እሌኒ ፈጠነ

እሌኒ ፈጠነ /1910- 2003/

መዝገበ-አእምሮ ላይ የህይወት ታሪካቸው ከተሰነደላቸው የሚድያ ሰዎች መካከል ወይዘሮ ሮማንወርቅ ካሳሁን ቀጥሉ የተረከቡት ጋዜጠኛ ወይዘሮ እሌኒ ፈጠነ ናቸው፡፡ እኒህ ሴት ማና ቸው?

ቀልጣፋዋ ፍልቅልቋ ድማም ጋዜጠኛ የሴቶች አምድ ዋና አዘጋጅ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና አንባቢ የማስታወቂያ ሚንስቴር ዶክመቴሽን ክፍል ሰራተኛ ነበረች፡፡ ጋዜጠኛ እሌኒ ፈጠነ ከአባቷ ቀኝ አዝማች ፈጠነ እና ከእናቷ ወ/ሮ ቦጋለች በ 1910 ዓ.ም በአዲስአበባ ከተማ ነበር የተወለደችው ። በሀገራችን የዶክመንቴሽን ሥርዓት ደካማ መሆን ሳቢያ ስለጋዜጠኛ እሌኒ ፈጠነ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የተሟላ እና ፈርጠም ያለ መረጃ ያገኘን ባይሆንም በአዲስአበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ማለትም ኮሜርስ መማሯ ግን እርግጥ ነበር።

ከዚያም በ 1940ዎቹ መጨረሻ 1950ቹ መጀመሪያ አካባባቢ ጋዜጠኛ ሮማንወርቅን ተክታ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና አንባቢ ሆነች። በዚህም ለረዥም ጊዜ የሰራች ሲሆን የድምጽ ጋዜጣ ሲጀመር የሴቶች አምድ ዋና አዘጋጅ ሆና ብዙ አገልግላለች ። የሴቶችን አቅም የሚያሳዩ ማህበራዊ ህይወት ፣ የበጎ ሥራ ማህበራት ፣ የእደጥበብ ሥራዎችና ሌሎችንም የሚዳስሱ ጽሑፎች እንዲታተሙ ስታደርግ ቆይታለች ። ይህም ሴቶችን የሚያበረታታ ከማጀት ወደ አደባባይ በስፋት ብቅ የሚያደርግ እንዲሁም በወቅቱ የሥራ እኩልነት እንዲነቃቃ የበኩሏን አስተዋጽኦ አበርክታለች ።

በዚያን ዘመን እንደአሁኑ የቴክኖሎጂ እገዛ በሌለበት ነገሮችን በአንድ ጊዜ አሳልጦ ለማስኬድ አደጋች በሆነበት ጊዜ እሌኒ እጅግ በጣም ፈጣን በርካታ ሥራዎችን በአንድ ጊዜ የምትከውን ብርቱ ጋዜጠኛ ነበረች ። መረጃዎችን አፈላልጋ ፤ ቀን በቀጠሮ ቦታ ቀድማ በመገኘች ቃለመጠይቅ ሰርታ ማታ በእጆቿ ጽፋ ጠዋት ማተሚያ የምትሰጥ ቀልጣፋ ነበረች፡፡ ሁሉነገር በጉልበትና በሰዓት በሚሰራበት ወቅት እሌኒ ሥራዋን ታቀላጥፍ ነበር። የጋዜጠኛ እሌኒ ወንድም የሆነው ሻንበል አፈወርቅ ልጅ ዮሀንስ ከተወዳጅ ሚዲያ ጋር በነበረው ቆይታ ስለአክስቱ የሚያስታውሰውን ሲናገር ታዲያ አክስቴ የምትለፋ ፣ የምትጥር የተግባርና የውሳኔ ሰው የሆነች በአንድ ሰው ሆና ሳለ እንደብዙ የምትሰራ ነበረች ይላል።

እሌኒ መኩሪያ በኋላ ከኢትዮጰያ ሬዲዮ ወደ ማስታወቂያ ሚንስተር ተዘዋውራ በዶክመንቴሽን ክፍል እስከ ጡረታ ጊዜዋ ድረስ አገልግላለች ።በ 1970ቹ ገደማ ይህም ማለት በደርግ ዘመነ-መንግሥት ጡረታ ወጥታለች። በራሷ ብዙ ነገሮችን ማድረግ የምትወደው እሌኒ ጡረታ ወጥቻለሁ ብላ መቀመጥን አልመረጠችም ። ለቀጣይ ቤቷ ለነፍሷ ስንቅ የሚሆናትን ሐይማኖት አጥብቃ በመያዝ እስከዚያ ለስጋዋ ማሰንበቻ ይሆናት ዘንድ የባልትና ውጤቶችን አዘጋጅታ በመሸጥ በኋላም ጌጃ ሰፈር የሰራችውን ቤት እየኖረች በማከራየት ህይወቷን መርታለች።

እሌኒ በጥቅሉ 6 ልጆችን ከ 3 ባሎች የመውለዷ ሚስጢር ሴት ጋዜጠኞች በጊዜው የሚገጥማቸው ፈተና ከባድ እንደሆነና ቤተሰብ የመምራትና የሥራ ጫና መብዛት የተረጋጋ ህይወት እንዳይመሩ ያደርጋቸው እንደነበረ ያስረዳል ። ከስራም የጋዜጠኝነት ስራ ሙሉ ጊዜን የሚጠይቅ ከቦታ ቦታ ዝውውር እንቅስቃሴ የሚያስፈልገው የንባብና ልምድ የሚጠይቅ በመሆኑ ወልዶ ከማሳደግ ትዳር ይዞ ቤት ከመምራት ጋር በእጅጉ አቻችሎ ለመሄድ በተለይም በዚያ ዘመን አስቸጋሪ ነበር።

የእሌኒ የመጀመሪያ ልጅ አለማየሁ ፈጠነ በኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄን ከፈጠሩት አንዱና ” የስሜት መስታወት ” የተሰኘ ልቦለድ ደራሲ ነው። አብዛኖቹ ልጆቻቸው ኑሯቸውን በአሜሪካን ሀገር ያደረጉ ናቸው ። እሌኒ ፈጠነ በዚያን ዘመን በጋዜጠኝነት ሙያ አገልግሎቷ ሀገሯን እና ህዝቧን ያገለገለች በህትመት ሥራዎቿ በሴቶች ዘንዳ ጥሩ መነቃቃትን የፈጠረች ጋዜጠኛ ነች ። እሌኒ በተወለደች በ 86 ዓመቷ ከዛሬ 11 ዓመታት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *