ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን የባለሙያዎችን የሕይወት ታሪክ ሰንዶ በማስቀመጥና በማሰራጨት፣ በመፅሐፍ ላይ እንዲታተም በማድረግ የባለሙያዎች አበርክቶ ተዘንግቶ እንዳይቀር የበኩላችን እየተወጣ ይገኛለን፡፡ እስከዛሬ ከ 400 በላይ በሚድያ እና በኪነ ጥበብ ሙያ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ጨምሮ ሌሎችም ታሪካቸው በመረጃ ቋታችን ላይ እንዲቀመጥ አድርገናል፡፡ ስለ እነርሱ ለማወቅ በተፈለገ ጊዜም ፣ታሪካቸው በቀላሉ መገኘት እንዲችል የዲጂታል አማራጮችን በማቅረብ የታሪኰቹ ተደራሽነት ዕውን እንዲሆን ሁሉን አመቻችተናል፡፡
ታሪኮቹ በጥራዝ መልክ ተሠንደው ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑም ቅፅ አንድ እና ቅፅ ሁለት መዝገበ አእምሮን እያንዳንዳቸውን በ600ገፅ አድርገን አዘጋጅተን፣ አሳትመን ፣ አስተዋውቀን እና አስመርቀን ሀገራዊ ኃላፊነታችንን ተወጥተናል፡፡ አሁንም የስነዳ ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን የመማክርት አባላት እንዲሰነዱ ስምምነት የደረሱባቸው ባለሙያዎችን እያፈላለግን መሥራታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በቅፅ ሁለት የሕይወት ታሪካቸው ከሚሰነድላቸው መካከል የአዲስ ነገሩ ዐቢይ ተክለማሪያም አንዱ ነው፡፡ ስለ ዐቢይ ለመፃፍ ስንነሳ ቀዳሚ ግባችን በአገሪቱ የሕትመት ሚድያ አፃፃፍ ላይ የራሱን አሻራ ያኖረ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለትም የዛን ጊዜ የነበረው የመዝናኛ እና የአዲስ ነገር ጋዜጦች የዝግጅት ቡድን ምን ያህል ጠንካራ ስብስብ እንደነበር ለማሳየት በማሰብ ነው፡፡ ይህ ቡድን በዐቢይ የሚመራ በመሆኑ የዛን ጊዜ ከነበረው ዐቅምና ጉልበት የዛሬዎቹ የሚድያ ሰዎች ምን ልንማር እንችላለን ? የሚለውንም ለመጠቆም ፈልገንም ነው።በአሁኑ ሰዓት የሕትመት ሚድያው ማንሠራራት ሲገባው ጭራሽ ያሉትም የህልውና አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡ እናም በዚህ አጋጣሚ የሚመለከታቸውን ለማንቃት ይህ መጣጥፍ አንዳች አስተዋፅዖ ያበረክታል ብለን እናምናለን፡፡
ይህን ፅሑፍ ለማጠናከር ቀና ተባባሪ ሆነው መረጃ የሰጡንን ሰዎች ከታች በተቀመጠው መልኩ ምስጋናችንን ልናቀርብ እንወዳለን፡፡
ሕሊና ተክለማሪያም የዐቢይ ታናሽ እህት
ጌታቸው አዲሱ የዩኒቨርሲቲ አብሮ አደግ ጓደኛ
ዳኝነት መኰንን የሥራ ባልደረባ
ኤፍሬም ታደሰ አብሮ አደግ
ኤፍሬም ወዳጆ ገብሩ ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ የሚተዋወቁ
ባሳዝነው ወንድሜነህ የአዲስ ነገር ግራፊክስ ዲዛይነር
በተለይ ዳኝነት መኰንን እና የሕግ ባለሙያ ጌታቸው አዲሱ ‘የሠራ ሰው በአደባባይ መመስገን እና መታየት አለበት ታሪኩም ዘመን በሻጋሪ ዀኖ መሰነድ ይኖርበታል’ የሚለውን መርሀችንን ተገንዝበው በተገቢው መልኩ ስለረዱን እና ትክክለኛ መረጃ ስለሰጡንም በልዩ ሁኔታ የምስጋና ቃላትን ማቅረብ እንወዳለን፡፡
ይህ የሕይወት ታሪክ ፅሑፍ ከነገ ወዲያ ሐምሌ 7 2017 በይፋ የሚከበረውን 48ኛ ዓመት የዐቢይን ልደት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ሲሆን የፅሑፉም ባለመብት ተወዳጅ ሚድያ መዝገበ አእምሮ ዝግጅት ክፍል ሲሆን ፅሑፉንም ወስደው ሲያሰራጩ ምንጭ መጥቀሱን ፈፅሞ እንዳይዘነጉት፡፡ የፅሁፉ አዘጋጆች ታደሰ ማሞ እና ዕዝራ እጅጉ ሲሆኑ የማህበራዊ ሚድያውን ፖስተር ያሰናዳው ዘሪሁን አሰፋ ነው፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ነገር ጋዜጣ እና ዐቢይ ተክለማርያም
መግቢያ
በኢትዮጵያ የህትመት ታሪክ የ1980ዎቹን አጋማሽና እንዲሁም ከምርጫ 97 ፊትና ኋላ ጋር ተያይዞ የታዩትን የጋዜጣና የመፅሄት ህትመቶች መናኘት የሚያስታውሱ አብዛኞቹ አንባቢያን ክስተቱን በዝናብ ወቅት መሬትን ፈንቅሎ አየሩን እየቀዘፈ የአእዋፋት ቀለብ ከሚሆነው የክረምት አሸን ጋር ያመሳስሉታል፡፡
በተለይ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ የሥራ ፈቃድ ወስደው መታተም ከጀመሩትና የንባብን ጥም ይቆርጡ ነበር ከሚባሉት ጋዜጦች መካከል ከጥቅምት 16 /2000 ዓ.ም ጀምሮ ገበያውን ተቀላቅላ የነበረችው “አዲስ ነገር “ጋዜጣ አንዷ ናት፡፡በየሳምንቱ ቅዳሜ ትታተም የነበረችውን ጋዜጣ ቀኑ ደርሶ ገዝተው አዝናኝ ትንታኔዎቿን ይኮመኮሙ የነበሩ አንባቢዎቿ በደስታ ይጦፉበት የነበረው የጋዜጣዋ ትዝታቸው ዛሬም ድረስ አልበረደላቸውም፡፡
ዐቢይ ተክለማርያም ማነው ?
