ተክለሚካኤል አበበ

 

ተወዳጅ ሚድያ ላልተነገረላቸው ልዩ ክብር አለው።ታሪካቸውን ከመሰነድ ባለፋ ልዩ ቀናቸውን እያሰብ ማስታወሻ ያዘጋጃል። አሁን ታሪኩን የምናቀርብለት ሰው በአንድ በኩል የህግ ባለሙያ በሌላ የሥነ ፅሑፍ ፍቅር ያሳደረ ነው።

ደግነት መለያው ሲሆን በነፃ የህግ የምክር አገልግሎት የሰጣቸው ለዚህ ቀዳሚ ምስክር ናቸው። ሀሣቡን በነፃነት ከመግለፅ ባለፈ ኢትዮጵያን ይወዳል። ከዛሬ 25 አመት ቀደም ብሎ በስደት ከአገሩ ቢወጣም ዛሬም ኢትዮጵያ ውስጤ ነች ይላል። ተክለሚካኤል አበበ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት መሪ ሆኖ አካዳሚክ ነፃነት ይስፈን በማለቱ ብዙ ጫና ደርሶበታል። ጫናው ሲበዛበት እናቱ አገሩን ለቆ ኬንያ በስደት አቀና። ከዚያም ከአመታት ቆይታ በኃላ ካናዳ ገባ። ያቋረጠውን የህግ ትምህርት ቀጥሎ ዛሬ አንቱ የተባለ የህግ አማካሪ ሆኖ ደስ ብሎት በካናዳ እየኖረ ነው። ተክሌ የካናዳ ምድርን ከረገጠ ዛሬ ሚያዝያ 18 2018 21 አመት ሞላው። ሰው ልደቱን ብቻ ሳይሆን በህይወቱ ላይ መልካም አጋጣሚ ያገኘበትንም ቀን ማሰብ አለበት ብለን እናስባለን። ተክሌም የካናዳ ምድርን የረገጠበትን 21ኛ ዓመት አስመልክቶ የህይወት ታሪኩን ልናስነብብ እነሆ ብለናል። ይህ የማስታወሻ የባለታሪኩን ይሁንታ ያገኘ፣ የቅርብ ሰዎቹ ምስክርነት የተካተተበት በ2500 ቃላት ወይም በ10 ገፅ የተሰናዳ ፅሁፍ ነው። ይህንን ፅሑፍ ዕዝራ እጅጉ እና አይናለም ሀድራ እንደሚከተለው አጠናክረውታል።

#ውልደት፣እድገትና ትምህርት

ተክለሚካኤል አበበ ሳህለማርያም በልጅነት ስሙ: ‘ታገል’በአጭሩ ደግሞ ተክሌ: በሐምሌ: 1969 ዓ.ም በነገሌ ቦረና ነው የተወለደው። ከቡልጋው ሰው ከሃምሳ አለቃ አበበ ሳህለማርያም እና ከወለዬይቱ እናቱ ወይዘሮ ሰብለ ለምለም፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እስከ 5ኛ ክፍል በነገሌ ቦረና ሾላ ትምህርት ቤት ተምሯል። አባቱ ሀምሳ አለቃ አበበ ከ32 ዓመት የጦር ሠራዊት አገልግሎት በኃላ በጡረታ ሲሰናበቱ ቤተሰባቸው በነሐሴ 1981 ወደ ነገሌ አርሲ ተዛወረ። እዚያም ከስድስተኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 10ኛ ክፍል ተማረ፡፡ አስራ አንደኛ ክፍልን ቀጨኔ አጎቱ ጋር ተቀምጦ አዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ተምሯል። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታው ገፋ ያለ የመብት ጥያቄ በማንሳት ይታወቅ ነበር፡፡ በየትኛውም ሁኔታ የተማሪዎችን ጥያቄ በማንሳት ከመከራከር ወደ ኋላ ባለማለቱም ስሙ ይነሳል፡፡

11ኛ ክፍልን በድጋሚ በአዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ካጠናቀቀ በኋላ በ1989 ዓ.ም ወደ ነጌሌ አርሲ ተመልሶ በመማር የ12ኛ ደረጃ መልቀቂያን ወሰደ፡፡

በ1988 ዓ.ም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እያለም ከነ ሁሴን ከድር ፣በሀይሉ ገብረ እግዚአብሔር ፣አበበ ቶላ ፍቅርተ ካሕሳይ፣ ሌሎችም ወጣቶች ጋር በመሆን “ሐመረ ኪነ የሥነ-ጽሁፍ ማህበርን” አቋቁመው ተሳትፎም ያደርግ ነበር።

በመንፈሳዊ አገልግሎቱም በሐምሌ ቅዱስ ገብርኤል
በ1983 ዓ.ም ከወቅቱ የዝዋይ ሐ/ብርሀን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ዲቁና ወሰደ፡፡ ከዚያ በኋላ ለ7 ዓመታት ገደማ በቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በነገሌ መድሃኒዓለም እና በቀርሳ ኢላላ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ቀድሷል።እንደውም የቀርሳ ኢላላ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን መስራችና የመጀመሪያ ሰሞንኛ ዲያቆን ሆኖ በ15 ብር ደመወዝ አገልግሏል።

ከፍተኛ ትምህርት እና ስደት

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተና ማትሪክ አምስት “A” (5A) በማምጣት በ1990 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀላቀለ፡፡ በ1991 ዓ.ም በ2ተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታው የህግ ትምህርት (Law School) ክፍል ገባ፡፡ ከአንድ አመት በኋላ የሕግ ሁለተኛ: የዪኒሸርሲቲው 3ኛ ዓመት ተማሪ እያለ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ሆኖ ተመርጦ በተቋሙ ማገልገል ጀመረ። በሚያዚያ 1993 ዓ.ም በነበረው ረብሻ ምክንያት ወደ ኬንያ ተሰደደ፡፡ በዚያ ለ4 ዓመታት ቆይቶ በሚያዚያ 1997 ወደ ካናዳ አቀና፡፡

በካናዳ ትምህርቱን በላንጌራ college ቀጥሎ በRoyal Roads University የመጀመሪያ ዲግሪ በ Bachelor of Arts in Justice Studies እንዲሁም University of British Columbia በ2010 እ.ኤ.አ የህግ ትምህርቱን በJ.D. አጠናቋል። በ University of Ottawa ደግሞ በማስተርስ ዲግሪ በ International Humanitarian Law (Law of Armed Conflicts) ተመርቋል።

የትምህርት ጉዞ እና ተግዳሮት

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታው ገፋ ያለ የመብት ጥያቄ በማንሳት ይታወቅ ነበር፡፡ በየትኛውም ሁኔታ የተማሪዎችን ጥያቄ በማንሳት ከመከራከር ወደ ኋላ ባለማለቱም ስሙ ይነሳል፡፡
በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም በተለያዩ ክበባት አገልግሏል። በተለይም የተማሪዎች ፕሬዚደንት ሆኖ ከተመረጠ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን ከጓደኞቹ ጋር ይሰራ ነበር፡፡ ለምሳሌም ህሊና የምትባል መጽሄት ያሳትሙ ነበር፡፡ የተማሪዎችን ነፃነት ለማስከበርም የዩኒቨርሲቲውን አስተዳደር ይሞግት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት በፖሊሶች ክትትል እና ምርመራ ይደረግበት እንደነበር ይናገራል። አመጽ ቀስቅሰሃል በሚልም መከሰሱን ያስታውሳል፡፡ በ1993 ዓ.ም በመጋቢት ወር ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ (ኢሰመጉ) ጋር በመሆን ከተደረገ ስብሰባ በኋላ በአአዩ በተቀሰቀሰው ረብሻ ምክንያትም ጓደኞቹና ወንድሞቹ ታስረውበት ነበር። በዚህ ሳቢያ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ጫና ምክንያት ወደ ኬንያ ተሰዶ ለ4 ዓመታት ከቆየ በኋላ ነው ወደ ኬንያ የተሰደደው በ1997 ዓ.ም የኢትዮጵያ ምርጫ ሁለት ሳምንት ሲቀረው ወደ ቫንኩቨር ካናዳ ተጓዘ።

#የስራ ህይወት*

ተክሌ ወደካናዳ እንደገባ የመጀመሪያ ስራው: ጽዳት ነበር።ለ 2 ወራት። ከዚያ ወደ ጥበቃ አደገ። law school በነበረ ሰአት የቤት አልባዎች መጠለያ ውስጥ ረዳት ሆኖ ሰርቷል። በካናዳ 2ተኛ ዲግሪውን ከሰራ በኋላ በ2012 እ.ኤ.አ ለአንድ ዓመት ያህል በኢሳት (ESAT) ቴሌቪዥን በበጎ ፈቃደኝነት በረዳት ጋዜጠኝነት እና በዜና አንባቢነት ሰርቷል። በ2013 እ.ኤ.አ ወደ ኦንታሪዮ (ቶሮንቶ) በመዛወር የጥብቅና ፈተና (Bar Exam) ወስዶ እ.ኤ.አ ከሴፕቴምበር 2014 (መስከረም 2007 ዓ.ም) ጀምሮ የህግ ባለሙያ (Licensed Lawyer) በመሆን ላለፉት 11 ዓመታት በህግ ስራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል።

በልጅነቱ በአካባቢው የሚኖሩ ሴቶች በጉልበተኞች ሳቢያ በሚደርስባቸው እንግልት እና በደል ከዚህም ባለፈ ሰዎች በመሬት፣ በስራ፣ በቤተሰብ ወይም በባለስልጣናት እና በሀብታሞች ግፊት ሲበደሉ ማየት ያሳዝነው ስለነበር፣ ሁልጊዜም ለተበደሉ እና ለተጨቆኑ ሰዎች ፍትህ የመስጠት ለሰዎች ሰላምን እና እረፍትን የሚሰጡ ውሳኔዎችን የማሳለፍ ህልም ነበረው። ዳኛ የመሆን ፍላጎት ነበረው። ታዲያ በከፊልም ቢሆን ተምሮ ያሳካው ይህንኑ ነው፡፡

