ካሳሁን ገርማሞ – የቴዲ አፍሮ አባት

ካሳሁን ገርማሞ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡

በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል የሚድያ ሰውና የመድረክ አስተዋዋቂ ካሳሁን ገርማሞ ይጠቀሳል፡፡ካሳሁን ገርማሞ በጥበቡ አለም ለ33 አመት የቆየ ሲሆን በፖሊስ ኦርኬስትራ ውስጥ በመድረክ አስተዋዋቂነት ለ21 አመት አገልግሏል፡፡ በፖሊስ ሬድዮም ውስጥ ለ11 አመት በጋዜጠኝነት ያገለገለ ሲሆን በመስከረም 17 1993 በ53 አመቱ ከዚህ አለም በሞት የተለየ ነው፡፡ ካሳሁን ገርማሞ የእውቁ ሀገር ወዳድ ድምጻዊ የቴዴ አፍሮ ወላጅ አባት ሲሆን የህይወት ታሪኩንም ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ሰንዶታል፡፡ ይህን የህይወት ታሪክ በዚህ መልኩ እንድንሰራ ትብብር ላደረጉልን ለወዳጆቻችን አዳነች ወልደገብርኤል / አዲ/፤ ጌታቸው ማንጉዳይ ፤ ምክትል ኮማንደር ብርቄ ወልደገብርኤል እንዲሁም ለጋዜጠኛ ሰለሞን አምባቸው የከበረ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡

በተጨማሪም ሀገር ወዳዱ እና ታሪክ አፍቃሪው ቴዲ አፍሮ ይህን ታሪክ እንድንሰራ ፈቃዱን ስለሰጠን እና የስነዳ ፕሮጀክታችንን ስላደነቀ እያመሰገንን እስከዛሬ ብዙም ያልታዩ የካሳሁን ገርማሞን ምስል እያያችሁ ጽሁፉን ታነቡ ዘንድ በታላቅ አክብሮት እንጋብዛለን፡፡

ውልደትና ወጣትነት

ጋዜጠኛ ካሳሁን ገርማሞ ከአባቱ ከአቶ ገርማሞ ውፍዮ እና ከእናቱ ከወይዘሮ ዘነበች አንጨ ጥር 1 ቀን 1939 አ.ም ተወለደ፡፡ የኪነጥበብ ባለሙያ ካሳሁን ገርማሞ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በሲዳሞ ክፍለሀገር ተፈሪ ኬላ በተስፋ ኮከብ ት/ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ ከተማ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቀቀ፡፡ ካሳሁን ወደ ጋዜጠኝነት አለም ከመምጣቱ በፊት ወደ ስራው አለም የተቀላቀለው በመድረክ አስተዋዋቂነት ነው፡፡ በዚህ ስራው በፖሊስ ሙዚቃ ክፍል በቴአትርና ሙዚቃ አስተዋዋቂነት ከ1960-1966 በጊዜያዊነት ከሰራ በኋላ የጥበብ ልዩ ችሎታ እንዳለው በመረጋገጡ ከ1967 ጀምሮ በቋሚነት ተቀጥሮ ማገልገል ጀመረ፡፡ በጊዜው ካሳሁን የ28 አመት ወጣት ነበር፡፡

የጥበብ ዝንባሌ

በፖሊስ ሙዚቃ ክፍል ውስጥ የዘፈን ግጥሞችን እና ዜማዎችን በመድረስ ለሰራዊቱ ሙዚቃ ክፍል ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብረውት የሰሩ ይናገራሉ፡፡ ከ1967-1980 ለ13 አመታት በሙዚቃ ክፍሉ ውስጥ ከሰራ በኋላ በ1981 አ.ም ወደ ጋዜጠኝነቱ በመዞር በፖሊስ ሬድዮ ውስጥ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ካሳሁን እውቀቱንም ለማሻሻል በነበረው ልዩ ፍላጎት ዩኒቲ ኮሌጅ በመግባት በህግ ዲፕሎማውን ለማግኘት ችሏል፡፡ የኪነ- ጥበብ ሰው ካሳሁን ገርማሞ በልዩ ልዩ ጊዜያት ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ከመንግስታዊና ከህዝባዊ ድርጅቶች የእውቅና እና የምስጋና የምስክር ወረቀት አግኝቷል፡፡

አርቲስት ተስፋዬ አበበ / ፋዘር / ካሳሁን ገርማሞ ፖሊስ ሙዚቃ ክፍል ሊቀጠር ሲመጣ ጀምሮ ያውቁታል፡፡ ያን ጊዜ ካሳሁን 21 አመቱን አክብሮ ነበር፡፡ ታዲያ ፈታኝ ከነበሩት አንዱ አቶ ተስፋዬ አበበ ነበሩ፡፡ ጋሽ ተስፋዬ 55 አመት ወደ ኋላ ተመልሰው ሲያስታውሱ ካሳሁን በጊዜው የኮሜዲ ልዩ ክህሎት ነበረው፡፡

ጋሽ ተስፋዬ ስለ ካሳሁን የሚድያ ሰብእና ሲናገሩ በሬድዮ የነበረው ልዩ አቀራረብ በአድማጮች ዘንድ ፈጽሞ የማይረሳ ነበር ይላሉ፡፡ በተለይ ደግሞ በፖሊስና ህብረተሰብ መሰናዶ ላይ ካሳሁን የነበረው ሚና ትልቅ እንደነበር ጋሽ ተስፋዬ ይመሰክራሉ፡፡ የካሳሁን ስነ-ምግባርን በተመለከተ ከሁሉ ጋር ተግባቢ መሆኑን ጋሽ ተስፋዬ ያስረዳሉ፡፡ እንዲያውም ካሳሁን ለሰዎች ምን ላድርግ ይላል እንጂ ከሰዎች የሚጠብቅ አለመሆኑንም ጨምረው ፋዘር ነግረውናል፡፡

‹‹ ካሳሁን ባለችው ደሞዝ ሰው ለመርዳት ይጥር ነበር;;››

አርቲስት ተስፋዬ

ካሳሁን ትዳር ከመያዙ በፊት የቤት እቃዎችን ያሟላ ነበር፡፡ በወቅቱ ቲቪ እንደ ብርቅ በሚታይበት ጊዜ ካሳሁን ጥቁርና ነጭ የሚያሳይ ቲቪ እንደነበረው ጋሽ ተስፋዬ አጫውተውናል፡፡ ‹‹ታዲያ ያኔ በ1968 ግድም ቤቱን በወጉ ካሟላ በኋላ 10 አለቃ የነበረችውን ተወዛዋዥ ጥላዬ አራጌን አጨ፡፡ እኛም በሰርግ አጋባነው፡፡ እንዲያውም የነገር አባት እኔ ነበርኩ፡፡ በኋላ ላይ ኢትዮጵያን ያስጠራ ታላቁን ቴዲ አፍሮን ወለደችለት፡፡ ›› በማለት ጋሽ ተስፋዬ 47 አመት ወደ ኋላ ወስደውናል፡፡ ካሳሁን ገርማሞ በጦር ግንባርም በማቅናት ጦር ሰራዊቱን በመቀስቀስ ሙያዊ አደራውን በሚገባ የተወጣ ሰው ነበር፡፡ ካሳሁን ታላቅ የሀገር ፍቅር ስሜት ያለው በመሆኑ በጊዜው የሚያቀርባቸው ስራዎች ጊዜውን የተከተሉና ደስ ብሎት የሚሰራቸው ነበሩ፡፡

‹‹….. ካሳሁን እና ሂሩት በቀለ ብቻ ነበሩ ከሁሉም እርስዎ እያሉ የሚጠሩኝ፡፡ እውነት ለመናገር ካሳሁን ሰው አክባሪ ነው፡፡ ከእኔ ጋር ደግሞ የበለጠ የቅርብ ወዳጅነት አለን፡፡ ስለ ሀገር ፍቅር ጉዳይ ስናወራ በጣም እንግባባ ነበር፡፡ ግጥሞና ዜማዎች ስጽፍ ሀሳብ በመስጠት ሞራል በመለገስ ያበረታታኝ ነበር፡፡›› በማለት ፋዘር ትዝታቸውን አውግተዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ አንድ ቀን ካሳሁንን ያገኙታል፡፡ በጊዜው ካሳሁን አዲስ ቮልስ ዋገን ገዝቶ ነበርና ይህን መኪና ልጄ ቴዲ አፍሮ ነው የገዛልኝ ብሎ እንደነገራቸው ያስታውሳሉ፡፡ ፋዘር እንደሚናገሩት ከዚያ በኋላ ካሳሁንን እንዳላገኙትና ማረፉን እንደሰሙ አጫወቱን፡፡

ፋዘር / ተስፋዬ አበበ/ ካሳሁን የልጁን የቴዲ አፍሮን ስኬት ቢያይ ኖሮ ብለው ይመኙ ነበር፡፡ ካሳሁን ለልጁ ለቴዲ አፍሮ ትልቅ ፍቅር ስለነበረው ተንከባክቦ ነበር ያሳደገው፡፡ ሲያስተምረውም ጥሩ ት/ቤት ውድ ከፍሎ ነበር ያስተማረው፡፡ ጋሽ ተስፋዬ ይህን ሲያጤኑ የካሳሁን መልካም አባትነት ይታሰባቸዋል፡፡ ብዙዎቹ የካሳሁን ባልደረቦች ትህትናውን ይወዱለታል፡፡ ቁምነገር አዋቂነቱን ያደንቁለታል፡፡ በጊዜው የነበሩ ተመልካቾችም ካሳሁንን በጣም ይወዱታል፡፡ ገና መድረክ ላይ ሲወጣ ሁሉም በደስታ ይሞሉ ነበር፡፡ ለዛ ያላቸው ቀልዶቹም የሚወደዱ ነበሩ፡፡

ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ስለአባቱ

አባቴና እናቴ የተገናኙበትን ጊዜ በትክክል ባላውቀውም መስሪያ ቤታቸው አንድ ላይ መሆኑን አውቅ ነበር፡፡ እርሱ የመድረክ መሪ እርሷ ደግሞ የመድረክ ተወዛዋዥ ነበረች፡፡ የተጋቡት በ1967 ዓ.ም ነው እናቴ ጥላዬ አራጌ የ17 ዓመት ወጣት ነበረች፡፡ እርሱ ደግሞ ወደ 20ዎቹ መጨረሻ ነበር ሲሉ አውቃለሁ፡፡ በተጋቡ በአንድ አመታቸው እኔ ተወለድኩኝ፡፡ ነገር ግን ከዚያ በኋላ ብዙ አመት አብረው አልኖሩም፡፡ የተለያዩበትን ቀን በትክክል ባላውቀውም ለ6ኛ የልደት ቀኔ እለት ግን እናቴ አልነበረችም፡፡በ1974 መሆኑ ነው፡፡ አባቴ ከዚያ በኋላ ለራሱ አልኖረም፡፡ እናትም አባትም ሆኖ አሳደገኝ፡፡ የኖረው ለእኔ ነበር፡፡ ጥሩ ትምህርት ቤት አስተምሮኛል፡፡ በዘመናዊ አስተዳደግና በጥሩ ስነምግባር አሳድጐኛል።

አባቴ ሙዚቀኛ እንድሆን ፈጽሞ አይፈልግም፡፡ አስቦትም አያውቅም፡፡ ምክንያቱም በእነርሱ ዘመን በኪነጥበቡ አካባቢ የነበሩ ሰዎችን በኑሮ ውጤታማ አለመሆንን በማየት ይመስለኛል፡፡ በተጨማሪም ልክ የምስራ ሳይሆን የማጠፋ ስለሚመስለው የኔን ሙዚቀኝነት አልወደደውም ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን የስራ ውጤቴን የእኔንም ስነስርዓት ሲያየው ሞያዬን እየተቀበለው መጥቶ ነበር፡፡ ግን መጨረሻውን ሳያየው ቀረ የምወደው አባቴ በ1993 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡

መልካም የሚመኝ ቀና ሰው

አቶ ፍቃዱ ዋሪ የአምባሰል ሙዚቃ ቤት ባለቤት ሲሆን ካሳሁንን ከ1970ዎቹ ጀምሮ ያውቀዋል፡፡ ፍቃዱ ዋሪ ካሳሁንን ያወቀው መድረክ ላይ ሲሆን በጊዜው የካሳሁን ስም የገነነበት ወቅት ነበር፡፡ አቶ ፍቃዱ ስለካሳሁን ሲናገር ‹‹……ካሳሁንን በፊት አስተዋዋቂ ሳለ እርሱ ባያውቀኝም አውቀው ነበር፡፡ ትዝ እንደሚለኝ ኦሪስ የሚባል መስሪያ ቤት ውስጥ ሙዚቃዎችን ከሪል ወደ ቴፕ ይገለብጥ ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ እኔ አምባሰል ሙዚቃ ቤትን ስከፍት የበለጠ የመቀራረቡ እድል ተፈጠረ፡፡ እና በስራችን ላይ ትልቁን ሙያዊ እገዛ በስፋት ይሰጠን ነበር፡፡ ይህ እገዛ የእኛን ሞራል ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ካሳሁን ለሰው ልጅ እድገት መልካም የሚመኝ ቀና ሰው ነበር፡፡ ከካሳሁን ጋር እንደወንድም እንቀራረብ ስለነበር ገና ቴዲ ልጅ ሳለ ከቤተሰቡ ጋር ቅርበት መፍጠር ችያለሁ፡፡ ያኔ ቴዲ ገና ታዳጊ ቢሆንም ግጥሞችን ይሞክር ነበር፡፡ አዳዲስ ሙዚቃዎች ሲወጡ ሙዚቃ ቤቱ በራፍ ላይ ያሉትን ማስታወቂያዎች የሚሰራልን ካሳሁን ነበር፡፡ በጊዜው ሬድዮ ላይ ማስታወቂያ መንገር ብዙም ባልተጀመረበት ጊዜ ካሳሁን ብዙ ማስታወቂያ ሰርቶልናል፡፡›› በማለት ፍቃዱ ዋሪ ትዝታውን አውግቶናል፡፡

ልዩ የማሰብ ብቃት

በአንድ ወቅት ካሳሁን ገርማሞ ከወዳጁ ተስፋዬ ማሞ ጋር በመሆን የመሀሙድ አህመድን ታሪክ በዘጋቢ ፊልም ለመስራት ችሎ ነበር፡፡ የዘጋቢ ፊልሙ ርዕስም ማህሙድ አህመድ”ከሊስትሮነት እስከ ዝነኛ ድምፃዊነት” ይሰኝ ነበር። ካሳሁን በዚህ ስራ ላይ ሰዎችን ቃለ-ምልልስ ከማድረግ ጀምሮ ስራውን እስከ ፍጻሜ በማድረስ የጎላ ሚና መጫወቱን ተስፋዬ ማሞና ፍቃዱ ዋሪ ነግረውናል፡፡ ይህ በካሳሁን እና በወዳጁ በተስፋዬ ማሞ የተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም በቪኤችኤስ ወጥቶ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ ነበር፡፡

ፍቃዱ ዋሪ እንደሚናገረው ቴዲ አፍሮ የኪነጥበብ ተሰጥኦን ከአባቱ ወርሶታል፡፡ አባቱ አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር ላይ ተክኖበታል፡፡ ቴዲም በተመሳሳይ መልኩ ነገሮችን ባልታየ መልኩ የማየት እይታ እንዳለው ፍቃዱ ያምናል፡፡

ካሳሁን የፍቃዱ ዋሪ ብቻ ሳይሆን የኢትዮ ሙዚቃ ቤት ባለቤት የአስራት ዋሪም ወዳጅ ነው፡፡ ካሳሁን ሁሉም የተስማሙበት መልካም ሰብእና የተላበሰ ሰው እንደሆነ የዚህ ታሪክ ሰናጅ አረጋግጧል፡፡ ይህ ታሪክ በሚሰነድበት ጊዜ አቶ ፍቃዱ ዋሪ መኖሪያውን በአሜሪካ ያደረገ ሲሆን ለእረፍት አሜሪካ የመጣ ጊዜ ነው የዚህ ታሪክ ሰናጅ ቃለ-ምልልስ ያደረገለት፡፡

ፍቃዱ የወዳጁ ታሪክ በዚህ መልክ ከበርካታ ባለሙያዎች ጋር አብሮ መውጣቱ ደስ እንዳሰኘው ተናግሯል፡፡ ለሀገር ውለታ የዋሉ ሰዎችን በእንዲህ መልኩ ማስታወሱ ሊበረታታ ይገባል ሲልም ሀሳቡን ሰንዝሯል፡፡

ከራሱ አልፎ ክፍሉን ያስጠራ

ም/ኮ/ር ብርቄ ወ/ገብርኤል ጋዜጠኛ ካሳሁን ገርማሞን ከዛሬ 48 አመት ጀምሮ ታውቀዋለች፡፡ ከ1967-1994 ዓ.ም አብራ በአንድ አይነት ሙያ ላይ በመቆየቷ የጋዜጠኛ ካሳሁን አቅም ልዩ መሆኑን ትመሰክራለች፡፡ ምክትል ኮማንደር ብርቄ እንደምትናገረው ካሳሁን በመድረክ ስራው ብቃት ያለው ሰውን የሚያዝናና በሙያ ችሎታው ከራሱ አልፎ የክፍሉን ስም ያስጠራ መሆኑን ታምንበታለች፡፡ ካሳሁን ከመድረክ አስተዋዋቂነቱ ባሻገር እንደዘፋኝ ከታዋቂዋ ድምፃዊት ሂሩት በቀለ ጋር ንካው ባንገትህ ንኪው ባንገትሸ የሚለውን ዜማ አብረው ተጫውተው ተመልካቹን ደስ አሰኝተው ያለፉበት ጊዜም ነበር፡፡

ካሳሁን እንደ ሁለገብ ባለሙያ

ብርቄ ስታስታውስ ‹‹…የዘፈን ግጥሞችን ለድምፃዊያን ይሰጥ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ በተጨማሪም የፖሊስ ሬድዮ ፕሮግራም በ1969 ሲቋቋም የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ስልጠና ወስዶ ከሙዚቃ ክፍሉ ስራ ጎን ለጎን የጋዜጠኝነት ስራውን በተደራቢነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ካሳሁን እንደ አንድ ሪፖርተር ዜናዎችን አቀነባብሮ በማቅረብ ግሩም በሆነ ድምፅ ያነብ ነበር፡፡

የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ስራውን ለረጅም ጊዜ በተደራቢነት እየሰራ እውቅናውና ተደማጭነቱ እየጎላ ሲመጣ ለሙዚቃ ክፍሉ ሌሎች አስተዋዋቂዎች እንዲተኩ አድርጎና አሰልጥኖ የመድረክ ማስተዋወቅ ስራውን ትቶ በዝውውር በሬዲዮ ጋዜጠኝነቱ ቀጠለ፡፡›› በማለት ብርቄ ካሳሁን ገርማሞ ሁለ-ገብ ብቃት መላበሱን ትመሰክራለች፡፡

የሬድዮ ሰው

ከ1970-1990ዎቹ ድረስ ካሳሁን በዜና አንባቢነት በዜና ሐተታና በዜና ትረካ ስራው ምትክ የለሸ ሆኖ የአድማጭን ጆሮ ይዞ የቆየ ልሳነ መልካም ጋዜጠኛ ነበር፡፡ በፖሊስ ሬዲዮ ውስጥ እስካሁን በብዙ አድማጮች ዘንድ የማይዘነጋ ‹‹የምርመራ ማህደር፡›› በተሰኘው ዝግጅቱ መ/አለቃ ካሳሁን ብርሃኑ ከውጭ የተገኙትን በመተርጎምና ከሃገር ውስጥ ከምርጥ መርማሪዎች የተገኘውን የምርመራ መዝገብ አገላብጦ በማቀነባበር ካሳሁን ገርማሞ ደግሞ እንደፅሁፉ ባህሪ የብዙ ሰዎችን የድምፅ ተሳትፎ እሱ ብቻውን በሚገርም አገላለፅ በማቅረብ እጅግ ታዋቂና ተወዳጅ ነበር፡፡ ምክትል ኮማንደር ብርቄ ወልደገብርኤል ስለ ካሳሁን ስትገልጽ ‹‹…. ካሳሁንን በምርጥ አዘጋጅነት የሚገልፀው ከክልልም ይሁን ከአዲስ አበባ ከየጣቢያዎቹ ያገኛቸውን የወንጀል ስራ ክስተቶች የሚያቀርብበት ከጣቢያዎቻችን የተሰኘው ዝግጅት ምርጥና ካሳሁንን ለይቶ ያሳወቀው ስራው ነበር፡፡

ካሳሁን ከመድረክ አስተዋዋቂነቱና ከጋዜጠኝነቱ ባሻገር ከሰዎች ጋር ተግባቢ ጥሩ ስነምግባር ያለው ሙያውን አፍቃሪ ነበር፡፡ የመድረኩ አድማቂና ድምፀ ማራኪ ጋዜጠኛ ካሳሁን ገርማሞ በኖረባቸው ዘመኖች ሁሉ ለህይወት ትርጉም የሚሰጥ አስተዋይ ነገሮችን ሁሉ በትኩረት የሚያይ ጠንቃቃ ከመሆኑም በላይ ኑሮው በዕቅድና በጥናት ላይ የተመረኮዘ ነበር፡፡›› በማለት ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡

ካሳሁን በህይወት እያለ ያፈራቸው ልጆች ሁለት ናቸው፡፡ ሴትና ወንድ የመጀመሪያ ልጁ ዘወትር ካሳሁን፣ ካሳሁን ከማረፉ በፊት ታማ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡ ሁለተኛ ልጁን ደግሞ የኪነጥበብ ባለሙያ ከሆነችው ጥላዬ አራጌ ጋር በትዳር ተሳስረው የተወለደው ልጅ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ብርቅና ታሪክ ዘካሪ የሆነ የህዝብ ልጅ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ከሁለቱ አብራክ የተገኘ የህዝብ ስጦታ ነው፡፡ ካሳሁን ገርማሞ ልጁን ቴዎድሮስን በጉጉትና በስስት ቢያሳድገውም ቴዲ የወለዳቸውን ፍሬዎቹንና ስራ ውጤቱን የማየት እድል አልገጠመውም፡፡

ካሳሁን ገርማሞ የተለመደ ስራውን ለማቀነባበር በጉጉት ለሚጠብቀው አድማጭ ከየጣቢውና ከህብረተሰቡ መሃል የሚያሰባስባቸውን አስተማሪ አስጠንቃቂና አዝናኝ ዝግጅቶችን ለስራ ክልል ሄዶ በነበረበት ወቅት በመሃል ላይ የጤና መታወክ ገጥሞት ስራውን አቋርጦ አዲስ አበባ መጥቶ ፖሊስ ሆስፒታል በመታከም ላይ እያለ መስከረም 17 1993 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

1994 መስከረም ወር የፖሊስ ሙዚቃና ቲያትር ክፍል ምርጥ ተወዛዋዥ የነበርና በዛን ወቅት ፖሊስ ሙዚቃ ክፍልን በውዝዋዜ ወደር ያልነበራቸውን ተወዛዋዦችን አሰልጣኝ (ኬሮግራፈር) የነበረው የካሳሁን ገርማሞ የረጅም ጊዜ ጓደኛ ሻለቃ ባሻ ጌታቸው አንዳርጌና የመድረኩ አድማቂና ምርጡ ጋዜጠኛ ካሳሁን ገርማሞ በሶስት ቀን ልዩነት ከዚህ አለም በሞት ያጣንበት ወቅት ስለነበር ባለሙያዎቹን የሚያውቅ አይዘነጋውም፡፡

ካሳሁን ገርማሞ በታምሩ ጎንቼ ብዕር

ከአቶ ካሳሁን (1939 – 1993) ጋር በመጨረሻዎቹ ቀናት አብረን ነበረን። ካለፈ በኋላ እንጂ ያኔ ግን ቀናቱ የመጨረሻ ስለመሆናቸው ምን ምልክት ነበረን? በ1992 ዓም ማብቂያ ለምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ የፖሊስ ሚዲያ ጋዜጠኞች በታቀደ የሶስት ሳምንት የሙያ ማሻሻያ ፕሮግራም ቡድን መሪ የህዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ሓላፊው አቶ ጌታቸው ወ/ሰማያት፣ ከሬዲዮ አቶ ካሳሁን፣ ከምስለድምጽ/አዲዮቪዡዋል ሻለቃ ባሻ አሰበጻድቅ ኮስትሬ እና ከፖሊስናርምጃው ጋዜጣ ጸሃፊው ጅጅጋ ነበርን።

በሁለተኛው ሳምንት መጨረሻ ምሳም ሆነ ራት ላይ አቶ ካሳሁን ከቅባት ነገሮች ርቆ ፓስታ፣ ሰላጣዎች መጠያየቅ፣ ለቢራ ብቅ ስንልም ለስላሳ ማዘዝ ጀመረ።

እንግዲህ በመስክ ስራ ላይ የተለመደ መተራረብ አለ አይደል፣ ሄይ፣ ቁጠባ ተጀመረ እንዴ? … ምናምን እንላለን። ፈገግ ብሎ ያልፈናል። በሚቀጥሉት የሶስተኛው ሳምንት ቀናት ከእራት ስንነሳ፣ “በሉ ተጫወቱ፤ እኔ ልግባ፣ ጥሩ አይደለሁም” ይለን ጀመር።

ትንሽ እንዲጫወት እንከራከረውና ባሻ አሰበ፣ “ተዉት ይግባ፤ ይረፍ ግዴለም” ይላል። ይሁን እንላለን። አቶ ጌታቸው በምናውቀው ጨዋታው፣ “ጥለኸኝ ሄድክ? ግባ እሺ፣ ብሩም ይደር፤ ስጨርስ ታበድረኛለህ፤ መቼም አትጨክንብኝም፣ ማን አለኝ?” እያለ ይሸኘዋል።

በ3ኛው ሳምንት መጨረሻ የሄድንበት ሥራ አበቃ። ስንመለሰ ባቢሌ አካባቢ ከምስራቅ ሲጓዝ የዋለ ተሸከርካሪ እንዳለ በረዥም ሰልፍ ተገጥግጦ ጠበቀን። ገጠር ውስጥ በተፈጠረ ጸብ መንገዱ ለትራፊክ ዝግ መሆኑን ሰማን። ማለፍ አይቻልም ተብሎ መንገደኛ ሁላ መኝታ ፍለጋ ወዲህ ወዲያ ይላል። ወሬው ስላጓጓን ከመኪና ወርደን ከተማው መውጫ ባለ ቁልቁለት ትንሽ ሄድንና ለጥበቃ ወደቆሙ ታጣቂዎች ጠጋ አልን። ከግጭቱ እፍታ በኋላ ወታደር ወደ ስፍራው እየገባ ነው። ለመጓዝም ይሁን ለወሬ ከዚህ በላይ መጠጋት አልሆን ሲል ቆም አልን። ከሶስት ሳምንት ወጣሪ ስራ በኋላ ይሄን ነጻ የማጠቃለያ ሌሊት በምን አይነት እናሳልፈው? እየተባባልን ወደ ከተማው መሃል ስንመለስ፣ “ወንድሞቼ” አለ ካሳሁን። ከ2ኛው ሳምንት መጨረሻ የጀመረ ህመም በዚች ደቂቃም እየተሰማው መሆኑን ገልጾ እንደምንም መሄድ ቢችል ጥሩ እንደሆነ ነገረን።

እንግዲህ ጅጅጋ ሆነን፣ ‘ዛሬ ልክ አይደለሁም’፣ ‘ዛሬ ጥሩ አይደለሁም’ ያለንን እንቁጠር ካላልን ስለህመም ቃሉን ከራሱ የሰማሁት እዚህጋ ነው። ስራ ተከፋፈልንና አቶ ጌታቸውና ባሻ አሰበጻድቅ፣ ካሳሁንን መሸኘት ይቻል እንደሆነ ለመሞከር መንገድ ዳር ከቆመ ትራፊክ ፖሊስ ጋር ሲነጋገሩ እኔ ወደ አልጋ ፍለጋ ዞርኩ። በኋላ ስንገናኝ፣ በጥርጊያ መንገድ ዝጉን አልፎ ወደ አዳማ ሊጓዝ የተነሳ አንድ ባለፒካፕ እንደተባበራቸው ነገሩኝ። እዚያው አድረን በነጋታው ጉዞ ላይ ካሳሁንን አነሳንና እህኔ ቤቱ ይገባል ምናምን ተባባልን።

በመጣን በ2ኛው ወይም በ3ኛው ቀን፣ ጥቁር ካፖርት ለብሶ ወደ ቢሮ ሲገባ በትይዩ ካለው ቢሮዬ ሆኜ በአራት ሜትር ርቀት አየሁት። ወጥቼ እንዴት ሆንክ አላልኩትም። በማንኛውም ደቂቃ ወጣ ስል እንደምንገናኝ አስቤ ማለት ነው። ድኖ ስራ መግባቱ ነው የመሰለኝ። ረፋድ ላይ ላነጋግረው ቢሮ ጎራ ብል የለም። የሬዲዮ ልጆች – ሰለሞንና ደረጄ እንደነበሩ አስታውሳለሁ – ወደ ሆስፒተል መመለሱን ነገሩኝ። ለካ የመጣው ከመተኛቱ በፊት ከምስራቅ ያመጣቸውን ስራዎች መስመር ለማስያዝ ነበር።

ጧት ሳየው ስራ እየገባ እንደሆነ ማመኔ ለህልፈተ ህይወት መብቃት ብሎ ነገር በፍጹም ያልተገመተ ዱብዳ እንደሆነ ሳይጠቁም አይቀርም። ከስራ ጓደኞቻችን ጋር የጅጅጋ ወሬአችንን ሳንጨርስ ነው የ‘ሱ ህልፈት የተሰማው። ስድስት መቶ ምናምን ኪሜ ተጉዞ፣ ጥሩ አይደለሁም፣ ሃኪም ይየኝ ብሎ፣ ራሱ በቀጥታ ወደ ሆስፒተል በእግሩ የሄደ ሰው አረፈ ሲባል ማመን ይቸግራል። በዚህ ፍጥነት ለሞት የሚያበቃ ከባድ ህመም የጅጅጋ ፕሮግራሙን እንዲያቋርጥ እንዴት አላስገደደውም? አልኩ።

ከሥራ በኋላ በጊዜ ወደ መኝታው ከመግባት፣ አትክልትና ለስላሳ ከመፈለግ ሌላ ምንም ያየሁበት ነገር የለም። ይሄም በማጠናቀቂያው ሶስተኛ ሳምንት ነው። ሚሪንዳ ባዘዘ ቁጥር የኛ ተረብ መቀጠሉ ምን ይጠቁማል? ቀልዱ የፈለገ ያህል ጥሞን ቢሆን እንኳ፣ ሰው እየታመመ ለመሆኑ ምልክት እንዳየን ቀልድ ይቆማል። ይሄ ሁላችንምጋ ያለ ሰዋዊ ስሜት በመሆኑ፣ ቀልዳችን መቀጠሉ ካሳሁን ለሚያየው ሰው ጤናማ እንደነበረ ያግባባናል ብዬ አምናለሁ። ሥራውን አንድ ቀን ሳያስተጓጉል እኩል ጨርሶ ነው ጅጅጋዎችን ተሰነባብተን የተመለስነው – ልክ በያዝነው እቅድ መሰረት። የምረቃው ስነስርአት ላይም ነበር። በዚያ ሰሞን እንዲያውም ስለዘፈን ግጥሞች ባህርያት ንገረኝ እያልኩ በስክርቢቶ የጫርኳቸውን ስምንት ይሁኑ አስር ሙከራዎች ሰጥቼው ነበር። ከጅጅጋ መልስ የሆነ ቀን አረፍ ስንል እንጫወታለን እንዳለኝ ያ የሆነ ቀን ከመምጣቱ በፊት ተለያየን። በይሆናል ተስፋ ከማቀድ ውጪ በነገ ላይ ምን ስልጣን አለን?

እነዚህን ማሳያዎች የምዘረዝረው፣ ህልፈቱ፣ ቢጫ ሳናይ ከአርንጓዴ በቀጥታ ቀይ ቦግ ካደረገ የትራፊክ መብራት ጋር መፋጠጥ ነበር ልላችሁ ነው።

ስለባህርዩ ማሰብ ብፈልግ አይበት የነበረው ጥልቅ እርጋታ ነው የሚታወሰኝ። የሚያውቁት በዚህ የሚስማሙ ይመስለኛል። ሲናገር ድምጹ ውስጥ፣ ዝም ሲልም ፊቱ ላይ እርጋታ አለ። እርጋታ ምን ነበር? አለመዋከብ? ግን እሱ በወከባም ውስጥ ቢሆን ከእርጋታው ጋር መቆየት ይችላል። ይሄ አቅም ያለው ሰው ችግር ቢገጥመው በቀላሉ ፍንክች ስለማይል መታመሙ አለማስታወቁና የጅጅጋ ስራውን አጠናቅቆ መመለስ መቻሉ የገጠመውን በዚህ አቅሙ ተቋቁሞት እንደሚሆን በኋላ ላይ ተነጋገርን። አቋርጦት ወደ ሀኪም ቢሄድ ይድን ነበር ወይ? ሊድን ይችላል። ሊድን ከቻለ ለህመሙ ቅድሚያ ባለመስጠት ራሱን ጎዳ ልንል ነው። ሰው ያለአንድ ትልቅ ምክንያት ራሱን አይጎዳምና ለምን? ማለታችን አይቀርም። ህመም ሲሰማው የት ነበር? ምን ሲያደርግ ነበር? የሚሉ ጥያቄዎች ወደ ምክንያቱ ይመሩን ይሆናል። ክብደቱን የምትመዝኑት ሆኖ፣ በራሱ በኩል ግን ክፍሉን ወክሎ የጀመረው የጅጅጋ ፕሮጄክት እንዳይደናቀፍ መጠንቀቁ ግልጽ ነው ካልን፣ ሃላፊነትን ስለመወጣት የሚፈነጥቀው ጨረር ይኖር እንደሆነ ማዶውን አየት ማድረግ ነው። አቶ ካሳሁን አንጋፋ እንደመሆኑ ወጣት ጋዜጠኞች በመማማሪያ መልክ ሃሳብ ልትለዋወጡበት ትችላላችሁ። ሥራ፣ ሙያ የምንለው ነገር ከህልውናችን፣ ከግል ህይወታችን በጣም የተቆራኘ አካላዊና ህሊናዊ አቅማችንን ወጪ አድርገን የምንከውነው ነው። በደንብ መስራት ስለምንፈልግ ብዙ እንከፍልበታለን። ለሙያ ሲባል ከቤተሰብ መለየት፣ በረሃ ለበረሃ መንከራተት፣ ወደ ከፍታ ወጥቶ ህይወትንም መስጠት አለ። ለጡረታ ዘመን ስንደርስም ሙሉ አቅም ይዘን አይደለም፤ የልፋቱ፣ የውጣ ውረዱ አሻራ አብሮን አለ። ለዚያ የሰላሳ ዓመታት የስራ ጉዞ ዋና አገልጋይ የነበረው የሰውነታችን ክፍል ሻክሮ፣ ደድሮ፣ ፈዝዞ፣ ጎብጦ እናገኘዋለን። ጀበርና ምን እንደሚያደርግ የወታደሮችን ትከሻ ገለጥ አድርጋችሁ እዩ። ኬሚካል፣ ማእድን አካባቢ ብዙ ማየት ይቻላል። ታዳሽነት ያላቸው ክፍሎች ልፋቱን፣ ውጣ ውረዱን ይበልጥ ልምድ እያዳበሩበት፣ እየጎለበቱ ሲሄዱ፣ ታዳሽነት የሌላቸው ባትሪዎች ቀድመው ከአገልግሎት ይሰናበታሉ። ጡረታ ላይ ያለው የፖሊስ ምስለድምጽ ክፍል ካሜራ ባለሙያ ሳህሉ … ሁለቱም አይኖቹ ማብቃታቸውን በዚያ ሰሞን ስሰማ ለካሜራ ሰው ዋና ስራቤት ወይዘሪት አይን እንደመሆኗ ላምባዋን ጨርሳ ጠፋች ሲባል በቀጥታ

የመጣብኝ የኖረበት ሙያና ከሙሉ አካሉ ቀድሞ የተሰናበተው የሰውነቱ ክፍል ግጥምጥሞሽ ነው። የመሰናክሎች አይነትና መነሻ እልፍ እንደመሆኑ ጥናት ይፈልጋልና ይሄ እንደሙያዊ አስተያየት ሳይወሰድ ግን በግርድፉ ስራ/ሙያ የምንለው ነገር ወጪ እንዳለው እንግባባለን። ይሄ ወጪ በጉዳት ደረጃ ብዙ እንዳያስከፍለን፣ ከከፈልንም ማካካሻ/መጠገኛ ሊሆኑ ስለሚችሉ ሰልቶች መነጋገር ጥሩ ሊሆን ይችላል።

ወደ ተነሳሁበት። ከ1939 – 1993። የዚህ ቆይታ ጣሪያ፣ ሞት ቢመጣም ይሁን እንግዲህ የሚባልበት የድካም እድሜ አይደለም። ገና ሥራ ላይ አይደል። በሃምሳ ምናምን ዘመን ሞት ተቀባይነት የለውም። (ባትቀበል ምን የምታመጣ ሆነህ ነው?)

የሆነ ሆኖ የካሳሁን ህልፈት እንዳልኩት የመንፈስ ዝግጅት ስላልነበረ በተለይ በመጨረሻዎቹ ቀናት አብረን ለነበርነው ድምጹ ጆሮአችን ውስጥ፣ ፊቱ አይናችን ውስጥ እያለ በሳምንት ጊዜ ድንገትና በፍጥነት ገጹ መታጠፉ ያለማመን ንዝረት አለው። ንዝረት ምን ነበር? የሰልስት ድንኳን ውስጥ መጥተው ቁጭ የሚሉት አባ ይሄን ንዝረት እንደርእደመሬት ገና ሲጀምር ከሩ … … ቅ ነው የሚሰሙት። ትንሽ መርገቢያ ጊዜ ይሰጡታል። ከዚያ ካባቸውን እያስተካካሉ ይነሱና፣ “በቃችሁ!” ይላሉ። “ወንድማችን በህመም ዳኛ፣ ባልጋ ቁራኛ ሳይሰቃይ ሄደ፤ የጻድቅ ሞት ነው! ሌላ ምን እንዲሆን ፈለጋችሁ?”

እዚህጋ ግን እኛም አንድ ጥያቄ ማንሳት እንችላለን፦ በጤና ኤክስቴንሽን እንጂ በህመም ኤክስቴንሽን ምን? ማለፍ ግድ ከሆነ፣ በተራዘመ ህመም በመሰቃየት ውስጥ ምን አለ?

የስራ ባልደረባውና ጓደኛው ጋዜጠኛ ሰለሞን አምባቸው በጠያቂው ሲጠየቅ ፕሮግራም ከጋዜጠኛ ቦጋለ ተስፋዬ ጋር ባደረገው ቆይታ ይህን ብሏል።

‘’1987ወደ ኢቲትቪ ስገባ የፈተነኝ ካሳሁን ግርማሞ ነው። ቢሮዋ እራሷ ትዝ ትለኛለች፤የፖሊስ ጋዜጠኝነት ከባድ ነው ምን ያህል ዝግጁ ነህ ብሎ ሲመክረኝ አስታውሳለው። ወደ ስራ ከገባው በሃላም አቅጣጫ ያሳዩኝ ሻምበል ግዛው ዳኜና ካሳሁን ግርማሞ ናቸው።ካሳሁ ለየት የሚያደርገው ጥሩ ፀሃፊ ነው ከዚህም በላይ ግን ትረካ የሚያክለው አልነበረም፤በሙያው ሁለገብ፤ባባህሪው ልታይ ልታይ የማይል ሰው ነበር።ካሳሁን ግርማሞ ሰው ከቴዲ ጋር ያያዘዋል ካስሽ ግን ብቻውን በቂ ነው የቴዲ አባት ስልሆነ ሳይሆን እራሱን ችሎ የሚወራ ታሪክ ያለው ሰው ነው። ካሳሁን ኑሮዉን በዲሲፕሊን የሚመራ ሰው ነው፤ያለውን ደሞዝ አብቃቅቶ የሚኖር፤ባለሙያ ነበር።

ካሳሁን ጎበዝ መድረክ መሪ ነው በተለይ ፖሊስ ኦርኬስትራ ውስጥ በጣም ይታወቅ ነበር። የማስታውቅያ ባለሙያም ነበር። በተለይ የነ ኤፍሬም ታምሩን፤የነ አስቴር አወቀ፤ካሴቶቻቸው ሲወጣ አምባሰል ሙዚቃ ቤት የሚሰማው የሱ ማስታወቅያ ነበር። ያኔ እንደውም ከግጥሞች እያወጣ እያዋዛ ነበር ማስታወቅያ ውን ይሰራ የነበረው።

ወደ መጨረሻ አከባቢ ቴዲ ደረሰለት፤በቴዲም ዘፈን ማውጣት ደስተኛ ያልነበረው ካስሽ ምክረው እባክህ ይለኝ ነበር። አባት ለልጁ ነጋዴ ወይም የብዕር ሰው እንዲሆን ይፈልግ ነበር፤ቴዲም የአባቱን ቁጣ ስለሚያውቅ ተደብቆት ነው የሚሰራው’’

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት እና በታሪክ ሰናጁ በእዝራ እጅጉ የተጻፈ እና ሀምሌ 20 2015 በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች የተሰነደ ነው፡፡ኢትዮጵያ አሁንም ልጆቿ ሲጠሩ ደስ ይላታል፡፡ ሲረሱ ይከፋታል፡፡ እናት ልጆቿ በደማቅ ብእር ሲከተቡ እንደማየት ደስ የሚያሰኛት ነገር የለም፡፡ እኛም ኢትዮጵያን የምንወድ እና የምንሰንድ እንደመሆናችን የሰራ ታሪኩ ለትውልድ ሲተላለፍ ደስ ይለናል፡፡ ግባችን የህይወት ታሪክን ማቀበል ነው፡፡ የተቀበለ ያስቀምጣል፡፡ ካላቀበልን ወይም የምናቀብለውን ካላኖርን ነገ ምን ተስፋ አለን? ቴዲ አፍሮ እንደሚለው የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ ነውና በብዙ አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች የተሸፈኑ የተደበቁ ፤ ሰዎችን ማስታወስና ማንቃት ያለብን አሁን ነው፡፡

ካሳሁን ገርማሞ በዚያ ወርቃማ ዘመን የራሱን ደማቅ አሻራ ትቶ አልፏል፡፡ እርግጥ ነው በልጁ ሁሌም ይታወሳል፡፡ ቢሆንም ግን ቀዳሚው ተመስጋኝ አባት ነውና ካሳሁን ገርማሞን ለማክበር እነሆ ታሪኩን አካፍለናል፡፡ የጥበብ ሰዎች ብዙም በኑሮ በማይጠቀሙበት ዘመን ካሳሁን ዋጋ ከፍሎም ቢሆን የሚድያው እና የመዝናኛው ዘርፍ ላይ የራሱን ስም ለመትከል ሞክሯል፡፡ ይህም መመዝገብ አለበት፡፡ ዛሬ እኛ ካልመዘገብነው እኛ ስናልፍ በቀላሉ ይረሳል፡፡ በቃል ያለ ይረሳል በጽሁፍ ያለ ይወረሳል፡ እንዲሉ ካሳሁንን በጽሁፍ አስቀምጠነዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለልጁ ለቴዲ ኩራት ለመላ የካሳሁን አድናቂዎች ደግሞ ደስ የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡ እኛም ይህን ጽሁፍ በተጨማሪ ሀሳቦች አጠናክረን በካሳሁን ውስጥ ኢትዮጵያን ፈልጎ ለማግኘት ብዙ እንደክማለን፡፡