አዲስ ነገር ጋዜጣ ስትታወስ በተለይም በገፅ ሁለት ላይ የወቅቱን አቢይ ጉዳይ በመተንተን የሚታወቀው የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ ዐቢይ ተክለማርያምን በዋናነት አለማንሳት አይቻልም፡፡
ዐቢይ ተክለማርያም መገንታ ከአባቱ ከአቶ ተክለማርያም መገንታ እና ከእናቱ ከወይዘሮ ፋንቱ መንገሻ በአዲስ አበባ በሰሜን መውጫ በር በኩል ልዩ ስሟ “ዳትሰን ሰፈር” በምትባለው አካባቢ ሐምሌ 7 1969 ዓ.ም ተወለደ፡፡ዐቢይ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በአለም ብርሃንና በራስ አበበ አረጋይ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በየካቲት 12 (በመነን) ተከታትሎ ያጠናቀቀ ቀለም የገባው ተማሪ ነው ይላሉ ቤተሰቦቹና አብሮ አደጎቹ፡፡
ዐቢይ በ1990 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪውን ያገኘ ሲሆን ኋላም ወደ እንግሊዝ አምርቶ በሚዲያ ህግ በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቋል፡፡በዚህም ሳያበቃ በለንደን ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በዶክትሬት ደረጃ በክብር ተመርቋል፡፡ዓቢይ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ከሁሉም ተማሪዎች አንደኛ እየወጣ ይሸለም የነበረ በዩኒቨርሲቲም ሰቅሎ የተመረቀ የልጅ አዋቂ ነው ይሉታል አብረው የተማሩ ጓደኞቹ፡፡ለዚህም የረዳው በየላይብረሪው እያሳደደ የሚያነባቸው መፃህፍትና የቤተሰቦቹ የየእለት ክትትልና ምክር እንደሆነም ታናሽ እህቱ ህሊና ተክለማርያም የጓደኞቹን ምስክርነት ታፀናለች፡፡
ያማ ባይሆን ኖሮ ለፒያሳ ቅርብ በሆነችውና አፍንጮ በርን፣ዶሮ ማነቂያን፣አዲሱ ገበያን፣ሰባራ ባቡርና ገዳም ሰፈርን ተጎራብታ በምትገኘው ዳትሰን ሰፈር የተወለደው ይህ ብላቴና፤ገና በልጅነቱ በእግር ኳስ እና በሙዚቃ ፍቅር እንደመንደዱ ቀለሜዋው ዐቢይ መገኛው ሌላ ቦታ በሆነ ነበር፡፡
እህቱ ህሊና እና ዐቢይ
ህሊና አቢይን አቢቲ በማለት አቆላምጣ መጥራት ደስ ይላታል፡፡ገና በጨቅላነቱ በእግር ኳስ ፍቅር መጦፉን የምትናገረው ህሊና ዐቢይን የገለፀችው ‹‹ያለ ኳስ እግር ኳስ›› በግቢው ውስጥ እየተጫወተ እና ስታዲየም ውስጥ በተሰበሰበ ተመልካች ድባብ ብቻውን ሲጮህ ሲውል የማይደክመው ነበር ትላለች፡፡ለእግር ኳስ ብዙም ቁብ የማልሰጠው እኔ እህቱ እንኳን ኳስ ሳይኖረው ኳስ እየተጫወተ ሲጮህ በማየው አቢቲ ተስቤ ማንችስተር ዩናይትድን መደገፍ የጀመርኩት ከእርሱ ኮርጄ ነው ትላለች፡፡
ዐቢይ በመፃህፍትና በህግ ትምህርት የተከበበ ህይወት ቢኖረውም የልጅነት የእግር ኳስ ፍቅሩ እያማለለው ዘልቆበት ሁለተኛ ዲግሪውን ከያዘ በኋላም ቢሆን የተለያዩ የቢዝነስ ሃሳቦችን ሲያመነጭ ቆይቶ ሸገር ሬድዮ ላይ ቶክ ፉትቦልን ጀምሮ ከመንሱር አብድልቀኒ፣ከፍስሀ ተገኝ እና ከሚሊዮን ዓለሙ ጋር በመሆን ጥልቅ ትንታኔ ስለ እግር ኳስ በመስጠት ብዙ አድማጭና ተከታይ ጋዜጠኞችን ማፍራት ችለዋል፡፡
እያለም ወደ መዝናኛ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነት፤በኋላም ከመስፍን ነጋሽ፣ማስረሻ ማሞ፣ዳኝነት መኮንን፣ግርማ ተስፋው፣ተስፋለም ወልደየስ፣ታምራት ነገራና ሌሎችም ጋር በመቀናጀት አዲስ ነገር ጋዜጣን መስርተው በዐቢይ ተክለማርም ዋና አዘጋጅነትና በመስፍን ነጋሽ ምክትል ዋና አዘጋጅነት እጅ ለእጅ ተያይዘው የዘለቁበትን ጥንካሬ፣ ብርታትና መግባባት እህቱ ህሊና የሚገርም የቡድን ስብስብ ነበራቸው በማለት ትገልፀዋለች፡፡
ታታሪው ዐቢይ
በወላጆቹ ማንነት የጀርመንና የፈረንሳይ ጥምር ዜግነት የነበረውና በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ከ1875 እስከ 1968 የኖረው ደራሲው፣የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ፣ፈላስፋው፣የፊዚክስ ሊቁ እና የሙዚቃ ጠቢቡ አልበርት ሽዌትዘር ‹‹ ስኬት ደስታ የሚገኝበት መንገድ አይደለም ይልቁንም ደስተኛ መሆን ወደ ስኬት ይወስዳል እንጂ፤እናም የሚሠራውን ስራ የሚወድ ሰው ስኬታማ ይሆናል ›› በሚል ያሰፈረው ጥልቅ ምክሩ እንደ ዐቢይ ተክለማርያም እና ጓደኞቹ ላሉ የሚወዱትን በመሥራት ደስታን ለተቀዳጁት ሁሉ ከአንጀት ጠብ የሚል ነው፡፡
በወቅቱ ጠንካራ የፖለቲካ ትንታኔዎችን፣ጥበባዊና ሳይንሳዊ መጣጥፎችን እንዲሁም የጤና እና የስፖርት መረጃዎችን በጥልቀት ታስነብብ የነበረችው አዲስ ነገር ጋዜጣ እና ጋዜጠኞችን በመምራትና በማስተባበር ረገድ የአንበሳውን ድርሻ የተረከበው ዐቢይ ተክለማርያም ህዳር 21 / 2000 ዓ.ም ለህትመት በበቃችው እና ‹ የግሉ ፕሬስ እንቆቅልሽ › በሚል ርዕስ በገፅ ሁለት ላይ ባሰፈረው የትንታኔ ፅሁፉ ‹‹…በ1984 ዓ.ም የግሉ ፕሬስ ሲጀመር ወደ ሥራው የገቡት ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ በመንግስት ሚዲያ ይሠሩ የነበሩና አዲሱ መንግስት በስልጣን ላይ ሲወጣ በተለያዩ ምክንያቶች የመንግስት ሚዲያውን ለቀው የወጡና በወታደራዊ ክፍሎች በጋዜጠኝነት፣በፕሮፓጋንዳ እና ከፅሁፍ ሥራ ጋር በተያያዙ ዘርፎች ይሠሩ የነበሩ ፀሀፊዎች ናቸው ›› በሚል ነጥብ ስለግል ፕሬሶች አመሠራረት አትቶ ሆኖም ወደኋላ ላይ ሥራውና ጋዜጠኞቹ የገቡበትን አጣብቂኝ የተለያዩ ጥናት አቅራቢዎችን በዋቢነት በማጣቀስ አስነብቧል፡፡
መጋቢት 5/ 2001 ዓ.ም በታተመችው አዲስ ነገር ጋዜጣ ገፅ ሁለት የአቢይ ጉዳይ ትንታኔ ላይም እንዲሁ ‹ የአቶ መለስ የሀይል ኡደት › በሚለው የትንታኔ ፅሁፉ ‹‹…የታከታቸው ይመስላሉ፡፡ፊታቸው ላይ ድካም እና ድብታ ይታያል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከመላው አገሪቱ ከተወጣጡ 5000 ያህል ሴቶች ጋር የተደረገውን ወይይት ጨምሮ ባለፉት አራት ሳምንታት ብቻ ከአስራ ሁለት ሰዓታት በላይ በውይይት አሳልፈዋል፡፡አንዳንድ የፖለቲካ ታዛቢዎች ውይይቶቹን ‹ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጅምላ ጠመቃ › ብለዋቸዋል ›› በሚል የጀመረው ትንታኔው አንባቢን ከማብቂው እስኪያዘልቅ ድረስ አስደማሚ እንደነበር ያነበቡት ሁሉ ያስታውሱታል፡፡
ዐቢይ እና ጓደኞቹ
ከዐቢይ ተክለማርያም ጋር በአንደኛ ደረጃ፣በሁለተኛ ደረጃ እና በኋላም አስከ ዩኒቨርሲቲ አብረው በመግባትና ዶርም እስከመጋራት ብሎም አብሮ ገዋን እስከመልበስ በጓደኝነትም ቤት አብሮ ተከራይቶ እስከ መኖር የዘለቁት ጌታቸው አዲስ፣ኤፍሬም ታደሰ እና ኤፍሬም ወዳጆ ገብሩ ከጨቅላነት ጀምሮ ያለውን የዐቢይን ሁለገብ ሰብዕና አውግተው አይጠግቡም፡፡
ልክ ታናሽ እህቱ ህሊና ተክለማርያም እንደገለፀችው ሁሉ ጓደኞቹም ዐቢይ ዝምተኛና ብዙ ማውራት የማይወድ ሆኖም ብዙ ማዳመጥና ማንበብን መገለጫዎቹ አድርጎ ዛሬ ድረስ የዘለቀ ስለመሆኑ ይናገሩለታል፡፡በትምህርት ዓለም ጉዞዎቹና በዩኒቨርሲቲ ቆይታዎቹ አብረውት የተማሩት ብቻ ሳይሆኑ ያስተማሩትና የሞገታቸው መምህራኖቹ ሳይቀሩ ይደመሙበት ነበር ይላሉ፡፡
“ፕሮፐርቲ ሎው” የተሰኘ ኮርስ ስንወስድ ይላል የልብ ጓደኛው ጌታቸው አዲስ ዐቢይ አንድም ቀን ክፍል ገብቶ ተምሮ አያውቅም ነበር፡፡የእርሱ ውሎና ማምሻው በኬኔዲና በህግ ፋኩልቲ ላይብረሪ ነበር፡፡ኋላ ላይ ፈተና ተቀምጠን ውጤት ሲገለፅ በትምህርቱ ኤ ያገኘው ብቸኛ ተማሪ ዐቢይ ሆነና መምህራችን ማነው ዐቢይ ብለው መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ቢሮ ድረስ መጥቶ ያነጋግረኝ ብለው አስጠሩት፡፡ክፍል ገብተህ ያልተማርከው ለምንድነው? ብለው ሲጠይቁትም “ታምሜ ነበር “ብሎ ነገራቸው፡፡በእኔ ትምህርት ክፍለ ጊዜ ብቻ እያመመህ የምትቀርበትን ምክንያት የሚገልፅ የሀኪም ማሰረጃ አምጣ አሉት፡፡ያው ያኔ አንዳንዴ ኒሞኒያ ያመው ስለነበር ከጤና ጣቢያ ማስረጃ አቀረበ፡፡መምህሩም ስለ ዐቢይ ማንነት ከተለያዩ ሰዎች አጣርተው ስለነበረና ባገኘው ውጤት በመደሰታቸው ኤ ፕላስ ሰጥተውት እባክህን ሳስተምር አንዳንዴ ብቅ እያልክ አግዘኝ ብለው ፈገግ አሰኝተው የሸኙትን እኔም አልረሳውም ብሏል፡፡
ዐቢይ ለፈተና የሚዘጋጀው ክፍል ውስጥ ብቻ የተማረውን አጥንቶ እንዳልነበር ጓደኞቹ ይናገራሉ፡፡ ከራሱም አልፎ እኛንም ወጥሮ ጥያቄ እያወጣ ለፈተና ብቁ ያደርገን ነበር፡፡ሆኖም ፈተናው ካለፈ በኋላ ስለፈተናው እና መልሱ ፈፅሞ ማውራት አይወድም ነበር፡፡ይሄ ደግሞ የታታሪ ተማሪዎች ባህሪ ነው ይላሉ ጓደኞቹ፡፡ለፈተና ሲቀመጡም ከሁሉም በፊት ቀድሞ ጨርሶ የሚወጣው እሱው ነበር ያለው ጌታቸው በተለምዶ ሶፎመር እና አድቫንስድ ኢንግሊሽ ያስተማረን ህንዳዊው መምህራችን ለዐቢይ ኤ ፕላስ ውጤት ከሰጠው በኋላ “በዩኒቨርሲቲ የመምህርነት ዘመኔ ለማንም ይህን ማርክ ሰጥቼ አላውቅም” ብሎ ፊት ለፊት ያደነቀው ፈፅሞ የማይረሳ ክስተት ነበር ይላል፡፡
ዐቢይና ፖለቲካ
የአቢይና ጓደኞቹ የዩኒቨርሲቲም ሆነ የመነን ት/ቤት ቆይታ ስድስት ኪሎ አጥር ተጋርተው በተገነቡ ተቋማት ያለፉ በመሆናቸው ረብሻ በተከሰተና ፖሊስ ግቢውን በተቆጣጠረ ቁጥር መነኖችም አብረው እንዲጮሁ የሚጋብዝ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ወዲህም የፖለቲካ ትኩሳቱ የተጋጋለበትና ደርግን ሸኝቶ ኢህአዴግን የተቀበለው የኢትዮጵያ ህዝብ በአዳዲስ ክስተቶች የተጠመደበት ወቅት ስለነበረ የነ ዐቢይ ዘመን ወጣቶች በግርግር ቀንና ሌሊትን ማሳለፍን ለምደውት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
በተለይ ደርግ የግንቦት ስምንት መፈንቅለ መንግስትን አቀናብራችኋል ባላቸው ጉምቱ የአገሪቱ ጄኔራሎች ላይ ርምጃ በወሰደበት ሰሞን መነን ትምህርት ቤት ውስጥ ተሰቅሎ የነበረውን የኮሎኔል መንግስቱ ምስል በድንጋይ አውርደው በመጎተት ተቃውሟቸውን መግለፃቸውን በትዝታ ያወጋሉ፡፡ ወታደሮች መነን ግቢ ውስጥ ዘልቀው አድማውን እስኪገቱት ድረስ ለአገራቸው ብዙ የደከሙ ጄኔራሎች እንደ ተራ ሽፍታ ርምጃ ለምን ይወሰድባቸዋል? በሚል በእጅጉ መቃወማቸውን የዐቢይ ጓደኞች ያወሳሉ፡፡
ሌላው አነጋጋሪው ጉዳይ ዐቢይ ጓደኞቹ ሁሉ ትምህርታቸው ላይ ሙጭጭ ሲሉ እርሱ ግን ለፖለቲካ ጉዳዮች ትኩረት ከመስጠት በተጨማሪ በእግር ኳስና በሙዚቃ ላይ የተለየ ፍላጎትና ዝንባሌ በማሳደር ጥልቅ ፍተሻ ያደርግ የነበረ መሆኑና ይህ ስሜቱም ዛሬም አንዳች ቅዝቃዜ እንዳላሳየ እህቱና ጓደኞቹ በመገረም ይናገራሉ፡፡ኬኔዲ ላይብረሪ ገብቶ በእግር ኳስ አሰለጣጠን ላይ የተፃፉ መፃህፍትን ማንበብ፣የእግር ኳስ አሰልጣኞችን የሜዳ ላይ የአሰላለፍ ትግበራና የግል ህይወታቸውን የተመለከቱ ጉዳዮችን ሁሉ መሸምደድ የየዕለት የዐቢይ ተግባራት ነበሩ፡፡
አንድ ጊዜ እንዲያውም የህግ ፋኩልቲ ተማሪዎች የቢዝነስና ኤኮኖሚክስ ተማሪዎችን በእግር ኳስ ሲገጥሙ ያነበበውን በብላክ ቦርድ ላይ በመተንተንና አሰላለፋቸውን በመዘርጋት አጋሮቹ አሸንፈው እንዲወጡ ያደረገበት አካሄድ ሁሉን ያስገረመ እንደነበር ኤፍሬም ያስታውሳል፡፡ሆኖም አቢይ የእግር ኳስ ሳይንስንና አሰለጣጠንን በሚገባ ይተንትን እንጂ ሜዳ ላይ ከኳስ ጋር ሲገናኝ እምብዛም እንደነበርም አይረሱትም፡፡
ንባብ የወለደው ድፍረትና ተሳትፎ
በ1987 ዓ.ም አቢይና ጓደኞቹ ገና ከፍሬሽ ተማሪነት ብዙም ሳይርቁ ከነሱ በፊት ፋኩልቲው ውስጥ ቆይታ የነበራቸው ተማሪዎች በህገ መንግስት ረቂቅ ውይይት ላይ ተሳትፈው ሲመለሱ በሃሳብ ይሞግቷቸው እንደነበርና የዚህ ዋናው ተዋናይ ዐቢይ እንደነበረ በመገረም ያወሳሉ፡፡በ1988 ዓ.ም ስቶክ ኤክስቼንጅ (የአክሲዮን ገበያ) ለአገሪቱ አስፈላጊ መሆኑን አቢይ እና እኔ በማመን ከትምህርታችን ጋር አዛምደንና ድራፍት አርቅቀን አዘጋጅተን ማቅረባችን ትዝ ይለኛል ያለው ጌታቸው ቆይቶም በአገር ደረጃ ያን መነሻ ያደረገ በህግ መልክ ረቆ መፅደቁን ያነሳል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር አንድሪያስ አይነት ታላላቅ ምሁራን ይሰጧቸው የነበሩትን ኮርሶች ቀድሞ በመረዳትና በማብራራት የሚታወቀውን ዐቢይን እንደ ቡድን መሪ ከፊት አድርገን ፓርላማ ድረስ እየገባን በህግ ጉዳዮች ላይ መሟገታችንን አልረሳውም ይላል ጌታቸው፡፡
ዐቢይ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ከህግ መፋለሶች ጋር ተያይዞ ያስተዋላቸውንና አግባብነት የላቸውም ብሎ ያመነባቸውን ጉዳዮች እየነቀሰ አርቲክሎችን በማዘጋጀት በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ እንዲነበቡና ትኩረት እንዲያገኙ ይሞክር ነበር፡፡አንድ ጊዜ እንዲያውም በሪፖርተር ላይ በብዕር ስሙ ባወጣው ፅሁፍ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎና ተጠይቆ ውሎም ሳያድር ተለቆ ነበር፡፡ዐቢይ በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቀ በኋላ የቴሌ ነገረ ፈጅ ሆኖ ተቀጠሮ ለጥቂት ጊዜያት ሠርቷል፡፡ከዚያም ባመለከተው መሰረት በንግድ ሥራ ኮሌጅ በትርፍ ጊዜ ሰዓት አስተማሪነት፤ኤስ ኦ ኤስ በተባለ ድርጅት ደግሞ የሙሉ ጊዜ ሠራተኛ ሆኖም አገልግሏል፡፡
የዐቢይን የንባብ አፍቃሪነትና የመፅሀፍ ወዳጅነት ለመረዳት በብሄራዊ ቴአትር፣በሰሜን ሆቴል፣በሀገር ፍቅር፣በሳሪስ እና በተለይ ጋንዲ ሆስፒታል ፊት ለፊት የነበሩ መፅሀፍት ሻጮችን ተግባር መጥቀስ ብቻ ይበቃል፡፡እነዚህ መፅሀፍ ነጋዴዎች የተለየ መጽሀፍ እጃቸው ላይ ሲገባ በቅድሚያ ለዐቢይ ደውለው አሳውቀው የማይፈልገው መሆኑን ሲረዱ ብቻ ነበር ለሌላ ፈላጊ የሚሸጡት፡፡ከመፅሀፍት ጋር በተያያዘ እህቱ ህሊና ያለችውንም እዚህ መጥቀስ ግድ ይላል፡፡በአንድ ወቅት ወንድሜ አቢቲ አሜሪካ ሄዶ ሲመለስ ምን አምጥቶልኝ ይሆን ?ብዬ ጓጉቼ ስቀበለውና የያዛቸው ሻንጣዎች ሁሉ ሲከፈቱ በመፅሀፍት የተሞሉ ሆነው ሳገኛቸው ተናድጄ ለረጅም ጊዜ አኩርፌው ነበር ትላለች፡፡
ዐቢይና አዲስ ነገር ጋዜጣ
አዲስ ነገር ጋዜጣ ከጥቅምት 16/ 2000 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ 19/ 2002 ዓ.ም ድረስ በህትመት ገበያው ላይ የቆየችና በ24 ገፆቿ ሰድራ በምታቀርባቸው ትንታኔዎቿ በአንባቢዎቿ ዘንድ የምትታወቅና የምትናፈቅ ነበረች፡፡ዐቢይና ጓደኞቹ በብሔራዊ ቴአትር የግራር ዛፍ ስር ተሰባስበው የአዲስ ነገር ጋዜጣን ምስረታ ካበሰሩባት ቀን ጀምሮ ያለመታከት ሰርተው ፣110 ዕትሞችን ካስነበቡ በኋላ ጋዜጣዋ ከህትመት ውጪ ሆናለች፡፡
ብዘዎቻችን በራሳችን ጉዳይ ስንጠመድ ዐቢይና መሰሎቹ ግን አገራዊ ለሆኑ ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥተውና ተንታኝ ጋዜጣ ዕውን አድርገው በገለልተኝነት ለማገልገል ቢሰማሩም ሁኔታው ስላልተመቻቸውና ወከባው ስለበዛባቸው ጋዜጣቸውንም ዘግተውና ሰራተኞቻቸውን በትነው መሰደዳቸውን ስናስብ ሀዘኑ የመርግ ያህል ይከብደናል ይላሉ የአቢይ አብሮ አደግ ጓደኞች፡፡
በጋዜጣዋ ላይ በግራፊክስ ዲዛይነርነት ሙያ ያገለገለው ባሳዝነው ወንድሜነህ በበኩሉ ዐቢይ ዋና አዘጋጅ ቢሆንም እንደ አለቃ የሚፈራ ሳይሆን እንደ ጓደኛ ቀርቦ ሰርቶ የሚያሰራና ሁሌ ለጋዜጣዋ ቅርፅና ይዘት ማማር የሚጨነቅ አለፍ ሲልም እንደ ዘ ሰን የመሳሰሉ የእንግሊዝ ጋዜጦችን በሞዴልነት እያመጣ እንዲህ ብናደርገውስ ብሎ ለጋዜጣዋ ሳቢነት የአቅሙን ሁሉ ሳይሰስት የሚሰጥ ነው ይለዋል፡፡
ጋዜጣዋ ቅዳሜ ገበያ ላይ ከዋለች በኋላ በየሳምንቱ እሁድ እየተገናኘን ጋዜጣዋን መገምገምና ስለቀጣይ ዕቅድ በነፃነት መተቻቸትና መተራረም፤ከዚያም በጋራ ምሳ በልቶ ተሳስቆ መለያየትና ነገን በተሻለ ማለም የሁላችንም ተግባር ነበር ይላል ባሳዝነው፡፡
የአዲስ ነገር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ዐቢይ ተክለማርያም ጋዜጣዋ ዕውን ከሆነች ጀምሮ በአዘጋጅነት የሚሰለፉትን በመወሰንና በየገፁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ብዕረኞችን በመምረጥና በማረቅ ጠንካሮችን ከጎኑ ማሰለፍ የቻለ ሰው ለመሆኑ መስካሪዎቹ የትየለሌ ናቸው፡፡በህግ ሰርዓተ ትምህርት ውስጥ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ዶክትሬት ደረጃ የዘለቀ በመሆኑ ህግና ሰርዓትን ተከትሎ ለመስራት ቀድሞውንም የተሟላ ሰብዕና፣ዝግጅትና ልምድ ያለው ነበር፡፡በአጭር ጊዜ ተወዳዳሪ እና ተነባቢ ጋዜጣ ወደ ገበያው ማስገባት የቻሉበትም ምስጢሩ ይሄው ነው፡፡የቅርብ ጓደኛው ጌታቸው ዐቢይ አዲስ ነገር ጋዜጣን የዚህ አገር ዋሽንግተን ፖስት እንድትሆን አደርጋታለሁ የሚል ጠንካራ ዕምነት ነበረው ይለናል፡፡
ዐቢቲ (ዐቢይ) የት ነህ ?
እናትና አባታችን አብረውን እያሉም በአያታችን ወይዘሮ ዘውዴ መተኪያ እጅ ቅብርር ብለን ስላደግን ከጠንካራዋ አያታችን መላው ቤተሰቡ ብርታትና ጥንካሬን ወርሷል ትላለች ህሊና ተክለማርያም፡፡ዐቢይም ባህር ማዶ ሆኖ የአያቱን ማረፍ ሲሰማ ብርቱ ሀዘን ላይ መውደቁን ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከነፎቶአቸው ባጋራው አጭር ፅሁፉ አስነብቧል፡፡
ከኢህአዴግ ስልጣን መልቀቅ በኋላ ከስደት ወደ አገሩ ተመልሶና ጓደኞቹን አሰባስቦ የቀድሞ ስራውን እንዲቀጥል፤ፈቃደኛ ከሆነም መንግስታዊ ተቋማትን በሀላፊነት ከሙያው አኳያ እንዲመራ ከመንግስት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብለትም ሌሎችን እያሳመነ ወደ አገር ቤት ልኮ እሱ ግን በሀገረ እንግሊዝ በለንደን ከተማ በመምህርነቱ ገፍቷል፡፡ዐቢቲ ናፍቆኛል፡፡ዐቢቲ የት ነህ ? ትላለች እህቱ ህሊና ተክለማርያም፡፡
የአዲስ ነገር ጋዜጣ የአቢይ ገፅ ተንታኙ ዐቢይ ተክለማርያም ገፀ ብዙ ህይወትን ተንትኖና አውርቶ ለማብቃት የሚቻል አይሆንም፡፡ከእናቱና ከአባቱ እንዲሁም ከአያቱ በተጨማሪ በታላቅ ወንድሙ ኢንጅነር ሳሙኤል ተክለማርያም እና በእህቱ ዶ/ር ሂሩት ተክለማርያም የየእለት ክትትልና በንባብ ባበለፀገው አእምሮው ለወደፊቱም ገና ብዙ እንደሚያሳየን ተስፋ በማድረግ እና እንኳን ለ48ኛው ዓመት የልደት ቀንህ አደረሰህ በማለት መልካም ምኞታችንን እንገልፅለታለን፡፡ረጅም ዕድሜና ጤና ለዐቢይ ተክለማርያም፡፡ቺርስ፡፡
የኔ ዐቢይ … ዐብዬ በዳኝነት መኰንን (አሜሪካ)
ወዳጄን የምጠራው … ዐብዬ ብዬ ነው። ዐብዬ… ብዙ ነገሬ ነው፤ ወንድሜም፣
ጓደኛዬም ፣ ባልንጀራዬም፣ ባልደረባዬም፣ መምህሬም፣ የጉዞ መሪዬም… ወዘተ። ዐብዬ (ላልቶ ይነበብ) ባለበት በዚያ በእርግጠኝነት የሚኖሩ ሦስት ነገሮች አሉ። የደራ ጨዋታ ፣ የእግር ጉዞ ፣ ምሉዕ ነገ … ሦስቱም በንባብ ተረክ ተዋስዖ ፣ በኪን ፣ እና በፍልስፍና የተሸመኑ የዐብዬ ወዳጅ የመኾን ገፀ በረከቶች ናቸው።
ዐብዬ መፈተሹን ሳያሳብቅ፣ ምቾት ሳይነሳ በርብሮ ጠያቂ ነው። ከዐዋቂውም ኾነ ካላዋቂው ፣ ከትልቁም ኾነ ከትንሹ ጋራ የወል ጨዋታ መፈልፈል እና ማሳደግ ሥጦታው ነው። አላዋቂውም ትንሹም ከዐብዬ ጋራ ኹኖ ወደ ምርጥ ማንነቱ ከፍ ይላል። ዐብዬ “ወክ እየበላ” ዝም ካለ በሐሳብ ከተወሰወሰበት በጥያቄ የማናጠብ እጣ ፈንታ በአብሮ ተጓዡ ላይ ይወድቃል። ለእኔም ይኽ እጣ ፈንታ ከነሙሉ ክብሩና ማእረጉ ደጋግሞ ደርሶኛል። በዚህ አጋጣሚ የዐብዬ ፊተኛ ባልንጀራ በመኾኔ ያለኝ ኩራት ከቃላት በላይ መኾኑ ይታወቅልኝ።
ዐብዬ ወደ ኢትዮዽያ ሁለተኛ ዲግሪዉን “ሚዲያ ሎዉ” አጥንቶ ከእንግሊዝ እንደተመለሰ በአገራችን የሚዲያ መልከዐ ምድር ላይ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ከባልንጀራው ሚልዮን ዓለሙ ጋራ በሸርክና የሕግና የሚዲያ ቢሮ አቋቁመዉ በሺህ ሰለሞን ሕንፃ ላይ ከፈቱ። የዐብይ የሕግና የሚዲያ ሕብር ማንነት ሁለተኛ ምዕራፍ “ቶክ ፉትቦልን” በማዘጋጀት ተጀመረ። በምዕራፍ ዐንድ የቀነበብሁት የዐብዬ የጋዜጠኝነት ጅማሬ ወደ እንግሊዝ አገር ከመሄዱ በፊት በኮሜርስ የሕግ መምህር ሳለ የሪፖርተር እንግሊዝኛ ጋዜጣ ላይ የሠራበት ዘመን ነው።
የኔ የምለው ዐብዬ … ዐቢይነቱ ለቤተሰዎቹም ፣ ላደገበት “ዳትሰን” ሰፈርም ፣ ለሚያውቁትም ኹሉ ነው። ሰፈሩን ብቻ ሳይኾን ከተማይቱን አዲስ አበባን የምር ማፍቀራቸውን ከምመሰክርላቸው ወዳጆቼ ፊተኛው ዐብዬ ነው። በጽሑፎቹ መጠነዙሪያ ብትሾሩ ከዐብዬ ወዲያ አዲስ አበቤ ላ’ሳር ነው።
ዐብዬ ለለንደን እና ለኒው ዮርክ ስስ ልብ አለው፤ ለአዲስ አበባም ያይ፣ ይመኝ ፣ እና ይጽፍ የነበረው ለንደንን ባየበትና ባስተዋለበት የተዋቡ ዐይኖቹ ነው። ያኹኒቷን ነጭ፣ ብልጭልጭ፣ ወና ፒያሣ እንኳን ዐላየ ልል ብዬ …ተውኹት። ታድዬ … በወዳጄ ዐብዬ የጉዞ መሪነት ከልቡ ሥር የሚወዳቸውን ኹለቱን ከተሞች (ለንደንን እና ኒው ዮርክን) በዐብዬ ዐይን እና አንደበት ለተደጋጋሚ ቀናት በእግር ጉዞ ጎብኝቻለሁ። ይኽን መሣይ ልዩ ዕድል ያገኘ ማን እንደኔ ? በነገራችን ላይ … ላደግኹባት፣ ለኖርኹባት አዲስ አበባ ዐብዬ ያይላት፣ ይመኝላት፣ እና ይጽፍላት የነበረችው ከተማችን እንዳይኾን ፣ እንዳይኾን ኹና ፣ ድኾቿን ወደ ዳር ገፍታ መብለጭለጯ ከልብ ያሳዝነኛል።
ከዐብዬ ጋራ የምንተዋወቀው ስድስት ኪሎ ግቢ ነው። ከለንደን እንደተመለሰ ዳግም የተገናኘነው ቶሞካ ኮፊ ነበር። ቡና ጠጣን ፣ ወግ አደራን። ቀዳሚዋ ርእሳችን ጂጂ (እጅግ ዐየሁ ሽባባው) ነበረች። የጂጂ ጉድ ፈላ አልበም እንዴት ጉድ እንዳደረገን በላይ በላይ በቶሞካ ቡና የጫማ ከፍታ ተንፈላሰስንበት። እኔና ወዳጄ መሥፍን አሰፋ በጂጂ አልበም ላይ የተመሠረተ “የጉራማይሌ ምሽት” ልንመደርክ ስላሰብነው የጥበብ ምሽት ለዐብዬ አነሳሁበት። ዐብዬም ለጥበብ ምሽቱ ያዘጋጀነውን የስፖንሰርሺፕ ፕሮፖዛላችንን ቢሮ ይዤ እንድመጣ ገፋፋኝ። በየቀኑ እየተገናኘን ቡና እየጠጣን ፣ “ወክ እየበላን”፣ በምንወዳቸው በግል ፣ በከተማችን ፣ እና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ መወያየት ቀጠልን።
እግር ኳስ ወዳጅ አይደለሁም። ነገር ግን የዐብዬን የ”ቶክ ፉትቦል” ዝግጅት ሥራዬ ብዬ አደምጣለሁ። የኳስ ጨዋታውን የሐሳብ ገበያ ፣ የፍልስፍና ዐውድማ በማድረግን የተካነ … ማን እንደ ዐብዬ! ። የፍሥሐ ተገኝን በኳስ ዕውቀት የተመላ አስተናባሪነት፣ በመንሱር አብድልቀኒ የስፖርት ጋዜጠኝነት አምሳልነት፣ እና የዐብዬን ሰፊና ጥልቅ አሳቢነት የምናይበት ያ ዝግጅት ፍሰቱን፣ ቅመራውን፣ እና ይዘቱን እንፈትሽ ፤ በሬዲዮ ሾዉ ላይ ስለተነሱ ሰፊ ጉዳዮች ሞቅ ያለ ውይይት እናደርግ ነበር።
በቶክ ፉትቦል ላይ የምናደርገው ውይይት እያለ ሠይፉ ፋንታሁን ፣ ሚልዮን ዓለሙ ፣ እና ዐብይ ተክለ ማርያም መዝናኛ ጋዜጣን ማሳተም ጀመሩ። ከወዳጄ ማስረሻ ማሞ ጋራ ኾነን የመዝናኛ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ዐብይ ባለበት በጋዜጣው ላይ በወጡ ጽሑፎች ላይ ያየናቸውን ብርቱ እና ደካማ ጎኖችን እናነሳ እና እንጥል ነበር። ጋዜጣውን ማኄስ ሥራችን ብለን መያዛችንን ያየው ዐብዬ ከኂስ ባሻገር ግጥሞቻችንን እና ጽሑፎቻችንን እንድናዋጣ ጋበዘን። ቀስ በቀስም ከኂስ አዉራጅነት ወደ ጽሑፍና መጣጥፍ ፣ ወደ ግጥምና ዝርው ግጥም አዋጭነት ከዚያም ወደ ጋዜጣው ባልደረባነት ተዘዋወርን። የዐብዬ የጋዜጠኝነት እና የባለጋዜጣነት ምዕራፍ ሦስት በመዝናኛ ጋዜጣ ምሥረታ እና እድገት ውስጥ በገሀድ ይታያል።
ከሦስቱ ሸሪኮች (ሠይፉ፣ ዐቢይ ፣ እና ሚልዮን) በተጨማሪ እኔ ፣ ማስረሻ ማሞ ፣ ግርማ ተስፋው፣ በዕውቀቱ ሥዩም፣ መሥፍን ነጋሽ፣
ባንከኛው አብርሃም የመዝናኛ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ባልደረቦች ኾንን። መዝናኛ ጋዜጣም ዐብዬ ወደ ዐየላት ግብ መዳህ ፣ ወፌ ቆመች መባል ጀመረች። አዲሱ የጸሐፍት ቡድን ከተቀላቀለ ከዐምስት ዕትም በኋላ መዝናኛ ጋዜጣ በመልክም፣ በይዘት፣ እና በዲዛይን መዋቅራዊ ለውጥ ውስጥ አልፋ ሰፋፊ ኪናዊና ማኀበራዊ ፊቸር መጣጥፎችን፣ ቋሚ ዐምዶች እና ዐምደኞችን እያሳተፈች ምሉዕ ጋዜጣ ለመኾን ትንደረደር ጀመር። እስከዚህ ምዕራፍ መዝናኛ ጋዜጣ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አታነሳም ነበር።
በሚዲያው ላይ የዐብዬ መዝናኛ ጋዜጣ ከተለምዶዉ ለየት ያሉ ሉላዊ አካኼዶችን ፣ የአጻጻፍ ዘዬዎችን፣ እና የኤዲቶሪያል ፖሊሲዎችን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ለማስተዋወቅ ጥረቷን ጀመረች። በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ፖለቲካም በ1997 የምርጫ ትኩሳት ጠቋሚ ምልክቶች ውስጥ እያለፈ ነበር። የአቶ መለስ ዜናዊ ኢህአዴግ ነፃና ገለልተኛ ፣ እንከን የለሽ ምርጫ አካሂዳለሁ አለ። የቅንጅት የምረጡኝ ማስታወቂያዎች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይተላለፉ ጀመር። የቅንጅት የምርጫ ማኒፌስቶ ይፋ መደረግ ዐብዬን እና የዐቢይን መዝናኛ ጋዜጣ አቅጣጫ ሙሉ ለሙሉ ቀየረው።
ይኽን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ታሪክ ወሳኝ ወቅት (Critical Juncture) ዳር ላይ ኹኖ መመልከት ከታሪክ መጉደል ፣ የዜግነት ኃላፊነትን እና ሞያዊ ግዴታን አለመወጣት መኾኑን የመዝናኛ ጋዜጣ ባልደረቦች ተመካክረው የጋራ ስምምነት ላይ ደረሱ። የዐቢይ ተክለ ማርያም መዝናኛ ጋዜጣም
አለወትሮዋ የምርጫ ፖለቲካውን መዘገብ ኀትመተ ምክንያቴ እና ነገረ ጉዳዬ ነው ብላ በይፋ አወጀች። መዝናኛ ጋዜጣ ሎጎም ላይ “ማንበብ መዝናናት ነው!” የሚል መፈክር ተጨመረ። የመጀመሪያው የፖለቲካ ፊቸር መጣጥፍም “Vote or Die” በሚል ርእስ ታተመ። መዝናኛ ጋዜጣ የ1997 ምርጫ ዋዜማን፣ የዕለተ ግንቦት ሰባት የምርጫ ሂደት፣ የግንቦት ስምንቱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ እስከ ጥቅምት ሦስተኛ ሳምንት 1998 የዘለቁ ድኀረ ምርጫ ውዝግቦች በመዘገብ የነፃው ፕሬስ ፍፁም እስከ ተዘጉበት ወሳኝ ወቅቶች በኢትዮጵያ የምርጫ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ኹነኛ ፋይዳ ያለው ተሳትፎ አድርጋለች። በዐብዬ መሪነት የመዝናኛ ጋዜጣ አዘጋጆችም የቅንጅት አመራሮች እና ጋዜጠኞች ሲታሰሩ “በመሪዎቻችን ይፈቱ” ዘመቻዎች ፣ በተለያዩ የሕቡዕ ሕትመት ውጤቶች ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ሕትመት ውጤቶች በአቶ መለስ መንግሥት ትዕዛዝ ከገበያ ሲሳደዱ፣ ሲታገዱ፣ እና ሲታሰሩ የመዝናኛ ጋዜጣ እጣ ፈንታም መዘጋት ኾነ። የመዝናኛ ጋዜጣ ባልደረቦችን ቀን እስኪወጣ ይዞ የሚያቆይ ዐንድ መላም ዐብዬ አመጣ። ይኸውም መላ … “ www.ethiomirror.com የሚባል የረጅም እና የአጭር ጊዜ ግብ ያለው ድረ-ገፅ ዲዛይን እናስደርግ” የሚል ነበር። www.ethiomirror.com ድረ-ገፅ የረጅም ጊዜ ርዕዩ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ e-commerce website መኾንም ነበር። ለኢትዮዽያ ከጊዜው በጥቂት የቀደመ ሐሳብ ቢኾንም የዐብዬን ቢዝነስ ፕሮፖዛል አምነውበት ቤተሰዎቻችን እና ጓደኞቻችን ገንዘብ አዋጡና ሥራው ተጀመረ። ድረገፃችን
ኢትዮ ሚረር የአጭር ጊዜ ግቡን መታ። ድረገፁ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ባላየ የሚያልፍ ዲጂታል መጽሔት (ኦንላይን ሜጋዚን) እያዘጋጀ ማተም ጀመረ። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላም የመዝናኛ ጋዜጣ ባልደረቦች www.ethiomirror.com ድረ ገፅን በእንግሊዝኛ ቋንቋ አዘጋጁ። የድረገፁ የረጅም ጊዜ ግብ ግን ጉም መዝገን ኾነ። የኢ-ኮሜርስ ገበያው ድረ ገፅ ገንቢዎች ዛሬ ነገ እያሉ ቀናት ወራትን፣ ወራትም መንፈቅን ወለዱ። የኢ-ኮሜርስ ገበያውንም ማቆም ተሳናቸው። ዲጂታል መጽሔቱን በገንዘብ ምሰሶ ኹኖ ያቆመዋል ያልነው የኢ-ኮሜርስ ገበያ ላም አለኝ በሰማይ ኾነ።
በዚህ ጭንቅጥብ ውስጥ እያለን የኢትዮዽያ ሚሌንየም መጣ መጣ እየተባለ ከየአቅጣጫው ነጋሪት ይጎሰም፣ ከበሮ ይደለቅ ጀመር። የታሰሩት የቅንጅት አመራሮች እና ጋዜጠኞች በይቅርታ ሊፈቱ ነው የሚባል ወሬ ከተማችንን ሞላት። ወሬውም እውነት ኾኖ እሥረኞቹ ተፈቱ። ከዚህ በኃላ ነው አዲስ ነገርን ለመመስረት ደፋ ቀና ማለት የተጀመረው፡፡