በልጅነቱ እንደተራበው እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ የህግ ፈቃድ (License) አግኝቶ በመስኩ እያገለገለ ይገኛል፡፡
የስደት እና ስደተኞች ህግ በሚመለከት አዲስ ወደ ካናዳ የሚመጡ ስደተኞችን መርዳት እና ጉዳያቸው ውድቅ ሲደረግ በፌዴራል ፍርድ ቤት መከራከር አንዱ ስራው ነው።
የባል እና የሚስት ጠብ (Domestic Violence) ፣ የልጆች ጉዳይ፣ ጠጥቶ ማሽከርከር መንዳት (Impaired Driving)፣ ጠብ (Bar Fight) እና የመኪና አደጋ ጉዳዮች ሲገጥም ምክር በመስጠት ብዙዎችን ረድቷል። ህግ ባለማወቅ ወይም በተለያዩ አጋጣሚዎች በስርቆት የሚከሰሱ ሰዎችን እና ህጻናትን ያግዛል፡፡
በሃገር ቤት ያሉ ቤተሰቦችን በማምጣት ሂደት ያሉ ችግሮችን መፍታት እንዲሁም በስደት ሂደት ላይ የሚፈጠሩ ስህተቶችን የማስተካከል ስራዎችን ይሠራል።

ከዚሁ ከህግ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ እስካሁን ድረስ ከ10,000 በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች የምክር አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ ከ2,100 በላይ ዳጎስ ያሉ መዝገቦችንም መያዙን ነው ተክሌ የሚናገረው፡፡። እንግዶች ባለማወቅ ስህተት ሰርተው ሲከሰሱ ያግዛል ያማክራል፡፡ በተለይ ሰዎች አዲስ ሆነው ወደ ካናዳ ሲመጡ ህጉን አያውቁምና ግራ ይጋባሉ ለተለያዩ ችግሮችም ይጋለጣሉ በዚህ ጊዜ ፈጥኖ ደራሽ ነው፡፡

የማህበረሰብ አገልግሎት እና የበጎ አድራጎት ሥራዎች
በተለያዩ የማህበረሰብ እና የቤተክርስቲያን ስራዎች ላይ መሳተፍ ለተክሌ የልቡ ደስታ ነው፡፡ በቶሮንቶ ካናዳ በሚገኘው የኢትዮጵያ ማህበር ውስጥ ለሦስት ዓመታት በቦርድ ዳይሬክተርነት እና በምክትል ፕሬዝዳንትነት አገልግሏል።

ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ከኪሱ በየወሩ ከ1,500 ዶላር በላይ በማውጣት የተለያዩ እንግዶችን ታዋቂ ግለሰቦችን: የአየር ቲኬትና የሆቴል ወጪ በመሸፈን: ወደ ካናዳ እንዲመጡ በመጋበዝ የወሩ የመጀመሪያው ቅዳሜ ላይ ዝግጅት ያደርጋሉ ። ከተጋባዦቹ መካከል አቶ ተካልኝ ገዳሙ፣ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ፣ ፕሮፈሰር ሃረገወይን አሰፋ: ምስጢረ አደራው: እና ፕሮፌሰር አለማንተ ገብረሥላሴ ይገኙበታል፡፡

መጻህፍን በመግዛትና በማከፋፈልም ደራሲያንን በማበረታታት ረገድ ከፍተኛ ተሳትፎ ያደርጋል ፡፡ ለማህበረሰቡ የሚሰጠው አገልግሎት ለእርሱ ትልቅ የህይወት እርካታ እንደሚሰጠው ይናራል፡፡

ምስክርነት

እህት ስመኝ አበበ

ተክሌ በልጅነቱ እናቱ “ታገል” እያሉ ይጠሩት ስለነበር ሁሉም “ታገል” ይሉታል። በጣም ታዛዥ እና ትልቅ ትንሹን አክባሪ እንደነበረ ነው እህቱ የምትናገረው፡፡

በሰፈር ሰው በጎረቤትም ዘንድ በጣም አክባሪ፣ ከሰው ጋር ተግባቢ፣ እና ፀብ የማይወድ በጣም መልካም ልጅ ነበር። ከቤተሰብም ጨዋታ አዋቂ፣ ቀልደኛ እና ተጫዋች ነው። ጨዋታዎችን ከየት እንደሚያመጣቸው እስከማይታወቅ ድረስ ሁልጊዜም ሰውን በማስቅ እና በማጫወት የተካነ ነው። በዚህ የተነሳ እናታቸው “አሙቀኝ” እያሉ ይጠሩት ነበር፡፡

በአንደኛ ደረጃ በትምህርት ቤት በነበረው ቆይታ በጣም ጎበዝ ተማሪ የነበረና ከብዙ ክፍሎች አንደኛ በመውጣት የሚታወቅ እንደነበር ነው እህቱ የምታስታውሰው፡፡ በትምህርቱ ካሳየው ከፍተኛ ብቃት የተነሳ፣ በትምህርት ቤቱ ከተመረጡ ጥቂት ተማሪዎች መካከል አንዱ በመሆን በአዳማ/ናዝሬት፣ በሚዘጋጁ የትምህርት ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ተሸላሚ በመሆን ቤተሰቡን ያስመሰግን ነበር።

በትምህርት ቤት ውስጥ እንደ ስነጽሁፍ እና ድራማ ስፖርት ባሉ የክበባት እንቅስቃሴዎች ላይም በንቃት ይሳተፍ ነበር።
ታገል ተማሪ በነበረበት ወቅት ከራሱ ብቃት ባሻገር ሌሎችን ለመርዳት መስዋዕትነትን ይከፍል ነበር፡፡ እህቱን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎችን ቅዳሜ እና በእረፍት ሰዓታቸው እየጠራ በፈቃደኝነት ያስጠናቸው ነበር።

በዚህና በሌሎች መልካምነቱ በትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ዘንድ “ተወዳጁ” ተብሎ እስከሚጠራ ድረስ እጅግ ተወዳጅ ተማሪ ነበር።
ከትምህርቱ ጎን ለጎን እናቱን በጉልበት ስራዎች ቤት በማጽዳት፣ ቤት በመጥረግ እና እንጨት በመፍለጥ ያግዝ ነበር። ለሁለት አመታት በክረምት ወራት ጋሪ በመግፋት: የአረቄ እንጨት ቀመጫን: ለቤተሰቡ ተጨማሪ ገቢ ያስገኝ ነበር።

ስለ ተክሌ (ታገል) ምስክርነቷን የሰጠችው እህቱ የታገል እህት በመሆኗ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፤
የአባት ምትክ እና “ከአባትም በላይ” ሆኖ የሚታይ፣ ልዩ ወንድም ነው ትላለች፡፡

የጋዜጠኛ ቃለእየሱስ በቀለ ምስክርነት

ተክሌ በቶሮንቶ ዙሪያና አካባቢዋ በጣም የሚታወቅ የህግ ባለሙያ ነው፡፡ የኢምግሬሽን ህግ አገልግሎትን በመስጠት ይታወቃል፡፡ በይበልጥ ግን በቶሮንቶና አካባቢዋ ባለው የኢትዮጲያ ማህበረሰብ ዘንድ በማህበራዊ አገልግሎቶቹ ስሙ ይነሳል፡፡ ገቢ ማሰባሰቢያን ጨምሮ በበጎ አድራጎት ስራዎችና በተለያዩ አገልግሎቶች ላይ ይሳተፋል፡፡ በኢትዮጲያ ኮሚኒቲ ጽህፈት ቤት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ በየወሩ አዲስ ለመጡ ኢትዮጲያውያን ስደተኞች ከኢሚግሬሽን ጋር በተያያዘ ሊገጥሟቸው ስለሚችሉ ሁኔታዎችና ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው የኢሚግሬሽን ጉዳያቸውን በዕውቀት ላይ ተመስርተው እንዲፈጽሙ በነጻ የምክር አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በየወሩ በኢትዮጲያ ኮሚኒቲ ጽህፈት ቤት በመገኘት ይህንን አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያም በየሳምንቱ ቲክቶክ ላይ ለጥያቄዎች ማብራሪያ ይሰጣል በዚሁ በስደተኞች ጉዳይ፡፡
ተክሌ ደግና ቀና ልብ ያለው ሰው ነው ይላል ቃለእየሱስ በቀለ፡፡ የተለያየ የህይወት ፈተና ለገጠማቸው ሰዎች በመድረስ ይታወቃል፡፡ በቶሮንቶም ሆነ በሌሎች ከተሞች ያሉ በኢትዮጲያውያን የሚመሩ የንግድ ተቋማትን( ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ሱቆችና ሌሎች) ያበረታታል ያለምንም ክፍያም ያስተዋውቃል፡፡
ቃለእየሱስ እንደሚለው ተክሌ ኢትዮጲያዊያን ጸሃፍት የጻፏቸውን መጻህፍት ከኢትዮጲያ በማስመጣት ሰዎች እንዲያነቡ ያደርጋል እርሱም ያነባል፡፡ በዚህም የንባብ ልምድ እንዲዳብር የበኩሉን ያደርጋል፡፡
ከቶሮንቶና አካባቢዋ በተጨማሪ በኢትዮጲያ ላሉም ተቋማት እና ለተቸገሩ ዜጎች ድጋፍ ያደርጋል ገቢ ያሰባስባል ይሄ መለያው ነው፡፡
ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ የሚዲያ ነጻነትና የህግ የበላይነት መከበር፣እንዲሁም የሰው ልጆች ሰብአዊ መብት መከበር ላይ አጥብቆ የሚሟገት መሆኑንም ባልንጀራው ይናገራል፡፡

የመስፍን አማን ምስክርነት

ትውውቃቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያሉ ነው፡፡ መስፍን እንደሚለው ተክሌ በወቅቱ ‘አባ ኪያ’ እየተባለ ነበር የሚጠራው፡፡ ጨዋታ አዋቂ ሰው የሚከበው አይነት ተማሪ ነበር፡፡ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ልሳን የነበረው “ህሊና” ጋዜጣ ተማሪው ተስፋ የጣለበት ስራ ነበር፡፡ ተክሌ እራሱ ጽሁፍ አበርክቶ ነበር፡፡ በጋዜጣው ላይ ተክሌን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎች መጣጥፎችን አዘጋጅተዋል፡፡ በተለይም በተማሪዎች አገልግሎት ዙሪያ የሚታዩ ድክመቶችን የሚተች ጽሁፍ ተጽፎ ነበርና ያንን የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር መቋቋም አልቻለም፡፡ ይሄንን ተከትሎም በተማሪዎች ማህበሩ ላይ ጫና ማድረግ ተጀመረ፤ ጋዜጣዋም እንድትቆም ተደረገች፡፡ ከዚህ የተነሳም ተቃውሞ ተነሳ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ እንደዚያ ጠንከር ያለ የተማሪዎች አመጽ ሲነሳ ከብዙ ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው እንደነበር መስፍን ያስታውሳል፡፡ አመጹ በሁሉም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካምፓሶች ነው የተካሄደው፡፡ እንደውም ሌሎች የሃገሪቱ የዩኒቨርሲቲና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችም አመጹን ተቀላቀሉ፡፡ በጊዜው አመጹን ለማዳፈን መንግስት የጉልበት አማሪጭ ተጠቅሞ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ አመጹ አስቸጋሪ ሆነ፡፡ መንግስት ተማሪዎችን ከጊቢ አባረረ አመራሮቹንም አደን ጀመረ፡፡ በወቅቱ በመንግስት ሃይሎች ከተያዙና ከታሰሩት መካከልም እራሱ መስፍን ይገኝበታል፡፡ በስተመጨረሻ እነተክሌ አማራጭ ስላልነበራቸው ከሃገር መውጣታቸውን ያስታውሳል፡፡

ተክሌ በሥነጽሁፍም የጎላ ተሳትፎ እንደነበረው መስፍን ይናገራል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል አዳራሽ ውስጥ በወር አንድ ጊዜ የሚካሄድ ዝግጅት ነበርና ከነበውቀቱ ስዩም፣ ፍቅር ይልቃል፣ ይርጋ ገላው: ስመኘው መብራሕቱ: ና ሌሎች ተማሪዎች ጋር አንዱ የግጥም አቅራቢ ተክሌ እንደነበር መስፍን ያስታውሳል፡፡

የልዩ ሰው ምስክርነት ትውውቅ

የመጀመሪያ ትውውቃቸው በስልክ ነበር በ2004 ዓ.ም ልዩሰው በሃሊፋክስ፤ ኖቫ ስኮሽያ ዳልሀውሲ ዩኒቨርስቲ የህግ ድህረ ምረቃ ተማሪ እያለ፡፡

በ2006 ዓም ቶሮንቶ ከመጣ በኋላ አልፎ አልፎ በማህበራዊ ጉዳዮችና ትምህርቱን በሚመመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተገናኝተው ይጨዋወቱ ነበር፡፡

ይበልጥ የተቀራረቡት ግን ልዩሰው የኢትዮጵያ የህግ ዲግሪውን ወደ ካናዳ አቻው ለማስቀየር የሚረዳውን ትምህርት አጠናቆ ወደ ጥብቅና ሙያ ለመግባት የሚያስችለውን የተግባር ልምምድ (አርቲክሊንግ) ስራ ፍለጋ ላይ ሆኖ ነበር፡፡

ማንን ማናገር እንዳለበትና የት መሄድ እንዳለበት እያሰሰ እያለ ኦማር የሚባል የኤርትራ ትውልድ ያለው መምህሩን ያገኘዋል፡፡ ኦማር የተክሌ ጓደኛ ነበርና ልዩሰውን ወደ ተክሌ ይልከዋል፡፡
ከተክሌ ጋር በስልክ አውርተው በአካልም ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ ሊዩሰው ከተክሌ ቢሮ ተቀጠረ፡፡ ቅርርባቸውም በዚህ መልክ ተጀመረ፡፡
በዚህ መልኩ የጠነከረው ትውውቃቸው የበለጥ እየዳበር ላለፉት 9 ዓመታ ቀጥሎ፤ አሁን ተክሌ እና ልዩሰው የአንድ ቤተሰብ አባላት የታላቅና ታናሽ ወንድማማቾች ያህል ነው አብሮነታቸው፡፡

የተክሌ ስብዕና

ሌሎቹ የተክሌ ወዳጆች እንደሚሉት ሁሉ ልዩሰውም ተክሌ ቅን፤ ታታሪ፤ አስተዋይ፣ የማያውቀውን የሚያውቅና ለመማሪ ሁሌም ዝግጁ፤ የሚያውቀውን ለማካፈል የሚተጋ፤ ተዕግስተኛ፤ ችር በረከቶቹን በማካፍል ደስ የሚለው እንደሆነ ይናገራል፡፡
የተክሌን ቅንንት ሲያስረዳም በተክሌ ቢሮ ያለፈ ካናዳ ውስጥ በህግ ሙያ የተሰማራን ትውልደ ኢትዮጵያውን ጠበቆችን አታገኝም ይላል፡፡ በእሱ የሰለጠኑ የሱ የገበያ ተፎካካሪዎች በመሆናቸውም ኩራት እንደሚሰማቸው ይገልጻል፡፡
ልዩ ሰው የግሉን የህግ ድርጅት ሲጀምር ተክሌ የዋለለትን አይረሳም፡፡ ለስኬቱ እንደው እንደነገሩ የመልካም ምኞት መግለጫ መላክ ሳይሆን ብቻ ሳይሆን ከአንድ ዓመት በላይ በነጻ ቢሮውን በመስጠት አግዞታል፤ ድርጅቱንም የሚያስተዋውቅበት የተለያዩ መድረኮችን አመቻችቶለታል፡፡

ልዩ ሰው የተክሌን ታታሪነት ሲገልጽ “ፈጣሪ ለተክሌ በቀን 48 ሰዓት ነው ሳያድለው አይቀርም“ በማለት ነው፡፡ ልዩሰው እንደሚለው ተክሌ ማለዳ ተነስቶ 5 ኪሎ ሜትር ይሮጣል፤ እሱ ( ልዩሰው) በሁለት ቀን የማይጨርሰውን ስራ በ8 ሰዓታት ውስጥ ጨርሶ፣ የኮሚኒት ስብሰባ (“ረጅምና ትዕግስን የሚፈትን”) ተሳትፎ፣ እንግዳ ኤርፖርት ተቀብሎ፣ ራት ጋብዞ፣ እንግዳውን ማረፊያው አድርሶ፤ ቤቱ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ገብቶ ጥቂት ሰዓታት አርፎ ቀጣዩን ቀን እንዲሁ በማለዳ ተነስቶ ይጀምረዋል፡፡ ከሙሉ ቀን ችሎት በኋላ፤ ለፍርድ ቤት ወይም ለቦርድ የሚዘጋጅ ጽሁፍ አዘጋጅቶ፤ ከዛም በኋላ አንድ ወይም ሁለት ሚዲያ ላይ ስለወቅታዊ ጉዳይ ውይይት ሊያደረግ ይችላል ሲል ይገልጸዋል፡፡ ልዩሰው”እሱ(ተክሌ) እኔን ታታሪ ይላል፤ ታታሪነት እኔን የሚገልጽ ቅጽል ከሆን የሱን ጥንካሬና የስራ ውጤታማነት (ፕሮዳክቲፊቲ) የሚገል ቅጽል ማግኝት ይከብዳል፡፡“ ነው የሚለው፡፡
ልዩ ሰው የተክሌን አስተዋይነትም ይመሰክራል፡፡ በሙያ ውስብስብ ጉዳዮች፤ በተለይም ከባድ ኢቲካል (የ“ስነ፟ ምግባር”) ጉዳዮች ሲገጥመው ያላየውን ያላገናዘበውን አቅጣጫ ስለሚያሳየው ተክሌን ማማከር ይመርጣል፡፡ እንዳንድ ጉዳዮችንማ ይህ የተክሌን እይታ ፍርድ (ጀጅመንት) ይሻል ብሎ ደንበኞችን ወደ እርሱ ይመራል፡፡

ልዩሰው ተክሌ ሁሌም ለመማር ዝግጁ መሆኑንም በተለያዩ መገለጫዎች ያነሳል፡፡ በቡድን አገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲያደርጉ ሃሳብን ይቀበላል፤ በማያውቀው ነገር ላይ በእርግጠኝነት አያወራም፡፡ ከዚህ በፊት ሰርቶት በማያውቀው ጉዳይ ላይ ደንበኛ የጥብቅና አገልግሎት ከፈለግ፤ በግልጽ የጉዳዩን አዲስነት ተናግሮ በአጭር ጊዜ ምርምርና ዝግጅት በማድረግ ጉዳዩን መያዝ የሚችል ከሆነ ይህንኑ ለደንበኛው ይናገራል፤ ይህን እንደማይችል ከመዘነ ደግሞ ለባለጉዳዩ በጉዳዩ ላይ በቂ ልምድና እውቀት አለው ብሎ ወድሚያስበው ባለሙያ ይመራል እንጂ እንዳው ዝም ብሎ ለጥቅም ሲል ደንበኞችን አያሞኝም ነው ልዩ ሰው ስለ ተክሌ የሚለው፡፡

ልዩ ሰው ወዳጁ ስለ ተክሌ የሚመሰክረው ብዙ አለው፡፡ አቋሙን ለደንበኞቹም ሆነ አብረውት በሃሳብ ላይ ለሚወያዩ ካለመታከት ማስረዳት መለያው ነው፡፡ በተጠየቅ (ሎጂክ)ና ታማኝ በሆነ ማስራጃ (ዋቢ) ለሞገተው ላስረዳውም ምላሹ ቀና ነው አምኖ ይቀበላል፡፡ እኔ ያልኩት ካልሆነ ወይም ሃሳቤ ሃያል ነው የሚል ኢጎ ተክሌ ዘንድ እንደማይገኝ ልዩሰው ረገጥ አድርጎ ይናገራል፡፡ ተክሌን በቡድናዊ አስተሳስብ ውስጥ ማግኝት እንደማይታሰብም ያስረዳል፤ ምክንያቱም ተክሌ ታማኝነቱ ለሃሳብ ልዕልና ስለሆነ የተሻላ ሃስብ ካገኝ የተሻለውን ይዞ ይሄዳል ብሎ ያምናል፡፡ ተክሌ መሰረታዊ የፖለቲካ፤ የማህበራዊ መስተጋብሮችና እሴትች ላይ ቋሚ እይታዎቹ አይቀየሩምም ነው ልዩሰው የሚለው፡፡

