አያሌው  በዛብህ


ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን፣ መዝገበ-አእምሮ (የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል።

ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች፣ በመጽሐፍ፣ በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት 4 ዓመታት ከ5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መጽሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።

ቅፅ 3 መዝገበ አእምሮ መፅሐፍ ፣ከ20 በላይ ዘርፎች ይኖሩታል። ከእነዚህም ዘርፎች አንዱ ባንክና ኢንሹራንስ ሲሆን ታሪካቸው የሚሰነደውም የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የመጀመሪያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አያሌው በዛብህ ናቸው። እርሳቸው በአሁኑ ሰዓት የ86 ዓመት ሰው ሲሆኑ በኢንሹራንስ ኢንደስትሪ ውስጥም ፈፅሞ የማይረሳ አሻራ አኑረዋል። ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት እርሳቸውን ቃለ- መጠይቅ በማድረግ የሕይወት ታሪካቸውን ሰንደናል። ዕዝራ እጅጉ እና ባንቺአየሁ አሰፋ ታሪኩን እንደሚከተለው ሰንደውታል።


የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን ለዓመታት መርተዋል፡፡ ከሕብረት ኢንሹራንስ ጀምሮ በርካታ ኢንሹራንሶችን በሥራ አስኪያጅነት 12 ዓመታት ገደማ አገልግለዋል፡፡ ዛሬም ድረስ ኢንሹራንሶች የሚተዳደሩበትን ማኑዋል አዘጋጅተዉ ይገለገሉበት ዘንድ አበርክተዋል፡፡ በአጠቃላይ 14 ዓመታትን በኢንሹራንሽ ዘርፍ 12 ዓመታት በላይ በንግድ ዘርፍ በጥቅሉ ከ 26 ዓመታት በላይ ሀገራቸዉን እና ህዝባቸዉን አገልግለዋል፡፡ የያኔዉ ወጣት የአሁኑ የ 85 ዓመት አዛዉንት አቶ አያሌው በዛብህ፡፡

አቶ አያሌው በዛብህ በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በአማራ ክልል፣ በጥታዊቷ ጎንደር፣ በበጌምድር ላስቤን ጠቅላይ ግዛት ደብረታቦር አውራጃ ሚያዚያ 27 ቀን 1932 ዓ.ም  ተወለዱ፡፡ ልጅነታቸው ብዙ ያልተቃና ቢሆንም በራሳቸው መፍጨርጨር አድገው በቄስ ትምህርት ቤት ፊደል ለይተዋል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸዉን ደ/ታቦር አፄ ቴዎድሮስ እስከ 5ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከ 6-8 ጎንደር ፃድቀ ዮሀንስ የተማሩ ሲሆን የሀገር አቀፍ ምዘና ፈተናቸውን በጥሩ ውጤት አጠናቅቀው በቀዳማዊ አፄ ኃለሥላሴ ኮተቤ አዳሪ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡ በኋላም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1957 ዓ.ም አግኝተዋል፡፡

አቶ አያሌዉ በዛብህ ከተወዳጅ ሚዲያ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ እንዲህ ሲሉ የልጅነት ራዕያቸዉን ያስታዉሳሉ፡፡

“… እኛ በልጅነታችን ህልማችን የነበረዉ ትምህርት ተምረን ጨርሰን ሀገራችንን ማገልገል ነበር፡፡ ሀገራችንን ለማገልገል ካለን ጉጉት የተነሳ ኢትዮጵያዊ የሆነ ድርጅት ውስጥ መቀጥር እንፈልግ ነበር “ይላሉ፡፡

ተመርቀዉ እንደጨረሱም ህልማቸዉ እዉን ሆኖ ኢትዮጵያዊ በሆነዉ የሥጋ ሀብት ልማት ድርጅት ውስጥ  የሒሳብ ባለሙያ በመሆን ሥራቸውን ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ ከተመደቡበት ቦታ አኳያ የአየር ንብረት ለውጡን ሊቋቋሙት ባለመቻላቸው መሥሪያ ቤቱ ብዙም ደስተኛ ሊያደርጋቸዉ አልቻለምና 5 ወራት እንደሠሩ ለቅቀዉ ኢትዮጵያዊ ወዳልሆነዉ ፊሊፕስ አቀኑ፡፡  ፊሊፕስ በጥሩ ደመወዝ ቀጠራቸው፡፡ አቶ አያሌዉ በሙያቸዉ በፊሊፕስ ን ለ 7 ዓመታት አገለገሉ፡፡ እንደ ሆላንድ እና አየር ላንድ ባሉ የአውሮፓ ሀገራት ተዛዋውረው ጥልቅ የሆነ የማርኬቲንግ ሙያን ለመማር እና ጠቃሚ ልምዶችንም ለመቅሰም ዕድል አገኙ፡፡ በተግባር የተፈተሸ የንግድ እውቀትም አካብተውበታል፡፡

የኋላ ኋላ ግን በፊሊፕስ በመልቀቅ ኢትዮጵያን አማልጋሜት ገቡ፡፡ በሦስት ዓመታት የስራ ሂደት ከፍተኛ የሆነ ለዉጥም ማስመዝገብ ቻሉ፡፡ በ1968 አገሪቱ ላይ ለዉጥ የመጣበት ነበርና ኢኮኖሚዉን ሙሉበሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ሥር ለማዋል ደርግ የወረሳቸውን የግል የኢንሹራንሽ ኩባንያዎች ጠቅሎ በኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሥር እንዲሆኑ ባደረገበት ወቅት ማን ይረከብ ?ሲባል እንዲረከቡ ከታዘዙት ሰዎችም አንዱ አቶ አያሌው ነበሩ፡፡ ስለኢንሹራንስ በቂ የሆነ ዕዉቀት ስላልነበራቸዉ ሕብረት ኢንሹራንስን ኩባንያን እያንገራገሩም ቢሆን እጅግ ጥንቃቄ በተሞላዉ ሁኔታ ተረከቡት። መንግስት ወረስኩ ብሎ እንዲረከቡ የላካቸዉ ኩባንያ እዳ ብቻ ነበርና ገና ከመግባታቸዉ 7 ገጽ ሪፖርት በመጻፍ ኩባንያዉ ያለበትን አቋም በማሳወቅ ራሳቸዉን እና መንግስትን ከከባድ የገንዘብ እዳ ታድገዋል፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል ከኢንሹራንሱ ሒሳብ በኩል ኀይለሚካኤል ኩምሳ እና ከኢንሹራንሱ የቴክኒክ ባለሙያ ገብረእግዚ ጋር በመተጋገዝ የኢንሹራንሱ ሥራ አስኪያጅ ሆነዉ መርተዋል፡፡ በሂደት Re-order ሆኖ ኦዲት ተደርጎ ሲያልቅም አንድ ራሱን የቻለ ትርፋማና የተደራጀ የመድን ድርጅት እንዲሆን አበቁት፡፡ አቶ አያሌዉ ብዙም ሳይቆዩ ከትንሹ ኩባንያ ወደትልቁ የኢምፔሪያል ኢንሹራንስ ዋና ስራ አሰኪያጅ ሆነዉ ተሾሙ፡፡ ይሁን እንጂ ለተሰጣቸው የኃላፊነት ቦታ የሚመጥን ሥራ ባለመኖሩ ኢንሹራንሱን ትተው ወደ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አቀንተዋል፡፡ በዚያም በባህርዳር የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ሆነዉ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት አግልግለዋል፡፡
ከ 2 ዓመታት ቆይታ በኋላ ከባህርዳር ጨርቃጨርቅ ተጠርተዉ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ( የኢንሹራንሶች ጀነራል ማኔጀር ) ሆነዉ ተሾሙ፡፡ በታሪክም ድርጅቱን ለረጅም ጊዜ የመሩ ሰዉ ናቸዉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢንሹራንሶች የያዙት ቅርፅ እና አስተዳደራዊ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የተዘረጋው በእርሳቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በኢንሹራንሶቹ አሰራር ላይ ዛሬም አንዳች የተቀነሰም ሆነ የተጨመረ ነገር የለም ይላሉ፡፡ የኢንሹራንሶቹን የአሰራር ሂደት በማዘመን ወጥ የመተዳደሪያ ደንብ እንዲኖር ኮሚቴ አዋቅረው ራሳቸዉም የኮሚቴዉ አባል ሆነዉ ጥናት በማድረግ ፣ ፈትሸው ወደሥራ እንዲገባ የማርቀቅ እና የማፅደቅ ሥራን ሠርተዋል፡፡ የኢንሹራንስ አገልግሎት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝበ እንዲዳረስ የሚያስችል አሰራር ዘርግተዋል፡፡ አጥጋቢ የሆነ ውጤት እንዲመጣ አድርገዋል፡፡ ኢንቨስት የሚደረግ ፈንድ እንዲጠራቀም እና ቢዝነሱ የተሳካ እንዲሆን ጥረት በማድረጋቸው ምሥጋና ይቸራቸዋል።

የኢንሹራንሶችን ቅርንጫፍ በማብዛት የኢንሹራንስን ምንነት እንዲታወቅ በማድረግ፣ ለሰራተኞች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ለመንግስት የሥራ ማረጋገጫ ሪፖርት እንዲቀርብ በማድረግ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል፡፡ ስኬቶችንም ተጎናጽፈዋል፡፡ በመዲናዋ አዲስ አበባ ብቻ ተወስነው የቀሩት ኢንሹራንሶቹ በአቶ አያሌው የሥራ ዘመን ተደራሽነታቸዉን በማስፋት በጎንደር፣ ሀዋሳ፣ ጅማ፣ ናዝሬት፣ ድሬዳዋ፣ ነቀምት፣ ኮምቦልቻ እና ጅቡቲ ድረስ እንዲስፋፉ ሆኗል፡፡ ዓላማቸውም መድን ድርጅቱ አንድ ትልቅ ትርፋማ የመንግስት ድርጅት እንዲሆን ነበር፡፡ ስለሆነም አንድ ኢንሹራንስ ኩባንያ የመጀመሪያ ሥራው ምንድነዉ? አንድ ግለሰብ አገልግሎት ፈልጎ በመጣ ጊዜ ትክክለኛ የሆነ የሆነ ኢንሹራንስ አለዉ ወይስ የለዉም? ብሎ እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል ፣ የኢንሹራንስ አከፋፈል ሥርዓትና ፖሊሲዉ ምን መምሰል አለበት? የሚሉትን መሰል ጥያቄዎች የሚመልስ ለሁሉም የኢንሹራንስ ቅርንጫፎች መተዳደሪያ የሚሆን ድርጅታዊ አሰራር ፈጥረዋል፡፡ አቶ አያሌዉ የኢንሹራንስ አገልግሎትን ከማስፋፋት እና አዳዲስ ግንባታዎችን ከማስገንባት ባሻገር የተደራጀ ተቋም እንዲሆን እና የተደራጀ ተቋማዊ አሰራር እንዲኖር አድርገዋል፡፡ የቅርንጫፍ ቢሮዎቹን ግንባታዉን ለየት የሚያደርቸዉ ደግሞ ለኢንሹራንሱ ከፍተኛ የሥራ ባለሙያዎች መኖሪያን ያካተቱ መሆናቸው ነው፡፡ አቶ አያሌዉ በሥራ ዘመናቸው በእያንዳንዱ መስክ  ቢሮ ከመክፈት፣ ሰራተኞችን ከማስተዳደር፣ ዲፓርትመንቶችን ከመከፋፈል፣ ሥራዎችን ከመምራት ባሻገር በዘርፉ ላይ በርካታ የራሳቸው የሆነ አሻራም አሳርፈዋል፡፡ ቀላል የማይባል ለዘመናት የዘለቀ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ የኢንሹራንስ አገልግሎት ላይ ጥልቅ ግንዛቤን እንዲፈጠር እና ስለኢንሹራንስ አገልግሎት ይበልጥ እንዲታወቅ ማስታወቂያዎችን በማሠራት፣ በተመረጡ የክልል ከተሞች ግዙፍ የኢንሹራንስ ግንባታዎችን በማካሄድ፣ ጉልህ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ፣ የቅርንጫፎችን ቁጥር በመጨመር፣ የሥራ ዕድልን በማስፋፋት፣ ለተቀላጠፈ እንቅስቃሴ የሚያግዙ ተሸከርካሪዎችን በማዘጋጀት፣ ራሱን የቻለ የሥልጠና ዲፓርትመንት በማቋቋም እና ላይብረሪ በመክፈት ዕውቀት እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡

 ብቁና የሰለጠነ የሰዉ ኃይል በመፍጠር ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ ባለሙያዎችን ለዓለማቀፍ የሥራ ዕድል በማብቃት ፣ ኢንሹራንሶች መተዳደሪያ ማኑዋል በመቅረፅ እና በማዘጋጀት ብሎም ወደሥራ በማስገባት፣ የኢንሹራንስ አከፋፈል ሥርዓትን ጨምሮ ሙሉ የመድን የሥራ ሲስተም በመዘርጋት፣ በአሰራር ሂደት ሊፈጠሩ የሚችሉ ብልሹ የአሠራር ሥርዓቶችን በማስቀረት፣ ኢንሹራንሾች ትርፋማ የሚሆኑበትን አማራጭ በመጠቀም ለመንግስትም ከፍተኛ ገቢ እንዲገኝ አድርገዋል፡፡ ስለ ፕራይም ኢንሹራንሽ፣ ሞቶር ኢንሹራንስ እና አከፋፈል ሥርዓትን ጨምሮ በርካታ ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡ ለሁሉም የኢንሹራንስ ዓይነቶች ኢንሹራንስ የሚገባበትን ዋጋ በማመጣጠን ሰዎችን የኢንሹራንስ ተጠቃሚ በማድረግ በርካታ የመንግስትና የግለሰብ ኪሳራዎችን እንዲሸፈኑ አድርገዋል፡፡ በሥራ ዘመናቸዉ በሚሰሩበት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ተቋም ከ 80 -100 ሚሊዮን ትርፍም አስገኝተዋል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አባት ናቸው ብንል በእርግጥም ግነት የለውም፡፡ የትኛዉም ፍሬ፣ የትኛዉም ቅርንጫፍ ሥር ከሌለዉ ዉል አልባ ነዉና፡፡
አቶ አያሌዉ እንዲህ ይላሉ ‹‹በኢንሹራንስ የሥራ ዘመኔ የደርግ መንግስት በሦስት ዓመት ዕድሜ ይበልጠኛል፡፡ ቢሆንም ከኢህአደግ ጋር ግን አብሮ መክረም አልተቻለም፡፡ የኢሠፓ አባል በማለት የግል አመለካከቴን ነቅፎ ለወራት ዕድሜ ወህኒ ወርውሮኝ ነበር፡፡ በሠራተኞች ግፊት እና ተቃዉሞ የተነሳ ከወህኒ ወጣሁ፡፡ ጡረታዬንም ሳላስከብር በስተርጅና ወደ ሀገረ አሜሪካ ተሰደድሁ፡፡›› ይላሉ።

አቶ አያሌዉ ትልቁን ኢትዮያዊ አትራፊ ድርጅት ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል።

የፀሐይ ኢንሹራንስ አማካሪ በመሆን ለ 3 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ መልካሙን ተመኘን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *