ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣ መዝገበ-አእምሮ ( የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች ፣በመፅሀፍ፣በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል።በተለይ ጉግል ላይ ታሪካቸው ሲፈለግ የማይገኝ ሰዎች አሁን የሙያ አበርክቷቸው በቀላሉ ኢንተርኔት ላይ በግልፅ ተቀምጦ ይገኛልደ ባለፉት 4 ዓመት ከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መፅሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።
ከእነዚህ ውስጥ የሚድያ ሰዎችና የቴአትር ባለሙያዎች ይገኙበታል። አጠቃላይ 74 ከፍተኛ የሚድያ አመራሮች፣ 50 በላይ የፊልምና የቴአትር ባለሙያዎች ፣ሚኒስትሮች ፣ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የግል ሚድያ መሥራቾች፣ዋና አዘጋጆች እና መካከለኛ አመራሮች ተካተዋል። 35 ያህሉ በዋና ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ያሉ ሲሆን የሁሉም ታሪክ በተሟላ ደረጃ ለመሰነድ ተችሏል። የእነዚህን አመራሮች እና የሚድያ ሰዎች ታሪክ ሰንዶ ለአንባቢ ተደራሽ ማድረግ ፈታኝ ቢሆንም አሳክተነዋል። በዚህ ተግባራችንም ተጠናክረን እንቀጥላለን።
በዚህ ፅሑፍ የሙያ ታሪኳ የሚሰነድላት ጠንካራ ባለሙያ መሠረት መብራቴ ትባላለች። መሠረት በቴአትር ትወና እና በማስታወቂያ ፣በፊልም ሥራዎቿ የራሷን ትልቅ አሻራ ያኖረች ባለሙያ ናት። የተወዳጅ ሚድያ የስነዳ ቡድን ባደረገው ጥናት መሠረት በጥሩ ሥነ ምግባር የታነፀች ብርቱ ባለሙያ መሆኗን አረጋግጧል። ይህን አርአያነቷን ግምት ውስጥ በማስገባት የመዝገበ አእምሮ ( የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ) የቦርድ አባላት የሙያ ታሪኳ መሰነድ እንዳለበት ወስነዋል። በመሆኑም በቀጣይ በሚወጣው ቅፅ 3 መዝገበ አእምሮ መፅሐፍ ላይ የመሠረት ታሪክ ይካተታል። እስከዚያ ግን የመሠረትን ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎቻችን እንዲያነቡት ተጋብዘዋል። ዕዝራ እጅጉ ታሪኳን እንደሚከተለው ሰንዶታል። በዚህ ፅሑፍ ውስጥ የተካተቱት ምስሎችና ታሪኮች የባለ ታሪኳን ፋቃድ ፣ይሁንታና ማረጋገጫ ያገኙ ናቸው።ይህን ታሪክ እንድንሠራ ለተባበረን ለዕንቁ ንቁ ሴት ሽልማት መሥራች ሳሙኤል ገረመው ምሥጋናችን ይድረሰው።
ልጅነት፣ትምህርት
አርቲስት መሰረት መብራቴ ከወላጅ እናቷ ወ/ሮ ገነት ሲሳይ እና ከአባቷ አቶ መብራቴ ተከተል አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ግቢ ገብርኤል አካባቢ ተወለደች።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ኢትዮጵያ አንድነት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በዳግማዊ ምኒሊክ ት/ቤት ተምራለች። በሚኒ ሚዲያ ተሳትፋለች። በሰንበት ት/ቤት ከነበራት የዝማሬ የድርሰትና የግጥም አገልግሎት ጎን ‘የካታኮምቡ ሰማእት’ የተባለ ቴአትር ለመጀመሪያ ለቴሌቭዥን ትወና ተመረጠች።
ወደ ትወና መምጣት እና የዩኒቨርስቲ ቆይታ
በ1991 ዓ.ም በወርሀ መስከረም በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በተላለፈ ‘የሻማ እምባ’ ስራዋ ተወዳጅነትንና አድናቆትን በማትረፍ የትወና ሙያን ተቀላቀለች።
ክህሎቷን በትምህርት ለማገዝ የትወና፣ የዳይርክቲንግ እና የቪዲዮግራፊ ኮርሶችን ወስዳለች። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴያትር ጥበባት የመጀመሪያ ዲግሪዋን የማስተርስ ዲግሪዋንም በመልቲ ሚዲያ ቴያትር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለቱንም በማዕረግ ተቀብላለች።
አስተዋፅዖ
በርካታ የመድረክ፣ የሬዲዮ ፣የቴሌቭዥን የፊልም፣ ድራማዎችና የማስታወቂያ ሥራዎችን ሠርታለች።
ቴያትሮች:- ቀዝቃዛ ረመጥ፣ ካብ ለካብ፣ ጠያቂ፣ የልብ እሳት፣ መሀላ፣ ላጤ እንዲሁም ፍሬሽ ማን የተሰኘ ቴአትርን በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ያሳየች ሲሆን፤ “ናዳ” የተሰኘ ቴያትርን በእስራኤል ሀገር በቴልአቪቭና እየሩሳሌም ከተሞች አቅርባለች።
“ኦቴሎም ” በጉልህ ከሚጠቀሱ ሥራዎቿ መሐል ይገኛል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዊሊያም ሼክስፒር ክላሲካል ሥራዎች መሀል A mid summer’s night dream ( የበጋ ሌሊት ህልም) በሚል በበላይነህ አቡኔ የተተረጎመ ቴአትር ላይ በትወናና በረዳት አዘጋጅነት ተሳትፋለች፣ እንዲሁም Othelo ቴያትር ላይ የዴዝዴሞና ገፀ- ባህሪን ወክላ በብቃት ተውናለች።
ፊልም:- የፍቅር ሽሚያ፣ ድማሚት፣ዳግማዊት፣ የእሳት ራት፣ ጉዲፈቻ፣ ንጉስ ናሁሰናይ፣ ዜማ ህይወት፣ ቫኬሽን ፍሮም አሜሪካ፣ ሂሮሺማ፣ የሞሪያም ምድር፣ኅረየት ተወዳጅ ሰራዎቿ ናቸው።
የቴሌቭዥን ድራማዎች:- የሻማ እምባ፣ ገመና አንድ እና ገመና ሁለት፣ በቀናት መካከል፣ንፁህ ምኞት እና እርቃን ይገኙበታል::
በቅዳሜና እሁድ መዝናኛ የሬድዮ ፕሮግራሞች በርካታ አጫጭርና ተከታታይ የሬድዮ ድራማዎችን ተጫውታለች።
ከ 300 በላይ የቴሌቭዥን ማስታወቂያዎች ሰርታለች::
በ1990 ዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በስሟና በፎቶግራፎቿ የተሰሩ የሰንደል እና የፖስት ካርድ ምርቶችም እጅጉን ተወዳጅ ነበሩ። በተለይም ” መሲ ሰንደል” በገጠር በከተማ እጅግ ተወዳጅ የነበረ ምርት እና ምስሉም አሁንም ድረስ በብዙዎች ቤት ማስታወሻ ሆኖ የተቀመጠ ነው።
” መሰረት አድቨርታይዚንግ” በሚል የማስታወቂያ ድርጅቷ ውስጥ ሥራ አስኪያጅ በመሆን እየሠራች ትገኛለች። በትወና ብቻ ሳይሆን በፅሁፍ እና በዳይሬክተርነትም ጉልህ ሚና አላት። ለታላላቅ ድርጅቶችም ብራንድ አምባሳደር በመሆን እየሠራች ነው። በሙያዋም ሆነ በሥነ-ምግባሯ በርካታ ድርጅቶች አብረዋት ለመሥራት የሚሽቀዳደሙባት ቀዳሚ ምርጫቸው ናት።
የቴያትር ሥራዎቿንም በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች እና በእስራኤል ሀገር በቴል አቪቭ እና እየሩሳሌም ከተሞች ማቅረብ ችላለች።
“ገመና “በተባለ ተከታታይ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማ በህዝብ ድምፅ ተመርጣ በመላው ዓለም በቀጥታ በተላለፈ የቴሌቭዥን መርሀግብር አንደኛ በመሆን የወርቅ ዋንጫና የገንዘብ ሽልማት ተሸልማለች::
በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራ ውስጥ አምባሳደር በመሆን አገልግላለች።
በሴቶች የህፃናት እና የአረጋውያን እንዲሁም የጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶችን በሚረዱ በርካታ ድርጅት ጋር በበጎ ፈቃደኛት አገልግላለች።
የፀረ HIV ግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ፌስቱላን የመከላከል ማስተማሪያ መርሀ-ግብሮች ላይ ብርቱ ተሳትፎ አድርጋለች። ሜሪጆይ እና ኤልሻዳይ ከተባሉ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋርም በሰፊው አገልግላለች።
በምታደርገው የማህበረሰብ አገልግሎት በኢትዮጵያ ሚሊኒየም “ተምሳሌት ወጣት” በሚል ከወቅቱ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ እጅ ሜዳሊያ ተበርክቶላታል።
በአሁኑ ሰአት የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል የበጎ ፈቃድ አምባሳደር በመሆን እያገለገለች ትገኛለች:: በግልም በማእከልም ከምትከውናቸው በጎ ተግባራት ባሻገር በሰሜን አሜሪካ በተለያዩ ግዛቶች ተዘዋውራ ባደረገችው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር $ ከ126,000 USD በላይ ለማዕከሉ ማስገባት ችላለች። በኢትዮጵያ 6,000,000,000 ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ አሰባስባ በርካታ ህፃናት የህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ምክንያት ሆናለች።
መቀመጫውን በአሜሪካን ሀገር ዳላስ ከተማ ያደረገው ዓድዋ የባህልና የታሪክ ህብረት “አርአያ ሰው” በሚል የክብር ሜዳሊያና የሰርተፊኬት ሽልማትን አበርክቶላታል።
በዘጠነኛው የጉማ ፊልም አዋርድስ ላይ “አርአያ ሰብ ከያኒ” በሚል መጠሪያ በተዘጋጀ የሽልማት ዘርፍም አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላታል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር “ክብር ለጥበብ” በሚል መጠሪያ ለዓመታት በሙያዋ ላበረከተችው አስተዋፅኦ እንዲሁም ዝናዋን ለመልካም ተግባር በማዋሏ የዋንጫና የክብር ካባ ሽልማት አበርክቶላታል።
በአሜሪካን ሀገር በሎስ አንጀለስ ከተማ December 10. 2024 የ Los Angeles city council እና U.S Africa institute በጋራ ባዘጋጁት “Humanitarian Award” ሽልማትን በካውንስሉ አባላት ፊት በክብር አበረክቶላታል።
መሲ ትዳሯን አክባሪ ሀገሯንና ሀይማኖቷን እጅግ አጥብቃ የምትወድ፤ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም በገንዘብም ሆነ በሙያዋ ግንባት ቀደም ተሳታፊ ናት። ” ግዴታዬ ነው! ዝቅ ብዬ የምገዛለት፣ እስከ ሞት የምታመንለት ጉዞዬ ነው ትላለች።
አገልግሎት በረከቴ ነው ብላ የምታምን ሰውን መርዳት እና ማገዝ እጅግ የሚያስደስታት ሴት ናት። ለብዙዎች ህይወት በበጎ መለወጥም የራሷን አሻራ አኑራለች።
በፈተናዎች መሀል በፅናት መቆምን፣ ዝነኛ መሆን ብቻ ሳይሆን ዝናና ክብርን ለአመታት ጠብቆ መቆየትን አስመስክራለች።
ለበርካታ ወጣቶችም በሀይማቷም ሆነ በበጎ አድራጎት አገልግሎት ሰራዋ ሮል ሞዴል ናት። ወጣቶች የሷን ፈለግ በመከተልም ወደዚህ በጎ መንገድ ተስበዋል።
በሀገራችን በአማርኛም ሆነ በእንግሊዘኛ የሚታተሙ ጋዜጦችና መጽሔቶች የፊት ሽፋን በመስጠት በሰፊው ዘግበውላታል።
የዓመታት የጥበብ ጉዞዋ በልምድ የካበተ ብቻ ሳይሆን በእውቀትና በትምህርት የዳበረ ነው።
በረዥም የጥበብ አገልግሎተቷ በሙያዋ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አድናቆትን ለማግኘት ችላለች።
ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል በምታደርገው የበጎአገልግሎት ስራዋም በትንሽ በትልቁ ልብ ውስጥ በክብር ተቀምጣለች። ብዙዎች ጨዋ ኢትዮጵያዊት ሴት በማለት አክብሮታቸውን ይቸሯታል። እርሷም ስለሁሉም ክብሩን እግዚአብሔር ይውሰድ የምትለውን መሰረት መብራቴ 8ኛው የዕንቁ ሴት አዋርድ ሆና ተመርጣለች።
መሠረት ስለ ንባብ እና ሌሎችን ስለማገዝ
መሠረት ስለ ንባብ ህይወቷ ና ሌሎችን ስለማገዝ ይህን ብላለች”…ቀደም ባሉ ጊዜያት ልቦለድ፣ የስለላ ታሪኮች የነ (ሞሳድ፣ ኬ.ጂ.ቢ) የስለላ ታሪኮች ይመስጡኝ ነበር። ማንበብ እወዳለሁ።
አሁን የ Psychology እና biography ( autobiography) መፃህፍትን ማንበብ ያስደስተኛል።
ካለፍኩበት የህይወት ተሞክሮ ( experience ) ካነበብኩት፣ ከተማርኩት፣ ከደረስኩበት እውነትና መመንፈሳዊ ግንዛቤ ታዳጊዎችን መምከር፣ ወጣቶችን ማበረታታት እና ማገዝ እጅግ ያሰደስተኛል።” በማለት ተናግራለች።
ስለ መሠረት ሌሎች ምን አሉ?
ስለ መሠረት ምስክርነት እንዲሰጠን የጠየቅነው ረዳት ፕሮፌሰር ሙልጌታ ጀዋሬ መሠረትን ሲገልጻት ለቁምነገር ለመሥራት የተፈጠረች የቁምነገር ንግሥት ይላታል። ለዓላማዋ እስከመጨረሻ የምትሄድ ፣ ሁሌም በከፍታ የምትራመድ በማለት ለመሠረት ያለውን ልዩ አክብሮት ገልጿል።
መሠረት በውበቷ የማትመፃደቅ ፣ ልዩ ትህትና ያላት ተማሪዬ በመሆኗ አድናቆቴ ከፍተኛ ነው ሲልም ሀሣቡን ይገልጻል።
” መሠረት በትምህርቷ ጎበዝ እና አሰላሳይ ናት።ስትማርም በሥነ ምግባር የምትማር ታታሪ ነበረች።ከዚህ አንፃር ለአገራችን ሴት የጥበብ ሰዎች አርአያ የምትሆን ነች።እኔ ሳስተምራት” ሚድ ሰመር ናይት ድሪም” የሚለው ቴአትር ላይ እምቅ ክሆሎቷን ሳትደብቅ አሳይታለች። በእኔ እምነት መሢ ለቴአትርም ለፊልምም የተፈጠረች ናት” ሲል ሙልጌታ ሀሣቡን ለተወዳጅ ሚድያ ሰጥቷል።
ዶክተር ባለው ደምሴ ስለ መሠረት ከተናገረው
መሠረት የማስተርስ ትምህርቷን ስትከታተል አማካሪዋ ነበርኩ። በጊዜው 3 ኮርሶችንም አስተምሬያታለሁ። ከመሠረት ያየሁት ትልቅ ጥንካሬ ፅናቷ፣ ዲሲፕሊኗ ፣ ብሩህ አእምሮ ያላት መሆኑን ነው። ይህ ሁሉ ከልዩ ትህትና ጋር የታጀበ ነው።
በእኔ ዕይታ መሠረት በትምህርቷ ጥሩ ውጤት የምታመጣ ብቻ ሳትሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ለትወና የተለየ ክህሎት ያላት ባለሙያ ነች። ላመነችበት ነገር ራሷን በደንብ አድርጋ ትሰጣለች። የማስተርስ መመረቂያ ወረቀቷን ብንወስድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ክዋኔዎች ላይ ነበር የሠራችው። ይህ እንግዲህ ለጉዳዩ ያላትን ቀረቤታና ዕውቀት የሚያሳየን ይመስለኛል።
መሠረት በዚህ ብቻ አትወሰንም። የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ትሳተፋለች። አገራችን ላይ በሚደረጉ የእሴት እና የባህል ማሳደግ ንቅናቄዎች መሠረት ቀዳሚ ናት። በዚህ በጎነቷ የተከበረች የኪነ ጥበብ ሰው ብለን ልንጠራት ይገባል።