መስጠትና መሰጠት

በአንድም በሌላም መልኩ እርሱ ሲባረክ ብቻውን ከመሆን ይልቅ ስለሌሎች ማሰብ የተክሌ ትልቅ ስጦታው ነው ባይ ነው ልዩ ሰው፡፡ እንኳን ለሌላ በቢሮ ለሚሰሩ ቢዝነሱ በሰፋ ቁጥር ከበረከቱ ያለስስት ያካፍላል፤ ለተለያዩ ኮሚኒቲ ዝግጅቶች፤ የሃይማኖት ተቋማት፤ ለትምህርት ቤቶችና ለተማሪዎች ከሚያገኝው ሁሉ ቸርነትን ያደርጋል፡፡ ለታመምና ለተቸገረ ደራሽ፤ ላዘነም አጽናኝ ነው፡፡

ሙያዊ አበርክቶ

ከሙያ አንጻር ብዙ እንደሰራ ለብዙዎችም እንደደረሰ ልዩሰው ህያው ምስክር እንደሆነ ይናገራል፡፡ ልዩሰው እንደሚለው ተክሌ በካናዳ ውስጥ የመጀመሪያ ትውልድ (ፊርስት ጄኔሪሽን) ስደተኛ ሆኖ በጥብቅና ሙያ የተሰማራ ፈር ቀዳጅ ነው፡፡ ከሱ በፊት የነበረው አቶ ዳንኤል ደጋጎ ብቻ ነቀር። በጥብቅና ሙያምው በካናዳ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ወገኖች ለሚያጋጥማቸው የኢሚግሬሽን፤ የወንጅል፤ የቤተስብና ውርስ ጉዳዮች ላይ ብቃት ያለውና መፍትሄ ተኮር አግልግሎት በመስጠት ትልቅ አስተዋጾ አበርክቶል፤ እያበረከተ ይገኛል፡፡

ሥራውን ከጀመረበት ከታህሳስ 2007 ዓም ጀምሮ በሺዎ ለሜቆጠሩ ደንበኞቹና እፎይታን ያስገኝ የጥብቅና አግልግሉት ሰጥቶል፡፡ ይህንን ለማወቅ ከተክሌ ጋር በቶሮንቶ ዋና ጎዳናዎች ላይ ለተውሰነ ጊዜ መጎዝ በቂ ነው ይላል ልዩ ሰው፡፡ መንገድ ላይ ከተክሌ ጋር ሲሄዱ በየመንገዱ አቁሞ በአክብሮትና በስስት ሰላም የሚለው የሚያመሰግነው ሰው ብዛት እና ስሜት፤ በስራው ላስገኝው የሚያስመሰግን ውጤት እማኝ ነው ይላል ወዳጁ ልዩሰው፡፡
ካናዳ ባለፉት አስር አመታት ውስጥ ለመጡ በኢትዮጵያውያ የህግ ትምህርት ላላቸው ባለሙያዎች ደግሞ በሙያቸው ካናዳ ውስጥ የሚሰሩበትንና ራሳቸውን በመለወጥ ለቤተሰቦቻቸውና ለማህበረሰባችው የሚተርፉበትን እድል አመቻችቷል፡፡
ለዚህ እራሱ ልዩሰው ምስክር ነው የተክሌ መኖር እጅግ አዳጋች የሆነውን የአርቲክሊንግ ስራ ፍለጋ አቅልሎለታልና፡፡ ተክሌ የፈጠረው የተመቻቸ የስራ ሁኔታም ስራውን በጣም እንዲወደውና ውጤታማ እንዲሆንበት አስችሎታል፡፡ከዚህ ባለፈም በተክሌ ሱፐርቪዥንና ሜንተርሺፕ የጥብቅና ሙያ ፈቃዱን በመስከርም 2011 አግኝቶ በሙያው እየሰራ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ ከእሱ(ልዩሰው) በኋላ አራት ወጣት ኢትዮጵያውያን የህግ ባለሙያዎች የጥብቅና ፈቃዳችውን ያገኙ ሲሆን አራቱም በተክሌ ቢሮ ውስጥ ያለፉ ናችው፡፡

ተክሌ ሌሎች ትውልድ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የህግ ባለሙያዎችን እያስተባበረ በቡድን በመሆን ለኮሚኒቲው መጠናክር የሚረዱ የህግ፤ የፖሊሲና የውትወታ (አድቮካሲ) ስራዎችን ለመስራት ላለፉት ሶስት ዓመታት ጥረት ላይ መሆኑንም ልዩሰው በአድናቆት ያነሳል፡፡

ደምሰው ከበደ (ሻምበል) ስለ ተክሌ

ከትውውቃቸው ጀምሮ ታገል እንጂ ተክሌ ብሎት አያውቅምና ምስክርነቱን ታገል (ታገል አባኪያ) እያለ ነው የሰጠው፡፡ ትውውቃቸው ገና የ6ተኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ በልዩ አጋጣሚ ነው የሚጀምረው፡፡ በወቅቱ ታገል በረኛ ሆኖ በጨዋታው ወቅት የተመቱ ኳሶች ሁሉ ገብተውበት ነበርና አጋጣሚውን በፈገግታ ያስታውሰዋል፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላ ነው የቅርብ ጓደኞች የሆኑት፡፡
ታገል በልጅነቱ ቤተክርስቲያን የሚወድ ከዛም ባለፈ ማንበብ መጫወት መሳቅ የሚወድ ልጅ እንደ ነበር የልጅነት ጓዱ ይናገራል፡፡ ከታገል ጋር እጅግ ብዙ አይረሴ ትዝታዎች ገጠመኞች እንዳሏቸው ያነሳል፡፡ አንዱ ብዙ አመታትን ወደ ኋላ ይወስደናል፡፡ 11ኛ ክፍል እያሉ የሆነ ነው፡፡ አንድ ምሽት ላይ ወደ ቤት እየገቡ ነበር ታገልና ይኸው አብሮ አደጉ፡፡ በመሃል አንድ የገጠር ሰው ሰክሮ እየጮኸ ዱላውን እያወዛወዘ ይመጣል፡፡ ሻምበልም ሽመል ከእጁ አይጠፋም ነበርና ሽመሉን እንደያዘ መንገዳቸውን እየሄዱ ነው፡፡ ታገል ውይይቶች ክርክሮች ላይ ችግር የለበትም ጸብ ግን አይወድም፡፡ የዛን ቀን ግን ሰካራሙ ሰው ሽመሉን ይዞ ወደ እነሱ ሲቀርብ አምጣ ብሎ ከጓደኛው ዱላውን ተቀብሎ የሰካራሙን ዱላ ሲመክት የሰውየው ምት የነታገልን ዱላ አሽቀንጥሮ ጣለው፡፡ ጓደኛሞቹ የሰውየውን ጥቃት መመከቱ እንደማያዋጣ ሲያዩ ታዲያ ደቂቃም ሳያባክኑ ጥለው መፈርጠጣቸውን በሳቅ በፈገግታ ያስታውሰዋል፡፡

ጥሬ ስጋ

መብራት ክፈሉ ተብለው የተላኩ ጊዜም የገጠማቸውን እንዲሁ ያስታውሳል፡፡ ያኔ ደግሞ የታዘዙትን ፈጽመው መብራት ከፍለው ማለት ነው መልሳቸውን ተቀብለው ሲመለሱ ስጋቤት ትኩስ ጥሩ ስጋ ተሰቅሎ ያያሉ፡፡ ታገል ደግሞ ጥሬ ስጋ እጅግ ይወዳል ታዲያ አይተው ማለፍ ተሳናቸውና በመልሱ ቁርጣቸውን አማርጠው በልተው ጠግበው ይወጣሉ፡፡ የቁርጥ አምሮታቸውን ከተወጡ በኋላ ቤተሰቦቻቸው መልስ ስለሚጠይቋቸው ተበድረው የከፈሉበትን ጊዜ አይረሳም፡፡

አንደበተ ርቱዕ

ሻምበል: ታገል አንደበተ ርቱዕ እንደሆነ ይናገራል ፡፡ በየትኛውም በመንፈሳዊውም ሆነ በማህበራዊ ስብስቦች ላይ መጠየቅ ሃሳቡን በሚገባ የመግለጽ ችግር የለበትም፤ ከፖለቲካም አንጻር አነጋጋሪ ጥያቄዎችን የማንሳት ልማድ እንደነበረው ነው ወዳጁ የሚያስታውሰው፡፡ ፍሃዊ ያልሆነ ነገር አይመቸውም ታገል ፡፡ ነገሮችን ፊትለፊት የመጋፈጥ ብቃቱና ድፍረቱም አይረሴ ናቸው ይላል: ደምስ።

የተማሪዎች ፕሬዚዳንት

ሻምበል እንደሚያነሳው ታገል የተማሪዎች ህብረት መሪ ሆኖ በተመረጠበት ወቅት “Let’s change the dark age of the union” የሚል መፈክር በማንገብ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የተለየ ከባቢ ለመፍጠር ጥረት አድርጓል፡፡ በጊቢው የሚያያቸውን ፍትሃዊ ያልሆኑ ነገሮች ለመቅረፍ ብዙ ጥሯል፡፡እንደውም አንድ ክረምት የእረፍት ጊዜውን ሰውቶ እዚያው በዩኒቨርሲቲው ጊቢ ውስጥ አሳልፏል እነዚህን ጉዳዮች ከዳር ለማድረስ፡፡

አለባበስ

ሳቅ መፍጠር የሚወደው ታገል ሲያሻው ስድስት ኪሎ campus በበረባሶ ጫማ ይታይ እንደነበር››› አንድ ግዜ ካልሲ ክራቫት አድርጎ እንደነበር ይናገራል፡፡ በተለይ በበአላት ወቅት ሙሉ የባህል ልብስና ጭራ መያዝም ያዘወትር ነበር፡፡

ተክሌ ወዳጃችን ክበርልን!!!!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *