የፋናው ፍስሐ ጌትነት እና ባልደረቦቹ ሊደነቁ ይገባል

 ከዕዝራ እጅጉ( ተወዳጅ ሚድያ)

ትናንት ምሽት ላይ ፋና ላይ ባየሁት የናሲዖል ዋሻ ዶክመንተሪ ተደንቄ ነበር። ተፈጥሮ ምን ያህል ረቂቅ፣ እግዚአብሔርም ድንቅ መሆኑን ያስተዋልኩበት ነው። የፋና የዘጋቢ ፊልም ቡድንም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለዕይታ አቅርቦልናል። ይህን ዋሻ ያገኘው ብቸኛው የዋሻ ተመራማሪ ናስር አህመድ ሊጨበጨብለት ይገባል። በእርግጠኝነት የቱሪዝም ሚኒስትር በናሲዖል ዋሻ ላይ ተጨማሪ ጉብኝት እንደሚመራ አልጠራጠርም። ቁርጠኛዋ ሚኒስትር ሰላማዊት ካሣ ይህን ሀሣብ ይዘው ናሲዖልን የቱሪዝም መዳረሻ ወይም የሚጎበኝ ሥፍራ እንደሚያደርጉት ዕምነት አለኝ። ይህን ዶክመንተሪ የሠራው ጋዜጠኛ ፍሰሐ ጌትነት አድናቆት ሊቸረው ይገባል። እርሱ ብቻ ሳይሆን መላ የቀረፃ ቡድን መመስገን አለበት።ዋጋ ከፍለው ነው የሠሩት።

ፍሰሐ ጋዜጠኝነትን የጀመረው በጎንደር ፋና ኤፍ ኤም 98.1 ነው፡፡ ከዚያም በቁምነገር መጽሔት እስከ ዋና አዘጋጅነት አገልግሎት ሰጥቷል።በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በስፖርት ጋዜጠኝነት፣ በዋልታ ቴሌቪዥን ከአዘጋጅ እስከ ክሬቲቭ ቡድን ዳይሬክተርነት እና አሁን ደግሞ በፋና ቴሌቪዥን የዶክመንተሪ ክፍል ረዳት ዋና አዘጋጅ በመሆን እየሠራ ይገኛል። ሥነ-ጽሁፍና ተፈጥሮን በእጅጉ ያደንቃል።

   ወደ ናሲኦል ዋሻ

ለቀረጻ የተንቀሳቀሱት የፋና ቴሌቪዥን ቡድን አባላት ሦስት ነበሩ፡፡ ሾፌር ጀማል እንድሬ፣ የካሜራ ባለሙያችን መስፍን በሪሁን እና አዘጋጁ ፍሠሀ ጌትነት።

ፍሰሀ ስለ ዋሻው አስቀድሞ በሰበሰባቸው መረጃዎች የተለያዩ ፎቶዎችንና ጥቂት ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በማየቱ ወደ ሥፍራው የመሄድ ጉጉቱ ከፍ ያለ ነበር፡፡ ናሲኦል ዋሻ ለመድረስ ከአዲስ አበባ ተነስተው ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ በመኪና ተጉዘዋል። አቅጣጫው ወደ ሐረር መስመር ሲሆን ከቆቦ ከተማ በኋላ ወደ ቀኝ ታጥፈው በአስቸጋሪ የጠጠር መንገድ ተጉዘው ነው መልካ በሎ ወረዳ የደረሱት፡፡ መልካ በሎ የናሲኦል ዋሻ መገኛ ቦታ ነው፡፡

ፍሰሀ ለተወዳጅ ሚድያ በሰጠው ሀሣብ፦

“…የአካባቢው ነዋሪዎች ዋሻው በሚዲያዎች እንዲተዋወቅ በእጅጉ ይፈልጋሉ፡፡ በደረስንባቸው ትንንሽ ከተሞችና የገጠር መንደሮች በፍቅር እየተቀበሉ አስተናግደውናል፡፡ የዋሻው አናት ድረስ የሚወስደንን ጥርጊያ መንገድ በእጃቸውና ባገኙት መሣሪያ በማስተካከል ድካማችንን አቅልለውልናል፡፡ ዳስ ሠርተው ማደሪያ አዘጋጅተውልናል፡፡ ” ሲል ፍሰሀ ለአካባቢው ነዋሪዎች ምስጋናውን ይቸራል።

ናሲኦል ዋሻ ዙሪያው በጫካ የተሸፈነ ከተራራ ስር የሚገኝ አስደናቂ ቦታ ነው፡፡ ይህን ዋሻ አስሶ ያገኘው በኢትዮጵያ ብቸኛው የዋሻ ተመራማሪ (ስፒሊዮሎጅስት) ናስር አህመድ ነው፡፡

ዋሻዎች ኃብትን፣ እውቀትንና ታሪክን በውስጣቸው የያዙ የሚስጢር ቋቶች ናቸው፡፡ ረጅሙ የሰው ልጆች የሕልውና ታሪክ የሚጀምረውም በዋሻዎች ውስጥ ነው፡፡

የዋሻ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ናስር አሕመድ÷ በምስራቅ ሐረርጌ፣ ምዕራብ ባሌ እና አርሲ አካባቢዎች በርካታ አስደናቂ ዋሻዎች በብዛት እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡

ከ400 በላይ የሚሆኑትን ፈልጎ በማግኘትና በማጥናት በመጽሐፍ አሳትሞ ለዓለም ቱሪዝም ለማስተዋወቅ ሙከራ ያደረጉት ተመራማሪው÷ እነዚህን ዋሻዎች በተመለከቱበት ወቅት ለአንድ ልዩ ዋሻ የተለየ ፍቅር እንዳደረባቸው ያስረዳሉ፡፡

ይህ ዋሻ ናሲኦል በመባል የሚጠራ ሲሆን ÷ ዋሻውን ያገኙት፣ መርምረው ርዝመቱን የደረሱበትና በውስጡ ተጉዘው ውበቱን በመቅረጽ ለዋሻ አፍቃሪዎች ያስተዋወቁት ተመራማሪ አቶ ናስር ናቸው፡፡

የዋሻው ስያሜም ከተመራማሪው ስም በመነሳት የተሰጠ ነው፤ “ናሲኦል” የሚለው ስያሜ ትርጉሙ ከሁሉም የላቀ ማለት እንደሆነ አብራርተዋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች ዋሻዎች ካላቸው ባህርይ አንጻር የሕክምና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ፊዚዮቴራፒ እና የቱሪዝም ዋሻዎች በሚል እንደሚከፋፈሉ ያስረዳሉ።

በዚህ ረገድ በተለያዩ ሀገራት ተዘዋውረው ብዙ ዋሻዎችን የተመለከቱት አቶ ናስር በውበቱ ተወዳዳሪ እንደሌለው የመሰከሩለት ናሲኦል ከቱሪዝም ዋሻዎች ጎራ የሚመደብ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

በቅርብ ጊዜ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ይህንን ድንቅ ዋሻ እንደሚጎበኙት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

እነ ፍሰሀ 530 ሜትር ያህል ርዝመት ባለው ዋሻ ውስጥ ከካሜራ ባለሙያ መስፍን በሪሁን ጋር በመሆን በቀን እና በምሽት፣ በካሜራና እና በድሮን ቀረጻ አድርገዋል።

በእያንዳንዱ ቀረጻ ወቅት በትንሹ ከስድስት ሰዓት በላይ በውስጡ ቢቆዩም የዋሻው ውበት ድካምንም፣ ረሀብንም የሚያስረሳ እንደነበር ፍሰሀ ይናገራል።

“…..በፎቶና በተንቀሳቃሽ ምስል ካየሁት በላይ እጅግ ድንቅ ነበር፡፡ በዋሻው ውስጥ ያለውን የኦክስጅን እጥረትና ከፍተኛ ሙቀት ተቋቁመን ለመጀመሪያ ጊዜ ከ500 ሜትር በላይ በውስጡ በመጓዝ ውበቱን በድሮን ካሜራ ጭምር ቀርጸን ለተመልካች ለማሳየት ችለናል።  ናሲኦል ለእኔ በውበቱ ከሶፍ ኡመርም በላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙትን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ተዘዋውሮ ዋሻዎችን የጎበኘው፣ ያጠናውና የመረመረው ናስር አህመድም ቢሆን ናሲኦልን ‹የውበት ልክ ነው ሲል ያወድሰዋል፡፡” በማለት ጋዜጠኛ ፍሰሀ ጌትነት አጫውቶናል። እኛም ይህን ዘጋቢ ፊልም ትመለከቱት ዘንድ ጋብዘናል።

https://www.facebook.com/reel/1143553250906258/?mibextid=rS40aB7S9Ucbxw6v

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *