ተፈራ ወርቁ

ተፈራ ወርቁ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ተፈራ ወርቁ ይገኝበታል፡፡ ተፈራ ቴአትርን ለማሳደግ ብዙ የለፋ ነው፡፡ ዝንባሌ ያላቸውን ከማሰልጠን አንስቶ ቴአትርን በኢንተርፕራይዝ ደረጃ በግል ተቋም ይዞ በማሳደግ ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ እንደ ፕሮዲዩሰር በመሆንም በርካታ ቴአትሮች ከመድረክ ከወረዱም በኋላ ዳግም ለእይታ እንዲበቁ አድርጓል፡፡ በዚህ ልዩ አስተዋጽኦው ምክንያት ለአዲሱ ትውልድ የሚያስተምረው ነገር አይጠፋም በሚል የህይወት ታሪኩን እንደሚከተለው ሰንደነዋል፡፡ አይናለም ሀድራ እና እዝራ እጅጉ ታሪኩን አጠናክረውታል፡፡

ትውልድና እድገት

ላለፉት 25 አመታት በቲያትርና በሙዚቃ ኢንደስትሪው ታላቅ አበርክቶ ያለው ተስፋ ኢንተርፕራይዝ መስራችና ባለቤት ነው ተፈራ ወርቁ። ተፈራ በ1969 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ አፍንጮ በር በመባል በሚጠራው አካባቢ ነው ። 1ኛ ደረጃ ትምህርቱን ፒያሳ አካባቢ በሚገኘው አፍሪካ አንድነት ትምህርት ቤት ፤ 2ኛ ደረጃን ደግሞ በዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማረው። ከኪነ- ጥበብ ጋር የተቆራኘው ገና ከብላቴናነቱ ጀምሮ መሆኑን ታሪኩ ያስረዳል።ታዋቂው አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ መንገሻ የስጋ ዘመዱ በመሆኑ ከእርሱ ወንድሞች ጋር በመሆን ስራውን ሲያይ አድጓል።የጥላሁን ቀንደኛ አድናቂም ነው።ጥላሁን ቲያትር ሰራ ተብሎ እነ ተፈራ አምልጧቸው አያውቅም። ከዚያ ባለፈም እነ ልመንህ፣ አለባቸውና የዘመኑ የጥበብ ፈርጦችን የማየት ዕድሉም ነበረው።ይሄ ሁሉ ተደማምሮ ለኪነ-ጥበብ ቅርብ አድርጎታል። በትምህርት ቤት ልዩ ዝግጅቶች ሲኖሩም መድረክ ለመምራትና ጭውውቶችን ለማቅረብ ድፍረቱም ብቃቱም ነበረው።

የቲያትር ጅማሮ

2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገባ ደግሞ ጅምሩ ከፍ አለ።በዘመኑ ዳግማዊ ሚኒልክ ትምህርት ቤት ጠንካራ የሚባል እነ ሃረገወይን አሰፋን፣ ተስፋዬ ሃይሌንና ሌሎችን ያፈራ የድራማ ክበብ እንዲሁም የተደራጀ የሙዚቃ ባንድም ነበረውና ተፈራ የድራማ ክበቡ አባል ሆነ።ክበቡ ለአባል ተማሪዎች የሚሆን ስልጠና ጠዋት ጠዋት ይሰጥ ነበር። ተፈራ ደግሞ የሳይንስ ተማሪ መሆን ይፈልግ ነበር።ምርጫውን ከጠበቀ የጠዋት ፈረቃ ይሆናል፡፡ ስልጠናውም ሊያመልጠው ሆነ። እናም መወሰን ነበረበትና ትምህርቱን ከሳይንስ ወደ አርት ቀይሮ ፈረቃው የከሰአት እንዲሆን አደረገ፡፡ (በጊዜው ትምህርት በፈረቃ ነበርና የተፈጥሮ ሳይንስ የመረጡ በጠዋት ክፍለጊዜ፤አርቶች ደግሞ በከሰዓት ክፍለ ጊዜ ይማራሉ)። ታዲያ ተፈራ ለጥበብ ይገባታል ያለውን ዋጋ ከፍሎ ትምህርቱን እየተማረ ስልጠናውን ተከታተለ። በክበቡ ከተፈራ ጋር ተሻለ ወርቁ፣ ዳንኤል ብርሃኑና ሌሎችም ነበሩ።

ተፈራ 9ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ለኪነ-ጥበብ የነበረውን ፍቅር ያየ የቤተሰቡ የቅርብ ሰው ገድሉ አሰግደው ክቡር ዶክተር ተስፋዬ አበበ ጋር ይዞት ሄደ።40 ተማሪዎች ለስልጠናው ተፈትነው ተፈራና ሰብለ ተፈራ ብቻ አለፉ።

በስልጠናው ወቅት የተስፋዬ አበበ ስራ በሆነው ‹‹ህይወት በየፈርጁ ››ቲያትር ላይ ተውኗል። ተፈራ መደበኛ ትምህርቱን እየተማረ ቲያትሩን ገፋበት።ቀጥሎም ተስፋዮ ሲማ ጋር በመሄድ ተጨማሪ የቲያትር ስልጠና ከነሽመልስ አበራና አለልኝ መኳንንት ጋር ወሰደ። “ተስፋዬ ሲማ ቲያትርን እንድወድ ሙያውን የሙጥኝ እንድል አድርጎኛል። ሙያው የሚጠይቀውን ከሱስ የጸዳ ስብዕና እንድላበስ አድርጎኛል” ይላል ተፈራ ስለ ስልጠና ቆይታው ሲናገር።ከ6 ወራት ስልጠና በኋላም እናት አለም ጠኑ ላይ ተውኗል፡፡ እንደ መመረቂያ ስራ።

ፋቡላ የቲያትር ክበብ

ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ እነ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ አባል የነበሩበትን ፋቡላ የቲያትር ክበብን መሰረተ። ክበቡ የቀበሌ አዳራሾችን ለልምምድ ለስብሰባ በመጠቀም ባገኘውአጋጣሚ ሁሉ ቲያትር ያሳያል፡፡ የሙዚቃ ዝግጅቶችንም ያቀርብ ነበር። እነ ማስረሻ ገብረማሪያም፣ ሸዋፈራው ደሳለኝ፣ ተሻለ ወርቁ፣ቴዎድሮስ ለገሰ፣ ሄኖክ ብርሃኑ፣ ቅድስት ገብረስላሴንና ሌሎችን በክበቡ ሰብስቦ አስተምሯል።

በዘመኑ በቲያትርና በሙዚቃው አለም ክበባት ትልቅ ሚና ነበራቸው።የኢትዮጲያ ቲያትርና ፊልም ላይ ለውጥ ያመጡ አንቱ የተባሉ ባለሙያዎችን አፍርተዋል።ፋቡላም የዚህ ታሪክ አካል ሆኖ ቆይቷል። ፋቡላ ወደ 5 አመታት ገደማ ከቆየ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶቸ መመናመን ሲጀምር ተፈራ ገና ከመነሻው እጁን ይዞ ቲያትር ያስጀመረውን ባለውለታውን ገድሉ አሰግደውን ለማሰብ ፋቡላን ወደ ገድሉ አሰግደው ቀይሮ ክበቡን አጠናክሮ ለ2 አመታት ቆየ።

ተስፋ ኢንተርፕራይዝ

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንደጨረሰ በ1990 ዓ.ም ተስፋ ኢንተርፕራይዝን ደግሞ መሰረተ።እነ ተፈራ በክበባት ቆይታቸው ጎልቶ ይታይ የነበረው የጥበብ ፍቅር እንጂ የጥቅም መሻት አልነበረምና ብዙ እንግልት፣ ረሃብ፣ ጥም፣ የስልጠናና የልምምድ ቦታ መቸገርንና ሌሎች ተግዳሮቶችን ያስተናግዱ ነበር። በመሆኑም ይህንን መሰል ችግሮችን ለመቅረፍና ተገቢውን ገቢ ሊያገኝበት የሚችልበትንና የጥበብ ፍላጎቱን ለማርካት ተስፋ ኢንተርፕራይዝን መሰረተ።

ያን ጊዜ የጥላሁን ጉግሳ አለሙ ሳላይሽ የስነ-ጥበባትና የማስታወቂያ ኢንተርፕራይዝ ስራ ጀምሮ ነበርና ቀርቦ ስራቸውን አየ፡፡ ከእነሱም ትምህርት ወስዶ ስራውን ጀመረ። ተስፋ ኢንተርፕራይዝ በ25 አመታት ውስጥ ከ20 በላይ ቲያትሮችን ፕሮዲውስ አድርጓል፤ በርካታ የሙዚቃ ኮንሰርቶችንም አዘጋጅቷል፤ የማለዳ ጤዛና የሞገዱ ዋናተኞች የተሰኙ የቴሌቪዥን ድራማዎችን ፕሮዲውስ አድርጓል። እንደ ሙያተኛ በግሉ ደግሞ ሰዓት እላፊ፣ ሰማያዊ ዓይን፣ ሩብ ጉዳይ፣ ነቃሽና አሁን በመታየት ላይ ያለውን የለሊት ሙሽሮች የተሰኘውን የውድነህ ክፍሌን ቲያትር ፕሮዲውስ አድርጓል።

ሱራፌል ጋሻው አዘጋጅቶት ለእይታ በቅቶ የነበረው ነቃሽ ቲያትር ለመጀመሪያ ጊዜ በተስፋ ኢንተርፕራይዝ አማካኝነት እንደገና አልአዛር ሳሙኤል እንዲያዘጋጀው ተደርጎ በመላው ኢትዮጲያ በአስመራም ጭምር እንዲታይ ተደረገ፡፡ይህም የተስፋ ኢንተርፕራይዝ የመጀመሪያ የቲያትር ስራ ሆኖ ተመዝግቧል።

ኢንተርፕራይዙ ተወዳጅ ቲያትር ሆኖ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ከመድረክ የወረደ ቲያትርን በመውሰድ እንደ አዲስ አዘጋጅቶ የማሳየት ስራን ሲሰራ ቆይቷል። ፍርሃትና የአለማየሁ ታደሰ ሚስጥረኞቹ ዳግም ለዕይታ ካበቃቸው ውስጥ ይገኛሉ።

ከሙዚቃ አንጻርም በ1990 ዓ.ም አክሱማዊት ባንድን ይዞ እነ አረጋኸኝ ወራሽን፣ ቴዎድሮስ ካሳሁንንና ፍቅርአዲስ ነቃጥበብን በማሳተፍ ለመጀመሪያ ጊዜ “አካባቢ የሙዚቃ ፌስቲቫልን ”በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ልደት አዳራሽ አቅርቧል።ከዛ በኋላም በርካታ ኮንሰርቶችን ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰን ጨምሮ ከሌሎች ከትልልቅ ባለሙያዎች ጋር ማዘጋጀት ችሏል።ትንሳኤ በረከት፣ በረከተ ገና፣ ናፍቆት የተሰኙና ሌሎች ኮንሰርቶችን ለታዳሚ አቅርቧል።

ተስፋ ኢንተርፕራይዝ በመስኩ ያለው ውጣ ውረድ ከባድ ቢሆንም ቲያትርን ለ25 አመታት የሙጥኝ ብሎ የዘለቀ ነው ብዙ ባለሙያዎችም ፈርተውበታል። በ2016 ዓ.ም ከወርሃ መስከረም ጀምሮም 25ተኛ አመቱን በድምቀት ለማክበር ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው። ተፈራ ወርቁ እንደሚለው ኢንተርፕራይዙ የራሱ የቲያትር አዳራሽ እንዲኖረው ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ የማስፋፊያ ስራዎች ይሰራሉ።

በሌላ በኩል ተፈራ ወርቁ ከሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን የበጎ አድራጎት ስራዎችን በመስራትም ይታወቃል።በደስታም በሃዘንም ለወገኑ ለጓዶቹ ደራሽ እንደሆነ ይነገራል።የታመሙ አሊያም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያሉትን ለመርዳት ዝግጅቶችን በማቅረብ ገቢ ያሰባስባል ድጋፍ ያደርጋል።

በተጨማሪም ቲያትሮች ቶሎ ቶሎ ስለማይመረቱ ሽልማቱን አመታዊ ማድረግ ባይቻልም ከዚህ ቀደም ተስፋ አዋርድ በሚል የቲያትር አዋርድም አስጀምሯል። ተፈራ ወርቁ በርካቶችን ሸልሟል አሸልሟል፡፡ አሁን ደግሞ እሱም በተራው አበርክቶው አፍ አውጥቶ ተናግሮለት ታሪክ እንዲህ ሸልሞታል።

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ የቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ተፈራ ወርቁ ቴአትርን ለማሳደግ 25 አመት ብዙ ሲደክም ኖሮአል፡፡ ቴአትር በቀዘቀዘበት ሰአት ተፈራ ኢንተርፕራይዙን በማጠንከር ሙያውን ታድጓል፡፡ ከዚህ በላይ ትልቅ አሻራ ከወደየት ይገኛል? ደግሞም ለሙያው ቅድሚያ የሚሰጥ ተቆርቋሪ እንዴት አይጻፍለትም? የእኛ አላማ እንዲህ አይነት ዝምተኛ ጀግኖችን ማውጣት ነው፡፡ መሸለም፤ መታወቅና መከበር ካለባቸው ወደ ኋላ የሰሩት ስራ በወጉ ታይቶ መሆን አለበት፡፡ እኛ ሰዎችን የምንመዝነው በዘመናቸው ምን ሰሩ የሚለውን በማጤን ነው፡፡ ተፈራ ደግሞ ብዙዎች በጓዳ የሚያደንቁት ብዙም የህይወት ታሪኩ የተጻፈለት ሰው አልመሰለንም፡፡ እኛ ግን አጥኚ ቡድኖችን በማሰማራት የተፈራ ሚና ትልቅ እንደነበር ማስተዋል ችለናል፡፡ መዝገበ-አእምሮ የሰሩ ሰዎች ዝርዝር የሚቀርብበት ታሪካዊ ሰነድ ከእነዚህ አንዱ ደግሞ ተፈራ ነው፡፡ እናም በጥረቱ እንዲቀጥል በማሰብ ታሪኩን ሰንደናል፡፡