሆነ በትልቅነቱ የአንደኝነት ደረጃን የያዘ ድራማ ሲሆን ይህ ድራማም ወቅታዊ የሆኑ ዜናዎችን የሚያስተላልፍ ዕለታዊ መረጃዎችን ለህዝብ የሚሰጥ ድራማዊ ሥነጽሑፍ ነበር። ለዚህም አርብ ምሽቱን ስለሞተው ማይክል ጃክሰን መርዶ የተሰማው በእማማ ጨቤ የቅዳሜ ጠዋት ድራማ መሆኑን ልብ ይሏል።
ብዕረኛው ደራሲ ፣ ጋዜጠኛና ፀሐፌ ተውኔት ዮናስ አብርሃም ከዘጋቢው ጀርባ የተሰኘ በጋዜጠኞች ህይወት ላይ የሚያጠነጥን ልቦለድ መጽሐፍ እና ሦስተኛው ዓይን የተሰኘ የግጥም መድብል መጽሐፍ ያሳተመ እና ወደህትመት ያላስገባቸው ከዘጠኝ በላይ መጽሐፍቶች በእጁ ላይ ያሉት ስክን ደራሲ ነው። ጋዜጠኛ ዮናስ አብረሃም ሳይኖር መኖር የሚቀናው ከግርግርና ከሁካታ ገለል ብሎ በህዝብ መካከል ደብዞ መኖርን የሚመርጥ የተረጋጋ ብዕረኛ ነው። ሀገርን ማህበረሰብን የኑሮ ውጣ ውረድን ነገና ትላንትን ከፍታና ዝቅታን ሁሉን እንደሁሉ ዛሬ ላይ ሆኖ የቃኘባቸው የብዕሩ ውጤቶች እልፍ ናቸው። ከእያንዳንዱ የማስታወቂያ ጀርባ ስክሪፕት በመጻፍ ፣ ትልልቅ መድረኮችን በመምራት ፣ የበዓል ቀን ድራማዎች በመሥራት ፣ የድርሰት ስራዎችን በመከወን ላይ ይገኛል።
ዮናስ ለሙዚቀኞችም በርካታ ግጥሞችን ሰጥቷል። ከሰጣቸው ሰዎች አንድ ለመንገድ እናንሳ ብንል ለተወዳጇ ድምፃዊት ፍቅር አዲስ ነቃጥበብ ” የእምዬን ውለታ ” ይጠቀሳል። በኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን ህፃናትን ከመቅረጽ አኳያ ብዙ ድርሻዎችን ተወጥቷል። ለትልልቅ ባንኮችና ልዩ ልዩ ተቋማት (Team Word or Moto) ሰርቷል። ለየኢትዮጵያ ሬዲዮ ” ከንጋት እስከ ንጋት በትጋት ” ለብስራት ሬዲዮ “ከማለዳ የወፎች ጫጫታ እስከ ውድቅት የነፍስታ ሲርሲርታ ” የዮናስ ብዕሮች ናቸው። እነዚህ ብቻ አለመሆናቸውን ግን ልብ ይሏል። ሰጥቶ ማንሳት ግብዝነት እንዳይሆን ሲባል ላለማንሳት በመፈለግ እንጂ ሌሎችም እጅግ በርካቶች ይገኙበታል።
ጋዜጠኛ ዮናስ አብረሃም በአዲስ አበባ Mass media School ፣ በህንድ ሀገርና በአፍሪካ ሀገራት ተጉዞ የጋዜጠኝነት ሥልጠናን ወስዷል። ይሁን እንጂ ዮናስ ” ጋዜጠኛ ትምህርትና እውቀቱ የሚታየው በሀገርና በህዝብ ላይ ነው። ጋዜጠኛ ሁለገብ የሆነ እውቀት ያስፈልገዋል። እኔ እውቀት እንጂ ወረቀት አያሻኝም ይላል። “
ጋዜጠኛ ዮናስ አብረሃም በአሁኑ ሰዓት ከማማ ጨቤ ቀጥሎ ወቅታዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን እያነሳ የሚያዝናና የጨረቃ ውል የተሰኘ ትልቁ ድራማ በፋና ሬዲዮ ላይ ከውጭ ሆኖ እየሰራ ይገኛል። ዮናስ አብረሃም ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን ምን’ኳ በስተመጨረሻ አባቱን በህይወት ያጣቸው ቢሆንም ከለውጡ በኋላ ቤተሰቡን ማግኘት እና እናቱን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት እና አብሮ መኖር ችሏል።
የመዝጊያ
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ጋዜጠኛ ዮናስ አብርሃምን እንዲህ ነው ብሎ ለመግለጽ በእርግጥም ያስቸግራል። እርሱ ተሰጥኦው ብዙ መቻሉ እልፍ ነውና አንድ የሙያ ምድብ ውስጥ ለመክተት ቀላል አይደለም። ከ (1987) ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከ 27ዓመታት በላይ በተለያዩ ሙያዎች ያገለገለ እና እያገለገለ ያለ ሀያል ብዕረኛ ነው። ሀገር ሲገፋው ፀንቶ የቆመ። ሲጠሉት የወደደ የምር ሰብዓዊ ሰው ነው።
አድማጭ አንድ የሆነ ቁምነገር ከኔ ዝግጂት ማግኘት አለበት ሲል ጥንቅቅ ያሉ ፕሮግራሞችን በመስራት ለህዝብ ሲያደርስ ቆይቷል። ሬዲዮ ሱቅ ሆኖ ማንም ሰው ተነስቶ በሚያፏጭበት እና ገንዘብ በሚያግበሰብስበት ሀገርና ህዝብ ለማጋጨት በስፖንሰር በሚንቀሳቀስበት በዚህ ወቅት ስለሰላም የሰበከ አብሮ መኖርን የመረጠ ከልብ ያስታረቀ ብዙዎችን በስሩ ያስጠለለ ዋርካ የመከረ ሽማግሌ ነው።
የበጎ ሰው አልያም የአርዓያ ሰው ሽልማት ቢኖር ኖሮ ሀገር የሚሸልመው በአንድ ልብ ለልብ ፕሮግራሙ ብቻ ጋዜጠኛ ዮናስ አብርሃምን ነው ብንል በእርግጥ አልተጋነነም። የጎጥ ፖለቲካ የሚያራምዱ ሚዲያውን ለጎጥ አላማ ብቻ የሚጠቀሙ ብዕራቸው የበለው በለው የሆኑቱ በእርግጥም ክፍያቸው የላቀ ዝናቸው ያነጋገረ ነው። እንደዮናስ ያሉትን ግን የድካማቸውን ሳያገኙ እንደ ምጣድ እህል ከላይ ከታች ሲበግኑ ይኖራሉ። ያልፋሉም።
ባለቸው ሙሉ አቅም ብዕራቸውን ሳይሰስቱ ፣ ጉልበታቸውንና ሙያቸውን ሳይቆጥቡ ሀገራቸውና ህዝባቸውን ለሚያገለግሉ ባለሙያዎችና ባለውለታዎች ምስጋናም፣አክብሮትም፣ ዕውቅናም መስጠት ይገባል። ይህንን ማድረግ ሌላ ባለሞያዎችን ለመፍጠር ያስችላል እነሱንም ማበርታት ነው ብሎ ተወዳጅ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን የሚያምን በመሆኑ የዮናስ አብርሃምን ታሪክ በጽሑፍ ሰንዷል።
ፀሐፈ-ተውኔት ፣ ደራሲ ፣ ገጣሚና ጋዜጠኛ ዮናስ አብርሃም ስላበረከታቸውና ወደፊትም ስለሚያበረክታቸው ሙያዊ አገልግሎቶቹ እንደተወዳጅ ሚድያ አክብሮታችንን እንገልጻለን፡፡/ ይህ ጽሁፍ ባለታሪኩን ቃለ-መጠይቅ በማድረግ፤የባለታሪኩን የቅርብ ሰዎች በማነጋገር ፤ የተጻፈ ነው፡፡ ጽሁፉ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉና በጋዜጠኛ ባንቺአየሁ አሰፋ