ጋዜጠኛ እና የዜና አቅራቢ ንግሥት አባተ
ተወዳጅ ሚድያ ከተመልካች አእምሮ ያልጠፉ ፣ የሚድያ ሰብዕና የተላበሱ የቲቪና የሬድዮ ሰዎችን የሙያ ታሪክ ሲያስተዋውቅ እንደነበር አይዘነጋም። ይህ የሙያ ታሪክ ለመጪውም ሆነ ለአዲሱ ትውልድ የመረጃ ምንጭ ሆኖ በዘመን ተሻጋሪነት እንዲቀመጥ እያደረግን እንገኛለን። እስከዛሬ ከ400 በላይ ባለሙያዎችን የሰነድን ሲሆን ታሪኮቹም በዲጂታል ሚድያ፣ በመፅሐፍ ፣በትረካ እየቀረቡ ይገኛሉ።
እስከአሁን “መዝገበ አእምሮ” በተሰኙ ባለ 600 ገፅ 2 መፅሀፎች የሙያ ታሪኮቹ ተሰንደዋል። ሦስተኛው መፅሐፍም በመዘጋጀት ላይ ይገኛል። ሦስተኛው መፅሐፍ ላይ ታሪካቸው ከሚካተትላቸው የዜና አቅራቢዎች መሀል ንግሥት አባተ ትነሳለች። ንግሥት፣ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ለ 13 ዓመታት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዜና በማቅረብ ትታወቃለች። ከብዙዎቻችን አእምሮ ያልጠፋችው ንግሥት ከ1992 ዓ .ም ወደ አሜሪካ አቅንታ በአሜሪካ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያውያን ቴሌቪዥን ቶክ ሾው በፈረንጆቹ አቆጣጠር ጃንዋሪ 2006 ልክ የዛሬ 20 ዓመት ለመጀመር የቻለች ሲሆን ታላላቅ ሰዎችንም በማቅረብ ኮምዩኒቲዋን በማገልገል ሙያዊ ግዴታዋን ለመወጣት ችላለች። ንግስት በወቅቱ በብቸኝነት የጀመረችው ;ቶክ ሾው’ እስካሁን ሲታወስ ይኖራል።
የንግሥት አባተን ታሪክ ለመሥራት እንቅስቃሴ የጀመርነው የዛሬ 4 ዓመት አካባቢ ሲሆን እነሆ ንግሥትም ፈቃደኝነቷን ገልጻ ታሪኳን ለመሰነድ ችለናል። የንግሥት አባተን ታሪክ በቅርቡ እናስነብባለን ብለን ያወጣነውን promo (ማስተዋወቂያ ) ዲጂታል ሚድያ ላይ ብቻ ከ130,000 በላይ ዕይታ አግኝቷል። ይህም የዜና አቅራቢ እና ጋዜጠኛ ንግሥት አባተ ከተመልካቹ አእምሮ ውስጥ ዛሬም እንዳለች ያመለክታል ።የንግሥትን ታሪክ ዕዝራ እጅጉ እንደሚከተለው ሰንዶታል።
ልጅነት እና ትምህርት
በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ “ካዛንቺስ” በሚባለው አካባቢ የተወለደችው ንግሥት በልጅነቷ ተግባቢና ለትምህርት ትኩረት የምትሰጥ ልጅ ነበረች። አንድ ነገርን ለማወቅ የምትጓጓ የነበረችው ንግሥት በመጠየቅ ታምናለች።ነገሮች፣ ወግና ሥርዓታቸውን ጠብቀው እንዲከወኑም ትሻለች። አንደኛ ደረጃን በካቴድራል ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ ናዝሬት ትምህርት ቤት የተማረች ሲሆን በአሜሪካን አገር በመገናኛ ብዙሃን ዙሪያ የቴሌቭዥን ፕሮዳክሽን እና በማርኬቲንግ በርካታ ስልጠናዎችን ወስዳለች።የንግሥት ጠንካራ መሠረት ባለው የትምህርት ተቋም መማር ለቀጣይ ሕይወቷ ትልቅ እገዛ አድርጎላታል።
ወደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ)
ገና በወጣትነቷ የመገናኛ ብዙኃን ፍላጎት የነበራት ንግሥት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በዜና አቅራቢነት ወይም (News Anchor) በመሆን ተቀጥራ ወዲያውኑ በተመልካች ተአማኒነትን አግኝታለች። ከዜና አቅራቢነቷ ባሻገር “ዓለም በዚህ ሳምንት” የተሰኘውን የዜና መሰናዶ ወደ ተመልካች ስታደርስ ቆይታለች።
በወቅቱ በአንድ ጊዜ ንባብ 35 ብር ይከፈላት ነበር። በወር ወደ አስራ ሁለት ጊዜ ታቀርብ ስለነበርም በወር 420 ብር ገደማ ነበር። ቆየት ብሎ በአንድ የዜና ክፍለ ጊዜ 100 ብር ተደረገ። በወር እስከ 1000 ብር የምናገኝበት ጊዜም ነበር። ንግሥት በወቅቱ እንደነበሩት የሙያ ጓደኞቿ ሙያውን ለገንዘብ ሳይሆን በፍቅር በ (passion) ታከናውን ነበር። የዚያን ጊዜ የነበሩት ጋዜጠኞች የጋዜጠኝነት ሙያ “ journalism with its integrity “ ወይም ጋዜጠኝነት ከነሙሉ ክብሩ” የሚለውን በተግባር አሳይተዋል ትላለች። ይህ አስተያየት የአሁኑን ትውልድ ለማጣጣል ሳይሆን በዚያ ጊዜ የነበረውን የጋዜጠኝነት professionalism ለማድነቅ ብላ ነው። ጋዜጠኝነት የሙያ ብቃትን የሚጠይቅ ሙያ ነው ስትልም ትናገራለች ።
ንግሥትና የቋንቋ ክህሎት
ከመጽሐፍት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያላት ንግሥት ከምንም በላይ የታሪክ መፃህፍትን ማንበብ ያስደስታታል። ልብወለድ መፅሀፍት ታነባለች።የደራሲ በዓሉ ግርማ አድናቂ መሆኗንም አጫውታናለች።
ለዜና አቅራቢነቴ ካቴድራልና ናዝሬት ትምህርት ቤት ጥሩ የቋንቋ መሠረት ሰጥቶኛል ትላለች ንግሥት።
“…ብዙዎች እነዚህ ትምህርት ቤቶች እንግሊዝኛ ቋንቋ ላይ የሚያተኩሩ ይመስላቸዋል። አማርኛንም ሆነ ሌሎች ትምህርቶችን በደንብ ነው የሚያስተምሩት። ለምሳሌ ናዝሬት ት/ቤት የማስታውሰው አንድ አማርኛ አስተማሪያችን ብዙውን ነገር በተረትና ምሳሌ ነበር የሚያስረዱን ። ለመጥቀስ ይህል ስንረብሽ “በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ” ወይም ተማሪ ሲኮራረጅ ሲያዩ ” ነብር አየኝ በይ” እና የመሳሰሉትን ይሉ ነበር። ይህን የሚያደርጉት ተረትና ምሳሌን በምሳሌ አድርገው ማስተማራቸው ነው። ይህ ሰምና ወርቅ እና ተረትና ምሳሌን በደንብ እንድናውቅ ረድቶናል ። በአማርኛ ክፍለ-ጊዜ እንግሊዝኛ አንቀላቅልም። ለዚህም ነው የአሁኑ ጊዜ አገላለፆች (መኮመት, መፓሰት ወዘተ) የማይመቹኝ ። እኚሁ አስተማሪ ወደ ክፍል ሲመጡ ኩታ/ነጠላ ለብሰው ነበር የሚመጡት። ይህንንም የሚያደርጉት እኛን ባህል ለማስተማር ይመስለኛል ። ተማሪዎች “የኔታ” የሚል የቅፅል ስም እንዳወጣንላቸው አስታውሳለሁ” በማለት ንግሥት ወደ ኃላ መለስ ብላ ለባህል፣ለእሴት፣ ለቋንቋ መሠረት የሰጧትን ትምህርት ቤቶቿንና መምህሮቿን ታስታውሳለች።
ንግሥትና ሌሎች ዜና አንባቢዎች
ንግሥት ዜና ማንበብ በጀመረችበት ጊዜ አገራችን በርካታ ስመ -ጥር የሚድያ ሰዎች ነበሯት ።
በወቅቱ ከነበሩት ሙያ አጋሮቿ መካከል ከአማርኛ የዜና ክፍል ግዛው ዳኜ፣ሚሊዬን ተረፈ፣ዜናነህ መኮንን፣ ሰሎሞን አባተ፣ ኤልሳቤጥ ፈቃደ፣ፍሬህይወት በቃና : ይገኙበታል። ከእንግሊዝኛ ደግሞ በሁሉም ሰው ተወዳጅ የነበረው አቶ ልዑል ሰገድ ኩምሳ በኃላም ቤዛዊት አፈወርቅ ጥሩ እንግሊዘኛ አቅራቢዎች ነበሩ። ከእነዚህ ሁሉ ጋር የመሥራት ዕድል የገጠማት ንግሥት ያንን ዘመን እንዲህ ስትል ትገልፀዋለች። “….በዚያን ጊዜ የሚድያ ሰዎች ላይ ይስተዋል የነበረው ሥነ ሥርዐት፣ የሙያ ክብርና የአለባበስ ወግም ጭምር እንደ አርአያ የሚቆጠር ነው ። ትክክለኛ አለባበስ ተመልካችን ማክበር እንደሆነ ነበር የሚነገረን ። ሙያውን የማይመጥን አለባበስ ለብሶ የመጣ ጋዜጠኛ ካለ በዕለቱ በሌላ ሰው ይተካል። አንድ የማልረሳውን አጋጣሚ ልንገርህ ። አንድ ጊዜ ሠርግ ሄጄ ልብስ ለመቀየር ጊዜ ስላጣሁ ተረኛ ስለነበርኩ በዚያው ሥራ ገባሁ። የለበስኩት ልብስ ያን ያህል ከመስመር ባይወጣም: ትንሽ ከተለመደው አለባበሴ የተለየ ነበር ። ታዲያ አንብቤ እንደጨረስኩ አለቃዬ ከቤቱ ይመለከት ስለነበር እንደጨረስኩ ደውሎ ስለ አለባበሴ ትንሽ ገስፆኝ ነበር። ይህ የሚያመለክተው ሙያው ምን ያህል ክብር እንደነበረው ነው። ከአለባበስ ጭምር!!
የያኔው ትዝታ ዛሬም ከህሊናዬ አልጠፋም….” ትላለች ንግሥት።
ንግሥት እንደምታስታውሰው ትምህርት ቤት የክርክር ክፍለ ጊዜ እና የንባብ ክፍለ ጊዜም ነበራቸው ።እነዚህ ሁሉ ለሚዲያ ሥራው ትልቅ መሠረት ሆነዋታል።
“ሚሊዬን ተረፈን አደንቃታለሁ። አብሬው ባልሠራም ጌታቸው ኃ/ማርያምን አደንቀዋለሁ።አሁን CNN ላይ ካሉት የሚተናነሱ አልነበሩም ።በአጠቃላይ እኛ በነበርንበት ጊዜ የነበሩት ጋዜጠኞች የጋዜጠኛነትን ሥራ የሚሠሩት ከነሙሉ ክብሩ ነበር ። ያውም በትንሽ ክፍያ።ከእነርሱ ብዙ ተምሬያለሁ።” በማለት ንግሥት የቀድሞ የሚድያ ሰዎች መመስገን እንዳለባቸው አጠንክራ ትናገራለች።
ቶክ ሾው በምድረ አሜሪካ
ንግሥት የዛሬ 26 ዓመት ጓዟን ጠቅልላ አሜሪካ ከገባች በኃላ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያውያን ቶክ ሾው “ The Ethiopian Talk Show “ በሚል ስያሜ ልክ የዛሬ 20 አመት ( January,2006) በዋሺንግተን ዲሲና እና አካባቢው በመጀመሯ እጅግ ኩራት ይሰማታል። በጣም አድካሚ ሥራ እንደነበር የገለፀችው ንግስት አሁን ላይ ስታስበው ህብረተሰቡን ማገልገሏ እና የአገሯን ባህል ለሌሎች ማስተዋወቋ ደስታን ፈጥሮላታል። ይህን ቶክ ሾው ስታዘጋጅ ከፕሮግራሙ የምታገኘው የገንዘብ ጥቅም አልነበረም። ይልቁንም ከራሷ ኪስ እየደጎመች ፕሮግራሙን ለ5 ዓመታት እንዲቀጥል አድርጋለች።
‘የኢትዮጵያውያን ቶክ ሾው’ The Ethiopian Talk show በዋሽንግተን ዲሲ እጅግ ተፅእኖ ፈጣሪ የሆነ በንግሥት አባተ የሚመራ ፕሮግራም ነበር። ይህ ‘ቶክ ሾው’ በልዩ ልዩ ሙያ ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ያስተናገደ ሲሆን ጥሩ ተመልካቾችንም ለማፍራት የቻለ ነበር።
የተለያዩ ባለሙያዎችንና የህብረተሰቡን ክፍል በመጋበዝ በተለያዩ ርእሶች ላይ ለመወያየት በቶክ ሾው መድረኳ አቅርባለች: ለመጥቀስ ያህል የኢትዮጵያ ኩራት የነበረው የሙዚቃው ንጉስ ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰ አለማየሁ እሸቴ ንዋይ ደበበ ዓለምፀሃይ ወዳጆ ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው።
በተጨማሪ ፣በአሜሪካ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ኢትዮጵያውያን ወጣቱን ትውልድ እንዲያበረታቱ ለስኬታቸው መብቃት ያሳለፉትን እንዲያካፍሉ በፕሮግራሟ ላይ ትጋብዝ ነበር። ለመጥቀስ ያህል የናሳው የጠፈር ባለሙያ ዶ/ር ብሩክ፣ የወርልድ ስፔስ ኩባንያ መሥራች አቶ ኖህ ሳማራና የሥነልቦና ባለሙያው ዶ/ር ክንፈ ሚካኤል ካሳዬ ፣ ዘመናዊ ህክምናን በአገራችን በማስፋፋት ጉልህ አስተዋፅዖ ያደረገው ዶ/ር አከዛ ጣዕመና ሌሎችም ብዙ ባለሙያዎች ቀርበዋል። በነገራችን ላይ ዶ/ር አከዛ
“ዘመናዊ ህክምናን በአገራችን በማስፋፋት ጉልህ አስተዋፅዖ ያደረገው እና የአሜሪካ ሜዲካል ሴንተር መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነው።
በአጠቃላይ በፕሮግራሙ ላይ የህግ የህክምና ባለሙያዎች ፣ የሥነ -ልቦና ተመራማሪዎች፣ የጥበብ ሰዎች፣ ለወጣቱ ትውልድ አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ስኬታማ ኢትዮጵያዊያን እና ከኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ጋር ትስስር ያላቸው እንግዶችን በፕሮግራሟ ላይ ታቀርብ ነበር።
ንግሥት 20 ዓመት ወደ ኃላ ተጉዛ እነዚህን ስታስብ ኩራትና ደስታ ይሰማታል።
በተለይ፣ በጊዜው የማህበራዊ ሚድያ ሰፊ ባልነበረበት ጊዜ ንግሥት በቴሌቪዥን መስኮትና እና በውስን ማህበራዊ ሚዲያ ፕሮግራሙን አየር ላይ እያዋለች ተመልካችን ለማሳወቅ ጥረት አድርጋለች።
ንግስት ቶክ ሾ መጀመርን እንዴት አሰበችው?
“…እንደመጣሁ ቴሌቪዥን እከታተል ነበር። በዚያን ጊዜ የኦፕራ ሾው በብዙዎች የሚወደድ ታዋቂ ፕሮግራም ነበር። የስፓኒሽ ኮምዩኒቲም ብዙ የቶክ ሾው ፕሮግራሞች አየር ላይ ያውሉ ነበር። አሜሪካን ሀገር የምንኖር ኢትዮጵያውያን ቁጥራችን ቢበዛም የራሳችን የቴሌቪዥን መድረክ አለመኖሩ ይቆጨኝ ነበር። በደንብ ካሰብኩበት በኃላ ለምን እኔ አልጀምረውም? በማለት ሥራውን ለመሥራት ተነሣሁ።ይህ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2006 ነበር ።ቀላል አልነበረም። የሶሻል ሚዲያ እገዛ ውስን ነበር ።አሁን ሳስበው ጥንካሬዬ ይገርመኛል:: ታዲያ ፕሮግራሙ ባጭር ጊዜ በጣም ተወዳጅነትን አገኘ። ያም ለእኔ ጥሩ ሞራል ሰጠኝ። በ passion (በፍቅር) ነበር የምሠራው። ፕሮግራሜን ለማስተላለፍ ለቴሌቪዥን ጣቢያ የሚከፈለው ክፍያ አቅምን እጅግ የሚፈታተን ነበር። በእርግጥ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የመሣሠሉ ትልልቅ ድርጅቶች አልፎ አልፎ ፕሮግራሜን ለመደገፍ ስፓንሰር ያደርጉልኝ ነበር። ለዚህም አመሰግናለሁ።
በወቅቱ ማህበራዊ ሚዲያ ሰፊ ስላልነበረ ስርጭቱ በቴሌቪዥንና በውስን ማህበራዊ ገፅ ላይ ነበር።
እንደዚያም ሆኖ ባጭር ጊዜ ታዋቂና ግሩም እንግዶች የሚቀርቡበት መድረክ መሆን ጀመረ። ” በማለት ስለቶክ ሾው አጀማመሯ ነግራናለች።
አንዳንድ ጥያቄ ለንግሥት
ከመጻፍ እና ከማንበብ የቱ ይመችሻል? የሚል ጥያቄ ለንግሥት አቅርቤላት ነበር፦
“…ቋንቋ ይሆነኛል ።በአማርኛም በእንግሊዘኛም መፃፍና ማንበብን እኩል የማስኬዳቸው ይመስለኛል። ትርጉም በጣም ይቀለኛል።ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ወይም ከአማርኛ ወደ እንግሊዘኛ ምንም ትርጉሙን ሳይለቅ ለሚዲያ በሚመጥን በደንብ ተርጉሜ እፅፋለሁ” ብላናለች።
ንግሥት እስከዛሬ ኢቲቪ ካነበበቻቸው ዜናዎች ፣ ያሳቃት ያሳዘናት እና ያስደነገጣት የቱ እንደሆነ ጠይቄያት ነበር።
“በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጠቅላላ የሠራሁት 13 ዓመት ሲሆን በደርግ ጊዜ 3 ዓመት ነው የሠራሁት። በደርግ ጊዜ የኮሎኔል መንግስቱን ዜና ስናነብ በክብርና በጥንቃቄ ነበር ። ባጋጣሚ ከአገር በወጡ ቀን እኔ ተረኛ ነበርኩ። ኮ/ል መንግስቱ ከአገር ፈረጠጡ ብዬ ሳነብ አስደንጋጭ ነበር።
ንግሥት አሁን ምን እየሠራች ነው?
ንግሥት በአሁኑ ሰዓት Donohoe Hospitality በሚል የሆቴል ማኔጅመንት ስር ለማርዬት ሆቴል የሽያጭና የማርኬቲንግ ዳይሬክተር በመሆን ታገለግላለች።
ንግሥት በባህሪይ ቁጡ ሳትሆን በጣም ግልፅ ናት። የሚመስላትን ነገር ፊት ለፊት ትናገራለች ።ይህንን ስታደርግም ሰውን እያከበረች ነው።
ሥራ ፈጥኖ የመሥራት ባህሪይም አላት። ሰው ሥራዋን ካዘገየባት ወይም በመንገዷ ላይ ከቆመ ዝም አትልም ሥራን ለማፍጠን ስትሞክር በሰዎች ዘንድ የተቆጣች ልትመስል ትችላለች። ትኩረቷ ሥራዋና ሥራዋ ላይ ብቻ ነው።
ንግሥት እንደገና
ንግሥት የዛሬ 20 ዓመት ጀምራው የነበረውን ሾው ዳግም ለመጀመር ህልም ሰንቃለች፦
“… ከሁሉም የህብረተሰቡ ክፍሎች ታላላቅ እንግዶችን አቅርቤ ስለነበር በህይወት የሌሉትን ቀድሞ የተደረገውን ኢንተርቪው እንደገና ማስተላለፍ ህዝቡን እንደሚያስደስተው አልጠራጠርም። ብዙ የተደከመባቸው ፕሮግራሞች ነበሩ:: አንዳንዶቹን ቃለ -መጠይቆች እኔ ራሴ እንደ አዲስ ሳያቸው ያስደስቱኛል ።
በተጨማሪ ብዙ ፕሮግራሜን ይከታተሉ የነበሩ ሰዎች እንደገና እንድጀምር በተደጋጋሚ ጠይቀውኛል ።ራሴን ማድነቅ አይሁንብኝና ግሩም ሥራዎች ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪም
በህይወት ያሉትን “where are they now” ወይም “የት ደረሱ?” ብዬ እንደገና ለማቅረብ እቅድ አለኝ።
ሌሎች ስለ ንግሥት ምን አሉ?
ንግሥት ከዛሬ 20 ዓመት ቀደም ብሎ ታቀርባቸው የነበሩት መሰናዶዎች ብዙ መልሶችንም ያስተናገዱ ነበሩ። ቃለ- ምልልስ የምታደርጋቸውም እንግዶች በኢሜይል የአድናቆት ቃላትን ይሰነዝሩላት ነበር።
የተወሰኑትን በከፊል እናቅርብ።
ሰላም ንግሥት፣ ከፕሮፌሰር ለማ ሰንበት ጋር ያደረግሽውን ቆይታ ተመለከትኩት። መረጃ ሰጪ እና ጥሩ ሆኖም አግኝቼዋለሁ። ተመልካቾች ብዙ ቁምነገር እንደቃረሙ አልጠረጥርም።የሜሪ ላንድ ዩኒቨርሲቲ 3ኛ ዓመት ተማሪ የሆነ የቅርብ ዘመዴ በፕሮግራምሽ ደስ መሰኘቱን እና ቁምነገር መቃረሙን አጫውቶኛል።
በጥሩ ሥራሽ እንድትቀጥይ መልካም ምኞቴ ነው።
ዶክተር ምሥራቅ ገዝሙ የሂሣብና የስታትስቲክስ ባለሙያ
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከቴአትር ዲፓርትመንት የተመረቀውና በ120 ፕሮግራም ከአድማስ ባሻገር ፕሮግራም አዘጋጅ የነበረው ግርማ ደገፋ ንግሥት ፕሮግራሟን የጀመረች ሰሞን በኢሜል አንድ መልዕክት አድርሷት ነበር። እንዲህ የሚል፦
“ሰላም ንግሥት እንኳን ደስ ያለሽ። ትክክለኛ የቲቪ ሾው ይዘሽ በመቅረብሽ ልትመሰገኚ ይገባል እላለሁ። ለዓይናችን ምግብ ሊሆን የሚችል መሰናዶ እያቀረብሽ መሆኑን መመስከር እወዳለሁ። ድንቅ ሥራ” በማለት ግርማ አድናቆቱን ገልፆ ነበር።
ፕሮፌሰር ለማ ወልደ ሰንበት ደግሞ
“..ፕሮፌሽናል ቃለ-መጠይቅ በማድረግሽ የተሰማኝን ታላቅ ደስታ ልገልፅ እወዳለሁ ። በአንቺ ኢንተርቪው በመደረጌም የተሰማኝ ደስታ ትልቅ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መናገር እፈልጋለሁ ።” ” ብለዋል።
በፌስቱላ ሆስፒታል የምትሠራው ፀዳለ አሰፋ ደግሞ፦” እጅግ የተወደደ ፕሮግራም አየር ላይ በማዋልሽ ላመሰግንሽ እፈልጋለሁ ።” በማለት ግብረ- መልስ ሰጥታ ነበር።
ወርቁ የተባሉ ተመልካች ደግሞ ” ልጄ ያንቺን ፕሮግራም መከታተል ከጀመረች ወዲህ የአማርኛ የንግግር ክህሎቷን አዳብራለች” በማለት ሀሣብ ሰጥቶ ነበር።
ሰሎሜ ታደሰ ስለ ንግሥት
በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ የምትገኘው የኢቲቪ ኃላፊና የመንግስት ቃል አቀባይ የነበረችው ሰሎሜ ታደሰ ስለ ንግሥት አባተ ያጫወተችን ነበር፦
እኔና ንግሥት አብረን ነው ያደግነው። በልጅነቷ ብሩህ አእምሮ ያላት ልጅ ነበረች። አሜሪካ ሳለች የጀመረችው ቶክ ሾው ከባድ ሥራ ነበር። ረጅም ዓመት ቆይታበታለች ። ምንም ዓይነት ‘ቶክ ሾው’ ባልነበረበት የንግሥት ሾው ትልቅ ማህበራዊ ኃላፊነቱን የተወጣ ይመስለኛል።
ፕሮግራሙ እዚህ ለሚያድጉ ልጆች ጥሩ አስተዋፅዖ ያደርጋል። የምታነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች ወሳኝና መሠረታዊ ናቸው። መተንፈሻ ፕሮግራም እንደማለት ነው።
ንግሥት ጥንቅቅ ያለ የአማርኛ ዕውቀት ነው ያላት። መሳቅ ትወዳለች። ሁለገብ ናት። passion and professional የሙያ መሠጠት እና ባለሙያነት ሲገጣጠሙ ንግሥት ጋር አሉ።
ንግሥት ከዚህም በላይ የመሥራት አቅም ያላት ባለሙያ ናት።በዕውቀት ስለምትሠራም በተመልካች ከበሬታን ማትረፍ ቻለች።
ለንግሥት መልካሙን ተመኘን። እናከብርሻለን።