አቶ ክብረወርቅ አባተ(ኤሌክትሪክ መሀንዲስ(1922-2018)

የአንጋፋው የሙዚቃ ባለሙያ የአበጋዙ ክብረወርቅ ወላጅ አባት አቶ ክብረወርቅ አባተ በተወለዱ በ96 ዓመታቸው ህይወታቸው አልፎ የቀብር ሥነሥርዓታቸውም በመንበረ ፀባዖት ሥላሤ ቤተክርስቲያን ከቀኑ 6:30 ተፈጽሟል።

የአቶ ክብረወርቅ አባተ ታሪክ በተወዳጅ ሚድያ እንደሚከተለው ተሰንዷል።

በአገራችን ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የኤሌክትሪክ መሐንዲስ የሆኑት አቶ ክብረወርቅ አባተ አበጋዝ፣ ከአባታቸው ከአቶ አባተ አበጋዝ እና ከወላጅ እናታቸው ከወ/ሮ አማረች ስንቄ መጋቢት 29 ቀን 1922 ዓ.ም በቀድሞው ወሎ ክፍለ ሀገር በደሴ ከተማ ተወለዱ።

እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም በንጉሥ ሚካኤል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በልጅነታቸው ትምህርት ወዳድ የነበሩት አቶ ክብረወርቅ አባተ፣ በአስተማሪዎቻቸው የተወደዱ መሆናቸው ይነገርላቸዋል።

በ1943 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ የመጡት አቶ ክብረወርቅ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን
በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን እዚያም ሳሉ ለትምህርታቸው ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ እንደነበር አብረዋቸው የተማሩ ይመሰክራሉ።

የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም በኢትዮጵያ አየር ኃይል መሥሪያ ቤት በመግባት በአብራሪነት አገራቸውን በከፍተኛ ትጋት አገልግለዋል።

በመቀጠልም፣ በኢትዮጵያ ቴሌኮምዩኒኬሽን መሥሪያ ቤትና በፖይንት 4 ሙያዊ አገልግሎት መስጠት ችለዋል። አቶ ክብረወርቅ በቴሌኮሚኒኬሽን ማሠልጠኛ ለ2 ዓመታት ሥልጠና የወሰዱ ሲሆን ይህንን ሥልጠናቸውን በመውሰድ ላይ ሳሉ ነበር የነፃ የትምህርት ዕድል ያገኙት።
አቶ ክብረወርቅ አባተ በ1954 ዓ.ም ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ ጃፓን ያቀኑ ሲሆን ከቶክዮ ዩኒቨርስቲም በኤሌክትሪካል ምህንድስና የባችለር ኦፍ ሳይንስ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።አቶ ክብረወርቅ አባተ ዲግሪያቸውን ከማግኘታቸው ቀደም ብሎ በጃፓን ታዋቂ የሬድዮ ኮምዩኒኬሽን ማሰልጠኛ ገብተው ትምህርት የቀሰሙ ሲሆን ይህም ለሬድዮ ኮምዪኒኬሽን ዘርፍ ከፍተኛ ፍቅር እንዲያድርባቸው አድርጓል።

ከዛሬ 62 ዓመት አስቀድሞ የጃፓንን የሥልጣኔ መንገድ በቀላሉ ለማየት የቻሉት የኤሌክትሪክ መሐንዲስ ክብረወርቅ አባተ የጃፓንን ባህል እና ቋንቋ ለመልመድ ከመቻላቸው ባሻገር በርካታ ጃፓናውያን ወዳጆችን ለማፍራት ችለዋል።

በ1957 ዓ.ም የቶኪዮ ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ አገር ወዳዱ አቶ ክብረወርቅ አባተ ኢትዮጵያን ማገልገል እንዳለባቸው ፅኑ ዕምነት አሳድረው ነበር። ይህን ዕምነታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ባላቸው ቁርጠኝነት ወደ እናት አገራቸው በመመለስ በሙያቸው ማገልገል ጀመሩ። በመቀጠልም፣ በኢትዮ ናይለን እና በሞጆ ጨርቃጨርቅ በትጋት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት የተወጡ ሲሆን ሞጆ ጨርቃጨርቅንም ያቋቋሙ ናቸው።

ኤሌክትሪካል መሐንዲስ ክብረወርቅ አባተ የአፍሪካ ኩራት ወደሆነው ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ በ1958 ዓ. ም የተቀጠሩ ሲሆን እዚያም ሳሉ በጥራት ቁጥጥር መሀንዲስነት፣በግራውንድ ቴክኒሻንነት እና በሽያጭ ክፍል ኃላፊነት ለ15 ዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ አገልግሎት የሰጡ ሲሆን ያሳዩት ከፍተኛ ትጋትም በአየር መንገዱ የበላይ አመራሮች አድናቆት የተቸረው ነበር።በተለይም ካሜሩን ተመድበው ይሠሩ በነበረበት ጊዜ ትጋት አሳይተዋል።

አገር ወዳዱ ባለሙያ ክብረወርቅ አባተ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሳሉ አገርን ይጠቅማል ብለው ካሰቡ ሀሣብ ያቀርቡ ነበር። በወቅቱ አገራችን ለመለዋወጫዎች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ታወጣ ስለነበር ዕቃዎቹ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ተሻሽለው የሚሠሩበትን መንገድ በማመቻቸት ሀሣቡም ተግባራዊ እንዲሆን የግላቸውን ጥረት አድርገዋል።
በቴክኖሎጂ ፈጠራ ከፍተኛ እመርታ ካሳየችው አገር ከጃፓን የመጡት ክብረወርቅ አባተ የመተየቢያ መሣሪያን ለመጀመሪያ ጊዜ ሠርተው በዚህም ዕውቅና ለማግኘት የቻሉ አዲስ ቴክኖሎጂ ቅርብ የነበሩ ባለሙያ ነበሩ።
ጃፓን በነበሩበት ወቅት የኮምዩኒኬሽን ሥልጠና ወስደው ስለነበር አገር ቤት ሳሉም የወታደራዊ የኮምዪኒኬሽን መሣሪያዎች ብልሽት በሚያጋጥምበት ጊዜ መፍትሄ በመስጠት ይታወቃሉ። በአንድ ወቅትም አምባሳደር ካሣ ከበደ የኮምዩኒኬሽን መሣሪያ ብልሽት ባጋጠመ ጊዜ አቶ ክብረወርቅ እንዲገጥሙ ተጠይቀው ሙያዊ እገዛቸውን በመስጠታቸው ምስጋና ተችሯቸዋል።

በአንድነት አገርን ማሳደግና ትምህርት መማር ቀዳሚ ነገር እንደሆነ የሚያምኑት መሀንዲስ ክብረወርቅ አባተ ኢትዮጵያ አገራችን የብዙ ታሪክ ባለቤት መሆኗን በየጊዜው የሚናገሩ የአገር ባለውለታ አባት ነበሩ።

በደግነት እና ለሰው አሳቢ በመሆን በብዙዎች የሚመሰከርላቸው አቶ ክብረወርቅ አባተ ለልጆቻቸው መልካም አባት፣ ለእህት ለወንድሞቻቸው ጋሻ መከታ በመሆናቸው ምንጊዜም ሲከበሩና ሲታወሱ ይኖራሉ።

አቶ ክብረወርቅ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለረጅም አመታት ካገለገሉ በኋላ ወደ አሰብ ነዳጅ ማጣሪያ ድርጅት ሲያገለግሉ ቆይተው ጡረታ ከወጡ በኋላ፣ ወደ አሜሪካን አገር ከልጆቻቸው አጠገብ ለመሆን ሄደው እዛ ከኖሩ በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰው፣ ህዳር 5 ቀን በድንገት በደረሰባቸው ሕመም በ96 ዓመታቸው በሞት ተለይተዋል።

አቶ ክብረወርቅ አባተ 6 ልጆች አባት “ሁለት ሴቶችና የአራት ወንድ ልጆች አባትና ቸው። የ8 የልጅ ልጆች አያት በመሆን ተባርከዋል። የቀብር ሥነ ሥርዐታቸውም ማክሰኞ ህዳር 9 2018 በመንበረ ፀባዖት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ቤተሰብ፣ወዳጅ ዘመድ በተገኘበት ተፈፅሟል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *